Skip to Content
የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን | YEHIWOT MELHEK BETEKIRSTIAN
የ2019 ዓ.ም የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ 📖 ዛሬን አንብብ →

የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን

Yehiwot Melhek Betekirstian

ሳምንት 8 · ቀን 36 (ሰኞ) 📅 Tikimt 23, 2019

ኦሪት ዘሌዋውያን 8, 9, 10, 11 · መዝሙረ ዳዊት 110 · ወደ ዕብራውያን 4

📖 የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም፦ 1954 መጽሐፍ ቅዱስ አዲሱ መደበኛ ትርጒም

ኦሪት ዘሌዋውያን

ምዕራፍ 8

1.እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 2.አሮንን፥ ከእርሱም ጋር ልጆቹን፥ ልብሱንም፥ የቅብዓቱንም ዘይት፥ ለኃጢአት መሥዋዕትም የሆነውን ወይፈን፥ ሁለቱንም አውራ በጎች፥ የቂጣውንም እንጀራ ሌማት ውሰድ፤ 3.ማኅበሩንም ሁሉ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ሰብስባቸው። 4.ሙሴም እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ፤ ማኅበሩ ሁሉ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ተሰበሰቡ። 5.ሙሴም ማኅበሩን። እግዚአብሔር ይደረግ ዘንድ ያዘዘው ነገር ይህ ነው አላቸው። 6.ሙሴም አሮንንና ልጆቹን አቀረበ፥ በውኃም አጠባቸው። 7.ሸሚዝም አለበሰው፥ በመታጠቂያም አስታጠቀው፥ ቀሚስም አለበሰው፥ ኤፉድም ደረበለት፥ በብልሃትም በተጠለፈ ቋድ አስታጠቀውና በእርሱ ላይ አሰረው። 8.የደረት ኪስ በእርሱ ላይ አደረገ፤ በደረቱ ኪስም ውስጥ ኡሪምንና ቱሚምን አኖረበት። 9.እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው በራሱ ላይ መጠምጠሚያውን አደረገ፤ በመጠምጠሚያውም ላይ በፊቱ በኩል የተቀደሰውን አክሊል፥ ቅጠል የሚመስለውን የወርቅ ምልክት፥ አደረገ። 10.ሙሴም የቅብዓቱን ዘይት ወሰደ፥ ማደሪያውንና በውስጡ ያለውን ሁሉ ቀብቶ ቀደሳቸው። 11.ከእርሱም በመሠዊያው ላይ ሰባት ጊዜ ረጨ፤ ይቀድሳቸውም ዘንድ መሠዊያውንና ዕቃውን ሁሉ፥ የመታጠቢያውን ሰንና መቀመጫውን ቀባ። 12.ከቅብዓቱም ዘይት በአሮን ራስ ላይ አፈሰሰ፥ ይቀድሰውም ዘንድ ቀባው። 13.እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው ሙሴ የአሮንን ልጆች አቀረበ፥ ቀሚሶችንም አለበሳቸው፥ በመታጠቂያም አስታጠቃቸው፥ ቆብም ደፋባቸው። 14.የኃጢአትንም መሥዋዕት ወይፈን አቀረበ፤ አሮንና ልጆቹም በኃጢአቱ መሥዋዕት ወይፈን ራስ ላይ እጆቻቸውን ጫኑ። 15.አረደውም፤ ሙሴም ደሙን ወስዶ በጣቱ የመሠዊያውን ቀንዶች ዙሪያ ቀባ፥ መሠዊያውንም አነጻው፤ ደሙንም ከመሠዊያው በታች አፈሰሰው፥ ያስተሰርይለትም ዘንድ ቀደሰው። 16.በሆድ ዕቃውም ላይ ያለውን ስብ ሁሉ፥ የጕበቱንም መረብ፥ ሁለቱንም ኵላሊቶች ስባቸውንም ወሰደ፤ ሙሴም በመሠዊያው ላይ አቃጠለው። 17.እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው ወይፈኑን፥ ቁርበቱንም፥ ሥጋውንም፥ ፈርሱንም ከሰፈሩ ውጭ በእሳት አቃጠለ። 18.ለሚቃጠል መሥዋዕትም የሚሆን አውራ በግ አቀረበ፤ አሮንና ልጆቹም በአውራው በግ ራስ ላይ እጆቻቸውን ጫኑ። 19.አረደውም፤ ሙሴም ደሙን በመሠዊያው ዙሪያ ረጨው። 20.አውራውንም በግ በየብልቱ ቈረጠ፤ ሙሴም ጭንቅላቱን ብልቶቹንም ስቡንም አቃጠለ። 21.የሆድ ዕቃውንና እግሮቹንም በውኃ አጠበ፤ ሙሴም አውራውን በግ ሁሉ በመሠዊያው ላይ አቃጠለው፤ ይህ ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን የሚቃጠል መሥዋዕት ነበረ፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው ለእግዚአብሔር የእሳት ቍርባን ነበረ። 22.ለቅድስናም የሚሆነውን ሁለተኛውን አውራ በግ አቀረበ፤ አሮንና ልጆቹም በአውራው በግ ራስ ላይ እጆቻቸውን ጫኑ። 23.አረደውም፤ ሙሴን ከደሙ ወስዶ የአሮንን የቀኝ ጆሮውን ጫፍ፥ የቀኝ እጁንም አውራ ጣት የቀኝ እግሩንም አውራ ጣት አስነካው። 24.የአሮንንም ልጆች አቀረበ፤ ሙሴም የቀኝ ጆሮአቸውን ጫፍ፥ የቀን እጃቸውንም አውራ ጣት፥ የቀኝ እግራቸውንም አውራ ጣት ከደሙ አስነካ፤ ሙሴም ደሙን በመሠዊያው ዙሪያ ረጨ። 25.ስቡንና ላቱን፥ በሆድ ዕቃውም ላይ ያለውን ስብ ሁሉ፥ የጕበቱንም መረብ፥ ሁለቱንም ኵላሊቶች ስባቸውንም፥ ቀኝ ወርቹንም ወሰደ፤ 26.በእግዚአብሔር ፊት ካለው ከቂጣው እንጀራ ሌማት አንድ የቂጣ እንጐቻ፥ አንድም የዘይት እንጀራ፥ አንድም ስስ ቂጣ ወስዶ በስቡና በቀኝ ወርቹ ላይ አኖራቸው። 27.ሁሉንም በአሮንና በልጆቹ እጆች ላይ አደረገ፥ በእግዚአብሔርም ፊት ለመወዝወዝ ቍርባን ወዘወዛቸው። 28.ሙሴም ከእጃቸው ተቀብሎ በመሠዊያው በሚቃጠለው መሥዋዕት ላይ አቃጠለው፤ የጣፋጭ ሽታ መቀደሻ ነበረ። እርሱም ለእግዚአብሔር የእሳት ቁርባን ነበረ። 29.ሙሴም ፍርምባውን ወስዶ በእግዚአብሔር ፊት ለመወዝወዝ ቍርባን ወዘወዘው፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው ይህ ለቅድስና ከታረደው አውራ በግ የሙሴ እድል ፈንታ ሆነ። 30.ሙሴም ከቅብዓቱ ዘይትና በመሠዊያው ላይ ካለው ከደሙ ወስዶ በአሮንና በልብሱ ላይ፥ በልጆቹና በልጆቹ ልብስ ላይ ረጨው፤ አሮንንና ልብሱንም፥ ልጆቹንም የልጆቹንም ልብስ ቀደሰ። 31.ሙሴም አሮንንና ልጆቹን አላቸው። ሥጋውን በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ቀቅሉ፤ አሮንና ልጆቹ ይበሉታል ብዬ እንዳዘዝሁ በዚያ እርሱንና በሌማቱ ያለውን የቅድስናውን እንጀራ ብሉ። 32.ከሥጋውና ከእንጀራውም የተረፈውን በእሳት ታቃጥሉታላችሁ። 33.ሰባት ቀን ይክናችኋልና የክህነታችሁ ቀን እስኪፈጸም ድረስ ሰባት ቀን ከማኅበሩ ድንኳን ደጃፍ አትውጡ። 34.በዚህ ቀን እንደ ተደረገ ለእናንተ ለማስተስረያ ይደረግ ዘንድ እንዲሁ እግዚአብሔር አዘዘ። 35.እግዚአብሔር እንዲሁ አዝዞኛልና እንዳትሞቱ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ሌሊቱንና ቀኑን ሰባት ቀን ተቀመጡ፥ የእግዚአብሔርንም ሥርዓት ጠብቁ። 36.አሮንና ልጆቹም እግዚአብሔር በሙሴ እጅ ያዘዘውን ሁሉ አደረጉ።

