Skip to Content
የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን | YEHIWOT MELHEK BETEKIRSTIAN
የ2019 ዓ.ም የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ 📖 ዛሬን አንብብ →

የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን

Yehiwot Melhek Betekirstian

ሳምንት 6 · ቀን 28 (ረቡዕ) 📅 Tikimt 11, 2019

ኦሪት ዘጸአት 22, 23, 24 · መዝሙረ ዳዊት 109 · ወደ ኤፌሶን ሰዎች 6

📖 የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም፦ 1954 መጽሐፍ ቅዱስ አዲሱ መደበኛ ትርጒም

ኦሪት ዘጸአት

ምዕራፍ 22

ንብረትን ስለ መጠበቅ

1.“አንድ ሰው በሬ ወይም በግ ሰርቆ ቢያርድ ወይም ቢሸጥ በአንድ በሬ ምትክ ዐምስት በሬዎች፤ በአንድ በግ ምትክ አራት በጎች ይክፈል። 2.“አንድ ሌባ በር ሲሰብር ተይዞ ቢደበደብና ቢሞት፣ ተከላካዩ የደም ባለዕዳ አይሆንም፤ 3.ነገር ግን ፀሓይ ከወጣች በኋላ ከተፈጸመ፣ ሰውየው በነፍስ ግድያ ይጠየቃል።
“ሌባ የሰረቀውን መክፈል አለበት፤ ምንም ከሌለው ግን የሰረቀውን ይከፍል ዘንድ ይሸጥ።
4.የሰረቀው እንስሳ በሬ ወይም አህያ ወይም በግ ከነሕይወቱ በእጁ ከተያዘ ዕጥፍ መክፈል አለበት። 5.“አንድ ሰው ከብቶቹን በመስክ ወይም በወይን ቦታ አሰማርቶ እንዲሁ ስድ ቢለቅቃቸውና የሌላውን ሰው መስክ ቢግጡ፣ ምርጥ ከሆነው ከራሱ መስክ ወይም የወይን ቦታ መክፈል አለበት። 6.“እሳት ተነሥቶ ወደ ቍጥቋጦ ቢዘምትና ክምርን ወይም ያልታጨደን እህል ወይም አዝመራውን እንዳለ ቢበላ፣ እሳቱን ያቀጣጠለው ሰው ካሳ ይክፈል። 7.“አንድ ሰው ብሩ ወይም ንብረቱ ያለ ሥጋት ይጠበቅለት ዘንድ ለጎረቤቱ ሰጥቶ ሳለ ቢሰርቅበትና፣ ሌባው ቢያዝ ዕጥፍ ይክፈል፤ 8.ሌባው ካልተያዘ ግን፣ የቤቱ ባለቤት በንብረቱ ስርቆት ላይ እጁ ይኑርበት ወይም አይኑርበት ይታወቅ ዘንድ ዳኞች ፊት ይቅረብ። 9.አንድ ሰው በሬን፣ አህያን፣ በግን፣ ልብስን ወይም ማንኛውንም ንብረት ያለ አግባብ በባለቤትነት ይዞ ሳለ፣ ‘የእኔ ነው’ ባይ ቢመጣና ክርክር ቢነሣ፣ ባለጕዳዮቹ ነገሩን ለዳኞች ያቅርቡት፤ ዳኞቹ ጥፋተኛ ነው ያሉትም ለጎረቤቱ ዕጥፉን ይክፈል። 10.“አንድ ሰው አህያ፣ በሬ፣ በግ ወይም ማንኛውንም እንስሳ በጎረቤቱ ዘንድ በዐደራ አስቀምጦ ሳለ እንስሳው ቢሞት ወይም ጕዳት ቢደርስበት ወይም ሰው ሳያይ ተነድቶ ቢወሰድ፣ 11.በሁለቱ መካከል ያለው አለመግባባት መፍትሒ የሚያገኘው፣ ጎረቤቱ የሌላውን ሰው ንብረት እንዳልወሰደ በእግዚአብሔር ፊት በመማል ነው። ባለቤቱም ይህን መቀበል አለበት፤ የካሳም ክፍያ አይጠየቅም። 12.እንስሳው ከጎረቤት ተሰርቆ ከሆነ ግን፣ ለባለቤቱ ካሳ መክፈል አለበት። 13.በዱር አራዊት ተበልቶ ከሆነ፣ ከአውሬ የተረፈውን ማስረጃ አድርጎ በማቅረብ፣ ስለ ተበላው እንስሳ ካሳ እንዲከፍል አይጠየቅም። 14.“አንድ ሰው ከጎረቤቱ እንስሳ ተውሶ ሳለ፣ ባለቤቱ በሌለበት ቢጐዳ ወይም ቢሞት ካሳ መክፈል አለበት። 15.ባለቤቱ ከእንስሳው ጋራ ከሆነ ግን፣ ተበዳሪው መክፈል የለበትም፤ እንስሳው ከተከራየም ለኪራይ የተከፈለው ገንዘብ ኪሳራውን ይሸፍናል።

