Skip to Content
የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን | YEHIWOT MELHEK BETEKIRSTIAN
የ2019 ዓ.ም የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ 📖 ዛሬን አንብብ →

የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን

Yehiwot Melhek Betekirstian

ሳምንት 4 · ቀን 16 (ሰኞ) 📅 Meskerem 25, 2019

ኦሪት ዘፍጥረት 41, 42 · የማርቆስ ወንጌል 16

📖 የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም፦ 1954 መጽሐፍ ቅዱስ አዲሱ መደበኛ ትርጒም

ኦሪት ዘፍጥረት

ምዕራፍ 41

1.ከሁለት ዓመት በኋላም ፈርዖን ሕልምን አየ፥ እነሆም፥ በወንዙ ዳር ቆሞ ነበር። 2.እነሆም፥ መልካቸው ያማረ ሥጋቸውም የወፈረ ሰባት ላሞች ከወንዙ ወጡ፥ በውኃውም ዳር በመስኩ ይሰማሩ ነበር። 3.ከእነርሱም በኋላ እነሆ መልካቸው የከፋ ሥጋቸውም የከሳ ሌሎች ሰባት ላሞች ከወንዝ ወጡ፥ በእነዚያም ላሞች አጠገብ በወንዙ ዳር ይቆሙ ነበር። 4.መልካቸው የከፋ ሥጋቸውም የከሳ እነዚያም ላሞች መልካቸው ያማረውን ሥጋቸው የወፈረውን ሰባቱን ላሞች ዋጡአቸው። ፈርዖንም ነቃ። 5.ደግሞም ተኛ ሁለተኛም ሕልምን አየ። እነሆም በአንድ አገዳ ላይ የነበሩ ያማሩና መልካም የሆኑ ሰባት እሸቶች ወጡ፤ 6.እነሆም ከእነርሱ በኋላ የሰለቱና በምሥራቅ ነፋስ የተመቱ ሰባት እሸቶች ወጡ፤ 7.የሰለቱትም እሸቶች ሰባቱን ያማሩና የዳበሩ እሸቶች ዋጡአቸው። 8.ፈርዖንም ነቃ፥ እነሆም ሕልም ነበረ። በነጋም ጊዜ ነፍሱ ታወከችበት፤ ወደ ሕልም ተርጓሚዎች ሁሉ ወደ ግብፅ ጠቢባንም ሁሉ ልኮ ወደ እርሱ ጠራቸው፤ ፈርዖንም ሕልሙን ነገራቸው፥ ነገር ግን ከእነርሱ ለፈርዖን የሚተረጕም አልተገኘም። 9.የዚያን ጊዜ የጠጅ አሳላፈዎቹ አለቃ እንዲህ ብሎ ለፈርዖን ተናገረ። እኔ ኃጢአቴን ዛሬ አስባለሁ፤ 10.ፈርዖን በባሪይዎቹ ላይ ተቆጣ፥ እኔንም የእንጀራ አበዛዎቹንም አለቃ በግዞት ስፍራ በዘበኞች አለቃ ቤት አኖረን፤ 11.