ሳምንት 4 · ቀን 19 (ሐሙስ)
📅 Meskerem 28, 2019
ኦሪት ዘፍጥረት 47, 48 · መዝሙረ ዳዊት 25 · ወደ ገላትያ ሰዎች 3
ኦሪት ዘፍጥረት
ምዕራፍ 47
1.ዮሴፍም ገባ ለፈርዖንም ነገረው እንዲህ ብሎ። አባቴና ወንድሞቼ በጎቻቸውም ላሞቻቸውም ያላቸውም ሁሉ ከከነዓን ምድር ወጡ፤ እነርሱም እነሆ በጌሤም ምድር ናቸው።
2.ከወንድሞቹም አምስት ሰዎችን ወስዶ በፈርዖን ፊት አቆማቸው።
3.ፈርዖንም ወንድሞቹን። ሥራችሁ ምንድር ነው? አላቸው። እነርሱም ፈርዖንን። እኛ ባሪያዎችህ፥ እኛም አባቶቻችንም፥ በግ አርቢዎች ነን አሉት።
4.ፈርዖንንም እንዲህ አሉት። በምድር ልንቀመጥ በእንግድነት መጣን፥ የባርያዎችህ በጎች የሚሰማሩበት ስፍራ የለምና፤ ራብ በከነዓን ምድር እጅግ ጸንቶአልና፤ አሁንም ባሪያዎችህ በጌሤም ምድር እንድንቀመጥ እንለምንሃለን።
5.ፈርዖንም ዮሴፍን ተናገረው እንዲህ ብሎ። አባትህና ወንድሞችህ መጥተውልሃል፤
6.የግብፅ ምድር በፊትህ ናት፤ በመልካሙ ምድር አባትህንና ወንድሞችህን አኑራቸው፤ በጌሤም ምድር ይኑሩ፤ ከእነርሱም ውስጥ እውቀት ያላቸውን ሰዎች ታውቅ እንደ ሆነ በእንስሶቼ ላይ አለቆች አድርጋቸው።
7.ዮሴፍም ያዕቆብን አባቱን አስገብቶ በፈርዖን ፊት አቆመው፤ ያዕቆብም ፈርዖንን ባረከው።
8.ፈርዖንም ያዕቆብን። የዕድሜህ ዘመን ስንት ዓመት ነው? አለው።
9.ያዕቆብም ለፈርዖን አለው። የእንግድነቴ ዘመን መቶ ሠላሳ ዓመት ነው፤ የሕይወቴ ዘመኖች ጥቂትም ክፉም ሆኑብኝ፥ አባቶቼ በእንግድነት የተቀመጡበትንም ዘመን አያህሉም።
10.ያዕቆብም ፈርዖንን ባረከው ከፈርዖንም ፊት ወጣ።
11.ዮሴፍም አባቱንና ወንድሞቹን አኖረ፥ ፈርዖን እንዳዘዘም በግብፅ ምድር በተሻለችው በራምሴ ምድር ጉልትን ሰጣቸው።
12.ዮሴፍም ለአባቱና ለወንድሞቹ ለአባቱም ቤተ ሰዎች ሁሉ እንደ ልጆቻቸው መጠን እህል ሰጣቸው።
13.በምድርም ሁሉ እህል አልነበረም፥ ራብ እጅግ ጸንቶአልና፤ ከራብም የተነሣ የግብፅ ምድርና የከነዓን ምድር ተጎዳ።
14.ዮሴፍም ከግብፅ ምድርና ከከነዓን ምድር በእህል ሸመት የተገኘውን ብሩን ሁሉ አከማቸ፤ ዮሴፍም ብሩን ወደ ፈርዖን ቤት አስገባው።
15.ብሩም በግብፅ ምድርና በከነዓን ምድር አለቀ፤ የግብፅ ሰዎችም ሁሉ ወደ ዮሴፍ መጡ እንዲህ ሲሉ። እንጀራ ስጠን፤ ስለ ምን በፊትህ እንሞታለን? ብሩ አልቆብናልና።
16.ዮሴፍም። ከብቶቻችሁን አምጡልኝ፤ ብር ካለቀባችሁ በከብቶቻችሁ ፋንታ እህል እሰጣችኋለሁ አለ።