ማኅበራዊ ኀላፊነት

16.“አንድ ሰው ያልታጨችን ልጃገረድ አታልሎ ክብረ ንጽሕናዋን ቢያጐድል፣ የማጫዋን ዋጋ ከፍሎ ሚስት ያድርጋት። 17.እርሷን ለርሱ የልጅቷ አባት በሚስትነት ለመስጠት ከቶ የማይፈቅድ ቢሆን፣ ለድንግሎች መከፈል የሚገባውን ማጫ አሁንም ቢሆን መክፈል ይገባዋል። 18.“መተተኛ ሴት በሕይወት እንድትኖር አትፍቀድ። 19.“ከእንስሳ ጋራ ሩካቤ ሥጋ የሚፈጽም ሰው ይገደል። 20.“ለእግዚአብሔር በቀር ለሌላ አማልክት የሚሠዋ ይጥፋ። 21.“መጻተኛውን አትበድሉት ወይም አታስጨንቁት፤ እናንተ በግብጽ መጻተኛ ነበራችሁና። 22.“ባል በሞተባት ወይም አባትና እናት በሌለው ልጅ ላይ ግፍ አትዋሉ። 23.ግፍ ብትውሉባቸውና ወደ እኔ ቢጮኹ፣ ጩኸታቸውን በርግጥ እሰማለሁ። 24.ቍጣዬ ይነሣል፤ በሰይፍም እገድላችኋለሁ፤ ሚስቶቻችሁ መበለቶች፣ ልጆቻችሁም አባት የለሽ ይሆናሉ። 25.“ከሕዝቤ መካከል ችግረኛ ለሆነው ለአንዱ ገንዘብ ብታበድሩ፣ እንደ ዐራጣ አበዳሪ አትሁኑ፤ ወለድ አትጠይቁት። 26.የጎረቤትህን ልብስ መያዣ አድርገህ ብትይዝ ሲመሽ መልስለት፤ 27.ምክንያቱም ለሰውነቱ መሸፈኛ ያለው ልብስ ያ ብቻ ነው፤ ሌላ ምን ለብሶ ይተኛል? ወደ እኔ ሲጮኽ እኔ እሰማለሁ፤ እኔ ርኅሩኅ ነኝና። 28.“በእግዚአብሔር ላይ የስድብ ቃል አታሰማ፤ ወይም የሕዝብህን መሪ አትርገም። 29.“የእህልህን ወይም የወይን ጠጅህን በኵራት ለእኔ ከማቅረብ ወደ ኋላ አትበል።
“የወንድ ልጆችህን በኵር ለእኔ ስጠኝ።
30.ከቀንድ ከብትህና ከበጎችህም እንዲሁ አድርግ፤ ለሰባት ቀን ከእናቶቻቸው ጋራ ይቈዩ፤ በስምንተኛው ቀን ግን ለእኔ ሰጠኝ። 31.“እናንተ ለእኔ ቅዱስ ሕዝብ ትሆናላችሁ፤ ስለዚህ አውሬ የዘነጠለውን የእንስሳ ሥጋ አትብሉ፤ ለውሾች ስጡት።