እኛም በአንዲት ሌሊት ሕልምን አለምን፥ እኔና እርሱ፤ እያንዳንዳችን እንደ ሕልማችን ትርጓሜ አለምን። 12.በዚያም የዘበኞቹ አለቃ ባሪያ የሆነ አንድ ዕብራዊ ጕልማሳ ከእኛ ጋር ነበረ፤ ለእርሱም ነገርነው፥ ሕልማችንንም ተረጐመልን፤ ለእያንዳንዱም እንደ ሕልሙ ተረጐመልን። 13.እንዲህም ሆነ፤ እንደ ተረጐመልን እንደዚያው ሆነ፤ እኔ ወደ ሹመቴ ተመለስሁ፥ እርሱም ተሰቀለ። 14.ፈርዖንም ልኮ ዮሴፍን አስጠራ፥ ከግዞት ቤትም አስቸኰሉት፤ እርሱም ተላጨ፥ ልብሱንም ለወጠ፥ ወደ ፈርዖንም ገባ። 15.ፈርዖንም ዮሴፍን አለው። ሕልምን አየሁ፥ የሚተረጕመውም አልተገኘም፤ ሕልምን እንደ ሰማህ፥ እንደ ተረጐምህም ስለ አንተ ሰማሁ። 16.ዮሴፍም ለፈርዖን እንዲህ ብሎ መለሰ። ይህ በእኔ አይደለም፤ እግዚአብሔር ግን ለፈርዖን በደኅንነት ይመልስለታል። 17.ፈርዖንም ለዮሴፍ እንዲህ አለው። እነሆ፥ በሕልሜ በወንዝ ዳር ቆሜ ነበር፤ 18.እነሆም፥ ሥጋቸው የወፈረ መልካቸውም ያማረ ሰባት ላሞች ወጡ፥ በመስኩም ይሰማሩ ነበር፤ 19.ከእነርሱም በኋላ እነሆ የደከሙ መልካቸውም እጅግ የከፋ ሥጋቸውም የከሳ ሌሎች ሰባት ላሞች ወጡ፤ በግብፅም ምድር ሁሉ እንደ እነርሱ መልከ ክፉ ከቶ አላየሁም፤ 20.የከሱትና መልከ ክፋዎቹ ላሞች የመጀመሪያዎቹን ወፍራሞቹን ሰባት ላሞች ዋጡአቸው፥ 21.በሆዳቸውም ተዋጡ፤ በሆዳቸውም እንደተዋጡ አልታወቀም፥ መልካቸውም በመጀመሪያ እንደ ነበረው የከፋ ነበረ። ነቃሁም። 22.በሕልሜም እነሆ የዳበሩና መልካም የሆኑ ሰባት እሸቶች በአንድ አገዳ ሲወጡ አየሁ፤ 23.ከእነርሱም በኋላ እነሆ የደረቁና የሰለቱ በምሥራቅ ነፋስ የተመቱ ሰባት እሸቶች ወጡ፤ 24.የሰለቱት እሸቶች ያማሩትን ሰባቱን እሸቶች ዋጡአቸው። ለሕልም ተርጓሚዎችም ሕልሜን ነገርሁ የሚተረጕምልኝም አጣሁ። 25.ዮሴፍም ፈርዖንን አለው። የፈርዖን ሕልሙ አንድ ነው፤ እግዚአብሔር ሊያደርገው ያለውን ለፈርዖን ነግሮታል። 26.ሰባቱ መልካካሞች ላሞች ሰባት ዓመታት ናቸው፥ ሰባቱም መልካካሞች እሸቶች ሰባት ዓመታት ናቸው፤ ሕልሙ አንድ ነው። 