ሳምንት 3 · ቀን 11 (ሰኞ)
📅 Meskerem 18, 2019
ኦሪት ዘፍጥረት 28, 29 · የማርቆስ ወንጌል 11
ኦሪት ዘፍጥረት
ምዕራፍ 28
1.ይሥሐቅ ያዕቆብን አስጠርቶ ከመረቀው በኋላ፣ እንዲህ ሲል አዘዘው፤ “ምንም ቢሆን ከነዓናዊት ሴት አታግባ።
2.አሁኑኑ ተነሥተህ በሰሜን ምዕራብ መስጴጦምያ ወደሚኖረው፣ ወደ እናትህ አባት ወደ ባቱኤል ቤት ሂድ፤ እዚያም ከአጎትህ ከላባ ሴቶች ልጆች መካከል አንዲቷን አግባ።
3.ሁሉን ቻይ አምላክ ይባርክህ፤ ብዙ ሕዝብ እስክትሆን ድረስ ልጆች አፍራ፤ ዘርህን ያብዛው።
4.እግዚአብሔር ለአብርሃም ሰጥቶ የነበረውን አንተም በስደት የምትኖርበትን ይህችን ምድር ርስት አድርጎ ያወርስህ ዘንድ፣ ለአብርሃም የሰጠውን በረከት ለአንተና ለዘርህ ይስጥ።”
5.ይሥሐቅም ያዕቆብን በሰሜን ምዕራብ መስጴጦምያ ወደሚኖረው፣ የያዕቆብና የዔሳው እናት የርብቃ ወንድም ወደ ሆነው ወደ ሶርያዊው የባቱኤል ልጅ ወደ ላባ ላከው።
6.ዔሳው፣ ይሥሐቅ ያዕቆብን መርቆ ሚስት እንዲያገባ ወደ ሰሜን ምዕራብ መስጴጦምያ እንደ ላከውና በባረከውም ጊዜ “ከነዓናዊት ሴት አታግባ” ብሎ ትእዛዝ እንደ ሰጠው ሰማ።
7.ያዕቆብ የአባት የእናቱን ፈቃድ ለመፈጸም፣ ወደ መስጴጦምያ መሄዱንም ተረዳ።
8.በዚህም የከነዓናውያን ሴቶች በአባቱ በይሥሐቅ ዘንድ የቱን ያህል የተጠሉ መሆናቸውን ተገነዘበ፤
9.ስለዚህም ወደ እስማኤል ሄደ፣ የአብርሃም ልጅ እስማኤል የወለዳትን፣ የነባዮትን እኅት ማዕሌትን በሚስቶቹ ላይ ተጨማሪ አድርጎ አገባ።
ያዕቆብ በቤቴል ያየው ሕልም
10.ያዕቆብ ከቤርሳቤህ ተነሥቶ ወደ ካራን ሄደ። 11.ወደ አንድ ስፍራ እንደ ደረሰም ፀሓይዋ ጠልቃ ስለ ነበር፣ ዐዳሩን በዚያ አደረገ፤ በአቅራቢያው ከነበሩትም ድንጋዮች አንዱን ተንተርሶ ተኛ። 12.በሕልሙም፣ ጫፉ ሰማይ የሚደርስ መሰላል በምድር ላይ ቆሞ፣ በላዩም የእግዚአብሔር መላእክት ሲወጡና ሲወርዱ አየ። 13.እግዚአብሔርም ከጫፉ ላይ ቆሞ እንዲህ አለ፤ “የአባትህ የአብርሃም አምላክ፣ የይሥሐቅ አምላክ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ የተኛህበትን ምድር ለአንተና ለዘርህ እሰጣለሁ። 14.ዘርህ እንደ ምድር አሸዋ ይበዛል፤ በምዕራብና በምሥራቅ፣ በሰሜንና በደቡብ ትስፋፋለህ፤ የምድርም ሕዝቦች ሁሉ በአንተና በዘርህ አማካይነት ይባረካሉ። 15.እኔ ከአንተ ጋራ ነኝ፤ በምትሄድበት ስፍራ ሁሉ እጠብቅሃለሁ፤ ወደዚህችም ምድር እመልስሃለሁ፤ የሰጠሁህን ተስፋ እስከምፈጽምልህ ድረስ አልተውህም።” 