Skip to Content
የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን | YEHIWOT MELHEK BETEKIRSTIAN
የ2019 ዓ.ም የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ 📖 ዛሬን አንብብ →

የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን

Yehiwot Melhek Betekirstian

ሳምንት 6 · ቀን 29 (ሐሙስ) 📅 Tikimt 12, 2019

ኦሪት ዘጸአት 25, 26, 27 · መዝሙረ ዳዊት 90 · ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 1

📖 የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም፦ 1954 መጽሐፍ ቅዱስ አዲሱ መደበኛ ትርጒም

ኦሪት ዘጸአት

ምዕራፍ 25

1.እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው። 2.ስጦታ ያመጡልኝ ዘንድ ለእስራኤል ልጆች ተናገር፤ በገዛ እጁ ሊሰጠኝ በልቡ ከሚያምረው ሰው ሁሉ መባ ተቀበሉ። 3.ከእነርሱም የምትቀበሉት መባ ይህ ነው፤ 4.ወርቅ፥ ብር፥ ናስም፥ ሰማያዊና ሐምራዊ ቀይም ግምጃ፥ ጥሩ በፍታም፥ 5.የፍየልም ጠጕር፥ ቀይ የአውራ በግ ቁርበት፥ የአቆስጣ ቁርበት፥ የግራርም እንጨት፥ 6.የመብራትም ዘይት፥ ለቅብዓት ዘይትና ለጣፋጭ ዕጣን ቅመም፥ 7.መረግድም፥ ለኤፉድና ለደረት ኪስ የሚደረግ ፈርጥ። 8.በመካከላቸውም አድር ዘንድ መቅደስ ይሥሩልኝ። 9.እኔ እንደማሳይህ ሁሉ፥ እንደ ማደሪያው ምሳሌ እንደ ዕቃውም ሁሉ ምሳሌ፥ እንዲሁ ሥሩት። 10.ከግራር እንጨትም ታቦትን ይሥሩ፤ ርዝመቱ ሁለት ክንድ ተኩል፥ ወርዱም አንድ ክንድ ተኩል፥ ቁመቱም አንድ ክንድ ተኩል ይሁን። 11.በውስጥና በውጭም በጥሩ ወርቅ ለብጠው፤ በእርሱም ላይ በዙሪያው የወርቅ አክሊል አድርግለት። 12.አራት የወርቅ ቀለበቶችም አድርግለት፥ እነርሱንም በአራቱ እግሮቹ ላይ አኑር፤ በአንድ ወገን ሁለት ቀለበቶች፥ በሌላው ወገን ሁለት ቀለበቶች ይሁኑ። 13.መሎጊያዎችንም ከግራር እንጨት ሥራ፥ በወርቅም ለብጣቸው። 14.ለታቦቱ መሸከሚያ በታቦቱ ጐን ባሉት ቀለበቶች መሎጊያዎቹን አግባ። 15.መሎጊያዎቹም በታቦቱ ቀለበቶች ውስጥ ይኑሩ፥ ከቶም አይውጡ። 16.በታቦቱም ውስጥ እኔ የምሰጥህን ምስክር ታስቀምጣለህ። 17.ከጥሩ ወርቅም ርዝመቱ ሁለት ክንድ ተኩል፥ ወርዱም አንድ ክንድ ተኩል የሆነ የስርየት መክደኛ ሥራ። 18.ሁለት ኪሩቤል ከተቀጠቀጠ ወርቅ ሥራ፥ በስርየት መክደኛውም ላይ በሁለት ወገን ታደርጋቸዋለህ። 19.ከስርየት መክደኛውም ጋር አንዱን ኪሩብ በአንድ ወገን፥ ሁለተኛውንም ኪሩብ በሌላው ወገን አድርገህ በአንድ ላይ ትሠራዋለህ። 20.