Skip to Content
የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን | YEHIWOT MELHEK BETEKIRSTIAN
የ2019 ዓ.ም የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ 📖 ዛሬን አንብብ →

የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን

Yehiwot Melhek Betekirstian

ሳምንት 8 · ቀን 37 (ማክሰኞ) 📅 Tikimt 24, 2019

ኦሪት ዘሌዋውያን 12, 13, 14 · መዝሙረ ዳዊት 111 · ወደ ዕብራውያን 5

📖 የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም፦ 1954 መጽሐፍ ቅዱስ አዲሱ መደበኛ ትርጒም

ኦሪት ዘሌዋውያን

ምዕራፍ 12

ከወሊድ በኋላ የመንጻት ሥርዐት

1.እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 2.“እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፤ ‘ሴት አርግዛ ወንድ ልጅ በምትወልድበት ጊዜ፣ ልክ እንደ ወር አበባዋ ጊዜ እስከ ሰባት ቀን ትረክሳለች። 3.ሕፃኑም በስምንተኛው ቀን ሸለፈቱን ይገረዝ። 4.ሴትዮዋም ከደሟ እስክትነጻ ድረስ ሠላሳ ሦስት ቀን ትቈይ፤ የመንጻቷም ወራት እስኪፈጸም ድረስ ማንኛውንም የተቀደሰ ነገር አትንካ፤ ወደ ቤተ መቅደስም አትግባ። 5.ነገር ግን የወለደችው ሴት ልጅ ከሆነ፣ እንደ ወር አበባዋ ጊዜ ሁለት ሳምንት ትረክሳለች፤ ከዚያም ከደሟ እስክትነጻ ስድሳ ስድስት ቀን ትቈይ። 6.“ ‘ሴትዮዋ ወንድ ወይም ሴት ልጅዋን ወልዳ የመንጻቷ ጊዜ ሲፈጸም፣ ለሚቃጠል መሥዋዕት የአንድ ዓመት ጠቦት፣ ለኀጢአት መሥዋዕት አንድ የዋኖስ ጫጩት ወይም አንድ ርግብ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ወስዳ ካህኑ ዘንድ ታቅርብ። 7.ካህኑም በእግዚአብሔር ፊት ያቅርበው፤ ያስተስርይላትም፤ ሴትዮዋም ከደሟ ፈሳሽ ትነጻለች።
“ ‘ሴትዮዋ ወንድ ወይም ሴት ብትወልድ ሕጉ ይኸው ነው።
8.ጠቦት ለማምጣት ዐቅሟ ካልፈቀደ፣ ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የርግብ ጫጩቶች፣ አንዱ ለሚቃጠል መሥዋዕት፣ ሌላው ደግሞ ለኀጢአት መሥዋዕት ታቅርብ፤ በዚህም ካህኑ ያስተሰርይላታል፤ እርሷም ትነጻለች።’ ”

