Skip to Content
የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን | YEHIWOT MELHEK BETEKIRSTIAN
የ2019 ዓ.ም የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ 📖 ዛሬን አንብብ →

የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን

Yehiwot Melhek Betekirstian

ሳምንት 6 · ቀን 28 (ረቡዕ) 📅 Tikimt 11, 2019

ኦሪት ዘጸአት 22, 23, 24 · መዝሙረ ዳዊት 109 · ወደ ኤፌሶን ሰዎች 6

📖 የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም፦ 1954 መጽሐፍ ቅዱስ አዲሱ መደበኛ ትርጒም

ኦሪት ዘጸአት

ምዕራፍ 22

1.ሰው በሬ ወይም በግ ቢሰርቅ፥ ቢያርደው ወይም ቢሸጠው፥ በበሬው ፋንታ አምስት በሬዎች፥ በበጉም ፋንታ አራት በጎች ይክፈል። 2.ሌባው ቤት ሲምስ ቢገኝ፥ እርሱም እስኪሞት ቢመታ፥ በመታው ሰው ላይ የደም ዕዳ አይሆንበትም። 3.ፀሐይ ግን ከወጣችበት የደም ዕዳ አለበት፤ ሌባው የሰረቀውን ይመልስ፤ የሚከፍለውም ቢያጣ ስለ ሰረቀው ይሸጥ። 4.የሰረቀው ደኅና ሆኖ በእጁ ቢገኝ፥ በሬም ወይም አህያ ወይም በግ ቢሆን፥ የሰረቀውን ያህል ሁለት እጥፍ ይክፈል። 5.ማንም ሰው ወደ እርሻ ወይም ወደ ወይን ስፍራ ከብቱን ቢነዳው፥ የሌላውንም እርሻ ቢያስበላ፥ ከተመረጠ እርሻው ከማለፊያውም ወይኑ ይካስ። 6.እሳት ቢነሣ፥ እሾኽንም ቢይዝ፥ ክምሩንም ወይም ያልታጨደውን እህል ወይም እርሻውን ቢያቃጥል፥ እሳቱን ያነደደው ይካስ። 7.ሰው በባልንጀራው ዘንድ ብር ወይም ሌላ ነገር እንዲጠብቅለት አደራ ቢያኖር ከቤቱም ቢሰረቅ፥ ሌባው ቢገኝ ስለ አንድ ሁለት ይክፈል። 8.ሌባውም ባይገኝ ባለቤቱ ወደ ፈራጆች ይቅረብ፥ እጁንም በባልንጀራው ከብት ላይ እንዳልዘረጋ ይማል። 9.ሰዎች ስለ በሬ ወይም ስለ አህያ ወይም ስለ በግ ወይም ስለ ልብስ ወይም ስለ ሌላ ስለ ጠፋ ነገር ቢካሰሱ፥ አንዱም። ይህ የእኔ ነው ቢል፥ ክርክራቸው ወደ ፈራጆች ይድረስ፤ ፈራጆቹም የፈረዱበት እርሱ ለባልንጀራው በአንድ ሁለት ይክፈል። 10.