ሳምንት 8 · ቀን 36 (ሰኞ)
📅 Tikimt 23, 2019
ኦሪት ዘሌዋውያን 8, 9, 10, 11 · መዝሙረ ዳዊት 110 · ወደ ዕብራውያን 4
ኦሪት ዘሌዋውያን
ምዕራፍ 8
አሮንና ልጆቹ ካህናት ሆነው መሾማቸው
8፥1-36 ተጓ ምብ – ዘፀ 29፥1-37
1.እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤
2.“አሮንንና ልጆቹን፣ ልብሰ ተክህኖውን፣ የመቅቢያ ዘይቱን፣ ለኀጢአት መሥዋዕት የሚሆነውን ወይፈን፣ ሁለቱን አውራ በጎችና ቂጣ ያለበትን መሶብ አምጣ፤
3.ማኅበሩን በሙሉ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ሰብስብ።”
4.ሙሴም እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ፤ ማኅበሩም በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ተሰበሰበ።
5.ሙሴም ማኅበሩን፣ “እግዚአብሔር እንዲደረግ ያዘዘው ይህ ነው” አላቸው።
6.ሙሴም አሮንንና ልጆቹን ወደ ፊት አወጣቸው፤ በውሃም ዐጠባቸው።
7.አሮንን እጀ ጠባብ አለበሰው፤ መቀነት አስታጠቀው፤ ቀሚስ አጠለቀለት፤ ኤፉድ ደረበለት፤ በልዩ ጥበብ በተጠለፈው መታጠቂያ ኤፉዱን አስታጠቀው፤ በላዩም አሰረው፤
8.የደረት ኪሱን በላዩ አደረገለት፤ በደረት ኪሱም ውስጥ ኡሪምንና ቱሚምን አኖረ።
9.እግዚአብሔር ባዘዘውም መሠረት፣ ሙሴ መጠምጠሚያውን በአሮን ራስ ላይ አደረገ፤ በመጠምጠሚያው ላይ በፊት ለፊቱ በኩል የተቀደሰውን የወርቅ አክሊል አደረገለት።
10.ሙሴም መቅቢያ ዘይቱን ወሰደ፤ ማደሪያ ድንኳኑንና በውስጡ የሚገኘውን ሁሉ ቀብቶ ቀደሰ።
11.ከዘይቱም ጥቂት ወስዶ በመሠዊያው ላይ ሰባት ጊዜ ረጨ፤ ይቀድሳቸውም ዘንድ መሠዊያውን ከነመገልገያ ዕቃው ሁሉ እንዲሁም የመታጠቢያ ሳሕኑን ከነማስቀመጫው በዘይት ቀባ።
12.ከመቅቢያ ዘይቱም በአሮን ራስ ላይ አፈሰሰ፤ የተቀደሰ እንዲሆንም ቀባው።
13.እግዚአብሔርም ባዘዘው መሠረት ሙሴ፣ የአሮንን ልጆች ወደ ፊት አቅርቦ እጀ ጠባብ አለበሳቸው፤ መታጠቂያዎችን አስታጠቃቸው፤ ቆብም ደፋላቸው።
14.ሙሴም የኀጢአት መሥዋዕት የሆነውን ወይፈን አመጣ፤ አሮንና ልጆቹም በወይፈኑ ራስ ላይ እጃቸውን ጫኑ።
15.ሙሴም ወይፈኑን ዐረደ፤ ደሙንም ወስዶ መሠዊያውን ያነጻ ዘንድ በጣቱ የመሠዊያውን ቀንዶች ሁሉ ቀባ፤ የቀረውንም ደም ከመሠዊያው ሥር አፈሰሰው። ለመሠዊያውም እንዲህ አድርጎ ያስተሰርይለት ዘንድ ቀደሰው።
16.ሙሴም የሆድ ዕቃውን የሚሸፍነውን ሥብ ሁሉ፣ የጕበቱን ሽፋን፣ ኵላሊቶችንና ሥባቸውን ወስዶ በመሠዊያው ላይ አቃጠለ።
17.ሙሴም እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት ወይፈኑን፣ ቈዳውን፣ ሥጋውንና ፈርሱን ከሰፈር ውጭ አቃጠለ።
18.ሙሴ ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነውን አውራ በግ አቀረበ፤ አሮንና ልጆቹም እጃቸውን በበጉ ላይ ጫኑ።
19.ሙሴም በጉን ዐርዶ ደሙን በመሠዊያው ላይ ዙሪያውን ረጨ።