ምዕራፍ 13

ተላላፊ የቈዳ በሽታ

1.እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤ 2.“ማንኛውም ሰው በሰውነቱ ቈዳ ላይ ዕብጠት ወይም ችፍታ ወይም ቋቍቻ ቢወጣበትና ይህም ወደ ተላላፊ የቈዳ በሽታ የሚለወጥበት ከሆነ፣ ወደ ካህኑ አሮን ወይም ካህናት ከሆኑት ልጆቹ ወደ አንዱ ያምጡት። 3.ካህኑም በሰውየው ቈዳ ላይ ያለውን ቍስል ይመርምር፤ በቍስሉ በተበከለው አካባቢ ያለው ጠጕር ወደ ነጭነት ተለውጦ ቢያገኘውና ቦታው ጐድጕዶ ወደ ውስጥ ቢገባ፣ ይህ ተላላፊ የቈዳ በሽታ ነው። ካህኑም መርምሮ ይህን ባወቀ ጊዜ፣ ሰውየው በአምልኮው ሥርዐት መሠረት ርኩስ መሆኑ ይገለጽ። 4.በቈዳው ላይ ያለው ቋቍቻ ነጭ ሆኖ ቢታይ፣ ነገር ግን ከቈዳው በታች ዘልቆ ባይገባና በቦታው ላይ የሚገኘው ጠጕር ወደ ነጭነት ባይለወጥ፣ ካህኑ በሽተኛውን ሰባት ቀን ያግልለው። 5.በሰባተኛውም ቀን ካህኑ በሽተኛውን ይመርምረው፤ ቍስሉ ለውጥ ካላመጣና በቈዳውም ላይ ካልተስፋፋ እንደ ገና ሰባት ቀን ያግልለው። 6.በሰባተኛው ቀን ካህኑ እንደ ገና ይመርምረው፤ ቍስሉ ከከሰመና በቈዳው ላይ ካልተስፋፋ፣ ካህኑ ሰውየው ንጹሕ መሆኑን ያስታውቅ፤ ቍስሉ ችፍታ እንጂ ሌላ አይደለም። ሰውየው ልብሱን ይጠብ፤ ንጹሕም ይሆናል። 7.ራሱን ለካህን አሳይቶ መንጻቱ ከታወቀ በኋላ፣ ችፍታው በቈዳው ላይ እየተስፋፋ ከሆነ፣ እንደ ገና ካህኑ ፊት ይቅረብ፤ 8.ካህኑም ይመርምረው፤ ችፍታው በቈዳው ላይ ተስፋፍቶ ከተገኘ፣ ካህኑ ሰውየው ርኩስ መሆኑን ያስታውቅ፤ ተላላፊ የቈዳ በሽታ ነው። 9.“ማንኛውም ሰው ተላላፊ የቈዳ በሽታ ከያዘው፣ ወደ ካህኑ ያምጡት፤ 10.ካህኑም ይመርምረው፤ በሰውነቱ ላይ ጠጕሩን ወደ ነጭነት የለወጠ ነጭ ዕባጭ ካለና በዕብጠቱም ውስጥ ቀይ ሥጋ ቢታይ፣ 11.ሥር የሰደደ የቈዳ በሽታ ነውና ሰውየው ርኩስ መሆኑን ካህኑ ያስታውቅ፤ ርኩስ መሆኑ ግልጽ ስለ ሆነም ሰውየውን አያግልለው። 12.“ደዌው በአካላቱ ሁሉ ላይ በመውጣት በሽተኛውን ከራስ ጠጕር እስከ እግር ጥፍር ያለበሰው መሆኑን ካህኑ እስካየ ድረስ፣ 13.ካህኑ ይመርምረው፤ ደዌው የሰውየውን ሰውነት ሙሉ በሙሉ ሸፍኖት ከተገኘ፣ ያ ሰው ንጹሕ መሆኑን ያስታውቅ፤ ሙሉ በሙሉ ነጭ ስለ ሆነ ንጹሕ ነው፤ 14.ነገር ግን ቍስሉ አመርቅዞ ቀይ ሥጋ ቢታይበት ርኩስ ይሁን። 15.ካህኑም የተገለጠውን ቀይ ሥጋ በሚያይበት ጊዜ ርኩስ መሆኑን ያስታውቅ፤ ቀይ ሥጋ ርኩስ ስለ ሆነ፣ ተላላፊ በሽታ ነው። 16.ቀይ ሥጋ ተለውጦ ከነጣ ግን ወደ ካህኑ ይሂድ፤ 17.ካህኑም ይመርምረው፤ ቍስሎች ወደ ነጭነት ተለውጠው ከተገኙ፣ የታመመው ሰው ንጹሕ መሆኑን ካህኑ ያስታውቅ፤ ንጹሕም ይሆናል። 18.“አንድ ሰው በገላው ላይ ዕባጭ ወጥቶ ቢድን፣ 19.ዕባጩ በነበረበት ቦታ ላይም ነጭ ዕብጠት ወይም ነጣ ያለ ቀይ ቋቍቻ ቢታይ፣ ካህኑ ዘንድ ይቅረብ። 20.ካህኑም ይመርምረው፤ ከቈዳው በታች ዘልቆ የገባ ቢሆን በቦታውም ያለው ጠጕር ቢነጣ፣ ሰውየው ርኩስ መሆኑን ካህኑ ያስታውቅ። 21.ነገር ግን ካህኑ በሚመረምርበት ጊዜ ነጭ ጠጕር በውስጡ ከሌለ፣ ዘልቆ ካልገባና የከሰመ ቢሆን፣ ካህኑ ሰባት ቀን ያግልለው። 22.በቈዳው ላይ ተስፋፍቶ ካገኘውም፣ ርኩስ መሆኑን ካህኑ ያስታውቅ፤ የሚተላለፍ ነው። 23.ቋቍቻው ግን ባለበት ከቈየና ወደ ሌላ ስፍራ ካልተስፋፋ፣ የዕባጩ ጠባሳ እንጂ ሌላ አይደለም፤ ካህኑም ንጹሕ መሆኑን ያስታውቅ። 