ሳምንት 8 · ቀን 40 (አርብ)
📅 Tikimt 27, 2019
ኦሪት ዘሌዋውያን 21, 22, 23 · ወደ ዕብራውያን 8
ኦሪት ዘሌዋውያን
ምዕራፍ 21
1.እግዚአብሔርም ሙሴን። ለካህናቱ ለአሮን ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው አለው። ማንም ሰው ከሕዝቡ ስለ ሞተው፥
2.ከሚቀርበው ዘመዱ፥ ከእናቱ፥ ወይም ከአባቱ፥ ወይም ከወንድ ልጁ፥ ወይም ከሴት ልጁ፥ ወይም ከወንድሙ በቀር አይርከስ።
3.ወይም የቀረበችው ያልተጋባች ድንግል እኅቱ በእርስዋ ይርከስ።
4.የሕዝቡ አለቃ ራሱን ያጐሰቍል ዘንድ አይርከስ።
5.ራሳቸውን አይላጩ፥ ጢማቸውንም አይላጩ፥ ሥጋቸውንም አይንጩ።
6.ለአምላካቸው ቅዱሳን ይሁኑ፥ የአምላካቸውንም ስም አያጐስቍሉ፤ የእግዚአብሔርን የእሳት ቍርባንና የአምላካቸውን እንጀራ ያቀርባሉና ቅዱሳን ይሁኑ።
7.ለአምላኩ የተቀደሰ ነውና ጋለሞታን ሴት ወይም የረከሰችውን አያግባ፤ ወይም ከባልዋ የተፈታችውን አያግባ።
8.የአምላክህን እንጀራ ያቀርባልና ስለዚህ ትቀድሰዋለህ፤ እኔም የምቀድሳችሁ እግዚአብሔር ቅዱስ ነኝና እርሱ ቅዱስ ይሁንልህ።
9.የካህንም ልጅ ራስዋን በግልሙትና ብታረክስ አባትዋን ታረክሰዋለች፤ በእሳት ትቃጠል።
10.በራሱም ላይ የቅባት ዘይት የፈሰሰበት፥ የክህነትም ልብስ ይለብስ ዘንድ የተቀደሰ ከወንድሞቹ የበለጠው ካህን ራሱን አይግለጥ ልብሱንም አይቅደድ።
11.ወደ በድንም ሁሉ አይግባ፥ በአባቱም ወይም በእናቱ አይርከስ።
12.የአምላኩም ቅባት ዘይት ቅዱስነት በላዩ ነውና ከመቅደስ አይውጣ፥ የአምላኩንም መቅደስ አያርክስ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
13.እርሱም ሚስትን በድንግልናዋ ያግባ።
14.ባልዋ የሞተባትን፥ ወይም የተፋታችውን፥ ወይም ጋለሞታይቱን አያግባ፤ ነገር ግን ከሕዝቡ ድንግሊቱን ያግባ።
15.እኔም የምቀድሰው እግዚአብሔር ነኝና በሕዝቡ መካከል ዘሩን አያጐስቍል።
16.እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
17.ለአሮን እንዲህ ብለህ ንገረው። ከዘርህ በትውልዳቸው ነውር ያለበት ሰው ሁሉ የአምላኩን እንጀራ ያቀርብ ዘንድ አይቅረብ።
18.ዕውር፥ ወይም አንካሳ፥ ወይም አፍንጫ ደፍጣጣ፥ ወይም፤ ትርፍ አካል ያለው፥
19.ወይም እግረ ሰባራ፥ ወይም እጀ ሰባራ፥
20.ወይም ጐባጣ፥ ወይም ድንክ፥ ወይም ዓይነ መጭማጫ፥ ወይም እከካም፥ ወይም ቋቍቻም፥ ወይም ጃንደረባ፥ ነውረኛ ሁሉ አይቅረብ።
21.ከካህኑ ከአሮን ዘር ነውር ያለበት ሰው የእግዚአብሔርን የእሳት ቍርባን ያቀርብ ዘንድ አይቅረብ፤ ነውረኛ ነው፤ የአምላኩን እንጀራ ያቀርብ ዘንድ አይቅረብ።
