Skip to Content
የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን | YEHIWOT MELHEK BETEKIRSTIAN
የ2019 ዓ.ም የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ 📖 ዛሬን አንብብ →

የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን

Yehiwot Melhek Betekirstian

ሳምንት 3 · ቀን 14 (ሐሙስ) 📅 Meskerem 21, 2019

ኦሪት ዘፍጥረት 35, 36, 37 · መዝሙረ ዳዊት 12 · የማርቆስ ወንጌል 14

📖 የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም፦ 1954 መጽሐፍ ቅዱስ አዲሱ መደበኛ ትርጒም

ኦሪት ዘፍጥረት

ምዕራፍ 35

1.እግዚአብሔርም ያዕቆብን አለው። ተነሥተህ ወደ ቤቴል ውጣ፥ በዚያም ኑር፤ ከወንድምህ ከዔሳው ፊት በሸሸህ ጊዜ ለተገለጠልህ ለእግዚአብሔርም መሠውያውን አድርግ።2.ያዕቆብም ለቤተ ሰቡና ከእርሱ ጋር ላሉት ሁሉ እንዲህ አለ። እንግዶቹን አማልክት ከመካከላችሁ አስወግዱ፥ ንጹሐንም ሁኑ፥ ልብሳችሁንም ለውጡ፤3.ተነሥተንም ወደ ቤቴል እንውጣ፤ በዚያም በመከራዬ ጊዜ ለሰማኝ፥ በሄድሁበትም መንገድ ከእኔ ጋር ለነበረው ለእግዚአብሔር መሠውያን አደርጋለሁ።4.በእጃቸው ያሉትንም እንግዶችን አማልክት ሁሉ በጆሮአቸውም ያሉትን ጕትቾች ለያዕቆብ ሰጡት፤ ያዕቆብም በሴኬም አጠገብ ካለችው የአድባር ዛፍ በታች ቀበራቸው።5.ተነሥተውም ሄዱ፤ የእግዚአብሔርም ፍርሃት በዙሪያቸው ባሉት ከተሞች ሁሉ ወደቀ፥ የያዕቆብንም ልጆች ለማሳደድ አልተከተሉአቸውም።6.ያዕቆብም፥ እርሱ ከእርሱ ጋርም የነበሩት ሰዎች ሁሉ፥ በከነዓን ምድር ወዳለችው ወደ ሎዛ መጡ፤ እርስዋም ቤቴል ናት።7.በዚያም መሰውያውን ሠራ፥ የዚያንም ቦታ ስም ኤልቤቴል ብሎ ጠራው፤ እርሱ ከወንድሙ ፊት በሸሸበት ጊዜ እግዚአብሔር በዚያ ተገልጦለት ነበርና።8.የርብቃ ሞግዚት ዲቦራም ሞተች፥ በቤቴልም ከአድባር ዛፍ በታች ተቀበረች፤ ስሙም አሎንባኩት ተብሎ ተጠራ።9.እግዚአብሔርም ለያዕቆብ ከሁለት ወንዞች መካከል ከሶርያ ከተመለሰ በኋላ እንደ ገና ተገለጠለት፥ ባረከውም።10.እግዚአብሔርም። ስምህ ያዕቆብ ነው፤ ከእንግዲህም ወዲህ ስምህ ያዕቆብ ተብሎ አይጠራ፥ ስምህ እስራኤል ይባል እንጂ አለ፤ ስሙንም እስራኤል ብሎ ጠራው።11.እግዚአብሔርም አለው። ሁሉን ቻይ አምላክ እኔ ነኝ፤ ብዛ፥ ተባዛም፤ ሕዝብና የአሕዛብ ማኅበር ከአንተ ይሆናል፥ ነገሥታትም ከጕልበትህ ይወጣሉ።12.ለአብርሃምና ለይስሐቅም የሰጠኋትን ምድር ለአንተ እሰጣለሁ፥ ከአንተም በኋላ ለዘርህ ምድሪቱን እሰጣለሁ።13.እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ከተነጋገረበት ስፍራ ወደ ላይ ወጣ።14.ያዕቆብም እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር በተነጋገረበት ቦታ የድንጋይ ሐውልት ተከለ፤ የመጠጥ መሥዋዕትንም በእርሱ ላይ አፈሰሰ፥ ዘይትንም አፈሰሰበት።15.ያዕቆብም እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር የተነጋገረበትን ያን ቦታ ቤቴል ብሎ ጠራው።16.ከቤቴልም ተነሡ፤ ወደ ኤፍራታም ሊደርሱ ጥቂት ሲቀራቸው ራሔልን ምጥ ያዛት፥ በምጡም ተጨነቀች።17.ምጡም ባስጨነቃት ጊዜ አዋላጂቱ። አትፍሪ፥ ይኸኛው ደግሞ ወንድ ልጅ ይሆንሻልና አለቻት።18.እርስዋም ስትሞት ነፍስዋ በምትወጣበት ጊዜ ስሙን ቤንኦኒ ብላ ጠራችው፤ አባቱ ግን ብንያም አለው።19.ራሔልም ሞተች፥ ወደ ኤፍራታ በምትወስድም መንገድ ተቀበረች፤ እርስዋም ቤተልሔም ናት።20.ያዕቆብም በመቃብርዋ ላይ ሐውልት አቆመ፤ እርሱም እስከ ዛሬ የራሔል የመቃብርዋ ሐውልት ነው።21.እስራኤልም ከዚያ ተነሣ፥ ድንኳኑንም ከጋዴር ግንብ በስተ ወዲያ ተከለ።22.እስራኤልም በዚያች አገር በተቀመጠ ጊዜ ሮቤል ሄደ የአባቱንም ቁባት ባላን ተገናኛት፤ እስራኤልም ሰማ። የያዕቆብም ልጆች አሥራ ሁለት ናቸው፤23.የልያ ልጆች፤ የያዕቆብ በኵር ልጅ ሮቤል፥ ስምዖን፥ ሌዊ፥ ይሁዳ፥ ይሳኮር፥ ዛብሎን፤25.የራሔል ልጆች፤ ዮሴፍ፥ ብንያም፤ የራሔል ባርያ የባላ ልጆችም፤ ዳን፥ ንፍታሌም፤26.የልያ ባሪያ የዘለፋ ልጆችም፤ ጋድ፥ አሴር፤ እነዚህ በሁለቱ ወንዞች መካከል በሶርያ የተወለዱለት የያዕቆብ ልጆች ናቸው።27.ያዕቆብም ወደ አባቱ ወደ ይስሐቅ አብርሃምና ይስሐቅ እንግዶች ሆነው ወደ ተቀመጡባት ወደ መምሬ ወደ ቂርያትአርባቅ እርስዋም ኬብሮን ወደምትባለው መጣ።28.የይስሐቅም ዕድሜ መቶ ሰማንያ ዓመት ሆነ።29.ይስሐቅም ነፍሱን ሰጠ፥ ሞተም፤ ሸምግሎ ዕድሜንም ጠግቦ ወደ ወገኖቹ ተከማቸ፤ ልጆቹም ዔሳውና ያዕቆብ ቀበሩት።