24.“አንድ ሰው እሳት ቈዳውን ቢያቃጥለውና በተቃጠለው ስፍራ ነጣ ያለ ቀይ ወይም ነጭ ቋቍቻ ቢታይበት፣ 25.ካህኑ ይመርምረው፤ ቋቍቻው ባለበትም ቦታ ያለው ጠጕር ቢነጣና ከቈዳው በታች ዘልቆ ቢገባ፣ በቃጠሎው ሰበብ ከውስጥ የወጣ ተላላፊ በሽታ ነው፤ ሰውየው ርኩስ መሆኑን ካህኑ ያስታውቅ፤ ተላላፊ የቈዳ በሽታ ነው። 26.ነገር ግን ካህኑ በሚመረምርበት ጊዜ ነጭ ጠጕር የሌለበት፣ ከቈዳውም በታች ዘልቆ ያልገባና የከሰመ ቢሆን፣ ካህኑ ሰውየውን ሰባት ቀን ያግልለው። 27.በሰባተኛው ቀን ካህኑ ይመርምረው፤ በሽታውም በቈዳው ላይ ተስፋፍቶ ቢያገኘው፣ ሰውየው ርኩስ መሆኑን ካህኑ ያስታውቅ፤ ተላላፊ የቈዳ በሽታ ነው። 28.ቋቍቻ ባለበት ከቈየና በቈዳው ላይ ካልተስፋፋ፣ ይልቁንም እየከሰመ ከሄደ፣ በቃጠሎው ሰበብ የተከሠተ ዕብጠት ነውና ካህኑ ንጹሕ መሆኑን ያስታውቅ፤ የቃጠሎው ጠባሳ እንጂ ሌላ አይደለም። 29.“በወንድ ወይም በሴት ዐናት ወይም አገጭ ላይ ቍስል ቢወጣ፣ 30.ካህኑ ቍስሉን ይመርምር፤ ከቈዳው በታች ዘልቆ ከገባ፣ በውስጡም ያለው ጠጕር ቢጫና ቀጭን ከሆነ ያ ሰው ርኩስ መሆኑን ካህኑ ያስታውቅ፤ የሚያሳክክ የራስ ወይም የአገጭ ተላላፊ በሽታ ነው። 31.ካህኑ እንዲህ ዐይነቱን ቍስል በሚመረምርበት ጊዜ፣ ከቈዳው በታች ዘልቆ ካልገባና በውስጡም ጥቍር ጠጕር ከሌለ፣ ካህኑ ሰውየውን ሰባት ቀን ያግልለው። 32.ካህኑም በሰባተኛው ቀን ቍስሉን ይመርምር፤ የሚያሳክከው ቦታ ያልሰፋ፣ ቢጫ ጠጕር የሌለውና ከቈዳው በታች ዘልቆ ያልገባ ከሆነ፣ 33.ከቈሰለው ቦታ በቀር ጠጕሩን ይላጭ፤ ካህኑ ሰባት ተጨማሪ ቀን ሰውየውን ያግልል። 34.ካህኑ በሰባተኛው ቀን የሚያሳክከውን የሰውየውን ቍስል ይመርምር፤ በቈዳው ላይ ካልሰፋና ከቈዳው በታች ዘልቆ ካልገባ ካህኑ ያ ሰው ንጹሕ መሆኑን ያስታውቅ፤ ልብሱን ዐጥቦ ንጹሕ ይሁን። 35.ንጹሕ መሆኑ ከተገለጠ በኋላ ግን የሚያሳክከው ቍስል ተስፋፍቶ ቢገኝ፣ 36.ካህኑ ይመርምረው፤ ቍስሉ በቈዳው ላይ ከሰፋ፣ ካህኑ የጠጕሩን ቢጫ መሆን አለመሆን ማየት አያሻውም፤ ሰውየው ርኩስ ነው። 37.ነገር ግን ቍስሉ በካህኑ አመለካከት ለውጥ ያላሳየ ከሆነና በውስጡ ጥቍር ጠጕር ካበቀለ ቍስሉ ድኗል፤ ሰውየው ነጽቷል፤ ካህኑም ንጹሕ መሆኑን ያስታውቅ። 38.“በወንድ ወይም በሴት ቈዳ ላይ ቋቍቻ ቢወጣ፣ 39.ካህኑ ይመርምራቸው፤ ቋቍቻው ዳለቻ ከሆነ፣ በቈዳ ላይ የወጣ ጕዳት የማያስከትል ችፍታ ነው፤ ሰውየውም ንጹሕ ነው። 40.“አንድ ሰው የራሱ ጠጕር ከዐናቱ ዐልቆ መላጣ ቢሆን ንጹሕ ነው። 41.ጠጕሩ ከፊት ለፊት ተመልጦ ራሰ በራ ቢሆንም ንጹሕ ነው። 42.ነገር ግን በመላጣው ወይም በበራው ላይ ነጣ ያለ ቀይ ቍስል ቢወጣበት፣ ያ ከመላጣው ወይም ከበራው የወጣ ተላላፊ በሽታ ነው። 43.ካህኑ ይመርምረው፤ በመላጣው ወይም በበራው ላይ ያበጠው ተላላፊ የቈዳ በሽታ የሚመስል ነጣ ያለ ቍስል ከሆነ፣ 44.ሰውየው ደዌ አለበት፤ ርኩስም ነው፤ በራሱ ላይ ካለው ቍስል የተነሣም ሰውየው ርኩስ መሆኑን ካህኑ ያስታውቅ። 45.“እንዲህ ያለ ተላላፊ በሽታ ያለበት ሰው የተቀደደ ልብስ ይልበስ፤ ጠጕሩን ይግለጥ፤ እስከ አፍንጫውም ድረስ ተሸፋፍኖ ‘ርኩስ ነኝ! ርኩስ ነኝ!’ እያለ ይጩኽ። 46.ተላላፊ በሽታው እስካለበት ጊዜ ድረስ ርኩስ ነው፤ ብቻውን ይቀመጥ፤ ከሰፈር ውጪም ይኑር።

