ሳምንት 3 · ቀን 13 (ረቡዕ)
📅 Meskerem 20, 2019
ኦሪት ዘፍጥረት 32, 33, 34 · መዝሙረ ዳዊት 145 · የማርቆስ ወንጌል 13
ኦሪት ዘፍጥረት
ምዕራፍ 32
1.ያዕቆብም መንገዱን ሄደ፥ የእግዚአብሔር መላእክትም ተገናኙት።2.ያዕቆብም ባያቸው ጊዜ። እነዚህ የእግዚአብሔር ሠራዊት ናቸው አለ፤ የዚያንም ስፍራ ስም መሃናይም ብሎ ጠራው።3.ያዕቆብም ወደ ወንድሙ ወደ ዔሳው ወደ ሴይር ምድር ወደ ኤዶም አገር ከፊቱ መልእክተኞችን ላከ፤4.እንዲህም ብሎ አዘዛቸው። ለጌታዬ ለዔሳው። ባሪያህ ያዕቆብ እንዲህ አለ ብላችሁ ንገሩት። በላባ ዘንድ በስደት ተቀመጥሁ፤ እስከ አሁን ድረስ ቆየሁ፤5.ላሞችንም አህዮችንም በጎችን ወንዶች ባሪያዎችንም ሴቶች ባሪያዎችንም አገኘሁ፤ አሁንም በፊትህ ሞገስን አገኝ ዘንድ ለጌታዬ ለማስታወቅ ላክሁ።6.መልእክተኞቹም ወደ ያዕቆብ ተመልሰው እንዲህ አሉት። ወደ ወንድምህ ወደ ዔሳው ሄደን ነበር፤ እርሱም ደግሞ ሊቀበልህ ይመጣል፥ ከእርሱም ጋር አራት መቶ ሰዎች አሉ።7.ያዕቆብም እጅግ ፈርቶ ተጨነቀ፤ ከእርሱም ጋር ያሉትን ሰዎች መንጎችንም ላሞችንም ግመሎችንም በሁለት ወገን ከፈላቸው፤8.እንዲህም አለ። ዔሳው መጥቶ አንዱን ወገን የመታ እንደ ሆነ የቀረው ወገን ያመልጣል።9.ያዕቆብም አለ። የአባቴ የአብርሃም አምላክ ሆይ፥ የአባቴም የይስሐቅ አምላክ ሆይ። ወደ ምድርህ ወደ ተወለድህበትም ስፍራ ተመለስ፥ በጎነትንም አደርግልሃለሁ ያልኸኝ እግዚአብሔር ሆይ፤10.ለባሪያህ ከሠራኸው ከምሕረትህና ከእውነትህም ሁሉ ትንሽ ስንኳ የማይገባኝ ነኝ፤ በትሬን ብቻ ይዤ ይህን ዮርዳኖስን ተሻግሬ ነበርና፥ አሁን ግን የሁለት ክፍል ሠራዊት ሆንሁ።11.ከወንድሜ ከዔሳው እጅ አድነኝ፤ መጥቶ እንዳያጠፋኝ፥ እናቶችንም ከልጆች ጋር እንዳያጠፋ እኔ እፈራዋለሁና።12.አንተም። በእርግጥ መልካም አደርግልሃለሁ፥ ዘርህንም ከብዛቱ የተነሣ እንደማይቈጠር እንደ ባሕር አሸዋ አደርጋለሁ ብለህ ነበር።13.በዚያችም ሌሊት ከዚያው አደረ። ከያዘውም ሁሉ ለወንድሙ ለዔሳው እጅ መንሻን አወጣ፤14.ሁለት መቶ እንስት ፍየሎችንና ሀያ የፍየል አውራዎችን፥ ሁለት መቶ እንስት በጎችንና ሀያ የበግ አውራዎችን፥15.ሠላሳ የሚያጠቡ ግመሎችን ከግልገሎቻቸው ጋር፥ አርባ ላም፥ አሥር በሬ፥ ሀያ እንስት አህያ፥ አሥርም የእህያ ግልገሎችን።16.መንጎቹን በየወገኑ ከፍሎ በባሪያዎቹ እጅ አደረጋቸው፤ ባሪያዎቹንም። በፊቴ እለፉ መንጋውንና መንጋውንም አራርቁት አለ።17.የፊተኛውንም እንዲህ ብሎ አዘዘው። ወንድሜ ዔሳው ያገኘህ እንደሆነ። አንተ የማን ነህ? ወዴትስ ትሄዳለህ? በፊትህ ያለው ይህስ የማን ነው? ብሎ የጠየቀህም እንደ ሆነ፥18.