ሳምንት 3 · ቀን 11 (ሰኞ)
📅 Meskerem 18, 2019
ኦሪት ዘፍጥረት 28, 29 · የማርቆስ ወንጌል 11
ኦሪት ዘፍጥረት
ምዕራፍ 28
1.ይስሐቅም ያዕቆብን ጠራው፥ ባረከውም፥ እንዲህ ብሎም አዘዘው። ከከነዓናውያን ሴቶች ልጆች ሚስትን አታግባ፤2.ተነሣና ወደ እናትህ አባት ወደ ባቱኤል ቤት ወደ ሁለቱ ወንዞች መካከል ሂድ፤ ከዚያም ከእናትህ ወንድም ከላባ ሴቶች ልጆች ሚስትን አግባ።3.ሁሉን የሚችል አምላክም ለብዙ ሕዝብ ጉባኤ እንድትሆን ይባርክህ፥ ያፍራህ፥ ያብዛህ፤4.ስደተኛ ሆነህ የተቀመጥህባትን እግዚአብሔርም ለአብርሃም የሰጣትን ምድር ትወርስ ዘንድ የአብርሃምን በርከት ለአንተ ይስጥህ፥ ለዘርህም እንዲሁ እንደ አንተ።5.ይስሐቅም ያዕቆብን ሰደደው፥ እርሱም የያዕቆብና የዔሳው እናት የርብቃ ወንድም የሚሆን የሶርያዊ ባቱኤል ልጅ ላባ ወዳለበት ወደ ሁለቱ ወንዞች መካከል ሄደ።6.ዔሳውም ይስሐቅ ያዕቆብን እንደ ባረከው ባየ ጊዜ፥ ከዚያም ሚስትን ያገባ ዘንድ ወደ ሁለት ወንዞች መካካል እንደ ሰደደው፥ በባረከውም ጊዜ። ከከነዓን ሴቶች ልጆች ሚስትን አታግባ ብሎ እንዳዘዘው፥7.ያዕቆብም የአባቱንና የእናቱን ቃል ሰምቶ ወደ ሁለቱ ወንዞች መካከል እንደሄደ፥8.የከነዓናውያንም ሴቶች ልጆች በአባቱ በይስሐቅ ፊት የተጠሉ እንደሆኑ ዔሳው ባየ ጊዜ፥9.ዔሳው ወደ እስማኤል ሄደ፥ ማዕሌትንም በፊት ካሉት ሚስቶቹ ጋር ሚስት ትሆነው ዘንድ አገባ፤ እርስዋም የአብርሃም ልጅ የሆነ የእስማኤል ልጅና የነባዮት እኅት ናት።10.ያዕቆብም ከቤርሳቤህ ወጥቶ ወደ ካራን ሄደ።11.ወደ አንድ ስፍራም ደረሰ፥ ፀሐይም ጠልቃ ነበርና ከዚያ አደረ፤ በዚያም ስፍራ ድንጋይ አነሣ፥ ከራሱም በታች ተንተርሶ በዚያ ስፍራ ተኛ።12.ሕልምም አለመ፤ እነሆም መሰላል በምድር ላይ ተተክሎ፥ ራሱም ወደ ሰማይ ደርሶ፥ እነሆም የእግዚአብሔር መላእክት ይወጡበት ይወርዱበት ነበር።13.እነሆም፥ እግዚአብሔር በላይ ቆሞበት ነበር፥ እንዲህም አለ። የአባትህ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ይህችን አንተ የተኛህባትን ምድር ለአንተም ለዘርህም እሰጣለሁ፤14.ዘርህም እንደ ምድር አሸዋ ይሆናል፤ እስከ ምዕራብና እስከ ምሥራቅ እስከ ሰሜንና እስከ ደቡብ ትስፋፋለህ፤ የምድርም አሕዛብ ሁሉ በአንተ በዘርህም ይባረካሉ።15.እነሆም እኔ ከአንተ ጋር ነኝ፥ በምትሄድባትም መንገድ ሁሉ እጠብቅሃለሁ፥ ወደዚችም ምድር እመልስሃለሁ፤ የነገርሁህን ሁሉ እስካደርግልህ ድረስ አልተውህምና።