ሳምንት 6 · ቀን 30 (አርብ)
📅 Tikimt 13, 2019
ኦሪት ዘጸአት 28, 29, 30, 31 · ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 2
ኦሪት ዘጸአት
ምዕራፍ 28
ልብሰ ተክህኖ
1.“ካህናት ሆነው ያገለግሉኝ ዘንድ ከእስራኤላውያን መካከል ወንድምህ አሮንን ከወንዶች ልጆቹ ከናዳብ፣ ከአብዩድ፣ ከአልዓዛርና ከኢታምር ጋራ ወደ አንተ አቅርባቸው። 2.ለርሱም ማዕርግና ክብር ለመስጠት ለወንድምህ ለአሮን የተቀደሱ መጐናጸፊያዎችን አብጅለት። 3.ካህን ሆኖ እንዲያገለግለኝ የተለየ ይሆን ዘንድ ጥበብ ለሰጠኋቸው በዚህ ጕዳይ ላይ ጥበበኛ ለሆኑ ሰዎች ሁሉ ለአሮን መጐናጸፊያዎችን እንዲሠሩለት ንገራቸው። 4.የሚሠሯቸው መጐናጸፊያዎች የደረት ልብስ ኤፉድ ቀሚስ፣ ጥልፍ ሸሚዝ፣ ጥምጥምና መታጠቂያ ናቸው፤ ካህን ሆነው ያገለግሉኝ ዘንድ የተቀደሱ መጐናጸፊያዎችን ለአሮንና ለወንድ ልጆቹ ይሠራሉ። 5.ወርቅ፣ ሰማያዊ፣ ሐምራዊ፣ ቀይ ማግና ቀጭን በፍታ ይጠቀሙ።ኤፉድ
28፥6-14 ተጓ ምብ – ዘፀ 39፥2-7
6.“የጥልፍ ዐዋቂዎች ኤፉዱን ከወርቅ፣ ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊ፣ ከቀይ ማግና በቀጭኑ ከተፈተለ በፍታ ይሥሩት።
7.መተሳሰር እንዲችል ሆኖ፣ ዳርና ዳር ከሚገኙት ከሁለቱ ጐኖች ጋራ የተያያዙ ሁለት የትከሻ ንጣዮች ይኑሩት።
8.በጥበብ የተጠለፈው የወገብ መታጠቂያ ከወርቅ፣ ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊ፣ ከቀይ ማግና በቀጭኑ ከተፈተለ ሐር ከኤፉድ ጋራ አንድ ወጥ ሆኖ የተሠራ ይሁን።
9.“ሁለት የመረግድ ድንጋዮች ውሰድና የእስራኤልን ልጆች ስሞቻቸውን ቅረጽባቸው።
10.እንደ ልደታቸው ቅደም ተከተል ስድስቱን ስሞች በአንዱ ድንጋይ ላይ የቀሩትንም ስሞች በሌላው ላይ ቅረጽባቸው።
11.የእጅ ጥበብ ባለሙያ ማኅተም እንደሚቀርጽ የእስራኤልን ልጆች ስም በሁለቱ ድንጋዮች ላይ ቅረጽ፤ ከዚያም ድንጋዮቹን በወርቅ ፈርጥ ክፈፋቸው፤
12.ለእስራኤል ልጆች መታሰቢያ ድንጋዮች ይሆኑ ዘንድ በኤፉዱ ትከሻ ላይ ካሉት ንጣዮች ጋራ አያይዛቸው፤ በእግዚአብሔር ፊት መታሰቢያ እንዲሆኑ አሮን ስሞቹን በትከሻው ላይ ይሸከማቸው።
13.የወርቅ ፈርጦችን አብጅ፤
14.እንደ ገመድ ያሉ ሁለት በንጹሕ ወርቅ የተጐነጐኑ ድሪዎችን አብጅተህ ከፈርጡ ጋራ አያይዛቸው።
የደረት ኪስ
28፥15-28 ተጓ ምብ – ዘፀ 39፥8-21
15.“የፍርድ መስጫውን የደረት ኪስ ብልኅ ሠራተኛ እንደሚሠራው አድርገህ አብጀው፤ ልክ እንደ ኤፉዱ ከወርቅ፣ ከሐምራዊ፣ ከቀይ ማግና በቀጭኑ ከተፈተለ በፍታ አብጀው።
16.ርዝመቱ አንድ ስንዝር፣ ወርዱም አንድ ስንዝር ሆኖ ባለአራት ማእዘንና በድርቡ የታጠፈ ይሁን።
17.ከዚያም በላዩ ላይ በአራት ረድፍ የከበሩ ድንጋዮች አድርግበት፤ በመጀመሪያው ረድፍ ሰርድዮን፣ ቶጳዝዮን፣ የሚያበረቀርቅ ዕንቍ፤
18.በሁለተኛውም ረድፍ በሉር፣ ሰንፔርና፣ አልማዝ፤