16.ያዕቆብም ከእንቅልፉ ሲነቃ፣ “በእውነት እግዚአብሔር በዚህ ስፍራ አለ፤ እኔ ግን ይህን አላወቅሁም ነበር” አለ። 17.እርሱም በፍርሀት፣ “ይህ ስፍራ እንዴት የሚያስፈራ ነው! ይህስ ሌላ ሳይሆን የእግዚአብሔር ቤት መሆን አለበት፤ የሰማይ ደጅ ነው” አለ። 18.ያዕቆብም በማግስቱም ማልዶ ተነሣ፣ ተንተርሶት ያደረውን ድንጋይ አንሥቶ እንደ ሐውልት አቆመው፤ በዐናቱም ላይ የወይራ ዘይት አፈሰሰበት። 19.ያን ቦታ ቤቴል ብሎ ሰየመው፤ ቀደም ሲል ግን የከተማዪቱ ስም ሎዛ ነበር። 20.ከዚያም ያዕቆብ እንዲህ ሲል ተሳለ፤ “እግዚአብሔር ከእኔ ጋራ ቢሆን በምሄድበትም መንገድ ቢጠብቀኝ፣ የምበላው ምግብ፣ የምለብሰው ልብስ ቢሰጠኝ 21.ወደ አባቴ ቤትም በደኅና ቢመልሰኝ፣ እግዚአብሔር አምላኬ ይሆናል፤ 22.ይህ ሐውልት አድርጌ ያቆምሁት ድንጋይ፣ የእግዚአብሔር ቤት ይሆናል፤ ከምትሰጠኝም ሀብት ሁሉ፣ ከዐሥር እጅ አንዱን ለአንተ እሰጣለሁ።”ምዕራፍ 29
ያዕቆብ መስጴጦምያ ደረሰ
1.ያዕቆብም ጕዞውን ቀጠለ፤ የምሥራቅም ሰዎች ወደሚኖሩበት ምድር ደረሰ። 2.እዚያም በአንድ ሜዳ ላይ ሦስት የበግ መንጋዎች ተኝተው በነበሩበት አጠገብ የውሃ ጕድጓድ አየ። የበግ መንጋዎቹ የሚጠጡት ከዚሁ ጕድጓድ ሲሆን፣ የጕድጓዱም አፍ ትልቅ የድንጋይ መክደኛ ነበረው። 3.መንጎቹ ሁሉ በጕድጓዱ አጠገብ በሚሰበሰቡበት ጊዜ፣ እረኞች ድንጋዩን ያንከባልሉና በጎቹን ውሃ ያጠጣሉ፤ ከዚያም ድንጋዩን በቦታው መልሰው የጕድጓዱን አፍ ይገጥሙታል። 4.ያዕቆብም እረኞቹን፣ “ወንድሞቼ፤ ከየት ነው የመጣችሁት?” ብሎ ጠየቃቸው።እነርሱም፣ “ከካራን ነን” አሉት። 5.እርሱም፣ “የናኮርን የልጅ ልጅ ላባን ታውቁታላችሁ?” አላቸው።
እነርሱም፣ “አዎን እናውቀዋለን” አሉት። 6.ያዕቆብም፣ “ለመሆኑ ደኅና ነው?” አላቸው።
እነርሱም፣ “አዎን ደኅና ነው፤ ልጁም ራሔል እነሆ፤ በጎች እየነዳች በመምጣት ላይ ናት” አሉት። 7.ያዕቆብም፣ “እንደምታዩት ጊዜው ገና ነው፤ መንጎቹ የሚገቡበት ሰዓት አይደለም፤ ታዲያ፣ ለምን በጎቹን አጠጥታችሁ ወደ ግጦሽ አትመልሷቸውም?” አላቸው። 8.እነርሱም፣ “መንጎቹ ሁሉ ተሰብስበው ድንጋዩ ከጕድጓዱ አፍ ካልተንከባለለ በቀር አንችልም፤ ከዚያም በጎቹን እናጠጣቸዋለን” አሉ። 9.ያዕቆብ ከእረኞቹ ጋራ በመነጋገር ላይ ሳለ፣ ራሔል፣ እረኛ ነበረችና የአባቷን በጎች እየነዳች መጣች። 10.ያዕቆብ የእናቱን ወንድም የላባን ልጅ ራሔልን፣ እንዲሁም የአጎቱን የላባን በጎች ሲያይ፣ ወደ ጕድጓዱ ሄዶ ድንጋዩን ከጕድጓዱ አፍ አንከባለለ፤ የአጎቱንም በጎች አጠጣ። 