Skip to Content
የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን | YEHIWOT MELHEK BETEKIRSTIAN
የ2019 ዓ.ም የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ 📖 ዛሬን አንብብ →

የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን

Yehiwot Melhek Betekirstian

ሳምንት 8 · ቀን 38 (ረቡዕ) 📅 Tikimt 25, 2019

ኦሪት ዘሌዋውያን 15, 16, 17, 18 · መዝሙረ ዳዊት 31 · ወደ ዕብራውያን 6

📖 የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም፦ 1954 መጽሐፍ ቅዱስ አዲሱ መደበኛ ትርጒም

ኦሪት ዘሌዋውያን

ምዕራፍ 15

የሚያረክስ የሰውነት ፈሳሽ

1.እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤ 2.“ለእስራኤላውያን እንዲህ ብላችሁ ንገሯቸው፤ ‘ማንም ሰው ከሰውነቱ ፈሳሽ ነገር ቢወጣ ያ ሰው ርኩስ ነው። 3.ከሰውነቱ የሚወጣው ፈሳሽ መፍሰሱን ቢቀጥል ወይም ባይቀጥል ሰውየው ርኩስ ነው፤ ፈሳሹም ርኩሰት የሚያስከትለው እንደዚህ ነው፤ 4.“ ‘ፈሳሽ ነገር የሚወጣው ሰው የተኛበት የትኛውም መኝታ ርኩስ ይሆናል፤ እርሱ የተቀመጠበት ማንኛውም ነገር ርኩስ ይሆናል። 5.ዐልጋውን የነካ ማንኛውም ሰው ልብሱን ይጠብ፤ ሰውነቱንም በውሃ ይታጠብ፤ እስከ ማታ ድረስ ግን ርኩስ ይሆናል። 6.ፈሳሽ ነገር የሚወጣው ሰው በተቀመጠበት በየትኛውም ነገር ላይ የተቀመጠ ሰው ሁሉ ልብሱን ይጠብ፤ ሰውነቱንም በውሃ ይታጠብ፤ እስከ ማታ ድረስ ግን ርኩስ ይሆናል። 7.“ ‘ፈሳሽ ነገር የሚወጣውን ሰው የነካ ማንኛውም ሰው ልብሱን ይጠብ፤ ሰውነቱንም በውሃ ይታጠብ፤ እስከ ማታ ድረስ ግን ርኩስ ይሆናል። 8.“ ‘ፈሳሽ ነገር የሚወጣው ሰው ንጹሕ በሆነ ሰው ላይ ቢተፋ፣ የተተፋበት ሰው ልብሱን ይጠብ፤ ሰውነቱንም በውሃ ይታጠብ፤ እስከ ማታ ድረስ ግን ርኩስ ይሆናል። 9.“ ‘ፈሳሽ ነገር የሚወጣው ሰው የተቀመጠበት ኮርቻ ሁሉ ርኩስ ይሆናል፤ 10.ከበታቹ ያለውንም ነገር ሁሉ የነካ ማንም ሰው እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል። እነዚህንም ነገሮች የሚያነሣ ማንም ሰው ልብሱን ይጠብ፤ ሰውነቱንም በውሃ ይታጠብ፤ እስከ ማታ ድረስ ግን ርኩስ ይሆናል። 11.“ ‘ፈሳሽ ነገር የሚወጣው ሰው እጁን በውሃ ሳይታጠብ ሌላውን ሰው ቢነካ፣ የተነካው ሰው ልብሱን ይጠብ፤ ሰውነቱንም በውሃ ይታጠብ፤ እስከ ማታ ድረስ ግን ርኩስ ይሆናል። 12.“ ‘ፈሳሽ ነገር የሚወጣው ሰው የነካው የሸክላ ዕቃ ይሰበር፤ ከዕንጨት የተሠራ ዕቃ ከሆነ በውሃ ይታጠብ። 13.“ ‘ፈሳሽ ነገር የሚወጣው ሰው ከፈሳሹ ሲነጻ፣ በሕጉ መሠረት ለመንጻቱ ሰባት ቀን ይቍጠር፤ ልብሱን ይጠብ፤ ሰውነቱንም በምንጭ ውሃ ይታጠብ፤ ንጹሕም ይሆናል። 14.በስምንተኛውም ቀን ሁለት ርግቦች ወይም ሁለት የዋኖስ ጫጩቶች ይዞ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ በእግዚአብሔር ፊት በመቅረብ ለካህኑ ይስጥ። 