19.በሦስተኛው ረድፍ ያክንት፣ ኬልቄዶንና፣ አሜቴስጢኖስ፤
20.በአራተኛውም ረድፍ ቢረሌ፣ መረግድና ኢያሰጲድ አድርግበት፤ በወርቅ ፈርጥም ክፈፋቸው።
21.የዐሥራ ሁለቱ ነገዶች ስሞች እንደ ማኅተም የተቀረጸባቸው ለእያንዳንዱ የእስራኤል ልጆች ስም ዐሥራ ሁለት ድንጋዮች ይሁኑ።
22.“ለደረት ኪሱ ከንጹሕ ወርቅ እንደ ገመድ ሆኖ የተጌጠ ጕንጕን አብጅለት።
23.ለርሱም ሁለት የወርቅ ቀለበቶች አብጅተህ ከደረት ኪሱ ሁለት ጐኖች ጋራ አያይዘው።
24.ሁለቱን የወርቅ ጕንጕኖች በደረት ኪሱ ጐኖች ላይ ካሉት ቀለበቶች ጋራ አያይዛቸው።
25.ሌሎቹን የጕንጕን ጫፎች በፊት ላይ ካለው ኤፉድ በትከሻው ላይ ካሉት ንጣዮች ጋራ በማጋጠም ከሁለቱ የወርቅ ፈርጦች ጋራ አያይዛቸው።
26.ሁለት የወርቅ ቀለበቶች አበጅተህ ከኤፉዱ ቀጥሎ ባለው በውስጠኛ ጠርዝ ላይ፣ በሌላ በኩል ካሉት ሁለት የደረት ኪስ ጐኖች ጋራ አያይዛቸው።
27.ሁለት ተጨማሪ የወርቅ ቀለበቶች አበጅተህ ከኤፉዱ መታጠቂያ ከፍ ብሎ ከመጋጠሚያው አጠገብ ካለው በኤፉዱ ፊት ለፊት፣ በትከሻ ላይ ካሉት ንጣዮች ግርጌ ጋራ አያይዘው።
28.የደረት ኪሱም ቀለበቶች፣ የደረት ኪሱ ከኤፉዱ ጋራ እንዳይላቀቅ፣ ከመታጠቂያው ጋራ በማገናኘት በሰማያዊ ገመድ ከኤፉዱ ቀለበቶች ጋራ ይያያዙ።
29.“አሮን ወደ መቅደሱ በሚገባበት ጊዜ በእግዚአብሔር ፊት ለዘላለም መታሰቢያ ይሆን ዘንድ የእስራኤልን ልጆች ስሞች በፍርድ መስጫው ደረት ኪስ በልቡ ላይ ይሸከም።
30.ወደ እግዚአብሔር ፊት በሚገባበት ጊዜ በአሮን ልብ ላይ ይሆኑ ዘንድ ኡሪሙንና ቱሚሙን በደረት ኪሱ አድርግ፤ ስለዚህ አሮን ሁልጊዜ ለእስራኤላውያን የፍርድ መስጫውን በእግዚአብሔር ፊት በልቡ ላይ ይሸከማል።
ሌሎቹ አልባሳት
28፥31-43 ተጓ ምብ – ዘፀ 39፥22-31
31.“የኤፉዱ ቀሚስ ሙሉ በሙሉ ከሰማያዊ ጨርቅ ይሁን፤
32.ከላይ በኩል በመካከሉ ዐንገትጌ አድርገህ አብጀው፤ እንዳይቀደድም በማስገቢያው ዙሪያ እንደ ክሳድ ያለ ዝምዝም ጠርዝ ሥራለት።
33.በጨርቁ ጠርዝ ዙሪያ ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊና ከቀይ ማግ ሮማኖቹን፣ በመካከሉም የወርቅ ሻኵራዎችን አብጅ።
34.የወርቅ ሻኵራዎቹና ሮማኖቹ በጨርቁ ጠርዝ ዙሪያ በመፈራረቅ ይሆናሉ።
35.አሮንም በአገልግሎቱ ጊዜ ይህን መልበስ አለበት፤ በእግዚአብሔር ፊት ወደ መቅደሱ በገባና ከመቅደሱ ሲወጣ እንዳይሞት የሻኵራዎቹ ድምፅ ይሰማል።
36.“ከንጹሕ ወርቅ ዝርግ ሳሕን አበጅተህ፣ቅዱስ ለእግዚአብሔር
በማለት በማኅተም ላይ እንደሚቀረጽ ቅረጸው። 37.ከመጠምጠሚያው ጋራ እንዲያያዝ ሰማያዊ ፈትል እሰርበት፤ እርሱም በመጠምጠሚያው ፊት በኩል ይሁን። 38.ይህም በአሮን ግንባር ላይ ይሆናል፤ እስራኤላውያን ለይተው በሚያቀርቧቸው በማናቸውም የተቀደሱ ስጦታዎች ውስጥ ያለውን በደል ይሸከማል፤ በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነት እንዲኖራቸው ሁልጊዜ በአሮን ግንባር ላይ ይሆናል። 