በዚያን ጊዜ አንተ። ለጌታዬ ለዔሳው እጅ መንሻ የሰደደው የባሪያህ የያዕቆብ ነው፤ እርሱም ደግሞ እነሆ ከኋላችን ነው በለው።19.እንዲሁም ሁለተኛውንና ሦስተኛውን ከመንጎችም በኋላ የሚሄዱትን ሁሉ እንዲሁ ብሎ አዘዘ። ዔሳውን ባገኛችሁት ጊዜ ይህንኑ ነገር ንገሩት፤20.እንዲህም በሉት። እነሆ ባሪያህ ያዕቆብ ከኋላችን ነው። በፊቴ በሚሄደው እጅ መንሻ እታረቀዋለሁ፤ ከዚያም በኋላ ምናልባት ይራራልኛል ፊቱንም አያለሁ ብሎአልና።21.እጅ መንሻው ከእርሱ ቀድሞ አለፈ፤ እርሱ ግን በዚያች ሌሊት በሰፈር አደረ።22.በዚያች ሌሊትም ተነሣ፥ ሁለቱን ሚስቶቹንና ሁለቱን ባሪያዎቹን አሥራ አንዱንም ልጆቹን ወስዶ የያቦቅን ወንዝ ተሻገረ።23.ወሰዳቸውም ወንዙንም አሻገራቸው፥ ከብቱንም ሁሉ አሻገረ።24.ያዕቆብ ግን ለብቻው ቀረ፤ አንድ ሰውም እስከ ንጋት ድረስ ይታገለው ነበር።25.እንዳላሸነፈውም ባየ ጊዜ የጭኑን ሹልዳ ነካው፤ ያዕቆብም የጭኑ ሹልዳ ሲታገለው ደነዘዘ።26.እንዲህም አለው። ሊነጋ አቀላልቶአልና ልቀቀኝ። እርሱም። ካልባረክኸኝ አልለቅቅህም አለው።27.እንዲህም አለው። ስምህ ማን ነው? እርሱም። ያዕቆብ ነኝ አለው።28.አለውም። ከእንግዲህ ወዲህ ስምህ እስራኤል ይባል እንጂ ያዕቆብ አይባል፤ ከእግዚአብሔር ከሰውም ጋር ታግለህ አሸንፈሃልና።29.ያዕቆብም። ስምህን ንገረኝ ብሎ ጠየቀው። እርሱም። ስሜን ለምን ትጠይቃለህ? አለው። በዚያም ስፍራ ባረከው።30.ያዕቆብም። እግዚአብሔርን ፊት ለፊት አየሁ፥ ሰውነቴም ድና ቀረች ሲል የዚያን ቦታ ስም Dኒኤል ብሎ ጠራው።31.Dኒኤልንም ሲያልፍ ፀሐይ ወጣችበት፥ እርሱም በጭኑ ምክንያት ያነክስ ነበር።32.ስለዚህም የእስራኤል ልጆች እስከ ዛሬ ድረስ የወርችን ሹልዳ አይበሉም፤ የያዕቆብን ጭን ይዞ የወርችን ሹልዳ አደንዝዞአልና። q ቍ@ 30፤ ጵኒኤል የሚለውን ቃል የግእዝ መጽሐፍ ራእየ እግዚአብሔር ይለዋል። a
ምዕራፍ 33
1.ያዕቆብም ዓይኑን አነሣ፥ እነሆም ዔሳውን ሲመጣ አየው፥ ከእርሱም ጋር አራት መቶ ሰዎች ነበሩ፤ ልጆቹንም ከፍሎ ወደ ልያና ወደ ራሔል ወደ ሁለቱም ባሪያዎች አደረጋቸው፤2.ባሪያዎችንና ልጆቻቸውንም በፊት አደረገ፥ ልያንና ልጆችዋንም በኋለኛው ስፍራ፥ ራሔልንና ዮሴፍንም ከሁሉ በኋላ አደረገ።3.እርሱም በፊታቸው አለፈ፤ ወደ ወንድሙም እስኪደርስ ድረስ ወደ ምድር ሰባት ጊዜ ሰገደ።4.ዔሳውም ሊገናኘው ሮጠ፥ አንገቱንም አቅፎ ሳመው፤ ተላቀሱም።5.ዓይኑንም አነሣና ሴቶችንና ልጆችን አየ፥ እንዲህም አለ። እነዚህ ምኖችህ ናቸው? እርሱም። እግዚአብሔር ለእኔ ለባሪያህ የሰጠኝ ልጆች ናቸው አለ።