15.ካህኑም አንዱን ለኀጢአት መሥዋዕት፣ ሌላውንም ለሚቃጠል መሥዋዕት ያቅርብ፤ በዚህ መሠረት ስለ ፈሳሹ በእግዚአብሔር ፊት ለሰውየው ያስተሰርይለታል። 16.“ ‘አንድ ሰው ዘሩ በሚፈስስበት ጊዜ ሰውነቱን በሙሉ በውሃ ይታጠብ፤ እስከ ማታ ድረስ ግን ርኩስ ይሆናል። 17.የፈሰሰው ዘር የነካው ማንኛውም ልብስ ወይም ቍርበት በውሃ ይታጠብ፤ እስከ ማታ ድረስ ግን ርኩስ ይሆናል። 18.አንድ ሰው ከአንዲት ሴት ጋራ ግብረ ሥጋ ፈጽሞ ዘር ቢፈስሰው፣ ሁለቱም በውሃ ይታጠቡ፤ እስከ ማታ ድረስ ግን ርኩሳን ይሆናሉ። 19.“ ‘ሴት ጊዜውን እየጠበቀ የሚመጣው የደም መፍሰስ ቢኖርባት፣ የወር አበባዋ ርኩሰት እስከ ሰባት ቀን ይቈያል፤ በዚህ ጊዜ ማንም ሰው ቢነካት እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል። 20.“ ‘በወር አበባዋ ጊዜ የምትተኛበት ማንኛውም ነገር ርኩስ ይሆናል፤ የተቀመጠችበትም ነገር ርኩስ ይሆናል። 21.መኝታዋን የነካ ማንኛውም ሰው ልብሱን ይጠብ፤ ሰውነቱንም በውሃ ይታጠብ፤ እስከ ማታ ድረስ ግን ርኩስ ይሆናል። 22.የተቀመጠችበትን ማንኛውንም ነገር የነካ ሰው ልብሱን ይጠብ፤ ሰውነቱንም በውሃ ይታጠብ፤ እስከ ማታ ድረስ ግን ርኩስ ይሆናል፤ 23.መኝታዋን ወይም የተቀመጠችበትን ማንኛውንም ነገር የነካ ሰው እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል። 24.“ ‘አንድ ሰው ከርሷ ጋራ ቢተኛና የወር አበባዋ ቢነካው፣ እስከ ሰባት ቀን ድረስ ርኩስ ይሆናል፤ እርሱ የሚተኛበት መኝታ ሁሉ ርኩስ ይሆናል። 25.“ ‘ሴት ከወር አበባዋ ጊዜ ሌላ ብዙ ቀን ደም ቢፈስሳት፣ ወይም የወር አበባዋ ጊዜ ካለፈ በኋላ የደሙ መፍሰስ ባይቋረጥ፣ ልክ እንደ ወር አበባዋ ጊዜ፣ ደም መፍሰሱ እስኪቆም ድረስ ርኩስ ትሆናለች። 26.ደሟ መፍሰሱን በቀጠለበት ጊዜ ሁሉ፣ የምትተኛበት ማንኛውም መኝታ ልክ በወር አበባዋ ጊዜ እንደ ነበረው መኝታ ርኩስ ይሆናል፤ የምትቀመጥበትም ማንኛውም ነገር ልክ እንደ ወር አበባዋ ጊዜ ርኩስ ይሆናል። 27.እነዚህንም የሚነካ ማንኛውም ሰው ርኩስ ይሆናል፤ ልብሱን ይጠብ፤ ሰውነቱንም በውሃ ይታጠብ፤ እስከ ማታ ድረስ ግን ርኩስ ይሆናል። 28.“ ‘ከደሟ ፍሳሽ ሳትነጻ ሰባት ቀን ትቍጠር፤ ከዚያም በኋላ በሥርዐቱ መሠረት ንጹሕ ትሆናለች። 29.በስምንተኛውም ቀን ሁለት ርግቦች ወይም ሁለት የዋኖስ ጫጩቶች ይዛ በመቅረብ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ለካህኑ ትሰጣለች። 30.ካህኑም አንዱን ለኀጢአት መሥዋዕት፣ ሌላውንም ለሚቃጠል መሥዋዕት ያቅርብ፤ በዚህ መሠረት ስለ ፈሳሿ ርኩሰት በእግዚአብሔር ፊት ያስተሰርይላታል። 31.“ ‘በመካከላቸው ያለችውን ማደሪያዬን እንዳያረክሱና በርኩሰታቸው እንዳይሞቱ፣ እስራኤላውያንን ከሚያረክሳቸው ነገር ለዩአቸው።’ ” 32.ፈሳሽ ነገር የሚወጣውን፣ ዘሩም በመፍሰሱ ርኩስ የሆነውን ሰው ሁሉ፣ 33.በወር አበባ ላይ ያለችን ሴት፣ ፈሳሽ ነገር የሚወጣቸውን ወንድ ወይም ሴት፣ በሥርዐቱ መሠረት ርኩስ ከሆነች ሴት ጋራ የሚተኛውን ወንድ በሚመለከት ሕጉ ይኸው ነው።