16.ያዕቆብም ከእንቅልፉ ተነሥቶ። በእውነት እግዚአብሔር በዚህ ስፍራ ነው፤ እኔ አላወቅሁም ነበር አለ።17.ፈራ፥ እንዲህም አለ። ይህ ስፍራ እንዴት ያስፈራ፤ ይህ ስፍራ የእግዚአብሔር ቤት ነው እንጂ ሌላ አይደለም፤ ይህም የሰማይ ደጅ ነው።18.ያዕቆብም ማልዶ ተነሣ፥ ተንተርሶት የነበረውንም ድንጋይ ወስዶ ሐውልት አድርጎ አቆመው፥ በላዩም ዘይትን አፈሰሰበት።19.ያዕቆብም ያንን ስፍራ ቤቴል ብሎ ጠራው፤ አስቀድሞ ግን የዚያች ከተማ ስም ሎዛ ነበረ።20.ያዕቆብም እንዲህ ብሎ ስእለት ተሳለ። እግዚአብሔር ከእኔ ጋር ቢሆን፥ በምሄድባትም በዚች መንገድ ቢጠብቀኝ፥ የምበላውንም እንጀራ የምለብሰውንም ልብስ ቢሰጠኝ፥21.ወደ አባቴ ቤትም በጤና ብመለስ፥ እግዚአብሔር አምላኬ ይሆንልኛል፤22.ለሐውልት የተከልሁት ይህም ድንጋይ የእግዚአብሔር ቤት ይሆናል፤ ከሰጠኸኝም ሁሉ ለአንተ ከአሥር እጅ አንዱን እሰጥሃለሁ። a
ምዕራፍ 29
1.ያዕቆብም ተነሥቶ ወደ ምሥራቅ ሰዎች አገር ሄደ።2.በሜዳውም እነሆ ጕድጓድን አየ፥ በዚያም ሦስት የበጎች መንጎች በላዩ ተመስገው ነበር፤ ከዚያ ጕድጓድ በጎቹን ያጠጡ ነበርና፤ በጕድጓዱም አፍ የነበረው ድንጋይ ትልቅ ነበረ።3.መንጎችም ሁሉ ከዚያ በተከማቹ ጊዜ ድንጋዩን ከጕድጓዱ አፍ ገለል አድርገው በጎቹን ያጠጡ ነበር፤ ድንጋዩንም ወደ ስፍራው መልሰው በጕድጓዱ አፍ እንደ ገና ይገጥሙት ነበር።4.ያዕቆብም። ወንድሞቼ ሆይ፥ እናንት የወዴት ናችሁ? አላቸው። እነርሱም። እኛ የካራን ነን አሉት።5.የናኮርን ልጅ ላባን ታውቁታላችሁን? አላቸው። እነርሱም። እናውቀዋለን አሉት።6.እርሱ። ደኅና ነውን? አላቸው። እነርሱም። አዎን ደኅና ነው፤ አሁንም ልጁ ራሔል ከበጎች ጋር መጣች አሉት።7.እርሱም። ቀኑ ገና ቀትር ነው፥ ከብቶቹ የሚከማቹበት ሰዓቱም ገና አልደረሰም፤ አሁንም በጎቹን አጠጡና ሄዳችሁ አሰማሩአቸው አላቸው።8.እነርሱም አሉ። መንጎች ሁሉ እስኪከማቹና ድንጋዩን ከጕድጓዱ አፍ እስኪገለብጡት ድረስ አንችልም፤ ከዚያም በኋላ በጎቹን እናጠጣለን።9.እርሱም ገና ከእነርሱ ጋር ሲነጋገር እነሆ የላባ ልጅ ራሔል ከአባትዋ በጎች ጋር ደረሰች፤ እርስዋ የአባትዋን በጎች ትጠብቅ ነበርና።10.ያዕቆብም የእናቱን ወንድም የላባን ልጅ ራሔልንና የእጎቱን የላባን በጎች ባየ ጊዜ፥ ቀረበ ከጕድጓዱም አፍ ድንጋዩን ገለበጠ፥ የአጎቱን የላባን በጎችንም አጠጣ።11.