ምዕራፍ 23

የፍትሕና የምሕረት ሕጎች

1.“የሐሰት ወሬ አትንዛ፤ ተንኰል ያለበትን ምስክርነት በመስጠት ክፉውን ሰው አታግዝ። 2.“ክፉ በማድረግ ብዙዎችን አትከተል፤ በሕግ ፊት ምስክርነት ስትሰጥ፣ ከብዙዎቹ ጋራ ተባብረህ ፍትሕ አታጣምም። 3.በዳኝነት ጊዜ ለድኻው አታድላ። 4.“የጠላትህ በሬ ወይም አህያ ሲባዝን ብታገኘው ወደ እርሱ መልሰው። 5.የሚጠላህ ሰው አህያ፣ ጭነት ከብዶት ወድቆ ብታየው ርዳው እንጂ ትተኸው አትሂድ። 6.“በዳኝነት ጊዜ በድኻው ላይ ፍርድ አታጓድልበት። 7.ከሐሰት ክስ ራቅ፤ በደል የሌለበትን ወይም ጻድቁን ሰው ለሞት አሳልፈህ አትስጥ፣ በደለኛውን ንጹሕ አላደርግምና። 8.“ጕቦ አትቀበል፤ ጕቦ አጥርተው የሚያዩትን ሰዎች ዐይን ያሳውራል፤ የጻድቃንንም ቃል ያጣምማልና። 9.“መጻተኛውን አትጨቍን፤ በግብጽ መጻተኛ ስለ ነበራችሁ፣ መጻተኛ ምን እንደሚሰማው እናንተ ራሳችሁ ታውቃላችሁና።

የሰንበት ሕጎች

10.“ስድስት ዓመት በዕርሻህ ላይ ዝራ፤ አዝመራንም ሰብስብ፤ 11.ነገር ግን በሰባተኛው ዓመት ምድሪቱን ሳትጠቀምባትና ሳታርሳት እንዲሁ ተዋት፤ ከዚያም በወገንህ መካከል ያሉት ድኾች ከርሷ ምግብ ያገኛሉ፤ የዱር አራዊትም ከእነርሱ የተረፈውን ይበላሉ። በወይን ቦታህና በወይራ ዛፎችህም ላይ እንዲሁ አድርግ። 12.“ስድስት ቀን ሥራህን ሥራ፤ በሬህና አህያህ በቤትህ የተወለደው ባሪያና መጻተኛው ያርፉ ዘንድ በሰባተኛው ቀን ምንም አትሥራ። 13.“ያልኋችሁን ሁሉ ታደርጉ ዘንድ ተጠንቀቁ፤ የሌሎችን አማልክት ስም አትጥሩ፤ ከአፋችሁም አይስሙ።

ሦስቱ ዐውደ ዓመታዊ በዓላት

14.“በዓመት ሦስት ጊዜ ለእኔ በዓልን ታከብራላችሁ። 15.“የቂጣ በዓልን አክብር፤ እንዳዘዝሁህ ሰባት ቀን እርሾ የሌለውን ቂጣ ብላ፤ ይህንም በአቢብ ወር በተወሰነ ቀን አድርግ፤ በዚያ ወር ከግብጽ ወጥተሃልና።
“ማንም በፊቴ ባዶ እጁን አይቅረብ።
16.“በማሳህ ላይ በዘራኸው እህል በኵራት የመከርን በዓል አክብር።
“በዓመቱ መጨረሻ በማሳህ ላይ ያለውን እህልህን ስትሰበስብ የመክተቻውን በዓል አክብር።
17.“በዓመት ሦስት ጊዜ ወንድ ሁሉ በጌታ በእግዚአብሔር ፊት ይቅረብ። 18.“የመሥዋዕትን ደም እርሾ ካለበት ነገር ጋራ አድርገህ ለእኔ አታቅርብ።
“የበዓል መሥዋዕቴ ስብ እስከ ንጋት ድረስ አይቈይ።
19.“የምድርህን ምርጥ ፍሬ በኵራት ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ቤት አምጣ።
“ጠቦት ፍየልን በእናቱ ወተት አትቀቅል።

