Skip to Content
የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን | YEHIWOT MELHEK BETEKIRSTIAN
የ2019 ዓ.ም የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ 📖 ዛሬን አንብብ →

የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን

Yehiwot Melhek Betekirstian

ሳምንት 8 · ቀን 37 (ማክሰኞ) 📅 Tikimt 24, 2019

ኦሪት ዘሌዋውያን 12, 13, 14 · መዝሙረ ዳዊት 111 · ወደ ዕብራውያን 5

📖 የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም፦ 1954 መጽሐፍ ቅዱስ አዲሱ መደበኛ ትርጒም

ኦሪት ዘሌዋውያን

ምዕራፍ 12

1.እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 2.ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው። ሴት ብታረግዝ ወንድ ልጅም ብትወልድ፥ ሰባት ቀን ያህል የረከሰች ናት፤ እንደ ሕመምዋ መርገም ወራት ትረክሳለች። 3.በስምንተኛውም ቀን ልጁ ከሥጋው ሸለፈት ይገረዝ። 4.ከደምዋም እስክትነጻ ሠላሳ ሦስት ቀን ትቀመጥ፤ የመንጻትዋ ቀንም እስኪፈጸም ድረስ የተቀደሰን ነገር አትንካ፥ ወደ መቅደስም አትግባ። 5.ሴት ልጅም ብትወልድ እንደ መርገምዋ ወራት ሁለት ሳምንት ያህል የረከሰች ናት፤ ከደምዋም እስክትነጻ ድረስ ስድሳ ስድስት ቀን ትቀመጥ። 6.የመንጻትዋ ወራትም በተፈጸመ ጊዜ፥ ለወንድ ልጅ ወይም ለሴት ልጅ፥ የአንድ ዓመት ጠቦት ለሚቃጠል መሥዋዕት፥ የርግብም ግልገል ወይም ዋኖስ ለኃጢአት መሥዋዕት ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ወደ ካህኑ ታምጣለት። 7.እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ያቀርበዋል ያስተሰርይላትማል፤ ከደምዋም ፈሳሽ ትነጻለች። ወንድ ወይም ሴት ለምትወልድ ሴት ሕጉ ይህ ነው። 8.ጠቦት ለማምጣት ገንዘብዋ ያልበቃት እንደ ሆነ ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የርግብ ግልገሎች፥ አንዱን ለሚቃጠል መሥዋዕት ሌላውንም ለኃጢአት መሥዋዕት ታቀርባለች፤ ካህኑም ያስተሰርይላታል፥ እርስዋም ትነጻለች።