በልብስ ላይ የሚታይ ተላላፊ በሽታ

47.“ከበግ ጠጕር ወይም ከበፍታ የተሠራ ማንኛውም ዐይነት ልብስ በተላላፊ በሽታ ቢበከል፣ 48.በሸማኔ ዕቃ ወይም በእጅ የተሠራ ማንኛውም ዐይነት የበግ ጠጕር ወይም የበፍታ ልብስ ወይም ማንኛውም ቈዳ ወይም ከቈዳ የተሠራ ነገር ቢሆን፣ 49.በልብስ ወይም በዐጐዛ፣ በሸማኔ ዕቃ በተሠራ ወይም በእጅ በተጠለፈ ወይም ከቈዳ በተሠራ ዕቃ ላይ አረንጓዴ ወይም ቀይ መሳይ ደዌ ቢከሠት፣ እየሰፋ የሚሄድ ተላላፊ በሽታ ስለ ሆነ ካህኑ ይየው። 50.ካህኑ ደዌውን ይመርምር፤ በደዌ የተበከለውንም ዕቃ ሰባት ቀን ያግልል። 51.በሰባተኛውም ቀን ይመርምረው፤ ደዌው በልብሱ፣ በሸማኔ ዕቃ በተሠራው ወይም በእጅ በተጠለፈው ጨርቅ ወይም ለማንኛውም አገልግሎት በሚውል ዐጐዛ ላይ ተስፋፍቶ ቢገኝ፣ ክፉ ደዌ ነው፤ ዕቃውም ርኩስ ነው። 52.ልብሱን ወይም በሸማኔ ዕቃ የተሠራውን ወይም በእጅ የተጠለፈውን የበግ ጠጕር ወይም በፍታ ወይም ደዌው ያለበትን ማንኛውንም ከቈዳ የተሠራ ዕቃ ያቃጥል፤ ደዌው ክፉ ነውና፤ ዕቃው ይቃጠል። 53.“ነገር ግን ካህኑ በሚመረምርበት ጊዜ ደዌው በልብሱ ወይም በሸማኔ ዕቃ በተሠራው ወይም በእጅ በተጠለፈው ጨርቅ ላይ፣ ወይም ከቈዳ በተሠራው ዕቃ ላይ ተስፋፍቶ ካልተገኘ፣ 54.ካህኑ ደዌው ያለበት ነገር እንዲታጠብ ይዘዝ፤ ዕቃውንም ሰባት ቀን ደግሞ ያግልል። 55.ደዌው ያለበት ዕቃ ከታጠበ በኋላ ካህኑ ይመርምረው፤ ደዌው ባይስፋፋም እንኳ መልኩን ካልለወጠ፣ ርኩስ ነው፤ ደዌው የወጣው በውስጥም ሆነ በውጭ ዕቃው በእሳት ይቃጠል። 56.ዕቃው ከታጠበ በኋላ ካህኑ በሚመረምርበት ጊዜ ደዌው ከስሞ ቢገኝ፣ በደዌ የተበከለውን ቦታ ከልብሱ ወይም ከቈዳው ወይም በሸማኔ ዕቃ ከተሠራው ወይም በእጅ ከተጠለፈው ጨርቅ ቀዶ ያውጣ። 57.ነገር ግን ደዌው በልብሱ ወይም በሸማኔ ዕቃ በተሠራው ወይም በእጅ በተጠለፈው ጨርቅ ላይ ወይም ከቈዳ በተሠራው ዕቃ ላይ ቢታይ፣ መስፋፋቱ ስለ ሆነ ደዌው ያለበት ማንኛውም ነገር በእሳት ይቃጠል። 58.ታጥቦ ከደዌ የጠራ ልብስ ወይም በሸማኔ ዕቃ የተሠራ ወይም በእጅ የተጠለፈ ጨርቅ ወይም ከቈዳ የተሠራ ማንኛውም ዕቃ እንደ ገና ይታጠብ፤ ንጹሕም ይሆናል።” 59.ከበግ ጠጕር ወይም ከበፍታ የተሠራ ልብስ ወይም በሸማኔ ዕቃ የተሠራ ወይም በእጅ የተጠለፈ ጨርቅ ወይም ከቈዳ የተሠራ ማንኛውም ዕቃ በደዌ ቢበከል፣ ንጹሕ ወይም ርኩስ መሆኑን ለማወቅ ሕጉ ይህ ነው።

