ሳምንት 3 · ቀን 15 (አርብ)
📅 Meskerem 22, 2019
ኦሪት ዘፍጥረት 38, 39, 40 · የማርቆስ ወንጌል 15
ኦሪት ዘፍጥረት
ምዕራፍ 38
ይሁዳና ትዕማር
1.በዚያም ወራት ይሁዳ ከወንድሞቹ ተለይቶ፣ ኤራ ወደ ተባለ ዓዶላማዊ ሰው ወረደ፤ እርሱም ዘንድ ለመኖር ቤቱ ገባ። 2.እዚያም ሳለ፣ ይሁዳ የከነዓናዊውን የሹዓን ሴት ልጅ አየ፤ እርሷንም አግብቶ ዐብሯት ተኛ፤ 3.እርሷም ፀንሳ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ስሙም ዔር ተባለ። 4.እንደ ገናም ፀንሳ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ስሙን አውናን አለችው። 5.አሁንም ደግማ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ስሙንም ሴሎም ብላ አወጣችለት፤ እርሱንም የወለደችው ክዚብ በተባለ ቦታ ነበር። 6.ይሁዳ የበኵር ልጁን ዔርን፣ ትዕማር የምትባል ሚስት አጋባው። 7.የይሁዳ የበኵር ልጅ ዔር ግን በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነበር፤ እግዚአብሔርም ቀሠፈው። 8.በዚህ ጊዜ ይሁዳ አውናንን፣ “ዋርሳዋ እንደ መሆንህ ከወንድምህ ሚስት ጋራ ሩካቤ ሥጋ በመፈጸም የወንድምህን ስም የሚያስጠራለት ዘር ተካለት” አለው። 9.አውናን ግን የሚወለደው ልጅ የርሱን ስም የሚያስጠራ እንደማይሆን ስላወቀ፣ ከወንድሙ ሚስት ጋራ ሩካቤ ሥጋ በፈጸመ ቍጥር የወንድሙንም ስም የሚያስጠራ ልጅ እንዳይወልድ ዘሩን በምድር ላይ ያፈስስ ነበር። 10.ይህም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አድራጎት ሆኖ ስለ ተገኘ፣ እርሱንም እግዚአብሔር በሞት ቀሠፈው። 11.ከዚያም ይሁዳ ምራቱን ትዕማርን፣ “ልጄ ሴሎም ለአካለ መጠን እስኪደርስ ድረስ ወደ አባትሽ ቤት ሄደሽ መበለት ሆነሽ ብትኖሪ ይሻላል” አላት። ይህን ያለውም፣ ሴሎም እንደ ወንድሞቹ ተቀሥፎ ይሞትብኛል ብሎ ስለ ሠጋ ነበር። ትዕማርም እንዳላት ሄደች፤ በአባቷም ቤት ተቀመጠች። 12.ከብዙ ጊዜ በኋላ የሹዓ ልጅ፣ የይሁዳ ሚስት ሞተች። ይሁዳ ከሐዘኑ ከተጽናና በኋላ ከዓዶላማዊው ከኤራ ጋራ የበጎቹን ጠጕር የሚሸልቱ ሰዎች ወዳሉበት ወደ ተምና ሄደ። 13.ሰዎቹም ለትዕማር፣ “ዐማትሽ የበጎቹን ጠጕር ወደሚሸልቱ ሰዎች ዘንድ ወደ ተምና እየሄደ ነው” አሏት። ይህን እንደ ሰማች 14.የመበለትነት ልብሷን አውልቃ፣ ማንነቷ እንዳይታወቅ ፊቷን በሻሽ ተከናንባ ወደ ተምና በሚወስደው መንገድ ዳር ባለች ኤናይም በተባለች ከተማ መግቢያ ላይ ተቀመጠች፤ ይህን ያደረገችው፣ ሴሎም ለአካለ መጠን ቢደርስም፣ እርሷን እንዲያገባ አባቱ አለመፈለጉን ስላወቀች ነው። 