ኪሩቤልም ክንፎቻቸውን ወደ ላይ ይዘረጋሉ፥ የስርየት መክደኛውንም በክንፎቻቸው ይሸፍናሉ፥ ፊታቸውም እርስ በርሱ ይተያያል፤ የኪሩቤልም ፊቶቻቸው ወደ ስርየት መክደኛው ይመለከታሉ። 21.የስርየት መክደኛውንም በታቦቱ ላይ ታደርገዋለህ፤ እኔም የምሰጥህን ምስክር በታቦቱ ውስጥ ታኖረዋለህ። 22.በዚያም ከአንተ ጋር እገናኛለሁ፤ የእስራኤልንም ልጆች ታዝዝ ዘንድ የምሰጥህን ነገር ሁሉ፥ በምስክሩ ታቦት ላይ ባለው በሁለት ኪሩቤል መካከል፥ በስርየት መክደኛውም ላይ ሆኜ እነጋገርሃለሁ። 23.ርዝመቱም ሁለት ክንድ፥ ወርዱም አንድ ክንድ፥ ቁመቱ አንድ ክንድ ተኩል የሆነ ገበታ ከግራር እንጨት ሥራ። 24.በጥሩም ወርቅ ትለብጠዋለህ፤ በዙሪያውም የወርቅ አክሊል አድርግለት፤ 25.በዙሪያውም አንድ ጋት የሚያህል ክፈፍ አድርግለት፤ የወርቅም አክሊል በክፈፉ ዙሪያ አድርግለት። 26.አራትም የወርቅ ቀለበቶች አድርግለት፤ ቀለበቶቹንም አራቱ እግሮቹ ባሉበት በአራቱ ማዕዘኖች አድርግ። 27.ገበታውንም ለመሸከም መሎጊያዎቹ እንዲሰኩባቸው ቀለበቶቹ በክፈፉ አቅራቢያ ይሁኑ። 28.ገበታውን ይሸከሙባቸው ዘንድ መሎጊያዎቹን ከግራር እንጨት ሠርተህ በወርቅ ለብጣቸው። 29.ለማፍሰሻም ይሆኑ ዘንድ ወጭቶችዋን ጭልፋዎችዋንም መቅጃዎችዋንም ጽዋዎችዋንም አድርግ፤ እነርሱንም ከጥሩ ወርቅ አድርጋቸው። 30.በገበታም ላይ የገጽ ኅብስት ሁልጊዜ በፊቴ ታደርጋለህ። 31.መቅረዝንም ከጥሩ ወርቅ አድርግ፤ መቅረዙ ከእግሩና ከአገዳው ጋር በተቀጠቀጠ ሥራ ይደረግ፤ ጽዋዎቹም ጕብጕቦቹም አበቦቹም አንድነት በእርሱ ይደረጉበት። 32.በስተጎኑ ስድስት ቅርንጫፎች ይውጡለት፤ ሦስት የመቅረዙ ቅርንጫፎች በአንድ ወገን፥ ሦስትም የመቅረዙ ቅርንጫፎች በሌላ ወገን ይውጡ። 33.በአንደኛውም ቅርንጫፍ ጕብጕብና አበባ ሦስትም የለውዝ አበባ የሚመስሉትን ጽዋዎች፥ በሁለተኛውም ቅርንጫፍ ጕብጕብና አበባ ሦስትም የለውዝ አበባ የሚመስሉትን ጽዋዎች፤ እንዲሁም ከመቅረዙ ለሚወጡ ለስድስቱ ቅርንጫፎች አድርግ። 34.በመቅረዙም ጕብጕቦቹንና አበቦቹን አራትም የለውዝ አበባ የሚመስሉትን ጽዋዎች አድርግ። 35.ከመቅረዙ ለሚወጡ ለስድስቱ ቅርንጫፎች ከሁለት ቅርንጫፎች በታች አንድ ሆኖ የተሠራ አንድ ጕብጕብ፥ ከሁለትም ቅርንጫፎች በታች አንድ ሆኖ የተሠራ አንድ ጕብጕብ፥ ደግሞ ከሁለት ቅርንጫፎች በታች አንድ ሆኖ የተሠራ አንድ ጕብጕብ ይሁን። 36.ጕብጕቦቹና ቅርንጫፎቹ ሁሉ ከእርሱ ጋር አንድ ይሁኑ፤ ሁሉም አንድ ሆኖ ከተቀረጸ ከጥሩ ወርቅ ይደረግ። 37.ሰባቱንም መብራቶች ሥራ፤ በፊቱ ያበሩ ዘንድ መብራቶቹን ያቀጣጥሉአቸዋል። 38.መኰስተሪያዎችዋን የኵስታሪ ማድረጊያዎችዋንም ከጥሩ ወርቅ አድርግ። 39.መቅረዙም ዕቃውም ሁሉ ከአንድ መክሊት ጥሩ ወርቅ ይሠሩ። 40.በተራራ ላይ እንዳሳየሁህ ምሳሌ እንድትሠራ ተጠንቀቅ።