ምዕራፍ 13

1.እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው። 2.ማናቸውም ሰው በሥጋው ቁርበት ላይ እባጭ ወይም ብጕር ወይም ቋቁቻ ቢታይ፥ በሥጋው ቁርበት እንደ ለምጽ ደዌ ቢመስል፥ ወደ ካህኑ ወደ አሮን ወይም ከካህናቱ ልጆቹ ወደ አንዱ ያምጡት። 3.ካህኑም በሥጋው ቁርበት ያለውን ደዌ ያያል፤ ጠጕሩም ተለውጦ ቢነጣ ደዌውም ወደ ሥጋው ቁርበት ቢጠልቅ፥ እርሱ የለምጽ ደዌ ነው፤ ካህኑም አይቶ። ርኩስ ነው ይበለው። 4.ቋቁቻውም በሥጋው ቁርበት ላይ ቢነጣ፥ ከቁርበቱም የጠለቀ ባይመስል፥ ጠጕሩም ባይነጣ፥ ካህኑ የታመመውን ሰው ሰባት ቀን ይዘጋበታል። 5.በሰባተኛውም ቀን ካህኑ ያየዋል፤ እነሆም፥ ደዌው በዓይኑ ፊት እንደ ነበረ ቢሆን፥ በቁርበቱም ላይ ባይሰፋ፥ ካህኑ ሰባት ቀን ደግሞ ይዘጋበታል። 6.ደግሞ በሰባተኛው ቀን ካህኑ ያየዋል፤ እነሆም፥ ደዌው ቢከስም፥ ደዌውም በቁርበቱ ላይ ባይሰፋ፥ ካህኑ። ንጹሕ ነው ይለዋል፤ እከክ ነው፤ ልብሱንም አጥቦ ንጹሕ ይሆናል። 7.ስለ መንጻቱ በካህኑ ዘንድ ከታየ በኋላ እከኩ በቁርበቱ ላይ ቢሰፋ፥ እንደ ገና ሊታይ ወደ ካህኑ ይቀርባል። 8.ካህኑም ያያል፤ እነሆም፥ እከኩ በቁርበቱ ላይ ቢሰፋ፥ ካህኑ። ርኩስ ነው ይለዋል፤ ለምጽ ነው። 9.የለምጽ ደዌ በሰው ውስጥ ቢሆን እርሱን ወደ ካህኑ ያመጡለታል። 10.ካህኑም ያያል፤ እነሆም፥ በቁርበቱ ላይ ነጭ እባጭ ቢሆን፥ ጠጕሩም ተለውጦ ቢነጣ፥ ሥጋውም በእባጩ ውስጥ ቢያዥ፥ 11.እርሱ በሥጋው ቁርበት ላይ አሮጌ ለምጽ ነው፥ ካህኑም። ርኩስ ነው ይለዋል፤ እርሱ ርኩስ ነውና አይዘጋበትም። 12.ለምጹም በቁርበቱ ላይ ሰፍቶ ቢወጣ፥ ለምጹም የታመመውን ሰው ቁርበቱን ሁሉ ከራሱ እስከ እግሮቹ ድረስ እንደ ከደነው ለካህኑ ቢመስለው፥ ካህኑ ያያል፤ 13.እነሆም፥ ለምጹ ሥጋውን ሁሉ ቢከድን የታመመውን ሰው። ንጹሕ ነው ይለዋል፤ ሥጋው ሁሉ ፈጽሞ ተለውጦ ነጭ ሆኖአል፤ ንጹሕ ነው። 14.የሚያዠው ሥጋ ግን ሲታይበት ርኩስ ይሆናል። 15.ካህኑም የሚያዠውን ሥጋ አይቶ። ርኩስ ነው ይለዋል፤ የሚያዠው ሥጋ ለምጽ ነውና ርኩስ ነው። 16.የሚያዠውም ሥጋ ተለውጦ ቢነጣ እንደ ገና ወደ ካህኑ ይመጣል። 17.ካህኑም ያየዋል፤ እነሆም፥ ደዌው ቢነጣ ካህኑ የታመመውን። ንጹሕ ነው ይለዋል፤ ንጹሕ ነው። 18.በሥጋውም ቁርበት ላይ ቍስል ቢሆንና ቢሽር፥ 19.በቍስሉም ስፍራ ነጭ እባጭ ወይም ቀላ ያለ ቋቁቻ ቢወጣ፥ በካህኑ ዘንድ ይታያል። 20.ካህኑም ያያል፤ እነሆም፥ ወደ ቁርበቱ ውስጥ ጠልቆ ቢታይ፥ ጠጕሩም ተለውጦ ቢነጣ፥ ካህኑ። ርኩስ ነው ይለዋል፤ የለምጽ ደዌ ነው፤ ከቍስሉ ውስጥ ወጥቶአል። 21.