ሰው በባልንጀራው ዘንድ አህያ ወይም በሬ ወይም በግ ወይም ሌላ እንስሳ እንዲጠብቅለት አደራ ቢያኖር፥ ማንም ሳያይ ቢሞት ወይም ቢጎዳ ወይም ቢማረክ፥ 11.በባልንጀራው ከብት ላይ እጁን እንዳልዘረጋ የእግዚአብሔር መሐላ በሁለታቸው መካከል ይሁን፤ የከብቱም ባለቤት መሐላውን ይቀበል፥ እርሱም ምንም አይክፈል። 12.ከእርሱም ዘንድ ቢሰረቅ የጠፋውን ያህል ለባለቤቱ ይመልስ። 13.ተቧጭሮም ቢገኝ ለምስክር ያምጣው፤ በመቧጨሩም ምክንያት አይክፈል። 14.ከባልንጀራው አንዳች ቢዋስ ባለቤቱ ከእርሱ ጋር ሳይኖር ቢጎዳ፥ ወይም ቢሞት፥ ፈጽሞ ይክፈለው። 15.ባለቤቱ ግን ከእርሱ ጋር ቢኖር አይክፈል፤ ቢከራየው በክራዩ ይግባ። 16.ሰው ያልታጨችውን ድንግል ቢያስታት፥ ከእርስዋም ጋር ቢተኛ፥ ማጫዋን ሰጥቶ ሚስት ያድርጋት። 17.አባትዋም እርስዋን እንዳይሰጠው ፈጽሞ እንቢ ቢል እንደ ደናግል ማጫ ያህል ብር ይክፈላት። 18.መተተኛይቱን በሕይወት እንድትኖር አትፍቀድላት። 19.ከእንስሳ ጋር የሚረክስ ፈጽሞ ይገደል። 20.ከእግዚአብሔር በቀር ለአንዳች አምላክ የሚሠዋ ፈጽሞ ይጥፋ። 21.እናንተ በግብፅ ምድር ስደተኞች ነበራችሁና ስደተኛውን አትበድለው፥ ግፍም አታድርግበት። 22.መበለቲቱንና ድሀ አደጎቹን አታስጨንቁአቸው። 23.ብታስጨንቁአቸውና ወደ እኔ ቢጮኹ እኔ ጩኸታቸውን ፈጽሞ እሰማለሁ፤ 24.ቍጣዬም ይጸናባችኋል፥ በሰይፍም አስገድላችኋለሁ፤ ሚስቶቻችሁም መበለት፥ ልጆቻችሁም ድሀ አደጎች ይሆናሉ። 25.ከአንተ ጋር ለተቀመጠው ለወገኔ ለድሀው ገንዘብ ብታበድረው፥ እንደ ባለ አራጣ አትሁን፥ አራጣም አትጫንበት። 26.የባልንጀራህን ልብስ ለመያዣ ብትወስድ ፀሐይ ሳትገባ መልስለት፤ 27.ሥጋውን የሚከድንበት እርሱ ብቻ ነውና፤ የሚተኛበትም ሌላ የለውምና፤ ወደ እኔም ቢጮኽ መሐሪ ነኝና እሰማዋለሁ። 28.ፈራጆችን አትስደብ፥ የሕዝብህንም አለቃ አትርገመው። 29.ነዶህንም የወይንህንም ጭማቂ ለማቅረብ አትዘግይ፤ የልጆችህንም በኵር ትሰጠኛለህ። 30.እንዲህም በበሬዎችህና በበጎችህ ታደርገዋለህ፤ ሰባት ቀን ከእናቱ ጋር ይቀመጥ፥ በስምንተኛውም ቀን ለእኔ ትሰጠዋለህ። 31.ቅዱስ ወገን ትሆኑልኛላችሁ፤ ስለዚህ በምድረ በዳ አውሬ የቧጨረውን ሥጋ ለውሻ ጣሉት እንጂ አትብሉት።