ምዕራፍ 36

1.የዔሳው ትውልድ ይህ ነው፤ እርሱም ኤዶም ነው።2.ዔሳው ከከነዓን ልጆች ሚስቶችን አገባ፤ የኬጢያዊውን የዔሎንን ልጅ ዓዳን፥ የኤዊያዊው የፅብዖን ልጅ ዓና የወለዳትን አህሊባማን፥3.የእስማኤልን ልጅ የነባዮትን እኅት ቤሴሞትን።4.ዓዳ ለዔሳው ኤልፋዝን ወለደች፤ ቤሴሞትም ራጉኤልን ወለደች፤5.አህሊባማም የዑስን፥ የዕላምን፥ ቆሬን ወለደች፤ በከነዓን ምድር የተወለዱለት የዔሳው ልጆች እነዚህ ናቸው።6.ዔሳውም ሚስቶቹን ወንዶች ልጆቹንና ሴቶች ልጆቹን ቤተሰቡንም ሁሉ ከብቱንም ሁሉ እንስሶቹንም ሁሉ በከነዓንም አገር ያገኘውን ሁሉ ይዞ ከወንድሙ ከያዕቆብ ፊት ወደ ሌላ አገር ሄደ።7.ከብታቸው ስለ በዛ በአንድነት ይቀመጡ ዘንድ አልቻሉም፤ በእንግድነት የተቀመጡባትም ምድር ከከብታቸው ብዛት የተነሣ ልትበቃቸው አልቻለችም።8.ዔሳውም በሴይር ተራራ ተቀመጠ፤ ዔሳውም ኤዶም ነው።9.በሴይር ተራራ የሚኖሩ የኤዶማውያን አባት የዔሳው ትውልድም ይህ ነው።10.የዔሳው ልጆች ስም ይህ ነው፤ የዔሳው ሚስት የዓዳ ልጅ ኤልፋዝ፤ የዔሳው ሚስት የቤሴሞት ልጅ ራጉኤል።11.የኤልፋዝም ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ቴማን፥ ኦማር፥ ስፎ፥ ጎቶም፥ ቄኔዝ።12.ቲምናዕም ለዔሳው ልጅ ለኤልፋዝ የጭን ገረድ ነበረች፥ አማሌቅንም ለኤልፋዝ ወለደችለት፤ የዔሳው ሚስት የዓዳ ልጆች እነዚህ ናቸው።13.የራጉኤልም ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ናሖት፥ ዛራ፥ ሣማ፥ ሚዛህ፤ እነዚህም የዔሳው ሚስት የቤሴሞት ልጆች ናቸው።14.የፅብዖን ልጅ የዓና ልጅ የዔሳው ሚስት የአህሊባማ ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ለዔሳውም የዑስን፥ የዕላማን፥ ቆሬን ወለደች።15.የዔሳው ልጆች አለቆች እነዚህ ናቸው፤ ለዔሳው የበኵር ለኤልፋዝ ልጆች፤ ቴማን አለቃ፥ ኦማር አለቃ፥ ስፎ አለቃ፥ ቄኔዝ አለቃ፥16.ቆሬ አለቃ፥ ጎቶም አለቃ፥ አማሌቅ አለቃ፤ በኤዶም ምድር የኤልፋዝ አለቆች እነዚህ ናቸው፤ እነዚህ የዓዳ ልጆች ናቸው።17.የዔሳው ልጅ የራጉኤል ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ናሖት አለቃ፥ ዛራ አለቃ፥ ሣማ አለቃ፥ ሚዛህ አለቃ፤ በኤዶም ምድር የራጉኤል ልጆች አለቆች እነዚህ ናቸው፤ እነዚህም የዔሳው ሚስት የቤሴሞት ልጆች ናቸው።18.የዔሳው ሚስት የአህሊባማ ልጆች እነዚህ ናቸው፤ የዑስ አለቃ፥ የዕላማ አለቃ፥ ቆሬ አለቃ፤ የዔሳው ሚስት የዓና ልጅ የአህሊባማ አለቆች እነዚህ ናቸው።19.የዔሳው ልጆችና አለቆቻቸው እነዚህ ናቸው፤ እርሱም ኤዶም ነው።20.በዚያች አገር የተቀመጡ የሖሪው የሴይር ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ሎጣን፥ ሦባል፥ ፅብዖን፥ ዓና፥ ዲሶን፥ ኤጽር፥ ዲሳን፤21.እነዚህ በኤዶም ምድር የሖሪው የሴይር ልጆች አለቆች ናቸው።22.የሎጣን ልጆችም ሖሪ፥ ሄማም ናቸው፤ የሎጣንም እኅት ቲምናዕ ናት።23.የሦባል ልጆችም እነዚህ ናቸው፤ ዓልዋን፥ ማኔሐት፥ ዔባል፥ ስፎ፥ አውናም።24.የፅብዖን ልጆችም እነዚህ ናቸው፤ አያ፥ ዓና፤ ይህም ዓና በምድረ በዳ የአባቱን የፅብዖንን አህዮች ሲጠብቅ ፍልውኆችን ያገኘ ነው።25.የዓና ልጆችም እነዚህ ናቸው፤26.ዲሶን፥ አህሊባማም የዓና ሴት ልጅ። የዲሶንም ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ሔምዳን፥ ኤስባን፥ ይትራን፥ ክራን።27.የኤጽር ልጆችም እነዚህ ናቸው፤ ቢልሐን፥ ዛዕዋን፥ ዓቃን።28.የዲሳን ልጆችም እነዚህ ናቸው፤ ዑፅ፥ አራን።29.የሖሪ አለቆች እነዚህ ናቸው፤ ሎጣን አለቃ፥ ሦባል አለቃ፥ ፅብዖን አለቃ፥30.ዓና አለቃ፥ ዲሶን አለቃ፥ ኤጽር አለቃ፥ ዲሳን አለቃ፤ በሴይር ምድር አለቆች የሆኑ የሖሪ አለቆቹ እነዚህ ናቸው።31.በእስራኤል ልጆች ላይ ንጉሥ ከመኖሩ በፊት በኤዶም አገር የነገሡ ነገሥታት እነዚህ ናቸው።32.በኤዶምም የቢዖር ልጅ ባላቅ ነገሠ፤ የከተማውም ስም ዲንሃባ ናት።33.ባላቅም ሞተ፥ በስፍራውም የባሶራው የዛራ ልጅ ኢዮባብ ነገሠ።34.ኢዮባብም ሞተ፥ በስፍራውም የቴማኒው አገር ሑሳም ነገሠ።35.ሑሳምም ሞተ፥ በስፍራውም የምድያምን ሰዎች በሞዓብ ሜዳ የመታ የባዳድ ልጅ ሃዳድ ነገሠ፤ የከተማውም ስም ዓዊት ተባለ።36.ሃዳድም ሞተ፥ በስፍራውም የመሥሬቃው ሠምላ ነገሠ።37.ሠምላም ሞተ፥ በስፍራውም በወንዝ አጠገብ ካለችው ከርሆቦት ሳኦል ነገሠ።38.ሳኦልም ሞተ፥ በስፍራውም የዓክቦር ልጅ በኣልሐናን ነገሠ።39.የዓክቦር ልጅ በኣልሐናንም ሞተ፥ በስፍራውም ሃዳር ነገሠ፤ የከተማውም ስም ፋዑ ነው፤ ሚስቱም የሜዛሃብ ልጅ መጥሬድ የወለደቻት መሄጣብኤል ትባላለች።40.የዔሳውም የአለቆቹ ስም በወገናቸው በስፍራቸው በስማቸውም ይህ ነው፤ ቲምናዕ አለቃ፥ ዓልዋ አለቃ፥ የቴት አለቃ፥41.አህሊባማ አለቃ፥ ኤላ አለቃ፥ ፊኖን አለቃ፥42.ቄኔዝ አለቃ፥ ቴማን አለቃ፥ ሚብሳር አለቃ፥43.መግዲኤል አለቃ፥ ዒራም አለቃ፥ እነዚህ በግዛታቸው ምድር በየመኖሪያቸው የኤዶም አለቆች ናቸው። የኤዶማውያን አባት ይህ ዔሳው ነው። a