20.በጉንም በየብልቱ ቈራረጠ፤ ሙሴም ጭንቅላቱን፣ ብልቶቹንና ሥቡን አቃጠለ።
21.ሆድ ዕቃውንና እግሮቹን በውሃ አጠበ፤ ሙሴም እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት፣ በጉን በሙሉ ለእግዚአብሔር በእሳት የሚቀርብ፣ ሽታውም ደስ የሚያሰኝ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ በመሠዊያው ላይ አቃጠለው።
22.ሙሴ ለቅድስና የሚሆነውን ሌላ አውራ በግ አቀረበ፤ አሮንና ልጆቹም እጆቻቸውን በበጉ ራስ ላይ ጫኑ።
23.ሙሴ አውራ በጉን ዐረደ፤ ከደሙም ጥቂት ወስዶ የአሮንን ቀኝ ጆሮ ጫፍ፣ የቀኝ እጁን አውራ ጣትና የቀኝ እግሩን አውራ ጣት አስነካ፤
24.የአሮንንም ልጆች ወደ ፊት ጠራ፤ ሙሴም ከደሙ ጥቂት ወስዶ የቀኝ ጆሯቸውን ጫፍ፣ የቀኝ እጃቸውን አውራ ጣትና የቀኝ እግራቸውን አውራ ጣት አስነካ፤ የቀረውንም ደም በመሠዊያው ላይ ዙሪያውን ረጨ።
25.ሥቡን፣ ላቱን፣ ሆድ ዕቃውን የሚሸፍነውን ሥብ ሁሉ፣ የጕበቱን ሽፋን፣ ሁለቱን ኵላሊቶችና ሥባቸውን እንዲሁም ቀኝ ወርቹን ወሰደ፤
26.በእግዚአብሔርም ፊት ካለው፣ ያለ እርሾ የተጋገረ ቂጣ ካለበት መሶብ ላይ አንድ ኅብስት፣ አንድ በዘይት የተጋገረ ቂጣ እንዲሁም ስስ ቂጣ ወስዶ በሥቦቹና በቀኝ ወርቹ ላይ አኖረ።
27.እነዚህን ሁሉ ለአሮንና ለወንዶች ልጆቹ በእጃቸው ሰጣቸው፤ እነርሱም የሚወዘወዝ መሥዋዕት አድርገው በእግዚአብሔር ፊት ወዘወዙት።
28.ሙሴም ከእጃቸው ተቀብሎ፣ ለእግዚአብሔር በእሳት የሚቀርብ፣ መዐዛውም ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕት አድርጎ በመሠዊያው ላይ በሚቃጠለው መሥዋዕት ላይ አቃጠለው።
29.ሙሴም እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት፣ ድርሻው የሆነውን ክህነት የመስጫውን አውራ በግ ፍርምባ ወስዶ የሚወዘወዝ መሥዋዕት በማድረግ በእግዚአብሔር ፊት ወዘወዘው።
30.ቀጥሎም ሙሴ በመቅቢያው ዘይትና በመሠዊያው ላይ ካለው ደም ጥቂት ወስዶ፣ በአሮንና በልብሱ እንዲሁም በአሮን ልጆችና በልብሳቸው ላይ ረጨ፤ በዚህም ሁኔታ አሮንንና ልብሱን፣ ልጆቹንና ልብሳቸውን ቀደሰ።
31.ሙሴም አሮንና ልጆቹን እንዲህ አላቸው፤ “ሥጋውን በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ቀቅሉት፤ በዚያም፣ ‘አሮንና ልጆቹ ይብሉት’ ተብዬ በታዘዝሁት መሠረት፣ በክህነት መስጫው መሥዋዕት መሶብ ውስጥ ካለው ቂጣ ጋራ ብሉት፤
32.የተረፈውንም ሥጋና ቂጣ በእሳት አቃጥሉ።
33.የክህነት መቀበያችሁ ሥርዐት እስከሚፈጸምበት እስከ ሰባት ቀን ድረስ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ቈዩ፤ ሥርዐቱንም ለመፈጸም ሰባት ቀን ይወስዳልና።
34.ዛሬ የተፈጸመው ይህ ሥርዐት ለእናንተ ማስተስረያ እግዚአብሔር ያዘዘው ነው።