ምዕራፍ 23

1.ሐሰተኛ ወሬ አትቀበል፤ ሐሰተኛ ምስክርም ትሆን ዘንድ ከኃጢአተኛ ጋር እጅህን አታንሣ። 2.ክፉውን ለማድረግ ብዙ ሰዎችን አትከተል፤ ፍርድንም ለማጥመም ከብዙ ሰዎች ጋር ተስማምተህ አትመስክር። 3.በፍርድ ነገርም ለድሀው አታድላ። 4.የጠላትህን በሬ ወይም አህያውን ጠፍቶ ብታገኘው በፍጹም መልስለት። 5.የሚጠላህን ሰው አህያ ከሸክሙ በታች ወድቆ ብታየው አትተወው፥ ነገር ግን ከእርሱ ጋር አንሣው። 6.በሚምዋገትበት ጊዜ የድሀህን ፍርድ አታጥምም። 7.ከሐሰት ነገር ራቅ፤ እኔ ኃጢአተኛውን አላጸድቅምና ንጹሕንና ጻድቅን አትግደል። 8.ማማለጃን አትቀበል፤ ማማለጃ የዓይናማዎችን ሰዎች ዓይን ያሳውራልና፥ የጻድቃንንም ቃል ያጣምማልና። 9.በስደተኛው ግፍ አታድርጉ፤ እናንተ በግብፅ ምድር ስደተኞች ስለ ነበራችሁ የስደተኛ ነፍስ እንዴት እንደ ሆነች አውቃችኋልና። 10.ስድስት ዓመት ምድርህን ዝራ፥ ፍሬዋንም አግባ፤ 11.በሰባተኛው ዓመት ግን ተዋት አሳርፋትም፤ የሕዝብህም ድሆች ይበሉታል፤ ያስቀሩትንም የሜዳ እንስሳ ይብላው። እንዲሁም በወይንህና በወይራህ አድርግ። 12.ስድስት ቀን ሥራህን ሥራ፤ በሬህና አህያህ ያርፉ ዘንድ ለባሪያህም ልጅ ለመጻተኛውም ዕረፍት ይሆን ዘንድ በሰባተኛው ቀን ዕረፍ። 13.ያልኋችሁንም ነገር ሁሉ ጠብቁ፤ የሌሎችንም አማልክት ስም አትጥሩ፥ ከአፋችሁም አይሰማ። 14.በዓመት ሦስት ጊዜ በዓል ታደርግልኛለህ። 15.የቂጣውን በዓል ጠብቅ፤ በአቢብ ወር ከግብፅ ምድር ወጥታችኋልና በዚህ ወር እንዳዘዝሁህ ሰባት ቀን ቂጣ እንጀራ ትበላለህ፤ በፊቴም ባዶ እጃችሁን አትታዩ። 16.በእርሻም የምትዘራትን የፍሬህን በኵራት የመከር በዓል፥ ዓመቱም ሳያልቅ ፍሬህን ከእርሻ ባከማቸህ ጊዜ የመክተቻውን በዓል ጠብቅ። 17.በዓመት ሦስት ጊዜ በአንተ ዘንድ ያለው ወንድ ሁሉ በጌታ በእግዚአብሔር ፊት ይታይ። 18.የመሥዋዕቴን ደም ከቦካ እንጀራ ጋር አትሠዋ፤ የበዓሌም ስብ እስኪነጋ አይደር። 19.የተመረጠውን የምድርህን ፍሬ በኵራት ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ቤት አምጣ። ጠቦትን በእናቱ ወተት አትቀቅል። 20.በመንገድ ይጠብቅህ ዘንድ ወዳዘጋጀሁትም ስፍራ ያገባህ ዘንድ፥ እነሆ፥ እኔ መልአክን በፊትህ እሰድዳለሁ። 21.በፊቱ ተጠንቀቁ፥ ቃሉንም አድምጡ፤ ስሜም በእርሱ ስለ ሆነ ኃጢአት ብትሠሩ ይቅር አይልምና አታስመርሩት። 22.አንተ ግን ቃሉን ብትሰማ፥ ያልሁህንም ሁሉ ብታደርግ፥ ጠላቶችህን እጣላቸዋለሁ፥ የሚያስጨንቁህንም አስጨንቃቸዋለሁ። 23.መልአኬ በፊትህ ይሄዳልና፥ ወደ አሞራውያንም ወደ ኬጢያውያንም ወደ ፌርዛውያንም ወደ ከነዓናውያንም ወደ ኤዊያውያንም ወደ ኢያቡሳውያንም ያገባሃል፤ እኔም አጠፋቸዋለሁ። 24.ለአማልክቶቻቸው አትስገድ፥ አታምልካቸውም፤ እንደ ሥራቸውም አትሥራ፤ ነገር ግን ፈጽመህ አፍርሳቸው፥ ሐውልቶቻቸውንም ሰባብራቸው። 25.አምላካችሁንም እግዚአብሔርን ታመልኩታላችሁ፥ እርሱም እህልህንና ውኃህን ይባርካል፤ በሽታንም ከመካከልህ አርቃለሁ። 26.በምድርህም መካን ወይም የምትጨነግፍ አትሆንም፤ የዘመንህን ቍጥር እሞላለሁ። 27.መፈራቴንም በፊትህ እሰድዳለሁ፥ የምትሄድበትንም ሕዝብ ሁሉ አስደነግጣቸዋለሁ፥ ጠላቶችህንም ሁሉ በፊትህ ጀርባቸውን እንዲያዞሩ አደርጋለሁ። 28.በፊትህም ተርብ እሰድዳለሁ፥ ኤዊያዊውንም ከነዓናዊውንም ኬጢያዊውንም ከፊትህ አባርራለሁ። 29.ምድር ባድማ እንዳትሆን፥ የምድር አራዊትም እንዳይበዙብህ፥ በአንድ ዓመት ከፊታችሁ አላባርራቸውም። 30.ነገር ግን እስክትበዛ ምድርንም እስክትወርስ ድረስ በጥቂት በጥቂት አባርራቸዋለሁ። 31.ድንበርህንም ከኤርትራ ባሕር እስከ ፍልስጥኤም ባሕር፥ ከምድረ በዳም እስከ ወንዙ ድረስ አደርጋለሁ፤ በምድር የሚኖሩትን በእጅህ እጥላለሁና፤ ከፊትህም ታባርራቸዋለሁ። 32.ከእነርሱና ከአማልክቶቻቸው ጋር ቃል ኪዳን አታድርግ። 33.አማልክቶቻቸውንም ብታመልክ ወጥመድ ይሆኑብሃልና እኔን እንድትበድል እንዳያደርጉህ በአገርህ አይቀመጡ።