27.ከእነርሱም በኋላ የወጡት የከሱትና መልከ ክፋዎቹ ሰባት ላሞች ሰባት ዓመታት ናቸው፥ የሰለቱትና የምሥራቅ ነፋስ የመታቸው ሰባቱም እሸቶች እነርሱ ራብ የሚሆንባቸው ሰባት ዓመታት ናቸው። 28.ለፈርዖን የነገርሁት ነገር ይህ ነው፤ እግዚአብሔር ሊያደርገው ያለውን ለፈርዖን አሳየው። 29.እነሆ በግብፅ ምድር ሁሉ እጅግ ጥጋብ የሚሆንባቸው ሰባት ዓመታት ይመጣሉ፤ 30.ደግሞ ከዚህ በኋላ የሰባት ዓመት ራብ ይመጣል፥ በግብፅ አገር የነበረውም ጥጋብ ሁሉ ይረሳል፤ ራብም ምድርን በጣም ያጠፋል፤ 31.በኋላ ከሚሆነው ከዚያ ራብ የተነሣም በምድር የሆነው ጥጋብ አይታወቅም፥ እጅግ ጽኑ ይሆናልና። 32.ሕልሙም ለፈርዖን ደጋግሞ መታየቱ ነገሩ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተቈረጠ ስለ ሆነ ነው፥ እግዚአብሔርም ፈጥኖ ያደርገዋል። 33.አሁንም ፈርዖን ብልህና አዋቂ ሰውን ይፈልግ፥ በግብፅ ምድር ላይም ይሹመው። 34.ፈርዖን በምድር ላይ ሹማምትን ይሹም፤ በሰባቱም የጥጋብ ዓመታት ከሚገኘው ፍሬ በግብፅ ምድር ሁሉ ከአምስት እጅ አንደኛውን ይውሰድ። 35.የሚመጡትን የመልካሞቹን ዓመታት እህላቸውን ያከማቹ፤ ስንዴውንም ከፈርዖን እጅ በታች ያኑሩ፥ እህሎችም በከተሞች ይጠበቁ። 36.በግብፅ ምድር ስለሚሆነው ስለ ሰባቱ ዓመታት ራብ እህሉ ተጠብቆ ይኑር፥ ምድሪቱም በራብ አትጠፋም። 37.ነገሩም በፈርዖንና በሎሌዎቹ ፊት መልካም ሆነ፤ 38.ፈርዖንም ሎሌዎቹን እንዲህ አላቸው። በውኑ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበትን እንደዚህ ያለ ሰው እናገኛለንን? 39.ፈርዖንም ዮሴፍን አለው። እንደ አንተ ያለ ብልህ አዋቂም ሰው የለም፥ እግዚአብሔር ይህን ሁሉ ገልጦልሃልና። 40.አንተ በቤቴ ላይ ተሾም፥ ሕዝቤም ሁሉ ለቃልህ ይታዘዝ፤ እኔ በዙፋኔ ብቻ ከአንተ እበልጣለሁ። 41.ፈርዖንም ዮሴፍን። በግብፅ ምድር ሁሉ ላይ ሾምሁህ አለው። 42.ፈርዖን ቀለበቱን ከእጁ አወለቀ በዮሴፍ እጅም አደረገው፥ ነጭ የተልባ እግር ልብስንም አለበሰው፥ በአንገቱም የወርቅ ዝርግፍን አደረገለት፤ 43.