Skip to Content
የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን | YEHIWOT MELHEK BETEKIRSTIAN
የ2019 ዓ.ም የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ 📖 ዛሬን አንብብ →

የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን

Yehiwot Melhek Betekirstian

ሳምንት 6 · ቀን 26 (ሰኞ) 📅 Tikimt 9, 2019

ኦሪት ዘጸአት 16, 17, 18 · ወደ ኤፌሶን ሰዎች 4

📖 የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም፦ 1954 መጽሐፍ ቅዱስ አዲሱ መደበኛ ትርጒም

ኦሪት ዘጸአት

ምዕራፍ 16

1.ከኤሊምም ተጓዙ፥ የእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ ከግብፅ አገር ከወጡ በኋላ በሁለተኛው ወር ከወሩም በአሥራ አምስተኛው ቀን በኤሊምና በሲና መካከል ወዳለችው ወደ ሲን ምድረ በዳ መጡ። 2.የእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ በምድረ በዳ በሙሴና በአሮን ላይ አንጐራጐሩ። 3.የእስራኤልም ልጆች። ይህን ጉባኤ ሁሉ በራብ ልትገድሉ እኛን ወደዚች ምድረ በዳ አውጥታችኋል፤ በሥጋው ምንቸት አጠገብ ተቀምጠን እንጀራ ስንበላ ስንጠግብ ሳለን በግብፅ ምድር በእግዚአብሔር እጅ ምነው በሞትን! አሉአቸው። 4.እግዚአብሔርም ሙሴን። በሕጌ ይሄዱ ወይም አይሄዱ እንደሆነ እኔ እንድፈትናቸው፥ እነሆ ከሰማይ እንጀራን አዘንብላችኋለሁ፤ ሕዝቡም ወጥተው ለዕለት ለዕለት የሚበቃቸውን ይልቀሙ። 5.እንዲህም ይሆናል፤ በስድስተኛው ቀን ያመጡትን ያዘጋጁ፥ ዕለት ዕለትም ከሚለቅሙት ይልቅ ሁለት እጥፍ ይሁን አለው። 6.ሙሴና አሮንም ለእስራኤል ልጆች ሁሉ። እግዚአብሔር ከግብፅ ምድር እንዳወጣችሁ ማታ ታውቃላችሁ፥ 7.የእግዚአብሔርንም ክብር ጥዋት ታያላችሁ፤ በእግዚአብሔር ላይ ያንጐራጐራችሁትን ሰምቶአልና በእኛም ላይ የምታንጐራጕሩ እኛ ምንድር ነን? አሉ። 8.ሙሴም። እግዚአብሔር ያንጐራጐራችሁበትን ማንጐራጐራችሁን ሰምቶአልና በመሸ ጊዜ ትበሉ ዘንድ ሥጋን፥ ማልዶም ትጠግቡ ዘንድ እንጀራን እግዚአብሔር ይሰጣችኋል፤ እኛም ምንድር ነን? ማንጐራጐራችሁ በእግዚአብሔር ላይ ነው እንጂ በእኛ አይደለም አለ። 9.ሙሴም አሮንን። ለእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ። ማንጐራጐራችሁን ሰምቶአልና ወደ እግዚአብሔር ፊት ቅረቡ በል አለው። 10.እንዲህም ሆነ፤ አሮን ለእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ በተናገረ ጊዜ ወደ ምድረ በዳ ፊታቸውን አቀኑ፤ እነሆም የእግዚአብሔር ክብር በደመናው ታየ።
11.