ምዕራፍ 9

1.በስምንተኛውም ቀን እንዲህ ሆነ፤ ሙሴ አሮንንና ልጆቹን የእስራኤልንም ሽማግሌዎች ጠራ። 2.አሮንንም አለው። ስለ ኃጢአት መሥዋዕት ከመንጋው እምቦሳውን፥ ስለሚቃጠልም መሥዋዕት አውራውን በግ ነውር የሌለባቸውን ወስደህ በእግዚአብሔር ፊት አቅርባቸው። 3. 4.የእስራኤልንም ልጆች። ዛሬ እግዚአብሔር ይገለጥላችኋልና ለኃጢአት መሥዋዕት አውራ ፍየልን፥ ለሚቃጠልም መሥዋዕት ነውር የሌለባቸውን አንድ ዓመት የሆናቸውን እምቦሳና ጠቦትን፥ ለደኅንነትም መሥዋዕት በሬንና አውራን በግ፥ በዘይትም የተለወሰ የእህልን ቍርባን በእግዚአብሔር ፊት ይሠዉ ዘንድ ውሰዱ ብለህ ንገራቸው። 5.ሙሴም ያዘዛቸውን ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ አመጡ፤ ማኅበሩም ሁሉ ቀርበው በእግዚአብሔር ፊት ቆሙ። 6.ሙሴም። ታደርጉት ዘንድ እግዚአብሔር ያዘዘው ይህ ነው፤ የእግዚአብሔርም ክብር ይገለጥላችኋል አለ። 7.ሙሴም አሮንን። ወደ መሠዊያው ቀርበህ የኃጢአትህን መሥዋዕትና የሚቃጠለውን መሥዋዕትህን ሠዋ፥ ለራስህና ለሕዝቡም አስተስርይ፤ እግዚአብሔርም እንዳዘዘ የሕዝቡን ቍርባን አቅርብ አስተስርይላቸውም አለው። 8.አሮንም ወደ መሠዊያው ቀርቦ ስለ ራሱ ኃጢአት መሥዋዕት የሆነውን እምቦሳ አረደ። 9.የአሮንም ልጆች ደሙን አቀረቡለት፤ ጣቱንም በደሙ ውስጥ ነክሮ የመሠዊያውን ቀንዶች አስነካ፥ ደሙንም ከመሠዊያው በታች አፈሰሰው። 10.እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው ከኃጢአቱ መሥዋዕት ስቡንና ኵላሊቶቹን፥ የጕበቱንም መረብ በመሠዊያው ላይ አቃጠለ። 11.ሥጋውንና ቁርበቱንም ከሰፈሩ ውጭ በእሳት አቃጠለ። 12.የሚቃጠለውንም መሥዋዕት አረደ፤ የአሮንም ልጆች ደሙን አመጡለት፥ እርሱም በመሠዊያው ላይ በዙሪያው ረጨው። 13.የሚቃጠለውንም መሥዋዕት በየብልቱ፥ ራሱንም አመጡለት፤ እርሱም በመሠዊያው ላይ አቃጠለው። 14.የሆድ ዕቃውንና እግሮቹንም አጠበ፤ በመሠዊያውም በሚቃጠለው መሥዋዕት ላይ አቃጠለው። 15.የሕዝቡንም ቍርባን አቀረበ፤ ስለ ሕዝቡ ለኃጢአት መሥዋዕት የሆነውን ፍየል ወስዶ አረደው፥ ስለ ኃጢአትም እንደ ፊተኛው ሠዋው። 16.የሚቃጠለውንም መሥዋዕት አቀረበ፥ እንደ ሥርዓቱም አደረገው። 17.የእህሉንም ቍርባን አቀረበ፥ ከእርሱም እፍኝ ሙሉ ወስዶ በጥዋት ከሚቃጠለው መሥዋዕት ሌላ በመሰዊያው ላይ አቃጠለው። 18.ስለ ሕዝቡ የሆነውን የደኅንነት መሥዋዕት በሬውንና አውራውን በግ አረደ፤ የአሮንም ልጆች ደሙን አመጡለት፥ 19.በመሠዊያውም ላይ በዙሪያው ረጨው፤ የበሬውንና የአራውንም በግ ስብ፥ ላቱንም፥ የሆድ ዕቃውንም የሚሸፍነውን ስብ፥ ኩላሊቶቹንም፥ የጉበቱንም መረብ አመጡለት። 20.ስቡንም በፍርምባዎቹ ላይ አደረጉ፥ ስቡንም በመሠዊያው ላይ አቃጠለ፤ 21.እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው አሮን ፍርምባዎቹንና ቀኝ ወርቹን በእግዚአብሔር ፊት ለመወዝወዝ ቁርባን ወዘወዘው። 22.አሮንም እጆቹን ወደ ሕዝቡ ዘረጋ ባረካቸውም፤ የኃጢያቱን የሚቃጠለውንም የደኅንነቱንም መሥዋዕት ከሠዋ በኋላ ወረደ። 23.ሙሴና አሮንም ወደ መገናኛው ድንኳን ገቡ፤ ወጡም፥ ሕዝቡንም ባረኩ፤ የእግዚአብሔርም ክብር ለሕዝቡ ሁሉ ተገለጠ። 24.እሳትም ከእግዚአብሔር ዘንድ ወጣ፥ በመሠዊያውም ላይ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ስቡንም በላ፤ ሕዝቡም ሁሉ አይተው እልል አሉ፥ በግምባራቸውም ወደቁ።