የእርሱም በምትሆን በሁለተኛይቱ ሰረገላ አስቀመጠው፥ አዋጅ ነጋሪም። ስገዱ እያለ በፊት በፊቱ ይጮኽ ነበር፤ እርሱም በግብፅ ምድር ሁሉ ላይ ተሾመ። 44.ፈርዖንም ዮሴፍን አለው። እኔ ፈርዖን ነኝ፤ በግብፅ አገር ሁሉ ያለ አንተ ማንም እጁንም እግሩንም አያንሣ። 45.ፈርዖንም የዮሴፍን ስም ጸፍናት ፐዕናህ ብሎ ጠራው፤ የሄልዮቱ ከተማ ካህን የDoጥፌራ ልጅ የምትሆን አስናትን አጋባው። ዮሴፍም በግብፅ ምድር ሁሉ ወጣ። 46.ዮሴፍም በግብፅ ንጉሥ በፈርዖን ፊት በቆመ ጊዜ ዕድሜው ሠላሳ ዓመት ነበረ። ዮሴፍም ከፈርዖን ፊት ወጣ፥ የግብፅ ምድርንም ሁሉ ዞረ። 47.በሰባቱም በጥጋብ ዓመታት የምድሪቱ ፍሬ ክምር ሆነ። 48.በግብፅ ምድር ሁሉ ያለውን የሰባቱን ዓመት እህል ሁሉ ሰበሰበ፥ እህልንም በከተሞቹ አደለበ፤ በየከተማይቱ ዙሪያ ያለውን የእርሻውን እህል ሁሉ በዚያው ከተተ። 49.ዮሴፍም እንደ ባሕር አሸዋ እጅግ ብዙ የሆነ ስንዴን አከማቸ፥ መስፈርን እስኪተው ድረስ፤ ሊሰፈር አልተቻለምና። 50.ለዮሴፍም የሄልዮቱ ከተማ ካህን የDoጥፌራ ልጅ አስናት የወለደችለት ሁለት ልጆች የራብ ዘመን ገና ሳይመጣ ተወለዱለት። 51.ዮሴፍም የበኵር ልጁን ስም ምናሴ ብሎ ጠራው፥ እንዲህ ሲል። እግዚአብሔር መከራዬን ሁሉ የአባቴንም ቤት አስረሳኝ፤ 52.የሁለተኛውንም ስም ኤፍሬም ብሎ ጠራው፥ እንዲህ ሲል። እግዚአብሔር በመከራዬ አገር አፈራኝ። 53.በግብፅ ምድር የነበረውም የሰባቱ ዓመት ጥጋብ አለፈ፥ 54.ዮሴፍም እንደ ተናገረ የሰባቱ ዓመት ራብ ጀመረ። በየአገሩም ሁሉ ራብ ሆነ፤ በግብፅ ምድር ሁሉ ግን እህል ነበረ። 55.የግብፅ ምድርም ሁሉ ተራበ፥ ሕዝቡም ስለ እህል ወደ ፈርዖን ጮኸ፤ ፈርዖንም የግብፅ ሰዎችን ሁሉ። ወደ ዮሴፍ ሂዱ፥ እርሱ ያላችሁንም ሁሉ አድርጉ አላቸው። 56.በምድርም ሁሉ ላይ ራብ ሆነ፤ ዮሴፍም እህል ያለበትን ጎተራ ሁሉ ከፍቶ ለግብፅ ሰዎች ሁሉ ይሸጥ ነበር፤ ራብም በግብፅ ምድር ጸንቶ ነበር። 57.አገሮችም ሁሉ እህል ይገዙ ዘንድ ወደ ግብፅ ወደ ዮሴፍ መጡ፤ በምድር ሁሉ ራብ እጅግ ጸንቶ ነበርና።
​