ምዕራፍ 16

የስርየት ቀን

16፥2-34 ተጓ ምብ – ዘሌ 23፥26-32፤ ዘኍ 29፥7-11
1.በእግዚአብሔር ፊት በቀረቡ ጊዜ ከሞቱት፣ ከሁለቱ የአሮን ልጆች ሞት በኋላ እግዚአብሔር ሙሴን ተናገረው። 2.እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “እኔ በስርየቱ መክደኛ ላይ በደመና ውስጥ እገለጣለሁና ወንድምህ አሮን በመጋረጃው ውስጥ ወዳለው ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ማለት በታቦቱ ላይ ወዳለው ወደ ስርየቱ መክደኛ ፊት፣ በፈለገ ጊዜ ሁሉ እንዳይገባና እንዳይሞት ንገረው። 3.“ወደ ተቀደሰው ስፍራ በሚገባበት ጊዜ፣ አሮን እንዲህ ያድርግ፤ ለኀጢአት መሥዋዕት አንድ ወይፈን፣ ለሚቃጠል መሥዋዕት አንድ አውራ በግ ይዞ ይምጣ፤ 4.የተቀደሰውን የበፍታ ቀሚስ ይልበስ፤ በሰውነቱ ላይ የሚያርፈውን ከበፍታ የተሠራውን የውስጥ ሱሪ ያጥልቅ፤ የበፍታውን መታጠቂያ ይታጠቅ፤ የበፍታውን መጠምጠሚያ ይጠምጥም፤ ልብሶቹ የተቀደሱ በመሆናቸው እነዚህን ከመልበሱ በፊት ሰውነቱን በውሃ ይታጠብ። 5.ከእስራኤል ማኅበረ ሰብ ለኀጢአት መሥዋዕት ሁለት ተባዕት ፍየሎች፣ ለሚቃጠል መሥዋዕት አንድ አውራ በግ ይውሰድ። 6.“አሮን ለራሱና ለቤተ ሰቡ ማስተስረያ ይሆን ዘንድ፣ ወይፈኑን የኀጢአት መሥዋዕት አድርጎ ስለ ራሱ ያቅርብ፤ 7.ሁለቱንም አውራ ፍየሎች ወስዶ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ በእግዚአብሔር ፊት ያቁማቸው። 8.አሮንም አንዱን ዕጣ ለእግዚአብሔር፣ ሌላውን ለሚለቀቀው ፍየል ለማድረግ በሁለቱ ፍየሎች ላይ ዕጣ ይጣል። 9.በዕጣ ለእግዚአብሔር የደረሰውንም ፍየል አምጥቶ ለኀጢአት መሥዋዕት በማድረግ ይሠዋ። 10.ወደ ምድረ በዳ ተለቅቆ ማስተስረያ ይሆን ዘንድ፣ እንዲለቀቅ ዕጣ የወጣበትን ፍየል ከነሕይወቱ በእግዚአብሔር ፊት ያቅርብ። 11.“አሮን ለራሱና ለቤተ ሰቡ ማስተስረያ ይሆን ዘንድ ወይፈኑን የኀጢአት መሥዋዕት አድርጎ ስለ ራሱ ያቅርብ፤ ወይፈኑንም ስለ ራሱ የኀጢአት መሥዋዕት አድርጎ ይረድ። 12.በእግዚአብሔር ፊት ካለው መሠዊያ ፍም ተወስዶ የተሞላበትን ጥና ይያዝ፤ ሁለት እጅ ሙሉ መልካም መዐዛ ያለው ዕጣን ይውሰድ፤ እነዚህንም ወደ መጋረጃው ውስጥ ይዞ ይግባ። 13.እንዳይሞትም የዕጣኑ ጢስ በምስክሩ ላይ ያለውን ስርየት መክደኛ ይሸፍነው ዘንድ፣ በእግዚአብሔር ፊት ዕጣኑን በእሳቱ ላይ ይጨምረው። 14.ከወይፈኑም ደም ወስዶ በስርየቱ መክደኛ ፊተኛው ወገን ላይ በጣቱ ይርጭ፤ ደግሞም በስርየቱ መክደኛ ትይዩ በጣቱ ሰባት ጊዜ ይርጭ። 15.“ፍየሉንም ለሕዝቡ የኀጢአት መሥዋዕት አድርጎ ይረደው፤ ደሙንም ወደ መጋረጃው ውስጥ ወስዶ በወይፈኑ ደም እንዳደረገው በዚህኛው ያድርግ፤ ደሙን በስርየቱ መክደኛ ላይ፣ እንዲሁም በመክደኛው ትይዩ ይርጭ። 16.ከእስራኤላውያን ርኩሰትና ዐመፅ፣ ከየትኛውም ኀጢአታቸው ይነጻ ዘንድ በዚህ ሁኔታ ለቅድስተ ቅዱሳኑ ያስተሰርይለታል፤ በርኩሰታቸው መካከል በእነርሱ ዘንድ ላለችውም የመገናኛዋ ድንኳን እንደዚሁ ያደርጋል። 