Skip to Content
የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን | YEHIWOT MELHEK BETEKIRSTIAN
የ2019 ዓ.ም የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ 📖 ዛሬን አንብብ →

የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን

Yehiwot Melhek Betekirstian

ሳምንት 3 · ቀን 13 (ረቡዕ) 📅 Meskerem 20, 2019

ኦሪት ዘፍጥረት 32, 33, 34 · መዝሙረ ዳዊት 145 · የማርቆስ ወንጌል 13

📖 የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም፦ 1954 መጽሐፍ ቅዱስ አዲሱ መደበኛ ትርጒም

ኦሪት ዘፍጥረት

ምዕራፍ 32

1.ያዕቆብ፣ ወንድሙን ዔሳውን ሊገናኝ ተዘጋጀ
1 ያዕቆብም ጕዞውን ቀጠለ፤ የእግዚአብሔርም መላእክት ተገናኙት፤
2.ያዕቆብም ባያቸው ጊዜ፣ “ይህ የእግዚአብሔር ሰፈር ነው” አለ፤ የዚያንም ቦታ ስም መሃናይም አለው። 3.ያዕቆብም በኤዶም አገር ሴይር በተባለው ምድር ወደሚኖረው ወንድሙ ወደ ዔሳው መልእክተኞችን አስቀድሞ ላከ፤ 4.እንዲህም ብሎ አዘዛቸው፤ “ጌታዬን ዔሳውን እንዲህ ትሉታላችሁ፤ ‘አገልጋይህ ያዕቆብ እንዲህ ብሏል በሉት፤ “ከላባ ዘንድ ተቀምጬ እስከ አሁን ድረስ እዚያው ኖርሁ፤ 5.ከብቶች፣ አህዮች፣ የበግና የፍየል መንጎች እንደዚሁም የወንድና የሴት አገልጋዮች አሉኝ፤ አሁንም ይህን መልእክት ለጌታዬ መላኬ በጎ ፈቃድህን እንዳገኝ በማሰብ ነው።” ’ ” 6.የተላኩትም ሰዎች ወደ ያዕቆብ ተመልሰው፣ “ወደ ወንድምህ ወደ ዔሳው ሄደን ነበር፤ እርሱም ሊቀበልህ በመምጣት ላይ ነው፤ አራት መቶ ሰዎችም ዐብረውት አሉ” አሉት። 7.ያዕቆብም በታላቅ ፍርሀትና ጭንቀት ተውጦ፣ ዐብረውት የነበሩትን ሰዎች ሁለት ቦታ ከፈላቸው፤ በጎቹን፣ ፍየሎቹን፣ ከብቶቹንና ግመሎቹን ሁለት ቦታ ከፈላቸው። 8.“ዔሳው መጥቶ በአንደኛው ላይ አደጋ ቢጥል፣ ሌላው ክፍል ሊያመልጥ ይችላል” ብሎ ዐስቦ ነበር። 9.ያዕቆብ እንዲህ ሲል ጸለየ፤ “የአባቴ የአብርሃም አምላክ፣ የአባቴ የይሥሐቅ አምላክ ሆይ፤ ‘ወደ አገርህና ወደ ዘመዶችህ ተመለስ፤ እኔም በጎ ነገር አደርግልሃለሁ’ ያልኸኝ እግዚአብሔር ሆይ፤ 10.እኔ ባሪያህ እስካሁን ላደረግህልኝ ቸርነትና ታማኝነት ብቁ አይደለሁም፤ ዮርዳኖስን ስሻገር በእጄ ላይ ከነበረው በትር በቀር ምንም አልነበረኝም፤ አሁን ግን ይኸው ሁለት ሰራዊት ሆኛለሁ። 11.ከወንድሜ ከዔሳው እጅ እንድታድነኝ እለምንሃለሁ፤ መጥቶ እኔንም ሆነ እነዚህን እናቶች ከነልጆቻቸው ያጠፋናል ብዬ ፈርቻለሁና፤ 12.ነገር ግን፣ አንተ ራስህ፣ ‘አበለጽግሃለሁ፤ ዘርህንም ሊቈጠር እንደማይቻል እንደ ባሕር አሸዋ አበዛዋለሁ’ ብለኸኛል።” 13.በዚያችም ሌሊት ያዕቆብ እዚያው ዐደረ፤ ካለው ሀብት ለወንድሙ ለዔሳው እጅ መንሻ እነዚህን መረጠ፦ 14.ሁለት መቶ እንስት ፍየሎችና ሃያ አውራ ፍየሎች፣ ሁለት መቶ እንስት በጎችና ሃያ አውራ በጎች፣ 15.ሠላሳ የሚያጠቡ ግመሎች ከነግልገሎቻቸው፣ አርባ ላሞችና ዐሥር ኰርማዎች፣ ሃያ እንስት አህዮችና ዐሥር ተባዕት አህዮች። 16.እነዚህንም በየመንጋው ለይቶ፣ የሚነዷቸውን ጠባቂዎች መደበላቸው፤ ጠባቂዎቹንም፣ “እናንተ ቀድማችሁኝ ሂዱ፣ መንጋዎቹንም አራርቃችሁ ንዷቸው” አላቸው። 17.ቀድሞ የሚሄደውንም እንዲህ ሲል አዘዘው፤ “ዔሳው አግኝቶህ፣ ‘የማን ነህ? ወዴትስ ትሄዳለህ? የምትነዳውስ ይህ ሁሉ ከብት የማን ነው?’ ብሎ ቢጠይቅህ፣ 18.‘የአገልጋይህ የያዕቆብ ናቸው፤ ለጌታዬ ለዔሳው እጅ መንሻ የሰደዳቸው ናቸው፤ እርሱም ከበስተኋላችን እየመጣ ነው’ ብለህ ንገረው።” 19.እንዲሁም ሁለተኛውን፣ ሦስተኛውንና መንጎችን የሚነዱትን ሌሎቹንም ሁሉ እንዲህ ሲል አዘዛቸው፤ “ዔሳውን ስታገኙት ይህንኑ ትነግሩታላችሁ፤ 20.በተለይም ‘አገልጋይህ ያዕቆብ ከኋላችን እየመጣ ነው’ ማለትን አትዘንጉ።” ይህንም ያዘዘው፣ “ዔሳው ከእኔ ጋራ ከመገናኘቱ በፊት እጅ መንሻዬ አስቀድሞ ቢደርሰው ምናልባት ልቡ ይራራና በሰላም ይቀበለኛል” ብሎ ስላሰበ ነበር። 21.ስለዚህ የያዕቆብ እጅ መንሻ ከርሱ አስቀድሞ ተላከ፤ እርሱ ራሱ ግን እዚያው በሰፈሩበት ቦታ ዐደረ።