17.ከብቶቻቸውንም ወደ ዮሴፍ አመጡ፥ ዮሴፍም በፈረሶቻቸው በበጎቻቸውም በላሞቻቸውም በአህዮቻቸውም ፋንታ እህልን ሰጣቸው፤ በዚያች ዓመትም ስለ ከብቶቻቸው ሁሉ ፋንታ እህልን መገባቸው።
18.ዓመቱም ተፈጸመ፤ በሁለተኛውም ዓመት ወደ እርሱ መጥተው እንዲህ አሉት። እኛ ከጌታችን አንሰውርም፤ ብሩ በፍጹም አለቀ፥ ከብታችንም ከጌታችን ጋር ነው፤ ከሰውነታችንና ከምድራችን በቀር በጌታችን ፊት አንዳች የቀረ የለም፤
19.እኛ በፊትህ ስለ ምን እንሞታለን? ምድራችንስ ስለ ምን ትጠፋለች? እኛንም ምድራችንንም በእህል ግዛን፥ እኛም ለፈርዖን ባሪያዎች እንሁን፥ ምድራችንም ለእርሱ ትሁን፤ እኛ እንድንድን እንዳንሞትም ምድራችንም እንዳትጠፋ ዘር ስጠን።
20.ዮሴፍም የግብፅን ምድር ሁሉ ለፈርዖን ገዛ፥ የግብፅ ሰዎች ሁሉ ራብ ስለ ጸናባቸው ርስታቸውን ሸጠዋልና፤ ምድሪቱ ለፈርዖን ሆነች።
21.ሕዝቡንም ሁሉ ከግብፅ ዳርቻ አንሥቶ እስከ ሌላው ዳርቻዋ ድረስ ባሪያዎች አደረጋቸው።
22.የካህናትን ምድር ብቻ አልገዛም፥ ካህናቱ ከፈርዖን ዘንድ ድርጎ ያገኙ ነበርና፥ ፈርዖንም የሰጣቸውን ድርጎ ይበሉ ነበር፤ ስለዚህም ምድራቸውን አልሸጡም።
23.ዮሴፍም ሕዝቡን እንዲህ አለ። እነሆ ዛሬ እናንተንና ምድራችሁን ለፈርዖን ገዝቻችኋለሁ፤ ዘር ውሰዱና ምድሪቱን ዝሩ፤
24.በመከርም ጊዜ ፍሬውን ከአምስት እጅ አንዱን እጅ ለፈርዖን ስጡ፤ አራቱም እጅ ለእናንተ ለራሳችሁ፥ ለእርሻው ዘርና ለእናንተ ምግብ፥ ለቤተ ሰዋችሁና ለሕፃናቶቻችሁም ሲሳይ ይሁን።
25.እነርሱም። አንተ አዳነኸን፤ በጌታችን ፊት ሞገስን አናግኝ፥ ለፈርዖንም ባሪያዎች እንሆናለን አሉት።
26.ዮሴፍም ለፈርዖን ካልሆነችው ከካህናቱ ምድር በቀር አምስተኛው እጅ ለፈርዖን እንዲሆን በግብፅ ምድር እስከ ዛሬ ድረስ ሕግ አደረጋት።
27.እስራኤልም በግብፅ ምድር በጌሤም አገር ተቀመጠ፤ ገዙአትም፥ ረቡ፥ እጅግም በዙ።
28.ያዕቆብም በግብፅ ምድር አሥራ ሰባት ዓመት ተቀመጠ፤ የያዕቆብም ሙላው የሕይወቱ ዘመን መቶ አርባ ሰባት ዓመት ነው።
29.የእስራኤልም የሞቱ ቀን ቀረበ፤ ልጁን ዮሴፍንም ጠርቶ እንዲህ አለው። በፊትህ ሞገስን አግኝቼ እንደ ሆንሁ እጅህን ከጭኔ በታች አድርግ፥ በግብፅ ምድርም እንዳትቀብረኝ ምሕረትንና እውነትን አድርግልኝ፤
30.ከአባቶቼም ጋር በተኛሁ ጊዜ ከግብፅ ምድር አውጥተህ ትወስደኛለህ፥ በመቃብራቸውም ትቀብረኛለህ። እርሱም። እንደ ቃልህ አደርጋለሁ አለ።
31.እርሱም። ማልልኝ አለው። ዮሴፍም ማለለት፤ እስራኤልም በአልጋው ራስ ላይ ሰገደ።
ምዕራፍ 48
1.ከዚህም ነገር በኋላ እንዲህ ሆነ፤ እነሆ አባትህ ታምሞአል ብለው ለዮሴፍ ነገሩት፤ እርሱም ሁለቱን ልጆቹን ምናሴንና ኤፍሬምን ይዞ ሄደ።