12.እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። የእስራኤልን ልጆች ማንጐራጐር ሰማሁ። ወደ ማታ ሥጋን ትበላላችሁ፥ ማለዳም እንጀራን ትጠግባላችሁ፤ እኔም እግዚአብሔር አምላካችሁ እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ በላቸው። 13.እንዲህም ሆነ፤ በመሸ ጊዜ ድርጭቶች መጡ፥ ሰፈሩንም ከደኑት፤ ማለዳም በሰፈሩ ዙሪያ ጠል ወድቆ ነበር። 14.የወደቀውም ጠል ባለፈ ጊዜ፥ እነሆ በመሬት ላይ እንደ ደቃቅ ውርጭ ሆኖ ቅርፊት የሚመስል ደቃቅ ነገር በምድረ በዳ ታየ። 15.የእስራኤልም ልጆች ባዩት ጊዜ ያ ምን እንደ ሆነ አላወቁምና እርስ በእርሳቸው። ይህ ምንድር ነው? ተባባሉ። ሙሴም። ትበሉት ዘንድ እግዚአብሔር የሰጣችሁ እንጀራ ነው። 16.እግዚአብሔር ያዘዘው ነገር ይህ ነው። እያንዳንዱ የሚበላውን ያህል ይልቀም፤ በድኳኑ ባሉት ነፍሶች ቍጥር ለአንድ ሰው አንድ ጎሞር ውሰዱ አላቸው። 17.የእስራኤልም ልጆች እንዲሁ አደረጉ፤ አንዱ አብዝቶ አንዱም አሳንሶ ለቀመ። 18.በጎሞርም በሰፈሩት ጊዜ እጅግ ለለቀመ አልተረፈውም ጥቂትም ለለቀመ አልጐደለበትም፤ ሁሉ እያንዳንዱ የሚበላውን ያህል ለቀመ። 19.ሙሴም። ማንም ከእርሱ አንዳች ለነገ አያስቀር አላቸው። 20.ነገር ግን ሙሴን አልሰሙትም፤ አንዳንድ ሰዎችም ከእርሱ ለነገ አስቀሩ፥ እርሱም ተላ ሸተተም፤ ሙሴም ተቈጣቸው። 21.ሰውም ሁሉ ዕለት ዕለት የሚበላውን ያህል በጥዋት ለቀመ፤ ፀሐይም በተኰሰ ጊዜ ቀለጠ። 22.እንዲህም ሆነ፤ በስድስተኛው ቀን ሁለት እጥፍ አድርገው እያንዳንዳቸው ሁለት ጎሞር እንጀራ ለቀሙ፤ የማኀበሩም አለቆች ሁሉ መጥተው ለሙሴ ነገሩት። 23.እርሱም። እግዚአብሔር የተናገረው ይህ ነው። ነገ ዕረፍት፥ ለእግዚአብሔርም የተቀደሰ ሰንበት ነው፤ የምትጋግሩትን ጋግሩ፥ የምትቀቅሉትንም ቀቅሉ፥ የተረፈውን ሁሉ ለነገ እንዲጠበቅ አኑሩት አላቸው። 24.ሙሴም እንዳዘዘ ለነገ አኖሩት፤ አልሸተተም፥ ትልም አልሆነበትም። 25.ሙሴም። የእግዚአብሔር ሰንበት ዛሬ ነውና ብሉት፤ ዛሬ በሜዳ አታገኙትም። 26.ስድስት ቀን ልቀሙት፤ ሰባተኛው ቀን ግን ሰንበት ነው፤ በእርሱ አይገኝም አለ። 27.በሰባተኛውም ቀን እንዲህ ሆነ፤ ከሕዝቡ አንዳንድ ሰዎች ሊለቅሙ ወጡ፥ ምንምን አላገኙም። 28.እግዚአብሔርም ሙሴን። ትእዛዞቼንና ሕጎቼን ለመጠበቅ እስከ መቼ እንቢ ትላላችሁ? 29.እግዚአብሔር ሰንበትን እንደ ሰጣችሁ እዩ፤ ስለዚህ በስድስተኛው ቀን የሁለት ቀን እንጀራ ሰጣችሁ፤ ሰው ሁሉ በስፍራው ይቀመጥ፥ በሰባተኛው ቀን ማንም ከስፍራው አይሂድ አለው። 30.ሕዝቡም በሰባተኛው ቀን ዐረፈ። 31.የእስራኤልም ወገን ስሙን መና ብለው ጠሩት፤ እርሱም እንደ ድንብላል ዘር ነጭ ነው፤ ጣዕሙም እንደ ማር ቂጣ ነው። 32.ሙሴም። እግዚአብሔር ያዘዘው ነገር ይህ ነው። ከግብፅ ምድር ባወጣኋችሁ ጊዜ በምድረ በዳ ያበላኋችሁን እንጀራ ያዩ ዘንድ ከእርሱ አንድ ጎሞር ሙሉ ለልጅ ልጆቻችሁ ይጠበቅ አለ። 33.ሙሴም አሮንን። አንድ ማድጋ ወስደህ ጎሞር ሙሉ መና አግባበት፥ ለልጅ ልጃችሁም ይጠበቅ ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት አኑረው አለው። 34.እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው እንዲሁ ይጠበቅ ዘንድ አሮን በምስክሩ ፊት አኖረው። 35.የእስራኤልም ልጆች ወደሚኖሩባት ምድር እስኪመጡ ድረስ አርባ ዓመት መና በሉ፤ ወደ ከነዓን ምድር ድንበር እስኪመጡ ድረስ መና በሉ። 36.ጎሞርም የኢፍ መስፈሪያ አሥረኛ ክፍል ነው።