17.አሮን ለማስተስረይ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ለራሱ፣ ለቤተ ሰቡና ለእስራኤል ማኅበረ ሰብ ሁሉ አስተስርዮ እስኪወጣ ድረስ ማንም ሰው በመገናኛው ድንኳን ውስጥ አይገኝ። 18.“ከዚያም መጥቶ በእግዚአብሔር ፊት ወዳለው መሠዊያ ይምጣ፤ ለመሠዊያውም ያስተስርይለት፤ ከወይፈኑና ከፍየሉ ደም ወስዶ የመሠዊያውን ቀንዶች ሁሉ ያስነካ፤ 19.ከእስራኤላውያንም ርኩሰት መሠዊያውን ለማንጻትና ለመቀደስ ከደሙ ወስዶ በጣቱ ሰባት ጊዜ ይርጭበት። 20.“አሮን ለቅድስተ ቅዱሳኑ፣ ለመገናኛው ድንኳንና ለመሠዊያው የሚያደርገውን ስርየት ከፈጸመ በኋላ፣ በሕይወት ያለውን ፍየል ወደ ፊት ያቅርበው። 21.ሁለት እጆቹን በሕይወት ባለው ፍየል ራስ ላይ ይጫን፤ በላዩም የእስራኤላውያንን ክፋትና ዐመፅ፣ ኀጢአታቸውንም ሁሉ ይናዘዝበት፤ እነዚህንም በፍየሉ ራስ ላይ ይጫን፤ ፍየሉንም ለዚሁ ተግባር በተመደበ ሰው እጅ ወደ ምድረ በዳ ይስደደው። 22.ፍየሉም ኀጢአታቸውን ሁሉ ተሸክሞ ወደ ምድረ በዳ ይሄዳል፤ ሰውየውም ፍየሉን ሰው ሊኖርበት በማይችል ስፍራ ይልቀቀው። 23.“ከዚህ በኋላ አሮን ወደ መገናኛው ድንኳን ሄዶ፣ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ሊገባ ሲል የለበሳቸውን የበፍታ ልብሶች አውልቆ በዚያው ይተዋቸው። 24.በተቀደሰውም ስፍራ ሰውነቱን በውሃ ይታጠብ፤ የዘወትር ልብሱንም ይልበስ፤ ከዚያም ወጥቶ ለራሱ ማስተስረያ የሚቃጠል መሥዋዕት ያቅርብ፤ ለሕዝቡም ማስተስረያ የሚቃጠል መሥዋዕት ያቅርብ። 25.የኀጢአት መሥዋዕቱንም በመሠዊያው ላይ ያቃጥል። 26.“የሚለቀቀውን ፍየል የወሰደው ሰው ልብሱን ይጠብ፤ ሰውነቱንም በውሃ ይታጠብ፤ ከዚህ በኋላ ወደ ሰፈር መግባት ይችላል። 27.ደማቸው ለማስተስረያነት ወደ ቅድስተ ቅዱሳን የገባው፣ ለኀጢአት መሥዋዕት የቀረቡት ወይፈንና ፍየል ከሰፈር ውጭ ተወስደው ቈዳቸው፣ ሥጋቸውና ፈርሳቸው ይቃጠል። 28.እነዚህንም የሚያቃጥል ሰው ልብሱን ይጠብ፤ ሰውነቱንም በውሃ ይታጠብ፤ ከዚህ በኋላ ወደ ሰፈር መግባት ይችላል። 29.“ለእናንተ የተሰጣችሁ የዘላለም ሥርዐት ይህ ነው፦ ሰባተኛው ወር በገባ በዐሥረኛው ቀን ሰውነታችሁን አድክሙ፤ የአገሩ ተወላጅም ሆነ በመካከላችሁ የሚኖር መጻተኛ ምንም ሥራ አይሥራ፤ 30.የምትነጹበት ስርየት በዚህች ዕለት ይደረግላችኋልና፤ በእግዚአብሔርም ፊት ከኀጢአታችሁ ሁሉ ትነጻላችሁ። 31.ይህች የፍጹም ዕረፍት ሰንበት ናት፤ ሰውነታችሁን አድክሙባት፤ የዘላለም ሥርዐት ናት። 32.ሊቀ ካህናት ለመሆን አባቱን በመተካት የተቀባና የተሾመ ካህን ያስተስርይ፤ የተቀደሰውንም የበፍታ ልብስ ይልበስ፤ 33.ለቅድስተ ቅዱሳኑ፣ ለመገናኛው ድንኳንና ለመሠዊያው፣ ለካህናቱና ለማኅበረ ሰቡ ሁሉ ያስተስርይ። 34.“ይህ የዘላለም ሥርዐት ይሁናችሁ፤ በዚህም ሥርዐት መሠረት ለእስራኤላውያን ኀጢአት ሁሉ በዓመት አንድ ጊዜ ስርየት ይደረግ።”
እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘ እንዲሁ ተደረገ።