35.እንዳትሞቱ ሰባቱን ቀንና ሌሊት ከመገናኛው ድንኳን ደጃፍ አትለዩ፤ የእግዚአብሔርንም ሥርዐት ጠብቁ፤ የታዘዝሁት እንዲህ ነውና።”
36.አሮንና ልጆቹም እግዚአብሔር በሙሴ አማካይነት ያዘዘውን ሁሉ አደረጉ።
ምዕራፍ 9
ካህናቱ አገልግሎታቸውን ጀመሩ
1.በስምንተኛውም ቀን ሙሴ አሮንንና ልጆቹን እንዲሁም የእስራኤልን ሽማግሌዎች ጠራቸው። 2.አሮንንም እንዲህ አለው፤ “የኀጢአት መሥዋዕት እንዲሆንልህ አንድ እንቦሳ እንዲሁም የሚቃጠል መሥዋዕት እንዲሆንልህ አንድ አውራ በግ ወስደህ፣ በእግዚአብሔር ፊት አቅርባቸው፤ ሁለቱም እንከን የሌለባቸው ይሁኑ። 3.እስራኤላውያንንም እንዲህ በላቸው፤ ‘ለኀጢአት መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል፣ ለሚቃጠል መሥዋዕት እንከን የሌለባቸውን የአንድ ዓመት እንቦሳና የአንድ ዓመት ጠቦት፣ 4.ለኅብረት መሥዋዕት አንድ በሬና አንድ አውራ በግ በዘይት ከተለወሰ የእህል ቍርባን ጋራ በእግዚአብሔር ፊት ለመሠዋት አቅርቡ፤ እግዚአብሔር ዛሬ ይገለጥላችኋልና።’ ” 5.እነርሱም ሙሴ ያዘዛቸውን ሁሉ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ አመጡ፤ ሕዝቡም በሙሉ ቀርበው በእግዚአብሔር ፊት ቆሙ። 6.ሙሴም፣ “የእግዚአብሔር ክብር ይገለጥላችሁ ዘንድ፣ እንድታደርጉት እግዚአብሔር ያዘዛችሁ ይህ ነው” አለ። 7.ሙሴ አሮንን፣ “ወደ መሠዊያው ቀርበህ የኀጢአት መሥዋዕትህንና የሚቃጠለውን መሥዋዕትህን ሠዋ፤ ለራስህና ለሕዝቡም አስተስርይ፤ እግዚአብሔርም ባዘዘው መሠረት የሕዝቡን መሥዋዕት አቅርብ፤ አስተስርይላቸውም” አለው። 8.አሮንም ወደ መሠዊያው መጥቶ ስለ ራሱ የኀጢአት መሥዋዕት የቀረበውን እንቦሳ ዐረደው። 9.ልጆቹም ደሙን አመጡለት፤ እርሱም ጣቱን በደሙ ውስጥ ነክሮ የመሠዊያውን ቀንዶች ቀባ፤ የተረፈውንም ደም በመሠዊያው ግርጌ አፈሰሰው። 10.እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት የኀጢአት መሥዋዕቱን ሥብ፣ ኵላሊቶቹንና የጕበቱን ሽፋን በመሠዊያው ላይ አቃጠለው፤ 11.ሥጋውንና ቍርበቱንም ከሰፈሩ ውጭ በእሳት አቃጠለው። 12.ከዚህ በኋላ አሮን የሚቃጠለውን መሥዋዕት ዐረደ፤ ልጆቹ ደሙን አቀበሉት፤ እርሱም ደሙን በመሠዊያው ላይ ዙሪያውን ረጨ። 13.ልጆቹም የሚቃጠለውን መሥዋዕት ብልት አንድ በአንድ፣ ጭንቅላቱን ሳይቀር አምጥተው ሰጡት፤ እርሱም በመሠዊያው ላይ አቃጠለው። 14.የሆድ ዕቃውንና እግሮቹን ዐጥቦ በመሠዊያው ላይ ካለው ከሚቃጠለው መሥዋዕት በላይ አቃጠለ። 15.አሮንም የሕዝቡን መሥዋዕት አቀረበ፤ ስለ ሕዝቡ የኀጢአት መሥዋዕት የሆነውን ፍየል ወስዶ ዐረደው፤ እንደ ፊተኛው ሁሉ ይህንም በኀጢአት መሥዋዕትነት ሠዋው። 16.የሚቃጠለውንም መሥዋዕት አምጥቶ በሥርዐቱ መሠረት አቀረበው። 17.የእህል ቍርባኑን አመጣ፤ ከላዩም ዕፍኝ ሙሉ ወስዶ ጧት ጧት ከሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕት በተጨማሪ በመሠዊያው ላይ አቃጠለ። 18.