ምዕራፍ 17

1.የእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ እግዚአብሔር እንዳዘዘ ከሲን ምድረ በዳ ሊጓዙ ተነሡ፥ በራፊዲምም ሰፈሩ፤ ሕዝቡም ይጠጡ ዘንድ ውኃ አልነበረም። 2.ሕዝቡም ሙሴን ተጣሉት። የምንጠጣውን ውኃ ስጠን አሉት። ሙሴም። ለምን ትጣሉኛላችሁ? እግዚአብሔርንስ ለምን ትፈታተናላችሁ? አላቸው። 3.ሕዝቡም በዚያ ስፍራ ውኃ ተጠሙ። እኛንና ልጆቻችንን ከብቶቻችንንም በጥማት ልትገድል ለምን ከግብፅ አወጣኸን? ሲሉ በሙሴ ላይ አንጐራጐሩ። 4.ሙሴም። ሊወግሩኝ ቀርበዋልና በዚህ ሕዝብ ምን ላድርግ? ብሎ ወደ እግዚአብሔር ጮኸ። 5.እግዚአብሔርም ሙሴን። በሕዝቡ ፊት እለፍ፥ ከእስራኤልም ሽማግሌዎች ከአንተ ጋር ውሰድ፤ ወንዙንም የመታህባትን በትር በእጅህ ይዘሃት ሂድ። 6.እነሆ እኔ በዚያ በኮሬብ በዓለት ላይ በፊትህ እቆማለሁ፤ ዓለቱንም ትመታለህ፥ ሕዝቡም ይጠጣ ዘንድ ከእርሱ ውኃ ይወጣል አለው። ሙሴም በእስራኤል ሽማግሌዎች ፊት እንዲሁ አደረገ። 7.ስለ እስራኤልም ልጆች ክርክር። እግዚአብሔር በመካከላችን ነውን ወይስ አይደለም? ሲሉ እግዚአብሔርን ስለተፈታተኑት የዚያን ስፍራ ስም ማሳህ፥ ደግሞም መሪባ ብሎ ጠራው። 8.አማሌቅም መጥቶ ከእስራኤል ጋር በራፊድም ተዋጋ። 9.ሙሴም ኢያሱን። ጕልማሶችን ምረጥልን፥ ወጥተህም ከአማሌቅ ጋር ተዋጋ፤ እኔ ነገ የእግዚአብሔርን በትር በእጄ ይዤ በኮረብታው ራስ ላይ እቆማለሁ አለው። 10.ኢያሱም ሙሴ እንዳለው አደረገ፥ ከአማሌቅም ጋር ተዋጋ፤ ሙሴና አሮንም ሖርም ወደ ኮረብታው ራስ ወጡ። 11.እንዲህም ሆነ፤ ሙሴ እጁን ባነሣ ጊዜ እስራኤል ድል ያደርግ ነበር፤ እጁንም ባወረደ ጊዜ አማሌቅ ድል ያደርግ ነበር። 12.የሙሴ እጆች ግን ከብደው ነበር፤ ድንጋይም ወሰዱ፥ በበታቹም አኖሩ፥ እርሱም ተቀመጠበት፤ አሮንና ሖርም አንዱ በዚህ አንዱ በዚያ ሆነው እጆቹን ይደግፉ ነበር፤ ፀሐይም እስክትገባ ድረስ እጆቹ ጠነከሩ። 13.ኢያሱም አማሌቅንና ሕዝቡን በሰይፍ ስለት አሸነፈ። 14.እግዚአብሔርም ሙሴን። የአማሌቅን ዝክር ከሰማይ በታች ጨርሼ እደመስሳለሁና ይህን ለመታሰቢያ በመጽሐፍ ጻፈው፥ በኢያሱም ጆሮ ተናገር አለው። 15.ሙሴም መሠዊያ ሠራ፥ ስሙንም ይህዌህ ንሲ ብሎ ጠራው፤ 16.እርሱም። እጁን በእግዚአብሔር ዙፋን ላይ ስለጫነ የእግዚአብሔር ሰልፍ በአማሌቅ ላይ ለልጅ ልጅ ይሁን አለ።