11.ከዚያም ያዕቆብ ራሔልን ሳማት፤ ድምፁንም ከፍ አድርጎ አለቀሰ። 12.ያዕቆብም የአባቷ ዘመድና የርብቃ ልጅ መሆኑን ለራሔል ነገራት፤ እርሷም ሮጣ ሄዳ ይህንኑ ለአባቷ ነገረችው። 13.ላባም የእኅቱ ልጅ ያዕቆብ መምጣቱን እንደ ሰማ ሊቀበለው ፈጥኖ ወጣ። ዐቅፎ ከሳመውም በኋላ፣ ወደ ቤቱ ይዞት ሄደ። ያዕቆብም ሁኔታውን ሁሉ ለላባ ነገረው። 14.ላባም ያዕቆብን፣ “አንተማ የዐጥንቴ ፍላጭ፣ የሥጋዬ ቍራጭ ነህ” አለው።
ያዕቆብ ልያንና ራሔልን አገባ
ያዕቆብ አንድ ወር ሙሉ ዐብሮት ከተቀመጠ በኋላ፣ 15.ላባ ያዕቆብን፣ “ዘመዴ በመሆንህ ብቻ በነጻ ልታገለግለን አይገባምና ደመወዝህ ምንድን ነው?” አለው። 16.ላባ ሁለት ሴቶች ልጆች ነበሩት፤ የታላቂቱ ስም ልያ የታናሺቱ ራሔል ነበር። 17.ልያ ዐይነ ልም ስትሆን ራሔል ግን ቁመናዋ ያማረ መልኳም የተዋበ ነበር። 18.ያዕቆብም ራሔልን ስለ ወደዳት፣ “ታናሺቱ ልጅህን ራሔልን የምትድርልኝ ከሆነ ሰባት ዓመት አገለግላለሁ” አለው። 19.ላባም መልሶ፣ “ለሌላ ሰው ከምድራት ላንተ ብድራት ይሻላል፤ እዚሁ ዐብረኸኝ ተቀመጥ” አለው። 20.ያዕቆብም ራሔልን ለማግኘት ሲል ሰባት ዓመት አገለገለ፤ ለርሷ ካለው ፍቅር የተነሣ፣ ሰባት ዓመት እንደ ጥቂት ቀን ሆኖ ታየው። 21.ከዚያም ያዕቆብ ላባን፣ “እነሆ፤ የተባባልነው ጊዜ አብቅቷል፤ ስለዚህ ሚስቴን አስረክበኝና የባልና የሚስት ወጋችንን እናድርስ” አለው። 22.ስለዚህ ላባ የአካባቢውን ሰዎች በሙሉ ጠርቶ ሰርግ አበላ። 23.ሲመሽ ግን ላባ ልጁን ልያን አምጥቶ ለያዕቆብ ሰጠው፤ ያዕቆብም ዐብሯት ተኛ። 24.ላባም ዘለፋ የተባለች አገልጋዩን ለልጁ ለልያ ደንገጥር እንድትሆን ሰጣት። 25.ሲነጋም እነሆ፤ ልያ ሆና ተገኘች፤ ስለዚህም ያዕቆብ ላባን፣ “ምነው፣ እንዲህ ጕድ ሠራኸኝ? ያገለገልሁህ ለራሔል ብዬ አልነበረምን? ታዲያ ለምን ታታልለኛለህ?” አለው። 26.ላባም እንዲህ አለው፤ “በአገራችን ታላቋ እያለች ታናሿን መዳር የተለመደ አይደለም፤ 27.ይህን የጫጕላ ሳምንት ፈጽምና ሌላ ሰባት ዓመት የምታገለግለን ከሆነ፣ ታናሺቱን ደግሞ እንሰጥሃለን።” 28.ያዕቆብም በነገሩ ተስማማ፤ ከልያ ጋራ ተሞሽሮ ሰባት ቀን ከቈየ በኋላ፣ ላባ ልጁን ራሔልን ለያዕቆብ ዳረለት፤ 29.ባላ የተባለች አገልጋዩንም ደንገጥር እንድትሆናት ለራሔል ሰጣት። 30.ያዕቆብ ከራሔልም ጋራ ተኛ፤ ራሔልን ከልያ አብልጦ ወደዳት፤ ከዚያም የተነሣ ሌላ ሰባት ዓመት ላባን አገለገለው። 