ሳምንት 8 · ቀን 39 (ሐሙስ)
📅 Tikimt 26, 2019
ኦሪት ዘሌዋውያን 19, 20 · ወደ ዕብራውያን 7
ኦሪት ዘሌዋውያን
ምዕራፍ 19
ልዩ ልዩ ሕግጋት
1.እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 2.“ለመላው የእስራኤል ሕዝብ ጉባኤ እንዲህ ብለህ ተናገራቸው፤ ‘እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ። 3.“ ‘ከእናንተ እያንዳንዱ እናቱንና አባቱን ያክብር፤ ሰንበታቴን ጠብቁ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። 4.“ ‘ወደ ጣዖታት ዘወር አትበሉ፤ ወይም ከቀለጠ ብረት ለራሳችሁ አማልክት አትሥሩ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። 5.“ ‘የኅብረት መሥዋዕት ለእግዚአብሔር በምታቀርቡበት ጊዜ፣ መሥዋዕታችሁ ተቀባይነት እንዲያገኝላችሁ አድርጋችሁ አቅርቡ። 6.መሥዋዕቱም ባቀረባችሁት ዕለት ወይም በማግስቱ ይበላ፤ እስከ ሦስተኛው ቀን የተረፈ ማንኛውም ነገር ይቃጠል። 7.በሦስተኛውም ቀን ቢበላ ርኩስ ነው፤ ተቀባይነትም የለውም። 8.ከመሥዋዕቱ የሚበላ ማንኛውም ሰው ለእግዚአብሔር የተቀደሰውን ነገር አርክሷልና ይጠየቅበታል፤ ያም ሰው ከወገኑ ተለይቶ ይጥፋ። 9.“ ‘የምድራችሁን መከር በምትሰበስቡበት ጊዜ፣ በዕርሻችሁ ዳርና ዳር ያለውን አትጨዱ፤ ቃርሚያውንም አትልቀሙ። 10.የወይንህን ዕርሻ አትቃርም፤ የወደቀውንም አትልቀም፤ ለድኾችና ለመጻተኞች ተውላቸው፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። 11.“ ‘አትስረቁ።“ ‘አትዋሹ።
“ ‘ከእናንተ አንዱ ሌላውን አያታልል። 12.“ ‘በስሜ በሐሰት አትማሉ፤ በዚህም የአምላካችሁን ስም አታርክሱ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 13.“ ‘ባልንጀራህን አታጭበርብር፤ አትቀማውም።
“ ‘የሙያተኛውን ደመወዝ ሳትከፍል አታሳድር። 14.“ ‘ደንቈሮውን አትርገም፤ በዐይነ ስውሩም ፊት ዕንቅፋት አታኑር፤ ነገር ግን አምላክህን ፍራ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 15.“ ‘ፍርድ አታዛቡ፤ ለድኻው አታድላለት፤ ለትልቁም ሰው ልዩ አክብሮት አትስጥ፤ ለብርቱው አታድላ፤ ነገር ግን ለባልንጀራህ በጽድቅ ፍረድ። 16.“ ‘በሕዝብህ መካከል ሐሜት አትንዛ።
“ ‘የባልንጀራህን ሕይወት አደጋ ላይ የሚጥል ማንኛውንም ነገር አታድርግ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 17.“ ‘ወንድምህን በልብህ አትጥላው፤ የበደሉ ተካፋይ እንዳትሆን ባልንጀራህን በግልጽ ገሥጸው። 18.“ ‘ወገንህን አትበቀል፤ ወይም በመካከልህ ከሚኖር በማንኛውም ሰው ላይ ቂም አትያዝ፤ ነገር ግን ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 19.“ ‘ሥርዐቴን ጠብቁ።