የእግዚአብሔር መልአክ መንገድ ስለ መምራቱ

20.“እነሆ፤ በጕዞ ላይ ሳለህ የሚጠብቅህንና ወዳዘጋጀሁልህ ስፍራ የሚያስገባህን መልአክ በፊትህ ልኬልሃለሁ። 21.በጥንቃቄ ተከተለው፤ የሚናገረውንም ልብ ብለህ ስማው፤ አታምፅበት። ስሜ በርሱ ላይ ነውና ዐመፅህን ይቅር አይልም። 22.የሚናገረውን በጥንቃቄ ብታደምጥና ያልኩህን ሁሉ ብታደርግ ለጠላቶችህ ጠላት እሆናለሁ፤ የሚቃወሙህን እቃወማለሁ። 23.መልአኬ በፊትህ ይሄዳል፤ አንተንም ወደ አሞራውያን፣ ወደ ኬጢያውያን፣ ወደ ፌርዛውያን፣ ወደ ከነዓናውያን፣ ወደ ኤዊያውያንና ኢያቡሳውያን ምድር ያስገባሃል፤ እኔም እነርሱን አጠፋቸዋለሁ። 24.ለአማልክታቸው አትስገድ፤ ወይም አታምልካቸው፤ ወይም ልምዳቸውን አትከተል፤ እነርሱን ማፈራረስ አለብህ፤ የአምልኮ ድንጋዮቻቸውንም ሰባብር። 25.አምላክህን እግዚአብሔርን አምልክ፤ በረከቱም በምትበላውና በምትጠጣው ላይ ይሆናል፤ በሽታንም ከአንተ ዘንድ አርቃለሁ። 26.በምድርህም የሚያስወርዳት ወይም መካን ሴት አትኖርም፤ ረዥም ዕድሜም እሰጥሃለሁ። 27.“በሚያጋጥሙህ አሕዛብ ሁሉ ላይ ማስፈራቴን በፊትህ እልካለሁ፤ ግራም አጋባቸዋለሁ፤ ጠላቶችህ ሁሉ ወደ ኋላ ተመልሰው እንዲሸሹ አደርጋለሁ። 28.ኤዊያውያንን፣ ከነዓናውያንን፣ ኬጢያውያንን ከመንገድህ ለማስወጣት ተርብን በፊትህ እሰድዳለሁ። 29.ነገር ግን በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ አላወጣቸውም፤ ምክንያቱም ምድሪቱ ባድማ ሆና የዱር አራዊት ይበዙባችኋል። 30.ቍጥርህ ጨምሮ ምድሪቱን ለመውረስ እስክትበቃ ድረስ ጥቂት በጥቂት ከፊታችሁ አባርራቸዋለሁ። 31.“ድንበርህን ከቀይ ባሕር እስከ ፍልስጥኤም ባሕር፣ ከምድረ በዳው እስከ ወንዙ ድረስ አደርገዋለሁ፤ በምድሪቱም ላይ የሚኖሩትን ሰዎች አሳልፌ እሰጥሃለሁ፤ አንተም አሳድደህ ከፊትህ ታስወጣቸዋለህ። 32.ከእነርሱም ሆነ ከአማልክታቸው ጋራ ኪዳን አታድርግ። 33.በምድርህ ላይ እንዲኖሩ አትፍቀድላቸው፤ አለዚያ እኔን እንድትበድል ያደርጉሃል፤ አማልክታቸውን ማምለክ በርግጥ ወጥመድ ይሆንብሃልና።”