ምዕራፍ 17

ደም መብላት ስለ መከልከሉ

1.እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 2.“ለአሮንና ለልጆቹ፣ ለእስራኤላውያንም ሁሉ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤ ‘እግዚአብሔር ያዘዘው ይህ ነው፤ 3.ማንኛውም እስራኤላዊ በሰፈር ውስጥ ወይም ከሰፈር ውጭ በሬ፣ በግ ወይም ፍየል ቢያርድ፣ 4.በእግዚአብሔር ማደሪያ ፊት ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አድርጎ ለማቅረብ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ባያመጣው፣ ያ ሰው በከንቱ ደም እንዳፈሰሰ ይቈጠራል፤ ደም በማፍሰሱም ከወገኖቹ ተለይቶ ይጥፋ። 5.እስራኤላውያን የሚሠዉትን መሥዋዕት ወደ እግዚአብሔር የሚያመጡበት ምክንያት ይህ ነው። ይህንም ካህኑ ዘንድ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ አምጥተው ለእግዚአብሔር የኅብረት መሥዋዕት በማድረግ ያቅርቡ። 6.ካህኑም ደሙን በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ባለው በእግዚአብሔር መሠዊያ ላይ ይርጭ፤ ሥቡንም እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሽታ እንዲሆን ያቃጥል። 7.ከዚህ በፊት ላመነዘሩባቸው አጋንንት ከእንግዲህ ወዲህ ማንኛውንም መሥዋዕት ሊሠዉ አይገባም። ይህ ለእነርሱና ከእነርሱ በኋላ ለሚነሣው ትውልድ ሁሉ የዘላለም ሥርዐት ይሁን።’ 8.“እንዲህም በላቸው፤ ‘የሚቃጠል መሥዋዕት ወይም ሌላ መሥዋዕት የሚያቀርብ ማንኛውም እስራኤላዊ ወይም በመካከላቸው የሚኖር ማንኛውም መጻተኛ፣ 9.ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ለእግዚአብሔር ባያቀርብ፣ ያ ሰው ከወገኖቹ ተለይቶ ይጥፋ። 10.“ ‘ማንኛውም እስራኤላዊ ወይም በመካከላቸው የሚኖር ማንኛውም መጻተኛ ደም ቢበላ፣ ደም በሚበላው በዚያ ሰው ላይ ፊቴን አከብድበታለሁ፤ ከወገኖቹም ለይቼ አጠፋዋለሁ፤ 11.የፍጡር ሕይወት በደሙ ውስጥ ነውና፤ በመሠዊያ ላይ ለሕይወታችሁ ማስተስረያ እንዲሆን ደሙን ሰጥቻችኋለሁ፤ ለሰውም ሕይወት ስርየት የሚያስገኝ ደም ነው። 12.ስለዚህ እስራኤላውያንን፣ “ከእናንተ ማንም ደም አይብላ፤ በመካከላችሁ የሚኖር መጻተኛም ቢሆን ደም አይብላ” አልሁ። 13.“ ‘እንዲበላ የተፈቀደውን ማንኛውንም እንስሳ ወይም ወፍ ዐድኖ የያዘ ማንኛውም እስራኤላዊ ወይም በመካከላችሁ የሚኖር ማንኛውም መጻተኛ ደሙን ከውስጡ ያፍስስ፤ ዐፈርም ያልብሰው፤ 14.የማንኛውም ፍጡር ሕይወት ደሙ ነውና። ስለዚህ እስራኤላውያንን፣ “የፍጡር ሁሉ ሕይወት ደሙ ነውና የማንኛውንም ፍጡር ደም አትብሉ፤ የበላው ሰው ሁሉ ተለይቶ ይጥፋ” አልኋቸው። 15.“ ‘ሞቶ የተገኘውን ወይም አውሬ የዘነጠለውን የበላ ማንኛውም የአገር ተወላጅ ወይም መጻተኛ ልብሱን ይጠብ፤ ሰውነቱንም በውሃ ይታጠብ፤ በሥርዐቱ መሠረት እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል፤ ከዚያም በኋላ ንጹሕ ይሆናል። 16.ልብሱን ባያጥብ፣ ሰውነቱንም ባይታጠብ ግን ኀጢአት ሠርቷልና ይጠየቅበታል።’ ”