2.ለያዕቆብም። እነሆ ልጅህ ዮሴፍ መጥቶልሃል ብለው ነገሩት፤ እስራኤልም ተጠነካከረ፥ በአልጋውም ላይ ተቀመጠ።
3.ያዕቆብ ዮሴፍን አለው። ሁሉን የሚችል አምላክ በከነዓን ምድር በሎዛ ተገለጠልኝ፥ ባረከኝም
4.እንዲህም አለኝ። እነሆ ፍሬያማ አደርግሃለሁ፥ አበዛሃለሁም፥ ለብዙም ሕዝብ ጉባኤ አደርግሃለሁ፤ ይህችንም ምድር ከአንተ በኋላ ለዘላለም ርስት ለዘርህ እሰጣታለሁ።
5.አሁንም እኔ ወደ አንተ ከመምጣቴ በፊት በግብፅ ምድር የተወለዱልህ ሁለቱ ልጆችህ ለእኔ ይሁኑ፤ ኤፍሬምና ምናሴ ለእኔ እንደ ሮቤልና እንደ ስምዖን ናቸው።
6.ከእነርሱም በኋላ የምትወልዳቸው ልጆች ለአንተ ይሁኑ፤ በርስታቸው በወንድሞቻቸው ስም ይጠሩ።
7.እኔም ከመስጴጦምያ በመጣሁ ጊዜ፥ ወደ ኤፍራታ ለመግባት ጥቂት ቀርቶኝ በመንገድ ሳለሁ፥ ራሔል በከነዓን ምድር ሞተችብኝ፤ በዚያም በኤፍራታ መንገድ ላይ፥ እርስዋም ቤተ ልሔም ናት፥ ቀበርኋት።
8.እስራኤልም የዮሴፍን ልጆች አይቶ። እነዚህ እነማን ናቸው? አለው።
9.ዮሴፍም ለአባቱ። እግዚአብሔር በዚህ የሰጠኝ ልጆቼ ናቸው አለ። እርሱም። እባርካቸው ዘንድ ወደዚህ አቅርብልኝ አለ።
10.የእስራኤልም ዓይኖች ከሽምግልና የተነሣ ከብደው ነበር፥ ማየትም አይችልም ነበር፤ ወደ እርሱም አቀረባቸው፥ ሳማቸውም፥ አቀፋቸውም።
11.እስራኤልም ዮሴፍን። ፊትህን አያለሁ ብዬ አላሰብሁም ነበር፤ እነሆም እግዚአብሔር ዘርህን ደግሞ አሳየኝ አለው።
12.ዮሴፍም ከጕልበቱ ፈቀቅ አደረጋቸው፥ ወደ ምድርም በግምባሩ ሰገደ።
13.ዮሴፍም ሁለቱን ልጆቹን ወሰደ፥ ኤፍሬምንም በቀኙ በእስራኤል ግራ፥ ምናሴንም በግራው በእስራኤል ቀኝ አደረገው፥ ወደ እርሱም አቀረባቸው።
14.እስራኤልም ቀኝ እጁን ዘርግቶ በኤፍሬም ራስ ላይ አኖረው፥ እርሱም ታናሽ ነበረ፥ ግራውንም በምናሴ ራስ ላይ አኖረ፤ እጆቹንም አስተላለፈ፥ ምናሴ በኵር ነበርና።
15.ያዕቆብም ዮሴፍን ባረከ እንዲህም አለ። አባቶቼ አብርሃምና ይስሐቅ በፊቱ የሄዱለት እርሱ እግዚአብሔር፥ ከታናሽነቴ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ እኔን የመገበኝ እግዚአብሔር፥
16.ከክፉ ነገር ሁሉ ያዳነኝ መልአክ፥ እርሱ እነዚህን ብላቴኖች ይባርክ፤ ስሜም የአባቶቼ የአብርሃምና የይስሐቅም ስም በእነርሱ ይጠራ፤ በምድርም መካከል ይብዙ።
17.ዮሴፍም አባቱ ቀኝ እጁን በኤፍሬም ራስ ላይ ጭኖ ባየ ጊዜ አሳዘነው፤ የአባቱንም እጅ በምናሴ ራስ ላይ ይጭነው ዘንድ ከኤፍሬም ራስ ላይ አነሣው።