ምዕራፍ 37

1.ያዕቆብም አባቱ በስደት በኖረበት አገር በከነዓን ምድር ተቀመጠ።2.የያዕቆብም ትውልድ ይህ ነው። ዮሴፍ የአሥራ ሰባት ዓመት ልጅ በሆነ ጊዜ ከወንድሞቹ ጋር በጎችን ይጠብቅ ነበር፤ እርሱም ከአባቱ ሚስቶች ከባላና ከዘለፋ ልጆች ጋር ሳለ ብላቴና ነበረ፤ ዮሴፍም የክፋታቸውን ወሬ ወደ አባታቸው አመጣ።3.እስራኤልም ዮሴፍን ከልጆቹ ሁሉ ይልቅ ይወደው ነበር፥ እርሱ በሽምግልናው የወለደው ነበርና፤ በብዙ ኅብር ያጌጠችም ቀሚስ አደረገለት ።4.ወንድሞቹም አባታቸው ከልጆቹ ሁሉ ይልቅ እንዲወደው ባዩ ጊዜ ጠሉት፥ በሰላም ይናገሩትም ዘንድ አልቻሉም።5.ዮሴፍም ሕልምን አለመ፥ ለወንድሞቹም ነገራቸው፤ እነርሱም እንደ ገና በብዙ ጠሉት።6.እርሱም አላቸው። እኔ ያለምሁትን ሕልም ስሙ፤7.እነሆ እኛ በእርሻ መካከል ነዶ ስናስር ነበርና፥ እነሆም፥ የእኔ ነዶ ቀጥ ብላ ቆመች፤ የእናንተም ነዶች በዙሪያ ከብበው እነሆ ለእኔ ነዶ ሰገዱ።8.ወንድሞቹም። በእኛ ላይ ልትነግሥብን ይሆን? ወይስ ልትገዛ ይሆን? አሉት። እንደ ገናም ስለ ሕልሙና ስለ ነገሩ ይልቁን ጠሉት።9.ደግሞም ሌላ ሕልምን አለመ፥ ለወንድሞቹም ነገራቸው፥ እንዲህም አለ። እነሆ ደግሞ ሌላ ሕልምን አለምሁ፤ እነሆ ፀሐይና ጨረቃ አሥራ አንድ ከዋክብትም ሲሰግዱልኝ አየሁ።10.ለአባቱና ለወንድሞቹም ነገራቸው፤ አባቱም ገሠጸው፥ እንዲህም አለው። ይህ ያለምኸው ሕልም ምንድር ነው? በውኑ እኔና እናትህ ወንድሞችህም መጥተን በምድር ላይ እንሰግድልህ ይሆን?11.ወንድሞቹም ቀኑበት አባቱ ግን ነገሩን ይጠብቀው ነበር።12.ወንድሞቹ በሴኬም የአባታቸውን በጎች ይጠብቁ ዘንድ ሄዱ።13.እስራኤልም ዮሴፍን። ወንድሞችህ በሴኬም በጎችን የሚጠብቁ አይደሉምን? ወደ እነርሱ እልክህ ዘንድ ና አለው። እርሱም። እነሆኝ አለው ።14.እርሱም። ሄደህ ወንድሞችህና በጎቹ ደኅና እንደ ሆኑ እይ፥ ወሬአቸውንም አምጣልኝ አለው። እንዲህም ከኬብሮን ቈላ ሰደደው፥ ወደ ሴኬምም መጣ።15.እነሆም በምድረ በዳ ሲቅበዘበዝ ሳለ አንድ ሰው አገኘው፤ ሰውዮውም። ምን ትፈልጋለህ? ብሎ ጠየቀው።16.እርሱም ወንድሞቼን እፈልጋለሁ፤ በጎቹን የሚጠብቁበት ወዴት እንደ ሆነ እባክህ ንገረኝ አለ።17.ሰውዮውም። ከዚህ ተነሥተዋል፤ ወደ ዶታይን እንሂድ ሲሉም ሰምቼአቸዋለሁ አለው። ዮሴፍም ወንድሞቹን ተከታትሎ ሄደ፥ በዶታይንም አገኛቸው።18.