ምዕራፍ 18

1.እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 2.“ለእስራኤላውያን እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤ ‘እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ፤ 3.በኖራችሁበት በግብጽ እነርሱ እንደሚያደርጉት አታድርጉ፤ እኔ በማስገባችሁ በከነዓን እንደሚያደርጉትም አታድርጉ፤ ልማዳቸውንም አትከተሉ። 4.ሕጌን ታዘዙ፤ ሥርዐቴንም በጥንቃቄ ጠብቁ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ። 5.ሥርዐቴንና ሕጌን ጠብቁ፤ እነዚህን የሚጠብቅ ሰው በእነርሱ ሕያው ይሆናልና፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 6.“ ‘ማንም ሰው ግብረ ሥጋ ለመፈጸም ወደ ማንኛውም የሥጋ ዘመዱ አይቅረብ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 7.“ ‘ከእናትህ ጋራ ግብረ ሥጋ በመፈጸም አባትህን አታዋርድ፤ እናትህ ናት፤ ከርሷ ጋራ በግብረ ሥጋ አትገናኝ። 8.“ ‘ከአባትህ ሚስት ጋራ ግብረ ሥጋ አትፈጽም፤ ይህ አባትህን ያዋርዳል። 9.“ ‘ከእኅትህ ጋራ ግብረ ሥጋ አትፈጽም፤ በቤት ወይም በውጭ የተወለደች ብትሆን፣ ከአባትህ ወይም ከእናትህ ሴት ልጅ ጋራ በግብረ ሥጋ አትገናኝ። 10.“ ‘ከወንድ ልጅህ ሴት ልጅ ወይም ከሴት ልጅህ ሴት ልጅ ጋራ ግብረ ሥጋ አትፈጽም፤ ይህ አንተን ያዋርዳል። 11.“ ‘የአባትህ ሚስት፣ ለአባትህ ከወለደቻት ሴት ልጅ ጋራ ግብረ ሥጋ አትፈጽም፤ እኅትህ ናት። 12.“ ‘ከአባትህ እኅት ጋራ ግብረ ሥጋ አትፈጽም፤ እርሷ የአባትህ የሥጋ ዘመድ ናት። 13.“ ‘ከእናትህ እኅት ጋራ ግብረ ሥጋ አትፈጽም፤ እርሷ የእናትህ የሥጋ ዘመድ ናትና። 14.“ ‘ከአባትህ ወንድም ሚስት ጋራ ግብረ ሥጋ በመፈጸም፣ የአባትህን ወንድም አታዋርድ፤ እርሷ አክስትህ ናት። 15.“ ‘ከምራትህ ጋራ ግብረ ሥጋ አትፈጽም፤ የልጅህ ሚስት ናት፤ ከርሷም ጋራ በግብረ ሥጋ አትገናኝ። 16.“ ‘ከወንድምህ ሚስት ጋራ ግብረ ሥጋ አትፈጽም፤ ይህ ወንድምህን ያዋርዳል። 17.“ ‘ከእናቲቱና ከሴት ልጇ ጋራ ግብረ ሥጋ አትፈጽም፤ ከወንድ ልጇ ሴት ልጅ ወይም ከሴት ልጇ ሴት ልጅ ጋራ ግብረ ሥጋ አትፈጽም፤ እነርሱ የሥጋ ዘመዶቿ ናቸው፤ ይህም ጸያፍ ነው። 18.“ ‘ሚስትህ በሕይወት እያለች እኅቷን ጣውንት አድርገህ አታግባት፤ ከርሷም ጋራ ግብረ ሥጋ አትፈጽም። 19.“ ‘በወር አበባዋ ርኩሰት ጊዜ ግብረ ሥጋ ለመፈጸም ወደ ሴት አትቅረብ። 20.“ ‘ከባልንጀራህ ሚስት ጋራ ግብረ ሥጋ በመፈጸም፣ ራስህን በርሷ አታርክስ። 21.“ ‘ከልጆችህ ማንኛውንም ለሞሎክ እንዲሠዋ አሳልፈህ አትስጥ፤ የአምላክህንም ስም አታርክስ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። 22.“ ‘ከሴት ጋራ እንደሚደረገው ሁሉ ከወንድ ጋራ አትተኛ፤ ይህ አስጸያፊ ነው። 23.“ ‘ከእንስሳ ጋራ ግብረ ሥጋ በመፈጸም ራስህን አታርክስ። ሴትም ከእንስሳ ጋራ ግብረ ሥጋ ለመፈጸም ራሷን አታቅርብ፤ ይህ አስጸያፊ ምግባር ነው። 24.“ ‘ከእነዚህ በአንዱ እንኳ ራሳችሁን አታርክሱ፤ ከፊታችሁ የማሳድዳቸው አሕዛብ በእነዚህ ሁሉ ረክሰዋልና። 25.ምድሪቱም ሳትቀር ረከሰች፤ እኔም ስለ ኀጢአቷ ቀጣኋት፤ ስለዚህ የሚኖሩባትን ሰዎች ተፋቻቸው። 26.እናንተ ግን ሥርዐቴንና ሕጌን ጠብቁ፤ እናንተ የአገር ተወላጆችና በመካከላችሁ የሚኖሩ መጻተኞች ከእነዚህ አስጸያፊ ድርጊቶች ማንኛውንም አትፈጽሙ። 27.ከእናንተ በፊት በምድሪቱ የኖሩ ሰዎች እነዚህን አስጸያፊ ነገሮች ሁሉ ስለ ፈጸሙ፣ ምድሪቱ ረክሳለች። 28.እናንተም ምድሪቱን ብታረክሷት፣ ከእናንተ በፊት የነበረውን ሕዝብ እንደ ተፋች እንዲሁ እናንተንም ትተፋችኋለች። 29.“ ‘ከእነዚህ አስጸያፊ ድርጊቶች ማንኛውንም የሚፈጽም ሰው ሁሉ ከወገኑ ተለይቶ ይጥፋ። 30.ትእዛዜን ጠብቁ፤ ከእናንተ በፊት በምድሪቱ የኖሩ ሰዎች ካደረጓቸው አስጸያፊ ድርጊቶች አንዱንም አትፈጽሙ፤ በእነዚህም ራሳችሁን አታርክሱ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።’ ”

መዝሙረ ዳዊት

ምዕራፍ 31

31፥1-4 ተጓ ምብ – መዝ 71፥1-3
1.ለመዘምራን አለቃ፤ የዳዊት መዝሙር።
1 እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተን መጠጊያ አደረግሁ፤
ከቶም አልፈር፤
በጽድቅህም ታደገኝ።
2.ጆሮህን ወደ እኔ አዘንብል፤
ፈጥነህ አድነኝ፤
መጠጊያ ዐለት ሁነኝ፤
ታድነኝም ዘንድ ምሽግ ሁነኝ።
3.አንተ ዐለቴና መጠጊያዬ ነህና፣
ስለ ስምህ ስትል ምራኝ፤
መንገዱንም ጠቍመኝ።
4.አንተ መጠጊያዬ ነህና፣
በስውር ከተዘረጋብኝ ወጥመድ አውጣኝ።
5.መንፈሴን በእጅህ እሰጣለሁ፤
እግዚአብሔር የእውነት አምላክ ሆይ፤
አንተ ተቤዠኝ።
6.ለከንቱ ጣዖታት ስፍራ የሚሰጡትን ጠላሁ፤
ነገር ግን በእግዚአብሔር ታመንሁ።
7.በምሕረትህ ደስ እሰኛለሁ፤ ሐሤትም አደርጋለሁ፤
መከራዬን አይተሃልና፤
የነፍሴንም ጭንቀት ዐውቀሃል።
8.ለጠላት አሳልፈህ አልሰጠኸኝም፤
ነገር ግን እግሮቼን ሰፊ ቦታ ላይ አቆምሃቸው።
9.እግዚአብሔር ሆይ፤ በመከራ ውስጥ ነኝና ማረኝ፤
ዐይኖቼ በሐዘን ደክመዋል፤
ነፍስና ሥጋዬም ዝለዋል።
10.ሕይወቴ በመጨነቅ፣
ዕድሜዬም በመቃተት ዐለቀ፤
ከመከራዬ የተነሣ ጕልበት ከዳኝ፤
ዐጥንቴም በውስጤ ሟሟ።
11.ከጠላቶቼ ሁሉ የተነሣ፣
ለጎረቤቶቼ መዘባበቻ፣
ለወዳጆቼ መሣለቂያ ሆኛለሁ፤
መንገድ ላይ የሚያገኙኝም ይሸሹኛል።
12.እንደ ሞተ ሰው ተረሳሁ፤
እንደ ተሰበረ የሸክላ ዕቃም ተቈጠርሁ።
13.የብዙ ሰዎችን ሹክሹክታ እሰማለሁና፤
ዙሪያው ሁሉ ሽብር አለ፤
በእኔ ላይ ባሤሩ ጊዜ፣
ሕይወቴን ለማጥፋት ዶለቱ።
14.እግዚአብሔር ሆይ፤ እኔ ግን በአንተ እታመናለሁ፤
“አንተ አምላኬ ነህ” እልሃለሁም።
15.ዘመኔ ያለው በእጅህ ነው፤
ከጠላቶቼ እጅ ታደገኝ፤
ከሚያሳድዱኝም አድነኝ።
16.ፊትህን በአገልጋይህ ላይ አብራ፤
በምሕረትህም አድነኝ።
17.እግዚአብሔር ሆይ፤
ወደ አንተ እጮኻለሁና አልፈር፤
ክፉዎች ግን ይፈሩ፤
ሲኦል ገብተውም ጸጥ ይበሉ።
18.በጻድቁ ላይ በእብሪት የሚናገሩ፣
ትዕቢትንና ንቀትን የተሞሉ፣
ዋሾ ከንፈሮች ድዳ ይሁኑ።
19.በሰዎች ልጆች ፊት፣
ለሚፈሩህ ያስቀመጥሃት፣
መጠጊያ ላደረጉህም ያዘጋጀሃት፣
በጎነትህ ምንኛ በዛች!
20.ከሰዎች ሤራ፣
በማደሪያህ ውስጥ ትሸሽጋቸዋለህ፤
ከአንደበት ጭቅጭቅም፣
በድንኳንህ ውስጥ ትከልላቸዋለህ።
21.በተከበበች ከተማ ውስጥ፣
የሚያስደንቅ ምሕረቱን ያሳየኝ፣
እግዚአብሔር ይባረክ።
22.እኔ በደነገጥሁ ጊዜ፣
“ከዐይንህ ፊት ተወግጃለሁ” አልሁ፤
አንተ ግን ወደ አንተ ስጮኽ፣
የልመናዬን ቃል ሰማህ።
23.እናንተ ቅዱሳኑ ሁሉ፣ እግዚአብሔርን ውደዱት!
እግዚአብሔር ታማኞችን ይጠብቃል፤
ትዕቢተኞችን ግን ፈጽሞ ይበቀላቸዋል።
24.እግዚአብሔርን ተስፋ የምታደርጉ ሁሉ፤
በርቱ፤ ልባችሁም ይጽና።