“ ‘የተለያዩ እንስሳትን አታዳቅል።
“ ‘በዕርሻህ ላይ ሁለት ዐይነት ዘር አትዝራ።
“ ‘ከሁለት ዐይነት ነገር የተሠራ ልብስ አትልበስ። 20.“ ‘አንድ ሰው ለሌላ ከታጨች ሴት ባሪያ ጋራ ግብረ ሥጋ ቢፈጽም፣ ሴቲቱም ያልተዋጀች ወይም ነጻ ያልወጣች ብትሆን ይቀጣል፤ ነገር ግን ሴቲቱ ነጻ ስላልወጣች አይገደሉም። 21.ሰውየውም ለበደል መሥዋዕት የሚሆን አንድ አውራ በግ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ለእግዚአብሔር ያምጣ። 22.ካህኑም በበደል መሥዋዕቱ አውራ በግ፣ ሰውየው ስለ ሠራው ኀጢአት በእግዚአብሔር ፊት ያስተሰርይለታል፤ ኀጢአቱም ይቅር ይባልለታል። 23.“ ‘ወደ ምድሪቱ ገብታችሁ ማንኛውንም ዐይነት ፍሬ የሚሰጥ ዛፍ በምትተክሉበት ጊዜ፣ ፍሬው ለመብላት ያልተገረዘ መሆኑን ዕወቁ፤ ለሦስት ዓመትም የተከለከለ በመሆኑ አይበላ። 24.በአራተኛውም ዓመት ፍሬው ሁሉ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ የምስጋና መሥዋዕት ይሆናል። 25.በዐምስተኛው ዓመት ግን ፍሬውን ትበላላችሁ፤ በዚህም ሁኔታ ፍሬው ይበዛላችኋል፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። 26.“ ‘ደም ያለበትን ማንኛውንም ሥጋ አትብሉ።
“ ‘ጥንቈላ ወይም አስማት አትሥሩ። 27.“ ‘የራስ ጠጕራችሁን ዙሪያ አትከርከሙ፤ ጢማችሁንም አሳጥራችሁ አትቍረጡ። 28.“ ‘ለሞተ ሰው ሰውነታችሁን አትንጩ፤ በሰውነታችሁም ላይ ንቅሳት አታድርጉ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 29.“ ‘ምድሪቱ ወደ ግልሙትና አዘንብላ በርኩሰት እንዳትሞላ፣ ሴት ልጅህ ጋለሞታ ትሆን ዘንድ አታዋርዳት። 30.“ ‘ሰንበታቴን ጠብቁ፤ መቅደሴንም አክብሩ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 31.“ ‘እንዳትረክሱባቸው ወደ ሙታን ጠሪዎች ዘወር አትበሉ፤ መናፍስት ጠሪዎችንም አትፈልጉ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። 32.“ ‘ዕድሜው ለገፋ ተነሥለት፤ ሽማግሌውን አክብር፤ አምላክህንም ፍራ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 33.“ ‘መጻተኛ በምድራችሁ ላይ ዐብሯችሁ በሚኖርበት ጊዜ አትበድሉት፤ 34.ዐብሯችሁ የሚኖረው መጻተኛ እንደ ገዛ ወገናችሁ ይታይ፤ እንደ ራሳችሁም ውደዱት፤ እናንተም በግብጽ መጻተኞች ነበራችሁና፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። 35.“ ‘በመስፈሪያ ወይም በሚዛን አታጭበርብሩ። 36.የጽድቅ መለኪያ፣ የጽድቅ ሚዛን፣ የጽድቅ የኢፍ መስፈሪያ፣ የጽድቅ የሂን መስፈሪያም ይኑራችሁ። ከግብጽ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። 37.“ ‘ሥርዐቴንና ሕጌን ሁሉ ጠብቁ፤ ተከተሏቸውም፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።’ ”