ምዕራፍ 10

1.የአሮንም ልጆች ናዳብና አብዩድ በየራሳቸው ጥናውን ወስደው እሳት አደረጉበት፥ በላዩም ዕጣን አኖሩበት፥ በእግዚአብሔርም ፊት እርሱ ያላዘዛቸውን ሌላ እሳት አቀረቡ። 2.እሳትም ከእግዚአብሔር ፊት ወጥቶ በላቸው፥ በእግዚአብሔርም ፊት ሞቱ። 3.ሙሴም አሮንን። እግዚአብሔር። ወደ እኔ በሚቀርቡ እቀድሳለሁ፥ በሕዝቡም ሁሉ ፊት እከብራለሁ ብሎ የተናገረው ይህ ነው አለው፤ አሮንም ዝም አለ 4.ሙሴም የአሮንን አጎት የዑዝኤልን ልጆች ሚሳኤልንና ኤልጻፋንን ጠርቶ። ቅረቡ፥ ወንድሞቻችሁንም ከመቅደሱ ፊት አንሥታችሁ ከሰፈር ወደ ውጭ ውሰዱአቸው አላቸው። 5.እነርሱም ቀርበው አነሡአቸው፥ ሙሴም እንዳለ በቀሚሳቸው ከሰፈር ወደ ውጭ ወሰዱአቸው። 6.ሙሴም አሮንን፥ ልጆቹንም አልዓዛርንና ኢታምርን። እንዳትሞቱ በማኅበሩም ሁሉ ላይ ቁጣ እንዳይወርድ ራሳችሁን አትንጩ፥ ልብሳችሁንም አትቅደዱ፤ እግዚአብሔር ስላቃጠለው ማቃጠል ግን ወንድሞቻችሁ የእስራኤል ቤት ሁሉ ያልቅሱ። 7.የእግዚአብሔር የቅብዓት ዘይት በላያችሁ ነውና እንዳትሞቱ ከመገናኛው ድንኳን ደጃፍ አትወጡም አላቸው። እንደ ሙሴ ቃልም አደረጉ። 8.እግዚአብሔርም አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 9.እንዳትሞቱ ወደ መገናኛው ድንኳን ስትገቡ አንተና ልጆችህ የወይን ጠጅና የሚያሰክርን ነገር ሁሉ አትጠጡ፤ ይህም ለልጅ ልጃችሁ የዘላለም ሥርዓት ይሆናል፤ 10.በተቀደሰውና ባልተቀደሰው፥ በርኩሱና በንጹሑም መካከል ትለያላችሁ፤ 11.እግዚአብሔርም በሙሴ ቃል የነገራቸውን ሥርዓት ሁሉ ለእስራኤል ልጆች ታስተምራላችሁ። 12.