ምዕራፍ 18

1.የምድያምም ካህን የሙሴ አማት ዮቶር እግዚአብሔር ለሙሴና ለሕዝቡ ለእስራኤል ያደረገውን ሁሉ፥ እግዚአብሔርም እስራኤልን ከግብፅ እንዳወጣ ሰማ። 2.በዚያን ጊዜ የሙሴ አማት ዮቶር መልሶአት የነበረውን የሙሴን ሚስት ሲፓራን ሁለቱንም ልጆቿን ወሰደ። 3.ከእነርሱ የአንደኛው ስም ጌርሳም ነበረ፤ አባቱ። በሌላ አገር ስደተኛ ነበርሁ ብሎአልና፤ 4.የሁለተኛውም ስም አልዓዛር ነበረ። የአባቴ አምላክ ረዳኝ፥ ከፈርዖንም ሰይፍ አዳነኝ ብሎአልና። 5.የሙሴ አማት ዮቶርም ከልጆቹና ከሚስቱ ጋር በእግዚአብሔር ተራራ አጠገብ በምድረ በዳ ወደ ሰፈረ ወደ ሙሴ መጣ። 6.ሙሴንም። እኔ አማትህ ዮቶር፥ ሚስትህም፥ ከእርስዋም ጋር ሁለቱ ልጆችዋ መጥተንልሃል አለው። 7.ሙሴም አማቱን ሊገናኝ ወጣ፥ ሰገደም፥ ሳመውም፤ እርስ በርሳቸውም ደኅንነታቸውን ተጠያየቁ፥ ወደ ድንኳኑም ገቡ። 8.ሙሴም እግዚአብሔር በፈርዖንና በግብፃውያን ላይ ስለ እስራኤል ያደረገውን ሁሉ፥ በመንገድም ያገኛቸውን ድካም ሁሉ፥ እግዚአብሔርም እንዳዳናቸው ለአማቱ ነገረው። 9.ዮቶርም እግዚአብሔር ለእስራኤል ስላደረገው ቸርነት ሁሉ፥ ከግብፃውያንም እጅ ስላዳናቸው ደስ አለው። 10.ዮቶርም። ከግብፃውያንና ከፈርዖን እጅ ያዳናችሁ፥ ከግብፃውያንም እጅ ሕዝቡን ያዳነ እግዚአብሔር ይባረክ። 11.ትዕቢት ባደረጉባቸው ነገር እግዚአብሔር ከአማልክት ሁሉ እንዲበልጥ አሁን አወቅሁ አለ። 12.የሙሴ አማት ዮቶርም የሚቃጠል መሥዋዕትንና ሌላ መሥዋዕትን ለእግዚአብሔር ወሰደ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ከሙሴ አማት ጋር እንጀራ ሊበሉ አሮን የእስራኤልም ሽማግሌዎች ሁሉ መጡ። 13.እንዲህም ሆነ፤ በነጋው ሙሴ በሕዝቡ ሊፈርድ ተቀመጠ፤ ሕዝቡም በሙሴ ፊት ከጥዋት እስከ ማታ ድረስ ቆመው ነበር። 14.