31.እግዚአብሔር ልያ እንዳልተወደደች ባየ ጊዜ ማሕፀኗን ከፈተላት፤ ራሔል ግን መካን ነበረች። 32.ልያ ፀነሰች፤ ወንድ ልጅም ወለደች፤ “እግዚአብሔር መከራዬን ስለ ተመለከተልኝ፣ ከእንግዲህ ባሌ ይወድደኛል” ስትል ስሙን ሮቤል አለችው። 33.እንደ ገናም ፀንሳ ወለደች፤ እርሷም “እግዚአብሔር እንዳልተወደድኩ ሰምቶ ይህን ልጅ በድጋሚ ሰጠኝ” አለች። ከዚያም የተነሣ ስምዖን ብላ ጠራችው። 34.አሁንም እንደ ገና ፀንሳ ወንድ ልጅ ወለደች፤ እርሷም፣ ሦስት ወንዶች ልጆች ስለ ወለድሁለት “ከእንግዲህ ባሌ ያቀርበኛል” አለች፤ ስለዚህ ሌዊ ብላ ጠራችው። 35.እንደ ገና ፀንሳ አሁንም ወንድ ልጅ ወለደች፤ እርሷም፣ “እንግዲህ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ” አለች፤ ስሙንም ይሁዳ ብላ ጠራችው። ከዚያም በኋላ መውለድ አቆመች።
የማርቆስ ወንጌል
ምዕራፍ 11
ኢየሱስ በታላቅ ክብር ወደ ኢየሩሳሌም ገባ
11፥1-10 ተጓ ምብ – ማቴ 21፥1-9፤ ሉቃ 19፥29-38
11፥7-10 ተጓ ምብ – ዮሐ 12፥12-15
1.ወደ ኢየሩሳሌም በደብረ ዘይት ተራራ አጠገብ ወዳሉት ወደ ቤተ ፋጌና ወደ ቢታንያ በቀረቡ ጊዜ፣ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን እንዲህ በማለት ላካቸው፤
2.“በፊታችሁ ወዳለው መንደር ሂዱ፣ ሰው ተቀምጦበት የማያውቅ የአህያ ውርንጫ እዚያ ታስሮ ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁ አምጡት፤
3.ማንም፣ ‘ምን ማድረጋችሁ ነው?’ ቢላችሁ፣ ‘ለጌታ ያስፈልገዋል፤ እርሱም ወዲያውኑ መልሶ ይልከዋል’ በሉት።”
4.እነርሱም ሄዱ፤ በአንድ ቤት በራፍ መንገድ ላይ የአህያ ውርንጫ ታስሮ አገኙ፤ ፈቱትም።
5.በዚያ ከቆሙት አንዳንድ ሰዎች፣ “ውርንጫውን የምትፈቱት ለምንድን ነው?” አሏቸው።
6.ደቀ መዛሙርቱም ኢየሱስ ያላቸውን ለሰዎቹ በነገሯቸው ጊዜ ፈቀዱላቸው።
7.ውርንጫውንም ወደ ኢየሱስ አምጥተው ልብሶቻቸውን በጀርባው ላይ አደረጉ፤ እርሱም ተቀመጠበት።
8.ብዙ ሰዎች ልብሶቻቸውን በመንገድ ላይ አነጠፉ፤ ሌሎች ደግሞ ከሜዳ ቅርንጫፍ እየቈረጡ ያነጥፉ ነበር።
9.የቀደሙትና የተከተሉትም በታላቅ ድምፅ እንዲህ ይሉ ነበር፤“ሆሳዕና!”
“በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው!” 10.“የምትመጣው የአባታችን የዳዊት መንግሥት የተባረከች ናት!”