ሙሴም አሮንን፥ የተረፉለትንም ልጆቹን አልዓዛርንና ኢታምርን አላቸው። ቅዱስ ቅዱሳን ነውና ለእግዚአብሔር ከሆነው ከእሳት ቁርባን የቀረውን የእህሉን ቁርባን ውሰዱ፥ ቂጣም አድርጋችሁ በመሠዊያው አጠገብ ብሉት እግዚአብሔርም እንዲህ አዞኛል፥ 13.ለእግዚአብሔር ከሆነው ከእሳት ቁርባን ለአንተም ለልጆችህም የተሰጠ ሥርዓት ነውና በቅዱስ ስፍራ ትበሉታላችሁ። 14.እነዚህም ከእስራኤል ልጆች ከደኅንነት መሥዋዕቶች ለአንተና ለልጆችህ ሥርዓት እንዲሆኑ ስለ ተሰጡ፥ የሚወዘወዘውን ፍርምባ፥ የሚነሣውንም ወርች አንተ፥ ከአንተ ጋርም ልጆችህ፥ ሴቶች ልጆችህም በንጹሕ ስፍራ ትበላላችሁ። 15.የሚነሣውን ወርች የሚወዘወዘውንም ፍርምባ በእግዚአብሔር ፊት ለመወዝወዝ ቁርባን እንዲወዘውዙ የእሳት ቁርባን ከሆነው ስብ ጋር ያመጣሉ፤ እግዚአብሔር እንዳዘዘ ለአንተ ከአንተ ጋርም ለልጆችህ የዘላለም ሥርዓት ይሆናል። 16.ሙሴም የኃጢያቱን መሥዋዕት ፍየል እጅግ ፈለገው፥ እነሆም ተቃጥሎ ነበር፤ ሙሴም የቀሩትን የአሮንን ልጆች አልአዛርንና ኢታምርን ተቈጥቶ። 17.ቅዱስ ቅዱሳን ነውና፥ የሕዝቡንም ኃጢያት እንድትሸከሙ፥ በእግዚአብሔርም ፊት እንድታስተሰርዩላቸው ለእናንተ ሰጥቶታልና ስለ ምን የኃጢያትን መሥዋዕት በቅዱሱ ስፍራ አልበላችሁም? 18.እነሆ ደሙን ወደ መቅደሱ ውስጥ አላገባችሁትም፤ እኔ እንዳዘዝሁ በቅዱሱ ስፍራ ውስጥ ትበሉት ዘንድ ይገባችሁ ነበር አላቸው። 19.አሮንም ሙሴን። እነሆ ዛሬ የኃጢያታቸውን መሥዋዕት፥ የሚቃጠለውንም መሥዋዕታቸውን በእግዚአብሔር ፊት አቀረቡ፤ ይህም ሁሉ ደረሰብኝ፤ ዛሬስ የኃጢያት መሥዋዕት በበላሁ ኖሮ በእግዚአብሔር ፊት መልካም ኖሮአልን? አለው። 20.ሙሴም ሰማ በፊቱም መልካም ሆነ።

