ሳምንት 3 · ቀን 15 (አርብ)
📅 Meskerem 22, 2019
ኦሪት ዘፍጥረት 38, 39, 40 · የማርቆስ ወንጌል 15
ኦሪት ዘፍጥረት
ምዕራፍ 38
1.በዚያም ወራት እንዲህ ሆነ፤ ይሁዳ ከወንድሞቹ ተለይቶ ወረደ፥ ስሙን ኤራስ ወደሚሉት ወደ ዓዶሎማዊውም ሰው ገባ።2.ከዚያም ይሁዳ የከነዓናዊውን የሴዋን ሴት ልጅ አየ፤ ወሰዳትም፥ ወደ እርስዋም ገባ።3.ፀነሰችም ወንድ ልጅንም ወለደች፤ ስሙንም ዔር ብላ ጠራችው።4.ደግሞም ፀነሰች ወንድ ልጅንም ወለደች፤ ስሙንም አውናን ብላ ጠራችው።5.እንደ ገና ደግሞ ወንድ ልጅን ወለደች፥ ስሙንም ሴሎም ብላ ጠራችው፤ እርሱንም በወለደች ጊዜ ክዚብ በሚባል አገር ነበረች።6.ይሁዳም ለበኵር ልጁ ለዔር ትዕማር የምትባል ሚስት አጋባው።7.የይሁዳም የበኵር ልጅ ዔር በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነበረ፤ እግዚአብሔርም ቀሠፈው።8.ይሁዳም አውናን። ወደ ወንድምህ ሚስት ግባ፥ አግባትም፥ ለወንድምህም ዘርን አቁምለት አለው።9.አውናንም ዘሩ ለእርሱ እንዳይሆን አወቀ፤ ወደ ወንድሙ ሚስት በገባ ጊዜ ለወንድሙ ዘር እንዳይሰጥ ዘሩን በምድር ያፈስስው ነበር።10.ይህም ሥራው በእግዚአብሔር ዘንድ ክፉ ሆነበት፥ እርሱንም ደግሞ ቀሠፈው።11.ይሁዳም ምራቱን ትዕማርን። ልጄ ሴሎም እስኪያድግ ድረስ በአባትሽ ቤት መበለት ሆነሽ ተቀመጪ አላት፤ እርሱ ደግሞ እንደ ወንድሞቹ እንዳይሞት ብሎአልና። ትዕማርም ሄዳ በአባትዋ ቤት ተቀመጠች።12.ከብዙ ዘመንም በኋላ የይሁዳ ሚስት የሴዋ ልጅ ሞተች፤ ይሁዳም ተጽናና፥ የበጎቹን ጠጕር ወደሚሸልቱት ሰዎችም ወደ ተምና ወጣ፥ እርሱም ዓዶሎማዊው ወዳጁም ኤራስ።13.ለትዕማርም። እነሆ አማትሽ ይሁዳ የበጎቹን ጠጕር ይሸልት ዘንድ ወደ ተምና ይወጣል ብለው ነገሩአት።14.እርስዋም የመበለትነትዋን ልብስ አወለቀች፥ መጎናጸፊያዋንም ወሰደች፥ ተሸፈነችም፥ ወደ ተምናም በሚወስደው መንገድ ዳር በኤናይም ደጅ ተቀመጠች፤ ሴሎም እንደ አደገ ሚስትም እንዳልሆነችው አይታለችና።15.ይሁዳም ባያት ጊዜ ጋለሞታን መሰለችው፤ ፊትዋን ተሸፍና ነበርና።16.ወደ እርስዋም አዘነበለ። እባክሽ ወደ አንቺ ልግባ አላት፤ እርስዋ ምራቱ እንደ ሆነች አላወቀም ነበርና። እርስዋም። ወደኔ ብትገባ ምን ትሰጠኛለህ? አለችው።17.የፍየል ጠቦት ከመንጋዬ እሰድድልሻለሁ አላት። እርስዋም። እስክትሰድድልኝ ድረስ መያዣ ትሰጠኛለህን? አለችው።18.እርሱም። ምን መያዣ ልስጥሽ? አላት። እርስዋም። ቀለበትህን፥ አምባርህን፥ በእጅህ ያለውን በትር አለች። እርሱም ሰጣትና ከእርስዋ ጋር ደረሰ፥ እርስዋም ፀነሰችለት።