39.“ሸሚዙን ከቀጭን በፍታ ሥራ፤ መጠምጠሚያውንም ከቀጭን በፍታ አብጀው፤ መታጠቂያውንም ጥልፍ ጠላፊ የሠራው ይሁን። 40.የአሮን ወንድ ልጆች ክብርና ማዕርግ እንዲኖራቸው ሸሚዞችን፣ መታጠቂያዎችን፣ የራስ ማሰሪያዎችን አብጅላቸው። 41.እነዚህን ልብሶች ለአሮንና ለወንድ ልጆቹ ካለበስህ በኋላ ቅባቸው፤ ካናቸው፤ ካህናት ሆነው ያገለግሉኝም ዘንድ ቀድሳቸው። 42.“ከወገብ ጀምሮ እስከ ጭን የሚደርስ ሰውነትን የሚሸፍን ከበፍታ የተሠራ የውስጥ ቍምጣ አብጅ። 43.አሮንና ወንድ ልጆቹ ወደ መገናኛው ድንኳን በሚገቡበት ጊዜ ወይም በመቅደሱ ለማገልገል ወደ መሠዊያው ሲቀርቡ፣ በደል ፈጽመው እንዳይሞቱ እነዚህን መልበስ አለባቸው።
“ለአሮንና ለትውልዶቹ ይህ የዘላለም ሥርዐት ይሆናል።
ምዕራፍ 29
የካህናት መቀደስ
29፥1-37 ተጓ ምብ – ዘሌ 8፥1-36
1.“ካህናት ሆነው እንዲያገለግሉኝ ትቀድሳቸው ዘንድ የምታደርገው ይህ ነው፤ ነቀፋ የሌለባቸው አንድ ወይፈንና ሁለት አውራ በጎች ውሰድ።
2.እርሾ ከሌለው ከምርጥ የስንዴ ዱቄት ቂጣ፣ በዘይት የተለወሰ የቂጣ ዕንጐቻና በዘይት የተቀባ ኅብስት ጋግር።
3.በሌማት ላይ አድርገህ ከወይፈኑና ከሁለቱ አውራ በጎች ጋራ አቅርባቸው።
4.ከዚያም አሮንና ወንድ ልጆቹን ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ በማምጣት በውሃ ዕጠባቸው።
5.ልብሶቹን ወስደህ ለአሮን አልብሰው፤ እጀ ጠባብ፣ የኤፉድ ቀሚስ፣ ኤፉዱንና የደረት ኪሱን አልብሰው፤ ኤፉዱን በርሱ ላይ በጥበብ በተሠራ መታጠቂያ እሰረው።
6.መጠምጠሚያውን በራሱ ላይ በማድረግ የተቀደሰውን አክሊል ከመጠምጠሚያው ጋራ አያይዘው።
7.ቅብዐ ዘይት ወስደህ በራሱ ላይ በማፍሰስ ቅባው።
8.ወንዶች ልጆቹን አምጥተህ እጀ ጠባቦቹን አልብሳቸው።
9.የራስ ማሰሪያዎችንም አድርግላቸው፤ ከዚያም አሮንንና ወንዶች ልጆቹን መታጠቂያዎችን አስታጥቃቸው፤ ክህነት የዘላለም ሥርዐት ይሆንላቸዋል።“በዚህም መንገድ አሮንንና ወንዶች ልጆቹን ትክናቸዋለህ። 10.“ወይፈኑን በመገናኛው ድንኳን ፊት ለፊት በማምጣት አሮንና ወንዶች ልጆቹ በራሱ ላይ እጆቻቸውን ይጫኑበት። 11.በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ላይ በእግዚአብሔር ፊት ወይፈኑን ዕረደው። 12.ከወይፈኑ ደም ወስደህ የመሠዊያው ቀንዶች ላይ በጣቶችህ አድርግበት፤ የቀረውንም ከመሠዊያው ሥር አፍስሰው። 13.ከዚያም በሆድ ዕቃዎች ያለውን ስብ ሁሉ፣ የጕበቱን መሸፈኛና ሁለቱንም ኵላሊቶች በዙሪያቸው ካለው ስብ ጋራ ወስደህ በመሠዊያው ላይ አቃጥላቸው። 14.ነገር ግን የወይፈኑን ሥጋ፣ ቈዳውንና ፈርሱን ከሰፈር ውጭ አቃጥለው፤ የኀጢአት መሥዋዕት ነው። 15.“ከሁለቱ አውራ በጎች አንዱን ወስደህ፣ አሮንና ወንዶች ልጆቹ በራሱ ላይ እጃቸውን ይጭኑበታል። 16.አውራውንም በግ ዕረደው፤ ደሙንም ወስደህ በመሠዊያው ላይ ዙሪያውን ርጨው። 17.አውራ በጉን በየብልቱ ቈራርጠህ፣ የሆድ ዕቃውንና እግሮቹን ዐጥበህ ከራሱና ከሌሎቹ ቍርጥራጭ ብልቶች ጋራ አኑረው። 