ምዕራፍ 24

ቃል ኪዳኑ ስለ መጽናቱ

1.ከዚያም ሙሴን “አንተና አሮን፣ ናዳብና አብዩድ ከሰባዎቹ የእስራኤል አለቆች ጋራ ወደ እግዚአብሔር ኑ፤ ከሩቅም ስገዱ አለው፤ 2.ነገር ግን ወደ እግዚአብሔር ሊቀርብ የሚችለው ሙሴ ብቻ ነው። ሌሎቹ መቅረብ የለባቸውም፤ ሕዝቡም ከርሱ ጋራ መምጣት የለበትም።” 3.ሙሴ ወደ ሕዝቡ ሄዶ የእግዚአብሔርን ቃሎችና ሕጎች ሁሉ በነገራቸው ጊዜ በአንድ ድምፅ ሆነው፣ “እግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እናደርጋለን” አሉ። 4.ከዚያም ሙሴ እግዚአብሔር ያለውን ሁሉ ጻፈ።
በማግስቱም ማልዶ ተነሥቶ፣ በተራራው ግርጌ መሠዊያን ሠራ፤ ዐሥራ ሁለቱን የእስራኤልን ነገዶች የሚወክሉ ዐሥራ ሁለት የድንጋይ ዐምዶችን አቆመ።
5.ከዚያም ወጣት ወንድ እስራኤላውያንን ላከ፤ እነርሱም የሚቃጠል መሥዋዕት አቀረቡ፤ ወይፈኖችን የኅብረት መሥዋዕት አድርገው ለእግዚአብሔር ሠዉ። 6.ሙሴ የደሙን እኩሌታ ወስዶ በጐድጓዳ ሳሕኖች አኖረው፤ የቀረውንም እኩሌታ በመሠዊያው ላይ ረጨው። 7.ከዚያም የኪዳኑን መጽሐፍ ወስዶ ለሕዝቡ አነበበላቸው፤ እነርሱም፣ “እግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እናደርጋለን፤ እንታዘዛለን” አሉ። 8.ከዚያም ሙሴ ደሙን ወሰደ፤ ሕዝቡም ላይ ረጭቶ፣ “ይህ እነዚህን ቃሎች በሰጠ ጊዜ፣ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋራ የገባው የኪዳኑ ደም ይህ ነው” አላቸው። 9.ሙሴና አሮን፣ ናዳብና አብዩድ እንደዚሁም ሰባዎቹ የእስራኤል አለቆች ወደ ተራራው ወጡ፣ 10.የእስራኤልንም አምላክ አዩ፤ ከእግሩም በታች እንደ ብሩህ ሰማይ የጠራ የሰንፔር ወለል ነበር። 11.ሆኖም እግዚአብሔር በእስራኤል ሕዝብ አለቆች ላይ እጁን አላነሣባቸውም። እግዚአብሔርን አዩ፣ በሉ፤ ጠጡም። 12.እግዚአብሔር ሙሴን፣ “በተራራው ላይ ወደ እኔ ና፤ በዚህም ቈይ፤ እኔም መመሪያ እንዲሆናቸው ሕግና ትእዛዞች የጻፍሁባቸውን የድንጋይ ጽላት እሰጥሃለሁ” አለው። 13.ከዚያም ሙሴ ከረዳቱ ከኢያሱ ጋራ ዐብሮ ሄደ፤ ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ተራራ ወጣ። 14.እርሱም ሽማግሌዎችን “ወደ እናንተ እስክንመለስ ድረስ በዚህ ቈዩ፤ አሮንና ሖር ከእናንተ ጋራ ናቸው፤ ክርክር ያለው ባለጕዳይ ቢኖር ወደ እነርሱ ይሂድ።” አላቸው። 15.ሙሴ ወደ ተራራ ሲወጣ ደመናው ተራራውን ሸፈነ፤ 16.የእግዚአብሔርም ክብር በሲና ተራራ ላይ ወረደ፤ ደመናውም ተራራውን እስከ ስድስት ቀን ድረስ ሸፈነው፤ በሰባተኛውም ቀን እግዚአብሔር በደመናው ውስጥ ሆኖ ሙሴን ጠራው። 17.ለእስራኤላውያን የእግዚአብሔር ክብር በተራራው ጫፍ ላይ እንደሚባላ እሳት ሆኖ ይታይ ነበር። 18.ከዚያም ሙሴ ወደ ተራራው ሲወጣ ደመናው ውስጥ ገባ፤ በተራራውም ላይ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ቈየ።