ምዕራፍ 14

ከተላላፊ የቈዳ በሽታ የመንጻት ሥርዐት

1.እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 2.“ለምጻሙ ሰው እንዲነጻ ወደ ካህኑ በሚወስዱት ጊዜ ሥርዐቱ እንዲህ ነው፦ 3.ካህኑ ከሰፈር ወደ ውጭ ወጥቶ ይመርምረው፤ ሰውየው ከተላላፊ የቈዳ በሽታው ተፈውሶ ከሆነ፣ 4.ካህኑ ስለሚነጻው ሰው፣ ለመብላት ከተፈቀደው የወፍ ዐይነት ሁለት ከነሕይወታቸው፣ የዝግባ ዕንጨት፣ ደመቅ ያለ ቀይ ድርና ሂሶጵ እንዲያመጣ ይዘዝ። 5.ካህኑም ከወፎቹ አንዱን በሸክላ ዕቃ ውስጥ ባለ የምንጭ ውሃ ላይ እንዲታረድ ይዘዝ። 6.በሕይወት ያለውንም ወፍ ከዝግባው ዕንጨት፣ ደመቅ ካለው ቀይ ድርና ከሂሶጵ ጋራ በምንጩ ውሃ ላይ በታረደው ወፍ ደም ውስጥ ይንከር። 7.ከተላላፊ በሽታ የሚነጻውንም ሰው ሰባት ጊዜ ይርጨው፤ መንጻቱንም ያስታውቅ፤ በሕይወት ያለውንም ወፍ ወደ ውጭ ይልቀቀው። 8.“የሚነጻው ሰው ልብሱን ይጠብ፤ ጠጕሩን በሙሉ ይላጭ፤ ሰውነቱን በውሃ ይታጠብ፤ በሥርዐቱም መሠረት ንጹሕ ይሆናል። ከዚህም በኋላ ወደ ሰፈር መግባት ይችላል፤ ነገር ግን ሰባት ቀን ከድንኳኑ ውጭ ይቈይ። 9.በሰባተኛውም ቀን ጠጕሩን በሙሉ ይላጭ፤ ራሱን፣ ጢሙን፣ ቅንድቡንና ሌላውንም ጠጕር ሁሉ ይላጭ። ልብሱን ይጠብ፤ ሰውነቱን በውሃ ይታጠብ፤ ንጹሕም ይሆናል። 10.“በስምንተኛው ቀን እንከን የሌለባቸውን ሁለት ተባዕት የበግ ጠቦቶችና ነውር የሌለባትን አንዲት የአንድ ዓመት እንስት በግ ያቅርብ፤ እንዲሁም ለእህል ቍርባን የሚሆን በዘይት የተለወሰ የኢፍ ሦስት ዐሥረኛ የላመ ዱቄት ያቅርብ፤ ደግሞ አንድ ሎግ ዘይት ያምጣ። 11.ሰውየው የነጻ መሆኑን የሚያስታውቀው ካህን የሚነጻውን ሰውና መሥዋዕቶቹን በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ላይ በእግዚአብሔር ፊት ያቅርብ። 12.“ካህኑም ከተባዕቱ ጠቦቶች በመውሰድ ከሎግ ዘይቱ ጋራ የበደል መሥዋዕት አድርጎ ያቅርብ፤ የሚወዘወዝ መሥዋዕት በማድረግም በእግዚአብሔር ፊት ይወዝውዛቸው። 13.ጠቦቱንም፣ የኀጢአት መሥዋዕትና የሚቃጠል መሥዋዕት በሚታረድበት በተቀደሰው ስፍራ ይረደው፤ የኀጢአት መሥዋዕቱ ለካህኑ እንደሚሰጥ ሁሉ የበደል መሥዋዕቱም ለካህኑ ይሰጥ፤ ይህም እጅግ የተቀደሰ ነው። 14.ካህኑ ከበደል መሥዋዕቱ ደም ወስዶ የሚነጻውን ሰው ቀኝ ጆሮ ታችኛውን ጫፍ፣ የቀኝ እጁን አውራ ጣትና የቀኝ እግሩን አውራ ጣት ያስነካ። 15.ካህኑም ከሎግ ዘይት ወስዶ በራሱ ግራ እጅ መዳፍ ውስጥ ይጨምር፤ 16.ካህኑም የቀኝ እጁንም ጣት በመዳፉ በያዘው ዘይት ውስጥ በመንከር በእግዚአብሔር ፊት ሰባት ጊዜ በጣቱ ይርጭ። 17.