15.ፊቷ በሻሽ ተሸፋፍኖ ሲያያት፣ ይሁዳ ዝሙት ዐዳሪ መሰለችው። 16.ምራቱ መሆኗን ባለማወቁ፣ እርሷ ወዳለችበት ወደ መንደሩ ዳር ጠጋ ብሎ፣ “እባክሽ ዐብሬሽ ልተኛ” አላት።እርሷም፣ “ዐብሬህ ብተኛ ምን ትሰጠኛለህ?” ብላ ጠየቀችው። 17.“ከመንጋዬ መካከል አንድ የፍየል ጠቦት እልክልሻለሁ” አላት። እርሷም መልሳ፣ “ጠቦቱን እስክትልክልኝ ድረስ ምን መያዣ ትሰጠኛለህ?” ብላ ጠየቀችው። 18.“ታዲያ ምን መያዣ ልስጥሽ?” አላት። እርሷም፣ “የማኅተም ቀለበትህን ከነማሰሪያው፣ እንደዚሁም ይህን በትርህን ስጠኝ” አለችው። የጠየቀችውን ሁሉ ሰጣትና ዐብሯት ተኛ፤ እርሷም ፀነሰች። 19.ከዚያም ወደ መኖሪያዋ ተመልሳ፣ ሻሿን አውልቃ እንደ ወትሮዋ የመበለት ልብሷን ለበሰች። 20.ይሁዳ በመያዣ ስም የሰጣትን ዕቃዎች ለማስመለስ የፍየሉን ጠቦት በዓዶላማዊ ወዳጁ እጅ ላከላት፣ መልእክተኛው ግን ሴትዮዋን ሊያገኛት አልቻለም። 21.“በኤናይም ከተማ መግቢያ ከመንገዱ ዳር የነበረች ያቺ ዝሙት ዐዳሪ የት ደረሰች?” ሲል ጠየቃቸው።
ሰዎቹም፣ “በዚህ አካባቢ ኧረ ምንም ዝሙት ዐዳሪ ታይታ አትታወቅም” አሉት። 22.መልእክተኛውም ወደ ይሁዳ ተመልሶ፣ “ሴቲቱን ላገኛት አልቻልሁም፤ ነዋሪዎቹም ‘በዚህ አካባቢ እንደዚህች ያለች ዝሙት ዐዳሪ የለችም’ አሉኝ” ብሎ ነገረው። 23.ይሁዳም፣ “እንግዲህ መያዣውን እንደ ያዘች ትቅር፣ አለዚያ መሣቂያ እንሆናለን። ለነገሩማ ይህን ፍየል ላክሁ፤ አንተም ፈልገህ አላገኘሃትም” አለ። 24.ከሦስት ወር ያህል በኋላ፣ “ምራትህ ትዕማር ዘማዊ ሆናለች፤ ከዚህም የተነሣ አርግዛለች” ተብሎ ለይሁዳ ተነገረው።
ይሁዳም፣ “አውጧትና በእሳት ተቃጥላ ትሙት” አለ። 25.እርሷም ተይዛ በምትወሰድበት ጊዜ ለዐማቷ፣ “እኔ ያረገዝሁት የእነዚህ ዕቃዎች ባለቤት ከሆነ ሰው ነው” ስትል ላከችበት፤ ደግሞም፣ “የማኅተሙ ቀለበት ከነማንጠልጠያውና በትሩ የማን እንደ ሆነ እስኪ ተመልከት” አለችው። 26.ይሁዳም ዕቃዎቹን ዐውቆ፣ “ልጄ ሴሎም እንዲያገባት ባለማድረጌ፣ እርሷ ከእኔ ይልቅ ትክክል ናት” አለ። ከዚያም በኋላ ከርሷ ጋራ አልተኛም። 27.የመውለጃዋ ጊዜ እንደ ደረሰም ፅንሷ መንታ መሆኑ ታወቀ። 28.በምትወልድበትም ጊዜ አንደኛው እጁን አወጣ፤ አዋላጂቱም፣ “ይህኛው መጀመሪያ ወጣ” ስትል በእጁ ላይ ቀይ ክር አሰረችለት፤ 29.ነገር ግን፣ እጁን መልሶ ሲያስገባ ወንድሙ ተወለደ። አዋላጂቱም “አንተ እንዴት ጥሰህ ወጣህ!” አለች፤ ከዚያም ስሙ ፋሬስ ተባለ። 30.ከዚያ በኋላ እጁ ላይ ቀይ ክር የታሰረለት ወንድሙ ተወለደ፤ ስሙም ዛራ ተባለ።