18.ከዚያም አውራ በጉን በሙሉ በመሠዊያው ላይ አቃጥለው፤ ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት ጣፋጭ መዐዛና ለእግዚአብሔር በእሳት የሚቀርብ መሥዋዕት ነው። 19.“ሌላውን አውራ በግ ወስደህ አሮንና ወንዶች ልጆቹ በራሱ ላይ እጆቻቸውን ይጭኑበታል። 20.አውራውንም በግ ዕረደው፤ ከደሙም ወስደህ የአሮንንና የወንዶች ልጆቹን የቀኝ ጆሮዎቻቸውን ጫፍ የቀኝ እጆቻቸውን አውራ ጣቶች፣ የቀኝ እግራቸውንም አውራ ጣቶች ቅባቸው፤ ከዚያም ደሙን በመሠዊያው ላይ ዙሪያውን ርጨው። 21.በመሠዊያው ላይ ካለው ደምና ከቅብዐ ዘይቱ ወስደህ በአሮንና በልብሶቹ ላይ እንዲሁም በወንዶች ልጆቹና በልብሶቻቸው ላይ ርጨው። ከዚያም እርሱና ወንዶች ልጆቹ እንዲሁም ልብሶቻቸው የተቀደሱ ይሆናሉ። 22.“ከዚህ አውራ በግ ሥቡን፣ ላቱን፣ በሆድ ዕቃው ውስጥ ያለውን ስብ፣ የጕበቱን ሽፋን፣ ሁለቱን ኵላሊቶችና በዙሪያቸው ያለውን ሥብና ቀኙን ወርች ውሰድ፤ ይህ የክህነት አውራ በግ ነው። 23.በእግዚአብሔር ፊት በሌማት ካለው ያለ እርሾ ከተጋገረው ቂጣ፣ ዳቦ፣ በዘይት የተሠራ ዕንጐቻና ኅብስት ውሰድ። 24.እነዚህን ሁሉ በአሮንና በወንዶች ልጆቹ እጆች ላይ በማኖር እንደሚወዘወዝ መሥዋዕት በእግዚአብሔር ፊት ወዝውዛቸው። 25.ከዚያም ከእጃቸው ወስደህ ከሚቃጠለው መሥዋዕት ጋራ ለእግዚአብሔር መልካም መዐዛ እንዲሆን በመሠዊያው ላይ አቃጥለው፤ ይህም ለእግዚአብሔር በእሳት የሚቃጠል መሥዋዕት ነው። 26.ለአሮን ክህነት የአውራ በጉን ፍርምባ ከወሰድህ በኋላ እንደሚወዘወዝ መሥዋዕት በእግዚአብሔር ፊት ወዝውዘው፤ ይህም የአንተ ድርሻ ይሆናል። 27.“ለአሮንና ለወንዶች ልጆቹ ለክህነት የሆኑትን የአውራውን በግ ብልቶች ቀድሳቸው። የተወዘወዘውን ፍርምባና የቀረበውን ወርች 28.ለአሮንና ለወንዶች ልጆቹ የዘወትር የእስራኤላውያን ድርሻ የሚሆነው ይህ ነው፤ ከኅብረት መሥዋዕታቸው እስራኤላውያን ለእግዚአብሔር የሚያቀርቡት ነው። 29.“የአሮን የተቀደሱ ልብሶች ለትውልዶቹ ይሆናሉ፤ ይኸውም በእነርሱ ይቀቡና ክህነትን ይቀበሉ ዘንድ ነው። 30.ካህን በመሆን እርሱን የሚተካውና በመቅደሱ ለማገልገል ወደ መገናኛው ድንኳን የሚመጣው ወንድ ልጅ ሰባት ቀን ይለብሳቸዋል። 31.“የክህነቱን አውራ በግ ወስደህ ሥጋውን በተቀደሰ ስፍራ ቀቅለው። 32.አሮንና ወንዶች ልጆቹ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ላይ የአውራውን በግ ሥጋና በሌማት ያለውን ዳቦ ይብሉ። 33.ለክህነታቸውና ለመቀደሳቸው ማስተስረያ የሆኑትን እነዚህን መሥዋዕቶች ይብሉ፤ የተቀደሱ ስለ ሆኑ ሌላ ማንም አይብላቸው። 34.ከክህነቱ የአውራ በግ ሥጋ ወይም ከቂጣው እስከ ንጋት ድረስ ቢተርፍ አቃጥለው፤ የተቀደሰ ስለ ሆነ መበላት የለበትም። 35.“ክህነታቸውን በሰባት ቀን በመፈጸም ለአሮንና ለወንዶች ልጆቹ ያዘዝሁህን ሁሉ አድርግላቸው። 36.