ያዕቆብ ከእግዚአብሔር ጋራ የገጠመው ትግል

22.በዚያች ሌሊት ያዕቆብ ተነሣ፤ ሁለቱን ሚስቶቹን እንዲሁም ሁለቱን ሴት አገልጋዮቹንና ዐሥራ አንድ ልጆቹን ይዞ በያቦቅ መልካ ተሻገረ። 23.ወንዙን አሻግሮ ከሸኛቸው በኋላ፣ ጓዙን ሁሉ ሰደደ። 24.ያዕቆብ ግን ብቻውን እዚያው ቀረ፤ አንድ ሰውም እስኪነጋ ድረስ ሲታገለው ዐደረ። 25.ያም ሰው ያዕቆብን ታግሎ ማሸነፍ እንዳቃተው በተረዳ ጊዜ፣ የጭኑን ሹልዳ ነካው፤ በግብግቡም የያዕቆብ ጭን ከመጋጠሚያው ላይ ተናጋ። 26.በዚያ ጊዜ ሰውየው፣ “እንግዲህ መንጋቱ ስለ ሆነ ልቀቀኝና ልሂድ” አለው።
ያዕቆብም፣ “ካልባረክኸኝ አልለቅህም” አለው።
27.ሰውየውም፣ “ስምህ ማን ነው?” አለው።
እርሱም፣ “ያዕቆብ ነው” አለ።
28.ሰውየውም፣ “ከእግዚአብሔርም፣ ከሰዎችም ጋራ ታግለህ አሸንፈሃልና ከእንግዲህ ስምህ እስራኤል እንጂ፣ ያዕቆብ አይባልም” አለው። 29.ያዕቆብም፣ “እባክህ ስምህን ንገረኝ” ብሎ ጠየቀው።
ሰውየውም፣ “ስሜን ለማወቅ ለምን ፈለግህ?” አለው፤ በዚያም ስፍራ ባረከው።
30.ስለዚህ ያዕቆብ፣ “እግዚአብሔርን ፊት ለፊት አይቼ እንኳ ሕይወቴ ተርፋለች” ሲል፣ የዚያን ቦታ ስም ጵኒኤል አለው። 31.ጵኒኤልንም እንዳለፈ ፀሓይ ወጣችበት፤ እርሱም በጭኑ ምክንያት ያነክስ ነበር። 32.ከዚህም የተነሣ የእስራኤል ልጆች እስከ ዛሬ ድረስ ሹልዳን ከጭኑ ጋራ የሚያገናኘውን ሥጋ አይበሉም፤ ምክንያቱም በጭኑ መጋጠሚያ ላይ ያለው የያዕቆብ ሹልዳ ተነክቶ ነበር።