19.እርስዋም ተነሥታ ሄደች፥ መጎናጸፊያዋንም አውልቃ የመበለትነትዋን ልብስ ለበሰች።20.ይሁዳም መያዣውን ከሴቲቱ እጅ ይቀበል ዘንድ በወዳጁ በዓዶሎማዊው እጅ የፍየሉን ጠቦት ላከላት፤ እርስዋንም አላገኛትም።21.እርሱም የአገሩን ሰዎች። በኤናይም በመንገድ ዳር ተቀምጣ የነበረች ጋለሞታ ወዴት ናት? ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም። በዚህ ጋለሞታ አልነበረችም አሉት።22.ወደ ይሁዳም ተመልሶ እንዲህ አለው። አላገኘኋትም፤ የአገሩም ሰዎች ደግሞ። ከዚህ ጋለሞታ አልነበረችም አሉኝ።23.ይሁዳም። እኛ መዘበቻ እንዳንሆን ትውሰደው፤ እነሆ የፍየሉን ጠቦት ሰደድሁላት፥ አንተም አላገኘሃትም አለ።24.እንዲህም ሆነ፤ ከሦስት ወር በኋላ ለይሁዳ። ምራትህ ትዕማር ሴሰነች፤ ደግሞም በዝሙት እነሆ ፀነሰች ብለው ነገሩት። ይሁዳም። አውጡአትና በእሳት ትቃጠል አለ።25.እርስዋም ባወጡአት ጊዜ ወደ አማትዋ እንዲህ ብላ ላከች። ለዚህ ለባለ ገንዘብ ነው የፀነስሁት፤ ተመልከት፤ ይህ ቀለበት፥ ይህ አምባር፥ ይህ በትር የማን ነው?26.ይሁዳም አወቀ። ከእኔ ይልቅ እርስዋ እውነተኛ ሆነች፤ ልጄን ሴሎምን አልሰጠኋትምና አለ። ደግሞም አላወቃትም።27.በመውለጃዋም ጊዜ እነሆ መንታ ልጆች በሆድዋ ነበሩ።28.ስትወልድም አንዱ እጁን አወጣ፤ አዋላጂቱም ቀይ ፈትል ወስዳ በእጁ አሰረች። ይህ መጀመሪያ ይወጣል አለች።29.እንዲህም ሆነ፤ እጁን በመለሰ ጊዜ እነሆ ወንድሙ ወጣ፤ እርስዋም። ለምን ጥስህ ወጣህ? አለች፤ ስሙንም ፋሬስ ብላ ጠራችው።30.ከእርሱም በኋላ ቀይ ፈትል በእጁ ያለበት ወንድሙ ወጣ፤ ስሙም ዛራ ተባለ።
ምዕራፍ 39
1.ዮሴፍ ግን ወደ ግብፅ ወረደ፤ የፈርዖን ጃንደረባ የዘበኞቹም አለቃ የሚሆን የግብፅ ሰው ጲጥፋራ ወደ ግብፅ ካወረዱት ከእስማኤላውያን እጅ ገዛው።2.እግዚአብሔር ከዮሴፍ ጋር ነበረ፥ ሥራውም የተከናወነለት ሰው ሆነ፤ በግብፃዊው ጌታውም ቤት ነበረ።3.ጌታውም እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር እንዳለ፥ እርሱ የሚሠራውንም ሁሉ እግዚአብሔር በእጁ እንዲያከናውንለት አየ።4.ዮሴፍም በጌታው ፊት ሞገስን አገኘ፥ እርሱንም ያገለግለው ነበር፤ በቤቱም ላይ ሾመው፥ ያለውንም ሁሉ በእጁ ሰጠው።5.እንዲህም ሆነ፤ በቤቱ ባለውም ሁሉ ላይ ከሾመው በኋላ እግዚአብሔር የግብፃዊውን ቤት ስለ ዮሴፍ ባረከው፤ የእግዚአብሔር በረከት በውጪም በግቢም ባለው ሁሉ ላይ ሆነ።6.