ካህኑም ቢያየው፥ ነጭም ጠጕር ባይኖርበት፥ ወደ ቁርበቱም ውስጥ ባይጠልቅ ነገር ግን ቢከስም፥ ካህኑ ሰባት ቀን ይዘጋበታል። 22.በቁርበቱም ላይ ቢሰፋ፥ ካህኑ። ርኩስ ነው ይለዋል፤ ደዌ ነው። 23.ቋቁቻው ግን በስፍራው ቢቆም ባይሰፋም፥ የቍስል ጠባሳ ነው፤ ካህኑም። ንጹሕ ነው ይለዋል። 24.በሥጋውም ቁርበት የእሳት ትኵሳት ቢኖርበት፥ በተቃጠለውም ስፍራ ነጭ ወይም ቀላ ያለ ቋቁቻ ቢታይ፥ 25.ካህኑ ያየዋል፤ እነሆም፥ በቋቁቻው ጠጕሩ ተለውጦ ቢነጣ፥ ወደ ቁርበቱም ውስጥ ቢጠልቅ፥ ለምጽ ነው፤ ከተቃጠለውም ስፍራ ወጥቶአል፤ ካህኑም። ርኩስ ነው ይለዋል፤ የለምጽ ደዌ ነው። 26.ካህኑም ቢያየው፥ በቋቁቻውም ነጭ ጠጕር ባይኖር፥ ወደ ቁርበቱም ባይጠልቅ ነገር ግን ቢከስም፥ ካህኑ ሰባት ቀን ይዘጋበታል። 27.ካህኑም በሰባተኛው ቀን ያየዋል፤ በቁርበቱም ላይ ቢሰፋ ካህኑ። ርኩስ ነው ይለዋል፤ የለምጽ ደዌ ነው። 28.ቋቁቻውም በስፍራው ላይ ቢቆም፥ በቁርበቱም ላይ ባይሰፋ ነገር ግን ቢከስም፥ የትኵሳት እባጭ ነው፤ የትኵሳትም ጠባሳ ነውና ካህኑ። ንጹሕ ነው ይለዋል። 29.ማናቸውም ወንድ ወይም ሴት በራሱ ወይም በአገጩ ደዌ ቢኖርበት፥ 30.ካህኑ ደዌውን ያያል፤ እነሆም፥ ወደ ቁርበቱ ቢጠልቅ፥ በውስጡም ቀጭን ብጫ ጠጕር ቢኖርበት፥ ካህኑ። ርኩስ ነው ይለዋል፤ ቈረቈር ነው፤ የራስ ወይም የአገጭ ለምጽ ነው። 31.ካህኑም የቈረቈሩን ደዌ ቢያይ፥ ወደ ቁርበቱም ባይጠልቅ፥ ጥቁርም ጠጕር ባይኖርበት፥ ካህኑ የቈረቈር ደዌ ያለበትን ሰው ሰባት ቀን ይዘጋበታል። 32.ካህኑም በሰባተኛው ቀን ደዌውን ያያል፤ እነሆም፥ ቈረቈሩ ባይሰፋ፥ በውስጡም ብጫ ጠጕር ባይኖር፥ የቈረቈሩም መልክ ወደ ቁርበቱ ባይጠልቅ፥ ይላጫል፥ 33.ቈረቈሩ ግን አይላጭም፤ ካህኑም ቈረቈር ያለበትን ሰው ሰባት ቀን ደግሞ ይዘጋበታል። 34.ካህኑም በሰባተኛው ቀን ቈረቈሩን ያያል፤ እነሆም፥ ቈረቈሩ በቁርበቱ ላይ ባይሰፋ፥ መልኩም ወደ ቁርበቱ ባይጠልቅ፥ ካህኑ። ንጹሕ ነው ይለዋል፤ ልብሱን አጥቦ ንጹሕ ይሆናል። 35.ከነጻ በኋላ ግን ቈረቈሩ በቁርበቱ ላይ ቢሰፋ፥ ካህኑ ያየዋል፤ 36.እነሆም፥ ቈረቈሩ በቁርበቱ ላይ ቢሰፋ ካህኑ ብጫውን ጠጕር አይፈልግም፤ ርኩስ ነው። 37.ቈረቈሩ ግን በዓይኑ ፊት እንደ ነበረ ቢሆን፥ ጥቁርም ጠጕር ቢበቅልበት፥ ቈረቈሩ ሽሮአል እርሱም ንጹሕ ነው፤ ካህኑም። ንጹሕ ነው ይለዋል። 38.ማናቸውም ወንድ ወይም ሴት በሥጋው ቁርበት ላይ ነጭ ቋቁቻ ቢኖርበት፥ 39.ካህኑ ያያል፤ እነሆም፥ በሥጋቸው ቁርበት ላይ ያለው ቋቁቻ ፈገግ ቢል አጓጐት ነው፤ ከቁርበቱ ውስጥ ወጥቶአል፤ ንጹሕ ነው። 40.የሰውም ጠጕር ከራሱ ቢመለጥ እርሱ ቡሀ ነው፤ ነገር ግን ንጹሕ ነው። 41.ጠጕሩም ከግምባሩ ቢመለጥ እርሱ ራሰ በራ ነው፤ ነገር ግን ንጹሕ ነው። 