ምዕራፍ 33

የያዕቆብና የዔሳው መገናኘት

1.ያዕቆብ አሻግሮ ተመለከተ፤ እነሆ ዔሳው አራት መቶ ሰዎች አስከትሎ እየመጣ ነበር። ስለዚህ ልጆቹን ለልያ፣ ለራሔልና ለሁለቱ አገልጋዮች አከፋፈላቸው። 2.ከዚያም ሁለቱን አገልጋዮች ከነልጆቻቸው አስቀደመ፤ ልያንና ልጆቿንም አስከተለ፤ ራሔልንና ዮሴፍን ግን ከሁሉ ኋላ እንዲሆኑ አደረገ። 3.እርሱ ራሱም ቀድሟቸው ሄደ፤ ወንድሙም ዘንድ እስኪደርስ ድረስ ሰባት ጊዜ ወደ መሬት ለጥ ብሎ እጅ ነሣ። 4.ዔሳው ግን ሊገናኘው ወደ እርሱ ሮጦ ሄዶ ዐቀፈው፤ በዐንገቱም ላይ ተጠምጥሞ ሳመው፤ ሁለቱም ተላቀሱ። 5.ከዚያም ዔሳው ቀና ብሎ ሲመለከት ሴቶቹንና ልጆቹን አየ፤ እርሱም፣ “እነዚህ ዐብረውህ ያሉት እነማን ናቸው?” ብሎ ጠየቀው።
ያዕቆብም መልሶ፣ “እነዚህማ እግዚአብሔር በቸርነቱ ለእኔ ለአገልጋይህ የሰጠኝ ልጆች ናቸው” አለው።
6.በዚህ ጊዜ ሁለቱ ሴት አገልጋዮችና ልጆቻቸው ቀርበው እጅ ነሡ፤ 7.ከዚያም ልያና ልጆቿ መጥተው እጅ ነሡ፤ በመጨረሻም ዮሴፍና ራሔል መጡ፤ እነርሱም ቀርበው እጅ ነሡ። 8.ዔሳውም፣ “ወደ እኔ ተነድቶ የመጣው ይህ ሁሉ መንጋ ምንድን ነው?” አለው።
እርሱም፣ “ጌታዬ ሆይ፤ በአንተ ዘንድ ሞገስ ባገኝ ብዬ ነው” አለው።
9.ዔሳው ግን፣ “ወንድሜ ሆይ፤ እኔ በቂ አለኝ፤ የራስህን ለራስህ አድርገው” አለው። 10.ያዕቆብም፣ “የለም፣ እንዲህ አይደለም፤ በአንተ ዘንድ ሞገስ አግኝቼ እንደ ሆነ፣ እጅ መንሻዬን ተቀበል፤ በመልካም ሁኔታ ተቀብለኸኝ ፊትህን ማየት መቻሌን የእግዚአብሔርን ፊት እንደ ማየት እቈጥረዋለሁ። 11.እግዚአብሔር በቸርነቱ አሟልቶ ስለ ሰጠኝ የሚያስፈልገኝ ሁሉ አለኝና ያቀረብሁልህን ስጦታዬን እባክህ ተቀበለኝ” አለው። ያዕቆብ አጥብቆ ስለ ለመነው፣ ዔሳው እጅ መንሻውን ተቀበለ። 12.ዔሳውም “በል ተነሥና ጕዟችንን እንቀጥል፤ እኔም እሄዳለሁ” አለው። 13.ያዕቆብ ግን እንዲህ አለው፤ “ጌታዬ፣ እንደምታየው ልጆቹ ይህን ያህል የጠኑ አይደሉም፣ ለሚያጠቡት በጎችና ጥገቶች እንክብካቤ ማድረግ አለብኝ፤ እንስሳቱ ለአንዲት ቀን እንኳ በጥድፊያ ቢነዱ በሙሉ ያልቃሉ። 14.ስለዚህ ጌታዬ፣ አንተ ቀድመኸኝ ሂድ፤ እኔም በምነዳቸው እንስሳትና በልጆቹ ጕዞ ዐቅም ልክ እያዘገምሁ ሴይር ላይ እንገናኛለን።” 15.ዔሳው፣ “እንግዲያስ ከሰዎቼ ጥቂቶቹን ልተውልህ” አለው።
ያዕቆብ ግን፣ “ለምን ብለህ ጌታዬ? በአንተ ዘንድ ሞገስ ማግኘቴ ብቻ ይበቃኛል” አለው።
16.ስለዚህ ዔሳው በዚሁ ዕለት ወደ ሴይር ለመመለስ ተነሣ። 17.ያዕቆብ ግን ወደ ሱኮት ሄደ፤ እዚያም ለራሱ መጠለያ፣ ለከብቶቹም በረት ሠራ፤ ከዚህም የተነሣ የቦታው ስም ሱኮት ተባለ። 18.ያዕቆብ ከሰሜን ምዕራብ መስጴጦምያ ከተመለሰ በኋላ፣ በከነዓን ወዳለችው ወደ ሴኬም በደኅና ደረሰ፤ በከተማዪቱም ፊት ለፊት ሰፈረ። 19.ድንኳኑን የተከለበትንም ቦታ ከኤሞር ልጆች በመቶ ጥሬ ብር ገዛ፤ ኤሞርም የሴኬም አባት ነበር። 20.በዚያም መሠዊያ አቁሞ፣ ኤል ኤሎሄ እስራኤል ብሎ ጠራው።