አሮንም ስለ ሕዝቡ የኅብረት መሥዋዕት የቀረቡትን በሬውንና አውራ በጉን ዐረደ፤ ልጆቹም ደሙን አመጡለት፤ እርሱም ደሙን በመሠዊያው ላይ ዙሪያውን ረጨ። 19.የበሬውንና የአውራ በጉን ሥብ፦ ላቱን፣ የሆድ ዕቃውን የሚሸፍነውን ሥብ፤ ኵላሊቶቹንና የጕበቱን ሽፋን፣ 20.በፍርምባዎቹ ላይ አስቀመጡ፤ አሮንም ሥቡን በመሠዊያው ላይ አቃጠለ፤ 21.አሮንም ፍርምባዎቹንና የቀኝ ወርቹንም ሙሴ ባዘዘው መሠረት፣ የመወዝወዝ መሥዋዕት አድርጎ በእግዚአብሔር ፊት ወዘወዘው። 22.አሮንም እጆቹን ወደ ሕዝቡ ዘርግቶ ባረካቸው፤ የኀጢአት መሥዋዕቱን፣ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የኅብረቱን መሥዋዕት ካቀረበ በኋላ ወረደ። 23.ከዚህ በኋላ፣ ሙሴና አሮን ወደ መገናኛው ድንኳን ገቡ፤ ከዚያ ሲወጡም ሕዝቡን ባረኩ፤ የእግዚአብሔርም ክብር ለሕዝቡ ሁሉ ተገለጠ። 24.እሳት ከእግዚአብሔር ዘንድ ወጥቶ፣ በመሠዊያው ላይ የነበረውን በላ፤ ሕዝቡም ሁሉ ይህን ባዩ ጊዜ እልል አሉ፤ በግንባራቸውም ተደፉ።ምዕራፍ 10
የናዳብና የአብዩድ መሞት
1.የአሮን ልጆች ናዳብና አብዩድ እያንዳንዳቸው ጥናዎቻቸውን ወስደው ፍም አደረጉባቸው፤ ዕጣንም ጨመሩባቸው፤ እርሱ ያላዘዛቸውን፣ ያልተፈቀደውን እሳት በእግዚአብሔር ፊት አቀረቡ። 2.ከዚህም የተነሣ እሳት ከእግዚአብሔር ዘንድ ወጥቶ በላቸው፤ በእግዚአብሔርም ፊት ሞቱ። 3.ሙሴም አሮንን እንዲህ አለው፤ “እግዚአብሔር፦“ ‘ወደ እኔ በሚቀርቡት መካከል፣
ቅድስናዬን እገልጣለሁ፤
በሕዝቡም ሁሉ ፊት፣
እከበራለሁ’
ብሎ የተናገረው ይህን ነው።” አሮንም ዝም አለ። 4.ሙሴ የአሮንን አጎት የዑዝኤልን ልጆች ሚሳኤልንና ኤልዳፋንን ጠርቶ፣ “ወደዚህ ኑና ወንድሞቻችሁን አንሡ፤ ከመቅደሱም ደጃፍ አርቃችሁ፣ ከሰፈር ወደ ውጭ ውሰዷቸው” አላቸው። 5.እነርሱም መጥተው ሙሴ ባዘዛቸው መሠረት፣ ሟቾቹ የክህነት ቀሚሳቸውን እንደ ለበሱ ተሸክመው ከሰፈር ወደ ውጭ አወጧቸው። 6.ሙሴም አሮንንና የአሮንን ልጆች፣ አልዓዛርንና ኢታምርን እንዲህ አላቸው፤ “እንዳትሞቱ፣ በሕዝቡም ላይ ቍጣ እንዳይመጣ ጠጕራችሁን አትንጩ፤ ልብሳችሁንም አትቅደዱ፤ ነገር ግን እግዚአብሔር በእሳት ስላጠፋቸው ሰዎች ወንድሞቻችሁ እስራኤላውያን ሊያለቅሱላቸው ይችላሉ። 7.የእግዚአብሔር የመቅቢያ ዘይት በላያችሁ ነውና እንዳትሞቱ ከመገናኛው ድንኳን አትውጡ።” እነርሱም ሙሴ እንዳላቸው አደረጉ። 8.እግዚአብሔርም አሮንን እንዲህ አለው፤ 9.“እንዳትሞቱ አንተና ልጆችህ ወደ መገናኛው ድንኳን በምትገቡበት ጊዜ የወይን ጠጅ ወይም ሌላ የሚያሰክር መጠጥ አትጠጡ፤ ይህም በልጅ ልጃችሁ ዘንድ የሚጠበቅ ዘላለማዊ ሥርዐት ነው። 10.የተቀደሰውንና ያልተቀደሰውን፣ ርኩሱንና ንጹሑን ለዩ፤ 11.እግዚአብሔርም በሙሴ አማካይነት የሰጣቸውን ሥርዐት ሁሉ ለእስራኤላውያን አስተምሩ።” 12.ሙሴም አሮንንና የተረፉትን ልጆቹን አልዓዛርንና ኢታምርን እንዲህ አላቸው፤ “በእሳት ለእግዚአብሔር ከቀረበው የእህል ቍርባን የቀረውን ወስዳችሁ ቂጣ ጋግሩ፤ እጅግ ቅዱስ ስለ ሆነ በመሠዊያው አጠገብ ብሉት። 