42.በቡሀነቱ ወይም በራሰ በራነቱ ነጭ ወይም ቀላ ያለ ደዌ ቢኖርበት፥ እርሱ ከቡሀነቱ ወይም ከራሰ በራነቱ የወጣ ለምጽ ነው። 43.ካህኑም ያየዋል፤ እነሆም፥ የደዌው እብጠት፥ በሥጋው ቁርበት ላይ የሆነ ለምጽ መስሎ፥ በቡሀነቱ ወይም በራሰ በራነቱ ነጭ ወይም ቀላ ያለ ቢሆን፥ 44.ለምጻም ሰው ነው፤ ርኩስ ነው፤ ካህኑ። በእርግጥ ርኩስ ነው ይለዋል፤ ደዌው በራሱ ነው። 45.የለምጽ ደዌ ያለበት ሰው ልብሱ የተቀደደ ይሁን፥ ራሱም የተገለጠ ይሁን፥ ከንፈሩንም ይሸፍን፤ ርኩስ ርኩስ ነኝ ይበል። 46.ደዌው ባለበት ዘመን ሁሉ ርኩስ ይሆናል፤ እርሱ ርኩስ ነው፤ ብቻውን ይቀመጣል፤ መኖሪያውም ከሰፈር በውጭ ይሆናል። 47.የለምጽም ደዌ በልብስ ላይ ቢሆን፥ ልብሱም የበግ ጠጕር ወይም በፍታ ቢሆን፥ 48.በድሩ ወይም በማጉ ላይ ቢሆን፥ በፍታ ወይም የበግ ጠጕር ቢሆን፥ አጐዛ ወይም ከአጐዛ የሚደረግ ነገር ቢሆን፥ 49.ደዌው በልብሱ ወይም በአጐዛው ወይም በድሩ ወይም በማጉ ወይም ከአጐዛው በሚደረገው ነገር አረንጓዴ ወይም ቀይ ቢሆን፥ የለምጽ ደዌ ነው፤ ለካህኑ ይታያል። 50.ካህኑም ደዌውን አይቶ ደዌው ያለበትን ነገር ሰባት ቀን ይዘጋበታል። 51.በሰባተኛውም ቀን ደዌውን ያያል፤ ደዌውም በልብስ ላይ ወይም በድሩ ወይም በማጉ ወይም በአጐዛው ወይም ከአጐዛው በሚደረግ ነገር ቢሰፋ፥ ደዌው እየፋገ የሚሄድ ለምጽ ነው፤ ርኩስ ነው። 52.ልብሱን ያቃጥል፤ ድሩ ወይም ማጉ የበግ ጠጕር ወይም በፍታ ቢሆን ወይም ከአጐዛው የተደረገ ቢሆን፥ ደዌ ያለበት ሁሉ፥ እየፋገ የሚሄድ ለምጽ ነውና በእሳት ይቃጠል። 53.ካህኑ ቢያይ፥ እነሆም፥ ደዌው በድሩ ወይም በማጉ ወይም ከአጐዛ በተደረገ ነገር ቢሆን በልብሱ ላይ ባይሰፋ፥ 54.ካህኑ ደዌ ያለበቱ ነገር እንዲታጠብ ይዘዝ፤ ሌላም ሰባት ቀን ይዘጋበታል። 55.ደዌውም ከታጠበ በኋላ ካህኑ ያያል፤ እነሆም፥ ደዌው መልኩን ባይለውጥ ባይሰፋም፥ ርኩስ ነው፤ በእሳት አቃጥለው፤ ምልክቱ በውስጥ ወይም በውጭ ቢሆን እየፋገ የሚሄድ ደዌ ነው። 56.ካህኑም ቢያይ፥ እነሆም፥ ደዌው ከታጠበ በኋላ ቢከስም፥ ከልብሱ ወይም ከአጐዛው ወይም ከድሩ ወይም ከማጉ ይቅደደው። 57.በልብሱም ወይም በድሩ ወይም በማጉ ወይም ከአጐዛው በተደረገ ነገር ላይ ደግሞ ቢታይ፥ የወጣ ለምጽ ነው፤ ደዌው ያለበትን ነገር አቃጥለው። 58.አንተም ካጠብኸው ልብስ ወይም ከድሩ ወይም ከማጉ ወይም ከአጐዛው ከተደረገው ነገር ላይ ደዌው ቢጠፋ፥ ሁለተኛ ጊዜ ይታጠባል፥ ንጹሕም ይሆናል። 59.በበግ ጠጕር ልብስ ወይም በበፍታ ወይም በድሩ ወይም በማጉ ወይም ከአጐዛ በተደረገ ነገር ላይ ቢሆን፥ ንጹሕ ወይም ርኩስ ያሰኝ ዘንድ የለምጽ ደዌ ሕግ ይህ ነው።