ምዕራፍ 39
ዮሴፍና የጲጥፋራ ሚስት
1.በዚህ ጊዜ ዮሴፍ ወደ ግብጽ ተወስዶ ነበር፤ ከፈርዖን ሹማምት አንዱ የሆነውም የዘበኞች አለቃ፣ ግብጻዊው ጲጥፋራ ወደዚያ ከወሰዱት ከእስማኤላውያን ነጋዴዎች እጅ ገዛው። 2.እግዚአብሔር ከዮሴፍ ጋራ ነበረ፤ ኑሮው ተቃናለት፤ እርሱም በግብጻዊው አሳዳሪው ቤት ኖረ። 3.አሳዳሪውም እግዚአብሔር ከርሱ ጋራ እንዳለና ሥራውንም ሁሉ እንዳከናወለት ባየ ጊዜ፣ 4.ዮሴፍ በርሱ ዘንድ ሞገስ አገኘ፤ የቅርብ አገልጋዩም ሆነ። ጲጥፋራ በቤቱ ላይ ሾመው፤ ያለውንም ሀብት ሁሉ በኀላፊነት ሰጠው። 5.ዮሴፍ በጲጥፋራ ቤትና ባለው ሀብት ሁሉ ላይ ከተሾመበት ጊዜ ጀምሮ፣ እግዚአብሔር የግብጻዊውን ቤት ባረከ፤ የእግዚአብሔርም በረከት በግቢም በውጭም ባለው የጲጥፋራ ሀብት ንብረት ሁሉ ላይ ሆነ። 6.ስለዚህ ጲጥፋራ ባለው ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጠው፤ የቀረበለትንም ከመመገብ በቀር፣ ማንኛውንም ጕዳይ በዮሴፍ ላይ ጥሎ ነበር።ዮሴፍ ጥሩ ቁመና ያለውና መልከ መልካም ነበር፤ 7.እያደርም የጌታው ሚስት በዮሴፍ ላይ ዐይኗን ጣለች፤ አፍ አውጥታም፣ “ዐብረኸኝ ተኛ” አለችው። 8.እርሱ ግን ፈቃደኛ አልሆነም፤ እንዲህም አላት፤ “ጌታዬ ያለውን ሁሉ በኀላፊነት ስለ ሰጠኝ፣ በቤቱ ውስጥ ስላለው ሁሉ ምንም የሚያውቀው ነገር የለም። 9.በዚህ ቤት ላይ ከእኔ የበለጠ ኀላፊነት ያለው ማንም የለም፤ እርሱ ያልሰጠኝ ነገር ቢኖር፣ አንቺን ብቻ ነው፤ ያውም ሚስቱ ስለሆንሽ ነው፤ ታዲያ፣ እኔ ይህን ክፉ ድርጊት ፈጽሜ እንዴት በእግዚአብሔር ፊት ኀጢአት እሠራለሁ?” 10.ምንም እንኳ ዮሴፍን በየቀኑ ብትጐተጕተውም፣ አልሰማትም፤ ከርሷ ጋራ መተኛት ይቅርና ዐብሯትም መሆን አልፈቀደም። 11.አንድ ቀን ዮሴፍ የዕለት ተግባሩን ለማከናወን ወደ ቤት ገባ፤ ከቤቱ አገልጋዮችም አንድም ሰው በቤት ውስጥ አልነበረም። 12.እርሷም ልብሱን ጨምድዳ ይዛ “በል ዐብረኸኝ ተኛ” አለችው። እርሱ ግን ልብሱን እጇ ላይ ጥሎ ሸሽቶ ከቤት ወጣ። 13.እርሷም ልብሱን እጇ ላይ ጥሎ ሸሽቶ መውጣቱን ባየች ጊዜ፣ 14.የቤት አገልጋዮቿን ጠራች፤ እንዲህም አለቻቸው፤ “አያችሁ፤ ለካስ ይህ ዕብራዊ የመጣው መሣለቂያ ሊያደርገን ኖሯል! ሊተኛኝ ወደ እኔ ገባ፤ እኔም ከፍ ባለ ድምፅ ጮኽሁ፤ 15.ለርዳታ መጮኼን ሲሰማም፣ ልብሱን አጠገቤ ጥሎ ሸሽቶ ወጣ።” 16.ጌታውም ወደ ቤት እስኪመለስ ድረስ፣ ልብሱን አጠገቧ አቈየችው። 17.ታሪኩንም እንዲህ ስትል ነገረችው፤ “አንተ ያመጣኸው ዕብራዊ ባሪያ መሣቂያ ሊያደርገን ወዳለሁበት ሰተት ብሎ ገባ፤ 18.ታዲያ እኔ ድረሱልኝ ብዬ ስጮኽ ልብሱን አጠገቤ ጥሎ ሸሽቶ ወጣ።” 19.ጌታውም፣ “ባሪያህ እንዲህ አደረገኝ” ብላ ሚስቱ የነገረችውን ታሪክ ሲሰማ ተቈጣ። 20.ጌታውም ዮሴፍን ወስዶ፣ የንጉሥ እስረኞች ወደ ተጋዙበት እስር ቤት አስገባው።