ምዕራፍ 34

የያዕቆብ ልጅ ተደፈረች

1.ልያ ለያዕቆብ የወለደችለት ሴት ልጅ ዲና፣ አንድ ቀን የዚያን አገር ሴቶች ለማየት ወጣች። 2.ሴኬም የተባለው የአገሩ ገዥ የኤዊያዊ የኤሞር ልጅ ባያት ጊዜ ይዞ በማስገደድ ደፈራት። 3.ልቡ በያዕቆብ ልጅ በዲና ተማረከ፤ ልጅቷንም በጣም ወደዳት፤ በጣፈጠም አንደበት አናገራት። 4.ሴኬምም አባቱን ኤሞርን፣ “ይህችን ልጅ አጋባኝ” አለው። 5.ያዕቆብ፣ ልጁን ዲናን ሴኬም እንዳስነወራት ሰማ፤ በዚህ ጊዜ ወንዶች ልጆቹ ከብቶቹን በመስክ ያግዱ ነበር፤ ያዕቆብም ልጆቹ እስኪመለሱ ድረስ ታግሦ ቈየ። 6.ከዚያም የሴኬም አባት ኤሞር፣ ያዕቆብን ሊያነጋግረው ወጣ። 7.የያዕቆብ ወንዶች ልጆችም የተፈጸመውን ድርጊት እንደ ሰሙ ወዲያውኑ ከመስክ መጡ፤ ሴኬም መደረግ የማይገባውን አስነዋሪ ነገር በእስራኤል ላይ በመፈጸም፣ የያቆብን ልጅ ስለ ደፈረ ዐዘኑ፤ ክፉኛም ተቈጡ። 8.ኤሞር ግን እንዲህ አላቸው፤ “ልጄ ሴኬም ልቡ በልጃችሁ ፍቅር ተነድፏል፤ እባካችሁ እንዲያገባት ፍቀዱለት። 9.በጋብቻ እንተሳሰር፤ ሴት ልጃችሁን ስጡን፤ የእኛንም ሴቶች አግቡ። 10.ዐብራችሁንም መኖር ትችላላችሁ፤ አገራችን አገራችሁ ናት፤ ኑሩባት፤ ነግዱባት፤ ሀብት ንብረትም አፍሩባት።” 11.ሴኬም ደግሞ የዲናን አባትና ወንድሞቿን እንዲህ አላቸው፤ “በእናንተ ዘንድ ሞገስ ላግኝ እንጂ የተጠየቅሁትን ሁሉ እሰጣለሁ፤ 12.ጥሎሽ ብትሉኝ ጥሎሽ፣ ስጦታ ብትሉም የፈለጋችሁትን ያህል እሰጣለሁ፤ ብቻ ልጅቱን እንዳገባ ፍቀዱልኝ።” 13.የያዕቆብ ወንዶች ልጆችም፣ በእኅታቸው በዲና ላይ ስለ ተፈጸመው ነውር፣ የሆዳቸውን በሆዳቸው ይዘው፣ ለሴኬምና ለአባቱ ለኤሞር በተንኰል መልስ ሰጡ፤ 14.እንዲህም አሏቸው፤ “እኅታችንን ላልተገረዘ ሰው ብንሰጥ ውርደት ስለሚሆንብን፣ እንዲህ ያለውን ነገር አናደርገውም። 15.ሆኖም የምንስማማበት አንድ መንገድ ብቻ አለ፤ ይህም ወንዶቻችሁን ሁሉ ገርዛችሁ እኛን የመሰላችሁ እንደ ሆነ ነው። 16.ከዚያ በኋላ ሴቶች ልጆቻችንን እንድርላችኋለን፤ ዐብረን እንኖራለን፤ አንድ ሕዝብም እንሆናለን። 17.በመገረዙ የማትስማሙ ከሆነ ግን ልጃችንን ይዘን እንሄዳለን።” 18.