ምዕራፍ 26

1.ደግሞም ከተፈተለ ከጥሩ በፍታ፥ ከሰማያዊ ከሐምራዊም ከቀይም ግምጃ የተሠሩ አሥር መጋረጆች ያሉበትን ማደሪያ ሥራ፤ ብልህ ሠራተኛ እንደሚሠራ ኪሩቤል በእነርሱ ላይ ይሁኑ። 2.የእያንዳንዱ መጋረጃ ርዝመት ሀያ ስምንት ክንድ፥ ወርዱም አራት ክንድ ይሁን፤ የመጋረጆቹ ሁሉ መጠን ትክክል ይሁን። 3.አምስቱ መጋረጆች እርስ በርሳቸው የተጋጠሙ ይሁኑ፤ አምስቱም መጋረጆች እንዲሁ እርስ በርሳቸው የተጋጠሙ ይሁኑ። 4.ከሚጋጠሙት መጋረጆች በአንደኛው መጋረጃ ዘርፍ ላይ የሰማያዊውን ግምጃ ቀለበቶች አድርግ፤ ደግሞ ከተጋጠሙት ከሌሎች በአንደኛው መጋረጃ ዘርፍ ላይ እንዲሁ አድርግ። 5.አምሳ ቀለበቶችን በአንድ መጋረጃ አድርግ፥ አምሳውንም ቀለበቶች በሁለተኛው መጋረጃ ዘርፍ አድርግ፤ ቀለበቶቹ ሁሉ እርስ በርሳቸው ፊት ለፊት ይሆናሉ። 6.አምሳ የወርቅ መያዣዎች ሥራ፤ ማደሪያውንም አንድ እንዲሆን መጋረጆችን እርስ በርሳቸው በመያዣዎች አጋጥማቸው። 7.ከማደሪያውም በላይ ለድንኳን የሚሆኑ መጋረጆች ከፍየል ጠጕር አድርግ፤ አሥራ አንድ መጋረጆች ታደርጋለህ። 8.እያንዳንዱም መጋረጃ ርዝመቱ ሠላሳ ክንድ፥ እያንዳንዱም መጋረጃ ወርዱ አራት ክንድ ይሁን፤ የአሥራ አንዱም መጋረጆች መጠናቸው ትክክል ይሁን። 9.አምስቱ መጋረጆች አንድ ሆነው ይጋጠሙ፥ ስድስቱም መጋረጆች እርስ በርሳቸው አንድ ሆነው ይጋጠሙ፤ ስድስተኛውም መጋረጃ በድንኳኑ ፊት ይደረብ። 10.ከተጋጠሙት መጋረጆች በአንደኛው መጋረጃ ዘርፍ ላይ አምሳ ቀለበቶች አድርግ፤ ደግሞ ከተጋጠሙት ከሌሎቹ በአንድኛው መጋረጃ ዘርፍ ላይ እንዲሁ አምሳ ቀለበቶች አድርግ። 11.አምሳም የናስ መያዣዎችን ሥራ፥ መያዣዎችንም ወደ ቀለበቶች አግባቸው፥ ድንኳኑም አንድ እንዲሆን አጋጥመው። 12.ከድንኳኑ መጋረጆች የቀረ ትርፍ ግማሽ መጋረጃ በማደሪያው ጀርባ ይንጠልጠል። 13.ማደሪያውን እንዲሸፍን ከርዝመቱ በአንድ ወገን አንድ ክንድ፥ በአንድ ወገንም አንድ ክንድ ከድንኳኑ መጋረጆች የቀረው ትርፍ በማደሪያው ውጭ በወዲህና በወዲያ ይንጠልጠል። 14.ለድንኳኑም መደረቢያ ከቀይ አውራ በግ ቁርበት፥ ከዚያም በላይ ሌላ መደረቢያ ከአቆስጣ ቁርበት አድርግ። 15.ለማደሪያውም የሚቆሙትን ሳንቆች ከግራር እንጨት አድርግ። 16.የሳንቃው ሁሉ ርዝመቱ አሥር ክንድ፥ ወርዱም አንድ ክንድ ተኩል ይሁን። 17.ለእያንዳንዱም ሳንቃ አንዱን በአንዱ ላይ የሚያያይዙ ሁለት ማጋጠሚያዎች ይሁኑለት፤ ለማደሪያው ሳንቆች ሁሉ እንዲሁ አድርግ። 18.