ይሁን እንጂ ዮሴፍ እዚያ እስር ቤት በነበረበት ጊዜ ሁሉ፣ 21.እግዚአብሔር ከዮሴፍ ጋራ ነበረ፤ ቸርነቱንም አበዛለት፤ በወህኒ አዛዡም ዘንድ ሞገስን ሰጠው። 22.ስለዚህ የወህኒው አዛዥ ዮሴፍን የእስረኞች ሁሉ አለቃ አደረገው፤ በእስር ቤቱ ላለውም ነገር ሁሉ ኀላፊ ሆነ። 23.እግዚአብሔር ከዮሴፍ ጋራ ሆኖ ሥራውን ሁሉ ያሳካለት ስለ ነበር፣ የወህኒ ቤት አዛዡ በዮሴፍ ኀላፊነት ሥር ስላለው ስለ ማንኛውም ጕዳይ ሐሳብ አይገባውም ነበር።
ምዕራፍ 40
የመጠጥ አሳላፊውና የእንጀራ ቤቱ
1.ከዚህም በኋላ የግብጽ ንጉሥ የመጠጥ አሳላፊና እንጀራ ቤቱ ጌታቸውን የግብጽን ንጉሥ በደሉት። 2.ፈርዖንም በመጠጥ አሳላፊዎቹ አለቃና በእንጀራ ቤቱ አዛዥ፣ በሁለቱም ሹማምቱ ላይ ክፉኛ ተቈጣ፤ 3.በዘበኞቹ አለቃ ቤት ወዳለው ዮሴፍ ወደ ተጋዘበትም እስር ቤት አስገባቸው። 4.የዘበኞቹም አለቃ እስረኞቹን ለዮሴፍ አስረከባቸው፤ ዮሴፍም በሚያስፈልጋቸው ይረዳቸው ነበር።እስር ቤት ገብተው ጥቂት እንደ ቈዩም፣ 5.ታስረው የነበሩት የግብጽ የንጉሥ የመጠጥ አሳላፊዎች አለቃና የእንጀራ ቤቱ አዛዥ፣ በአንድ ሌሊት የየራሳቸውን ሕልም አዩ፤ የሁለቱም ሕልም ለየራሱ የተለየ ፍች ነበረው። 6.በማግስቱም ጧት ዮሴፍ ወደ እነርሱ ሲገባ ተክዘው አገኛቸው። 7.ስለዚህም፣ “ምነው ዛሬስ ፊታችሁ ላይ ሐዘን ይነበባል?” በማለት ዐብረውት በጌታው ግቢ የታሰሩትን የፈርዖን ሹማምት ጠየቃቸው። 8.እነርሱም “ሁለታችንም ሕልም አየን፤ ነገር ግን የሚተረጕምልን ሰው አጣን” ሲሉ መለሱለት።
ዮሴፍም፣ “ሁልጊዜስ ቢሆን የሕልም ትርጓሜ ከእግዚአብሔር የሚገኝ አይደለምን? እስኪ ያያችሁትን ሕልም ንገሩኝ” አላቸው። 9.ስለዚህ የመጠጥ አሳላፊዎቹ አለቃ እንዲህ ሲል ሕልሙን ለዮሴፍ ነገረው፤ “ከፊት ለፊቴ አንዲት የወይን ተክል አየሁ፤ 10.ተክሏም ሦስት ሐረጎች ነበሯት፤ ወዲያው አቈጥቍጣ አበበች፤ ዘለላዎቿም ተንዠርግገው በሰሉ። 11.የፈርዖንንም ጽዋ ይዤ ነበረ፤ የወይኑን ፍሬ ለቅሜ በጽዋው ውስጥ ጨምቄ ጽዋውን በእጁ ሰጠሁት።” 12.ዮሴፍም እንዲህ አለው፤ “እንግዲህ የሕልሙ ትርጓሜ ይህ ነው፤ ሦስቱ ሐረግ ሦስት ቀን ነው፤ 13.