22.የቅዱሱንና የቅዱስ ቅዱሳኑን የአምላኩን እንጀራ ይብላ፤
23.ነገር ግን ነውረኛ ነውና መቅደሶቼን እንዳያረክስ ወደ መጋረጃው አይግባ፥ ወደ መሠዊያውም አይቅረብ፤ የምቀድሳቸው እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
24.ሙሴም ይህን ለአሮን፥ ለልጆቹም፥ ለእስራኤልም ልጆች ሁሉ ነገረ።
ምዕራፍ 22
1.እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
2.የእስራኤል ልጆች ለእኔ ከሚቀድሱአቸው ከቅዱሳን ነገሮች ራሳቸውን እንዲለዩ፥ የተቀደሰውንም ስሜን እንዳያረክሱ ለአሮንና ለልጆቹ ንገራቸው፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
3.እንዲህ በላቸው። ማናቸውም ሰው ከዘራችሁ በትውልዳችሁ ርኵሰት እያለበት የእስራኤል ልጆች ለእግዚአብሔር ወደሚቀድሱት ወደ ቅዱስ ነገር ቢቀርብ፥ ያ ሰው ከፊቴ ተለይቶ ይጥፋ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
4.ከአሮን ዘር ለምጽ ወይም ፈሳሽ ነገር ያለበት ሁሉ ንጹሕ እስኪሆን ድረስ ከተቀደሰው አይብላ። ከበድንም የተነሣ ርኩስ የሆነውን፥ ወይም ዘሩ ከእርሱ የሚፈስስበትን የሚነካ፥
5.ወይም የሚያረክሰውን ተንቀሳቃሽ፥ ወይም በሁሉ ዓይነት የረከሰውን ሰው የሚነካ፥
6.እነዚህን ሁሉ የሚነካ ሰው እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል፤ ገላውን በውኃ ካልታጠበ ከተቀደሰው አይብላ።
7.ፀሐይም በገባች ጊዜ ንጹሕ ይሆናል፤ ከዚያም በኋላ እንጀራው ነውና ከተቀደሰው ይብላ።
8.በእርሱም እንዳይረክስ፥ የሞተውን አውሬም የሰበረውን አይብላ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
9.ቢያረክሱአት እንዳይሞቱ ስለ እርስዋም ኃጢአትን እንዳይሸከሙ፥ ሕግን ይጠብቁ፤ የምቀድሳቸው እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
10.ልዩ ሰው ከተቀደሰው አይብላ የካህኑም እንግዳ ደመወዘኛውም ከተቀደሰው አይብላ።
11.ካህኑ ግን በገንዘቡ ባሪያ ቢገዛ እርሱ ይብላው፤ በቤቱም የተወለዱት ከእንጀራው ይብሉ።
12.የካህንም ልጅ ከልዩ ሰው ጋር ብትጋባ፥ እርስዋ ከተቀደሰው ቍርባን አትብላ።
13.የካህን ልጅ ግን ባልዋ ቢሞት፥ ወይም ብትፋታ፥ ልጅም ባይኖራት፥ በብላቴንነትዋ እንደ ነበረች ወደ አባትዋ ቤት ብትመለስ፥ ከአባትዋ እንጀራ ትብላ፤ ልዩ ሰው ግን ከእርሱ አይብላ።
14.ማናቸውም ሰው ሳያውቅ ከተቀደሰው ቢበላ አምስተኛ እጅ ጨምሮ የተቀደሰውን ለካህኑ ይስጥ።
15.