ካህኑ በመዳፉ ውስጥ ከቀረው ዘይት ጥቂቱን ወስዶ የሚነጻውን ሰው ቀኝ ጆሮ ታችኛውን ጫፍ፣ የቀኝ እጁን አውራ ጣትና የቀኝ እግሩን አውራ ጣት በበደል መሥዋዕቱ ደም ላይ ደርቦ ይቅባ። 18.ካህኑም በመዳፉ ላይ የቀረውን ዘይት በሚነጻው ሰው ራስ ላይ ያድርግ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ያስተስርይለት። 19.“ካህኑም የኀጢአት መሥዋዕቱን ያቅርብ፤ ከርኩሰቱ ለሚነጻውም ሰው ያስተስርይለት፤ ከዚህ በኋላ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ይረድ፤ 20.ካህኑም ከእህል ቍርባኑ ጋራ በመሠዊያው ላይ በማቅረብ ያስተስርይለት፤ ሰውየውም ንጹሕ ይሆናል። 21.“ሰውየው ድኻ ከሆነና እነዚህን ለማቅረብ ዐቅሙ ካልፈቀደለት፣ ማስተስረያ እንዲሆነው የሚወዘወዝ አንድ ተባዕት የበግ ጠቦት ለበደል መሥዋዕት፣ በዘይት የተለወሰ የኢፍ አንድ ዐሥረኛ የላመ ዱቄት ለእህል ቍርባን ያቅርብ፤ ደግሞም አንድ ሎግ ዘይት ያምጣ፤ 22.እንዲሁም ሁለት ርግቦች ወይም ሁለት የዋኖስ ጫጩቶች ዐቅሙ የፈቀደውን አንዱን ለኀጢአት መሥዋዕት፣ ሌላውን ለሚቃጠል መሥዋዕት ያቅርብ። 23.“እነዚህንም በስምንተኛው ቀን ስለ መንጻቱ ሥርዐት ወደ ካህኑ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ በእግዚአብሔር ፊት ያቅርብ። 24.ካህኑም ለበደል መሥዋዕት የሚሆነውን የበግ ጠቦትና አንድ ሎግ ዘይት ይቀበል፤ የሚወዘወዝ መሥዋዕት በማድረግም በእግዚአብሔር ፊት ይወዝውዛቸው። 25.ለበደል መሥዋዕት የሚሆነውንም የበግ ጠቦት ይረድ፤ ካህኑም ከደሙ ጥቂት ወስዶ የሚነጻውን ሰው የቀኝ ጆሮ ታችኛ ጫፍ፣ የቀኝ እጁን አውራ ጣትና የቀኝ እግሩን አውራ ጣት ያስነካ፤ 26.ካህኑም ከዘይቱ ጥቂቱን በግራ እጁ መዳፍ ውስጥ ያፍስስ፤ 27.ካህኑም የቀኝ እጁን ጣት በመዳፉ በያዘው ዘይት ውስጥ በመንከር በእግዚአብሔር ፊት ሰባት ጊዜ ይርጭ። 28.ካህኑም በመዳፉ ከያዘው ዘይት ጥቂቱን ወስዶ የበደል መሥዋዕቱን ደም ባስነካበት ቦታ፣ ይኸውም የሚነጻውን ሰው ቀኝ ጆሮ ጫፍ፣ የቀኝ እጁን አውራ ጣትና የቀኝ እግሩን አውራ ጣት ያስነካ። 29.ካህኑ በእግዚአብሔር ፊት ያስተሰርይለት ዘንድ በመዳፉ ከያዘው ዘይት የቀረውን በሚነጻው ሰው ራስ ላይ ያፍስስ፤ 30.ካህኑም ርግቦቹን ወይም የዋኖሶቹን ጫጩቶች የሰውየው ዐቅም የፈቀደውን ይሠዋል፤ 31.ከእነዚህም አንዱን ለኀጢአት መሥዋዕት፣ ሌላውን ለሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ ከእህሉ ቍርባን ጋራ ያቅርብ፤ በዚህም ሁኔታ ካህኑ ለሚነጻው ሰው በእግዚአብሔር ፊት ያስተሰርይለታል።” 32.ተላላፊ የቈዳ በሽታ ይዞት የሚነጻበትን መደበኛ መሥዋዕት ለማቅረብ ዐቅም ላነሰው ሰው ሕጉ ይህ ነው።