18.ዮሴፍም አባቱን። አባቴ ሆይ እንዲህ አይደለም፥ በኵሩ ይህ ነውና፤ ቀኝህን በራሱ ላይ አድርግ አለው።
19.አባቱም እንቢ አለ እንዲህ ሲል። አወቅሁ ልጄ ሆይ፥ አወቅሁ፤ ይህም ደግሞ ሕዝብ ይሆናል ታላቅም ይሆናል፤ ነገር ግን ታናሽ ወንድሙ ከእርሱ ይበልጣል፥ ዘሩም የአሕዛብ ሙላት ይሆናል።
20.በዚያም ቀን እንዲህ ብሎ ባረካቸው። በእናንተ እስራኤል እንዲህ ብሎ ይባርካል። እግዚአብሔር እንደ ኤፍሬምና እንደ ምናሴ ያድርግህ። ኤፍሬምንም ከምናሴ ፊት አደረገው።
21.እስራኤልም ዮሴፍን። እነሆ እኔ እሞታለሁ፤ እግዚአብሔርም ከእናንተ ጋር ይሆናል፥ ወደ አባቶቻችሁም ምድር ይመልሳችኋል፤
22.እኔም ከአሞራውያን በሰይፌና በቀስቴ የወሰድሁትን ለአንተ ከወንድሞችህ አንድ እጅ አብልጬ ሰጠሁህ አለው።
መዝሙረ ዳዊት
ምዕራፍ 25
1.የዳዊት መዝሙር።
አቤቱ፥ ወደ አንተ ነፍሴን አነሣለሁ። 2.አምላኬ፥ አንተን ታመንሁ፤ አልፈር፥ ጠላቶቼ በእኔ አይሣቁብኝ። 3.አንተን ተስፋ የሚያደርጉ አያፍሩም፤ በከንቱ የሚገበዙ ያፍራሉ። 4.አቤቱ፥ መንገድህን አመልክተኝ፥ ፍለጋህንም አስተምረኝ። 5.አንተ የመድኃኒቴ አምላክ ነህና በእውነትህ ምራኝ፥ አስተምረኝም፤ ቀኑን ሁሉ አንተን ተስፋ አድርጌአለሁ። 6.አቤቱ፥ ምሕረትህንና ቸርነትህን አስብ፥ ከጥንት ጀምሮ ናቸውና። 7.የልጅነቴን ኃጢአትና መተላለፍ አታስብብኝ፤ አቤቱ፥ ስለ ቸርነትህ ብዛት እንደ ምሕረትህ አስበኝ። 8.እግዚአብሔር ቸር ቅንም ነው፤ ስለዚህ ኃጢአተኞችን በመንገድ ይመራቸዋል። 9.ገሮችን በፍርድ ይመራል፥ ለገሮችም መንገድን ያስተምራቸዋል። 10.የእግዚአብሔር መንገድ ሁሉ ቸርነትና እውነት ነው። ቃል ኪዳኑንና ምስክሩን ለሚጠብቁ። 11.አቤቱ፥ ኃጢአቴ እጅግ ነውና ስለ ስምህ ይቅር በለኝ። 12.እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው ማን ነው? በሚመርጠው መንገድ ያስተምረዋል። 13.ነፍሱ በመልካም ታድራለች፥ ዘሩም ምድርን ይወርሳል። 14.እግዚአብሔር ለሚፈሩት ኃይላቸው ነው፥ ቃል ኪዳኑንም ያስታውቃቸዋል። 15.እርሱ እግሮቼን ከወጥመድ ያወጣቸዋልና ዓይኖቼ ሁልጊዜ ወደ እግዚአብሔር ናቸው። 16.እኔ ብቻዬንና ችግረኛ ነኝና ፊትህን ወደ እኔ አድርግ ማረኝም። 17.የልቤ ችግር ብዙ ነው፤ ከጭንቀቴ አውጣኝ። 18.ድካሜንና መከራዬን እይ፥ ኃጢአቴንም ሁሉ ይቅር በለኝ። 19.ጠላቶቼ እንደ በዙ እይ፥ የግፍም ጥል ጠልተውኛል። 20.ነፍሴን ጠብቅና አድነኝ፤ አንተን ታምኛለሁና አልፈር። 21.አንተን ተስፋ አድርጌአለሁና የውሃትና ቅንነት ይጠብቁኝ። 22.አቤቱ፥ እስራኤልን ከመከራው ሁሉ አድነው።