የሙሴም አማት በሕዝቡ ያደረገውን ሁሉ ባየ ጊዜ። ይህ በሕዝቡ የምታደርገው ምንድር ነው? ሕዝቡ ሁሉ ከጥዋት ጀምሮ እስከ ማታ ድረስ በዙሪያህ ቆመው ሳሉ አንተ ብቻህን ስለ ምን ተቀምጠሃል? አለው። 15.ሙሴም አማቱን። ሕዝቡ እግዚአብሔርን ለመጠየቅ ወደ እኔ ይመጣሉ፤ 16.ነገርም ቢኖራቸው ወደ እኔ ይመጣሉ፥ በዚህና በዚያ ሰውም መካከል እፈርዳለሁ፥ የእግዚአብሔርንም ሥርዓትና ሕግ አስታውቃቸዋለሁ አለው። 17.የሙሴም አማት አለው። አንተ የምታደርገው ይህ ነገር መልካም አይደለም። 18.ይህ ነገር ይከብድብሃልና አንተ ከአንተም ጋር ያለው ሕዝብ ትደክማላችሁ፤ አንተ ብቻህን ልታደርገው አትችልም። 19.አሁንም እመክርሃለሁና ቃሌን ስማ፥ እግዚአብሔርም ከአንተ ጋር ይሆናል፤ አንተ በእግዚአብሔር ፊት ለሕዝቡ ሁን፥ ነገራቸውንም ወደ እግዚአብሔር አድርስ፤ 20.ሥርዓቱንም ሕጉንም አስተምራቸው፥ የሚሄዱበትን መንገድ የሚያደርጉትንም ሥራ ሁሉ አሳያቸው። 21.አንተም ከሕዝቡ ሁሉ አዋቂዎችን፥ እግዚአብሔርን የሚፈሩትን፥ የታመኑ፥ የግፍንም ረብ የሚጠሉትን ሰዎች ምረጥ፤ ከእነርሱም የሺህ አለቆችን፥ የመቶ አለቆችን፥ የአምሳ አለቆችን፥ የአሥርም አለቆችን ሹምላቸው። 22.በሕዝቡ ላይ ሁልጊዜ ይፍረዱ፤ አውራውን ነገር ሁሉ ወደ አንተ ያምጡት፥ ታናሹንም ነገር ሁሉ እነርሱ ይፍረዱ፤ እነርሱም ከአንተ ጋር ሸክሙን ይሸከማሉ፥ ለአንተም ይቀልልልሃል። 23.ይህንም ብታደርግ፥ እግዚአብሔር እንዲሁ ቢያዝዝህ፥ መቆም ይቻልሃል፥ ደግሞም ይህ ሕዝብ ሁሉ በሰላም ወደ ስፍራው ይደርሳል። 24.ሙሴም የአማቱን ቃል ሰማ፥ ያለውንም ሁሉ አደረገ። 25.ሙሴም ከእስራኤል ሁሉ አዋቂዎችን መረጠ፥ በሕዝቡም ላይ የሺህ አለቆች፥ የመቶም አለቆች፥ የአምሳም አለቆች፥ የአሥርም አለቆች አድርጎ ሾማቸው። 26.በሕዝቡም ላይ ሁልጊዜ ፈረዱ፤ የከበደባቸውንም ነገር ወደ ሙሴ አመጡ፥ ታናሹን ነገር ሁሉ ግን እነርሱ ፈረዱ። 27.ሙሴም አማቱን ሰደደው፤ እርሱም ወደ አገሩ ተመለሰ።