ልብስ ላይ ከሚታይ ተላላፊ በሽታ መንጻት

33.እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤ 34.“ርስት አድርጌ ወደምሰጣቸው ወደ ከነዓን ምድር በገባችሁ ጊዜ፣ በዚያ አገር አንዱን ቤት በተላላፊ በሽታ የበከልሁ እንደ ሆነ፣ 35.ባለቤቱ ወደ ካህኑ ሄዶ፣ ‘በቤቴ ውስጥ ተላላፊ በሽታ የሚመስል ነገር አይቻለሁ’ ብሎ ይንገረው። 36.ካህኑ ወደዚያ ቤት በመግባት በሽታውን መርምሮ ርኩስ መሆኑን ከማስታወቁ በፊት፣ ቤቱን ባዶ እንዲያደርጉት ይዘዝ፤ ከዚህ በኋላ ካህኑ ወደ ቤቱ ገብቶ ይመርምር። 37.በግድግዳው ላይ ያለውን ተላላፊ በሽታ በሚመረምርበት ጊዜ፣ መልኩ ወደ አረንጓዴነት ወይም ወደ ቀይነት የሚያደላ የተቦረቦረ ነገር በግድግዳው ቢታይ፣ 38.ካህኑ ከቤቱ ወደ ደጅ ወጥቶ ቤቱን ሰባት ቀን ይዝጋው። 39.ካህኑም በሰባተኛው ቀን ቤቱን ለመመርመር ይመለስ፤ ተላላፊው በሽታ በግድግዳው ተስፋፍቶ ቢገኝ፣ 40.ካህኑ የተበከሉት ድንጋዮች ተሰርስረው እንዲወጡና ከከተማው ውጭ ባለው ርኩስ ስፍራ እንዲጣሉ ይዘዝ፤ 41.የቤቱ ግድግዳ በሙሉ በውስጥ በኩል እንዲፋቅና ፍቅፋቂው ከከተማው ውጭ ባለው ርኩስ ስፍራ እንዲደፋ ያድርግ። 42.በወጡትም ድንጋዮች ቦታ ሌሎች ድንጋዮች አምጥተው ይተኩ፤ ሌላም ጭቃ ወስደው ቤቱን ይምረጉ። 43.“ድንጋዮቹ ወጥተው፣ ቤቱ ከተፈቀፈቀና ከተመረገ በኋላ ተላላፊው በሽታ እንደ ገና በቤቱ ውስጥ ከታየ፣ 44.ካህኑ ሄዶ ይመርምረው፤ ተላላፊው በሽታ በቤቱ ውስጥ ተስፋፍቶ ከተገኘ፣ አደገኛ በሽታ ነው፤ ቤቱም ርኩስ ነው። 45.ስለዚህ ቤቱ ይፍረስ፤ ድንጋዩ፣ ዕንጨቱና ምርጊቱ በሙሉ ከከተማ ውጭ ባለው ርኩስ ስፍራ ይጣል። 46.“ቤቱ ተዘግቶ ሳለ ማንኛውም ሰው ቢገባበት፣ ያ ሰው እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል። 47.በዚያ ቤት ገብቶ የተኛ ወይም የበላ ማንኛውም ሰው ልብሶቹን ይጠብ። 48.“ነገር ግን ቤቱ ከተመረገ በኋላ፣ ካህኑ ሊመረምረው በሚመጣበት ጊዜ ተላላፊው በሽታ ሳይስፋፋ ቢገኝ፣ በሽታው ስለ ለቀቀው ቤቱ ንጹሕ መሆኑን ያስታውቅ። 49.ቤቱንም ለማንጻት ሁለት ወፎች፣ የዝግባ ዕንጨት፣ ደመቅ ያለ ቀይ ድርና ሂሶጵ ያቅርብ። 50.ከወፎቹም አንዱን በሸክላ ዕቃ ውስጥ ባለ የምንጭ ውሃ ላይ ይረድ። 51.የዝግባውን ዕንጨት፣ ሂሶጱን፣ ደመቅ ያለውን ቀይ ድርና በሕይወት ያለውን ወፍ ወስዶ በታረደው ወፍ ደምና በምንጩ ውሃ ውስጥ ይንከር፤ ቤቱንም ሰባት ጊዜ ይርጭ። 52.ቤቱንም በወፉ ደም፣ በምንጩ ውሃ፣ በሕይወት ባለው ወፍ፣ በዝግባው ዕንጨት፣ በሂሶጱና ደመቅ ባለው ቀይ ድር ያንጻው። 53.በሕይወት ያለውንም ወፍ ከከተማ ወደ ውጭ ይልቀቀው፤ በዚህ ሁኔታ ለቤቱ ያስተሰርይለታል፤ ቤቱም ንጹሕ ይሆናል።” 54.ይህ ሕግ ለማንኛውም ተላላፊ የቈዳ በሽታ፣ ለሚያሳክክ ሕመም፣ 55.በልብስና በቤት ላይ ለሚመጣ ተላላፊ በሽታ፣ 56.ለዕብጠት፣ ለችፍታ ወይም ለቋቍቻ፣ 57.አንድ ነገር ንጹሕ ወይም ርኩስ መሆኑ የሚታወቅበት ነው። ይህ ለተላላፊ የቈዳ በሽታ እንዲሁም በልብስና በቤት ላይ ለሚወጣ ተላላፊ በሽታ የሚያገለግል ሕግ ነው።