እነርሱም በሩቅ ሳለ አዩት፥ ወደ እነርሱም ገና ሳይቀርብ ይገድሉት ዘንድ በእርሱ ላይ ተማከሩ።19.አንዱም ለአንዱ እንዲህ አለው። ያ ባለ ሕልም ይኸው መጣ።20.አሁንም ኑ፥ እንግደለውና በአንድ ጕድጓድ ውስጥ እንጣለው። ክፉ አውሬም በላው እንላለን፤ ከሕልሞቹም የሚሆነውን እናያለን።21.ሮቤልም ይህን ሰማ፥ ከእጃቸውም አዳነው፥ እንዲህም አለ። ሕይወቱን አናጥፋ።22.ሮቤል። ደም አታፍስሱ፤ በዚህች ምድረ በዳ ባለችው ጕድጓድ ጣሉት፥ ነገር ግን እጃችሁን አትጣሉበት አላቸው። እንዲህም ማለቱ ከእጃቸው ሊያድነውና ወደ አባቱ ሊመልሰው ነው።23.እንዲህም ሆነ፤ ዮሴፍም ወደ ወንድሞቹ በቀረበ ጊዜ የለበሳትን በብዙ ኅብር ያጌጠቺቱን ቀሚሱን ገፈፉት፤24.ወስደውም ወደ ጕድጓድ ጣሉት፤ ጕድጓዱም ውኃ የሌለበት ደረቅ ነበረ።25.እንጀራም ሊበሉ ተቀመጡ፤ ዓይናቸውንም አንሥተው አዩ፥ እነሆም የእስማኤላውያን ነገዶች ወደ ግብፅ ለመውረድ ከገለዓድ መጡ፤ ግመሎቻቸውም ሽቱና በለሳን ከርቤም ተጭነው ነበር።26.ይሁዳም ወንድሞቹን እንዲህ አላቸው። ወንድማችንን ገድለን ደሙን ብንሸሽግ ጥቅማችን ምንድር ነው?27.ኑ፥ ለእስማኤላውያን እንሽጠው፥ እጃችንን ግን በእርሱ ላይ አንጣል፥ ወንድማችን ሥጋችንም ነውና። ወንድሞቹም የእርሱን ነገር ሰሙት።28.የምድያም ነጋዶችም አለፉ፤ እነርሱም ዮሴፍን አንሥተው ከጕድጓድ አወጡት፤ ለእስማኤላውያንም ዮሴፍን በሀያ ብር ሸጡት፤ እነርሱም ዮሴፍን ወደ ግብፅ ወሰዱት።29.ሮቤልም ወደ ጕድጓዱ ተመለሰ፥ እነሆም ዮሴፍ በጕድጓድ የለም፤ ልብሱንም ቀደደ።30.ወደ ወንድሞቹም ተመልሶ። ብላቴናው የለም፤ እንግዲህ እኔ ወዴት እሄዳለሁ? አለ።31.የዮሴፍንም ቀሚስ ወሰዱ፥ የፍየል አውራም አርደው ቀሚሱን በደም ነከሩት።32.ብዙ ኅብር ያለበትን ቀሚሱንም ላኩ፥ ወደ አባታቸውም አገቡት፥ እንዲህም አሉት። ይህንን አገኘነ፤ ይህ የልጅህ ልብስ እንደ ሆነ ወይም እንዳልሆነ እስኪ እየው።33.እርሱም አውቆ። የልጄ ቀሚስ ነው፤ ክፉ አውሬ በልቶታል፤ ዮሴፍ በእርግጥ ተበጫጭቋል አለ።34.ያዕቆብም ልብሱን ቀደደ፥ በወገቡም ማቅ ታጥቆ ለልጁ ብዙ ቀን አለቀሰ።35.ወንዶች ልጆቹና ሴቶች ልጆቹም ሁሉ ሊያጽናኑት ተነሡ፤ መጽናናትን እንቢ አለ፥ እንዲህም አለ። ወደ ልጄ ወደ ሙታን ስፍራ እያዘንሁ እወርዳለሁ። አባቱም ስለ እርሱ አለቀሰ።36.እነዚያ የምድያም ሰዎች ግን ዮሴፍን በግብፅ ለፈርዖን ጃንደረባ ለዘበኞቹ አለቃ ለጲጥፋራ ሸጡት።