በሦስት ቀን ውስጥ ፈርዖን ከእስር ቤት ያወጣሃል፣ ወደ ቀድሞ ሹመትህም ይመልስሃል፤ በፊት የመጠጥ አሳላፊ በነበርህበት ጊዜ ታደርግ እንደ ነበረው ሁሉ የፈርዖንን ጽዋ በእጁ ትሰጣለህ። 14.እንግዲህ፣ በጎ ነገር በገጠመህ ጊዜ፣ እኔን ዐስበህ ቸርነት አድርግልኝ፤ ስለ እኔም ለፈርዖን ንገርልኝ፤ ከዚህም እስር ቤት አስወጣኝ፤ 15.ከዕብራውያን ምድር ወደዚህ የመጣሁት በዐፈና ነው፤ አሁንም ቢሆን እዚህ እስር ቤት የተጣልሁት አንዳች ጥፋት ኖሮብኝ አይደለም።” 16.የእንጀራ ቤት አዛዡም፣ ለመጠጥ አሳላፊዎቹ አለቃ ሕልም፣ የተሰጠው ፍች ደስ የሚያሰኝ መሆኑን ሲሰማ፣ የራሱን ሕልም ለዮሴፍ እንዲህ ሲል ነገረው፤ “እኔም ደግሞ ሕልም አይቻለሁ፤ ሦስት መሶቦች በራሴ ላይ ተሸክሜ ነበር፤ 17.በላይኛው መሶብ ውስጥ ለፈርዖን የተዘጋጀ የተለያየ ምግብ ነበረበት፤ ወፎችም ራሴ ላይ ካለው መሶብ ይበሉ ነበር።” 18.ዮሴፍም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “የሕልሙ ፍች ይህ ነው፤ ሦስቱ መሶብ ሦስት ቀን ነው፤ 19.በሦስት ቀን ውስጥ ፈርዖን ከእስር ቤት ያወጣሃል፤ በዕንጨትም ላይ ይሰቅልሃል፤ ወፎችም ሥጋህን ይበሉታል።” 20.በሦስተኛውም ቀን የፈርዖን የልደት በዓል ነበረ፤ ለሹማምቱም ሁሉ ግብር አበላ። በዚያ ዕለትም የመጠጥ አሳላፊዎችን አለቃና የእንጀራ ቤት አዛዡን ሹማምቱ ባሉበት ከእስር ቤት አወጣቸው። 21.የመጠጥ አሳላፊዎቹን አለቃ ወደ ቀድሞ ሹመቱ መለሰው፤ እርሱም እንደ ቀድሞው ጽዋውን ለፈርዖን በእጁ ይሰጠው ጀመር። 22.የእንጀራ ቤት አዛዡን ግን ልክ ዮሴፍ እንደ ተረጐመላቸው ሰቀለው። 23.የሆነው ሆኖ፣ የመጠጥ አሳላፊዎቹ አለቃ ዮሴፍን አላስታወሰውም፤ ረሳው እንጂ።
የማርቆስ ወንጌል
ምዕራፍ 15
ኢየሱስ በጲላጦስ ፊት
15፥2-15 ተጓ ምብ – ማቴ 27፥11-26፤ ሉቃ 23፥2-3፤ 23፥18-25፤ ዮሐ 18፥29–19፥16
1.ወዲያውም በማለዳ የካህናት አለቆች ከሽማግሌዎች፣ ከጸሐፍትና ከመላው የሸንጎ አባላት ጋራ ከተማከሩ በኋላ፣ ኢየሱስን አስረው ወሰዱት፤ ለጲላጦስም አሳልፈው ሰጡት።
2.ጲላጦስም፣ “አንተ የአይሁድ ንጉሥ ነህን?”ሲል ጠየቀው፤ ኢየሱስም፣ “አንተው አልኸው፣” በማለት መለሰለት። 3.የካህናት አለቆችም በብዙ ነገር ከሰሱት። 4.ጲላጦስም፣ “ለምን መልስ አትሰጥም? እነሆ፤ በብዙ ነገር ከስሰውሃል” ሲል እንደ ገና ጠየቀው። 5.ኢየሱስ ግን ምንም አልመለሰም፤ ጲላጦስ ተገረመ። 6.በበዓል ሕዝቡ እንዲፈታላቸው የሚጠይቁትን እስረኛ የመልቀቅ ልማድ ነበር። 7.በዐመፃ ተነሣሥተው ነፍስ ከገደሉ ዐመፀኞች ጋራ የታሰረ በርባን የሚባል አንድ ሰው ነበረ። 8.