ምዕራፍ 14

1.እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው። 2.በመንጻቱ ቀን የለምጻሙ ሕግ ይህ ይሆናል፤ ወደ ካህኑ ይወስዱታል። 3.ካህኑም ከሰፈር ወደ ውጭ ይወጣል፤ ካህኑም ያያል፤ እነሆም፥ የለምጹ ደዌ ከለምጻሙ ላይ ቢጠፋ፥ 4.ካህኑ ስለሚነጻው ሰው ሁለት ንጹሐን ወፎች በሕይወታቸው፥ የዝግባም እንጨት፥ ቀይ ግምጃም፥ ሂሶጵም ያመጣ ዘንድ ያዝዛል። 5.ካህኑም ከሁለቱ ወፎች አንዱን በሸክላ ዕቃ ውስጥ በምንጭ ውኃ ላይ ያርድ ዘንድ ይዝዛል። 6.ሕያውንም ወፍ ዝግባውንም እንጨት ቀዩንም ግምጃ ሂሶጱንም ወስዶ ከሕያው ወፍ ጋር በምንጭ ውኃ ላይ በታረደው ወፍ ደም ውስጥ ይነክራቸዋል። 7.ከለምጹ በሚነጻው ሰው ላይ ሰባት ጊዜ ይረጫል፤ ንጹሕም ነው ይለዋል፥ ሕያውንም ወፍ ወደ ሜዳ ይለቅቀዋል። 8.የነጻውም ሰው ልብሱን ያጥባል፥ ጠጕሩንም ሁሉ ይላጫል፥ በውኃም ይታጠባል፥ ንጹሕም ይሆናል። ከዚያም በኋላ ወደ ሰፈር ይገባል፥ ነገር ግን ከድንኳኑ በውጭ ሆኖ ሰባት ቀን ይቀመጣል። 9.በሰባተኛውም ቀን ጠጕሩን ሁሉ ይላጫል፤ ራሱንም፥ ጢሙንም፥ ቅንድቡንም፥ የገላውንም ጠጕር ሁሉ ይላጫል፤ ልብሱንም፥ ገላውንም በውኃ ያጥባል፤ ንጹሕም ይሆናል። 10.በስምንተኛውም ቀን ነውር የሌለባቸውን ሁለት ተባት ጠቦት፥ ነውር የሌለባትንም አንዲት የዓመት እንስት ጠቦት፥ ስለ እህልም ቍርባን ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ ሦስት እጅ የሆነ በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት፥ አንድ የሎግ መስፈሪያም ዘይት ይወስዳል። 11.የሚያነጻውም ካህን እነዚህን ነገሮች የሚነጻውንም ሰው በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ አጠገብ በእግዚአብሔር ፊት ያኖራቸዋል። 12.ካህኑም አንዱን ጠቦት ወስዶ ስለ በደል መሥዋዕት ያቀርበዋል፥ ያንንም የሎግ መስፈሪያ ዘይት፤ ስለ መወዝወዝ ቍርባን በእግዚአብሔር ፊት ይወዘውዘዋል። 13.የኃጢአትን መሥዋዕትና የሚቃጠለውን መሥዋዕት በሚያርዱበት በተቀደሰው ስፍራ ጠቦቱን ያርደዋል፤ የኃጢአቱ መሥዋዕት ለካህኑ እንደሚሆን፥ እንዲሁ የበደል መሥዋዕት ነው፤ ቅዱስ ቅዱሳን ነው። 14.ካህኑም ከበደል መሥዋዕት ደም ወስዶ የሚነጻውን ሰው የቀኝ ጆሮውን ጫፍ፥ የቀኝ እጁንም አውራ ጣት፥ የቀኝ እግሩንም አውራ ጣት ያስነካዋል። 15.ካህኑም ከዘይቱ ከሎግ መስፈሪያው ወስዶ በግራ እጁ ውስጥ ያፈስሰዋል። 16.ካህኑም በግራ እጁ ውስጥ ባለው ዘይት ቀኝ ጣቱን ነክሮ ከዘይቱ በእግዚአብሔር ፊት ሰባት ጊዜ በጣቱ ይረጫል። 17.