ወደ ኤፌሶን ሰዎች

ምዕራፍ 4

1.እንግዲህ በጌታ እስር የሆንሁ እኔ በተጠራችሁበት መጠራታችሁ እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እለምናችኋለሁ፤ 2.በትሕትና ሁሉና በየዋህነት በትዕግሥትም፤ እርስ በርሳችሁ በፍቅር ታገሡ፤ 3.በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ። 4.በመጠራታችሁ በአንድ ተስፋ እንደ ተጠራችሁ አንድ አካልና አንድ መንፈስ አለ፤ 5.አንድ ጌታ አንድ ሃይማኖት አንዲት ጥምቀት፤ 6.ከሁሉ በላይ የሚሆን በሁሉም የሚሠራ በሁሉም የሚኖር አንድ አምላክ የሁሉም አባት አለ። 7.ነገር ግን እንደ ክርስቶስ ስጦታ መጠን ለእያንዳንዳችን ጸጋ ተሰጠን። 8.ስለዚህ። ወደ ላይ በወጣ ጊዜ ምርኮን ማረከ ለሰዎችም ስጦታን ሰጠ ይላል። 9.ወደ ምድር ታችኛ ክፍል ደግሞ ወረደ ማለት ካልሆነ፥ ይህ ወጣ ማለትስ ምን ማለት ነው? 10.ይህ የወረደው ሁሉን ይሞላ ዘንድ ከሰማያት ሁሉ በላይ የወጣው ደግሞ ያው ነው። 11.እርሱም አንዳንዶቹ ሐዋርያት፥ ሌሎቹም ነቢያት፥ ሌሎቹም ወንጌልን ሰባኪዎች፥ ሌሎቹም እረኞችና አስተማሪዎች እንዲሆኑ ሰጠ፤
12 -
13.ሁላችን የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኝ አንድነት፥ ሙሉ ሰውም ወደ መሆን፥ የክርስቶስም ሙላቱ ወደሚሆን ወደ ሙላቱ ልክ እስክንደርስ ድረስ፥ ቅዱሳን አገልግሎትን ለመሥራትና ለክርስቶስ አካል ሕንጻ ፍጹማን ይሆኑ ዘንድ። 14.እንደ ስሕተት ሽንገላ ባለ ተንኮል በሰዎችም ማታለል ምክንያት በትምህርት ነፋስ ሁሉ እየተፍገመገምን ወዲያና ወዲህም እየተንሳፈፍን ሕፃናት መሆን ወደ ፊት አይገባንም፥ 15.ነገር ግን እውነትን በፍቅር እየያዝን በነገር ሁሉ ወደ እርሱ ራስ ወደሚሆን ወደ ክርስቶስ እንደግ፤ 16.ከእርሱም የተነሣ አካል ሁሉ እያንዳንዱ ክፍል በልክ እንደሚሠራ፥ በተሰጠለት በጅማት ሁሉ እየተጋጠመና እየተያያዘ፥ ራሱን በፍቅር ለማነጽ አካሉን ያሳድጋል። 17.እንግዲህ አሕዛብ ደግሞ በአእምሮአቸው ከንቱነት እንደሚመላለሱ ከእንግዲህ ወዲህ እንዳትመላለሱ እላለሁ በጌታም ሆኜ እመሰክራለሁ። 18.እነርሱ ባለማወቃቸው ጠንቅ በልባቸውም ደንዳንነት ጠንቅ ልቡናቸው ጨለመ፥ ከእግዚአብሔርም ሕይወት ራቁ፤ 19.ደንዝዘውም በመመኘት ርኵሰትን ሁሉ ለማድረግ ራሳቸውን ወደ ሴሰኝነት አሳልፈው ሰጡ። 20.እናንተ ግን ክርስቶስን እንደዚህ አልተማራችሁም፤ 21.በእርግጥ ሰምታችሁታልና፥ እውነትም በኢየሱስ እንዳለ በእርሱ ተምራችኋል፤ 22.ፊተኛ ኑሮአችሁን እያሰባችሁ እንደሚያታልል ምኞት የሚጠፋውን አሮጌውን ሰው አስወግዱ፥ 23.በአእምሮአችሁም መንፈስ ታደሱ፥ 24.ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ። 25.ስለዚህ ውሸትን አስወግዳችሁ፥ እርስ በርሳችን ብልቶች ሆነናልና እያንዳንዳችሁ ከባልንጀሮቻችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ። 26.ተቆጡ ኃጢአትንም አታድርጉ፤ 27.በቁጣችሁ ላይ ፀሐይ አይግባ፥ ለዲያብሎስም ፈንታ አትስጡት። 28.የሰረቀ ከእንግዲህ ወዲህ አይስረቅ፥ ነገር ግን በዚያ ፈንታ ለጎደለው የሚያካፍለው እንዲኖርለት በገዛ እጆቹ መልካምን እየሠራ ይድከም። 29.ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ፥ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ። 30.ለቤዛም ቀን የታተማችሁበትን ቅዱሱን የእግዚአብሔርን መንፈስ አታሳዝኑ። 31.መራርነትና ንዴት ቁጣም ጩኸትም መሳደብም ሁሉ ከክፋት ሁሉ ጋር ከእናንተ ዘንድ ይወገድ። 32.እርስ በርሳችሁም ቸሮችና ርኅሩኆች ሁኑ፥ እግዚአብሔርም ደግሞ በክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ ይቅር ተባባሉ።
♫
Listen to the reading 4 chapter tracks
ኦሪት ዘጸአት Chapter 16
ኦሪት ዘጸአት Chapter 17
ኦሪት ዘጸአት Chapter 18
ወደ ኤፌሶን ሰዎች Chapter 4
Swipe to browse chapters
Listen 4