ሕዝቡም መጥተው እንደተለመደው እንዲያደርግላቸው ለመኑት። 9.ጲላጦስም፣ “የአይሁድን ንጉሥ እንድፈታላችሁ ትፈልጋላችሁን?” ሲል ጠየቃቸው፤ 10.ምክንያቱም የካህናት አለቆች ኢየሱስን አሳልፈው የሰጡት በቅናት መሆኑን ያውቅ ነበር። 11.የካህናት አለቆች ግን በርባንን በርሱ ምትክ እንዲፈታላቸው እንዲጠይቁ ሕዝቡን አነሣሡ። 12.ጲላጦስም እንደ ገና፣ “እንግዲያው የአይሁድ ንጉሥ የምትሉትን ምን እንዳደርገው ትፈልጋላችሁ?” አላቸው። 13.እነርሱም እንደ ገና፣ “ስቀለው!” እያሉ ጮኹ። 14.ጲላጦስም፣ “ለምን? ምን የፈጸመው ወንጀል አለ” አላቸው።
እነርሱ ግን፣ “ስቀለው!” እያሉ የባሰ ጮኹ። 15.ጲላጦስም ሕዝቡን ደስ ለማሠኘት ሲል በርባንን ፈታላቸው፤ ኢየሱስን ግን ገርፎ እንዲሰቀል አሳልፎ ሰጠው።
ወታደሮች በኢየሱስ ላይ አፌዙ
15፥16-20 ተጓ ምብ – ማቴ 27፥27-31
16.ወታደሮቹ ፕራይቶሪዮን ወደ ተባለ ወደ ገዥው ግቢ ወሰዱት፤ ሰራዊቱንም ሁሉ በአንድነት ሰበሰቡ።
17.ቀይ ልብስም አለበሱት፤ የእሾኽ አክሊል ጐንጕነው በራሱ ላይ ደፉበት።
18.ከዚያም፣ “የአይሁድ ንጉሥ ሆይ፤ ሰላም ለአንተ ይሁን!” እያሉ እጅ ነሡት፤
19.ራሱንም በበትር መቱት፤ ተፉበትም፤ ተንበርክከውም ሰገዱለት።
20.ካፌዙበት በኋላም ቀዩን ልብስ ገፈፉት፤ የገዛ ልብሱን አለበሱት፤ ሊሰቅሉትም ወሰዱት።
የኢየሱስ ስቅለት
15፥22-32 ተጓ ምብ – ማቴ 27፥33-44፤ ሉቃ 23፥33-43፤ ዮሐ 19፥17-24
21.የአሌክሳንድሮስና የሩፎስ አባት ስምዖን የተባለ አንድ የቀሬና ሰው ከገጠር ሲመጣ መስቀሉን እንዲሸከም አስገደዱት።
22.ከዚያም ኢየሱስን፣ ትርጕሙ “የራስ ቅል ስፍራ” ወደ ተባለ ወደ ጎልጎታ ወሰዱት።
23.ከከርቤ ጋራ የተቀላቀለ የወይን ጠጅም ሰጡት፤ እርሱ ግን አልተቀበለም።
24.ከዚያም ሰቀሉት፤ እያንዳንዱም ምን እንደሚደርሰው ለማወቅ ዕጣ ተጣጥለው ልብሱን ተከፋፈሉ።
25.ሲሰቅሉትም ጊዜው ከጧቱ ሦስት ሰዓት ነበረ።
26.የክሱ ጽሑፍም፣
የአይሁድ ንጉሥ
የሚል ነበር።
27.ከርሱም ጋራ ሁለት ወንበዴዎችን አንዱን በቀኙ አንዱን በግራው ሰቀሉ። [ 28.መጽሐፍ፣ “ከዐመፀኞች ጋራ ተቈጠረ” ያለውም በዚሁ ተፈጸመ።] 29.በመንገድ የሚያልፉትም ራሳቸውን እየነቀነቁ የስድብ ናዳ በማውረድ እንዲህ ይሉት ነበር፤ “አዪ፤ አንተ ቤተ መቅደስን አፍርሰህ በሦስት ቀን የምትሠራ፤ 30.እስኪ አሁን ከመስቀል ውረድና ራስህን አድን!” 31.እንዲሁም የካህናት አለቆችና ጸሐፍት በማሾፍ እርስ በርሳቸው እንዲህ አሉ፤ “ሌሎችን አዳነ፤ ራሱን ግን ማዳን አልቻለም! 32.አይተን እናምን ዘንድ ይህ ክርስቶስ፣ ይህ የእስራኤል ንጉሥ እስኪ ከመስቀል ይውረድ።” ከርሱ ጋራ የተሰቀሉትም እንደዚሁ የስድብ ናዳ ያወርዱበት ነበር።የኢየሱስ መሞት