ለማስተስረያ የሚሆን አንድ ወይፈን የኀጢአት መሥዋዕት አድርገህ በየዕለቱ ሠዋ፤ ለመሠዊያውም ማስተስረያ በማቅረብ መሠዊያውን አንጻው፤ ትቀድሰውም ዘንድ ቅባው። 37.ለሰባት ቀን ለመሠዊያው ማስተስረያ በማድረግ ቀድሰው፤ ከዚያም መሠዊያው እጅግ የተቀደሰ ይሆናል፤ የሚነካውም ሁሉ የተቀደሰ ይሆናል። 38.“በየዕለቱ ያለ ማቋረጥ በመሠዊያው ላይ የምታቀርበው ይህ ነው፤ ዓመት የሞላቸው ሁለት የበግ ጠቦቶች፤ 39.አንዱን ጠቦት በማለዳ፣ ሌላውን በማታ አቅርብ። 40.ከመጀመሪያው የበግ ጠቦት ጋራ የኢፍ መስፈሪያ አንድ ዐሥረኛ ምርጥ ዱቄትን ተወቅጦ ከተጠለለ ሩብ ኢፍ ዘይት ጋራ ለውስና ሩብ ሂን ወይንን ደግሞ የመጠጥ መሥዋዕት በማድረግ አቅርብ። 41.ሌላውን የበግ ጠቦት በማለዳው እንደ ቀረበው ተመሳሳይ ከሆነው የእህልና የመጠጥ መሥዋዕት ጋራ በማታ ሠዋው፤ ይህም ጣፋጭ መዐዛና ለእግዚአብሔር በእሳት የሚቀርብ መሥዋዕት ነው። 42.“ይህ የሚቃጠል መሥዋዕት በእግዚአብሔር ፊት በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ላይ በሚመጡት ትውልዶች ዘወትር ይደረጋል፤ በዚያ እገናኝሃለሁ፤ እናገርሃለሁም፤ 43.በዚያ ደግሞ ከእስራኤላውያን ጋራ እገናኛለሁ፤ ስፍራውም በክብሬ ይቀደሳል። 44.“ስለዚህ የመገናኛው ድንኳንና መሠዊያውን እኔ እቀድሳለሁ፤ ካህናት ሆነው እንዲያገለግሉኝ አሮንና ወንድ ልጆቹን እቀድሳለሁ። 45.ከዚያም በእስራኤላውያን መካከል እኖራለሁ፤ አምላካቸውም እሆናለሁ። 46.በመካከላቸውም እኖር ዘንድ ከግብጽ ያወጣኋቸው እኔ አምላካቸው እግዚአብሔር መሆኔን ያውቃሉ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው ነኝ።
ምዕራፍ 30
የዕጣን መሠዊያ
30፥1-5 ተጓ ምብ – ዘፀ 37፥25-28
1.“ዕጣን የሚጤስበት መሠዊያ ከግራር ዕንጨት ሥራ።
2.ርዝመቱና ጐኑ ባለአንድ አንድ ክንድ የሆነ ከፍታውም ሁለት ክንድ የሆነ አራት ማእዘን ይሁን፤ ከመሠዊያው ጋራ አንድ ወጥ የሆኑ ቀንዶች ይኑሩት።
3.ላዩን፣ ጐኖቹን ሁሉና ቀንዶቹን በንጹሕ ወርቅ ለብጣቸው፤ ዙሪያውን የወርቅ ክፈፍ አብጅለት።
4.መሠዊያውን ለመሸከም የሚያገለግሉትን መሎጊያዎች የሚይዙ፣ ከክፈፉ በታች ትይዩ የሆኑ ሁለት የወርቅ ቀለበቶችን ለመሠዊያው አብጅ።
5.መሎጊያዎቹንም ከግራር ዕንጨት ሠርተህ በወርቅ ለብጣቸው።
6.መሠዊያውን ከመጋረጃው ፊት ለፊት፣ ይኸውም ከምስክሩ ታቦት ፊት፣ ከምስክሩ በላይ ካለው እኔ አንተን ከምገናኝበት ከስርየት መክደኛው ፊት አስቀምጠው።
7.“አሮን መብራቶቹን በሚያዘጋጅበት ጊዜ፣ በየማለዳው ደስ የሚያሰኝ ሽታ ዕጣን በመሠዊያው ላይ ያጢስ።
8.ምሽት ላይ መብራቶቹን በሚያበራበትም ጊዜ ዕጣኑን ማጠን አለበት፤ ይኸውም በሚመጡት ትውልዶች ሁሉ ዕጣኑ በእግዚአብሔር ፊት ዘወትር እንዲጤስ ነው።
9.በዚህም መሠዊያ ላይ ሌላ ዕጣን ወይም ሌላ የሚቃጠል መሥዋዕት ወይም የእህል መሥዋዕት አታቅርብ፤ የመጠጥ መሥዋዕትም አታፍስስበት።