ምዕራፍ 11

1.እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው። 2.ለእስራኤል ልጆች እንዲህ በሉአቸው። ከምድር እንስሶች ሁሉ የምትበሉአቸው እነዚህ ናቸው። 3.የተሰነጠቀ ሰኮና ያለውንና የሚያመሰኳውን እንስሳ ሁሉ ብሉ። 4.ነገር ግን ከሚያመሰኩት፥ ሰኮናቸው ስንጥቅ ከሆነው ከእነዚህ አትበሉም፤ ግመል ያመሰኳል፥ ነገር ግን ሰኮናው ስላልተሰነጠቀ በእናንተ ዘንድ ርኩስ ነው። 5.ሽኮኮ ያመሰኳል፥ ነገር ግን ሰኰናው ስላልተሰነጠቀ በእናንተ ዘንድ ርኩስ ነው። 6.ጥንቸልም ያመሰኳል፥ ነገር ግን ሰኮናው ስላልተሰነጠቀ በእናንተ ዘንድ ርኩስ ነው። 7.እርያም ሰኮናው ተሰንጥቋል፥ ነገር ግን ስለማያመሰኳ በእናንተ ዘንድ ርኩስ ነው። 8.የእነዚህን ሥጋ አትበሉም፥ በድናቸውንም አትነኩም፤ በእናንተ ዘንድ ርኩሶች ናቸው። 9.በውኃ ውስጥ ከሚኖሩት ሁሉ እነዚህን ትበላላችሁ በውኆች በባሕሮችም በወንዞችም ውስጥ ከሚኖሩት ሁሉ ክንፍና ቅርፊት ያላቸውን ትበላላችሁ። 10.በውኆቹ ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ፥ በውኆች ውስጥ የሕይወት ነፍስ ካላቸው ሁሉ፥ በባሕሮችና በወንዞች ውስጥ ክንፍና ቅርፊት የሌላቸው ሁሉ በእናንተ ዘንድ የተጸየፉ ናቸው። 11.በእናንተም ዘንድ የተጸየፉ ይሆናሉ፤ ሥጋቸውንም አትበሉም፥ በድናቸውንም ትጸየፋላችሁ። 12.ክንፍና ቅርፊትም የሌላቸው በውኃ ውስጥ የሚኖሩት ሁሉ በእናንተ ዘንድ የተጸየፉ ናቸው። 13.ከወፎችም ወገን የምትጸየፉአቸው እነዚህ ናቸው፤ አይበሉም፤ የተጸየፉ ናቸው፤ 14.ንስር፥ ገዲ፥ ዓሣ አውጭ፥ ጭላት፥ ጭልፊት በየወገኑ፥ 15.ቁራ ሁሉ በየወገኑ፥ 16.ሰጎን፥ ጠላቋ፥ ዝዪ፥ በቋል በየወገኑ፥ 17. 18.ጕጕት፥ እርኩም፥ ጋጋኖ፥ የውኀ ዶሮ፥ 19.ይብራ፥ ጥምብ አንሣ አሞራ፥ ሽመላ፥ ሳቢሳ በየወገኑ፥ ጅንጁላቴ ወፍ፥ የሌሊት ወፍ። 20.የሚበርርም፥ በአራት እግሮችም የሚሔድ ተንቀሳቃሽ ሁሉ በእናንተ ዘንድ የተጸየፈ ነው። 21.ነገር ግን ከሚበርሩት፥ አራትም እግሮች ካሉአቸው፥ ከእግሮቻቸውም በላይ በምድር ላይ የሚዘልሉባቸው ጭኖች ካሉአቸው ተንቀሳቃሾች እነዚህን ትበላላችሁ። 22.ከእነርሱም እነዚህን ትበላላችሁ፤ አራቱን ዓይነት አንበጣዎች በየወገናቸው። 23.ነገር ግን የሚበርር፥ አራትም እግሮች ያሉት ተንቀሳቃሽ ሁሉ በእናንተ ዘንድ የተጸየፈ ነው። 24.በእነዚህም ርኩስ ትሆናላችሁ፤ የእነርሱንም በድን የሚነካ ሁሉ እስከ ማታ ርኩስ ነው። 25.ከእነርሱም በድን የሚያነሣ ሁሉ ልብሱን ይጠብ፥ እስከ ማታም ርኩስ ነው። 26.ሰኮናም ያለው፥ ነገር ግን ሰኮናው ያልተሰነጠቀ፥ የማያመሰኳም እንሰሳ ሁሉ በእናንተ ዘንድ ርኩስ ነው፤ እርሱን የሚነካ ሁሉ ርኩስ ነው። 27.በአራት እግሮቹ ከሚሄድ እንስሳ ሁሉ በመዳፎቹ ላይ የሚሄድ በእናንተ ዘንድ ርኩስ ነው፤ የእርሱን በድን የሚነካ ሁሉ እስከ ማታ ርኩስ ነው። 