ለማደሪያውም በደቡብ ወገን ሀያ ሳንቆችን አድርግ። 19.ከሀያውም ሳንቆች በታች አርባ የብር እግሮችን አድርግ፤ ከእያንዳንዱ ሳንቃ በታች ለሁለት ማጋጠሚያዎች ሁለት እግሮች ይሁኑ። 20.ለማደሪያው ለሁለተኛው ወገን በሰሜን በኩል ሀያ ሳንቆች፥ 21.ለእነርሱም አርባ የብር እግሮች ይሁኑ፤ ከእያንዳንዱም ሳንቃ በታች ሁለት እግሮች ይሁኑ። 22.ለማደሪያውም በምዕራቡ ወገን በስተ ኋላ ስድስት ሳንቆችን አድርግ። 23.ለማደሪያውም ለሁለቱ ማዕዘን በስተ ኋላ ሁለት ሳንቆችን አድርግ። 24.ከታችም እስከ ላይ እስከ አንደኛው ቀለበት ድረስ አንዱ ሳንቃ ድርብ ይሁን፤ እንዲሁም ለሁለቱ ይሁን፤ እነርሱም ለሁለቱ ማዕዘን ይሆናሉ። 25.ስምንት ሳንቆችና አሥራ ስድስት የብር እግሮቻቸው ይሁኑ፤ ከእያንዳንዱም ሳንቃ በታች ሁለት እግሮች ይሆናሉ። 26.ከግራርም እንጨት በማደሪያው በአንድ ወገን ላሉት ሳንቆች አምስት መወርወሪያዎች፥ 27.በማደሪያውም በሁለተኛው ወገን ላሉት ሳንቆች አምስት መወርወሪያዎች፥ በማደሪያውም በስተ ኋላ በምዕራብ ወገን ላሉት ሳንቆች አምስት መወርወሪያዎች አድርግ። 28.መካከለኛውም መወርወሪያ በሳንቆች መካከል ከዳር እስከ ዳር ይለፍ። 29.ሳንቆቹንም በወርቅ ለብጣቸው፤ ቀለበቶቻቸውንም የመወርወሪያ ቤት እንዲሆኑላቸው ከወርቅ ሥራቸው፤ መወርወሪያዎችንም በወርቅ ለብጣቸው። 30.ማደሪያውንም በተራራ እንዳሳየሁህ ምሳሌ አቁም። 31.መጋረጃውንም ከሰማያዊ ከሐምራዊም ከቀይም ግምጃ ከተፈተለ ከጥሩ በፍታም አድርግ፤ ብልህ ሠራተኛ እንደሚሠራ ኪሩቤል በእርሱ ላይ ይሁኑ። 32.በወርቅ በተለበጡት ከግራር እንጨትም በተሠሩት በአራቱ ምሰሶች ላይ ስቀለው፤ ኩላቦቻቸውም ከወርቅ፥ አራቱም እግሮቻቸው ከብር የተሠሩ ይሁኑ። 33.መጋረጃውንም ከመያዣዎቹ በታች ታንጠለጥለዋለህ፥ በመጋረጃውም ውስጥ የምስክርን ታቦት አግባው፤ መጋረጃውም በቅድስቱና በቅድስተ ቅዱሳኑ መካከል መለያ ይሁናችሁ። 34.በቅድስተ ቅዱሳኑም ውስጥ የስርየት መክደኛውን በምስክሩ ታቦት ላይ አድርግ። 35.ገበታውንም በመጋረጃው ውጭ፥ መቅረዙንም በገበታው ፊት ለፊት በማደሪያው በደቡብ ወገን አድርግ፤ ገበታውንም በሰሜን ወገን አድርገው። 36.ለድንኳኑም ደጃፍ ከሰማያዊ ከሐምራዊም ከቀይም ግምጃ ከተፈተለ ከጥሩ በፍታም በጥልፍ አሠራር የተሠራ መጋረጃ አድርግለት። 37.ለመጋረጃውም አምስት ምሰሶች ከግራር እንጨት አድርግ፥ በወርቅም ለብጣቸው፤ ኩላቦቻቸውም ከወርቅ የተሠሩ ይሁኑ፤ አምስትም እግሮች አድርግላቸው።