ያለውንም ሁሉ ለዮሴፍ አስረከበ፤ ከሚበላውም እንጀራ በቀር ምንም የሚያውቀው አልነበረም። የዮሴፍም ፊቱ መልከ መልካምና ውብ ነበረ።7.ከዚህም በኋላ እንዲህ ሆነ፤ የጌታው ሚስት በዮሴፍ ላይ ዓይንዋን ጣለች። ከእኔም ጋር ተኛ አለችው።8.እርሱም እንቢ አለ፥ ለጌታውም ሚስት እንዲህ አላት። እነሆ ጌታዬ በቤቱ ያለውን ምንም ምን የሚያውቀው የለም፥ ያለውንም ሁሉ ለእኔ አስረክቦኛል፤9.ለዚህ ቤት ከእኔ የሚበልጥ ሰው የለም፤ ሚስቱ ስለ ሆንሽ ከአንቺም በቀር ያልሰጠኝ ነገር የለም፤ እንዴት ይህን ትልቅ ክፉ ነገር አደርጋለሁ? በእግዚአብሔር ፊት እንዴት ኃጢአትን እሠራለሁ?10.ይህንም ነገር በየዕለቱ ለዮሴፍ ትነግረው ነበር፤ እርሱም ከእርስዋ ጋር ይተኛ ዘንድ ከእርስዋም ጋር ይሆን ዘንድ አልሰማትም።11.እንዲህም ሆነ፤ በዚያን ጊዜ ሥራውን እንዲሠራ፤ ወደ ቤቱ ገባ፤ በቤትም ውስጥ ከቤት ሰዎች ማንም አልነበረም።12.ከእኔ ጋር ተኛ ስትል ልብሱን ተጠማጥማ ያዘች፤ እርሱም ልብሱን በእጅዋ ትቶላት ሸሸ ወደ ውጭም ወጣ።13.እንዲህም ሆነ፤ ልብሱን ትቶ ወደ ውጭ እንደ ሸሸ ባየች ጊዜ፥14.የቤትዋን ሰዎች ወደ እርስዋ ጠርታ እንዲህ ብላ ነገረቻቸው። እዩ፤ ዕብራዊው ሰው በእኛ እንዲሣለቅ አግብቶብናል፤፤ እርሱ ከእኔ ጋር ሊተኛ ወደ እኔ ገባ፥ እኔም ድምፄን ከፍ አድርጌ ጮኽሁ፤15.ድምፄንም ከፍ አድርጌ እንደ ጮኽሁ ቢሰማ ልብሱን በእኔ ዘንድ ጥሎ ሸሸ ወደ ውጭም ወጣ።16.ጌታው ወደ ቤቱ እስኪገባ ድረስም ልብሱን ከእርስዋ ዘንድ አኖረች።17.ይህንም ነገር እንዲህ ብላ ነገረችው። ያገባህልን ዕብራዊው ባሪያ ሊሣለቅብኝ ወደ እኔ ገባ፤18.እኔም ድምፄን ከፍ አድርጌ ስጮኽ ልብሱን በእጄ ተወና ወደ ውጭ ሸሸ።19.ጌታውም። ባሪያህ እንዲህ አደረገኝ ብላ የነገረችውን የሚስቱን ቃል በሰማ ጊዜ እጅግ ተቆጣ።20.የዮሴፍም ጌታ ወሰደው፥ የንጉሡ እስረኞችም ወደሚታሰሩበት ስፍራ ወደ ግዞት ቤት አገባው፤ ከዚያም በግዞት ነበረ።21.እግዚአብሔርም ከዮሴፍ ጋር ነበረ ምሕረትንም አበዛለት፥ በግዞት ቤቱም አለቃ ፊት ሞገስን ሰጠው።22.የግዞት ቤቱም አለቃ በግዞት ያሉትን እስረኞች ሁሉ በዮሴፍ እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፤ በዚያም የሚደረገው ነገር ሁሉ እርሱ የሚያደርገው ነበረ።23.የግዞት ቤቱም አለቃ በእጁ ያለውን ነገር ከቶ አላሰበም፥ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነበረና፤ የሚያደርገውንም ሁሉ እግዚአብሔር ያቀናለት ነበር።
ምዕራፍ 40