“ሆሳዕና በአርያም!” 11.ኢየሱስም ኢየሩሳሌም ደረሰ፤ ከዚያም ወደ ቤተ መቅደስ ገባ፤ በዙሪያው ያለውንም ሁሉ ተመለከተ፤ ቀኑም ስለ መሸ ከዐሥራ ሁለቱ ጋራ ወደ ቢታንያ ወጣ።
ኢየሱስ ቤተ መቅደስን አጸዳ
11፥12-14 ተጓ ምብ – ማቴ 21፥18-22
11፥15-18 ተጓ ምብ – ማቴ 21፥12-16፤ ሉቃ 19፥45-47፤ ዮሐ 2፥13-16
12.በማግስቱም ከቢታንያ ሲወጡ ኢየሱስ ተራበ።
13.እርሱም ቅጠል ያላት የበለስ ዛፍ ከሩቅ አየ፤ ምናልባት ፍሬ ይገኝባት እንደ ሆነ ብሎ ወደ እርሷ መጣ፤ ነገር ግን የበለስ ወራት አልነበረምና ከቅጠል በቀር ምንም አላገኘባትም።
14.ከዚያም ዛፏን፣ “ከአሁን ጀምሮ ለዘላለም ማንም ከአንቺ ፍሬ አይብላ” አላት። ደቀ መዛሙርቱም ይህን ሲናገር ሰሙ።
15.ወደ ኢየሩሳሌምም መጡ፤ ከዚያም ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ፣ የሚሸጡትንና የሚገዙትን ያስወጣ ጀመር። የገንዘብ ለዋጮችን ጠረጴዛና የርግብ ሻጮችን መቀመጫ ገለባበጠ፤
16.ማንም ዕቃ ተሸክሞ በቤተ መቅደሱ ቅጥር ግቢ ውስጥ እንዳያልፍ ከለከለ።
17.ሲያስተምራቸውም፣ “ ‘ቤቴ ለሕዝቦች ሁሉ የጸሎት ቤት ይባላል’ ተብሎ አልተጻፈምን? እናንተ ግን ‘የወንበዴዎች ዋሻ አደረጋችሁት!’” አላቸው።
18.የካህናት አለቆችና ጸሐፍትም፣ ይህን ሲሰሙ እንዴት እንደሚያጠፉት መንገድ ይፈልጉ ጀመር፤ ሕዝቡ ሁሉ በትምህርቱ በመገረማቸው ፈርተውታልና።
19.በመሸም ጊዜ ከከተማዪቱ ወጥተው ሄዱ።
የበለሷ ዛፍ ደረቀች
11፥20-24 ተጓ ምብ – ማቴ 21፥19-22
20.በማግስቱም ጧት በመንገድ ሲያልፉ፣ በለሲቱ ከነሥሯ ደርቃ አዩ።
21.ጴጥሮስ ነገሩ ትዝ አለውና ኢየሱስን፣ “መምህር ሆይ፤ እነሆ፤ የረገምሃት በለስ ደርቃለች!” አለው።
22.ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “በእግዚአብሔር እመኑ፤
23.እውነት እላችኋለሁ፤ ማንም ይህን ተራራ፣ ‘ተነቅለህ ወደ ባሕር ተወርወር’ ቢለውና ይህንም በልቡ ሳይጠራጠር ቢያምን ይሆንለታል።
24.ስለዚህ በጸሎት የምትለምኑትን ሁሉ እንደ ተቀበላችሁት አድርጋችሁ እመኑ፤ ይሆንላችሁማል።
25.እንዲሁም ለጸሎት በምትቆሙበት ጊዜ፣ የሰማዩ አባታችሁ በደላችሁን ይቅር እንዲልላችሁ፣ እናንተም በሰው ላይ ያላችሁን ሁሉ ይቅር በሉ። [
26.ይቅር ባትሉ ግን የሰማዩ አባታችሁ በደላችሁን ይቅር አይላችሁም።”]
በኢየሱስ ሥልጣን ላይ ጥያቄ ተነሣ
11፥27-33 ተጓ ምብ – ማቴ 21፥23-27፤ ሉቃ 20፥1-8
27.እንደ ገና ወደ ኢየሩሳሌም መጡ፤ ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ ቅጥር ግቢ ውስጥ በሚዘዋወርበት ጊዜ፣ የካህናት አለቆች፣ ጸሐፍትና የሕዝብ ሽማግሌዎች ወደ እርሱ ቀርበው፣
28.“እነዚህን ነገሮች የምታደርገው በምን ሥልጣን ነው? እነዚህን እንድታደርግስ ይህን ሥልጣን የሰጠህ ማን ነው?” አሉት።
29.ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “እኔም አንድ ጥያቄ ልጠይቃችሁ፤ መልሱልኝ፤ እኔም እነዚህን ነገሮች በምን ሥልጣን እንደማደርግ እነግራችኋለሁ።
30.የዮሐንስ ጥምቀት ከሰማይ ነበረችን ወይስ ከሰው? መልሱልኝ!”
31.እነርሱም እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ፤ “ ‘ከሰማይ ነው’ ብንል፣ ‘ታዲያ ለምን አላመናችሁበትም?’ ይለናል፤
32.‘ከሰው ነው’ ብንል …” ሕዝቡ ሁሉ ዮሐንስ እውነተኛ ነቢይ እንደ ሆነ ይቈጥር ስለ ነበር ፈሩ።
33.ስለዚህ ለኢየሱስ፣ “አናውቅም” ብለው መለሱለት።ኢየሱስም፣ “እንግዲያውስ እኔም እነዚህን ነገሮች በምን ሥልጣን እንደማደርግ አልነግራችሁም” አላቸው።