ያቀረቡትም ሐሳብ ለኤሞርና ለልጁ ለሴኬም መልካም መስሎ ታያቸው። 19.ከአባቱ ቤተ ሰብ ሁሉ እጅግ የተከበረው ይህ ወጣት የያዕቆብን ልጅ እጅግ ወድዷት ስለ ነበር፣ ያሉትን ለማድረግ ጊዜ አልወሰደበትም። 20.ስለዚህ ኤሞርና ልጁ ሴኬም ይህንኑ ለወገኖቻቸው ለመንገር ወደ ከተማቸው በር ሄዱ፤ 21.እንዲህም አሏቸው፤ “እነዚህ ሰዎች ወዳጆቻችን ናቸው፤ በአገራችን እንዲኖሩ፣ ተዘዋውረውም እንዲነግዱ እንፍቀድላቸው፤ ምድሪቱ እንደሆን ለእኛም ለእነርሱም ትበቃለች። ሴቶች ልጆቻቸውን እናገባለን፤ እነርሱም የእኛን ሴቶች ያገባሉ። 22.ሆኖም ሰዎቹ ከእኛ ጋራ እንደ አንድ ሕዝብ ሆነው ዐብረውን ለመኖር ፈቃደኞች የሚሆኑት፣ የእኛ ወንዶች እንደ እነርሱ የተገረዙ እንደ ሆነ ብቻ ነው። 23.ታዲያ እንዲህ ብናደርግ ከብታቸው ንብረታቸው፣ እንስሶቻቸው ሁሉ የእኛው ይሆኑ የለምን? ስለዚህ ባሉት እንስማማ፤ እነርሱም ዐብረውን ይኑሩ።” 24.ከከተማዪቱ በር ውጭ የተሰበሰቡት ሁሉ በኤሞርና በልጁ በሴኬም ሐሳብ ተስማሙ፤ በከተማዪቱም ያሉት ወንዶች ሁሉ ተገረዙ። 25.በሦስተኛውም ቀን የሁሉም ቍስል ገና ትኵስ ሳለ ከያዕቆብ ልጆች ሁለቱ፣ የዲና ወንድሞች ስምዖንና ሌዊ፣ ሰይፋቸውን መዝዘው በድንገት ወደ ከተማዪቱ ገብተው ወንዶቹን በሙሉ ገደሏቸው። 26.ኤሞርንና ሴኬምንም በሰይፍ ገድለው፣ እኅታቸውን ዲናን ከሴኬም ቤት አውጥተው ይዘዋት ተመለሱ። 27.የያዕቆብ ልጆች ሁሉ በሬሳ ላይ እየተረማመዱ እኅታቸው የተደፈረችበትን ከተማ ዘረፉ። 28.የበግና የፍየል መንጎቻቸውን፣ ከብቶቻቸውንና አህዮቻቸውን እንዲሁም በከተማዪቱና በአካባቢው የሚገኘውን ንብረታቸውን ሁሉ ወሰዱባቸው፤ 29.ሀብታቸውን ሁሉ ዘርፈው ሴቶቻቸውንና ሕፃኖቻቸውን ሁሉ ማርከው በየቤቱ ያገኙትን ሁሉ ይዘው ሄዱ። 30.ያዕቆብም ስምዖንና ሌዊን እንዲህ አላቸው፤ “በዚህ አገር በሚኖሩት በከነዓናውያንና በፌርዛውያን ዘንድ እንደ ጥንብ አስቈጠራችሁኝ፤ ጭንቀትም እንዲደርስብኝ አድርጋችኋል። እኛ በቍጥር አነስተኞች ነን፤ ተባብረው ቢነሡብኝና ቢያጠቁኝ እኔና ቤተ ሰቤ መጥፋታችን አይደለምን?” 31.እነርሱ ግን፣ “ታዲያ፣ እኅታችንን እንደ ዝሙት ዐዳሪ ይድፈራት?” አሉት።