ምዕራፍ 24

1.ሙሴንም። አንተ አሮንም ናዳብም አብዩድም ከእስራኤልም ሰባ ሽማግሌዎች ወደ እግዚአብሔር ውጡ፥ በሩቁም ስገዱ፤ 2.ሙሴም ብቻውን ወደ እግዚአብሔር ይቅረብ፥ እነርሱ ግን አይቅረቡ፤ ሕዝቡም ከእርሱ ጋር አይውጡ አለው። 3.ሙሴም መጣ ለሕዝቡም የእግዚአብሔርን ቃሎች ሁሉ ሥርዓቱንም ሁሉ ነገረ፤ ሕዝቡም ሁሉ በአንድ ድምፅ። እግዚአብሔር የተናገራቸውን ቃሎች ሁሉ እናደርጋለን ብለው መለሱ። 4.ሙሴም የእግዚአብሔርን ቃሎች ጻፈ፤ ማለዳም ተነሣ፥ ከተራራውም በታች መሠዊያን፥ አሥራ ሁለትም ሐውልቶች ለአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ ሠራ። 5.የሚቃጠል መሥዋዕት እንዲያቀርቡ፥ ለእግዚአብሔርም ስለ ደኅንነት መሥዋዕት በሬዎችን እንዲሠዉ የእስራኤልን ልጆች ጐበዛዝት ሰደደ። 6.ሙሴም የደሙን እኵሌታ ወስዶ በቆሬ ውስጥ አደረገው፤ የደሙንም እኵሌታ በመሠዊያው ረጨው። 7.የቃል ኪዳኑንም መጽሐፍ ወስዶ ለሕዝቡ አነበበላቸው፤ እነርሱም። እግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እናደርጋለን እንታዘዛለንም አሉ። 8.ሙሴም ደሙን ውስዶ በሕዝቡ ላይ ረጨው። በዚህ ቃል ሁሉ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ያደረገው የቃል ኪዳኑ ደም እነሆ አለ። 9.ሙሴም አሮንም ናዳብም አብዩድም ከእስራኤልም ሰባ ሽማግሌዎች ወጡ፤ 10.የእስራኤልንም አምላክ አዩ፤ ከእግሩም በታች እንደ ሰማይ መልክ የሚያበራ እንደ ብሩህ ሰንፔር ድንጋይ የሚመስል ወለል ነበረ። 11.እጁንም በእስራኤል አዛውንቶች ላይ አልዘረጋም፤ እነርሱም እግዚአብሔርን አዩ፥ በሉም ጠጡም። 12.እግዚአብሔርም ሙሴን። ወደ እኔ ወደ ተራራው ውጣ፥ በዚያም ሁን፤ እነርሱን ታስተምር ዘንድ እኔ የጻፍሁትን ሕግና ትእዛዝ የድንጋይም ጽላት እሰጥሃለሁ አለው። 13.ሙሴና ሎሌው ኢያሱ ተነሡ፤ ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ተራራ ወጣ። 14.ሽማግሌዎችንም። ወደ እናንተ እስክንመለስ ድረስ በዚህ ቆዩን፤ አሮንና ሖርም እነሆ ከእናንተ ጋር ናቸው፥ ነገረተኛም ቢኖር ወደ እነርሱ ይምጣ አላቸው። 15.ሙሴም ወደ ተራራ ወጣ፥ ደመናውም ተራራውን ሸፈነው። 16.የእግዚአብሔርም ክብር በሲና ተራራ ላይ ተቀመጠ፥ ደመናውም ስድስት ቀን ሸፈነው፤ በሰባተኛውም ቀን ከደመናው ውስጥ ሙሴን ጠራው። 17.በተራራው ራስ ላይ በእስራኤል ልጆች ፊት የእግዚአብሔር ክብር መታየት እንደሚያቃጥል እሳት ነበረ። 18.ሙሴም ወደ ደመናው ውስጥ ገባ ወደ ተራራውም ወጣ፤ ሙሴም በተራራው ላይ አርባ ቀን አርባ ሌሊትም ቆየ።

