Skip to Content
የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን | YEHIWOT MELHEK BETEKIRSTIAN
የ2019 ዓ.ም የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ 📖 ዛሬን አንብብ →

የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን

Yehiwot Melhek Betekirstian

ሳምንት 8 · ቀን 39 (ሐሙስ) 📅 Tikimt 26, 2019

ኦሪት ዘሌዋውያን 19, 20 · ወደ ዕብራውያን 7

📖 የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም፦ 1954 መጽሐፍ ቅዱስ አዲሱ መደበኛ ትርጒም

ኦሪት ዘሌዋውያን

ምዕራፍ 19

1.እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 2.ለእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ እንዲህ ባላቸው። እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ቅዱስ ነኝና እናንተ ቅዱሳን ሁኑ። 3.ከእናንተ ሰው ሁሉ እናቱንና አባቱን ይፍራ፥ ሰንበታቴንም ጠብቁ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። 4.ወደ ጣዖታትም ዘወር አትበሉ፥ ቀልጠው የተሠሩትንም የአማልክት ምስሎች ለእናንተ አታድርጉ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። 5.የደኅንነትንም መሥዋዕት ለእግዚአብሔር ስትሰዉ እርሱን ደስ እንድታሰኙበት ሠዉት። 6.በምትሠዉት ቀንና በነጋው ይበላል፤ እስከ ሦስተኛውም ቀን ድረስ ቢተርፍ በእሳት ይቃጠላል። 7.በሦስተኛውም ቀን ቢበላ ጸያፍ ነው፥ ደስም አያሰኝም፤ 8.የበላውም ለእግዚአብሔር የተቀደሰውን ነገር አርክሶአልና ኃጢአቱን ይሸከማል፤ ያም ሰው ከሕዝቡ ተለይቶ ይጥፋ። 9.የምድራችሁንም መከር በሰበሰባችሁ ጊዜ የእርሻችሁን ድንበር ፈጽማችሁ አትጨዱ፥ የመከሩንም ቃርሚያ አትልቀሙ። 10.የወይንህንም ቃርሚያ አትቃርም፥ የወደቀውንም የወይንህን ፍሬ አትሰብስብ፤ ለድሆችና ለእንግዶች ተወው፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። 11.አትስረቁ፥ አትካዱም፥ ከእናንተም እርስ በርሳችሁ ሐሰት አትነጋገሩ። 12.በስሜም በሐሰት አትማሉ፥ የአምላካችሁንም ስም አታርክሱ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 13.በባልንጀራህ ግፍ አታድርግ፥ አትቀማውም። የሞያተኛው ዋጋ እስከ ነገ ድረስ በአንተ ዘንድ አይደርብህ። 14.ደንቆሮውን አትስደብ፥ በዕውርም ፊት ዕንቅፋት አታድርግ፥ ነገር ግን አምላክህን ፍራ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 15.በፍርድ ዓመፃ አታድርጉ፤ ለድሀ አታድላ፥ ባለ ጠጋውንም አታክብር፤ ነገር ግን ለባልንጀራህ በእውነት ፍረድ። 16.በሕዝብህ መካከል በሸንጋይነት አትዙር፤ በባልንጀራህም ደም ላይ አትቁም፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 17.ወንድምህን በልብህ አትጥላው፤ በባልንጀራህ ምክንያት ኃጢአት እንዳይሆንብህ ገሥጸው። 18.አትበቀልም፥ በሕዝብህም ልጆች ቂም አትያዝ፥ ነገር ግን ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 19.ሥርዓቴን ጠብቁ። እንስሳህ ከሌላ ዓይነት ጋር አይደባለቅ፤ በእርሻህም ሁለት ዓይነት ዘር አትዝራ፤ ከሁለት ዓይነት ነገር የተሠራ ልብስ አትልበስ። 20.ማናቸውም ሰው ከሴት ባሪያ ጋር ቢተኛ፥ እርስዋም ለባል የተሰጠች ዋጋዋም ያልተከፈለ አርነት ያልወጣች ብትሆን፥ ቅጣት አለባቸው፤ አርነት አልወጣችምና አይገደሉም። 21.እርሱም የበደሉን መሥዋዕት ይዞ ወደ እግዚአብሔር ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ይመጣል፥ ለበደልም መሥዋዕት አውራ በግ ያመጣል። 22.ካህኑም ስለ ሠራው ኃጢአት በእግዚአብሔር ፊት በበደል መሥዋዕት በግ ያስተሰርይለታል፤ የሠራውም ኃጢአት ይቀርለታል። 23.ወደ አገሩም በገባችሁ ጊዜ፥ የሚበላ የፍሬ ዛፍ ሁሉ በተከላችሁም ጊዜ፥ ፍሬውን እንዳልተገረዘ ትቈጥሩታላችሁ፤ ሦስት ዓመት እንዳልተገረዘ ይሆንላችኋል፤ አይበላም። 24.የአራተኛውም ዓመት ፍሬ ሁሉ ለእግዚአብሔር ምስጋና ቅዱስ ይሁን። 25.ፍሬውም ይበዛላችሁ ዘንድ የአምስተኛውን ዓመት ፍሬ ብሉ፤ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። 26.ከደሙ ጋር ምንም አትብሉ፤ አስማትም አታድርጉ፥ ሞራ ገላጭም አትሁኑ። 27.የራስ ጠጕራችሁንም ዙሪያውን አትከርክሙት፥ ጢማችሁንም ዙሪያውን አትቍረጡት። 28.ስለ ሞተውም ሥጋችሁን አትንጩ፥ ገላችሁንም አትንቀሱት፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 29.ምድሪቱ ከግልሙትና ከርኵሰትም እንዳትሞላ ሴት ልጅህን ታመነዝር ዘንድ አታርክሳት። 30.ሰንበታቴን ጠብቁ፥ መቅደሴንም አክብሩ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 31.ወደ መናፍስት ጠሪዎችና ወደ ጠንቋዮች አትሂዱ፤ እንዳትረክሱባቸውም አትፈልጉአቸው፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። 32.በሽበታሙ ፊት ተነሣ፥ ሽማግሌውንም አክብር፥ አምላክህንም ፍራ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 33.በአገራችሁ ውስጥ ከእናንተ ጋር እንግዳ ቢቀመጥ ግፍ አታድርጉበት። 34.እናንተ በግብፅ ምድር እንግዶች ነበራችሁና ከእናንተ ጋር የሚቀመጥ እንግዳ እንደ አገር ልጅ ይሁንላችሁ፥ እርሱንም እንደ ራስህ ውደድ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። 35.በፍርድ፥ በመለካትም፥ በመመዘንም፥ በመስፈርም ዓመፃ አታድርጉ። 36.የእውነትም ሚዛን፥ የእውነትም መመዘኛ፥ የእውነትም የኢፍ መስፈሪያ፥ የእውነትም የኢን መስፈሪያ ይሁንላችሁ፤ ከግብፅ ምድር ያወጣኋችሁ እግዚአብሔር አምላካችሁ እኔ ነኝ። 37.ሥርዓቴን ሁሉ ፍርዴንም ሁሉ ጠብቁ አድርጉም፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።

ምዕራፍ 20

1.እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 2.ደግሞ የእስራኤልን ልጆች እንዲህ በላቸው። ከእስራኤል ልጆች ወይም በእስራኤል ዘንድ ከሚቀመጡ እንግዶች ማናቸውም ሰው ዘሩን ለሞሎክ ቢሰጥ ፈጽሞ ይገደል፤ የአገሩ ሕዝብ በድንጋይ ይውገረው። 3.መቅደሴን ያረክስ ዘንድ፥ የተቀደሰውንም ስሜን ያጐሰቍል ዘንድ ዘሩን ለሞሎክ ሰጥቶአልና እኔ በዚያ ሰው ላይ ፊቴን አከብዳለሁ፥ ከሕዝቡም መካከል ለይቼ አጠፋዋለሁ። 4.ዘሩንም ለሞሎክ ሲሰጥ፥ የአገሩ ሕዝብ ያን ቸል ቢለው ባይገድሉትም፥ 5.እኔ በዚያ ሰውና በቤተ ሰቡ ላይ ፊቴን አከብዳለሁ፤ እርሱንም፥ ከሞሎክም ጋር ያመነዝሩ ዘንድ የሚከተሉትን ሁሉ ከሕዝባቸው መካከል ለይቼ አጠፋለሁ። 6.መናፍስት ጠሪዎችንና ጠንቋዮችንም በሚከተል፥ በሥራቸውም በሚያመነዝር፥ በዚያ ሰው ላይ ፊቴን አከብዳለሁ፥ ከሕዝቡም መካከል ለይቼ አጠፋዋለሁ። 7.እንግዲህ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝና ሰውነታችሁን ቀድሱ፥ ቅዱሳንም ሁኑ። 8.ሥርዓቴን ጠብቁ፥ አድርጉትም፤ እኔ የምቀድሳችሁ እግዚአብሔር ነኝ። 9.ማናቸውም ሰው አባቱን ወይም እናቱን ቢሰድብ ፈጽሞ ይገደል፥ አባቱንና እናቱን ሰድቦአልና፤ ደሙ በራሱ ላይ ነው። 10.ማናቸውም ሰው ከሌላ ሰው ሚስት ወይም ከባልንጀራው ሚስት ጋር ቢያመነዝር አመንዝራውና አመንዝራይቱ ፈጽመው ይገደሉ። 11.ማናቸውም ሰው ከአባቱ ሚስት ጋር ቢተኛ የአባቱን ኃፍረተ ሥጋ ገልጦአል፤ ሁለቱ ፈጽመው ይገደሉ፤ ደማቸው በላያቸው ነው። 12.ማናቸውም ሰው ከምራቱ ጋር ቢተኛ ሁለቱ ፈጽመው ይገደሉ፤ ጸያፍ ነገር አድርገዋል፤ ደማቸውም በላያቸው ነው። 13.ማናቸውም ሰው ከሴት ጋር እንደሚተኛ ከወንድ ጋር ቢተኛ ሁለቱ ጸያፍ ነገር አድርገዋል፤ ፈጽመው ይገደሉ፤ ደማቸው በላያቸው ነው። 14.ማናቸውም ሰው እናቲቱንና ልጂቱን ቢያገባ ርኵሰት ነው፤ በመካከላችሁ ኃጢአት እንዳይሆን እርሱና እነርሱ በእሳት ይቃጠሉ። 15.ማናቸውም ሰው ከእንስሳ ጋር ቢገናኝ ፈጽሞ ይገደል፤ እንስሳይቱንም ግደሉአት። 16.ማናቸይቱም ሴት ወደ እንስሳ ብትቀርብ፥ ከእርሱም ጋር ብትገናኝ፥ ሴቲቱንና እንስሳውን ግደል፤ ፈጽመው ይገደሉ፤ ደማቸው በላያቸው ነው። 17.ማናቸውም ሰው የአባቱን ልጅ ወይም የእናቱን ልጅ እኅቱን ቢያገባ፥ ኃፍረተ ሥጋዋንም ቢያይ፥ እርስዋም ኃፍረተ ሥጋውን ብታይ፥ ይህ ጸያፍ ነገር ነው፤ በሕዝባቸውም ልጆች ፊት ይገደሉ፤ የእኅቱን ኃፍረተ ሥጋ ገልጦአልና ኃጢአቱን ይሸከማል። 18.ማናቸውም ሰው ከባለ መርገም ሴት ጋር ቢተኛ ኃፍረተ ሥጋዋንም ቢገልጥ፥ ፈሳሽዋን ገልጦአልና፥ እርስዋም የደምዋን ፈሳሽ ገልጣለችና ሁለቱ ከሕዝባቸው መካከል ተለይተው ይጥፉ። 19.የአባትህን ወይም የእናትህን እኅት ኃፍረተ ሥጋ አትግለጥ፤ ይህን የሚያደርግ የዘመድን ኃፍረተ ሥጋ ገልጦአል፤ ኃጢአታቸውን ይሸከማሉ። 20.ሰውም ከአጎቱ ሚስት ጋር ቢተኛ፥ የአጎቱን ኃፍረተ ሥጋ ገልጦአል፤ ኃጢአታቸውን ይሸከማሉ፤ ያለ ልጅ ይሞታሉ። 21.ሰውም የወንድሙን ሚስት ቢያገባ ርኵሰት ነው፤ የወንድሙን ኃፍረተ ሥጋ ገልጦአል፤ ያለ ልጅ ይሆናሉ። 22.እንግዲህ ትቀመጡባት ዘንድ የማገባችሁ ምድር እንዳትተፋችሁ ሥርዓቴን ሁሉ፥ ፍርዴንም ሁሉ ጠብቁ፥ አድርጉትም። 23.ከፊታችሁ በምጥላቸውም ሕዝብ ወግ አትሂዱ፤ ይህን ሁሉ አድርገዋልና ተጸየፍኋቸው። 24.ነገር ግን እናንተን። ምድራቸውን ትወርሳላችሁ፤ ትወርሱአትም ዘንድ ወተትና ማር የምታፈስሰውን ምድር እሰጣችኋለሁ አልኋችሁ። እኔ ከአሕዛብ የለየኋችሁ አምላካችሁ እግዚአብሔር ነኝ። 25.እንግዲህ ንጹሑን እንስሳ ከርኩሱ፥ ንጹሑንም ወፍ ከርኩስ ትለያላችሁ፤ ርኩሶች ናቸው ብዬ በለየኋቸው በእንስሳና በወፍ በምድርም ተንቀሳቃሽ ሁሉ ነፍሳችሁን አታርክሱ። 26.እኔ እግዚአብሔር ቅዱስ ነኝና፥ ለእኔም ትሆኑ ዘንድ ከአሕዛብ ለይቻችኋለሁና ቅዱሳን ትሆኑልኛላችሁ። 27.ሰው ወይም ሴት መናፍስትን ቢጠሩ ወይም ጠንቋዮች ቢሆኑ ፈጽመው ይገደሉ፤ በድንጋይ ይውገሩአቸው፤ ደማቸው በላያቸው ነው።

ወደ ዕብራውያን

ምዕራፍ 7

1.የሳሌም ንጉሥና የልዑል እግዚአብሔር ካህን የሆነ ይህ መልከ ጼዴቅ አብርሃም ነገሥታትን ገድሎ ሲመለስ ከእርሱ ጋር ተገናኝቶ ባረከው፤ 2.ለእርሱም ደግሞ አብርሃም ከሁሉ አስራትን አካፈለው። የስሙም ትርጓሜ በመጀመሪያ የጽድቅ ንጉሥ ነው፥ ኋላም ደግሞ የሳሌም ንጉሥ ማለት የሰላም ንጉሥ ነው። 3.አባትና እናት የትውልድም ቍጥር የሉትም፥ ለዘመኑም ጥንት ለህይወቱም ፍጻሜ የለውም፥ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ልጅ ተመስሎ ለዘላለም ካህን ሆኖ ይኖራል። 4.የአባቶች አለቃ አብርሃም ከዘረፋው የሚሻለውን አስራት የሰጠው ይህ ሰው እንዴት ትልቅ እንደ ነበረ እስኪ ተመልከቱ። 5.ከሌዊ ልጆችም ክህነትን የሚቀበሉት ከህዝቡ ማለት ከወንድሞቻቸው፥ እነርሱ ምንም ከአብርሃም ወገብ ቢወጡ፥ ከእነርሱ አሥራትን በሕግ እንዲያስወጡ ትእዛዝ አላቸው፤ 6.ትውልዱ ከእነርሱ የማይቈጠረው ግን ከአብርሃም አሥራትን አውጥቶአል፥ የተስፋ ቃል የነበረውንም ባርኮአል። 7.ትንሹም በታላቁ እንዲባረክ ክርክር የሌለበት ነገር ነው። 8.በዚህስ የሚሞቱ ሰዎች አሥራትን ያስወጣሉ፥ በዚያ ግን የሚያስወጣ በሕይወት እንዲኖር የተመሰከረለት እርሱ ነው። 9.ይህንም ለማለት ሲፈቀድ፥ አሥራትን የሚያስወጣ ሌዊ እንኳ በአብርሃም እጅ አሥራትን ሰጥቶአል፤ 10.መልከ ጼዴቅ በተገናኘው ጊዜ ገና በአባቱ ወገብ ነበረና። 11.እንግዲህ ህዝቡ በሌዊ ክህነት የተመሠረተን ሕግ ተቀብለዋልና በዚያ ክህነት ፍጹምነት የተገኘ ቢሆን፥ እንደ አሮን ሹመት የማይቈጠር፥ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ግን የሆነ ሌላ ካህን ሊነሳ ወደፊት ስለ ምን ያስፈልጋል? 12.ክህነቱ ሲለወጥ፥ ሕጉ ደግሞ ሊለወጥ የግድ ነውና። 13.ይህ ነገር የተነገረለት እርሱ በሌላ ወገን ተካፍሎአልና፥ ከዚያም መሠዊያውን ያገለገለ ማንም የለም፤ 14.ጌታችን ከይሁዳ ነገድ እንደወጣ የተገለጠ ነውና፥ ስለዚህም ነገድ ሙሴ ምንም እንኳ ስለ ክህነት አልተናገረም።
15 -
16.በማያልፍም ሕይወት ኃይል እንጂ በሥጋ ትእዛዝ ሕግ ሳይሆን ሌላ ካህን በመልከ ጼዴቅ ምሳሌ ቢነሳ፥ ይህ እጅግ አብልጦ የሚገለጥ ነው። 17.አንተ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ካህን ነህ ብሎ ይመሰክራልና።
18 -
19.ሕጉ ምንም ፍጹም አላደረገምና፥ ስለዚህም የምትደክም የማትጠቅምም ስለሆነች የቀደመች ትእዛዝ ተሽራለች፥ ወደ እግዚአብሔርም የምንቀርብበት የሚሻል ተስፋ ገብቶአል።
20 -
21.እነርሱም ያለ መሐላ ካህናት ሆነዋልና፤ እርሱ ግን። ጌታ። አንተ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ካህን ነህ ብሎ ማለ አይጸጸትም ብሎ በተናገረለት ከመሐላ ጋር ካህን ሆኖአልና ያለ መሐላ ካህን እንዳልሆነ መጠን፥ 22.እንዲሁ ኢየሱስ ለሚሻል ኪዳን ዋስ ሆኖአል። 23.እነርሱም እንዳይኖሩ ሞት ስለ ከለከላቸው ካህናት የሆኑት ብዙ ናቸው፤ 24.እርሱ ግን ለዘላለም የሚኖር ስለሆነ የማይለወጥ ክህነት አለው፤ 25.ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና ስለዚህ ደግሞ በእርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል። 26.ቅዱስና ያለ ተንኮል ነውርም የሌለበት ከኃጢአተኞችም የተለየ ከሰማያትም ከፍ ከፍ ያለ፥ እንደዚህ ያለ ሊቀ ካህናት ይገባልና፤ 27.እርሱም እንደነዚያ ሊቃነ ካህናት አስቀድሞ ስለ ራሱ ኃጢአት በኋላም ስለ ሕዝቡ ኃጢአት ዕለት ዕለት መሥዋዕትን ሊያቀርብ አያስፈልገውም፤ ራሱን ባቀረበ ጊዜ ይህን አንድ ጊዜ ፈጽሞ አድርጎአልና። 28.ሕጉ ድካም ያላቸውን ሰዎች ሊቀ ካህናት አድርጎ ይሾማልና፤ ከሕግ በኋላ የመጣ የመሐላው ቃል ግን ለዘላለም ፍጹም የሆነውን ልጅ ይሾማል።
♫
Listen to the reading 3 chapter tracks
ኦሪት ዘሌዋውያን Chapter 19
ኦሪት ዘሌዋውያን Chapter 20
ወደ ዕብራውያን Chapter 7
Swipe to browse chapters
Listen 3