ምዕራፍ 27

1.ርዝመቱ አምስት ክንድ፥ ወርዱም አምስት ክንድ መሠዊያ ከግራር እንጨት አድርግ፤ አራት ማዕዘንም ይሁን፤ ከፍታውም ሦስት ክንድ ይሁን። 2.በአራቱም ማዕዘን ቀንዶችን ታደርጋለህ፥ ቀንዶቹም ከእርሱ ጋር በአንድ የተሠሩ ይሁኑ፤ በናስም ለብጠው። 3.አመድ የሚሆንባቸውን ምንቸቶች፥ መጫሪያዎቹንም፥ ድስቶቹንም፥ ሜንጦቹንም፥ ማንደጃዎቹንም አድርግ፤ ዕቃውንም ሁሉ ከናስ አድርግ። 4.እንደ መረብ ሆኖ የተሠራ የናስ መከታ አድርግለት፤ ለመከታውም አራት የናስ ቀለበት በአራት ማዕዘኑ አድርግለት። 5.መከታውም እስከ መሠዊያው እኵሌታ ይደርስ ዘንድ በመሰዊያው በሚዞረው በእርከኑ ታች አድርገው። 6.ለመሠዊያውም ከግራር እንጨት መሎጊያዎችን ሠርተህ በናስ ለብጣቸው። 7.መሎጊያዎቹም በቀለበቶች ውስጥ ይግቡ፤ መሠዊያውንም ስትሸከሙ መሎጊያዎቹ በሁለቱ ወገኖች ይሁኑ። 8.ከሳንቆች ሠርተህ ባዶ አድርገው፤ በተራራው እንዳሳየሁህ ምሳሌ እንዲሁ ያድርጉት። 9.የማደሪያውንም አደባባይ ሥራ፤ በደቡብ ወገን የጥሩ በፍታ መጋረጆች ይሁኑለት፥ የአንዱም ወገን ርዝመት መቶ ክንድ ይሁን፤ 10.ከናስ የተሠሩ ሀያ ምሰሶችና ሀያ እግሮች ይሁኑለት፤ የምሰሶቹም ኩላቦችና ዘንጎች የብር ይሁኑ። 11.እንዲሁም በሰሜን ወገን መቶ ክንድ ርዝመት ያላቸው መጋረጆች፥ ከናስ የተሠሩ ሀያ ምሶሶች ሀያም እግሮች ይሁኑ፤ ለምሰሶችም የብር ኩላቦችና ዘንጎች ይሁኑ። 12.በምዕራብም ወገን ለአደባባዩ ስፋት አምሳ ክንድ ርዝመት ያላቸው መጋረጆች፥ አሥርም ምሰሶች፥ አሥርም እግሮች ይሁኑለት። 13.በምሥራቅም ወገን የአደባባዩ ስፋት አምሳ ክንድ ይሁን። 14.በአንድ ወገን የመጋረጆቹ ርዝመት አሥራ አምስት ክንድ ይሁን፤ ምሰሶቹም ሦስት፥ እግሮቹም ሦስት ይሁኑ። 15.በሌላውም ወገን የመጋረጆች ርዝመት አሥራ አምስት ክንድ ይሆናል፤ ምሰሶቹም ሦስት፥ እግሮቹም ሦስት ይሁኑ። 16.ለአደባባዩም ደጅ ከሰማያዊ ከሐምራዊም ከቀይም ግምጃ ከጥሩ በፍታም በጥልፍ አሠራር የተሠራ ሀያ ክንድ መጋረጃ ይሆናል፤ ምሰሶቹም አራት፥ እግሮቹም አራት ይሁኑ። 17.በአደባባዩም ዙሪያ ላሉት ምሰሶች ሁሉ የብር ዘንጎች፥ የብርም ኩላቦች፥ የናስም እግሮች ይሁኑላቸው። 18.የአደባባዩ ርዝመት መቶ ክንድ ስፋቱም አምሳ ክንድ ይሁን፥ የመጋረጃውም ከፍታ አምስት ክንድ ይሁን፤ መጋረጃውም ከጥሩ በፍታ፥ እግሮቹም ከናስ የተሠሩ ይሁኑ። 19.ለማገልገል ሁሉ የማደሪያው ዕቃ ሁሉ፥ ካስማዎቹም ሁሉ የአደባባዩም ካስማዎች ሁሉ፥ የናስ ይሁኑ። 20.አንተም መብራቱን ሁልጊዜ ያበሩት ዘንድ ለመብራት ተወቅጦ የተጠለለ ጥሩ የወይራ ዘይት እንዲያመጡልህ የእስራኤልን ልጆች እዘዛቸው። 21.በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በምስክሩ ታቦት ፊት ባለው መጋረጃ ውጭ አሮንና ልጆቹ ከማታ እስከ ማለዳ ድረስ በእግዚአብሔር ፊት እንዲበራ ያሰናዱት፤ በእስራኤል ልጆች ዘንድ ለልጅ ልጃቸው የዘላለም ሥርዓት ይሁን።