ካህኑም በእጁ ውስጥ ከቀረው ዘይት የሚነጻውን ሰው የቀኝ ጆሮውን ጫፍ፥ የቀኝ እጁንም አውራ ጣት፥ የቀኝ እግሩንም አውራ ጣት የበደል መሥዋዕት ደም ባረፈበት ላይ ያስነካዋል። 18.በካህኑም እጅ ውስጥ የቀረውን ዘይት በሚነጻው ሰው ራስ ላይ ያደርግበታል፤ ካህኑም በእግዚአብሔር ፊት ያስተሰርይለታል። 19.ካህኑም የኃጢአቱን መሥዋዕት ያቀርባል፥ ከርኵሰቱም ለሚነጻው ሰው ያስተሰርይለታል፤ በኋላም የሚቃጠለውን መሥዋዕት ያርዳል። 20.ካህኑም የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የእህሉን ቍርባን በመሠዊያው ላይ ያቀርባል፥ ካህኑም ያስተሰርይለታል፤ እርሱም ንጹሕ ይሆናል። 21.ድሀም ቢሆን ይህንም ለማምጣት ገንዘቡ ባይበቃው፥ ማስተስረያ ይሆንለት ዘንድ እንዲወዘወዝ አንድ ጠቦት ለበደል መሥዋዕት፥ ከመስፈሪያውም ከአሥር እጅ አንድ እጅ የሆነ በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት ለእህል ቍርባን፥ አንድ የሎግ መስፈሪያም ዘይት ይወስዳል። 22.ሁለት ዋኖሶች ወይም የርግብ ግልገሎች እንደሚቻለው፥ አንዱን ለኃጢአት መሥዋዕት፥ ሌላውን ለሚቃጠል መሥዋዕት ይወስዳል። 23.በስምንተኛውም ቀን ስለ መንጻት ወደ ካህኑ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ በእግዚአብሔር ፊት ያመጣቸዋል። 24.ካህኑም የበደሉን መሥዋዕት ጠቦት የሎግ መስፈሪያውንም ዘይት ይወስዳል፤ ካህኑም ለመወዝወዝ ቍርባን በእግዚአብሔር ፊት ይወዘውዛቸዋል። 25.የበደሉንም መሥዋዕት ጠቦት ያርዳል፤ ካህኑም ከበደሉ መሥዋዕት ደም ወስዶ የሚነጻውን ሰው የቀኝ ጆሮውን ጫፍ፥ የቀኝ እጁንም አውራ ጣት፥ የቀኝ እግሩንም አውራ ጣት ያስነካዋል። 26.ካህኑም ከዘይቱ በግራ እጁ ውስጥ ያፈስሰዋል። 27.ካህኑም በግራ እጁ ውስጥ ካለው ዘይት በቀኝ ጣቱ ሰባት ጊዜ በእግዚአብሔር ፊት ይረጨዋል። 28.ካህኑም በእጁ ውስጥ ካለው ዘይት የሚነጻውን ሰው የቀኝ ጆሮውን ጫፍ፥ የቀኝ እጁንም አውራ ጣት፥ የቀኝ እግሩንም አውራ ጣት የበደል መሥዋዕት ደም ባረፈበት ላይ ያስነካዋል። 29.በእግዚአብሔር ፊት ያስተሰርይለት ዘንድ በካህኑ እጅ ውስጥ የቀረውን ዘይት በሚነጻው ሰው ራስ ላይ ያደርገዋል። 30.እንደሚቻለው ከዋኖሶች ወይም ከርግብ ግልገሎች አንዱን ያቀርባል። 31.እንደሚቻለው አንዱን ለኃጢአት መሥዋዕት፥ ሌላውንም ከእህል ቍርባን ጋር ለሚቃጠል መሥዋዕት ያቀርባል ካህኑም ለሚነጻው ሰው በእግዚአብሔር ፊት ያስተሰርይለታል። 32.ለመንጻቱ የሚያስፈልገውን ነገር ለማያገኝ የለምጽ ደዌ ላለበት ሰው ሕግ ይህ ነው። 33.እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው። 34.