10.አሮን በዓመት አንድ ጊዜ በቀንዶቹ ላይ ማስተስረያ ያደርግበታል፤ ይህ ዓመታዊ ማስተስረያ በሚመጡት ትውልዶች ሁሉ ለማስተስረያ ከሚሆን የኀጢአት መሥዋዕት ደም ጋራ መደረግ አለበት፤ ይህም ለእግዚአብሔር እጅግ ቅዱስ ነው።”
የማስተስረያ ገንዘብ
11.ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን አለው፤ 12.“የእስራኤላውያንን ጠቅላላ ቈጠራ በምታደርግበት ጊዜ እያንዳንዱ ሰው በሚቈጠርበት ወቅት ለሕይወቱ ቤዛ የሚሆን ወጆ ለእግዚአብሔር መክፈል አለበት፤ በዚህም ዐይነት ስትቈጥራቸው በእነርሱ ላይ መቅሠፍት አይመጣም። 13.ማንም ወደ ተቈጠሩት ዘንድ የሚያልፍ ሃያ አቦሊ በሚመዝን በመቅደሱ ሰቅል ሚዛን ግማሽ ሰቅል መስጠት አለበት፤ ይህ ግማሽ ሰቅል ለእግዚአብሔር የሚቀርብ መሥዋዕት ነው። 14.ዕድሜያቸው ሃያ ዓመትና ከሃያ በላይ ሆኖ ወደ ተቈጠሩት ያለፉት ሁሉ፣ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ማቅረብ አለባቸው። 15.ለሕይወታችሁ ማስተስረያ እንዲሆን ለእግዚአብሔር መሥዋዕት በምታቀርቡበት ጊዜ ባለጠጋው ከግማሽ ሰቅል በላይ፣ ድኻውም አጕድሎ አይስጥ። 16.የማስተስረያውን ገንዘብ ከእስራኤላውያን ተቀብለህ ለመገናኛው ድንኳን አገልግሎት አውለው፤ ለሕይወታችሁ ማስተስረያ በማድረግ በእግዚአብሔር ፊት የእስራኤላውያን ማስተስረያ ይሆናል።”የመታጠቢያ ሰን
17.ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን አለው፤ 18.“ለመታጠቢያ ከንሓስ ማስቀመጫው ጋራ የንሓስ መቆሚያ አብጅ፤ በመገናኛው ድንኳንና በመሠዊያው መካከል አስቀምጠህ ውሃ አድርግበት። 19.አሮንና ወንዶች ልጆቹ በውስጡ ባለው ውሃ እጃቸውንና እግራቸውን ይታጠቡበታል። 20.ወደ መገናኛው ድንኳን በሚገቡበት ጊዜ ሁሉ እንዳይሞቱ በውሃ ይታጠቡ፤ እንዲሁም ለእግዚአብሔር የእሳት መሥዋዕት ለማቅረብ ወደ መሠዊያው ለማገልገል በሚቀርቡበት ጊዜ፣ 21.እንዳይሞቱ እጃቸውንና እግራቸውን ይታጠባሉ፤ ይህም በሚመጡት ትውልዶች ሁሉ ለአሮንና ለትውልዶቹ የዘላለም ሥርዐት ይሆናል።”ቅብዐ ዘይት
22.ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን አለው፣ 23.“ምርጥ ቅመሞችን፣ ዐምስት መቶ ሰቅል ፈሳሽ ከርቤ፣ ግማሽ ይኸውም ሁለት መቶ ዐምሳ ሰቅል ጣፋጭ ቀረፋ፣ ሁለት መቶ ዐምሳ ሰቅል ከሙን፣ 24.ዐምስት መቶ ሰቅል ብርጕድ ውሰድ፤ ሁሉም እንደ መቅደሱ ሰቅልና አንድ የሂን መስፈሪያ የወይራ ዘይት ይሁን፤ 25.እነዚህን በቀማሚ እንደ ተሠራ እንደሚሸት ቅመም የተቀደሰ ቅብዐ ዘይት አድርግ፤ የተቀደሰ ቅብዐ ዘይት ይሆናል። 26.ከዚያም የመገናኛውን ድንኳን፣ የምስክሩን ታቦት፣ ቅባ። 27.ጠረጴዛውንና ዕቃዎቹን ሁሉ፣ መቅረዙንና ዕቃዎቹን፣ የዕጣን መሠዊያውን ቅባ። 28.የሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያውንና ዕቃዎቹን ሁሉ እንዲሁም የመታጠቢያ ሰኑን ከነመቆሚያው እንድትቀባበት ይሁን። 29.