13.ለእግዚአብሔር በእሳት ከሚቀርበው መሥዋዕት ያንተና የልጆችህ ድርሻ ይህ ስለ ሆነ፣ በተቀደሰ ስፍራ ብሉት፤ እንዲህ ታዝዣለሁና። 14.ከእስራኤላውያን የኅብረት መሥዋዕት ላይ የእናንተ ድርሻ ሆኖ ስለ ተሰጠ፣ የተወዘወዘውን ፍርምባና የቀረበውን ወርች አንተ፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆችህ በአምልኮው ሥርዐት መሠረት ንጹሕ በሆነ ስፍራ ብሉት። 15.የቀረበውን ወርችና የተወዘወዘውን ፍርምባ በእግዚአብሔር ፊት የመወዝወዝ መሥዋዕት ሆኖ በእሳት ከቀረበው ሥብ ጋራ ይምጣ። ይህም እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት ለአንተና ለልጆችህ ለዘላለም የተመደበ ድርሻ ይሆናል።” 16.ሙሴ ለኀጢአት መሥዋዕት የሚቀርበውን ፍየል አጥብቆ ፈለገ፤ መቃጠሉንም በተረዳ ጊዜ የተረፉትን የአሮንን ልጆች አልዓዛርንና ኢታምርን ተቈጣቸው፤ እንዲህም አላቸው፤ 17.“የኀጢአት መሥዋዕቱን ለምን በተቀደሰው ስፍራ አልበላችሁትም? እጅግ የተቀደሰ ነው፤ በእግዚአብሔር ፊት ስርየት በማስገኘት የሕዝቡን ኀጢአት እንድታስወግዱበት የተሰጣችሁ ነበር፤ 18.ደሙ ወደ ተቀደሰው ስፍራ ስላልገባ፣ በሰጠሁት ትእዛዝ መሠረት ፍየሉን በተቀደሰው ስፍራ መብላት ይገባችሁ ነበር።” 19.አሮንም ሙሴን፣ “እነሆ፤ በዛሬው ቀን የኀጢአት መሥዋዕታቸውንና የሚቃጠል መሥዋዕታቸውን በእግዚአብሔር ፊት አቀረቡ፤ እኔም እንዲህ ያለ ነገር የደረሰብኝ ሰው ነኝ፤ ታዲያ፣ ዛሬ የኀጢአት መሥዋዕቱን ብበላ ኖሮ እግዚአብሔርስ ደስ ይለው ኖሯልን?” አለው። 20.ሙሴም ይህን በሰማ ጊዜ መልሱ አረካው።
ምዕራፍ 11
የተፈቀደና ያልተፈቀደ መብል
11፥1-23 ተጓ ምብ – ዘዳ 14፥3-20
1.እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤
2.“እስራኤላውያንን እንዲህ በሏቸው፤ ‘በየብስ ከሚኖሩ እንስሳት ሁሉ የምትበሏቸው እነዚህ ናቸው፦
3.ሰኰናው የተሰነጠቀውን የሚያመሰኳውን ማንኛውንም እንስሳ መብላት ትችላላችሁ።
4.“ ‘የሚያመሰኩ ሆነው ሰኰናቸው ያልተሰነጠቀ ወይም ሰኰናቸው የተሰነጠቀ ሆኖ የማያመሰኩትን አትብሉ፤ ግመል ያመሰኳል፤ ሰኰናው ስላልተሰነጠቀ ግን በእናንተ ዘንድ ርኩስ ይሁን።
5.ሽኮኮ ያመሰኳል፤ ሰኰናው ስላልተሰነጠቀ ግን በእናንተ ዘንድ ርኩስ ይሁን።
6.ጥንቸል ያመሰኳል፤ ሰኰናው ስላልተሰነጠቀ ግን በእናንተ ዘንድ ርኩስ ይሁን።
7.ዐሣማ ሰኰናው የተሰነጠቀ ቢሆንም ስለማያመሰኳ በእናንተ ዘንድ ርኩስ ይሁን።
8.የእነዚህን እንስሳት ሥጋ አትብሉ፤ ጥንባቸውንም አትንኩ፤ በእናንተ ዘንድ ርኩሶች ይሁኑ።
9.“ ‘በባሕሮችና በወንዞች ውሃ ውስጥ ከሚኖሩት ፍጥረታት ክንፍና ቅርፊት ያላቸውን መብላት ትችላላችሁ፤
10.ነገር ግን በባሕሮችና በወንዞች ውስጥ ከሚኖሩት ፍጥረታት ሁሉ፣ ከሚንፏቀቁት ወይም በውሃ ውስጥ ከሚኖሩት ሕይወት ካላቸው ሌሎች ፍጥረታት መካከል ክንፍና ቅርፊት የሌላቸው በእናንተ ዘንድ አስጸያፊዎች ይሁኑ፤