6.ሴቶች ባሪያዎችም ከልጆቻቸው ጋር ቀርበው ሰገዱ፤7.ደግሞም ልያና ልጆችዋ ቀርበው ሰገዱ፤ ከዚያም በኋላ ዮሴፍና ራሔል ቀርበው ሰገዱ።8.እርሱም። ያገኘሁት ይህ ሠራዊት ሁሉ ምንህ ነው? አለ። እርሱም። በጌታዬ ፊት ሞገስን አገኝ ዘንድ ነው አለ።9.ዔሳውም። ለእኔ ብዙ አለኝ፤ ወንድሜ ሆይ፥ የአንተ ለአንተ ይሁን አለ።10.ያዕቆብም አለ። እንደዚህ አይደለም፤ ነገር ግን በፊትህ ሞገስን አግኝቼ እንደ ሆንሁ እጅ መንሻዬን ተቀበለኝ፤ የእግዚአብሔርን ፊት እንደሚያይ ፊትህን አይቼአለሁና፥ በቸርነትም ተቀብለኸኛልና።11.ይህችንም ያመጣሁልህን በረከቴን ተቀበል፤ እግዚአብሔር በቸርነት ሰጥቶኛልና፥ ለእኔም ብዙ አለኝና። እስኪቀበለውም ድረስ ዘበዘበው።12.እርሱም። ተነሣና እንሂድ፥ እኔም በፊትህ እሄዳለሁ አለ።13.እርሱም አለው። ጌታዬ ሆይ፥ ልጆቹ ደካሞች እንደ ሆኑ ታውቃለህ፤ በጎችና ላሞችም ግልገሎቻቸውን ያጠባሉ፤ ሰዎችም አንድ ቀን በችኮላ የነዱአቸው እንደ ሆነ ከብቶቹ ሁሉ ይሞታሉ።14.ጌታዬ ከባሪያው ፊት ቀድሞ ይለፍ፤ እኔም ወደ ሴይር ከጌታዬ ዘንድ እስክደርስ ድረስ ከፊቴ ባሉት በእንስሳቱ እርምጃና በሕፃናቱ እርምጃ መጠን በዝግታ እከተላለሁ።15.ዔሳውም። ከእኔ ጋር ካሉት ሰዎች ከፍዬ ልተውልህን? አለ። እርሱም። ይህ ለምንድር ነው? በጌታዬ ዘንድ ሞገስን ማግኘት ይበቃኛል አለ።16.ዔሳውም በዚያን ቀን ወደ ሴይር መንገዱን ተመለሰ።17.ያዕቆብ ግን ወደ ሱኮት ሄደ፤ በዚያም ለእርሱ ቤትን ሠራ፥ ለከብቶችም ዳሶችን አደረገ፤ ስለዚህም የዚያን ቦታ ስም ሱኮት ብሎ ጠራው።18.ያዕቆብም ከሁለት ወንዞች መካከል በተመለሰ ጊዜ በከነዓን ምድር ወዳለችው ወደ ሴኬም ከተማ በደኅንነት መጣ፤ በከተማይቱም ፊት ሰፈረ።19.ድንኳኑን ተክሎበት የነበረውንም የእርሻውን ክፍል ከሴኬም አባት ከኤሞር ልጆች በመቶ በጎች ገዛው።20.በዚያም መሠውያውን አቆመ፥ ያንም ኤል ኤሎሄ እስራኤል ብሎ ጠራው።
ምዕራፍ 34
1.ለያዕቆብ የወለደችለት የልያ ልጅ ዲናም የዚያን አገር ሴቶች ልጆችን ለማየት ወጣች።2.የአገሩ አለቃ የኤዊያዊ ሰው የኤሞር ልጅ ሴኬም አያት፤ ወሰዳትም ከእርስዋም ጋር ተኛ፥ አስነወራትም።3.ልቡናውም በያዕቆብ ልጅ በዲና ፍቅር ተነደፈ፥ ብላቴናይቱንም ወደዳት፥ ልብዋንም ደስ በሚያሰኛት ነገር ተናገራት።4.ሴኬምም አባቱን ኤሞርን። ይህችን ብላቴና አጋባኝ ብሎ ነገረው።5.ያዕቆብም ልጁን ዲናን እንዳስነወራት ሰማ፤ ልጆቹም ከከብቶቻቸው ጋር በምድረ በዳ ነበሩ፤ ያዕቆብም እስኪመጡ ድረስ ዝም አለ።6.የሴኬም አባት ኤሞርም ይነግረው ዘንድ ወደ ያዕቆብ ወጣ።7.