ያዕቆብም ራሔልን ሳማት፥ ቃሉንም ከፍ አድርጎ አለቀሰ።12.ያዕቆብም የአባትዋ ዘመድና የርብቃ ልጅ መሆኑን ለራሔል አስታወቃት፤ እርስዋም ሮጣ ሄዳ ለአባትዋ ይህን ነገር ነገረችው።13.ላባም የእኅቱን ልጅ የያዕቆብን ወሬ በሰማ ጊዜ ሊቀበለው ሮጠ፥ አቅፎም ሳመው፥ ወደ ቤቱም አገባው። ነገሩንም ሁሉ ለላባ ነገረው ።14.ላባም። በእውነት አንተ አጥንቴ ሥጋዬም ነህ አለው። አንድ ወር የሚያህልም ከእርሱ ጋር ተቀመጠ።15.ላባም ያዕቆብን። ወንድሜ ስለሆንህ በከንቱ ታገለግለኛለህን? ምንዳህ ምንድር ነው? ንገረኝ አለው።16.ለላባም ሁለት ሴቶች ልጆች ነበሩት፤ የታላቂቱ ስም ልያ የታናሺቱ ስም ራሔል ነበረ።17.ልያም ዓይነ ልም ነበረች፤ ራሔል ግን መልከ መልካም ነበረች ፊትዋም ውብ ነበረ።18.ያዕቆብም ራሔልን ወደደ፤ እንዲህም አለ። ስለ ታናሺቱ ልጅህ ስለ ራሔል ሰባት ዓመት እገዛልሃለሁ።19.ላባም። ለሌላ ሰው ከምሰጣት ይልቅ ለአንተ ብሰጣት ይሻላል፤ ከእኔ ጋር ተቀመጥ አለ።20.ያዕቆብም ስለ ራሔል ሰባት ዓመት ተገዛ፤ እርስዋንም ይወድዳት ስለነበረ በእርሱ ዘንድ እንደ ጥቂት ቀን ሆነለት።21.ያዕቆብም ላባን። ወደ እርስዋ እገባ ዘንድ ሚስቴን ስጠኝ፥ ቀኔ ተፈጽሞአልና አለው።22.ላባም የዚያን ስፍራ ሰዎች ሁሉ ሰበሰበ፥ ሰርግም አደረገ።23.በመሸም ጊዜ ልጁን ልያን ወስዶ ለያዕቆብ አገባለት፤ ያዕቆብም ወደ እርስዋ ገባ።24.ላባም ለልጁ ለልያ ባሪያይቱን ዘለፋን ባርያ ትሆናት ዘንድ ሰጣት።25.በነጋም ጊዜ እነሆ ልያ ሆና ተገኘች፤ ላባንም። ምነው እንደዚህ አደረግህብኝ? ያገለገልሁህ ስለ ራሔል አልነበረምን? ለምን አታለልኸኝ? አለው።26.ላባም እንዲህ አለ። በአገራችን ታላቂቱ ሳለች፥ ታናሺቱን እንሰጥ ዘንድ ወግ አይደለም፤27.ይህችንም ሳምንት ፈጽም፤ ሌላ ሰባት ዓመት ደግሞ እኔን ስለምታገለግለኝ አገልግሎት እርስዋን ደግሞ እሰጥሃለሁ።28.ያዕቆብም እንዲህ አደረገ፥ ይህችንም ሳምንት ፈጸመ፤ ልጁን ራሔልንም ለእርሱ ሚስት ትሆን ዘንድ ሰጠው።29.ላባም ለልጁ ለራሔል ባርያይቱን ባላን ባርያ ትሆናት ዘንድ ሰጣት ።30.ያዕቆብም ወደ ራሔል ደግሞ ገባ። ራሔልንም ከልያ ይልቅ ወደዳት፤ ሌላ ሰባት ዓመትም ተገዛለት።31.እግዚአብሔርም ልያ የተጠላች መሆንዋን ባየ ጊዜ ማኅፀንዋን ከፈተላት፤ ራሔል ግን መካን ነበረች።32.ልያም ፀነሰች፥ ወንድ ልጅንም ወለደች፥ ስሙንም ሮቤል ብላ ጠራችው፤ እግዚአብሔር መከራዬን አይቶአልና፥ እንግዲህም ወዲህ ባሌ ይወድደኛል ብላለችና።