እጅግ የተቀደሱ ይሆኑም ዘንድ ቀድሳቸው፤ የሚነካቸውም ሁሉ የተቀደሰ ይሆናል። 30.“ካህናት ሆነው ያገለግሉኝ ዘንድ አሮንንና ወንዶች ልጆቹን ቅባቸው፤ ቀድሳቸውም። 31.ለእስራኤላውያን ንገራቸው፤ ‘በሚመጡት ትውልዶች ሁሉ ይህ የእኔ የተቀደሰ የቅብዐት ዘይት ይሆናል። 32.በማንም ሰው ሰውነት ላይ አታፍስሱት፤ በተመሳሳይ መንገድ ምንም ዘይት አትሥሩ፤ የተቀደሰ ነው፤ ቅዱስ መሆኑን ልብ በሉ። 33.ተመሳሳይ ዐይነት የሠራና ከካህናት ሌላ በማንም ሰው ላይ ያፈሰሰ ሁሉ ከወገኑ ይወገድ።’ ”ዕጣን
34.ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን አለው፤ “ተመጣጣኝ በማድረግ የጣፋጭ ሽቱ ቅመሞች፣ የሚንጠባጠብ ሙጫ፣ በዛጐል ውስጥ የሚገኝ ሽቱ፣ የሚሸት ሙጫ እና ንጹሕ ዕጣን ወስደህ፣ 35.በቀማሚ እንደ ተሠራ ጣፋጭ መዐዛ ያለው የተቀመመ ዕጣን አብጅ፤ በጨው የተቀመመ፣ ንጹሕና የተቀደሰ ይሁን። 36.ከርሱም ጥቂቱን ወቅጠህ ዱቄት በማድረግ አልመህ በመገናኛው ድንኳን ከምስክሩ ፊት ለፊት ከአንተ ጋራ በምገናኝበት ስፍራ አስቀምጠው፤ ለአንተ እጅግ የተቀደሰ ይሆናል። 37.ለራስህ በዚያ ዐይነት መንገድ ምንም ዐይነት ዕጣን አታብጅ። ለእግዚአብሔር የተቀደሰ መሆኑን ልብ በል። 38.በመልካም ሽታው ይደሰት ዘንድ እርሱን አስመስሎ የሚሠራ ሁሉ ከወገኑ የተወገደ ይሁን።”ምዕራፍ 31
ባስልኤልና ኤልያብ
31፥2-6 ተጓ ምብ – ዘፀ 35፥30-35
1.ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤
2.“እነሆ፤ ከይሁዳ ነገድ የሑር የልጅ ልጅ የሆነውን የኡሪን ልጅ ባስልኤልን መርጬዋለሁ።
3.በጥበብ፣ በብልኀት፣ ዕውቀትና ማንኛውንም ዐይነት ሙያ እንዲኖረው የእግዚአብሔርን መንፈስ ሞልቼዋለሁ።
4.ይኸውም በወርቅ፣ በብርና በንሓስ ለሚሠሩት ሥራዎች በጥበብ የተሠሩ ጌጦችን እንዲያበጅ፣
5.ድንጋዮችን እንዲቈፍርና እንዲጠርብ ከዕንጨትም ጥርብ እንዲያወጣ፣ ሁሉንም ዐይነት የእጅ ጥበብ ሥራዎችን እንዲያከናውን ነው።
6.በተጨማሪም ከዳን ነገድ የሆነውን የአሂሳሚክን ልጅ ኤልያብን እንዲረዳው መርጬዋለሁ።“እንዲሁም ያዘዝሁህን ሁሉ ያደርጉ ዘንድ ለእጅ ጥበብ ዐዋቂዎች ሁሉ ብልኀትን ሰጥቻቸዋለሁ፤ 7.“ይኸውም የመገናኛውን ድንኳን፣
የምስክሩን ታቦት በላዩ ላይ ካለው ከስርየት መክደኛው ጋራ፣
ሌሎች የድንኳኑን መገልገያ ዕቃዎች ሁሉ፣ 8.ጠረጴዛውን ከነዕቃዎቹ፣
ከንጹሕ ወርቅ የተሠራውን የወርቅ መቅረዝ ከነዕቃዎቹ፣
የዕጣኑን መሠዊያ፣ 9.የሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያውን ከነዕቃዎቹ፣
ሰኑን፣ ከነማስቀመጫው፣ 10.ከፈትል የተሠሩ ልብሶችን
ይኸውም የካህኑን የአሮንን የተቀደሱ ልብሶችንና
ካህናት ሆነው ሲያገለግሉ የሚለብሷቸውን የወንድ ልጆቹ ልብሶች፣ 11.እንዲሁም የመቅደሱ የሆነውን ቅብዐ ዘይትና ጣፋጭ ሽታ ያለውን ዕጣን እንዲሠሩ ነው።
“ልክ እኔ እንዳዘዝሁህ ያብጇቸው።”
ሰንበት