መዝሙረ ዳዊት

ምዕራፍ 90

1.የእግዚአብሔር ሰው የሙሴ ጸሎት።
አቤቱ፥ አንተ ለትውልድ ሁሉ መጠጊያ ሆንህልን።
2.ተራሮች ሳይወለዱ፥ ምድርም ዓለምም ሳይሠሩ፥ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ አንተ ነህ። 3.ሰውን ወደ ኅሳር አትመልስም፤ የሰው ልጆች ሆይ፥ ተመለሱ ትላለህ፤ 4.ሺህ ዓመት በፊትህ እንዳለፈች እንደ ትናንት ቀን፥ እንደ ሌሊትም ትጋት ነውና። 5.ዘመኖች የተናቁ ይሆናሉ፥ በማለዳም እንደ ሣር ያልፋል። 6.ማልዶ ያብባል ያልፋልም፥ በሠርክም ጠውልጎና ደርቆ ይወድቃል። 7.እኛ በቍጣህ አልቀናልና፥ በመዓትህም ደንግጠናልና። 8.የተሰወረውን ኃጢአታችንን በፊትህ ብርሃን፥ በደላችንንም በፊትህ አስቀመጥህ። 9.ዘመናችን ሁሉ አልፎአልና፥ እኛም በመዓትህ አልቀናልና፤ ዘመኖቻችንም እንደ ሸረሪት ድር ይሆናሉ። 10.የዘመኖቻችንም ዕድሜ ሰባ ዓመት፥ ቢበረታም ሰማንያ ዓመት ነው፤ ቢበዛ ግን ድካምና መከራ ነው፤ ከእኛ ቶሎ ያልፋልና፥ እኛም እንገሠጻለንና። 11.የቍጣህን ጽናት ማን ያውቃል? ከቍጣህ ግርማ የተነሣ አለቁ። 12.በልብ ጥበብን እንድንማር፥ ቀኝህን እንዲህ አስታውቀን። 13.አቤቱ፥ ተመለስ፥ እስከ መቼስ ነው? ስለ ባሪያዎችህም ተምዋገት። 14.በማለዳ ምሕረትህን እንጠግባለን፤ በዘመናችን ሁሉ ደስ ይለናል ሐሤትም እናደርጋለን። 15.መከራ ባሳየኸን ዘመን ፈንታ፥ ክፉም ባየንባቸው ዘመኖች ፋንታ ደስ ይለናል። 16.ባሪያዎችህንና ሥራህን እይ፥ ልጆቻቸውንም ምራ። 17.የአምላካችን የእግዚአብሔር ብርሃን በላያችን ይሁን። የእጆቻችንንም ሥራ በላያችን አቅና።

ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች

ምዕራፍ 1

1.የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያዎች የሆኑ ጳውሎስና ጢሞቴዎስ በፊልጵስዩስ ለሚኖሩ ከኤጲስ ቆጶሳትና ከዲያቆናት ጋር በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት ቅዱሳን ሁሉ፤ 2.ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።
3 -
4
5.ሁልጊዜ በጸሎቴ ሁሉ ስለ እናንተ ሁሉ በደስታ እየጸለይሁ፥ ከፊተኛው ቀን እስከ ዛሬ ድረስ ወንጌልን በመስበክ አብራችሁ ስለ ሠራችሁ፥ ባሰብኋችሁ ጊዜ ሁሉ አምላኬን አመሰግናለሁ። 6.በእናንተ መልካምን ሥራ የጀመረው እስከ ኢየሱስ ክርስቶስ ቀን ድረስ እንዲፈጽመው ይህን ተረድቼአለሁና፤ 7.በእስራቴም ወንጌልንም መመከቻና መጽኛ በማድረግ ሁላችሁ ከእኔ ጋር በጸጋ ተካፋዮች ስለ ሆናችሁ፥ በልቤ ትኖራላችሁና ስለ ሁላችሁ ይህን ላስብ ይገባኛል። 8.በክርስቶስ ኢየሱስ ፍቅር ሁላችሁን እንዴት እንድናፍቃችሁ እግዚአብሔር ምስክሬ ነውና።
9 -
10
11.ለእግዚአብሔርም ክብርና ምስጋና ከኢየሱስ ክርስቶስ የሚገኝ የጽድቅ ፍሬ ሞልቶባችሁ፥ ለክርስቶስ ቀን ተዘጋጅታችሁ ቅኖችና አለ ነውር እንድትሆኑ የሚሻለውን ነገር ፈትናችሁ ትወዱ ዘንድ፥ ፍቅራችሁ በእውቀትና በማስተዋል ሁሉ ከፊት ይልቅ እያደገ እንዲበዛ ይህን እጸልያለሁ። 12.ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ይህ የደረሰብኝ በእውነት ወንጌልን ለማስፋት እንደ ሆነ ታውቁ ዘንድ እወዳለሁ። 13.ስለዚህም እስራቴ ስለ ክርስቶስ እንዲሆን በንጉሥ ዘበኞች ሁሉና በሌሎች ሁሉ ዘንድ ተገልጦአል፥ 14.በጌታም ካሉት ወንድሞች የሚበዙት ስለ እስራቴ ታምነው የእግዚአብሔርን ቃል እንዲነግሩ ያለ ፍርሃት ከፊት ይልቅ ይደፍራሉ። 15.አንዳንዶች ከቅንአትና ከክርክር እንኳ ሌሎች ግን ከበጎ ፈቃድ የተነሣ ክርስቶስን ይሰብኩታል፤ 16.እነዚህ ወንጌልን መመከቻ ለማድረግ እንደ ተሾምሁ አውቀው በፍቅር ይሰብካሉ፥ 17.እነዚያ ግን በእስራቴ ላይ መከራን ሊያመጡብኝ መስሎአቸው፥ ለወገናቸው የሚጠቅም ፈልገው በቅን አሳብ ሳይሆኑ ስለ ክርስቶስ ያወራሉ። 18.