ምዕራፍ 20
ኀጢአት የሚያስከትለው ቅጣት
1.እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 2.“ለእስራኤላውያን እንዲህ በላቸው፤ ‘ከልጆቹ አንዱን ለሞሎክ የሚሰጥ ማንኛውም እስራኤላዊ ወይም በእስራኤል የሚኖር መጻተኛ ይገደል፤ እርሱንም የአገሩ ሕዝብ በድንጋይ ይውገረው። 3.ልጁን ለሞሎክ በመስጠት መቅደሴን አርክሷልና፣ ቅዱሱን ስሜንም አቃልሏልና፣ በዚያ ሰው ላይ ጠላት እሆንበታለሁ፤ ከወገኖቹም ለይቼ አጠፋዋለሁ። 4.የአገሩ ሕዝብ፣ ሰውየው ልጁን ለሞሎክ ሲሰጥ አይተው ቸል ቢሉ፣ ባይገድሉትም፣ 5.በዚያ ሰውና በቤተ ሰቡ ላይ ጠላት እሆናለሁ፤ እርሱንና ከሞሎክ ጋራ በማመንዘር እርሱን የተከተሉትን ሁሉ ከሕዝባቸው መካከል ለይቼ አጠፋቸዋለሁ። 6.“ ‘ወደ ሙታን ጠሪዎችና ጠንቋዮች ዘወር በማለት፣ በሚከተላቸውና ከእነርሱም ጋራ በሚያመነዝር ሰው ላይ ጠላት እሆንበታለሁ፤ ከወገኖቹም ለይቼ አጠፋዋለሁ። 7.“ ‘ራሳችሁን ቀድሱ፤ ቅዱሳንም ሁኑ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝና። 8.ሥርዐቴን ጠብቁ፤ አድርጉትም፤ የምቀድሳችሁ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 9.“ ‘አባቱን ወይም እናቱን የሚረግም ማንኛውም ሰው ይገደል፤ አባቱን ወይም እናቱን ረግሟልና ደሙ በራሱ ላይ ነው። 10.“ ‘አንድ ሰው ከባልንጀራው ሚስት ጋራ ቢያመነዝር፣ አመንዝራውና አመንዝራዪቱ ይገደሉ። 11.“ ‘አንድ ሰው ከአባቱ ሚስት ጋራ ግብረ ሥጋ ቢፈጽም አባቱን አዋርዷል፤ ሰውየውና ሴትዮዋ ይገደሉ፤ ደማቸው በራሳቸው ላይ ነው። 12.“ ‘አንድ ሰው ከልጁ ሚስት ጋራ ግብረ ሥጋ ቢፈጽም፣ ሁለቱም ይገደሉ፤ ነውር አድርገዋልና ደማቸው በራሳቸው ላይ ነው። 13.“ ‘አንድ ወንድ ከሴት ጋራ ግብረ ሥጋ እንደሚፈጽም ሁሉ ከወንድ ጋራ ቢፈጽም፣ ሁለቱም አስጸያፊ ድርጊት ፈጽመዋልና ይገደሉ፤ ደማቸው በራሳቸው ላይ ነው። 14.“ ‘አንድ ሰው አንዲትን ሴትና እናቷን ቢያገባ፣ አድራጎቱ ጸያፍ ነው፤ በመካከላችሁ እንዲህ ዐይነት ርኩሰት እንዳይገኝ ሰውየውና ሴቶቹ በእሳት ይቃጠሉ። 15.“ ‘ማንኛውም ሰው ከእንስሳ ጋራ ግብረ ሥጋ ቢፈጽም፣ ይገደል፤ እንስሳዪቱንም ግደሏት። 16.“ ‘አንዲት ሴት ወደ እንስሳ ቀርባ ግብረ ሥጋ ብትፈጽም፣ ሴቲቱንና እንስሳውን ግደሉ፤ ደማቸው በራሳቸው ላይ ነው። 17.“ ‘አንድ ሰው የአባቱ ወይም የእናቱ ልጅ የሆነችውን እኅቱን አግብቶ ግብረ ሥጋ ቢፈጽም፣ አድራጎቱ አሳፋሪ ነው፤ በሕዝባቸው ፊት ከሕዝባቸው ተለይተው ይጥፉ። ሰውየው እኅቱን አዋርዷልና ይጠየቅበታል። 18.