መዝሙረ ዳዊት

ምዕራፍ 145

1.የዳዊት የምስጋና መዝሙር።
1 አምላኬና ንጉሤ ሆይ፤ ከፍ ከፍ አደርግሃለሁ፤
ስምህን ከዘላለም እስከ ዘላለም እባርካለሁ።
2.በየቀኑ እባርክሃለሁ፤
ስምህንም ከዘላለም እስከ ዘላለም አመሰግናለሁ።
3.እግዚአብሔር ታላቅ ነው፤ እጅግ ሊመሰገንም ይገባዋል፤
ታላቅነቱም አይመረመርም።
4.ሥራህን አንዱ ትውልድ ለሌላው ትውልድ ያስተጋባል፤
ብርቱ ሥራህን ያውጃል።
5.ስለ ግርማህ ውበትና ክብር ይናገራሉ፤
ስለ ድንቅ ሥራህም ያወራሉ።
6.ስለ ድንቅ ሥራህ ብርታት ይነጋገራሉ፤
እኔም ስለ ታላቅነትህ ዐውጃለሁ።
7.የበጎነትህን ብዛት በደስታ ያወሳሉ፤
ስለ ጽድቅህም በእልልታ ይዘምራሉ።
8.እግዚአብሔር ርኅሩኅና መሓሪ፣
ለቍጣ የዘገየ፣ ታማኝነቱም የበዛ ነው።
9.እግዚአብሔር ለሁሉ ቸር ነው፤
ምሕረቱም በፍጥረቱ ሁሉ ላይ ነው።
10.እግዚአብሔር ሆይ፤ ፍጥረትህ ሁሉ ያመሰግንሃል፤
ቅዱሳንህም ይባርኩሃል።
11.ስለ መንግሥትህ ክብር ይናገራሉ፤
ስለ ኀይልህም ይነጋገራሉ፤
12.በዚህም ለሰው ልጆች ብርቱ ሥራህን፣
የመንግሥትህንም ግርማ ክብር ያስታውቃሉ።
13.መንግሥትህ የዘላለም መንግሥት ናት፤
ግዛትህም ለትውልድ ሁሉ ጸንቶ ይኖራል።
እግዚአብሔር ቃሉን ሁሉ ይጠብቃል፤
በሥራውም ሁሉ ቸር ነው።
14.እግዚአብሔር የሚንገዳገዱትን ሁሉ ይደግፋል፤
የወደቁትንም ሁሉ ያነሣል።
15.የሁሉ ዐይን አንተን በተስፋ ይጠብቃል፤
አንተም ምግባቸውን በወቅቱ ትሰጣቸዋለህ።
16.አንተ እጅህን ትዘረጋለህ፤
የሕያዋን ፍጥረታትንም ሁሉ ፍላጎት ታረካለህ።
17.እግዚአብሔር በመንገዱ ሁሉ ጻድቅ፣
በሥራውም ሁሉ ቸር ነው።
18.እግዚአብሔር ለሚጠሩት ሁሉ፣
በእውነት ለሚጠሩት ሁሉ ቅርብ ነው።
19.ለሚፈሩት ፍላጎታቸውን ይፈጽማል፤
ጩኸታቸውን ይሰማል፤ ያድናቸዋልም።
20.እግዚአብሔር የሚወድዱትን ሁሉ ይጠብቃል፤
ክፉዎችን ሁሉ ግን ያጠፋል።
21.አፌ የእግዚአብሔርን ምስጋና ይናገራል፤
ፍጡር ሁሉ ከዘላለም እስከ ዘላለም፣
ቅዱስ ስሙን ይባርክ።