33.ደግሞም ፀነሰች፥ ወንድ ልጅንም ወለደች፤ እኔ እንደ ተጠላሁ እግዚአብሔር ስለ ሰማ ይህን ደገመኝ አለች፤ ስሙንም ስምዖን ብላ ጠራችው።34.ደግሞም ፀነሰች፥ ወንድ ልጅንም ወለደች፤ አሁንም ባሌ ወደ እኔ ይጠጋል፥ ሦስት ወንዶች ልጆችን ወልጄለታለሁና አለች፤ ስለዚህም ስሙን ሌዊ ብላ ጠራችው።35.ደግሞም ፀነስች፥ ወንድ ልጅንም ወለደች፤ በዚህም ጊዜ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ አለች፤ ስለዚህም ስሙን ይሁዳ ብላ ጠራችው። መውለድንም አቆመች።
የማርቆስ ወንጌል
ምዕራፍ 11
1.ወደ ኢየሩሳሌምም ከደብረ ዘይት አጠገብ ወዳሉቱ ወደ ቤተ ፋጌና ወደ ቢታንያ በቀረቡ ጊዜ፥ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን ልኮ።2.በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ፥ ወዲያውም ወደ እርስዋ ገብታችሁ ከሰው ማንም ገና ያልተቀመጠበት ውርንጫ ታስሮ ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁ አምጡልኝ።3.ማንም። ስለ ምን እንዲህ ታደርጋላችሁ? ቢላችሁ። ለጌታ ያስፈልገዋል በሉት፥ ወዲያውም ደግሞ ወደዚህ ይሰደዋል አላቸው።4.ሄዱም ውርንጫውንም በመንገድ መተላለፊያ በደጅ ውጭ ታስሮ አገኙት፥ ፈቱትም።5.በዚያም ከቆሙት አንዳንዶቹ። ውርንጫውን የምትፈቱት ምን ልታደርጉት ነው አሉአቸው።6.እነርሱም ኢየሱስ እንዳዘዘ አሉአቸው፤ ተዉአቸውም።7.ውርንጫውንም ወደ ኢየሱስ አመጡት፥ ልብሳቸውንም በላዩ ጣሉ፥ ተቀመጠበትም።8.ብዙ ሰዎችም ልብሳቸውን በመንገድ ላይ አነጠፉ፥ ሌሎችም ከዛፍ ቅጠሎችን እየቈረጡ ያነጥፉ ነበር።9.የሚቀድሙትም የሚከተሉትም። ሆሣዕና፤ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፤10.በጌታ ስም የምትመጣ የአባታችን የዳዊት መንግሥት የተባረከች ናት፤ ሆሣዕና በአርያም እያሉ ይጮኹ ነበር።11.ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወደ መቅደስ ገባ፤ ዘወር ብሎም ሁሉን ከተመለከተ በኋላ፥ ጊዜው መሽቶ ስለ ነበረ ከአሥራ ሁለቱ ጋር ወደ ቢታንያ ወጣ።12.በማግሥቱም ከቢታንያ ሲወጡ ተራበ።13.ቅጠልም ያላት በለስ ከሩቅ አይቶ ምናልባት አንዳች ይገኝባት እንደ ሆነ ብሎ መጣ፥ ነገር ግን የበለስ ወራት አልነበረምና መጥቶ ከቅጠል በቀር ምንም አላገኘባትም።