“ ‘ማንኛውም ሰው በወር አበባዋ ጊዜ ከሴት ጋራ ግብረ ሥጋ ቢፈጽም፣ የፈሳሿን ምንጭ ገልጧልና፣ እርሷም የፈሳሿን ምንጭ ገልጣለችና ሁለቱም ከሕዝባቸው መካከል ተለይተው ይጥፉ። 19.“ ‘ከእናትህም ሆነ ከአባትህ እኅት ጋራ ግብረ ሥጋ አትፈጽም፤ ይህ የሥጋ ዝምድናን ማቃለል ስለ ሆነ ሁለታችሁም ትጠየቁበታላችሁ። 20.“ ‘ማንኛውም ሰው ከአጎቱ ሚስት ጋራ ግብረ ሥጋ ቢፈጽም፣ አጎቱን አዋርዷልና ሁለቱም ይጠየቁበታል፤ ያለ ልጅም ይሞታሉ። 21.“ ‘ማንኛውም ሰው የወንድሙን ሚስት ቢያገባ አድራጎቱ ርኩሰት ነው፤ ወንድሙን አዋርዷልና፣ ያለ ልጅም ይቀራሉ። 22.“ ‘እንድትኖሩባት እናንተን የማስገባባት ምድር እንዳትተፋችሁ ሥርዐቴንና ሕጌን ጠብቁ፤ አድርጉም። 23.ከፊታችሁ የማሳድዳቸውን አሕዛብ ልማድ አትከተሉ፤ እነዚህን ሁሉ በማድረጋቸው ተጸየፍኋቸው። 24.እናንተ ግን፣ “ምድራቸውን ትወርሳላችሁ፤ ማርና ወተት የምታፈስሰውን አገር ርስት አድርጌ እሰጣችኋለሁ” አልኋችሁ፤ ከአሕዛብ የለየኋችሁ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። 25.“ ‘ንጹሕ በሆኑትና ንጹሕ ባልሆኑት እንስሳት እንዲሁም ንጹሕ በሆኑትና ንጹሕ ባልሆኑት ወፎች መካከል ልዩነት አድርጉ። ርኩስ ነው ብዬ በለየሁት በማንኛውም እንስሳ ወይም ወፍ ወይም በምድር ላይ በሚንቀሳቀስ በማንኛውም ነገር ራሳችሁን አታርክሱ። 26.እናንተ ለእኔ ቅዱሳን ትሆኑልኛላችሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ቅዱስ ነኝና፤ የእኔ ትሆኑ ዘንድ ከአሕዛብ መካከል ለይቻችኋለሁ። 27.“ ‘ከመካከላችሁ ሙታን ጠሪ ወይም መናፍስት ጠሪ የሆነ ማንኛውም ወንድ ወይም ሴት ይገደል፤ በድንጋይም ይወገሩ፤ ደማቸው በራሳቸው ላይ ነው።’ ”ወደ ዕብራውያን
ምዕራፍ 7
ካህኑ መልከ ጼዴቅ
1.ይህ መልከ ጼዴቅ የሳሌም ንጉሥና የልዑል እግዚአብሔር ካህን ነበር፤ እርሱም አብርሃም ነገሥታትን ድል አድርጎ ሲመለስ አግኝቶት ባረከው፤ 2.አብርሃምም ከሁሉ ነገር ዐሥራትን አውጥቶ ሰጠው። በመጀመሪያ ስሙ “የጽድቅ ንጉሥ” ማለት ነው፤ ኋላም ደግሞ “የሳሌም ንጉሥ” ማለትም “የሰላም ንጉሥ ማለት” ነው። 3.አባትና እናት ወይም የትውልድ ሐረግ የለውም፤ ለዘመኑ መጀመሪያ፣ ለሕይወቱም ፍጻሜ የለውም፤ ነገር ግን እንደ እግዚአብሔር ልጅ ለዘላለም ካህን ሆኖ ይኖራል። 4.እስኪ እርሱ የቱን ያህል ታላቅ እንደ ሆነ አስቡ፤ ርእሰ አበው የሆነው አብርሃም እንኳ ካገኘው ምርኮ ዐሥራት አውጥቶ ሰጠው! 5.ክህነት የተሰጣቸው የሌዊ ልጆች ምንም እንኳ ወንድሞቻቸው የአብርሃም ዘሮች ቢሆኑም፣ ከሕዝቡ ማለት ከገዛ ወንድሞቻቸው ዐሥራት እንዲቀበሉ ሕጉ ያዝዛል። 6.ይህ ግን ትውልዱ ከሌዊ ወገን አይደለም፤ ይሁን እንጂ ከአብርሃም ዐሥራት ተቀበለ፤ የተስፋ ቃል የተቀበለውንም ባረከው። 7.ትንሹ በትልቁ እንደሚባረክ ጥርጥር የለውም። 8.በአንድ በኩል ዐሥራት የሚቀበሉት ሟች ሰዎች ናቸው፤ በሌላ በኩል ግን ሕያው ሆኖ እንደሚኖር የተመሰከረለት ይቀበላል። 9.እንዲያውም ዐሥራት የሚቀበለው ሌዊ፣ ራሱ በአብርሃም በኩል ዐሥራት ከፍሏል ማለት ይቻላል፤ 10.ምክንያቱም መልከ ጼዴቅ አብርሃምን ባገኘው ጊዜ፣ ሌዊ ገና በአባቱ በአብርሃም አብራክ ነበር።ኢየሱስ እንደ መልከ ጼዴቅ
11.ፍጹምነት የተገኘውና ሕጉ ለሕዝቡ የተሰጠው በሌዊ ክህነት መሠረት ቢሆን ኖሮ፣ እንደ አሮን ሳይሆን እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ያለው ሌላ ካህን መምጣቱ ለምን አስፈለገ? 12.የክህነት ለውጥ ካለ ሕጉም ሊለወጥ ግድ ነውና። 13.ይህ ሁሉ የተነገረለት እርሱ ከሌላ ነገድ ነው፤ ከዚያም ነገድ በመሠዊያ ያገለገለ ማንም የለም። 14.ጌታችን ከይሁዳ ነገድ እንደ መጣ ግልጽ ነውና፤ ሙሴ ስለ ካህናት ሲናገር ይህን ነገድ አስመልክቶ የተናገረው ምንም ነገር የለም። 15.እንደ መልከ ጼዴቅ ያለ ሌላ ካህን ቢነሣ ግን እኛ የተናገርነው ይበልጥ ግልጽ ይሆናል፤ 16.እርሱ ካህን የሆነው በማይጠፋ የሕይወት ኀይል መሠረት እንጂ፣ እንደ ትውልዱ የሕግ ሥርዐት አይደለም፤ 17.እንዲህ ተብሎ ተመስክሮለታል፤“እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት፣
አንተ ለዘላለም ካህን ነህ።” 18.የቀድሞው ትእዛዝ ደካማና የማይጠቅም በመሆኑ ተሽሯል፤ 19.ሕጉ ማንንም ፍጹም ሊያደርግ ስለማይችል፣ ወደ እግዚአብሔር የምንቀርብበት የተሻለ ተስፋ መጥቷል። 20.ይህ ያለ መሐላ አልሆነም። ሌሎች ካህናት የሆኑት ያለ መሐላ ነው፤ 21.እርሱ ግን ካህን የሆነው በመሐላ ነው፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ተናግሮለታል፤
“ጌታ ማለ፤
አሳቡንም አይለውጥም፤
‘አንተ ለዘላለም ካህን ነህ።’ ” 22.ከዚህ መሐላ የተነሣ፣ ኢየሱስ ለተሻለ ኪዳን ዋስ ሆኗል። 23.በአገልግሎታቸው እንዳይቀጥሉ ሞት ስለ ከለከላቸው፣ የቀድሞዎቹ ካህናት ቍጥራቸው ብዙ ነበር፤ 24.ኢየሱስ ግን ለዘላለም የሚኖር በመሆኑ፣ ክህነቱ የማይሻር ነው። 25.ስለዚህ ስለ እነርሱ እየማለደ ሁልጊዜ በሕይወት ስለሚኖር፣ በርሱ በኩል ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል። 26.እንግዲህ ለእኛ የሚያስፈልገን፣ ቅዱስ፣ ነቀፋ የሌለበት፣ ንጹሕ፣ ከኀጢአተኞች የተለየና ከሰማያት በላይ የከበረ እንደዚህ ያለ ሊቀ ካህናት ነው። 27.እርሱም እንደ ሌሎቹ ሊቃነ ካህናት መጀመሪያ ስለ ራሱ ኀጢአት፣ ከዚያም ስለ ሕዝቡ ኀጢአት በየቀኑ መሥዋዕት ማቅረብ አያስፈልገውም፤ ራሱን በሰጠ ጊዜ፣ ስለ ኀጢአታቸው ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መሥዋዕት አቅርቧልና። 28.ሕጉ ደካማ የሆኑትን ሰዎች ሊቃነ ካህናት አድርጎ ይሾማልና፤ ከሕግ በኋላ የመጣው መሐላ ግን ለዘላለም ፍጹም የሆነውን ልጅ ሾሟል።