12.ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 13.“ለእስራኤላውያን ንገራቸው፤ ‘ሰንበቴን ማክበር አለባችሁ፤ ይህም በእኔና በእናንተ መካከል በሚመጡት ትውልዶች ሁሉ ምልክት ይሆናል፤ ይኸውም የምቀድሳችሁ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ እንድታውቁ ነው። 14.“ ‘ለእናንተ ቅዱስ ነውና ሰንበትን አክብሩ፤ ማንም ቢያረክሰው በሞት ይቀጣል፤ በዚያ ቀን ማንም የሚሠራ ቢኖር ከወገኑ ተነጥሎ ይለይ። 15.ስድስት ቀን ሥራ ይሠራል፤ ሰባተኛው ቀን ግን ለእግዚአብሔር የተቀደሰ የዕረፍት ሰንበት ነው፤ በሰንበት ቀን ማንም ቢሠራ በሞት መቀጣት አለበት። 16.እስራኤላውያን በሚመጡት ትውልዶች ሁሉ ሰንበትን በመጠበቅ የዘላለም ኪዳን አድርገው ማክበር አለባቸው፤ 17.በእኔና በእስራኤላውያን መካከል ለዘላለም ምልክት ይሆናል፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን በስድስት ቀን ሠርቶ፣ በሰባተኛው ቀን ከሥራ ታቅቦ ዐርፏልና።’ ” 18.እግዚአብሔር በሲና ተራራ ላይ ለሙሴ መናገሩን ከፈጸመ በኋላ፣ በእግዚአብሔር ጣት የተጻፈባቸውን የድንጋይ ጽላት፣ ሁለቱን የምስክር ጽላት ለርሱ ሰጠው።ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች
ምዕራፍ 2
ትሕትናን ከክርስቶስ መማር
1.ከክርስቶስ ጋራ ካላችሁ አንድነት የተነሣ የትኛውም መበረታታት፣ ከፍቅር የሆነ መጽናናት፣ የመንፈስ ኅብረት፣ ምሕረትና ርኅራኄ ካላችሁ፣ 2.በአንድ ሐሳብ፣ በአንድ ፍቅር፣ በአንድ መንፈስና በአንድ ዐላማ በመሆን ደስታዬን ፍጹም አድርጉልኝ። 3.ሌሎች ከእናንተ እንደሚሻሉ በትሕትና ቍጠሩ እንጂ፣ በራስ ወዳድነት ምኞት ወይም ከንቱ ውዳሴ ለማግኘት አንዳች አታድርጉ። 4.እያንዳንዳችሁ ሌሎችን የሚጠቅመውንም እንጂ፣ ራሳችሁን የሚጠቅመውን ብቻ አትመልከቱ። 5.በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረው ያ አስተሳሰብ፣ በእናንተም ዘንድ ይሁን፤ 6.እርሱ በባሕርዩ አምላክ ሆኖ ሳለ፣ከእግዚአብሔር ጋራ መተካከልን ሊለቅቀው እንደማይገባ አድርጎ አልቈጠረውም፤ 7.ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ፣
በሰውም አምሳል ተገኝቶ፣
ራሱን ባዶ አደረገ፤ 8.ሰው ሆኖ ተገልጦም፣
ራሱን ዝቅ አደረገ፤
እስከ ሞት፣ ያውም በመስቀል ላይ እስከ
መሞት ድረስ ታዛዥ ሆነ። 9.ስለዚህ እግዚአብሔር እጅግ ከፍ አደረገው፤
ከስምም ሁሉ በላይ የሆነውን ስም ሰጠው፤ 10.ይኸውም በሰማይና በምድር፣ ከምድርም በታች፣
ጕልበት ሁሉ ለኢየሱስ ስም ይንበረከክ ዘንድ፣ 11.ምላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር፣
ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደ ሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው።