Skip to Content
የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን | YEHIWOT MELHEK BETEKIRSTIAN
የ2019 ዓ.ም የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ 📖 ዛሬን አንብብ →

የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን

Yehiwot Melhek Betekirstian

ሳምንት 6 · ቀን 27 (ማክሰኞ) 📅 Tikimt 10, 2019

ኦሪት ዘጸአት 19, 20, 21 · መዝሙረ ዳዊት 33 · ወደ ኤፌሶን ሰዎች 5

📖 የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም፦ 1954 መጽሐፍ ቅዱስ አዲሱ መደበኛ ትርጒም

ኦሪት ዘጸአት

ምዕራፍ 19

በሲና ተራራ ላይ

1.በሦስተኛው ወር እስራኤላውያን ከግብጽ ለቅቀው በወጡበት በዚያችው ዕለት ወደ ሲና ምድረ በዳ መጡ። 2.ከራፊዲም ከተነሡ በኋላ ወደ ሲና ምድረ በዳ ገቡ፤ እስራኤልም በዚያ በምድረ በዳው በተራራው ፊት ለፊት ሰፈሩ። 3.ከዚያም ሙሴ ወደ እግዚአብሔር ወጣ፤ እግዚአብሔርም ከተራራው ጠራውና እንዲህ አለው፤ “ለያዕቆብ ቤት የምትለው ለእስራኤልም ሕዝብ የምትናገረው ይህ ነው፤ 4.‘በግብጽ ላይ ያደረግሁትን፣ በንስርም ክንፍ ተሸክሜ ወደ ራሴ እንዴት እንዳመጣኋችሁ እናንተ ራሳችሁ አይታችኋል። 5.አሁንም በፍጹም ብትታዘዙኝና ቃል ኪዳኔን ብትጠብቁ እነሆ ከአሕዛብ ሁሉ እናንተ የተወደደ ርስቴ ትሆናላችሁ፤ ምንም እንኳ ምድር ሁሉ የእኔ ብትሆንም፣ 6.እናንተ ለእኔ የመንግሥት ካህናት የተቀደሰ ሕዝብ ትሆናላችሁ፤’ ለእስራኤላውያን የምትነግራቸው ቃሎች እነዚህ ናቸው።” 7.ስለዚህ ሙሴ ተመልሶ የሕዝቡን አለቆች አስጠራ፤ እንዲናገር እግዚአብሔር ያዘዘውን ቃሎች ሁሉ ነገራቸው። 8.ሕዝቡም ሁሉ በአንድ ላይ “እግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እናደርጋለን” ብለው መለሱ፤ ስለዚህ ሙሴ እነርሱ ያሉትን መልሶ ወደ እግዚአብሔር ወሰደ። 9.እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ከአንተ ጋራ ስናገር ሕዝቡ እንዲሰሙኝና እምነታቸውን ምን ጊዜም በአንተ ላይ እንዲጥሉ በከባድ ደመና ወደ አንተ እመጣለሁ” ከዚያም ሙሴ ሕዝቡ ያሉትን ለእግዚአብሔር ነገረው። 10.እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ወደ ሕዝቡ ሂድና ዛሬና ነገ ቀድሳቸው፤ ልብሳቸውን እንዲያጥቡ አድርግ፤ 11.በሦስተኛውም ቀን ይዘጋጁ፤ ምክንያቱም በዚያ ቀን በሕዝቡ ፊት እግዚአብሔር በሲና ተራራ ላይ ይወርዳል። 12.በተራራው ዙሪያ ለሕዝቡ ወሰን አበጅተህ እንዲህ በላቸው፤ ‘ወደ ተራራው እንዳትወጡ ወይም ግርጌውን እንዳትነኩ ተጠንቀቁ፤ ማንም ተራራውን ቢነካ በርግጥ ይሞታል። 13.በድንጋይ ይወገራል ወይም በቀስት ይወጋል፤ ምንም እጅ በርሱ ላይ አያርፍም፤ ሰውም ሆነ እንስሳ በሕይወት እንዲኖር አይተውም።’ ወደ ተራራው መውጣት የሚችሉት ከፍ ባለ ድምፅ መለከት በተነፋ ጊዜ ብቻ ነው።” 14.ሙሴ ከተራራው ወርዶ ወደ ሕዝቡ ከሄደ በኋላ ቀደሳቸው፤ ልብሳቸውንም ዐጠቡ። 15.ከዚያም ለሕዝቡ፣ “ለሦስተኛው ቀን ራሳችሁን አዘጋጁ፤ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ከማድረግ ተቈጠቡ” አላቸው። 16.በሦስተኛውም ቀን ጧት ከባድ ደመና በተራራው ላይ ሆኖ ነጐድጓድና መብረቅ እንዲሁም ታላቅ የቀንደ መለከት ድምፅ ነበር፤ በሰፈሩ ያሉት ሁሉ ተንቀጠቀጡ። 17.ከዚያም ሙሴ ከእግዚአብሔር ጋራ ለማገናኘት ሕዝቡን ከሰፈር ይዞ ወጣ፤ ከተራራውም ግርጌ ቆሙ። 18.የሲና ተራራ እግዚአብሔር በእሳት ስለ ወረደበት በጢስ ተሸፍኖ ነበር። ጢሱ ከምድጃ እንደሚወጣ ጢስ ወደ ላይ ተትጐለጐለ፤ ተራራውም በሙሉ በኀይል ተናወጠ። 19.የመለከቱም ድምፅ እያየለ መጣ። ከዚያም ሙሴ ተናገረ፤ እግዚአብሔርም በድምፅ መለሰለት። 20.እግዚአብሔር በሲና ተራራ ጫፍ ላይ ወረደ፤ ሙሴን ወደ ተራራው ጫፍ ጠራው፤ ሙሴም ወጣ። 21.እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ሕዝቡ እግዚአብሔርን ለማየት በመጣደፍ ብዙዎቹ እንዳይጠፉ ውረድና አስጠንቅቃቸው 22.ወደ እግዚአብሔር የሚቀርቡት ካህናት እንኳ ራሳቸውን መቀደስ አለባቸው፤ አለዚያ እግዚአብሔር ቍጣውን ያወርድባቸዋል።” 23.ሙሴ እግዚአብሔርን እንዲህ አለው፤ “ሕዝቡ ወደ ሲና ተራራ ሊወጡ አይችሉም፤ ምክንያቱም አንተ ራስህ ‘በተራራው ዙሪያ ወሰን አድርግ፤ የተቀደሰም በማድረግ ለየው’ በማለት አስጠንቅቀኸናልና።” 24.እግዚአብሔርም እንዲህ አለ፤ “ውረድና አሮንን ከአንተ ጋራ ይዘኸው ውጣ፤ ካህናቱና ሕዝቡ ግን ወደ እግዚአብሔር ለመምጣት መጣደፍ የለባቸውም፤ አለዚያ እርሱ ቍጣውን ያወርድባቸዋል።” 25.ስለዚህ ሙሴ ወደ ሕዝቡ ወርዶ ነገራቸው።

ምዕራፍ 20

ዐሥርቱ ትእዛዛት

20፥1-17 ተጓ ምብ – ዘዳ 5፥6-21
1.እግዚአብሔር እነዚህን ቃሎች ሁሉ እንዲህ ብሎ ተናገረ፤ 2.“ከግብጽ ከባርነት ምድር ያወጣሁህ አምላክህ እግዚአብሔር እኔ ነኝ። 3.“ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይኑሩህ። 4.በላይ በሰማይ ወይም በታች በምድር ካለው ወይም ከምድር በታች ወይም በውሃ ውስጥ ከሚኖሩ ነገሮች በማናቸውም ዐይነት ምስል ለራስህ ጣዖትን አታብጅ። 5.አትስገድላቸው ወይም አታምልካቸውም፤ እኔ አምላክህ እግዚአብሔር የሚጠሉኝን ስለ አባቶቻቸው ኀጢአት እስከ ሦስትና እስከ አራት ትውልድ ድረስ ልጆቻቸውን የምቀጣ ቀናተኛ አምላክ ነኝ፤ 6.ለሚወድዱኝና ትእዛዞቼን ለሚጠብቁ ግን እስከ ሺሕ ትውልድ ፍቅርን የማሳይ ነኝ። 7.የእግዚአብሔር የአምላክህን ስም በከንቱ አታንሣ፤ እግዚአብሔር ስሙን በከንቱ የሚያነሣውን በደል አልባ አያደርገውምና። 8.የሰንበትን ቀን ቅዱስ አድርገህ አክብረው። 9.ስድስት ቀን ሥራ፤ ተግባርህንም ሁሉ አከናውን። 10.ሰባተኛው ቀን ግን ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ሰንበት ነው። በዚያ ቀን አንተም ሆንህ ወንድ ልጅህ ወይም ሴት ልጅህ፣ ወንድ አገልጋይህ ሆነ ሴት አገልጋይህ፣ ወይም እንስሳትህ፣ ወይም በደጅህ ያለ መጻተኛ ምንም ሥራ አትሠሩም። 11.እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን፤ ባሕርንም በውስጣቸውም የሚኖሩትን ሁሉ በስድስት ቀን ፈጥሮ፣ በሰባተኛው ቀን ዐርፏልና። ስለዚህ እግዚአብሔር የሰንበትን ቀን ባረከው፤ ቀደሰውም። 12.አባትህንና እናትህን አክብር፤ አምላክህ እግዚአብሔር በሚሰጥህ ምድር ላይ ዕድሜህ እንዲረዝም። 13.አትግደል። 14.አታመንዝር። 15.አትስረቅ። 16.በባልንጀራህ ላይ በሐሰት አትመስክር። 17.የባልንጀራህን ቤት አትመኝ፤ የባልንጀራህን ሚስት ወይም የርሱን ወንድ አገልጋይ ሆነ ሴት አገልጋይ፣ በሬውንም ሆነ አህያውን ወይም የርሱ የሆነውን ማንኛውንም ነገር አትመኝ።” 18.ሕዝቡም መብረቁንና ነጐድጓዱን የተራራውን መጤስና የመለከቱን ድምፅ ባዩና በሰሙ ጊዜ በፍርሀት ተንቀጠቀጡ፤ በርቀትም ቆሙ፤ 19.ሙሴን፣ “አንተ ራስህ ተናገረን፤ እኛም እናደምጥሃለን፤ እግዚአብሔር እንዲናገረን አታድርግ፤ አለዚያ መሞታችን ነው” አሉት። 20.ሙሴም ለሕዝቡ፣ “አትፍሩ፤ ኀጢአት እንዳትሠሩ የእግዚአብሔር ፍርሀት ከእናንተ ጋራ ይሆን ዘንድ፣ እግዚአብሔር ሊፈትናችሁ መጥቷል” አላቸው። 21.እግዚአብሔር ወዳለበት ጥቅጥቅ ወደ ሆነው ጨለማ ሙሴ ቀርቦ ሳለ፣ ሕዝቡ በርቀት ቆመው ነበር።

ጣዖቶችና መሠዊያዎች

22.ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን አለው፤ “ለእስራኤላውያን ይህን ንገራቸው፤ ‘ከሰማይ ሆኜ እንደ ተናገርኋችሁ እናንተ ራሳችሁ አይታችኋል፤ 23.ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይኑሯችሁ፤ ከብር ወይም ከወርቅ ለእናንተ አማልክትን አታብጁ። 24.“ ‘የጭቃ መሠዊያን ሥራልኝ፤ በርሱም ላይ የሚቃጠልና የኅብረት መሥዋዕትን ከበጎችህ፣ ከፍየሎችህና ከቀንድ ከብቶችህ ሠዋልኝ፤ ስሜ እንዲከበር በማደርግበት ቦታ ሁሉ ወደ አንተ እመጣና እባርክሃለሁ። 25.ከድንጋይ መሠዊያ የምትሠራልኝ ከሆነ፣ ከጥርብ ድንጋይ አትሥራ፤ መሣሪያ የነካው ከሆነ ታረክሰዋለህና። 26.ወደ መሠዊያዬም በደረጃ አትውጣ፤ አለዚያ ኀፍረተ ሥጋህ ይገለጣል።’

ምዕራፍ 21

1.“በፊታቸው የምትደነግጋቸው ሥርዐቶች እነዚህ ናቸው፤

ዕብራዊ አገልጋይ

21፥2-6 ተጓ ምብ – ዘዳ 15፥12-18
21፥2-11 ተጓ ምብ – ዘሌ 25፥39-55
2.“ዕብራዊ አገልጋይ ብትገዛ ስድስት ዓመት ያገልግልህ፤ በሰባተኛው ዓመት ግን ያለ ምንም ክፍያ በነጻ ይሂድ። 3.ብቻውን መጥቶ ከሆነ፣ ብቻውን በነጻ ይሂድ፤ ነገር ግን ሲመጣ ባለሚስት ከሆነ፣ እርሷ ዐብራው ትሂድ። 4.ጌታው ሚስት አጋብቶት ወንድ ወይም ሴት ልጅ ከወለደችለት፣ ሴትዮዋና ልጆቿ የጌታቸው ይሆናሉ፤ ሰውየው ብቻ በነጻ ይሂድ። 5.“ነገር ግን አገልጋዩ፤ ‘ጌታዬን፤ ሚስቴንና ልጆቼን እወድዳለሁ፤ ነጻ ሆኜ አልሄድም’ ቢል፣ 6.ጌታው ወደ ዳኞች ይውሰደው፤ ወደ በር ወይም ወደ በሩ መቃን ወስዶ ጆሮውን በወስፌ ይብሳው፤ ከዚያም ዕድሜ ዘመኑን የርሱ አገልጋይ ይሆናል። 7.“አንድ ሰው ሴት ልጁን አገልጋይ እንድትሆን ቢሸጣት፣ እንደ ወንዶቹ አገልጋዮች በነጻ መሸኘት የለባትም። 8.ለርሱ ትሆነው ዘንድ የመረጣትን ጌታዋን ደስ ባታሠኝ፣ በወጆ ይስደዳት፤ ለባዕዳን ይሸጣት ዘንድ መብት የለውም፤ ምክንያቱም ለርሷ ያለውን ታማኝነት አጓድሏልና። 9.ለወንድ ልጁ ትሆን ዘንድ መርጧት ከሆነ እንደ ራሱ ልጅ የሚገባትን መብት ይስጣት። 10.ሌላ ሴት ቢያገባ፣ ለመጀመሪያ ሚስቱ ምግቧን፣ ልብሷንና የጋብቻ መብቷን አይከልክላት። 11.እነዚህን ሦስት ነገሮች የማያሟላላት ቢሆን፣ ያለ አንዳች የገንዘብ ክፍያ በነጻ መሄድ ይኖርባታል።

በሕይወት ላይ ለሚደርስ ጕዳት

12.“ሰውን ደብድቦ የገደለ ሞት ይገባዋል። 13.ሆኖም እግዚአብሔር ፈቅዶ ሰውየው ሳያውቅ በድንገት አድርጎት ከሆነ፣ እኔ ወደምወስነው ስፍራ ይሽሽ። 14.አንድ ሰው በተንኰል ሆነ ብሎ ሌላውን ቢገድል፣ ከመሠዊያዬ ተወስዶ ይገደል። 15.“አባቱን ወይም እናቱን የሚመታ ይገደል። 16.“አንዱ ሌላውን ጠልፎ የሸጠ ወይም በተያዘ ጊዜ ከእጁ ላይ የተገኘበት ይገደል። 17.“አባቱን ወይም እናቱን የሚሰድብ ይገደል። 18.“ሰዎች ተጣልተው አንዱ ሌላውን በድንጋይ ወይም በቡጢ ቢመታውና ተመቺው ሳይሞት በዐልጋ ላይ ቢውል፣ 19.በትሩንም ይዞ ደጅ ለደጅ የሚል ቢሆን፣ በዱላ የመታው ሰው አይጠየቅበትም፤ ሆኖም ለተጐጂው ሰው ለባከነበት ጊዜ ገንዘብ ይክፈል፤ ፈጽሞ እስኪድን ክትትል ያድርግለት። 20.“አንድ ሰው ወንድ ወይም ሴት ባሪያውን በዱላ ቢመታና ባሪያውም በዚህ የተነሣ ቢሞት መቀጣት አለበት፤ 21.ነገር ግን ከአንድ ወይም ከሁለት ቀን በኋላ ባሪያው ቢነሣ መቀጣት የለበትም፤ ባሪያው ንብረቱ ነውና። 22.“በጥል ላይ ያሉ ሰዎች ነፍሰ ጡር ሴት ቢመቱና እርሷም ያለጊዜዋ ብትወልድ፣ ጕዳቱም ለክፉ የማይሰጥ ቢሆን፣ ