ሳምንት 8 · ቀን 40 (አርብ)
📅 Tikimt 27, 2019
ኦሪት ዘሌዋውያን 21, 22, 23 · ወደ ዕብራውያን 8
ኦሪት ዘሌዋውያን
ምዕራፍ 21
ለካህናት የተሰጠ መመሪያ
1.እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ለካህናቱ ለአሮን ልጆች ንገራቸው፤ እንዲህም በላቸው፤ ‘ማንኛውም ሰው ከዘመዶቹ መካከል ስለ ሞተው ሰው ራሱን አያርክስ፤ 2.ነገር ግን የቅርብ ዘመዶቹ ስለ ሆኑት እናቱ፣ አባቱ፣ ወንድ ልጁ፣ ሴት ልጁ፣ ወይም ወንድሙ፣ 3.እንዲሁም ባለማግባቷ ከርሱ ጋራ ስለምትኖር እኅቱ ራሱን ሊያረክስ ይችላል። 4.ከርሱ ጋራ በጋብቻ ለሚዛመዱት ግን ራሱን አያርክስ። 5.“ ‘ካህናት ዐናታቸውን አይላጩ፤ የጢማቸውን ዙሪያ አይላጩ፤ ሰውነታቸውንም አይንጩ፤ 6.ለአምላካቸው የተቀደሱ ይሁኑ፤ የአምላካቸውንም ስም አያርክሱ። ለእግዚአብሔር በእሳት የሚቀርበውን መሥዋዕት የአምላካቸውን ምግብ ስለሚያቀርቡ ቅዱሳን ይሁኑ። 7.“ ‘ካህናት በዝሙት የረከሱትንም ሆነ ከባሎቻቸው የተፋቱትን ሴቶች አያግቡ፤ ለእግዚአብሔር የተቀደሱ ናቸውና። 8.የአምላክህን ምግብ የሚያቀርብ ነውና ቀድሰው፤ እኔ የምቀድሳችሁ እግዚአብሔር ቅዱስ ነኝና ቅዱስ ይሁንላችሁ። 9.“ ‘የካህን ሴት ልጅ ዝሙት ዐዳሪ ሆና ራሷን ብታረክስ፣ አባቷን ታዋርዳለች፤ በእሳት ትቃጠል። 10.“ ‘ከወንድሞቹ መካከል ተለይቶ በራሱ ላይ ዘይት የፈሰሰበትና የክህነት ልብስ እንዲለብስ የተቀባው ካህን የራስ ጠጕሩን አይንጭ፤ ወይም ልብሱን አይቅደድ። 11.አስከሬን ወዳለበት ስፍራ አይግባ፤ ስለ አባቱም ሆነ ስለ እናቱ ራሱን አያርክስ፤ 12.የተቀደሰበት የአምላኩ የቅብዐት ዘይት በላዩ ስለ ሆነ የአምላኩን መቅደስ ትቶ በመሄድ መቅደሱን አያርክስ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 13.“ ‘ካህኑ የሚያገባት ሴት ድንግል ትሁን። 14.ባል የሞተባትን፣ የተፋታችውን ወይም በዝሙት ዐዳሪነት የረከሰችውን ሴት አያግባ፤ ነገር ግን ከወገኖቹ መካከል ድንግሊቱን ያግባ። 15.በወገኖቹ መካከል ዘሩን አያርክስ። እርሱን የምቀድሰው እኔ እግዚአብሔር ነኝ።’ ” 16.እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 17.“አሮንን እንዲህ በለው፤ ‘በሚቀጥሉት ትውልዶች ከዘርህ እንከን ያለበት ማንኛውም ሰው የአምላኩን ምግብ ይሠዋ ዘንድ አይቅረብ። 18.ዕውር ወይም ዐንካሳ፣ የፊቱ ገጽታ ወይም የሰውነቱ ቅርጽ የተበላሸ ማንኛውም የአካል ጕድለት ያለበት ሰው አይቅረብ። 19.እንዲሁም እግሩ ወይም እጁ ሽባ የሆነ፣ 20.ጐባጣ ወይም ድንክ፣ ማንኛውም ዐይነት የዐይን እንከን ያለበት፣ የሚያዥ ቍስል ወይም እከክ ያለበት ወይም ጃንደረባ አይቅረብ። 21.ከካህኑ ከአሮን ዘር ማንኛውም ዐይነት የአካል ጕድለት ያለበት ሰው ለእግዚአብሔር በእሳት የሚቀርብ መሥዋዕት ሊያቀርብ አይምጣ፤ እንከን ያለበት ስለ ሆነ፣ የአምላኩን ምግብ ለማቅረብ አይምጣ። 22.እርሱም የተቀደሰውንና እጅግ ቅዱስ የሆነውን የአምላኩን ምግብ ይብላ። 23.ነገር ግን እንከን ያለበት ስለ ሆነ መቅደሴን እንዳያረክስ ወደ መጋረጃው አይቅረብ ወይም ወደ መሠዊያው አይጠጋ፤ የምቀድሳቸው እኔ እግዚአብሔር ነኝ።’ ” 24.ሙሴም ይህን ለአሮን፣ ለልጆቹና ለእስራኤላውያን ሁሉ ነገራቸው።ምዕራፍ 22
1.እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤
2.“እስራኤላውያን ቀድሰው ለእኔ የለዩትን ቅዱስ መሥዋዕት በአክብሮት ባለመያዝ፣ ቅዱስ ስሜን እንዳያረክሱ ለአሮንና ለልጆቹ ንገራቸው፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
3.“እንዲህም በላቸው፤ ‘በሚቀጥሉት ትውልዶች ከዘርህ በሥርዐቱ መሠረት ንጹሕ ያልሆነ ማንኛውም ሰው፣ እስራኤላውያን ለእግዚአብሔር ለይተው ወዳቀረቡት ቅዱስ መሥዋዕት ቢቀርብ ያ ሰው ከፊቴ ይወገድ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
4.“ ‘ከአሮን ዘር ተላላፊ የቈዳ በሽታ ያለበት ወይም ከሰውነቱ ፈሳሽ ነገር የሚወጣው ማንኛውም ሰው እስኪነጻ ድረስ ቅዱሱን መሥዋዕት አይብላ፤ እንዲሁም በአስከሬን የረከሰውን ነገር ወይም የዘር ፈሳሽ ያለበትን ሰው ቢነካ፣
5.ወይም በደረቱ የሚሳብ የሚያረክስ ነገርን ወይም የሚያረክስ ማንኛውንም ሰው ቢነካ፣ የቱንም ዐይነት ርኩሰት ቢሆን፣
6.እንዲህ ያለውን ማንኛውንም ነገር የሚነካ እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል፤ ሰውነቱንም በውሃ ካልታጠበ፣ የተቀደሰውን መሥዋዕት አይብላ።
7.ፀሓይ በምትጠልቅበት ጊዜ ንጹሕ ይሆናል፤ ከዚያም በኋላ የተቀደሰውን መሥዋዕት መብላት ይችላል፤ ምግቡ ነውና።
8.እንዳይረክስ ማንኛውንም ሞቶ የተገኘውን ወይም አውሬ የዘነጠለውን አይብላ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
9.“ ‘ካህናት ትእዛዞቼን በመናቅ በደለኛ እንዳይሆኑና እንዳይሞቱ ይጠብቋቸው፤ የምቀድሳቸው እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
10.“ ‘ከካህን ቤተ ሰብ በቀር የካህኑ እንግዳም ሆነ ቅጥር ሠራተኛ የተቀደሰውን መሥዋዕት አይብላ።
11.ነገር ግን ካህኑ በገንዘብ የገዛው ወይም በቤቱ የተወለደ ባሪያ ቢኖረው፣ ያ ባሪያ ከካህኑ ድርሻ መብላት ይችላል።
12.የካህን ልጅ፣ ካህን ያልሆነ ሌላ ሰው ካገባች፣ ከተቀደሰው መሥዋዕት መብላት አትችልም።
13.ይሁን እንጂ የካህኑ ልጅ ባሏ ቢሞት ወይም ብትፋታ፣ ልጆችም ባይኖሯትና እንደ ልጅነት ጊዜዋ በአባቷ ቤት ለመኖር ብትመለስ፣ ከአባቷ ድርሻ መብላት ትችላለች፤ ያልተፈቀደለት ሰው ግን ከተቀደሰው መሥዋዕት መብላት አይችልም።
14.“ ‘ማንኛውም ሰው ባለማወቅ የተቀደሰውን መሥዋዕት ቢበላ፣ የመሥዋዕቱን አንድ ዐምስተኛ ጨምሮ ለካህኑ ይተካ።
15.እስራኤላውያን ለእግዚአብሔር የሚያቀርቡትን የተቀደሰ መሥዋዕት ካህናቱ አያርክሱት፤
16.ይህንኑ የተቀደሰ መሥዋዕት እንዲበሉና ቅጣት የሚያስከትል በደል እንዲፈጽሙ አያድርጉ፤ የምቀድሳቸው እኔ እግዚአብሔር ነኝ።’ ”
ለእግዚአብሔር መቅረብ የማይገባው መሥዋዕት
17.እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 18.“ለአሮን፣ ለልጆቹና ለእስራኤላውያን በሙሉ እንዲህ ብለህ ተናገር፤ ‘ከእናንተ ማንኛውም እስራኤላዊ ወይም በእስራኤል የሚኖር መጻተኛ ስእለት ለመፈጸም ወይም የበጎ ፈቃድ ስጦታ ለማበርከት ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት የሚያቀርብ ቢሆን፣ 19.መሥዋዕታችሁ ተቀባይነት እንዲኖረው ከላም ወገን ወይም ከበጎች ወይም ከፍየሎች እንከን የሌለበትን ተባዕት ያቅርብ። 20.እንከን ያለበትን ማንኛውንም ነገር አታቅርቡ፤ መሥዋዕታችሁ ተቀባይነት አይኖረውምና። 21.ማንኛውም ሰው ስእለት ለመፈጸም ወይም የበጎ ፈቃድ ስጦታ ለማበርከት ከላም ወይም ከበግ ወይም ከፍየል መንጋ ለእግዚአብሔር የኅብረት መሥዋዕት ሲያቀርብ፣ ተቀባይነት ይኖረው ዘንድ ፍጹም የሆነውንና እንከን የሌለበትን ያቅርብ። 22.ዕውር ወይም ሰባራ ወይም ጕንድሽ ወይም ማንኛውንም ዐይነት እከክ ወይም ቋቍቻ ወይም የሚመግል ቍስል ያለበትን እንስሳ ለእግዚአብሔር አታቅርቡ፤ ከእነዚህ መካከል የትኛውንም በመሠዊያው ላይ በእሳት የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር አታቅርቡ። 23.አካሉ ከመጠን በላይ የረዘመን ወይም ያጠረን በሬ ወይም በግ የበጎ ፈቃድ ስጦታ አድርጋችሁ ማቅረብ ትችላላችሁ፤ ይሁን እንጂ ስእለት ለመፈጸም ተቀባይነት አይኖረውም። 24.አባለዘሩ የተቀጠቀጠ ወይም የተኰላሸ፣ የተሰነጠቀ ወይም የተቈረጠ ማንኛውንም እንስሳ ለእግዚአብሔር አታቅርቡ፤ እነዚህንም በምድራችሁ አትሠዉ። 25.እንደነዚህ ያሉትን እንስሳት ከባዕዳን በመቀበል ለአምላካችሁ ምግብ አድርጋችሁ አታቅርቡ፤ ነውር ስላለባቸው ፍጹም አይደሉምና ተቀባይነት አይኖራቸውም።’ ” 26.እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 27.“ጥጃ ወይም የበግ ግልገል ወይም የፍየል ግልገል በሚወለድበት ጊዜ ሰባት ቀን ከእናቱ ጋራ ይቈይ፤ ከስምንተኛው ቀን ጀምሮ ግን ተቀባይነት ያለው ለእግዚአብሔር በእሳት የሚቀርብ መሥዋዕት ይሆናል። 28.ላምን ከጥጃዋ፣ በግንም ከግልገሏ ጋራ በአንድ ቀን አትረዱ። 29.“ለእግዚአብሔር የምስጋና መሥዋዕት በምታቀርቡበት ጊዜ፣ መሥዋዕታችሁ ተቀባይነት እንዲኖረው አድርጋችሁ አቅርቡት። 30.መሥዋዕቱ በዚያ ዕለት ይበላ፤ ለሚቀጥለውም ቀን አታሳድሩ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 31.“ትእዛዞቼን ጠብቁ፤ አድርጓቸውም፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 32.ቅዱሱን ስሜን አታርክሱ፤ እኔ ቅዱስ መሆኔ በእስራኤላውያን ዘንድ ይታወቅ፤ የምቀድሳችሁ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 33.አምላካችሁ እሆን ዘንድ ከግብጽ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።”ምዕራፍ 23
1.እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤
2.“ለእስራኤላውያን እንዲህ ብለህ ተናገር፤ ‘የተቀደሱ ጉባኤዎች ብላችሁ የምትዋጇቸው የእግዚአብሔር በዓላት እነዚህ ናቸው።
ሰንበት
3.“ ‘ሥራ የምትሠሩበት ስድስት ቀን አላችሁ፤ ሰባተኛው ቀን ግን የዕረፍት ሰንበት፣ የተቀደሰ ጉባኤ ዕለት ነው። የእግዚአብሔር ሰንበት ስለ ሆነ፣ በምትኖሩበት ስፍራ ሁሉ ምንም ዐይነት ሥራ አትሥሩበት።የፋሲካና የቂጣ በዓል
23፥4-8 ተጓ ምብ – ዘፀ 12፥14-20፤ ዘኍ 28፥16-25፤ ዘዳ 16፥1-8
4.“ ‘የተመረጡ የእግዚአብሔር በዓላት ብላችሁ በተወሰኑላቸው ጊዜያት የምታውጇቸው የተቀደሱ ጉባኤዎች እነዚህ ናቸው፤
5.የመጀመሪያው ወር በገባ በዐሥራ አራተኛው ቀን ምሽት የእግዚአብሔር ፋሲካ በዓል ይጀመራል።
6.በዚያው ወር በዐሥራ ዐምስተኛው ቀን የእግዚአብሔር የቂጣ በዓል ይጀመራል፤ ለሰባት ቀንም ቂጣ ብሉ።
7.በመጀመሪያው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ አድርጉ፤ የዘወትር ተግባራችሁንም አታከናውኑ።
8.ሰባት ቀን በእሳት የሚቃጠል መሥዋዕት ለእግዚአብሔር አቅርቡ፤ በሰባተኛው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ አድርጉ፤ በዚያ ዕለት የተለመደ ተግባራችሁን አታከናውኑ።’ ”
የበኵራት ስጦታ በዓል
9.እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 10.“ለእስራኤላውያን እንዲህ ብለህ ተናገር፤ ‘እኔ ወደምሰጣችሁ ምድር ገብታችሁ መከር በምትሰበስቡበት ጊዜ ከሰበሰባችሁት እህል የመጀመሪያውን ነዶ ለካህኑ አቅርቡ፤ 11.ነዶው ተቀባይነት እንዲያገኝላችሁም በእግዚአብሔር ፊት ይወዝውዘው፤ ካህኑ ነዶውን የሚወዘውዘው በሰንበት ቀን ማግስት ነው። 12.ነዶውን በምትወዘውዙበት ቀን እንከን የሌለበትን የአንድ ዓመት ተባዕት የበግ ጠቦት የሚቃጠል መሥዋዕት እንዲሆን ለእግዚአብሔር አቅርቡ፤ 13.ከዚህም ጋራ ለእግዚአብሔር በእሳት የሚቀርብ፣ ሽታውም ደስ የሚያሰኝ እንዲሆን ሁለት ዐሥረኛ የኢፍ መስፈሪያ በዘይት የተለወሰ የላመ ዱቄት ለእህል ቍርባን፣ አንድ አራተኛ የሂን መስፈሪያ የወይን ጠጅ ለመጠጥ ቍርባን አቅርቡ። 14.ስጦታውን ለአምላካችሁ እስከምታቀርቡበት እስከዚያ ቀን ድረስ፣ እንጀራም ቢሆን ቈሎ ወይም እሸት አትብሉ፤ ይህም በምትኖሩበት ስፍራ ሁሉ ለሚመጡት ትውልዶች የዘላለም ሥርዐት ነው።የመከር በዓል
23፥15-22 ተጓ ምብ – ዘኍ 28፥26-31፤ ዘዳ 16፥9-12
15.“ ‘የሚወዘወዘውን የነዶ መሥዋዕት ካቀረባችሁበት የሰንበት ማግስት አንሥታችሁ ሰባት ሙሉ ሳምንታት ቍጠሩ።
16.እስከ ሰባተኛው ሰንበት ማግስት ድረስ ዐምሳ ቀን ቍጠሩ፤ ከዚያም የአዲስ እህል ቍርባን ለእግዚአብሔር አቅርቡ።
17.በሁለት ዐሥረኛ የኢፍ መስፈሪያ የላመ ዱቄት፣ በእርሾ የተጋገረ ሁለት እንጀራ ለሚወዘወዝ መሥዋዕት፣ የበኵራት ስጦታ እንዲሆን ከየቤታችሁ ለእግዚአብሔር አምጡ።
18.ከእንጀራውም ጋራ ሰባት ነውር የሌለባቸው የአንድ ዓመት እንከን የሌለው ተባዕት የበግ ጠቦቶች፣ አንድ ወይፈንና ሁለት አውራ በጎች አቅርቡ፤ እነዚህም ከእህል ቍርባናቸውና ከመጠጥ ቍርባናቸው ጋራ ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት ይሆናሉ፤ ይህም በእሳት የሚቀርብ ሽታውም እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕት ነው።
19.እንዲሁም አንድ ተባዕት ፍየል ለኀጢአት መሥዋዕት፣ ሁለት የአንድ ዓመት ተባዕት ጠቦቶችም ለኅብረት መሥዋዕት አቅርቡ።
20.ካህኑም ሁለቱን የበግ ጠቦቶች ከበኵራቱ እንጀራ ጋራ የሚወዘወዝ መሥዋዕት አድርጎ በእግዚአብሔር ፊት ይወዘውዛቸዋል፤ እነዚህም ለእግዚአብሔር ቅዱስ መሥዋዕት፣ የካህኑም ድርሻ ናቸው።
21.በዚያ ዕለት የተቀደሰ ጉባኤ ዐውጁ፤ የተለመደ ተግባራችሁንም አታከናውኑ፤ ይህም በምትኖሩበት ስፍራ ሁሉ ለሚመጡት ትውልዶች የዘላለም ሥርዐት ነው።
22.“ ‘የምድራችሁን መከር በምትሰበስቡበት ጊዜ፣ የዕርሻችሁን ዳርና ዳር አትጨዱ፤ ቃርሚያውን አትልቀሙ፤ እነዚህንም ለድኾችና ለእንግዶች ተዉላቸው፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።’ ”
የመለከት በዓል
23፥23-25 ተጓ ምብ – ዘኍ 29፥1-6
23.እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤
24.“እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፤ ‘የሰባተኛው ወር የመጀመሪያ ቀን ዕረፍት ይሁንላችሁ፤ በመለከት ድምፅም የሚከበር የተቀደሰ ጉባኤ ይኑራችሁ።
25.መሥዋዕትን በእሳት ለእግዚአብሔር አቅርቡ እንጂ የተለመደ ተግባራችሁን አታከናውኑበት።’ ”
የስርየት ቀን
23፥26-32 ተጓ ምብ – ዘሌ 16፥2-34፤ ዘኍ 29፥7-11