ምዕራፍ 42

1.ያዕቆብም በግብፅ እህል እንዳለ ሰማ፥ ያዕቆብም ልጆቹን። ለምን እርስ በርሳችሁ ትተያያላችሁ? አላቸው። 2.እንዲህም አለ። እነሆ ስንዴ በግብፅ እንዲገኝ ሰምቼአለሁ፤ ወደዚያ ውረዱ፥ እንድንድንና እንዳንሞትም ከዚያ ሸምቱልን። 3.የዮሴፍም አሥሩ ወንድሞቹ ስንዴን ከግብፅ ይሸምቱ ዘንድ ወረዱ፤ 4.የዮሴፍን ወንድም ብንያምን ግን ያዕቆብ ከወንድሞቹ ጋር አልሰደደውም። ምናልባት ክፉ እንዳያገኘው ብሎአልና። 5.የእስራኤልም ልጆች ለእህል ሸመታ ከመጡቱ ጋር ገቡ፤ በከነዓን አገር ራብ ነበረና። 6.ዮሴፍም በምድር ላይ ገዥ ነበረ፥ እርሱም ለምድር ሕዝብ ሁሉ ይሸጥ ነበር፤ የዮሴፍም ወንድሞች በመጡ ጊዜ በምድር ላይ በግምባራቸው ሰገዱለት። 7.ዮሴፍም ወንድሞቹን አይቶ አወቃቸው፤ ተለወጠባቸውም፥ ክፉ ቃልንም ተናገራቸው። እናንተ ከወዴት መጣችሁ? አላቸው። እነርሱም። ከከነዓን ምድር እህል ልንሸምት የመጣን ነን አሉት። 8.ዮሴፍም ወንድሞቹን አወቃቸው፥ እነርሱ ግን አላወቁትም፤ 9.ዮሴፍም ስለ እነርሱ አይቶት የነበረውን ሕልም አሰበ። እንዲህም አላቸው። እናንተ ሰላዮች ናችሁ፤ የምድሩን ዕራቁትነት ልታዩ መጥታችኋል። 10.እነርሱም አሉት። ጌታችን ሆይ አይደለም፤ ባሪያዎችህ ስንዴን ሊገዙ መጥተዋል፤ 11.እኛ ሁላችን የአንድ ሰው ልጆች ነን፤ እኛ እውነተኞች ነን፥ ባሪያዎችህስ ሰላዩች አይደሉም። 12.እርሱም አላቸው። አይደለም፤ ነገር ግን የአገሩን ዕራቁትነት ልታዩ መጥታችኋል። 13.እነርሱም አሉ። ባሪያዎችህ አሥራ ሁለት ወንድማማች በከነዓን ምድር የአንድ ሰው ልጆች ነን፤ ታናሹም እነሆ ዛሬ ከአባታችን ጋር ነው፥ አንዱም ጠፍቶአል። 14.ዮሴፍም አላቸው። እናንተ ሰላዮች ናችሁ ብዬ የተናገርኋችሁ ይህ ነው፤ 15.በዚህ ትፈተናላችሁ፤ ታናሽ ወንድማችሁ ካልመጣ በቀር የፈርዖንን ሕይወት ከዚህ አትወጡም። 16.እውነትን የምትናገሩ ከሆነ ነገራችሁ ይፈተን ዘንድ ከእናንተ አንዱን ስደዱ፥ ወንድማችሁንም ይዞ ይምጣ እናንተም ታሥራችሁ ተቀመጡ፤ ይህ ካልሆነ የፈርዖንን ሕይወት ሰላዮች ናችሁ። 17.ሦስት ቀን ያህል በግዞት ቤት ጨመራቸው። 18.በሦስተኛውም ቀን ዮሴፍ እንዲህ አላቸው። ትድኑ ዘንድ ይህን አድርጉ፤ እኔ እግዚአብሔርን እፈራለሁና። 19.እናንተ የታመናችሁ ከሆናችሁ ከእናንተ አንዱ ወንድማችሁ በግዞታችሁ ቤት ይታሰር እናንተ ግን ሂዱ፥ እህሉንም ለቤታችሁ ራብ ውሰዱ፤ 20.ታናሹንም ወንድማችሁን ወደ እኔ ይዛችሁ ኑ፤ ነገራችሁም የታመነ ይሆናልና አትሞቱም። እንዲህም አደረጉ። 21.እነርሱም እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ። በእውነት ወንድማችንን በድለናል፥ እኛን በማማጠን ነፍሱ ስትጨነቅ አይተን አልሰማነውምና፤ ስለዚህ ይህ መከራ መጣብን። 