መዝሙረ ዳዊት

ምዕራፍ 109

​ለመዘምራን አለቃ፤ የዳዊት መዝሙር።
1.አምላክ ሆይ፥ ምሥጋናዬን ዝም አትበል፥
2.የኃጢአተኛ አፍና የተንኰለኛ አፍ በላዬ ተላቅቀውብኛልና፤ በሽንገላ አንደበትም በላዬ ተናገሩ፤ 3.በጥል ቃል ከበቡኝ፥ በከንቱም ተሰለፉብኝ። 4.በወደድኋቸው ፋንታ አጣሉኝ፥ እኔ ግን እጸልያለሁ። 5.በመልካም ፋንታ ክፉን በወደድኋቸውም ፋንታ ጠላትነትን መለሱልኝ። 6.በላዩ ኃጢአተኛን ሹም፤ ሰይጣንም በቀኙ ይቁም። 7.በተምዋገተም ጊዜ ተረትቶ ይውጣ፤ ጸሎቱም ኃጢአት ትሁንበት። 8.ዘመኖቹም ጥቂት ይሁኑ፤ ሹመቱንም ሌላ ይውሰድ። 9.ልጆቹም ድሀ አደግ ይሁኑ፥ ሚስቱም መበለት ትሁን። 10.ልጆቹም ተናውጠው ይቅበዝበዙ ይለምኑም፥ ከስፍራቸውም ይባረሩ። 11.ባለዕዳም ያለውን ሁሉ ይበርብረው፥ እንግዶችም ድካሙን ሁሉ ይበዝብዙት። 12.የሚያግዘውንም አያግኝ። ለድሀ አደግ ልጆቹም የሚራራ አይኑር። 13.ልጆቹ ይጥፉ፤ በአንድ ትውልድ ስሙ ይደምሰስ። 14.የአባቶቹ ኃጢአት በእግዚአብሔር ፊት ትታሰብ፤ የእናቱም ኃጢአት አትደምሰስ። 15.በእግዚአብሔር ፊት ሁልጊዜ ይኑሩ፤ መታሰቢያቸው ከምድር ይጥፋ። 16.ምሕረትን ያደርግ ዘንድ አላሰበምና ችግረኛንና ምስኪንን ልቡ የተሰበረውንም ሰው ይገድል ዘንድ አሳደደ። 17.መርገምን ወደደ ወደ እርሱም መጣች፤ በረከትንም አልመረጠም ከእርሱም ራቀች። 18.መርገምን እንደ ልብስ ለበሳት፥ እንደ ውኃም ወደ አንጀቱ፥ እንደ ቅባትም ወደ አጥንቱ ገባች። 19.እንደሚለብሰው ልብስ። ሁልጊዜም እንደሚታጠቀው ትጥቅ ይሁነው። 20.ይህ ሥራ ከእግዚአብሔር ዘንድ በሚያጣሉኝ በነፍሴም ላይ ክፉን በሚናገሩ ነው። 21.አንተ ግን አቤቱ ጌታዬ፥ ስለ ስምህ ምሕረትህን በእኔ ላይ አድርግ፤ ምሕረትህ መልካም ናትና አድነኝ። 22.እኔ ችግረኛ ምስኪንም ነኝና፥ ልቤም በውስጤ ደነገጠብኝ። 23.እንዳለፈ ጥላ አለቅሁ፥ እንደ አንበጣም እረገፍሁ። 24.ጕልበቶቼ በጾም ደከሙ፤ ሥጋዬም ቅቤ በማጣት ከሳ። 25.እኔም በእነርሱ ዘንድ ለነውር ሆንሁ፤ ባዩኝ ጊዜ ራሳቸውን ነቀነቁ። 26.አቤቱ አምላኬ፥ እርዳኝ፥ እንደ ምሕረትህም አድነኝ። 27.አቤቱ፥ እጅህ ይህች እንደ ሆነች፥ አንተም ይህችን እንዳደረግህ ይወቁ። 28.እነርሱ ይራገማሉ አንተ ግን ባርክ፤ በእኔ ላይ የሚነሡ ይፈሩ፥ ባሪያህ ግን ደስ ይበለው። 29.የሚያጣሉኝ እፍረትን ይልበሱ፤ እፍረታቸውን እንደ መጐናጸፊያ ይልበሱአት። 30.እግዚአብሔርን በአፌ እጅግ አመሰግነዋለሁ። በብዙዎችም መካከል አከብረዋለሁ፤ 31.ነፍሱን ከሚያሳድዱአት ያድን ዘንድ በድሀ ቀኝ ቆሞአልና።