መዝሙረ ዳዊት

ምዕራፍ 111

1.ሃሌ ሉያ።
በቅኖች ሸንጎ፣ በጉባኤም መካከል፣
ለእግዚአብሔር በፍጹም ልቤ ምስጋና አቀርባለሁ።
2.የእግዚአብሔር ሥራ ታላቅ ናት፤
ደስ የሚሰኙባትም ሁሉ ያውጠነጥኗታል።
3.ሥራው ባለክብርና ባለግርማ ነው፤
ጽድቁም ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።
4.ድንቅ ሥራው ሲታወስ እንዲኖር አደረገ፤
እግዚአብሔር ቸር፣ ርኅሩኅም ነው።
5.ለሚፈሩት ምግብን ይሰጣል፤
ኪዳኑንም ለዘላለም ያስባል።
6.ለሕዝቡ የአሕዛብን ርስት በመስጠት፣
የአሠራሩን ብርታት አሳይቷል።
7.የእጁ ሥራ እውነተኛና ቅን ነው፤
ሥርዐቱም ሁሉ የታመነ ነው፤
8.ከዘላለም እስከ ለዘላለም የጸና ነው፤
በእውነትና በቅንነትም የተሠራ ነው።
9.ለሕዝቡ መዳንን ሰደደ፤
ኪዳኑንም ለዘላለም አዘዘ፤
ስሙም የተቀደሰና የተፈራ ነው።
10.እግዚአብሔርን መፍራት የጥበብ መጀመሪያ ነው፤
ትእዛዙንም የሚፈጽሙ ጥሩ ማስተዋል አላቸው፤
ምስጋናውም ለዘላለም ይኖራል።

ወደ ዕብራውያን

ምዕራፍ 5

1.እያንዳንዱ ሊቀ ካህናት ከሰዎች መካከል ይመረጣል፤ የእግዚአብሔርም በሆነው ነገር ላይ ሰዎችን በመወከል ለኀጢአት የሚሆነውን መባንና መሥዋዕትን ለማቅረብ ይሾማል። 2.እርሱ ራሱ ድካም ያለበት በመሆኑ፣ አላዋቂ ለሆኑትና ለሚባዝኑት ሊራራላቸው ይችላል። 3.ስለ ራሱ ኀጢአትና ስለ ሌሎች ሰዎች ኀጢአት መሥዋዕት ማቅረብ የተገባው በዚሁ ምክንያት ነው። 4.አሮን እንደ ተጠራ በእግዚአብሔር መጠራት አለበት እንጂ፣ ይህን ክብር ለራሱ የሚወስድ ማንም የለም። 5.እንዲሁም ክርስቶስ ሊቀ ካህናት የመሆንን ክብር ለራሱ አልወሰደም፤ ነገር ግን እግዚአብሔር፣
“አንተ ልጄ ነህ፤
እኔ ዛሬ ወለድሁህ” አለው።
6.እንዲሁም በሌላ ስፍራ፣
“እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት፣
አንተ ለዘላለም ካህን ነህ” ይላል።
7.ኢየሱስ በዚህ ምድር በኖረበት ዘመን ከሞት ሊያድነው ወደሚችለው ጸሎትንና ልመናን ከታላቅ ጩኸትና ከእንባ ጋራ አቀረበ፤ ፍጹም ትሑት ሆኖ በመታዘዙም ጸሎቱ ተሰማለት። 8.የእግዚአብሔር ልጅ ቢሆንም እንኳ፣ ከተቀበለው መከራ መታዘዝን ተማረ፤ 9.በዚህም ፍጹም ሆኖ ከተገኘ በኋላ፣ እርሱን ለሚታዘዙ ሁሉ የዘላለም ድነት ምክንያት ሆነላቸው፤ 10.እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመትም ሊቀ ካህናት ተብሎ በእግዚአብሔር ተሾመ።

በእምነት ስላለመጽናት የተሰጠ ማስጠንቀቂያ

11.ስለዚህ ጕዳይ የምንናገረው ብዙ ነገር አለን፤ ነገር ግን ለመማር ዳተኛ ስለ ሆናችሁ ለማስረዳት አስቸጋሪ ነው። 12.በዚህ ጊዜ አስተማሪዎች ልትሆኑ ሲገባችሁ፣ ገና የእግዚአብሔርን ቃል የመጀመሪያ ትምህርት የሚያስተምራችሁ ሰው ያስፈልጋችኋል፤ የሚያስፈልጋችሁም ጠንካራ ምግብ ሳይሆን ወተት ነው። 13.ወተት የሚጋት ሁሉ ሕፃን ስለ ሆነ፣ ከጽድቅ ትምህርት ጋራ ገና አልተዋወቀም። 14.ጠንካራ ምግብ ግን መልካሙን ከክፉው ለመለየት ራሳቸውን ላስለመዱ፣ ለበሰሉ ሰዎች ነው።