የያዕቆብም ልጆች ይህንን በሰሙ ጊዜ ከምድረ በዳ መጡ፤ የያዕቆብን ልጅ በመተኛቱ በእስራኤል ላይ ስንፍናን ስላደረገ አዘኑ፥ እጅግም ተቈጡ፤ እንዲህ አይደረግምና።8.ኤሞርም እንዲህ ብሎ ነገራቸው። ልጄ ሴኬም በልጃችሁ ፍቅር ልቡ ተነድፎአልና ሚስት እንድትሆነው እባካችሁ እርስዋን ስጡት።9.ጋብቾችም ሁኑን፤ ሴቶች ልጆቻችሁን ስጡን፥ እናንተም የእኛን ሴቶች ልጆች ውሰዱ።10.ከእኛም ጋር ተቀመጡ፥ ምድሪቱም በፊታችሁ ናት፤ ኑሩባት፥ ነግዱም፥ ግዙአትም።11.ሴኬምም አባትዋንና ወንድሞችዋን እንዲህ አለ። በፊታችሁ ሞገስን ባገኝ የምትሉኝን እሰጣለሁ።12.ብዙ ማጫና እጅ መንሻ አምጣ በሉኝ፥ በነገራችሁኝም መጠን እሰጣለሁ፤ ይህችን ብላቴና ግን አጋቡኝ።13.የያዕቆብም ልጆች ለሴኬምና ለአባቱ ለኤሞር በተንኰል መለሱ፥ እኅታቸውን ዲናን አርክሶአታልና፤14.እንዲህም አሉአቸው። እኅታችንን ላልተገረዘ ሰው ለመስጠት ይህንን ነገር እናደርግ ዘንድ አይቻለንም፤ ይህ ነውር ይሆንብናልና።15.እንደ እኛ ሆናችሁ ወንዶቻችሁን ሁሉ ብትገርዙ በዚህ ብቻ እሺ እንላችኋለን፤16.ሴቶች ልጆቻችንን እንሰጣችኋለን፥ የእናንተንም ሴቶች ልጆች እንወስዳለን፤ አንድ ሕዝብም ሆነን ከእናንተ ጋር እንኖራለን።17.ትገረዙ ዘንድ እኛን ባትሰሙ ግን ልጃችንን ይዘን እንሄዳለን።18.ነገራቸውም በኤሞር ልጅ በሴኬምና በኤሞር ዘንድ የተወደደ ሆነ።19.ብላቴናውም ያሉትን ያደርግ ዘንድ አልዘገየም፥ የያዕቆብን ልጅ ወድዶአልና፤ እርሱም በአባቱ ቤት ካሉት ሁሉ የከበረ ነበረ።20.ኤሞርና ሴኬም ልጁም ወደ ከተማቸው አደባባይ ገቡ፥ ለከተማቸውም ሰዎች እንዲህ ብለው ነገሩ።21.እነዚህ ሰዎች በእኛ ዘንድ የሰላም ሰዎች ናቸው፤ በምድራችን ይቀመጡ፥ ይነግዱባትም፥ እነሆም ምድሪቱ ሰፊ ናት፤ ሴቶች ልጆቻቸውን እንውሰድ፥ ለእነርሱም ሴቶች ልጆቻችንን እንስጥ።22.ነገር ግን አንድ ሕዝብ ሆነን ከእኛ ጋር ይቀመጡ ዘንድ በዚህ ነገር ብቻ እሺ ይሉናል፤ እነርሱ እንደ ተገረዙ ወንዶቻችንን ሁሉ ብንገርዝ።23.ከብቶቻቸውም ያላቸውም ሁሉ እንስሶቻቸውም ሁሉ ለእኛ አይደሉምን? በዚህ ነገር ብቻ እሺ ያልናቸው እንደ ሆነ ከእኛ ጋር ይቀመጣሉ።24.ከከተማይቱም አደባባይ የሚወጡ ሁሉ ኤሞርንና ልጁን ሴኬምን እሺ አሉ፤ ከከተማይቱ አደባባይ የሚወጡት ወንዶች ሁሉ ተገረዙ።25.ሦስተኛም ቀን በሆነ ጊዜ እጅግ ቆስለው ሳሉ፥ የዲና ወንድሞች የያዕቆብ ልጆች ስምዖንና ሌዊ እየራሳቸው ሰይፋቸውን ይዘው ሳይፈሩ ወደ ከተማ ገቡ፥ ወንዱንም ሁሉ ገደሉ፤26.ኤሞርንና ልጁን ሴኬምንም በሰይፍ ገደሉ፥ እኅታቸውን ዲናንም ከሴኬም ቤት ይዘው ወጡ።27.