ወደ ኤፌሶን ሰዎች

ምዕራፍ 6

1.ልጆች ሆይ፥ ለወላጆቻችሁ በጌታ ታዘዙ፥ ይህ የሚገባ ነውና።
2 -
3.መልካም እንዲሆንልህ ዕድሜህም በምድር ላይ እንዲረዝም አባትህንና እናትህን አክብር፤ እርስዋም የተስፋ ቃል ያላት ፊተኛይቱ ትእዛዝ ናት። 4.እናንተም አባቶች ሆይ፥ ልጆቻችሁን በጌታ ምክርና በተግሣጽ አሳድጉአቸው እንጂ አታስቆጡአቸው። 5.ባሪያዎች ሆይ፥ ለክርስቶስ እንደምትታዘዙ በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ በልባችሁ ቅንነት በሥጋ ጌቶቻችሁ ለሆኑ ታዘዙ፤ 6.የእግዚአብሔርን ፈቃድ እንደሚያደርጉ እንደ ክርስቶስ ባሪያዎች እንጂ ለሰው ደስ እንደምታሰኙ ለታይታ የምትገዙ አትሁኑ። 7.ለሰው ሳይሆን ለጌታ እንደምትገዙ በትጋትና በበጎ ፈቃድ ተገዙ፤ 8.ባሪያ ቢሆን ወይም ጨዋ ሰው፥ እያንዳንዱ የሚያደርገውን መልካም ነገር ሁሉ ከጌታ በብድራት እንዲቀበለው ታውቃላችሁና። 9.እናንተም ጌቶች ሆይ፥ ዛቻውን ትታችሁ እንዲሁ አድርጉላቸው፥ በእነርሱና በእናንተ ላይ የሚገዛው ጌታ በሰማይ እንዳለ ለሰው ፊትም እንዳያደላ ታውቃላችሁና። 10.በቀረውስ በጌታና በኃይሉ ችሎት የበረታችሁ ሁኑ። 11.የዲያብሎስን ሽንገላ ትቃወሙ ዘንድ እንዲቻላችሁ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ ልበሱ። 12.መጋደላችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለምና፥ ከአለቆችና ከሥልጣናት ጋር ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር በሰማያዊም ስፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር ነው እንጂ። 13.ስለዚህ በክፉው ቀን ለመቃወም፥ ሁሉንም ፈጽማችሁ ለመቆም እንድትችሉ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ አንሡ።
14 -
15.እንግዲህ ወገባችሁን በእውነት ታጥቃችሁ፥ የጽድቅንም ጥሩር ለብሳችሁ፥ በሰላም ወንጌልም በመዘጋጀት እግሮቻችሁ ተጫምተው ቁሙ፤ 16.በሁሉም ላይ ጨምራችሁ የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ልታጠፉ የምትችሉበትን የእምነትን ጋሻ አንሡ፤ 17.የመዳንንም ራስ ቁር የመንፈስንም ሰይፍ ያዙ እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው። 18.በጸሎትና በልመናም ሁሉ ዘወትር በመንፈስ ጸልዩ፤ በዚህም አሳብ ስለ ቅዱሳን ሁሉ እየለመናችሁ በመጽናት ሁሉ ትጉ፤ 19.ደግሞ የወንጌልን ምሥጢር በግልጥ እንዳስታውቅ አፌን በመክፈት ቃል ይሰጠኝ ዘንድ ስለ እኔ ለምኑ፤ 20.ስለ ወንጌልም በሰንሰለት መልእክተኛ የሆንሁ፥ መናገር እንደሚገባኝ ስለ እርሱ በግልጥ እናገር ዘንድ ለምኑ። 21.ነገር ግን እናንተ ደግሞ እንዴት እንዳለሁ ኑሮዬን እንድታውቁ የተወደደ ወንድምና በጌታ የታመነ አገልጋይ ቲኪቆስ ሁሉን ያስታውቃችኋል፤ 22.ወሬአችንን እንድታውቁና ልባችሁን እንዲያጽናና ወደ እናንተ የምልከው ስለዚህ ምክንያት ነው። 23.ከእግዚአብሔር አብ ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምና ፍቅር ከእምነት ጋር ለወንድሞች ይሁን። 24.ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ባለመጥፋት ከሚወዱ ሁሉ ጋር ጸጋ ይሁን፤ አሜን።
♫
Listen to the reading 5 chapter tracks
ኦሪት ዘጸአት Chapter 22
ኦሪት ዘጸአት Chapter 23
ኦሪት ዘጸአት Chapter 24
መዝሙረ ዳዊት Chapter 109
ወደ ኤፌሶን ሰዎች Chapter 6
Swipe to browse chapters
Listen 5