16.የምቀድሳቸውም እግዚአብሔር እኔ ነኝና ከተቀደሰው በበሉ ጊዜ ኃጢአትንና በደልን እንዳይሸከሙ ወደ እግዚአብሔር የሚያቀርቡትን በእስራኤል ልጆች ዘንድ የተቀደሰውን ነገር አያርክሱ።
17.እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
18.ለአሮንና ለልጆቹ ለእስራኤልም ልጆች ሁሉ እንዲህ ብለህ ንገራቸው። ከእስራኤል ቤት ወይም ከእናንተ መካከል ከሚቀመጡት እንግዶች ማናቸውም ሰው ስእለቱን ሁሉ፥ በፈቃዱም የሚያቀርበውን ሁሉ፥ ለእግዚአብሔር ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚያቀርበውን ቍርባን ቢያቀርብ፥
19.ይሠምርላችሁ ዘንድ ከበሬ ወይም ከበግ ወይም ከፍየል ነውር የሌለበትን ተባቱን አቅርቡ።
20.ነገር ግን አይሠምርላችሁምና ነውር ያለበትን አታቅርቡ።
21.ማናቸውም ሰው ስእለቱን ለመፈጸም ወይም በፈቃዱ ለማቅረብ የደኅንነትን መሥዋዕት፥ ወይም በሬን ወይም በግን፥ ለእግዚአብሔር ቢያቀርብ፥ ይሠምርለት ዘንድ ፍጹም ይሁን፥ ነውርም አይሁንበት።
22.ዕውር ወይም ሰባራ ወይም ጕንድሽ ወይም የሚመግል ቍስል ያለበት ወይም እከካም ወይም ቋቍቻም ቢሆን፥ እነዚህን ሁሉ ለእግዚአብሔር አታቅርቡ፤ እነዚህም ለእሳት ቍርባን በመሠዊያው ላይ ለእግዚአብሔር አታሳርጉ።
23.በሬው ወይም በጉ የተጨመረበት ወይም የጐደለበት ነገር ቢሆን፥ ለፈቃድ መሥዋዕት ማቅረብ ትችላለህ፤ ለስእለት ግን አይሠምርም።
24.የተሰነጋውን ወይም የተቀጠቀጠውን ወይም የተሰበረውን ወይም የተቈረጠውን ለእግዚአብሔር አታቅርቡ፤ በምድራችሁም እነዚህን አትሠዉ።
25.ከእነዚህም ከእንግዳ ሰው እጅ ለአምላካችሁ እንጀራ አታቅርቡ፤ ርኵሰትም ነውርም አለባቸውና አይሠምሩላችሁም።
26.እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
27.በሬ ወይም በግ ወይም ፍየል ሲወለድ ሰባት ቀን ከእናቱ ጋር ይቀመጥ፤ በስምንተኛውም ቀን ከዚያም በላይ ለእግዚአብሔር የእሳት ቍርባን የሠመረ ይሆናል።
28.ላም ወይም በግ ብትሆን እርስዋንና ልጅዋን በአንድ ቀን አትረዱ።
29.የምስጋናንም መሥዋዕት ለእግዚአብሔር ስትሠዉ እንዲሠምርላችሁ ሠዉለት።
30.በዚያው ቀን ይበላል፤ ከእርሱ እስከ ነገ ምንም አትተዉ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
31.ትእዛዛቴን ጠብቁ፥ አድርጉትም፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
32.የተቀደሰውንም ስሜን አታርክሱ፤ እኔ ግን በእስራኤል ልጆች መካከል እቀደሳለሁ፤
33.የምቀድሳችሁ፥ አምላካችሁም እሆን ዘንድ ከግብፅ ምድር ያወጣኋችሁ እግዚአብሔር ነኝ። እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
ምዕራፍ 23
1.እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
2.ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው። የተቀደሰ ጉባኤ ብላችሁ የምታውጁአቸው በዓላቶቼ፥ የእግዚአብሔር በዓላት፥ እነዚህ ናቸው።
3.ስድስት ቀን ሥራ ይሠራል፤ በሰባተኛው ቀን ግን የዕረፍት ሰንበት ነው፤ የተቀደሰ ጉባኤ ይሆንበታል፤ ምንም ሥራ አትሠሩም፤ በምትኖሩበት ሁሉ ለእግዚአብሔር ሰንበት ነው።
4.እነዚህ የእግዚአብሔር በዓላት፥ በየዘመናቸው የምታውጁአቸው፥ የተቀደሰ ጉባኤ ናቸው።