11.በእናንተ ዘንድ አስጸያፊ ስለ ሆኑ ሥጋቸውን አትብሉ፤ በድናቸውንም ትጸየፋላችሁ፤
12.ክንፍና ቅርፊት የሌለው ማንኛውም በውሃ ውስጥ የሚኖር ፍጡር በእናንተ ዘንድ አስጸያፊ ይሁን።
13.“ ‘ከአዕዋፍ ወገን እነዚህን ትጸየፋላችሁ፤ ጸያፍ ስለ ሆኑም አትብሏቸው፦ ንስር፣ የጥንብ አሞራ፣ ግልገል አንሣ፣
14.ጭላት፣ ማንኛውም ዐይነት ጭልፊት፣
15.ማንኛውም ዐይነት ቍራ፣
16.ሰጎን፣ ጠላቋ፣ ዝዪ፣ ማንኛውም ዐይነት በቋል፣
17.ጕጕት፣ ርኩም፣ ጋጋኖ፣
18.የውሃ ዶሮ፣ ይብራ፣ ጥንብ አንሣ አሞራ፣
19.ሽመላ፣ ማንኛውም ዐይነት ሳቢሳ፣ ጃንጁላቴ ወፍና የሌሊት ወፍ።
20.“ ‘ክንፍ ኖሯቸው በአራት እግር የሚንቀሳቀሱ ነፍሳት ሁሉ በእናንተ ዘንድ አስጸያፊዎች ይሁኑ።
21.ነገር ግን ክንፍ ኖሯቸው በአራት እግር ከሚንቀሳቀሱ ነፍሳት መካከል ከምድር በሚፈናጠሩበት እግራቸው አንጓ ያለባቸውን መብላት ትችላላችሁ።
22.ከእነዚህ ማንኛውንም ዐይነት አንበጣ፣ ፌንጣና ኵብኵባ መብላት ትችላላችሁ።
23.ነገር ግን ክንፍ ኖሯቸው በአራት እግር የሚንቀሳቀሱትን ፍጥረታት ተጸየፏቸው።
24.“ ‘ከእነዚህ የተነሣ ትረክሳላችሁ፤ የእነዚህን በድን የሚነካ ሁሉ እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል።
25.የእነዚህንም በድን የሚያነሣ ሰው ሁሉ ልብሱን ይጠብ፤ ሆኖም እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ነው።
26.“ ‘ሰኰና ያለው፣ ነገር ግን ሰኰናው ያልተሰነጠቀና የማያመሰኳ ማንኛውም እንስሳ በእናንተ ዘንድ ርኩስ ይሁን። የእነዚህንም በድን የሚነካ ሰው ሁሉ ይረክሳል።
27.አራት እግር ካላቸው እንስሳት ሁሉ በመዳፋቸው የሚሄዱት በእናንተ ዘንድ ርኩሳን ናቸው፤ በድናቸውንም የሚነካ ሁሉ እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል።
28.የእነዚህን በድን የሚያነሣ ሰው ልብሱን ይጠብ፤ ሆኖም እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል፤ እንስሳቱም በእናንተ ዘንድ ርኩሳን ናቸው።
29.“ ‘ምድር ለምድር ከሚንቀሳቀሱ እንስሳት መካከል እነዚህ በእናንተ ዘንድ ርኩሳን ናቸው፦ ሙጭልጭላ፣ ዐይጥ፣ እንሽላሊት በየወገኑ፣
30.ዔሊ፣ ዐዞ፣ ገበሎ፣ አርጃኖ፣ ዕሥሥት።
31.ምድር ለምድር ከሚንቀሳቀሱ እንስሳት ሁሉ መካከል እነዚህ በእናንተ ዘንድ ርኩሳን ናቸው፤ ከእነዚህም የሞተውን የሚነካ ሁሉ እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል።
32.በድኑ በማንኛውም ዕቃ ላይ ቢወድቅ ያ ዕቃ ከዕንጨት፣ ከጨርቅ፣ ከቈዳ ወይም ከበርኖስ የተሠራ ከረጢት ቢሆን ርኩስ ይሆናል፤ በውሃ ውስጥ ይደረግ፤ ሆኖም ርኩስ ነው፤ ከዚያም በኋላ ንጹሕ ይሆናል።
33.በድኑም በሸክላ ዕቃ ውስጥ ቢወድቅ፣ በውስጡ ያለ ነገር ሁሉ ርኩስ ስለሚሆን ዕቃውን ስበሩት።
34.ማንኛውም ምግብ እንዲህ ካለው ዕቃ ውሃ ቢፈስስበት ይረክሳል፤ ከዚህ ዕቃ የሚጠጣውም ነገር ሁሉ ርኩስ ነው።