22.ሮቤልም መልሶ እንዲህ አላቸው። ብላቴናውን አትበድሉ ብያችሁ አልነበረምን? እኔም አልሰማችሁኝም፤ ስለዚህ እነሆ አሁን ደሙ ይፈላለገናል። 23.እነርሱም ዮሴፍ ነገራቸውን እንደሚሰማባቸው አላወቁም፥ በመካከላቸው አስተርጓሚ ነበረና። 24.ከእነርሱም ዘወር ብሎ አለቀሰ፤ ደግሞም ወደ እነርሱ ተመልሶ ተናገራቸው፥ ስምዖንንም ከእነርሱ ለይቶ ወሰዶ በፊታቸው አሰረው። 25.ዮሴፍም ዓይበታቸውን እህል ይሞሉት ዘንድ አዘዘ፤ የእየራሳቸውንም ብር በእየዓይበታቸው ይመልሱት ዘንድ ደግሞም የመንገድ ስንቅ ይሰጡአቸው ዘንድ አዘዘ። እንዲሁም ተደረገላቸው። 26.እነርሱም እህሉን በአህዮቻቸው ላይ ጫኑ፥ ከዚያም ተነሥተው ሄዱ። 27.ከእነርሱም አንዱ ባደሩበት ስፍራ ለአህያው ገፈራን ይሰጥ ዘንድ ዓይበቱን ሲፈታ ብሩን አየ፥ እነሆም በዓይበቱ አፍ ላይ ነበረች። 28.ለወንድሞቹም። ብሬ ተመለሰችልኝ፥ እርስዋም በዓይበቴ አፍ እነኋት አላቸው። ልባቸውም ደነገጠ፥ እየተንቀጠቀጡም እርስ በርሳቸው ተባባሉ። እግዚአብሔር ያደረገብን ይህ ምንድር ነው? 29.ወደ አባታቸውም ወደ ያዕቆብ ወደ ከነዓን ምድር መጡ፥ የደረሰባቸውንም ነገር ሁሉ እንዲህ ብለው አወሩ። 30.የአገሩ ጌታ የሆነው ሰው በክፉ ንግግር ተናገረን፥ የምድሪቱም ሰላዮች አስመሰለን። 31.እኛም እንዲህ አልነው። እውነተኞች ሰዎች ነን እንጂ ሰላዮች አይደለንም፤ 32.እኛ የአባታችን ልጆች አሥራ ሁለት ወንድማማች ነን፤ አንዱ ጠፍቶአል፥ ታናሹም በከነዓን ምድር ዛሬ ከአባታችን ጋር አለ። 33.የአገሩም ጌታ ያ ሰው እንዲህ አለን። የታመናችሁ ሰዎች ከሆናችሁ በዚህ አውቃለሁ፤ አንደኛውን ወንድማችሁን ከእኔ ጋር ተዉት፥ ለቤታችሁም ራብ እህልን ወስዳችሁ ሂዱ፤ 34.ታናሹንም ወንድማችሁን አምጡልኝ፥ እውነተኞች እንጂ ሰላዮች አለመሆናችሁንም በዚህ አውቀዋለሁ፤ ወንድማችሁንም እሰጣችኋለሁ፥ እናንተም በምድሩ ትነግዳላችሁ። 35.እንዲህም ሆነ፤ ዓይበታቸውን በፈቱ ጊዜ እነሆ ከእነርሱ እያንዳንዳቸው ብራቸውን በእየዓይበታቸው ተቋጥሮ አገኙት፤ እነርሱም አባታቸውም የብራቸውን ቍጥራት አይተው ፈሩ። 36.አባታቸው ያዕቆብም እንዲህ አላቸው። ልጅ አልባ አስቀራችሁኝ፤ ዮሴፍ የለም፥ ስምዖንም የለም፥ ብንያምንም ትወስዱብኛላችሁ፤ ይህ ሁሉ በእኔ ላይ ደረሰ። 37.ሮቤልም አባቱን አለው። ወደ አንተ መልሼ ያላመጣሁት እንደ ሆነ ሁለቱን ልጆቼን ግደል፤ እርሱን በእጄ ስጠኝ፥ እኔም ወደ አንተ እመልሰዋለሁ። 38.እርሱም አለ። ልጄ ከእናንተ ጋር አይወርድም፤ ወንድሙ ሞቶ እርሱ ብቻ ቀርቶአልና፤ በምትሄዱበት መንገድ ምናልባት ክፉ ነገር ቢያገኘው ሽምግልናዬን በኅዘን ወደ መቃብር ታወርዱታላችሁ።