5.በመጀመሪያው ወር በአሥራ አራተኛው ቀን ሲመሽ የእግዚአብሔር ፋሲካ ነው።
6.በዚህም ወር በአሥራ አምስተኛው ቀን ለእግዚአብሔር የቂጣ በዓል ነው፤ ሰባት ቀን ቂጣ እንጀራ ብሉ።
7.በመጀመሪያው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይሁንላችሁ፤ የተግባር ሥራ ሁሉ አትሥሩበት።
8.ሰባት ቀንም ለእግዚአብሔር የእሳት ቍርባን አቅርቡ፤ በሰባተኛው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ነው፤ የተግባር ሥራ ሁሉ አትሥሩበት።
9.እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
10.ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው። ወደምሰጣችሁ ምድር በገባችሁ ጊዜ፥ መከሩንም ባጨዳችሁ ጊዜ፥ የእናንተን መከር በኵራት ነዶ ወደ ካህኑ አምጡ፤
11.እርሱም ነዶውን በእግዚአብሔር ፊት እንዲሠምርላችሁ ይወዝውዘው፤ በማግስቱ ከሰንበት በኋላ ካህኑ ይወዝውዘው።
12.ነዶውንም በወዘወዛችሁበት ቀን ነውር የሌለበትን የአንድ ዓመት ተባት ጠቦት ለሚቃጠል መሥዋዕት ወደ እግዚአብሔር አቅርቡ።
13.የእህልም ቍርባን ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ ሁለት እጅ የሆነ በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን ለእሳት ቍርባን ይሁን፤ የመጠጡም ቍርባን የወይን ጠጅ የኢን መስፈሪያ አራተኛ እጅ ይሁን።
14.እንጀራውንም፥ የተጠበሰውንም እሸት፥ ለምለሙንም እሸት የአምላካችሁን ቍርባን እስከምታቀርቡበት እስከዚህ ቀን ድረስ አትብሉ። ይህ በምትቀመጡበት አገር ሁሉ ለልጅ ልጃችሁ የዘላለም ሥርዓት ነው።
15.የወዘወዛችሁትን ነዶ ከምታመጡበት ቀን በኋላ ከሰንበት ማግስት ፍጹም ሰባት ጊዜ ሰባት ቀን ቍጠሩ፤
16.እስከ ሰባተኛ ሰንበት ማግስት ድረስ አምሳ ቀን ቍጠሩ፤ አዲሱንም የእህል ቍርባን ወደ እግዚአብሔር አቅርቡ።
17.ከየማደሪያችሁ ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ ሁለት እጅ ከሆነ መልካም ዱቄት የተሠራ ሁለት የመወዝወዝ እንጀራ ታመጣላችሁ፤ ለእግዚአብሔር ለበኵራት ቍርባን እንዲሆን በእርሾ ይጋገራል።
18.ከእንጀራውም ጋር ነውር የሌለባቸውን የአንድ ዓመት ሰባት ጠቦቶች፥ አንድ ወይፈንም፥ ሁለትም አውራ በጎች ታቀርባላችሁ፤ ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት ይሁኑ፤ ከእህልም ቍርባን፥ ከመጠጡም ቍርባን ጋር ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን የእሳት ቍርባን ይሁኑ።
19.አንድም አውራ ፍየል ለኃጢአት መሥዋዕት፥ ሁለትም የአንድ ዓመት ተባት ጠቦቶች ለደኅንነት መሥዋዕት አቅርቡ።
20.ካህኑም ከበኵራቱ እንጀራ ከሁለቱም ጠቦቶች ጋር በእግዚአብሔር ፊት ለመወዝወዝ ቍርባን ይወዘውዛቸዋል፤ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ፈንታ ነው፤ ለካህኑ ይሁን።
21.በዚያም ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይሆንላችሁ ዘንድ ታውጃላችሁ፤ የተግባር ሥራ ሁሉ አታድርጉበት፤ በምትቀመጡበት አገር ሁሉ ለልጅ ልጃችሁ የዘላለም ሥርዓት ነው።