35.ከበድናቸው አንዱ የወደቀበት ነገር ሁሉ ይረክሳል፤ ምድጃም ይሁን ማሰሮ ይሰበር፤ ርኩሳን ናቸው፤ እናንተም ተጸየፏቸው።
36.ነገር ግን ምንጭ ወይም የውሃ ማጠራቀሚያ ጕድጓድ ንጹሕ እንደ ሆነ ይቈያል፤ ሆኖም በድኑን የነካ ይረክሳል።
37.በሚዘራ ዘር ላይ በድን ቢወድቅ ዘሩ ንጹሕ እንደ ሆነ ይቈያል።
38.ነገር ግን በዘሩ ላይ ውሃ ከፈሰሰበት በኋላ በድን ቢወድቅበት ዘሩ በእናንተ ዘንድ ርኩስ ነው።
39.“ ‘እንድትበሉ ከተፈቀደላችሁ እንስሳት አንዱ ቢሞት፣ በድኑን የሚነካ ማንኛውም ሰው እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል።
40.ማንም ሰው ከበድኑ ቢበላ ልብሱን ይጠብ፤ ሆኖም እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ነው፤ በድኑን የሚያነሣ ልብሱን ይጠብ፤ ሆኖም እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል።
41.“ ‘ምድር ለምድር የሚንቀሳቀስ ማንኛውም ፍጡር ጸያፍ ነው፤ አይበላም።
42.ምድር ለምድር የሚንቀሳቀሰውን ፍጡር ሁሉ፣ ይኸውም በደረቱ የሚሳበውን ወይም በአራት እግር የሚሄደውን ወይም ብዙ እግሮች ያሉትን አትብሉ፤ ጸያፍ ነው።
43.በእነዚህ ፍጥረታት ሁሉ ራሳችሁን አስጸያፊ አታድርጉ፤ በእነርሱም ራሳችሁን በማጕደፍ አትርከሱ።
44.እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ቅዱስ ነኝና እናንተም ተለዩ፤ ቅዱሳንም ሁኑ፤ ምድር ለምድር በሚንቀሳቀስ በማንኛውም ፍጡር ራሳችሁን አታርክሱ።
45.አምላካችሁ እሆን ዘንድ ከግብጽ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ስለዚህ እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ።
46.“ ‘እንስሳትንና አዕዋፍን፣ በውሃ ውስጥ የሚኖሩትንና ምድር ለምድር የሚንቀሳቀሱትን ፍጥረታት ሁሉ በሚመለከት የተሰጠ ሕግ ይህ ነው።
47.በዚህም በርኩሱና በንጹሑ መካከል፣ እንዲሁም ሕይወት ካላቸው ፍጥረታት የሚበሉትንና የማይበሉትን ትለያላችሁ።’ ”
መዝሙረ ዳዊት
ምዕራፍ 110
1.የዳዊት መዝሙር።
1 እግዚአብሔር ጌታዬን፣
“ጠላቶችህን ለእግርህ መረገጫ፣
እስከማደርግልህ ድረስ፣
በቀኜ ተቀመጥ” አለው። 2.እግዚአብሔር ብርቱ በትርህን ከጽዮን ወደ ውጭ ይሰድዳል፤
“አንተም በጠላቶችህ መካከል ሆነህ ትገዛለህ።” 3.ለጦርነት በምትወጣበት ቀን፣
ሰራዊትህ በገዛ ፈቃዱ በጐንህ ይቆማል፤
ከንጋት ማሕፀን፣
በቅዱስ ግርማ ደምቀህ፣
የጕልማሳነትህን ልምላሜ እንደ ጠል ትቀበላለህ። 4.“እንደ መልከ ጼዴቅ ሥርዐት፤
አንተ ለዘላለም ካህን ነህ” ብሎ፣
እግዚአብሔር ምሏል፤
እርሱ ሐሳቡን አይለውጥም። 5.ጌታ በቀኝህ ነው፤
በቍጣውም ቀን ነገሥታትን ያደቅቃቸዋል። 6.በሕዝቦች መካከል ይፈርዳል፤
በየአገሩ ያሉትንም ራሶች ከስክሶ ሬሳ በሬሳ ያደርጋቸዋል። 7.መንገድ ዳር ካለች ፈሳሽ ውሃ ይጠጣል፤