ወደምሰጣችሁ ርስት ወደ ከነዓን ምድር በገባችሁ ጊዜ፥ እኔም የለምጽ ደዌ በርስታችሁ ምድር በአንድ ቤት ባደረግሁ ጊዜ፥ 35.ባለቤቱ መጥቶ ካህኑን። ደዌ በቤቴ ውስጥ እንዳለ ይመስለኛል ብሎ ይንገረው። 36.ካህኑም በቤቱ ውስጥ ያለው ዕቃ ሁሉ እንዳይረክስ፥ እርሱ ደዌውን ለማየት ወደ ቤት ሳይገባ፥ ቤቱን ባዶ እንዲያደርጉት ያዝዛል፤ በኋላም ካህኑ ቤቱን ለማየት ይገባል። 37.ደዌውንም ያያል፤ እነሆም፥ ደዌው በግንቡ ላይ በአረንጓዴና በቀይ ቢዥጐረጐር፥ መልኩም ወደ ግንቡ ውስጥ ቢጠልቅ፥ 38.ካህኑ ከቤቱ ውስጥ ወደ ቤቱ በር ወጥቶ ሰባት ቀን ቤቱን ይዘጋዋል። 39.ካህኑም በሰባተኛው ቀን ተመልሶ ያያል፤ እነሆም፥ ደዌው በቤቱ ግንብ ላይ ቢሰፋ፥ 40.ካህኑ ደዌ ያለባቸውን ድንጋዮች እንዲያወጡ፥ ከከተማውም ወደ ውጭ ወደ ረከሰው ስፍራ እንዲጥሉአቸው ያዝዛል። 41.ቤቱንም በውስጡ በዙሪያው ያስፍቀዋል፤ የፋቁትንም የምርጊቱን አፈር ከከተማው ወደ ውጭ ወደ ረከሰ ስፍራ ያፈስሱታል። 42.በእነዚያም ድንጋዮች ስፍራ ሌሎች ድንጋዮች ያገባሉ፤ ሌላም ጭቃ ወስደው ቤቱን ይመርጉታል። 43.ደዌውም ዳግም ቢመለስ፥ ድንጋዮቹም ከወጡ ቤቱም ከተፋቀና ከተመረገ በኋላ በቤቱ ውስጥ ቢሰፋ፥ 44.ካህኑ ገብቶ ያያል፤ እነሆም፥ ደዌው በቤቱ ውስጥ ቢሰፋ በቤቱ ውስጥ ያለው እየፋገ የሚሄድ ለምጽ ነው፤ ርኩስ ነው። 45.ቤቱንም፥ ድንጋዮቹንም፥ እንጨቱንም፥ የቤቱንም ምርጊት ሁሉ ያፈርሳል፤ እነርሱንም ከከተማው ወደ ውጭ ወደ ርኩስ ስፍራ ያወጣል። 46.በተዘጋበትም ጊዜ ሁሉ ወደ ቤቱ የሚገባ እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል። 47.በቤቱም የሚተኛ ልብሱን ያጥባል፤ በቤቱም የሚበላ ልብሱን ያጥባል። 48.ካህኑም ገብቶ ቢያይ፥ እነሆም፥ ቤቱ ከተመረገ በኋላ ደዌው በቤቱ ውስጥ ባይሰፋ፥ ደዌው ስለ ሻረ ካህኑ ቤቱን። ንጹሕ ነው ይለዋል። 49.ቤቱንም ለማንጻት ሁለት ወፎች፥ የዝግባም እንጨት፥ ቀይ ግምጃም፥ ሂሶጵም ይወስዳል። 50.አንደኛውንም ወፍ በሸክላ ዕቃ ውስጥ ከምንጩ ውኃ በላይ ያርዳል። 51.የዝግባውን እንጨት፥ ሂሶጱንም፥ ቀዩንም ግምጃ፥ ሕያውንም ወፍ ወስዶ በታረደው ወፍ ደምና በምንጩ ውኃ ውስጥ ይነክራቸዋል፥ ቤቱንም ሰባት ጊዜ ይረጨዋል። 52.ቤቱንም በወፉ ደም በምንጩም ውኃ በሕያውም ወፍ በዝግባውም እንጨት በሂሶጱም በቀዩም ግምጃ ያነጻዋል። 53.ሕያውንም ወፍ ከከተማ ወደ ሜዳ ይሰድደዋል፤ ለቤቱም ያስተሰርይለታል፥ ንጹሕም ይሆናል። 54.ይህም ሕግ ነው ለሁሉ ዓይነት ለምጽ ደዌ፥ 55.ለቈረቈርም፥ በልብስና በቤትም ላለ ለምጽ፥ 56.ለእባጭም፥ ለብጕርም፥ ለቋቁቻም፤ 57.በሚረክስና በሚነጻ ጊዜ እንዲያስታውቅ ይህ የለምጽ ሕግ ነው።