1.ከዚህ ነገር በኋላም እንዲህ ሆነ፤ የግብፅ ንጉሥ የጠጅ አሳላፊና የእንጀራ አበዛ ጌታቸውን የግብፅ ንጉሥን በደሉ።2.ፈርዖንም በሁለቱ ሹማምቱ በጠጅ አሳላፊዎቹ አለቃና በእንጀራ አበዛዎቹ አለቃ ላይ ተቆጣ፤3.ዮሴፍ ታስሮ በነበረበትም በግዞት ስፍራ በዘበኞቹ አለቃ ቤት አስጠበቃቸው።4.የዘበኞቹም አለቃ ለዮሴፍ አሳልፎ ሰጣቸው፥ እርሱም ያገለግላቸው ነበር፤ በግዞት ቤትም አያሌ ቀን ተቀመጡ።5.በግዞት ቤት የነበሩት የግብፅ ንጉሥ ጠጅ አሳላፊና እንጀራ አበዛ ሁለቱም በአንዲት ሌሊት እንደ ሕልሙ ትርጓሜ እየራሳቸው ሕልምን አለሙ።6.ዮሴፍም ማልዶ ወደ እነርሱ ገባ፥ እነሆም አዝነው አያቸው።7.በጌታው ቤት ከእርሱ ጋር በግዞት የነበሩትንም የፈርዖንን ሹማምት እንዲህ ብሎ ጠየቃቸው። እናንተ ዛሬ ስለ ምን አዝናችኋል?8.እነርሱም። ሕልምን አልመን የሚተረጕምልን አጣን አሉት። ዮሴፍም አላቸው። ሕልምን የሚተረጕም እግዚአብሔር የሰጠው አይደለምን? እስቲ ንገሩኝ።9.የጠጅ አሳላፊዎች አለቃም ለዮሴፍ ሕልሙን እንዲህ ብሎ ነገረው። በሕልሜ የወይን ዛፍ በፊቴ ሆና አየሁ፥10.በዛፊቱም ሦስት አረግ አለባት፤ እርስዋም ቅጠልና አበባ አወጣች፥ ዘለላም አንጠለጠለች፥ የዘለላዋም ፍሬ በሰለ፤11.የፈርዖንም ጽዋ በእጄ ነበረ፤ ፍሬውንም ወስጄ በፈርዖን ጽዋ ጨመቅሁት፥ ጽዋውንም ለፈርዖን በእጁ ሰጠሁት።12.ዮሴፍም አለው። የዚህ ትርጓሜው ይህ ነው፤ ሦስቱ አረግ ሦስት ቀን ነው፤13.እስከ ሦስት ቀን ድረስ ፈርዖን ራስህን ከፍ ያደርጋል፥ ወደ ቀደመው ሹመትህም ይመልስሃል፤ ጠጅ አሳላፊ በነበርህበት ጊዜ ስታደርግ እንደ ነበረው እንደ ቀድሞው ሥርዓትም የፈርዖንን ጽዋ በእጁ ትሰጣለህ።14.ነገር ግን በጎ ነገር በተደረገልህ ጊዜ እኔን አስበኝ፥ ምሕረትንም አድርግልኝ፥ የእኔንም ነገር ለፈርዖን ነግረህ ከዚህ ቤት አውጣኝ፤15.እኔን ከዕብራውያን አገር ሰርቀው አምጥተውኛልና፤ ከዚህም ደግሞ በግዞት ያኖሩኝ ዘንድ ምንም አላደረግሁም።16.የእንጀራ አበዛዎቹ አለቃም ሕልሙን በመልካም እንደ ተረጎመ ባየ ጊዜ ዮሴፍን እንዲህ አለው። እኔም ደግሞ ሕልም አይቼ ነበር፥ እነሆም ሦስት መሶብ ነጭ እንጀራ በራሴ ላይ ነበረ፤17.በላይኛውም መሶብ ፈርዖን ከሚበላው ከጋጋሪዎች ሥራ ሁሉ ነበረበት፤ ወፎችም በራሴ ላይ ከመሶቡ ይበሉ ነበር።18.ዮሴፍም መልሶ እንዲህ አለው። የዚህ ትርጓሜው ይህ ነው፤ ሦስቱ መሶብ ሦስት ቀን ነው፤19.እስከ ሦስት ቀን ድረስ ፈርዖን ራስህን ከፍ ያደርጋል፥ በእንጨትም ላይ ይሰቅልሃል፤ ወፎችም ሥጋህን ይበሉታል።20.በሦስተኛውም ቀን ፈርዖን የተወለደበት ቀን ነበረ፥ ለሠራዊቱም ሁሉ ግብር አደረገ፤ የጠጅ አሳላፊዎቹን አለቃና የእንጀራ አበዛዎቹን አለቃ በአሽከሮቹ መካከል ከፍ አደረገ።21.የጠጅ አሳለፊዎቹንም አለቃ ወደ ስፍራው መለሰው፥ ጽዋውንም በፈርዖን እጅ ሰጠ፤22.የእንጀራ አበዛዎቹንም አለቃ ሰቀለው፥ ዮሴፍ እንደተረጎመላቸው።23.የጠጅ አሳላፊዎች አለቃ ግን ዮሴፍን አላሰበውም፥ ረሳው እንጂ። a