የያዕቆብም ልጆች እኅታቸውን ዲናን ሰለ አረከሱአት ወደ ሞቱት ገብተው ከተማይቱን ዘረፉ፤28.በጎቻቸውንም ላሞቻቸውንም አህዮቻቸውንም በውጭም በከተማም ያለውን ወሰዱ።29.ሀብታቸውን ሁሉ ሕፃናቶቻቸውንና ሴቶቻቸውንም ሁሉ ማረኩ፥ በቤት ያለውንም ሁሉ ዘረፉ።30.ያዕቆብም ሌዊንና ስሞዖንን እንዲህ አለ። በዚች አገር በሚኖሩ በከነዓናውያንና በፌርዛውያን ሰዎች የተጠላሁ ታደርጉኝ ዘንድ እኔን አስጨነቃችሁኝ፤ እኔ በቍጥር ጥቂት ነኝ፤ እነርሱ በእኔ ላይ ይሰበሰቡና ይመቱኛል፤ እኔም ከወገኔ ጋር እጠፋለሁ።31.እነርሱም። በጋለሞታ እንደሚደረግ በእኅታችን ያደርግባትን? አሉ። a
መዝሙረ ዳዊት
ምዕራፍ 145
1.አምላኬ ንጉሤ ሆይ፥ ከፍ ከፍ አደርግሃለሁ፥ ስምህንም ለዘላለም ዓለምም እባርካለሁ።2.በየቀኑ ሁሉ እባርክሃለሁ፥ ስምህንም ለዘላለም ዓለምም አመሰግናለሁ።3.እግዚአብሔር ታላቅ ነው እጅግም የተመሰገነ ነው፤ ለታላቅነቱም ፍጻሜ የለውም።4.ትውልደ ትውልድ ሥራህን ያመሰግናሉ፥ ኃይልህንም ያወራሉ።5.የቅድስናህን ግርማ ክብር ይናገራሉ፥ ተኣምራትህንም ይነጋገራሉ።6.የግርማህንም ኃይል ይናገራሉ፥ ታላቅነትህንም ይነጋገራሉ፥ ብርታትህንም ይነጋገራሉ።7.የቸርነትህን ብዛት መታሰብ ያወጣሉ፥ በጽድቅህም ሐሤትን ያደርጋሉ።8.እግዚአብሔር ርኅሩኅና መሓሪ ነው፥ ከቍጣ የራቀ፥ ምሕረቱም ብዙ ነው፤9.እግዚአብሔር ለሚታገሡት ቸር ነው። ምሕረቱም በሥራው ሁሉ ላይ ነው።10.አቤቱ፥ ሥራህ ሁሉ ያመሰግኑሃል፥ ቅዱሳንህም ይባርኩሃል።11.የመንግሥትህን ክብር ይናገራሉ፥ ኃይልህንም ይነጋገራሉ፥12.ለሰው ልጆች ኃይልህን የመንግሥትህንም ግርማ ክብር ያስታውቁ ዘንድ13.መንግሥትህ የዘላለም መንግሥት ናት፥ ግዛትህም ለልጅ ልጅ ነው።14.እግዚአብሔር በቃሎቹ የታመነ ነው፥ በሥራውም ሁሉ ጻድቅ ነው፤ እግዚአብሔር የተፍገመገሙትን ሁሉ ይደግፋቸዋል፥ የወደቁትንም ያነሣቸዋል።15.የሁሉ ዓይን አንተን ተስፋ ያደርጋል፤ አንተም ምግባቸውን በየጊዜው ትሰጣቸዋለህ።16.አንተ እጅህን ትከፍታለህ፥ ሕይወት ላለውም ሁሉ መልካምን ታጠግባለህ።17.እግዚአብሔር በመንገዱ ሁሉ ጻድቅ ነው በሥራውም ሁሉ ቸር ነው።18.እግዚአብሔር ለሚጠሩት ሁሉ፥ በእውነት ለሚጠሩት ሁሉ ቅርብ ነው።19.ለሚፈሩት ምኞታቸውን ያደርጋል፥ ልመናቸውንም ይሰማል ያድናቸዋልም።20.እግዚአብሔር የሚወድዱትን ሁሉ ይጠብቃል፤ ኃጢአተኞችንም ሁሉ ያጠፋል።21.አፌ የእግዚአብሔርን ምስጋና ይናገራል፤ ሥጋም ሁሉ ለዘላለም ዓለም የተቀደሰውን ስሙን ይባርክ።
የማርቆስ ወንጌል
ምዕራፍ 13