28.በድናቸውንም የሚያነሣ ልብሱን ይጠብ፥ እስከ ማታም ርኩስ ነው። እነርሱም በእናንተ ዘንድ ርኩሶች ናቸው። 29.በምድር ላይም ከሚንቀሳቀስ ተንቀሳቅሳሽ እነዚህ በእናንተ ዘንድ ርኩሶች ናቸው፤ ሙጭልጭላ፥ አይጥ፥ እንሽላሊት በየወገኑ፥ 30.ኤሊ፥ አዞ፥ ገበሎ፥ አርጃኖ፥ እስስት። 31.ከሚንቀሳቀሱት ሁሉ በእናንተ ዘንድ ርኩሶች የሚሆኑ እነዚህ ናቸው። ከእነርሱም የሞተውን የሚነካ ሁሉ እስከ ማታ ርኩስ ነው። 32.ከእነርሱም የሞተውን የሚነካ በምንም ላይ ቢወድቅ እርሱ ርኩስ ነው፤ የእንጨት ዕቃ ወይም ልብስ ወይም ቁርበት ወይም ከረጢት ቢሆን የሚሠራበት ዕቃ ሁሉ እርሱ በውኃ ውስጥ ይደረግ፥ እስከ ማታም ርኩስ ነው፤ ከዚያም በኋላ ንጹሕ ይሆናል። 33.ከእነርሱም አንዳች በውስጡ የወደቀበትን የሸክላውን ዕቃ ሁሉ ስበሩት፥ በውስጡም ያለው ሁሉ ርኩስ ነው። 34.በእርሱ ውስጥ ያለው፥ ውኃም የሚፈስስበት የሚበላ መብል ሁሉ ርኩስ ነው፤ በዚህም ዕቃ ሁሉ ያለው የሚጠጣ መጠጥ ሁሉ ርኩስ ነው። 35.ከእነዚህም በድን የሚወድቅበት ሁሉ ርኩስ ነው፤ እቶን ወይም ምድጃ ቢሆን ይሰባበራል፤ ርኩሶች ናቸው፤ በእናንተ ዘንድ ርኩሶች ይሆናሉ። 36.ነገር ግን ምንጩ፥ ጕድጓዱም፥ የውኃውም ኵሬ ንጹሐን ናቸው፤ በድናቸውን ግን የሚነካ ርኩስ ነው። 37.ከበድናቸውም በሚዘራ ዘር ላይ አንዳች ቢወድቅ እርሱ ንጹሕ ነው። 38.ነገር ግን በዘሩ ላይ ውኃ ቢፈስስበት፥ ከዚህ በኋላ ከበድናቸው አንዳች ቢወድቅበት፥ በእናንተ ዘንድ ርኩስ ነው። 39.ለመብል ከሚሆኑላችሁ እንስሶች የሞተ ቢኖር፥ በድኑን የሚነካ ሁሉ እስከ ማታ ርኩስ ነው። 40.ከበድኑም የሚበላ ልብሱን ያጥባል፥ እስከ ማታም ርኩስ ይሆናል፤ በድኑንም የሚያነሣ ልብሱን ይጠብ፥ እስከ ማታም ርኩስ ነው። 41.በምድርም ላይ የሚንቀሳቀስ ተንቀሳቃሽ ሁሉ የተጸየፈ ነው፥ አትብሉትም። 42.በሆዱ የሚሳብ፥ በአራትም እግሮች የሚሳብ፥ ብዙ እግሮችም ያሉት፥ በምድርም ላይ የሚንቀሳቀሱ ተንቀሳቃሾች ሁሉ የተጸየፉ ናቸውና አትብሉአቸው። 43.በሚንቀሳቀሱ ተንቀሳቃሾች ሁሉ ሰውነታችሁን አታስጸይፉ፤ በእነርሱም እንዳትረክሱ ሰውነታችሁን አታርክሱባቸው። 44.እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝና፤ ሰውነታችሁን ቀድሱ፥ ቅዱሳንም ሁኑ፥ እኔ ቅዱስ ነኝና፤ በምድርም ላይ በሚሳብ ተንቀሳቃሽ ሁሉ ሰውነታችሁን አታርክሱ። 45.እኔ አምላካችሁ እሆን ዘንድ ከግብፅ ምድር ያወጣኋችሁ እግዚአብሔር ነኝ፤ እንግዲህ እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተ ቅዱሳን ሁኑ። 46.የእንስሳና የወፍ፥ በውኃም ውስጥ የሚንቀሳቀስ የፍጥረት ሁሉ፥ በምድርም ላይ የሚንቀሳቀስ የፍጥረት ሁሉ ሕግ ይህ ነው። 47.በርኩስና በንጹሕ መካከል፥ የሕይወት ነፍስ ካላቸውም በምትበሉትና በማትበሉት መካከል እንድትለዩ ነው።