መዝሙረ ዳዊት

ምዕራፍ 109

1.ለመዘምራን አለቃ፤ የዳዊት መዝሙር።
1 የምስጋናዬ ምንጭ የሆንህ አምላክ ሆይ፤
ዝም አትበል፤
2.ክፉዎችና አታላዮች፣
አፋቸውን ከፍተውብኛልና፤
በውሸተኛ አንደበት ተናግረውብኛል።
3.በጥላቻ ቃል ከብበውኛል፤
ያለ ምክንያትም ጥቃት አድርሰውብኛል።
4.ስወድዳቸው ይወነጅሉኛል፤
እኔ ግን እጸልያለሁ።
5.በበጎ ፈንታ ክፋትን፣
በወደድኋቸው ፈንታ ጥላቻን ይመልሱልኛል።
6.ክፉ ሰው በላዩ ሹም፤
ከሳሽም በቀኙ ይቁም።
7.ፍርድ ፊት ሲቆም በደለኛ ሆኖ ይገኝ፤
ጸሎቱም ለፍርድ ትሁንበት።
8.ዕድሜው ይጠር፤
ሹመቱንም ሌላ ይውሰደው።
9.ልጆቹ ድኻ አደጎች ይሁኑ፤
ሚስቱም መበለት ትሁን።
10.ልጆቹ ይንከራተቱ፤ ለማኞችም ይሁኑ፤
ከፈረሰው ቤታቸውም ይሰደዱ።
11.ያለውን ሁሉ ዕዳ ጠያቂ ይውረሰው፤
የድካሙንም ዋጋ ባዕዳን ይቀሙት።
12.ማንም ሰው ምሕረት አያድርግለት፤
ለድኻ አደግ ልጆቹም የሚራራ አይኑር።
13.ዘሩ ተለይቶ ይጥፋ፤
ስማቸውም በሚቀጥለው ትውልድ ይደምሰስ።
14.የአባቶቹ በደል በእግዚአብሔር ፊት ይታሰብ፤
የእናቱም ኀጢአት አይደምሰስ።
15.መታሰቢያቸውን ከምድር ያጠፉ ዘንድ፣
ኀጢአታቸው ሁልጊዜ በእግዚአብሔር ፊት ይኑር።
16.ድኻውንና ችግረኛውን፣ ልቡም የቈሰለውን፣
እስከ ሞት አሳደደ እንጂ፣
ምሕረት ያደርግ ዘንድ አላሰበምና።
17.መራገምን ወደደ፤ ወደ እርሱም መጣች፤
በመባረክ ደስ አልተሠኘም፤
በረከትም ከርሱ ራቀች።
18.መርገምን እንደ ልብስ ለበሳት፤
እርሷም እንደ ውሃ ወደ ውስጥ ሰውነቱ፣
እንደ ዘይትም ወደ ዐጥንቱ ዘለቀች።
19.ገላውን እንደሚሸፍንበት ልብስ፣
ዘወትር እንደሚታጠቀውም መቀነት ትሁነው።
20.እግዚአብሔር ለሚወነጅሉኝ ሰዎች፣
በነፍሴም ላይ ክፉ ለሚናገሩ የሚከፍላቸው ይኸው ይሁን።
21.አንተ ግን ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤
ስለ ስምህ በበጎ ተመልከተኝ፤
ምሕረትህም መልካም ናትና አድነኝ።
22.እኔ ድኻና ችግረኛ ነኝና፤
ልቤም በውስጤ ቈስሏልና።
23.እንደ ምሽት ጥላ ከእይታ ተሰውሬአለሁ፤
እንደ አንበጣም ረግፌአለሁ።
24.ከጾም የተነሣ ጕልበቴ ዛለ፤
ሰውነቴም ከስቶ ዐመድ ለበሰ።
25.ለመሣለቂያ ሆንሁላቸው፤
ሲያዩኝም ራሳቸውን ይነቀንቃሉ።
26.እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ፤ ርዳኝ፤
እንደ ምሕረትህም አድነኝ።
27.እግዚአብሔር ሆይ፤ እጅህ ይህን እንዳደረገች፣
አንተም ይህን እንደ ፈጸምህ ይወቁ።
28.እነርሱ ይራገማሉ፤ አንተ ግን ትባርካለህ፤
በሚነሡበት ጊዜ ይዋረዳሉ፤
ባሪያህ ግን ሐሤት ያደርጋል።
29.የሚወነጅሉኝ ውርደትን ይከናነቡ፤
ዕፍረትንም እንደ ሸማ ይልበሱ።
30.እግዚአብሔርን በአንደበቴ እጅግ አመሰግናለሁ፤
በታላቅ ሕዝብም መካከል አወድሰዋለሁ።
31.በነፍሱ ላይ ከሚፈርዱት ያድነው ዘንድ፣
እርሱ በችግረኛው ቀኝ በኩል ይቆማልና።