የማርቆስ ወንጌል
ምዕራፍ 15
1.ወዲያውም ማለዳ የካህናት አለቆች ከሽማግሌዎችና ከጻፎች ከሸንጎውም ሁሉ ጋር ከተማከሩ በኋላ፥ ኢየሱስን አሳስረው ወሰዱትና ለጲላጦስ አሳልፈው ሰጡት።2.ጲላጦስም። አንተ የአይሁድ ንጉሥ ነህን? ብሎ ጠየቀው። እርሱም። አንተ አልህ ብሎ መለሰለት።3.የካህናት አለቆችም ብዙ ያሳጡት ነበር፤ እርሱ ግን ምንም አልመለሰም።4.ጲላጦስም ደግሞ። አንዳች አትመልስምን? እነሆ፥ በስንት ነገር ያሳጡሃል ብሎ ጠየቀው።5.ኢየሱስም ከዚያ በኋላ ጲላጦስ እስኪደነቅ ድረስ ምንም አልመለሰም።6.በዚያም በዓል የለመኑትን አንድ እስረኛ ይፈታላቸው ነበር።7.በዓመፅም ነፍስ ከገደሉት ከዓመፀኞች ጋር የታሰረ በርባን የተባለ ነበረ።8.ሕዝቡም ወጥተው እንደ ልማዱ ያደርግላቸው ዘንድ እየጮኹ ይለምኑት ጀመር።9.ጲላጦስም። የአይሁድን ንጉሥ እፈታላችሁ ዘንድ ትወዳላችሁን? ብሎ መለሰላቸው፤10.የካህናት አለቆች በቅንዓት አሳልፈው እንደ ሰጡት ያውቅ ነበርና።11.የካህናት አለቆች ግን በርባንን በእርሱ ፈንታ ይፈታላቸው ዘንድ ሕዝቡን አወኩአቸው።12.ጲላጦስም ዳግመኛ መልሶ። እንግዲህ የአይሁድ ንጉሥ የምትሉትን ምን ላደርገው ትወዳላችሁ? አላቸው።13.እነርሱም ዳግመኛ። ስቀለው እያሉ ጮኹ።14.ጲላጦስም። ምን ነው? ያደረገው ክፋት ምንድር ነው? አላቸው። እነርሱ ግን። ስቀለው እያሉ ጩኸት አበዙ።15.ጲላጦስም የሕዝቡን ፈቃድ ሊያደርግ ወዶ በርባንን ፈታላቸው፥ ኢየሱስንም ገርፎ እንዲሰቀል አሳልፎ ሰጠ።16.ወታደሮችም ፕራይቶሪዮን ወደሚባል ግቢ ውስጥ ወሰዱት፥ ጭፍራውንም ሁሉ በአንድነት ጠሩ።17.ቀይ ልብስም አለበሱት፥ የእሾህ አክሊልም ጎንጉነው ደፉበት፤18.የአይሁድ ንጉሥ ሆይ፥ ሰላም ለአንተ ይሁን እያሉ እጅ ይነሱት ጀመር፤19.ራሱንም በመቃ መቱት ተፉበትም፥ ተንበርክከውም ሰገዱለት።20.ከተዘባበቱበትም በኋላ ቀዩን ልብስ ገፈፉት፥ ልብሱንም አለበሱት፥ ሊሰቅሉትም ወሰዱት።21.አንድ መንገድ አላፊም የአሌክስንድሮስና የሩፎስ አባት ስምዖን የተባለ የቀሬና ሰው ከገጠር ሲመጣ መስቀሉን ይሸከም ዘንድ አስገደዱት።22.ትርጓሜውም የራስ ቅል ስፍራ ወደሚሆን ጎልጎታ ወደተባለ ስፍራ ወሰዱት።23.ከርቤም የተቀላቀለበትን የወይን ጠጅ እንዲጠጣ ሰጡት፤ እርሱ ግን አልተቀበለም።24.ሰቀሉትም፥ ልብሱንም ማን ማን እንዲወስድ ዕጣ ተጣጥለው ተካፈሉ።25.በሰቀሉትም ጊዜ ሦስት ሰዓት ነበረ።26.የክሱ ጽሕፈትም። የአይሁድ ንጉሥ የሚል ተጽፎ ነበር።27.ከእርሱም ጋር ሁለት ወንበዶች አንዱን በቀኙ አንዱንም በግራው ሰቀሉ።28.መጽሐፍም። ከአመፀኞች ጋር ተቆጠረ ያለው ተፈጸመ።29.የሚያልፉትም ራሳቸውን እየነቀነቁ ይሰድቡት ነበርና። ዋ፥ ቤተ መቅደስን የምታፈርስ በሦስት ቀንም የምትሠራ፥30.ከመስቀል ወርደህ ራስህን አድን አሉ።31.እንዲሁም የካህናት አለቆች ደግሞ ከጻፎች ጋር እርስ በርሳቸው እየተዘባበቱ። ሌሎችን አዳነ፤ ራሱን ሊያድን አይችልም፤32.አይተን እናምን ዘንድ የእስራኤል ንጉሥ ክርስቶስ አሁን ከመስቀል ይውረድ አሉ። ከእርሱም ጋር የተሰቀሉት ይነቅፉት ነበር።33.ስድስት ሰዓትም በሆነ ጊዜ፥ እስከ ዘጠኝ ሰዓት በምድር ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ።34.በዘጠኝ ሰዓትም ኢየሱስ። ኤሎሄ፥ ኤሎሄ፥ ላማ ሰበቅታኒ? ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ፤ ትርጓሜውም አምላኬ፥ አምላኬ፥ ለምን ተውኸኝ? ማለት ነው።35.በዚያም ከቆሙት ሰዎች ሰምተው። እነሆ፥ ኤልያስን ይጠራል አሉ።36.አንዱም ሮጦ ሆምጣጤ በሰፍነግ ሞላ በመቃም አድርጎ። ተዉ፤ ኤልያስ ሊያወርደው ይመጣ እንደ ሆነ እንይ እያለ አጠጣው።37.ኢየሱስም በታላቅ ድምፅ ጮኸ ነፍሱንም ሰጠ።38.የቤተ መቅደስም መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ከሁለት ተቀደደ።39.በዚያም በአንጻሩ የቆመ የመቶ አለቃ እንደዚህ ጮኾ ነፍሱን እንደ ሰጠ ባየ ጊዜ። ይህ ሰው በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነበረ አለ።41.አሁንም በመሸ ጊዜ የሰንበት ዋዜማ የሆነ የማዘጋጀት ቀን ስለ ነበረ፥ የከበረ አማካሪ የሆነ የአርማትያስ ዮሴፍ መጣ፥42.እርሱም ደግሞ የእግዚአብሔርን መንግሥት ይጠባበቅ ነበር፤ ደፍሮም ወደ ጲላጦስ ገባና የኢየሱስን ሥጋ ለመነው።43.ጲላጦስም አሁኑን እንዴት ሞተ ብሎ ተደነቀ፥ የመቶ አለቃውንም ጠርቶ ከሞተ ቆይቶአልን? ብሎ ጠየቀው፤44.ከመቶ አለቃውም ተረድቶ በድኑን ለዮሴፍ ሰጠው።45.በፍታም ገዝቶ አውርዶም በበፍታ ከፈነው ከዓለትም በተወቀረ መቃብር አኖረው፥ በመቃብሩ ደጃፍም ድንጋይ አንከባለለ።46.መግደላዊትም ማርያም የዮሳም እናት ማርያም ወዴት እንዳኖሩት ይመለከቱ ነበር።