22.የምድራችሁንም መከር በሰበሰባችሁ ጊዜ የእርሻችሁን ድንበር ፈጽማችሁ አትጨዱ፥ የመከሩንም ቃርሚያ አትልቀሙ፤ ለድሆችና ለእንግዶች ተዉት፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።
23.እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
24.ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው። በሰባተኛው ወር በመጀመሪያው ቀን ዕረፍት፥ በመለከት ድምፅ መታሰቢያ፥ የተቀደሰ ጉባኤ ይሁንላችሁ።
25.የተግባር ሥራ ሁሉ አታድርጉበት፥ ለእግዚአብሔርም የእሳት ቍርባንን አቅርቡ።
26.እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
27.በዚህ በሰባተኛው ወር አሥረኛው ቀን የማስተስረያ ቀን ነው፤ የተቀደሰ ጉባኤ ይሁንላችሁ፤ ሰውነታችሁን አስጨንቋት፥ ለእግዚአብሔርም የእሳት ቍርባንን አቅርቡ።
28.በአምላካችሁም በእግዚአብሔር ፊት ማስተስረያ ይሆንላችሁ ዘንድ የማስተስረያ ቀን ነውና በዚያ ቀን ሥራ ሁሉ አትሥሩ።
29.በዚያም ቀን የማይዋረድ ሰው ሁሉ ከሕዝቡ ተለይቶ ይጥፋ።
30.በዚያም ቀን ሥራ የሚሠራውን ሰው ሁሉ ከሕዝቡ መካከል አጠፋዋለሁ።
31.ሥራ ሁሉ አታድርጉበት፤ በምትቀመጡበት አገር ሁሉ ለልጅ ልጃችሁ የዘላለም ሥርዓት ነው።
32.የዕረፍት ሰንበት ይሁንላችሁ፥ ሰውነታችሁንም አዋርዱ፤ በወሩ በዘጠነኛው ቀን በማታ ጊዜ፥ ከማታ ጀምራችሁ እስከ ማታ ድረስ፥ ሰንበታችሁን አድርጉ።
33.እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።
34.ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው። በዚህ በሰባተኛው ወር ከአሥራ አምስተኛው ቀን ጀምሮ ሰባት ቀን ለእግዚአብሔር የዳስ በዓል ይሆናል።
35.በመጀመሪያው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይሁን፤ የተግባር ሥራ ሁሉ አታድርጉበት።
36.ሰባት ቀን ለእግዚአብሔር የእሳት ቍርባንን አቅርቡ፤ በስምንተኛውም ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይሁንላችሁ፥ ለእግዚአብሔርም የሚቃጠለውን ቍርባን አቅርቡ፤ ዋና ጉባኤ ነው፤ የተግባር ሥራ ሁሉ አታድርጉበት።
37.የሚቃጠለውን መሥዋዕት፥ የእህሉንም ቍርባን፥ መሥዋዕቱንም፥ የመጠጡንም ቍርባን፥ በየቀኑ የእሳት ቍርባን ወደ እግዚአብሔር ታቀርቡባቸው ዘንድ የተቀደሱ ጉባኤዎች እንዲሆኑ የምታውጁአቸው የእግዚአብሔር በዓላት እነዚህ ናቸው።
38.እነዚህም ከእግዚአብሔር ሰንበታት ሌላ፥ ለእግዚአብሔርም ከምትሰጡት ከስጦታችሁ ሌላ፥ ከስእለታችሁም ሁሉ ሌላ፥ በፈቃዳችሁም ከምታቀርቡአቸው ሁሉ ሌላ ናቸው።
39.ከሰባተኛውም ወር በአሥራ አምስተኛው ቀን የምድሩን ፍሬ ካከማቻችሁ በኋላ፥ የእግዚአብሔርን በዓል ሰባት ቀን ጠብቁ፤ በመጀመሪያው ቀን ዕረፍት ይሁን፥ በስምንተኛውም ቀን ዕረፍት ይሁን።
40.በመጀመሪያው ቀን የመልካም ዛፍ ፍሬ፥ የሰሌን ቅርንጫፍ፥ የለመለመውን ዛፍ ቅርንጫፍ፥ የወንዝም አኻያ ዛፍ ውሰዱ፤ በአምላካችሁም በእግዚአብሔር ፊት ሰባት ቀን ደስ ይበላችሁ።
41.ይህንንም በዓል በየዓመቱ ሰባት ቀን ለእግዚአብሔር አድርጉ፤ ለልጅ ልጃችሁ የዘላለም ሥርዓት ነው፤ በሰባተኛው ወር ትጠብቁታላችሁ።
42.
43.ሰባት ቀን በዳሶች ውስጥ ትቀመጣላችሁ፤ ከግብፅ ምድር ባወጣኋቸው ጊዜ የእስራኤልን ልጆች በዳስ ውስጥ እንዳስቀመጥኋቸው የልጅ ልጆቻችሁ ያውቁ ዘንድ፥ በእስራኤል ያሉት የአገር ልጆች ሁሉ በዳስ ውስጥ ይቀመጡ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።
44.ሙሴም የእግዚአብሔርን በዓላት ለእስራኤል ልጆች ተናገረ።
ወደ ዕብራውያን
ምዕራፍ 8
1.ከተናገርነውም ዋና ነገሩ ይህ ነው፤ በሰማያት በግርማው ዙፋን ቀኝ የተቀመጠ እንዲህ ያለ ሊቀ ካህናት አለን፤
2.እርሱም የመቅደስና የእውነተኛይቱ ድንኳን አገልጋይ ነው፥ እርስዋም በሰው ሳይሆን በጌታ የተተከለች ናት።
3.ሊቀ ካህናት ሁሉ መባንና መሥዋዕትን ሊያቀርብ ይሾማልና፤ ስለዚህም ለዚህ ደግሞ የሚያቀርበው አንዳች ሊኖረው የግድ ነው።
4.እንግዲህ በምድር ቢኖርስ፥ እንደ ሕግ መባን የሚያቀርቡት ስላሉ፥ ካህን እንኳ ባልሆነም፤
5.እነርሱም ሙሴ ድንኳኒቱን ሊሠራ ሳለ እንደ ተረዳ፥ ለሰማያዊ ነገር ምሳሌና ጥላ የሚሆነውን ያገለግላሉ። በተራራው እንደ ተገለጠልህ ምሳሌ ሁሉን ታደርግ ዘንድ ተጠንቀቅ ብሎት ነበርና።
6.አሁን ግን በሚሻል ተስፋ ቃል በተመሠረተ በሚሻል ኪዳን ደግሞ መካከለኛ እንደሚሆን በዚያ ልክ እጅግ የሚሻል አገልግሎት አግኝቶአል።
7.ፊተኛው ኪዳን ነቀፋ ባይኖረው፥ ለሁለተኛው ስፍራ ባልተፈለገም ነበር።
8.እነርሱን እየነቀፈ ይላቸዋልና። እነሆ፥ ከእስራኤል ቤትና ከይሁዳ ቤት ጋር አዲስ ኪዳን የምገባበት ወራት ይመጣል ይላል ጌታ፤
9.ከግብፅ አገር አወጣቸው ዘንድ እጃቸውን በያዝሁበት ቀን ከአባቶቻቸው ጋር እንደገባሁት ኪዳን አይደለም፤ እነርሱ በኪዳኔ አልጸኑምና፥ እኔም ቸል አልኋቸው ይላል ጌታ።
10.ከዚያ ወራት በኋላ ከእስራኤል ቤት ጋር የምገባው ቃል ኪዳን ይህ ነውና ይላል ጌታ፤ ሕጌን በልቡናቸው አኖራለሁ በልባቸውም እጽፈዋለሁ፥ እኔም አምላክ እሆንላቸዋለሁ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑልኛል።
11.እያንዳንዱም ጐረቤቱን እያንዳንዱም ወንድሙን። ጌታን እወቅ ብሎ አያስተምርም ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ሁሉ ያውቁኛልና።
12.ዓመፃቸውን እምራቸዋለሁና፥ ኃጢአታቸውንም ደግሜ አላስብም።
13.አዲስ በማለቱ ፊተኛውን አስረጅቶአል፤ አሮጌና ውራጅ የሆነውስ ሊጠፋ ቀርቦአል።