ወደ ዕብራውያን

ምዕራፍ 6

1.ስለዚህ ስለ ክርስቶስ የተሰጠውን የመጀመሪያ ትምህርት ትተን ወደ ብስለት እንሂድ፤ ከሞተ ሥራ ንስሓ ስለ መግባትና በእግዚአብሔር ስለ ማመን እንደ ገና መሠረትን አንጣል፤ 2.እንዲሁም ስለ ጥምቀቶች፣ እጆችን ስለ መጫን፣ ስለ ሙታን ትንሣኤና ስለ ዘላለም ፍርድ ትምህርት እንደ ገና አንመሥርት። 3.እግዚአብሔር ቢፈቅድ ይህን እናደርጋለን። 4.አንድ ጊዜ ብርሃን የበራላቸውን፣ ሰማያዊውን ስጦታ የቀመሱትን፣ ከመንፈስ ቅዱስ ተካፋዮች የሆኑትን፣ 5.መልካሙን የእግዚአብሔር ቃልና የሚመጣውን ዓለም ኀይል የቀመሱትን፣ 6.በኋላ ግን የካዱትን እንደ ገና ወደ ንስሓ መመለስ አይቻልም፤ ምክንያቱም እነርሱ ለገዛ ጥፋታቸው የእግዚአብሔርን ልጅ እንደ ገና ይሰቅሉታል፤ ያዋርዱታልም። 7.ዘወትር በርሷ ላይ የሚወርደውን ዝናብ የምትጠጣና ለሚያርሷትም ፍሬ የምትሰጥ መሬት ከእግዚአብሔር በረከትን ትቀበላለች። 8.ነገር ግን እሾኽና አሜከላ የምታበቅል መሬት ዋጋ ቢስ ትሆናለች፤ መረገሚያዋም ተቃርቧል፤ መጨረሻዋም በእሳት መቃጠል ነው። 9.ወዳጆች ሆይ፤ ምንም እንኳ እንደዚህ ብንናገርም፣ ከድነታችሁ ጋራ የተያያዘ ታላቅ ነገር እንዳላችሁ ርግጠኞች ነን። 10.እግዚአብሔር ዐመፀኛ አይደለም፤ እርሱ ሥራችሁን እንዲሁም በፊትም ሆነ አሁን ቅዱሳንን በመርዳት ስለ ስሙ ያሳያችሁትን ፍቅር አይረሳም። 11.የተሰጠው ተስፋ እስኪፈጸም ድረስ እያንዳንዳችሁ እንዲህ ያለውን ትጋት እስከ መጨረሻ እንድታሳዩ እንመኛለን። 12.በእምነትና በትዕግሥት የተስፋውን ቃል የሚወርሱትን እንድትመስሉ እንጂ ዳተኞች እንድትሆኑ አንፈልግም።

የእግዚአብሔር የተስፋ ቃል ርግጠኛነት

13.እግዚአብሔር ለአብርሃም ተስፋ በሰጠው ጊዜ፣ የሚምልበት ከርሱ የሚበልጥ ሌላ ባለመኖሩ፣ በራሱ ማለ፤ 14.እንዲህም አለ፤ “በርግጥ እባርክሃለሁ፤ ዘርህንም አበዛዋለሁ።” 15.አብርሃምም በትዕግሥት ከጠበቀ በኋላ የተሰጠውን ተስፋ አገኘ። 16.ሰዎች ከእነርሱ በሚበልጥ ይምላሉ፤ መሐላውም የተባለውን ነገር ስለሚያጸና በመካከላቸው የተነሣው ክርክር ሁሉ ይወገዳል። 17.እግዚአብሔር የማይለወጥ ዐላማውን ለተስፋው ቃል ወራሾች ግልጽ ለማድረግ ስለ ፈለገ፣ በመሐላ አጸናው። 18.እግዚአብሔር ከቶ ሊዋሽ አይችልም፤ እርሱ በሁለት በማይለወጡ ነገሮች በፊታችን ያለውን ተስፋ ለመያዝ ወደ እርሱ ለሸሸን ለእኛ ብርቱ መጽናናት እንድናገኝ አድርጓል። 19.እኛም የነፍስ መልሕቅ የሆነ ጽኑና አስተማማኝ ተስፋ አለን፤ ይህም ተስፋ ከመጋረጃው በስተጀርባ ወዳለው ውስጠኛ መቅደስ ይገባል። 20.ይህም ስፍራ ኢየሱስ ስለ እኛ ቀድሞ የገባበት ነው። እርሱም እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ሊቀ ካህናት ሆኗል።