መዝሙረ ዳዊት

ምዕራፍ 110

1.የዳዊት መዝሙር።
እግዚአብሔር ጌታዬን። ጠላቶችህን ለእግርህ መቀመጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው።
2.እግዚአብሔር የኃይልን በትር ከጽዮን ይልክልሃል፤ በጠላቶችህም መካከል ግዛ። 3.ከአንተ ጋር ቀድሞ በኃይልህ ቀን፥ በቅዱሳን ብርሃን፥ ከአጥቢያ ኮከብ አስቀድሞ ከሆድ ወለድሁህ። 4.እንደ መልከ ጼዴቅ ሥርዓት አንተ ለዘላለም ካህን ነህ ብሎ፥ እግዚአብሔር ማለ አይጸጸትም። 5.እግዚአብሔር በቀኝህ ነገሥታትን በቍጣው ቀን ይቀጠቅጣቸዋል። 6.በአሕዛብ መካከል ይፈርዳል፥ ሬሳዎችንም ያበዛል፤ በሰፊ ምድር ላይ ራሶችን ይቀጠቅጣል። 7.በመንገድ ከፈሳሽ ውኃ ይጠጣል፤ ስለዚህ ራስ ከፍ ከፍ ይላል።

ወደ ዕብራውያን

ምዕራፍ 4

1.እንግዲህ ወደ ዕረፍቱ ለመግባት ተስፋ ገና ቀርቶልን ከሆነ፥ ምናልባት ከእናንተ ማንም የማይበቃ መስሎ እንዳይታይ እንፍራ። 2.ለእነዚያ ደግሞ እንደ ተነገረ ለእኛ የምስራች ተሰብኮልናልና፤ ዳሩ ግን የሰሙት ቃል ከሰሚዎቹ ጋር በእምነት ስላልተዋሐደ አልጠቀማቸውም። 3.ሥራው ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ምንም እንኳ ቢፈጸም። እንዲህ። ወደ ዕረፍቴ አይገቡም ብዬ በቁጣዬ ማልሁ እንዳለ፥ እኛስ ያመንን ወደ ዕረፍቱ እንገባለን። 4.ስለ ሰባተኛው ቀን በአንድ ስፍራ። እግዚአብሔርም በሰባተኛው ቀን ከሥራው ሁሉ ዐረፈ ብሎአልና፤ 5.በዚህ ስፍራም ደግሞ። ወደ ዕረፍቴ አይገቡም። 6.እንግዲህ አንዳንዶች በዚያ እንዲገቡ ስለ ቀሩ፥ ቀድሞም የምስራች የተሰበከላቸው ባለመታዘዝ ጠንቅ ስላልገቡ። 7.ዛሬ ድምፁን ብትሰሙት ልባችሁን እልከኛ አታድርጉ በፊት እንደ ተባለ፥ ይህን ከሚያህል ዘመን በኋላ በዳዊት ሲናገር። ዛሬ ብሎ አንድ ቀን እንደ ገና ይቀጥራል። 8.ኢያሱ አሳርፎአቸው ኖሮ ቢሆንስ፥ ከዚያ በኋላ ስለ ሌላ ቀን ባልተናገረ ነበር። 9.እንግዲያስ የሰንበት ዕረፍት ለእግዚአብሔር ሕዝብ ቀርቶላቸዋል። 10.ወደ ዕረፍቱ የገባ፥ እግዚአብሔር ከሥራው እንዳረፈ፥ እርሱ ደግሞ ከሥራው አርፎአልና። 11.እንግዲህ እንደዚያ እንደ አለመታዘዝ ምሳሌ ማንም እንዳይወድቅ ወደዚያ ዕረፍት ለመግባት እንትጋ። 12.የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና፥ የሚሠራም፥ ሁለትም አፍ ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው፥ ነፍስንና መንፈስንም ጅማትንና ቅልጥምንም እስኪለይ ድረስ ይወጋል፥ የልብንም ስሜትና አሳብ ይመረምራል፤ 13.እኛን በሚቆጣጠር በእርሱ ዓይኖቹ ፊት ሁሉ ነገር የተራቆተና የተገለጠ ነው እንጂ፥ በእርሱ ፊት የተሰወረ ፍጥረት የለም። 14.እንግዲህ በሰማያት ያለፈ ትልቅ ሊቀ ካህናት የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ስላለን፥ ጸንተን ሃይማኖታችንን እንጠብቅ። 15.ከኃጢአት በቀር በነገር ሁሉ እንደ እኛ የተፈተነ ነው እንጂ፥ በድካማችን ሊራራልን የማይችል ሊቀ ካህናት የለንም። 16.እንግዲህ ምሕረትን እንድንቀበል በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ።
♫
Listen to the reading 6 chapter tracks
ኦሪት ዘሌዋውያን Chapter 8
ኦሪት ዘሌዋውያን Chapter 9
ኦሪት ዘሌዋውያን Chapter 10
ኦሪት ዘሌዋውያን Chapter 11
መዝሙረ ዳዊት Chapter 110
ወደ ዕብራውያን Chapter 4
Swipe to browse chapters
Listen 6