ወደ ኤፌሶን ሰዎች

ምዕራፍ 6

ወላጆችና ልጆች

1.ልጆች ሆይ፤ በጌታ ለወላጆቻችሁ ታዘዙ፤ ይህ ተገቢ ነውና። 2.“አባትህንና እናትህን አክብር” በሚለው ቀዳሚ ትእዛዝ ውስጥ ያለው ተስፋ፣ 3.“መልካም እንዲሆንልህ፣ ዕድሜህም በምድር ላይ እንዲረዝም” የሚል ነው። 4.አባቶች ሆይ፤ እናንተም ልጆቻችሁን አታስቈጧቸው፤ ነገር ግን በጌታ ምክርና ተግሣጽ አሳድጓቸው። 5.ባሮች ሆይ፤ ለክርስቶስ እንደምትታዘዙ፣ በምድር ጌቶቻችሁ ለሆኑት በአክብሮትና በፍርሀት፣ በቅን ልብም ታዘዙ፤ 6.ለታይታና ከእነርሱ ሙገሳን ለማግኘት ሳይሆን፣ እንደ ክርስቶስ ባሮች የእግዚአብሔርን ፈቃድ ከልብ በመፈጸም ታዘዟቸው። 7.ሰውን ሳይሆን ጌታን እንደምታገለግሉ ሆናችሁ በሙሉ ልብ አገልግሉ፤ 8.ምክንያቱም ባሪያም ሆነ ነጻ ሰው ለሚያደርገው በጎ ነገር ሁሉ ሽልማቱን ከጌታ እንደሚቀበል ታውቃላችሁ። 9.እናንተም ጌቶች ሆይ፤ ለባሮቻችሁ እንዲሁ አድርጉላቸው፤ የእነርሱም፣ የእናንተም ጌታ የሆነው በሰማይ እንዳለ፣ የሰውንም ፊት አይቶ እንደማያደላ ታውቃላችሁና አታስፈራሯቸው።

የእግዚአብሔር ጦር ዕቃ

10.በተረፈ በጌታና ብርቱ በሆነው ኀይሉ ጠንክሩ። 11.የዲያብሎስን የተንኰል ሥራ መቋቋም ትችሉ ዘንድ፣ የእግዚአብሔርን ሙሉ የጦር ዕቃ ልበሱ። 12.ምክንያቱም ተጋድሏችን ከሥጋና ከደም ጋራ ሳይሆን ከዚህ ከጨለማ ዓለም ገዦች፣ ከሥልጣናትና ከኀይላት እንዲሁም በሰማያዊ ስፍራ ካሉ ከርኩሳን መናፍስት ሰራዊት ጋራ ነው። 13.ክፉው ቀን ሲመጣ መቋቋም ትችሉ ዘንድ የእግዚአብሔርን ሙሉ የጦር ዕቃ ልበሱ፤ ሁሉን ከፈጸማችሁ በኋላ ጸንታችሁ መቆም ትችላላችሁና። 14.እንግዲህ ወገባችሁን በእውነት ዝናር ታጥቃችሁ፣ የጽድቅንም ጥሩር ለብሳችሁ፣ 15.በሰላም ወንጌል ዝግጁነት እግሮቻችሁ ተጫምተው ቁሙ። 16.ከእነዚህም ሁሉ ጋራ፣ የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ልታጠፉ የምትችሉበትን የእምነትን ጋሻ አንሡ፤ 17.የመዳንን ራስ ቍር አድርጉ፤ የመንፈስንም ሰይፍ ያዙ፤ እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው። 18.በሁሉ ዐይነት ጸሎትና ልመና፣ በማንኛውም ሁኔታ በመንፈስ ጸልዩ፤ ይህንም በማሰብ ንቁ፤ ስለ ቅዱሳንም ሁሉ በትጋት ልመና አቅርቡ። 19.የወንጌልን ምስጢር ለመግለጥ አፌን በምከፍትበት ጊዜ ሁሉ በድፍረት እንድናገር ቃል ይሰጠኝ ዘንድ ጸልዩልኝ። 20.በሰንሰለት የታሰረ መልእክተኛ የሆንሁት ለዚሁ ነውና። ስለዚህ መናገር የሚገባኝን ያለ ፍርሀት እንድናገር ጸልዩልኝ።

የመጨረሻ ሰላምታ

21.በምን ሁኔታ እንዳለሁና ምን እንደማደርግ ታውቁ ዘንድ ተወዳጅ ወንድምና በጌታ ታማኝ አገልጋይ የሆነው ቲኪቆስ ሁሉንም ነገር ይነግራችኋል። 22.የእኛን ሁኔታ እንድታውቁና ልባችሁን እንዲያበረታ ለዚሁ ስል ወደ እናንተ እልከዋለሁ። 23.ከእግዚአብሔር አብ፣ ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ሰላም፣ ፍቅርም ከእምነት ጋራ ለወንድሞች ይሁን። 24.ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ ፍቅር ለሚወድዱ ሁሉ ጸጋ ይሁን።