1.እርሱም ከመቅደስ ሲወጣ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ። መምህር ሆይ፥ እንዴት ያሉ ድንጋይዎችና እንዴት ያሉ ሕንጻዎች እንደ ሆኑ እይ አለው።2.ኢየሱስም መልሶ። እነዚህን ታላላቅ ሕንጻዎች ታያለህን? ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም አለው።3.በመቅደስም ትይዩ በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ፥ ጴጥሮስና ያዕቆብ ዮሐንስም እንድርያስም።4.ንገረን፥ ይህ መቼ ይሆናል? ይህስ ሁሉ ይፈጸም ዘንድ እንዳለው ምልክቱ ምንድር ነው? ብለው ለብቻቸው ጠየቁት።5.ኢየሱስም መልሶ እንዲህ ይላቸው ጀመር። ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ።6.ብዙዎች። እኔ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና፥ ብዙዎችንም ያስታሉ።7.ጦርንም የጦርንም ወሬ በሰማችሁ ጊዜ አትደንግጡ፤ ይህ ሊሆን ግድ ነውና፥ ነገር ግን መጨረሻው ገና ነው።8.ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣልና፤ በልዩ ልዩ ስፍራ የምድር መናወጥ ይሆናል፤ ራብ ይሆናል፤ እነዚህ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው።9.እናንተ ግን ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ ወደ ሸንጎ አሳልፈው ይሰጡአችኋል በምኵራብም ትገረፋላችሁ ምስክርም ይሆንባቸው ዘንድ ስለ እኔ በገዥዎችና በነገሥታት ፊት ትቆማላችሁ።10.አስቀድሞም ወንጌል ለአሕዛብ ሁሉ ይሰበክ ዘንድ ይገባል።11.ሲጐትቱአችሁና አሳልፈው ሲሰጡአችሁም ምን እንድትናገሩ አስቀድማችሁ አትጨነቁ፥ ዳሩ ግን በዚያች ሰዓት የሚሰጣችሁን ተናገሩ፤ የሚነግረው መንፈስ ቅዱስ ነው እንጂ እናንተ አይደላችሁምና።12.ወንድምም ወንድሙን አባትም ልጁን ለሞት አሳልፎ ይሰጣል፥ ልጆችም በወላጆቻቸው ላይ ይነሣሉ። ይገድሉአቸውማል፤13.በሁሉም ዘንድ ስለ ስሜ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፤ እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል።14.ነገር ግን በነቢዩ በዳንኤል የተባለውን የጥፋት ርኵሰት በማይገባው ስፍራ ቆሞ ብታዩ፥ አንባቢው ያስተውል፥ በዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራሮች ይሽሹ፥15.በሰገነትም ያለ ወደ ቤት አይውረድ ከቤቱም አንዳች ይወስድ ዘንድ አይግባ፥16.በእርሻም ያለ ልብሱን ይወስድ ዘንድ ወደ ኋላው አይመለስ።17.