መዝሙረ ዳዊት

ምዕራፍ 12

1.አቤቱ፥ አድነኝ፤ ደግ ሰው አልቆአልና፥ ከሰው ልጆችም መተማመን ጐድሎአልና።2.እርስ በርሳቸው ከንቱ ነገርን ይናገራሉ፤ በሽንገላ ከንፈር ሁለት ልብ ሆነው ይናገራሉ።3.የሽንገላን ከንፈሮች ሁሉ እግዚአብሔር ያጠፋቸዋል፥ ታላቅ ነገርን የምትናገረውን ምላስ፤4.ምላሳችንን እናበረታለን፤ ከንፈራችን የእኛ ነው፥ ጌታችን ማን ነው? የሚሉትን።5.ስለ ድሆች መከራ፥ ስለ ችግረኞች ጩኸት እግዚአብሔር። አሁን እነሣለሁ ይላል፤ መድኃኒትን አደርጋለሁ፥ በላዩም እገልጣለሁ።6.በምድር ላይ እንደ ተፈተነ ሰባት ጊዜ እንደ ተጣራ ብር። የእግዚአብሔር ቃላት የነጹ ቃላት ናቸው።7.አቤቱ፥ አንተ ጠብቀን፥ ከዚህችም ትውልድ ለዘላለም ታደገን።8.በሰው ልጆች ዘንድ ምናምንቴ ከፍ ከፍ ባለ ጊዜ ክፉዎች በዙሪያው ሁሉ ይመላለሳሉ።