14.መልሶም። ከአሁን ጀምሮ ለዘላለም ማንም ከአንቺ ፍሬ አይብላ አላት። ደቀ መዛሙርቱም ሰሙ።15.ወደ ኢየሩሳሌምም መጡ። ወደ መቅደስም ገብቶ በመቅደስ የሚሸጡትንና የሚገዙትን ያወጣ ጀመር፥ የገንዘብ ለዋጮችንም ገበታዎች የርግብ ሻጭዎችንም ወንበሮች ገለበጠ፤16.ዕቃም ተሸክሞ ማንም በመቅደስ ሊያልፍ አልፈቀደም።17.አስተማራቸውም። ቤቴ ለአሕዛብ ሁሉ የጸሎት ቤት ትባላለች ተብሎ የተጻፈ አይደለምን? እናንተ ግን የወንበዶች ዋሻ አደረጋችኋት አላቸው።18.የካህናት አለቆችም ጻፎችም ሰምተው፥ ሕዝቡ ሁሉ በትምህርቱ ይገረሙ ስለ ነበር ይፈሩት ነበርና እንዴት አድርገው እንዲያጠፉት ፈለጉ።19.ማታ ማታም ከከተማ ወደ ውጭ ይወጣ ነበር።20.ማለዳም ሲያልፉ በለሲቱን ከሥርዋ ደርቃ አዩአት።21.ጴጥሮስም ትዝ ብሎት። መምህር ሆይ፥ እነሆ፥ የረገምሃት በለስ ደርቃለች አለው።22.ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው። በእግዚአብሔር እመኑ።23.እውነት እላችኋለሁ፥ ማንም ያለው ነገር እንዲደረግለት ቢያምን በልቡ ሳይጠራጠር፥ ይህን ተራራ። ተነቅለህ ወደ ባሕር ተወርወር ቢል ይሆንለታል።24.ስለዚህ እላችኋለሁ፥ የጸለያችሁትን የለመናችሁትንም ሁሉ እንዳገኛችሁት እመኑ፥ ይሆንላችሁማል።25.ለጸሎትም በቆማችሁ ጊዜ፥ በሰማያት ያለው አባታችሁ ደግሞ ኃጢአታችሁን ይቅር እንዲላችሁ፥ በማንም ላይ አንዳች ቢኖርባችሁ ይቅር በሉት።26.እናንተ ግን ይቅር ባትሉ በሰማያት ያለው አባታችሁም ኃጢአታችሁን ይቅር አይላችሁም።27.ደግሞም ወደ ኢየሩሳሌም መጡ። እርሱም በመቅደስ ሲመላለስ፥ የካህናት አለቆችና ጻፎች ሽማግሌዎችም ወደ እርሱ መጥተው።28.እነዚህን በምን ሥልጣን ታደርጋለህ? ወይስ እነዚህን ለማድረግ ይህን ሥልጣን ማን ሰጠህ? አሉት።29.ኢየሱስም። እኔም አንዲት ነገር እጠይቃችኋለሁ፥ እናንተም መልሱልኝ፥ እኔም በምን ሥልጣን እነዚህን እንዳደርግ እነግራችኋለሁ።30.የዮሐንስ ጥምቀት ከሰማይ ነበረችን ወይስ ከሰው? መልሱልኝ አላቸው።31.እርስ በርሳቸውም ሲነጋገሩ። ከሰማይ ነው ብንል። እንግዲያውስ ስለ ምን አላመናችሁበትም? ይለናል፤32.ነገር ግን። ከሰው ነው እንበልን? አሉ፤ ሁሉ ዮሐንስን በእውነት እንደ ነቢይ ያዩት ነበርና ሕዝቡን ፈሩ።33.ለኢየሱስም መልሰው። አናውቅም አሉት ኢየሱስም። እኔም በምን ሥልጣን እነዚህን እንዳደርግ አልነግራችሁም አላቸው።