መዝሙረ ዳዊት

ምዕራፍ 111

1.ሃሌ ሉያ። አቤቱ፥ በቅኖች ሸንጎ በጉባኤም በፍጹም ልቤ አመሰግንሃለሁ። 2.የእግዚአብሔር ሥራ ታላቅ ናት፥ ደስ በሚሰኙባት ሁሉ ዘንድ የተፈለገች ናት። 3.ሥራው ምስጋናና ግርማ ነው፤ ጽድቁም ለዘላለም ይኖራል። 4.ለተአምራቱ መታሰቢያን አደረገ፤ እግዚአብሔር መሓሪና ይቅር ባይ ነው። 5.ለሚፈሩት ምግብን ሰጣቸው፤ ኪዳኑንም ለዘላለም ያስባል። 6.የአሕዛብን ርስት ይሰጣቸው ዘንድ ለሕዝቡ የሥራውን ብርታት አሳየ። 7.የእጆቹ ሥራ እውነትና ፍርድ ነው፤ ትእዛዙም ሁሉ የታመነ ነው፥ 8.ለዘላለምም የጸና ነው፥ በእውነትና በቅንም የተሠራ ነው። 9.መድኃኒትንም ለሕዝቡ ሰደደ፥ ኪዳኑንም ለዘላለም አዘዘ፤ ስሙ የተቀደሰና የተፈራ ነው። 10.የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው፥ ለሚያደርጓትም ሁሉ ደኅና ማስተዋል አላቸው፤ ምስጋናውም ለዘላለም ይኖራል።

ወደ ዕብራውያን

ምዕራፍ 5

1.ሊቀ ካህናት ሁሉ ስለ ኃጢአት መባንና መስዋዕትን ሊያቀርብ ከሰው ተመርጦ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ ስለ ሰው ይሾማልና፤ 2.እርሱ ራሱም ደግሞ ድካምን ስለሚለብስ፥ ላልተማሩትና ለሚስቱት ሊራራላቸው ይችላል፤ 3.በዚህም ምክንያት ስለ ሕዝብ እንደሚያቀርብ እንዲሁ ስለ ራሱ ደግሞ መስዋዕትን ስለ ኃጢአት ሊያቀርብ ይገባዋል። 4.እንደ አሮንም በእግዚአብሔር ከተጠራ በቀር ማንም ክብሩን ለራሱ የሚወስድ የለም። 5.እንዲሁ ክርስቶስ ደግሞ ሊቀ ካህናት ሊሆን ራሱን አላከበረም ነገር ግን። አንተ ልጄ ነህ እኔ ዛሬ ወልጄሃለሁ ያለው እርሱ ነው፤ 6.እንደዚህም በሌላ ስፍራ ደግሞ። አንተ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ካህን ነህ ይላል። 7.እርሱም በስጋው ወራት ከሞት ሊያድነው ወደሚችል ከብርቱ ጩኸትና ከእንባ ጋር ጸሎትንና ምልጃን አቀረበ፥ እግዚአብሔርንም ስለ መፍራቱ ተሰማለት፤ 8.ምንም ልጅ ቢሆን፥ ከተቀበለው መከራ መታዘዝን ተማረ፤
9 -
10.ከተፈጸመም በኋላ በእግዚአብሔር እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ሊቀ ካህናት ተብሎ ስለ ተጠራ፥ ለሚታዘዙለት ሁሉ የዘላለም መዳን ምክንያት ሆነላቸው። 11.ስለ እርሱም የምንናገረው ብዙ ነገር አለን፥ ጆሮቻችሁም ስለ ፈዘዙ በቃል ልንተረጕመው ጭንቅ ነው። 12.ከጊዜው የተነሳ አስተማሪዎች ልትሆኑ ሲገባችሁ፥ አንድ ሰው ስለ እግዚአብሔር ቃላት መጀመሪያ ያለውን የሕፃንነትን ትምህርት እንዲያስተምራችሁ እንደ ገና ያስፈልጋችኋልና፤ የሚያስፈልጋችሁም ወተት ነው እንጂ ጠንካራ ምግብ አይደለም። 13.ወተት የሚጋት ሁሉ ሕፃን ስለ ሆነ የጽድቅን ቃል አያውቅምና፤ 14.ጠንካራ ምግብ ግን መልካሙንና ክፉውን ለመለየት በስራቸው የለመደ ልቡና ላላቸው ለፍጹማን ሰዎች ነው።
♫
Listen to the reading 5 chapter tracks
ኦሪት ዘሌዋውያን Chapter 12
ኦሪት ዘሌዋውያን Chapter 13
ኦሪት ዘሌዋውያን Chapter 14
መዝሙረ ዳዊት Chapter 111
ወደ ዕብራውያን Chapter 5
Swipe to browse chapters
Listen 5