የማርቆስ ወንጌል

ምዕራፍ 14

1.ከሁለት ቀን በኋላ ፋሲካና የቂጣ በዓል ነበረ። የካህናት አለቆችም ጻፎችም እንዴት አድርገው በተንኰል እንደሚይዙትና እንደሚገድሉት ይፈልጉ ነበር።2.የሕዝብ ሁከት እንዳይሆን በበዓል አይሁን ይሉ ነበርና።3.እርሱም በቢታንያ በለምጻሙ በስምዖን ቤት በነበረ ጊዜ፥ በማዕድ ተቀምጦ ሳለ፥ አንዲት ሴት ዋጋው እጅግ የከበረ ጥሩ ናርዶስ ሽቱ የመላበት የአልባስጥሮስ ቢልቃጥ ይዛ መጣች፤ ቢልቃጡንም ሰብራ በራሱ ላይ አፈሰሰችው።4.አንዳንዶችም። ይህ የሽቱ ጥፋት ለምንድር ነው?5.ይህ ሽቱ ከሦስት መቶ ዲናር በሚበልጥ ዋጋ ተሽጦ ለድሆች ሊሰጥ ይቻል ነበርና ብለው በራሳቸው ይቈጡ ነበር፤ እርስዋንም ነቀፉአት።6.ኢየሱስ ግን እንዲህ አለ። ተዉአት፤ ስለ ምን ታደክሙአታላችሁ? መልካም ሥራ ሠርታልኛለች።7.ድሆች ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ይኖራሉና፥ በማናቸውም በወደዳችሁት ጊዜ መልካም ልታደርጉላቸው ትችላላችሁ፥ እኔ ግን ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር አልኖርም።8.የተቻላትን አደረገች፤ አስቀድማ ለመቃብሬ ሥጋዬን ቀባችው።9.እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ወንጌል በዓለሙ ሁሉ በሚሰበክበት በማናቸውም ስፍራ፥ እርስዋ ያደረገችው ደግሞ ለእርስዋ መታሰቢያ ሊሆን ይነገራል።10.ከአሥራ ሁለቱም አንዱ የአስቆሮቱ ይሁዳ አሳልፎ ሊሰጠው ወደ ካህናት አለቆች ሄደ።11.ሲሰሙም ደስ አላቸው ብርም ይሰጡት ዘንድ ተስፋ ሰጡት። በሚመች ጊዜም እንዴት አድርጎ አሳልፎ እንዲሰጠው ይፈልግ ነበር።12.ፋሲካን በሚያርዱበት በቂጣ በዓል መጀመሪያ ቀን ደቀ መዛሙርቱ። ፋሲካን ትበላ ዘንድ ወዴት ሄደን ልናሰናዳ ትወዳለህ? አሉት።13.ከደቀ መዛሙርቱም ሁለት ላከ እንዲህም አላቸው። ወደ ከተማ ሂዱ፥ ማድጋ ውኃ የተሸከመ ሰውም ይገናኛችኋል፤14.ተከተሉት፥ የሚገባበትንም የቤቱን ጌታ። መምህሩ። ከደቀ መዛሙርቴ ጋር ፋሲካን የምበላበት የእንግዳ ቤት ወዴት ነው? ይላል በሉት።15.እርሱም በደርብ ላይ ያለውን የተሰናዳና የተነጠፈ ታላቅ አዳራሽ ያሳያችኋል፤16.በዚያም አሰናዱልን። ደቀ መዛሙርቱም ወጡ ወደ ከተማም ሄደው እንዳላቸው አገኙ፥ ፋሲካንም አሰናዱ።17.በመሸም ጊዜ ከአሥራ ሁለቱ ጋር መጣ።18.ተቀምጠውም ሲበሉ ኢየሱስ። እውነት እላችኋለሁ፥ ከእናንተ አንዱ፥ እርሱም ከእኔ ጋር የሚበላው አሳልፎ ይሰጠኛል አለ።19.እነርሱም ያዝኑ፥ እያንዳንዳቸውም። እኔ እሆንን? ይሉት ጀመር።20.እርሱም መልሶ። ከአሥራ ሁለቱ አንዱ ከእኔ ጋር ወደ ወጭቱ እጁን የሚያጠልቀው ነው።21.የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ ይሄዳል፤ ነገር ግን የሰው ልጅ አልፎ ለሚሰጥበት ለዚያ ሰው ወዮለት፤ ያ ሰው ባልተወለደ ይሻለው ነበር አላቸው።