ምን አለ? ቢሆንም በሁሉ ጎዳና፥ በማመካኘት ቢሆን ወይም በቅንነት ቢሆን፥ ክርስቶስ ይሰበካል ስለዚህም ደስ ብሎኛል። 19.ወደ ፊትም ደግሞ ደስ ይለኛል፤ ይህ በጸሎታችሁና በኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ መሰጠት ለመዳኔ እንዲሆንልኝ አውቃለሁና፥ 20.ይህ ናፍቆቴ ተስፋዬም ነውና፤ በአንድ ነገር እንኳ አላፍርም ነገር ግን በህይወት ብኖር ወይም ብሞት፥ ክርስቶስ በግልጥነት ሁሉ እንደ ወትሮው አሁን ደግሞ በስጋዬ ይከብራል። 21.ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ፥ ሞትም ጥቅም ነውና። 22.ነገር ግን በስጋ መኖር ለእኔ የሥራ ፍሬ ቢሆን፥ ምን እንድመርጥ ኣላስታውቅም። 23.በእነዚህም በሁለቱ እጨነቃለሁ፤ ልሄድ ከክርስቶስም ጋር ልኖር እናፍቃለሁ፥ ከሁሉ ይልቅ እጅግ የሚሻል ነውና፤ 24.ነገር ግን በሥጋ መኖሬ ስለ እናንተ እጅግ የሚያስፈልግ ነው።
25 -
26.ይህንንም ተረድቼ፥ በእናንተ ዘንድ እንደ ገና ስለ መሆኔ፥ በእኔ መመካታችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ ይበዛ ዘንድ፥ በእምነት ታድጉና ደስ ይላችሁ ዘንድ እንድኖር ከሁላችሁም ጋር እንድቈይ አውቃለሁ። 27.ይሁን እንጂ፥ መጥቼ ባያችሁ ወይም ብርቅ፥ በአንድ ልብ ስለ ወንጌል ሃይማኖት አብራችሁ እየተጋደላችሁ፥ በአንድ መንፈስ እንድትቆሙ ስለ ኑሮአችሁ እሰማ ዘንድ፥ ለክርስቶስ ወንጌል እንደሚገባ ኑሩ። 28.በአንድም ነገር እንኳ በተቃዋሚዎች አትደንግጡ፤ ይህም ለእነርሱ የጥፋት፥ ለእናንተ ግን የመዳን ምልክት ነው፥ ይህም ከእግዚአብሔር ነው፤ 29.ይህ ስለ ክርስቶስ ተሰጥቶአችኋልና፤ ስለ እርሱ መከራ ደግሞ ልትቀበሉ እንጂ በእርሱ ልታምኑ ብቻ አይደለም፤ 30.በእኔ ያያችሁት አሁንም በእኔ እንዳለ የምትሰሙት፥ ያው መጋደል ደርሶባችኋልና።
♫
Listen to the reading 5 chapter tracks
ኦሪት ዘጸአት Chapter 25
ኦሪት ዘጸአት Chapter 26
ኦሪት ዘጸአት Chapter 27
መዝሙረ ዳዊት Chapter 90
ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች Chapter 1
Swipe to browse chapters
Listen 5