የማርቆስ ወንጌል

ምዕራፍ 13

የመጨረሻው ዘመን ምልክቶች

13፥1-37 ተጓ ምብ – ማቴ 24፥1-51፤ ሉቃ 21፥5-36
1.ከቤተ መቅደስ ሲወጣ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ፣ “መምህር ሆይ፤ ድንጋዮቹ እንዴት እንደ ሆኑ፣ ሕንጻውም እንዴት ውብ እንደ ሆነ እይ!” አለው። 2.ኢየሱስም መልሶ፣ “እነዚህን ታላላቅ ሕንጻዎች ታያለህን? አንዱ ድንጋይ በሌላው ላይ እንደ ሆነ አይቀርም፤ ሁሉም ፈራሽ ነው” አለው። 3.ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ ትይዩ፣ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ተቀምጦ ሳለ ጴጥሮስ፣ ያዕቆብ፣ ዮሐንስና እንድርያስ እንዲህ ሲሉ ጠየቁት፤ 4.“ይህ መቼ እንደሚሆን ንገረን፤ የዚህስ ሁሉ ፍጻሜ ምልክቱ ምንድን ነው?” 5.ኢየሱስም እንዲህ ይላቸው ጀመር፤ “ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ፤ 6.ብዙዎች፣ ‘እኔ እርሱ ነኝ’ እያሉ በስሜ ይመጣሉ፤ ብዙዎችንም ያስታሉ። 7.ስለ ጦርነትና ጦርነትን የሚያናፍስ ወሬ በምትሰሙበት ጊዜ አትደንግጡ፤ ይህማ መሆን አለበት፤ ፍጻሜው ግን ገና ነው። 8.ሕዝብ በሕዝብ ላይ፣ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣል፤ በብዙ ቦታም የመሬት መንቀጥቀጥና ራብ ይሆናል፤ እነዚህ ሁሉ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው። 9.“ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ ለአካባቢ ሸንጎ አሳልፈው ይሰጧችኋል፤ በምኵራቦቻቸውም ይገርፏችኋል፤ ምስክር ትሆኑም ዘንድ በእኔ ምክንያት በገዦችና በነገሥታት ፊት ትቆማላችሁ። 10.አስቀድሞ ግን ወንጌል ለሕዝብ ሁሉ መሰበክ አለበት። 11.ይዘው ለፍርድ አሳልፈው በሚሰጧችሁ ጊዜ ሁሉ፣ በዚያች ሰዓት የሚሰጣችሁን ተናገሩ እንጂ ምን እንናገራለን በማለት አስቀድማችሁ አትጨነቁ፤ የሚናገረው መንፈስ ቅዱስ እንጂ እናንተ አይደላችሁምና። 12.“ወንድም ወንድሙን፣ አባትም ልጁን ለሞት አሳልፎ ይሰጣል፤ ልጆች በወላጆቻቸው ላይ ያምፃሉ፤ ይገድሏቸዋልም። 13.ስለ ስሜ በሰው ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፤ እስከ መጨረሻው የሚጸና ግን ይድናል። 14.“ ‘የጥፋት ርኩሰት’ ስፍራው ባልሆነ ቦታ ቆሞ በምታዩት ጊዜ አንባቢው ያስተውል፤ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራሮች ይሽሹ፤ 15.በቤቱ ጣራ ላይ ያለ አይውረድ፤ ንብረቱንም ለማውጣት ወደ ቤቱ አይግባ፤ 16.በዕርሻ ቦታ ያለ ልብሱን ለመውሰድ አይመለስ። 17.በእነዚያ ቀናት ለነፍሰ ጡሮችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው! 18.ይህም በክረምት እንዳይሆን ጸልዩ፤ 19.በእነዚያ ቀናት፣ እግዚአብሔር ከፈጠረው ከፍጥረት መጀመሪያ እስከ አሁን ድረስ፣ ከዚህም በኋላ ከቶ የማይሆን ታላቅ መከራ ይሆናል። 20.“ጌታ ቀኖቹን ባያሳጥራቸው ኖሮ ማንም ሥጋ ለባሽ ባልዳነ ነበር፤ ስለ መረጣቸው ስለ ምርጦቹ ሲል ግን ቀኖቹን አሳጥሯል። 21.በዚያ ጊዜ ማንም፣ ‘እነሆ፤ ክርስቶስ እዚህ ነው!’ ቢላችሁ ወይም፣ ‘እነሆ፤ እዚያ ነው!’ ቢላችሁ አትመኑ። 22.ሐሰተኛ ክርስቶሶችና ሐሰተኛ ነቢያት ተነሥተው፣ ምልክቶችንና ድንቆችን በማድረግ፣ ቢቻላቸው የተመረጡትን እንኳ ያስታሉ። 23.ስለዚህ ተጠንቀቁ፤ ጊዜው ሳይደርስ ሁሉን ነግሬአችኋለሁ። 24.“በዚያ ጊዜ፣ ከመከራው በኋላ ‘ፀሓይ ትጨልማለች፣
“ ‘ጨረቃም ብርሃኗን አትሰጥም፤
25.ከዋክብት ከሰማይ ይረግፋሉ፤
የሰማይ ኀይላትም ይናወጣሉ።’
26.“በዚያ ጊዜም የሰው ልጅ በታላቅ ኀይልና ግርማ በደመና ሲመጣ ያዩታል። 27.እርሱም መላእክቱን ልኮ ከአራቱ ነፋሳት፣ ከምድር ዳርቻ እስከ ሰማያት ዳርቻ ምርጦቹን ይሰበስባል። 28.“ምሳሌውን ከበለስ ተማሩ፤ ቅርንጫፏ ሲለመልም፣ ቅጠሏ ሲያቈጠቍጥ፣ ያን ጊዜ በጋ እንደ ተቃረበ ታውቃላችሁ፤ 29.እንዲሁ ደግሞ እነዚህ ነገሮች መፈጸማቸውን ስታዩ እንደ ቀረበ፣ በደጅም እንደ ሆነ ዕወቁ። 30.እውነት እላችኋለሁ፣ እነዚህ ነገሮች እስከሚፈጸሙ ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም፤ 31.ሰማይና ምድር ያልፋሉ፣ ቃሌ ግን አያልፍም።

ቀኑና ሰዓቱ አይታወቅም

32.“ነገር ግን ስለዚያች ቀን ወይም ስለዚያች ሰዓት ከአብ በቀር፣ የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ፣ ወልድም ቢሆን ማንም አያውቅም። 33.ስለዚህ ጊዜው መቼ እንደሚሆን ስለማታውቁ ተጠንቀቁ! ትጉ! ጸልዩም! 34.ይህም ቤቱን ለባሮቹ ትቶ፣ እያንዳንዱን አገልጋይ በየሥራ ድርሻው ላይ አሰማርቶ፣ በረኛው ነቅቶ እንዲጠብቅ አዝዞ የሄደውን ሰው ይመስላል። 35.“እንግዲህ የቤቱ ባለቤት በምሽት ወይም በውድቅት፣ በዶሮ ጩኸት ወይም ጎሕ ሲቀድድ እንደሚመጣ አታውቁምና ተግታችሁ ጠብቁ፤ 36.ድንገት ሲመጣ ተኝታችሁ እንዳያገኛችሁ፤ 37.ለእናንተ የምነግራችሁን ለሰው ሁሉ እናገራለሁ፤ ‘ተግታችሁ ጠብቁ!’ ”