የማርቆስ ወንጌል

ምዕራፍ 16

ትንሣኤው

16፥1-8 ተጓ ምብ – ማቴ 28፥1-8፤ ሉቃ 24፥1-10
1.ሰንበት ካለፈ በኋላ መግደላዊት ማርያም፣ የያዕቆብ እናት ማርያምና ሰሎሜ ሄደው የኢየሱስን ሥጋ ለመቀባት ሽቱ ገዙ። 2.በሳምንቱ መጀመሪያ ቀን ጧት በማለዳ፣ ገና ፀሓይ እንደ ወጣች፣ ወደ መቃብሩ በመሄድ ላይ ሳሉ፣ 3.“ድንጋዩን ከመቃብሩ ደጃፍ ላይ ማን ያንከባልልልናል?” በማለት እርስ በርሳቸው ይነጋገሩ ነበር። 4.ቀና ብለው ሲመለከቱ፣ በጣም ትልቅ የነበረው ድንጋይ ከደጃፉ ላይ ተንከባልሎ አዩ። 5.ወደ መቃብሩ እንደ ገቡም፣ ነጭ ልብስ የለበሰ ጕልማሳ በቀኝ በኩል ተቀምጦ አዩና ደነገጡ። 6.እርሱ ግን እንዲህ አላቸው፤ “አትደንግጡ፤ የተሰቀለውን የናዝሬቱን ኢየሱስን ትፈልጉታላችሁ፤ እርሱ ግን ተነሥቷል! እዚህ የለም፤ እርሱን ያኖሩበት ስፍራ ይኸውላችሁ። 7.ነገር ግን ሄዳችሁ ለደቀ መዛሙርቱና ለጴጥሮስ፣ ‘ቀድሟችሁ ወደ ገሊላ ይሄዳል፤ እንደ ነገራችሁ እዚያ ታገኙታላችሁ’ ብላችሁ ንገሯቸው።” 8.ሴቶቹም እየተንቀጠቀጡና እየተደነቁ ከመቃብሩ ሸሽተው ወጡ፤ ፈርተው ስለ ነበር ለማንም አንዳች አልተናገሩም።

[

9.በሳምንቱ መጀመሪያ ቀን ማለዳ ከሙታን ከተነሣ በኋላ፣ ሰባት አጋንንት ላወጣላት ለማርያም መግደላዊት በመጀመሪያ ታየ። 10.እርሷም ሄዳ፣ ከርሱ ጋራ የነበሩት እያዘኑ ሲያለቅሱ አግኝታ ነገረቻቸው፤ እነርሱ ግን 11.እርሱ ሕያው መሆኑንና ለርሷም መታየቱን ሲሰሙ አላመኗትም። 12.ከዚህ በኋላ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱ ወደ ገጠር ሲሄዱ በሌላ መልክ ታያቸው። 13.እነርሱም ተመልሰው ይህንኑ ለቀሩት ነገሯቸው፤ ይሁን እንጂ እነርሱንም አላመኗቸውም። 14.ከዚያም ዐሥራ አንዱ በማእድ ላይ ሳሉ ተገለጠላቸው፤ ከተነሣ በኋላ ያዩት ሰዎች የነገሯቸውን ስላላመኗቸው፣ አለማመናቸውንና የልባቸውን ድንዳኔ ነቀፈ። 15.እንዲህም አላቸው፤ “ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ፤ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ፤ 16.ያመነ የተጠመቀ ይድናል፤ ያላመነ ግን ይፈረድበታል። 17.የሚያምኑትን እነዚህ ምልክቶች ይከተሏቸዋል፤ በስሜ አጋንንትን ያወጣሉ፤ በአዲስ ልሳንም ይናገራሉ፤ 18.እባቦችን በእጃቸው ይይዛሉ፤ የሚገድል መርዝ ቢጠጡ እንኳ አይጐዳቸውም፤ እጃቸውንም በሕመምተኞች ላይ ይጭናሉ፤ እነርሱም ይፈወሳሉ።” 19.ጌታ ኢየሱስ ይህን ከተናገራቸው በኋላ ወደ ሰማይ ዐረገ፤ በእግዚአብሔርም ቀኝ ተቀመጠ። 20.ከዚያም ደቀ መዛሙርቱ ወጥተው፣ በየስፍራው ሁሉ ሰበኩ፤ ጌታም ከእነርሱ ጋራ ይሠራ ነበር፤ ትምህርታቸውንም ተከትለው በሚፈጸሙ ምልክቶች ቃሉን ያጸና ነበር።]
♫
Listen to the reading 3 chapter tracks
ኦሪት ዘፍጥረት Chapter 41
ኦሪት ዘፍጥረት Chapter 42
የማርቆስ ወንጌል Chapter 16
Swipe to browse chapters
Listen 3