አቤቱ፥ ወደ አንተ ነፍሴን አነሣለሁ። 2.አምላኬ፥ አንተን ታመንሁ፤ አልፈር፥ ጠላቶቼ በእኔ አይሣቁብኝ። 3.አንተን ተስፋ የሚያደርጉ አያፍሩም፤ በከንቱ የሚገበዙ ያፍራሉ። 4.አቤቱ፥ መንገድህን አመልክተኝ፥ ፍለጋህንም አስተምረኝ። 5.አንተ የመድኃኒቴ አምላክ ነህና በእውነትህ ምራኝ፥ አስተምረኝም፤ ቀኑን ሁሉ አንተን ተስፋ አድርጌአለሁ። 6.አቤቱ፥ ምሕረትህንና ቸርነትህን አስብ፥ ከጥንት ጀምሮ ናቸውና። 7.የልጅነቴን ኃጢአትና መተላለፍ አታስብብኝ፤ አቤቱ፥ ስለ ቸርነትህ ብዛት እንደ ምሕረትህ አስበኝ። 8.እግዚአብሔር ቸር ቅንም ነው፤ ስለዚህ ኃጢአተኞችን በመንገድ ይመራቸዋል። 9.ገሮችን በፍርድ ይመራል፥ ለገሮችም መንገድን ያስተምራቸዋል። 10.የእግዚአብሔር መንገድ ሁሉ ቸርነትና እውነት ነው። ቃል ኪዳኑንና ምስክሩን ለሚጠብቁ። 11.አቤቱ፥ ኃጢአቴ እጅግ ነውና ስለ ስምህ ይቅር በለኝ። 12.እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው ማን ነው? በሚመርጠው መንገድ ያስተምረዋል። 13.ነፍሱ በመልካም ታድራለች፥ ዘሩም ምድርን ይወርሳል። 14.እግዚአብሔር ለሚፈሩት ኃይላቸው ነው፥ ቃል ኪዳኑንም ያስታውቃቸዋል። 15.እርሱ እግሮቼን ከወጥመድ ያወጣቸዋልና ዓይኖቼ ሁልጊዜ ወደ እግዚአብሔር ናቸው። 16.እኔ ብቻዬንና ችግረኛ ነኝና ፊትህን ወደ እኔ አድርግ ማረኝም። 17.የልቤ ችግር ብዙ ነው፤ ከጭንቀቴ አውጣኝ። 18.ድካሜንና መከራዬን እይ፥ ኃጢአቴንም ሁሉ ይቅር በለኝ። 19.ጠላቶቼ እንደ በዙ እይ፥ የግፍም ጥል ጠልተውኛል። 20.ነፍሴን ጠብቅና አድነኝ፤ አንተን ታምኛለሁና አልፈር። 21.አንተን ተስፋ አድርጌአለሁና የውሃትና ቅንነት ይጠብቁኝ። 22.አቤቱ፥ እስራኤልን ከመከራው ሁሉ አድነው።
ወደ ገላትያ ሰዎች
ምዕራፍ 3
1.የማታስተውሉ የገላትያ ሰዎች ሆይ፥ በዓይናችሁ ፊት ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ተሰቀለ ሆኖ ተሥሎ ነበር፤ ለእውነት እንዳትታዘዙ አዚም ያደረገባችሁ ማን ነው?
2.ይህን ብቻ ከእናንተ እንድማር እወዳለሁ፤ በሕግ ሥራ ወይም ከእምነት ጋር በሆነ መስማት መንፈስን ተቀበላችሁን?
3.እንዲህን የማታስተውሉ ናችሁ? በመንፈስ ጀምራችሁ አሁን በሥጋ ትፈጽማላችሁን?
4.በውኑ ከንቱ እንደ ሆነስ እንደዚህ ያለ መከራ በከንቱ ተቀበላችሁን?
5.እንግዲህ መንፈስን የሚሰጣችሁ በእናንተም ዘንድ ተአምራት የሚያደርግ፥ በሕግ ሥራ ነውን ወይስ ከእምነት ጋር በሆነ መስማት ነው?