15፥33-41 ተጓ ምብ – ማቴ 27፥45-56፤ ሉቃ 23፥44-49
33.ከስድስት ሰዓት ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በምድር ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ።
34.በዘጠኝም ሰዓት ኢየሱስ፣ “ኤሎሄ፣ ኤሎሄ፣ ላማ ሰበቅታኒ?” ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ፤ ትርጓሜውም “አምላኬ፣ አምላኬ፣ ለምን ተውኸኝ?” ማለት ነው።
35.በዚያ ቆመው ከነበሩት አንዳንዶቹ ይህን ሲሰሙ፣ “ኤልያስን ይጣራል” አሉ።
36.ከዚያም አንድ ሰው ፈጥኖ ሄዶ የኮመጠጠ የወይን ጠጅ በሰፍነግ ነከረ፤ በዘንግም ሰክቶ እንዲጠጣው ለኢየሱስ አቀረበለት፤ ከዚያም፣ “ተዉት፤ እስኪ ኤልያስ መጥቶ ሲያወርደው እናያለን” አለ።
37.ኢየሱስም በታላቅ ድምፅ ጮኾ፤ ነፍሱን ሰጠ።
38.የቤተ መቅደሱም መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ከሁለት ተቀደደ።
39.በኢየሱስ ትይዩ ቆሞ የነበረውም የመቶ አለቃ እንደዚህ ጮኾ ነፍሱን ሲሰጥ ባየ ጊዜ፣ “ይህ ሰው በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነበር!” አለ።
40.በዚህ ጊዜ ሴቶች ከሩቅ ሆነው ይመለከቱ ነበር፤ ከእነርሱም መካከል መግደላዊት ማርያም፣ የታናሹ ያዕቆብና የዮሳ እናት ማርያም፣ እንዲሁም ሰሎሜ ነበሩ፤
41.እነዚህ ሴቶች በገሊላ ሲከተሉትና ሲያገለግሉት የነበሩ ናቸው፤ ደግሞም ዐብረውት ወደ ኢየሩሳሌም የመጡ ሌሎች ብዙ ሴቶች ነበሩ።
የኢየሱስ መቀበር
15፥42-47 ተጓ ምብ – ማቴ 27፥57-61፤ ሉቃ 23፥50-56፤ ዮሐ 19፥38-42
42.ጊዜው እየመሸ መጥቶ የሰንበት ዋዜማ ይኸውም የመዘጋጀት ቀን ሆነ፤
43.የተከበረ የሸንጎ አባልና የእግዚአብሔርን መንግሥት ይጠባበቅ የነበረው የአርማትያሱ ዮሴፍ በድፍረት ወደ ጲላጦስ ሄዶ የኢየሱስን ሥጋ ለመነው።
44.ጲላጦስም እንዲህ በቶሎ መሞቱን ሲሰማ ተደነቀ፤ የመቶ አለቃውንም ወደ ራሱ ጠርቶ ከሞተ ምን ያህል ጊዜ እንደ ሆነ ጠየቀው፤
45.መሞቱንም ከመቶ አለቃው ካረጋገጠ በኋላ ሥጋውን ለዮሴፍ ሰጠው።
46.ዮሴፍም በፍታ ገዛ፤ ሥጋውንም አውርዶ በበፍታው ከከፈነው በኋላ፣ ከዐለት በተወቀረ መቃብር አኖረው፤ የመቃብሩንም ደጃፍ በድንጋይ ገጠመው።
47.ማርያም መግደላዊትና የዮሳ እናት ማርያም የት እንዳኖሩት ይመለከቱ ነበር።