ስለዚህ ራሱን ቀና ያደርጋል።
1 እግዚአብሔር ጌታዬን፣
“ጠላቶችህን ለእግርህ መረገጫ፣
እስከማደርግልህ ድረስ፣
በቀኜ ተቀመጥ” አለው። 2.እግዚአብሔር ብርቱ በትርህን ከጽዮን ወደ ውጭ ይሰድዳል፤
“አንተም በጠላቶችህ መካከል ሆነህ ትገዛለህ።” 3.ለጦርነት በምትወጣበት ቀን፣
ሰራዊትህ በገዛ ፈቃዱ በጐንህ ይቆማል፤
ከንጋት ማሕፀን፣
በቅዱስ ግርማ ደምቀህ፣
የጕልማሳነትህን ልምላሜ እንደ ጠል ትቀበላለህ። 4.“እንደ መልከ ጼዴቅ ሥርዐት፤
አንተ ለዘላለም ካህን ነህ” ብሎ፣
እግዚአብሔር ምሏል፤
እርሱ ሐሳቡን አይለውጥም። 5.ጌታ በቀኝህ ነው፤
በቍጣውም ቀን ነገሥታትን ያደቅቃቸዋል። 6.በሕዝቦች መካከል ይፈርዳል፤
በየአገሩ ያሉትንም ራሶች ከስክሶ ሬሳ በሬሳ ያደርጋቸዋል። 7.መንገድ ዳር ካለች ፈሳሽ ውሃ ይጠጣል፤
ስለዚህ ራሱን ቀና ያደርጋል።
ወደ ዕብራውያን
ምዕራፍ 4
የሰንበት ዕረፍት ለእግዚአብሔር ሕዝብ
1.እንግዲህ ወደ ዕረፍቱ ለመግባት የተሰጠው ተስፋ አሁንም የተጠበቀ ስለ ሆነ፣ ከእናንተ ማንም ለዚያ ሳይበቃ እንዳይቀር እንጠንቀቅ። 2.ለእነዚያ እንደ ተሰበከ ለእኛም ደግሞ ወንጌል ተሰብኮልናልና። ነገር ግን ሰሚዎቹ ቃሉን ከእምነት ጋራ ስላላዋሐዱት አልጠቀማቸውም። 3.እኛ ያመንነው ግን ወደዚያ ዕረፍት እንገባለን፤ እግዚአብሔርም፣“ስለዚህ በቍጣዬ እንዲህ ብዬ ማልሁ፤
‘ፈጽሞ ወደ ዕረፍቴ አይገቡም’ ” ብሏል።
ይሁን እንጂ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የርሱ ሥራ ተከናውኗል። 4.ስለ ሰባተኛውም ቀን በአንድ ስፍራ፣ “በሰባተኛውም ቀን እግዚአብሔር ከሥራው ሁሉ ዐረፈ” ብሏልና። 5.ቀደም ባለው ክፍል ደግሞ፣ “ፈጽሞ ወደ ዕረፍቴ አይገቡም” ይላል። 6.ወደ ዕረፍቱ ገና የሚገቡ አንዳንዶች አሉ፤ ቀድሞ የምሥራቹ ቃል የተሰበከላቸው ባለመታዘዛቸው ምክንያት ወደ ዕረፍት አልገቡም። 7.ስለዚህ እግዚአብሔር፣ “ዛሬ” ብሎ እንደ ገና አንድን ቀን ወሰነ፤ ይህም ከብዙ ዘመን በኋላ በዳዊት በኩል፣
“ዛሬ ድምፁን ብትሰሙ፣
ልባችሁን አታደንድኑ”
ተብሎ ቀደም ሲል እንደ ተነገረው ነው። 8.ኢያሱ ዕረፍትን ሰጥቷቸው ቢሆን ኖሮ፣ ከዚያ በኋላ እግዚአብሔር ስለ ሌላ ቀን ባልተናገረ ነበር። 9.ስለዚህ የሰንበት ዕረፍት ለእግዚአብሔር ሕዝብ ገና ቀርቶለታል፤ 10.ምክንያቱም ወደ እግዚአብሔር ዕረፍት የሚገባ ሁሉ፣ እግዚአብሔር ከሥራው እንዳረፈ፣ እርሱም ደግሞ ከሥራው ያርፋል። 11.እንግዲህ ማንም የእነዚያን አለመታዘዝ ምሳሌ ተከትሎ እንዳይወድቅ፣ ወደዚያ ዕረፍት ለመግባት እንትጋ። 12.የእግዚአብሔር ቃል ሕያውና የሚሠራ ነውና፤ በሁለት በኩል ስለት ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው፤ ነፍስንና መንፈስን፣ ጅማትንና ቅልጥምን እስኪለያይ ድረስ ዘልቆ ይወጋል፤ የልብንም ሐሳብና ምኞት ይመረምራል። 13.ከእግዚአብሔር ዐይን የተሰወረ ምንም ፍጥረት የለም፤ ስለ ራሳችን መልስ መስጠት በሚገባን በርሱ ፊት ሁሉም ነገር የተራቈተና የተገለጠ ነው።