6.እንዲሁ አብርሃም በእግዚአብሔር አመነና ጽድቅ ሆኖ ተቆጠረለት።
7.እንኪያስ ከእምነት የሆኑት እነዚህ የአብርሃም ልጆች እንደ ሆኑ እወቁ።
8.መጽሐፍም እግዚአብሔር አሕዛብን በእምነት እንዲያጸድቅ አስቀድሞ አይቶ። በአንተ አሕዛብ ሁሉ ይባረካሉ ብሎ ወንጌልን ለአብርሃም አስቀድሞ ሰበከ።
9.እንደዚህ ከእምነት የሆኑት ካመነው ከአብርሃም ጋር ይባረካሉ።
10.ከሕግ ሥራ የሆኑት ሁሉ በእርግማን በታች ናቸውና፤ በሕግ መጽሐፍ በተጻፉት ሁሉ ጸንቶ የማይኖር የማያደርግም ሁሉ የተረገመ ነው ተብሎ ተጽፎአልና።
11.ጻድቅ በእምነት ይኖራል ተብሎአልና ማንም በእግዚአብሔር ፊት በሕግ እንዳይጸድቅ ግልጥ ነው።
12.ሕግም ከእምነት አይደለም ነገር ግን። የሚያደርገው ይኖርበታል ተብሎአል።
13.በእንጨት የሚሰቀል ሁሉ የተረገመ ነው ተብሎ ተጽፎአልና ክርስቶስ ስለ እኛ እርግማን ሆኖ ከሕግ እርግማን ዋጀን፤
14.የመንፈስን ተስፋ በእምነት እንድንቀበል፥ የአብርሃም በረከት ወደ አሕዛብ በኢየሱስ ክርስቶስ ይደርስላቸው ዘንድ።
15.ወንድሞች ሆይ፥ እንደ ሰው ልማድ እላለሁ። የሰው ስንኳ ቢሆን እርግጠኛውን ኪዳን ማንም አይንቅም ወይም አይጨምርበትም።
16.ለአብርሃምና ለዘሩም የተስፋው ቃል ተነገረ። ስለ ብዙዎች እንደሚነገር። ለዘሮቹም አይልም፤ ስለ አንድ እንደሚነገር ግን። ለዘርህም ይላል፥ እርሱም ክርስቶስ።
17.ይህንም እላለሁ፤ ከአራት መቶ ሠላሳ ዓመት በኋላ የተሰጠው ሕግ አስቀድሞ በእግዚአብሔር የተረጋገጠውን ኪዳን የተስፋውን ቃል እስኪሽር ድረስ አያፈርስም።
18.ርስቱ በሕግ ቢሆንስ እንግዲያስ በተስፋ ቃል አይሆንም፤ በተስፋ ቃል ግን እግዚአብሔር ለአብርሃም ሰጥቶአል።
19.እንግዲህ ሕግ ምንድር ነው? ተስፋው የተሰጠው ዘር እስኪመጣ ድረስ በመካከለኛ እጅ በመላእክት በኩል ስለ ሕግ መተላለፍ ተጨመረ።
20.መካከለኛውም ለአንድ ብቻ አይደለም እግዚአብሔር ግን አንድ ነው።
21.እንግዲህ ሕግ የእግዚአብሔርን የተስፋ ቃል የሚቃወም ነውን? አይደለም። ሕያው ሊያደርግ የሚቻለው ሕግ ተሰጥቶ ቢሆንስ በእውነት ጽድቅ ከሕግ በሆነ ነበር፤
22.ነገር ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ከማመን የሆነው የተስፋ ቃል ለሚያምኑ ይሰጥ ዘንድ መጽሐፍ ከኃጢአት በታች ሁሉን ዘግቶታል።
23.እምነትም ሳይመጣ ሊገለጥ ላለው እምነት ተዘግተን ከሕግ በታች እንጠበቅ ነበር።
24.እንደዚህ በእምነት እንጸድቅ ዘንድ ሕግ ወደ ክርስቶስ የሚያመጣ ሞግዚታችን ሆኖአል፤
25.እምነት ግን መጥቶአልና ከእንግዲህ ወዲህ ከሞግዚት በታች አይደለንም።
26.በእምነት በኩል ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁና፤
27.ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋልና።
28.አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፥ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፥ ወንድም ሴትም የለም፤ ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና።
29.እናንተም የክርስቶስ ከሆናችሁ እንኪያስ የአብርሃም ዘር እንደ ተስፋውም ቃል ወራሾች ናችሁ።