22.ሲበሉም ኢየሱስ እንጀራን አንሥቶ ባረከ ቈርሶም ሰጣቸውና። እንካችሁ፤ ይህ ሥጋዬ ነው አለ።23.ጽዋንም አንሥቶ አመስግኖም ሰጣቸው፥ ሁሉም ከእርሱ ጠጡ።24.እርሱም። ይህ ስለ ብዙዎች የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ነው።25.እውነት እላችኋለሁ፥ በእግዚአብሔር መንግሥት ከወይኑ ፍሬ አዲሱን እስከምጠጣበት እስከዚያ ቀን ድረስ ደግሞ አልጠጣውም አላቸው።26.መዝሙርም ከዘመሩ በኋላ ወደ ደብረ ዘይት ወጡ።27.ኢየሱስም። በዚች ሌሊት ሁላችሁ በእኔ ትሰናከላላችሁ፤ እረኛዉን እመታለሁ በጎችም ይበተናሉ የሚል ተጽፎአልና።28.ነገር ግን ከተነሣሁ በኋላ ወደ ገሊላ እቀድማችኋለሁ አላቸው።29.ጴጥሮስም። ሁሉም ቢሰናከሉ እኔ ግን ከቶ አልሰናከልም አለው።30.ኢየሱስም። እውነት እልሃለሁ፥ ዛሬ በዚች ሌሊት ዶሮ ሁለት ጊዜ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ አለው።31.እርሱም ቃሉን አበርትቶ። ከአንተ ጋር የምሞት እንኳ ቢሆን ከቶ አልክድህም አለ። ሁሉም ደግሞ እንደዚሁ አሉ።32.ጌቴሴማኒ ወደምትባልም ስፍራ መጡ፥ ደቀ መዛሙርቱንም። ስጸልይ ሳለሁ፥ በዚህ ተቀመጡ አላቸው።33.ጴጥሮስንና ያዕቆብን ዮሐንስንም ከእርሱ ጋር ወሰደ፤ ሊደነግጥም ሊተክዝም ጀመረና።34.ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዘነች፤ በዚህ ቈዩ ትጉም አላቸው።35.ጥቂትም ወደ ፊት እልፍ ብሎ በምድርም ወድቆ፥ ይቻልስ ቢሆን ሰዓቲቱ ከእርሱ እንድታልፍ ጸለየና።36.አባ አባት ሆይ፥ ሁሉ ይቻልሃል፤ ይህችን ጽዋ ከእኔ ውሰድ፤ ነገር ግን አንተ የምትወደው እንጂ እኔ የምወደው አይሁን አለ።37.መጣም ተኝተውም አገኛቸው፥ ጴጥሮስንም። ስምዖን ሆይ፥ ተኝተሃልን? አንዲት ሰዓት ስንኳ ልትተጋ አልቻልህምን?38.ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉ ጸልዩም፤ መንፈስስ ተዘጋጅታለች፥ ሥጋ ግን ደካማ ነው አለው።39.ደግሞም ሄዶ ያንኑ ቃል ጸለየ።40.ደግሞም መጥቶ ዓይኖቻቸው በእንቅልፍ ከብደው ነበርና ተኝተው አገኛቸው፥ የሚመልሱለትንም አላወቁም።41.ሦስተኛም መጥቶ። እንግዲህስ ተኙ ዕረፉም፤ ይበቃል፤ ሰዓቲቱ ደረሰች፤ እነሆ፥ የሰው ልጅ በኃጢአተኞች እጅ አልፎ ይሰጣል።42.ተነሡ፥ እንሂድ፤ እነሆ፥ አሳልፎ የሚሰጠኝ ቀርቦአል አላቸው።43.ወዲያውም ገና ሲናገር ከአሥራ ሁለቱ አንዱ ይሁዳ መጣ፥ ከእርሱም ጋር ብዙ ሰዎች ሰይፍና ጐመድ ይዘው ከካህናት አለቆችና ከጻፎች ከሽማግሌዎችም ዘንድ መጡ።44.አሳልፎ የሚሰጠውም። የምስመው እርሱ ነው፤ ያዙት ተጠንቅቃችሁም ውሰዱት ብሎ ምልክት ሰጥቶአቸው ነበር።