በዚያን ወራትም ለርጉዞችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው።18.ነገር ግን ሽሽታችሁ በክረምት እንዳይሆን ጸልዩ፤19.በዚያን ወራት እግዚአብሔር ከፈጠረው ከፍጥረት መጀመሪያ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ያልሆነ ደግሞም የማይሆን የመከራ ዓይነት ይሆናልና።20.ጌታስ ወራቶቹን ባያሳጥር፥ ሥጋ የለበሰ ሁሉ ባልዳነም፤ ነገር ግን ስለ መረጣቸው ምርጦች ወራቶቹን አሳጠረ።21.በዚያን ጊዜም ማንም። እነሆ፥ ክርስቶስ ከዚህ አለ፥ ወይም። እነሆ፥ ከዚያ አለ ቢላችሁ አትመኑ፤22.ሐሰተኞች ክርስቶሶችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉና፥ ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳ ያስቱ ዘንድ ምልክትና ድንቅ ያደርጋሉ።23.እናንተ ግን ተጠንቀቁ፤ እነሆ፥ አስቀድሜ ሁሉን ነገርኋችሁ።24.በዚያን ወራት ግን ከዚያ መከራ በኋላ ፀሐይ ይጨልማል ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም፥25.ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፥ የሰማያትም ኃይላት ይናወጣሉ።26.በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ በብዙ ኃይልና ክብር በደመና ሲመጣ ያዩታል።27.በዚያን ጊዜም መላእክትን ይልካል ከአራቱ ነፋሳትም ከምድር ዳርቻ እስከ ሰማይ ዳርቻ የተመረጡትን ይሰበስባቸዋል።28.ምሳሌውንም ከበለስ ተማሩ፤ ጫፍዋ ሲለሰልስ ቅጠልዋም ሲያቈጠቍጥ፥ ያን ጊዜ በጋ እንደ ቀረበ ታውቃላችሁ፤29.እንዲሁ ደግሞ እናንተ ይህን ሁሉ መሆኑን ስታዩ ቀርቦ በደጅ እንደ ሆነ እወቁ።30.እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም።31.ሰማይና ምድር ያልፋሉ ቃሌ ግን አያልፍም።32.ስለዚያች ቀን ወይም ስለዚያች ሰዓት ግን የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም ቢሆን ከአባት በቀር የሚያውቅ የለም።33.ጊዜው መቼ እንዲሆን አታውቁምና ተጠንቀቁ፤ ትጉ፤ ጸልዩም።34.ቤቱን ትቶ ወደ ሌላ አገር እንደ ሄደ ሰው ነው፥ ለባሮቹም ሥልጣን ለእያንዳንዱም ሥራውን ሰጥቶ በረኛውን እንዲተጋ አዘዘ።35.እንግዲህ በማታ ቢሆን ወይም በእኩለ ሌሊት ወይም ዶሮ ሲጮኽ ወይም በማለዳ ቢሆን ባለቤቱ መቼ እንዲመጣ አታውቁምና36.ድንገት መጥቶ ተኝታችሁ እንዳያገኛችሁ ስለዚህ ትጉ።37.ለእናንተም የምነግራችሁ ለሁሉ እላለሁ፤ ትጉ።