26.እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤
27.“የሰባተኛው ወር ዐሥረኛ ቀን የስርየት ቀን ነው፤ የተቀደሰ ጉባኤ አድርጉ፤ አንዳች ነገርም አትብሉ፤ መሥዋዕትም በእሳት ለእግዚአብሔር አቅርቡ።
28.በእግዚአብሔር በአምላካችሁ ፊት ለእናንተ ስርየት የሚደረግበት የስርየት ቀን ስለ ሆነ፣ በዚያ ዕለት ምንም ሥራ አትሥሩ።
29.በዚያ ዕለት ሰውነቱን የማያጐሳቍል ማንኛውም ሰው ከወገኖቹ መካከል ተለይቶ ይጥፋ።
30.በዚያ ዕለት ማንኛውንም ሥራ የሚሠራውን ሰው ሁሉ ከወገኖቹ መካከል ለይቼ አጠፋዋለሁ።
31.ማንኛውንም ሥራ ከቶ አትሥሩበት፤ ይህ በምትኖሩበት ስፍራ ሁሉ ለልጅ ልጆቻችሁ የዘላለም ሥርዐት ነው።
32.ይህ ለእናንተ የዕረፍት ሰንበት ስለ ሆነ፣ ራሳችሁን ዝቅ ዝቅ አድርጉ በወሩም ከዘጠነኛው ቀን ምሽት ጀምራችሁ እስከሚቀጥለው ቀን ምሽት ድረስ ሰንበታችሁን አክብሩ።”
የዳስ በዓል
23፥33-43 ተጓ ምብ – ዘኍ 29፥12-39፤ ዘዳ 16፥13-17
33.እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤
34.“እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፤ ‘ሰባተኛውም ወር በገባ በዐሥራ ዐምስተኛው ቀን የእግዚአብሔር የዳስ በዓል ይጀምራል፤ እስከ ሰባት ቀንም ይቈያል።
35.የመጀመሪያው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ነውና የተለመደ ተግባራችሁን አታከናውኑበት።
36.ሰባት ቀን መሥዋዕቱን በእሳት ለእግዚአብሔር አቅርቡ፤ በስምንተኛው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ አድርጉ፤ መሥዋዕትን በእሳት ለእግዚአብሔር አቅርቡ፤ የተለመደ ተግባራችሁንም አታከናውኑበት።
37.“ ‘የሚቃጠል መሥዋዕትንና የእህል ቍርባንን፣ መሥዋዕትንና የመጠጥ ቍርባንን በተመደበላቸው ቀን ለእግዚአብሔር በእሳት ለማቅረብ፣ የተቀደሱ ጉባኤዎችን የምታውጁባቸው የእግዚአብሔር በዓላት እነዚህ ናቸው።
38.እነዚህ መሥዋዕቶች ለእግዚአብሔር ሰንበት ከምታቀርቡት፣ ከስጦታችሁ፣ ከስእለታችሁና ከበጎ ፈቃድ ስጦታችሁ በተጨማሪ የምታቀርቧቸው ስጦታዎች ናቸው።
39.“ ‘የምድራችሁን ፍሬ ከሰበሰባችሁ በኋላ በሰባተኛው ወር ከዐሥራ ዐምስተኛው ቀን ጀምራችሁ ሰባት ቀን ለእግዚአብሔር በዓል አክብሩ፤ የመጀመሪያው ቀን የዕረፍት ዕለት ነው፤ ስምንተኛውም ቀን እንደዚሁ የዕረፍት ዕለት ይሆናል።
40.በመጀመሪያው ቀን የመልካም ዛፍ ፍሬ፣ የዘንባባ ዝንጣፊ፣ የለመለመ ዛፍ ቅርንጫፍ የአኻያ ዛፍ ቅርንጫፍ ይዛችሁ ሰባት ቀን በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ፊት ደስ ይበላችሁ።
41.በየዓመቱም የእግዚአብሔር በዓል አድርጋችሁ ሰባት ቀን አክብሩ፤ ይህም ለልጅ ልጃችሁ የዘላለም ሥርዐት ነው፤ በሰባተኛውም ወር አክብሩት።
42.ሰባት ቀን ዳስ ውስጥ ተቀመጡ፤ በትውልዱ እስራኤላዊ የሆነ ሁሉ ዳስ ውስጥ ይሰንብት፤
43.በዚህም እኔ እስራኤላውያንን ከግብጽ ባወጣሁ ጊዜ፣ ዳስ ውስጥ እንዲቀመጡ ማድረጌን የልጅ ልጆቻችሁ ያውቃሉ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።’ ”
44.በዚህ ሁኔታም ሙሴ የተመረጡትን የእግዚአብሔር በዓላት ለእስራኤላውያን አስታወቀ።
ወደ ዕብራውያን
ምዕራፍ 8
የአዲስ ኪዳን ሊቀ ካህናት
1.እንግዲህ የምንናገረው ዋናው ነገር ይህ ነው፤ በሰማያት በግርማው ዙፋን ቀኝ የተቀመጠ እንዲህ ያለ ሊቀ ካህናት አለን፤ 2.እርሱም በሰው ሳይሆን በጌታ በተተከለችው፣ እውነተኛ ድንኳን በሆነችው ቤተ መቅደስ አገልጋይ ነው። 3.እያንዳንዱ ሊቀ ካህናት የሚሾመው መባንና መሥዋዕትን ለማቅረብ ነው፤ ስለዚህ ይህኛውም ሊቀ ካህን የሚያቀርበው ነገር ያስፈልገዋል። 4.እርሱ በምድር ቢኖር ኖሮ ካህን ባልሆነም ነበር፤ ምክንያቱም በሕግ በታዘዘው መሠረት መባን የሚያቀርቡ ሰዎች አሉ። 5.እነርሱ ያገለገሉት በሰማይ ላለችው መቅደስ ምሳሌና ጥላ በሆነችው ውስጥ ነው፤ ሙሴ ድንኳኒቱን ለመሥራት በተነሣ ጊዜ፣ “በተራራው ላይ በተገለጠልህ ምሳሌ መሠረት መሥራትህን ልብ በል” የሚል ትእዛዝ የተሰጠው በዚህ ምክንያት ነበር። 6.ነገር ግን ኢየሱስ መካከለኛ የሆነበት ኪዳን ከቀድሞው እንደሚበልጥ ሁሉ፣ የተቀበለውም አገልግሎት ከእነርሱ አገልግሎት ይበልጣል፤ ይህም የተመሠረተው በተሻለ የተስፋ ቃል ላይ ነው። 7.የመጀመሪያው ኪዳን ምንም ጕድለት ባይገኝበት ኖሮ፣ ለሁለተኛው ስፍራ ባልተፈለገም ነበር። 8.ነገር ግን እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ ጕድለት በማግኘቱ እንዲህ ይላቸዋል፤“ከእስራኤል ቤትና፣
ከይሁዳ ቤት ጋራ፣
አዲስ ኪዳን የምገባበት፣
ጊዜ ይመጣል፤ ይላል ጌታ። 9.ከግብጽ አወጣቸው ዘንድ፣
እጃቸውን ይዤ በመራኋቸው ጊዜ፣
ከአባቶቻቸው ጋራ እንደገባሁት ኪዳን አይደለም፤
ምክንያቱም እነርሱ በኪዳኔ አልጸኑም፤
እኔም ከእነርሱ ዘወር አልሁ፤
ይላል ጌታ። 10.ከዚያ ጊዜ በኋላ፣
ከእስራኤል ቤት ጋራ የምገባው ኪዳን ይህ ነው፤ ይላል ጌታ፤
ሕጌን በአእምሯቸው አኖራለሁ፤
በልባቸውም እጽፈዋለሁ።
እኔ አምላክ እሆናቸዋለሁ፤
እነርሱም ሕዝቤ ይሆናሉ። 11.ከእንግዲህ ማንም ሰው ጎረቤቱን
ወይም ወንድሙን፣ ‘ጌታን ዕወቅ’ ብሎ አያስተምርም፤
ምክንያቱም ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ፣
ሁሉም ያውቁኛል። 12.በደላቸውን ይቅር እላለሁ፤ ኀጢአታቸውን
ከእንግዲህ አላስብም።” 13.ይህን ኪዳን፣ “አዲስ” በማለቱ የፊተኛውን ኪዳን አሮጌ አድርጎታል፤ ስለዚህ ያረጀ ያፈጀው የሚጠፋበት ጊዜ ተቃርቧል።