45.መጥቶም ወዲያው ወደ እርሱ ቀረበና። መምህር ሆይ፥ መምህር ሆይ፥ ብሎ ሳመው፤46.እነርሱም እጃቸውን በእርሱ ላይ ጭነው ያዙት።47.በአጠገብ ከቆሙት ግን አንዱ ሰይፉን መዞ የሊቀ ካህናቱን ባሪያ መታ ጆሮውንም ቈረጠ።48.ኢየሱስም መልሶ። ወንበዴ እንደምትይዙ ሰይፍና ጐመድ ይዛችሁ ልትይዙኝ መጣችሁን?49.በመቅደስ ዕለት ዕለት እያስተማርሁ ከእናንተ ጋር ስኖር አልያዛችሁኝም፤ ነገር ግን መጻሕፍት ይፈጸሙ ዘንድ ይህ ሆነ አላቸው።50.ሁሉም ትተውት ሸሹ።51.ዕርቃኑን በነጠላ የሸፈነ አንድ ጎበዝ ይከተለው ነበር፥52.ጎበዛዝቱም ያዙት፤ እርሱ ግን ነጠላውን ትቶ ዕራቁቱን ሸሸ።53.ኢየሱስንም ወደ ሊቀ ካህናቱ ወሰዱት፥ የካህናት አለቆችም ሁሉ ሽማግሌዎችም ጻፎችም ተሰበሰቡ።54.ጴጥሮስም እስከ ሊቀ ካህናቱ ግቢ ውስጥ በሩቁ ተከተለው፥ ከሎሌዎችም ጋር ተቀምጦ እሳት ይሞቅ ነበር።55.የካህናት አለቆችም ሸንጎውም ሁሉ እንዲገድሉት በኢየሱስ ላይ ምስክር ይፈልጉ ነበር፥ አላገኙምም፤56.ብዙዎች በሐሰት ይመሰክሩበት ነበርና፥ ምስክርነታቸው ግን አልተሰማማም።58.ምስክርነታቸውም እንዲሁ እንኳ አልተሰማማም።59.ሊቀ ካህናቱም በመካከላቸው ተነሥቶ። አንዳች አትመልስምን? እነዚህስ በአንተ ላይ የሚመሰክሩብህ ምንድር ነው? ብሎ ኢየሱስን ጠየቀው።60.እርሱ ግን ዝም አለ አንዳችም አልመለሰም። ደግሞ ሊቀ ካህናቱ ጠየቀውና። የቡሩክ ልጅ ክርስቶስ አንተ ነህን? አለው።61.ኢየሱስም። እኔ ነኝ፤ የሰው ልጅም በኃይል ቀኝ ሲቀመጥ በሰማይም ደመና ሲመጣ ታያላችሁ አለ።62.ሊቀ ካህናቱም ልብሱን ቀደደና። ከእንግዲህ ወዲህ ምስክሮችን ምን ያስፈልገናል?63.ስድቡን ሰማችሁ፤ ምን ይመስላችኋል? አለ። እነርሱም ሁሉ። ሞት ይገባዋል ብለው ፈረዱበት።64.አንዳንዶችም ይተፉበት ፊቱንም ሸፍነው ይጐስሙትና። ትንቢት ተናገር ይሉት ጀመር፤ ሎሌዎችም በጥፊ እየመቱ ወሰዱት።65.ጴጥሮስም በግቢ ውስጥ ወደ ታች ሳለ ከሊቀ ካህናቱ ገረዶች አንዲቱ መጣች፥66.ጴጥሮስም እሳት ሲሞቅ አይታ ተመለከተችውና። አንተ ደግሞ ከናዝሬቱ ከኢየሱስ ጋር ነበርህ አለችው።67.እርሱ ግን። የምትዪውን አላውቅም አላስተውልምም ብሎ ካደ። ወደ ውጭም ወደ ደጅ ወጣ፤ ዶሮም ጮኸ።68.ገረዲቱም አይታው በዚያ ለቆሙት። ይህም ከእነርሱ ወገን ነው ስትል ሁለተኛ ትነግራቸው ጀመር።69.እርሱም ደግሞ ካደ። ጥቂት ቈይተውም በዚያ የቆሙት ዳግመኛ ጴጥሮስን። የገሊላ ሰው ነህና ከእነርሱ ወገን በእውነት ነህ አሉት።70.እርሱ ግን። ይህን የምትሉትን ሰው አላውቀውም ብሎ ይረገምና ይምል ጀመር። ወዲያውም ዶሮ ሁለተኛ ጮኸ።71.ጴጥሮስንም ኢየሱስ። ዶሮ ሁለት ጊዜ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ ያለው ቃል ትዝ አለው፤ ነገሩንም አስቦ አለቀሰ።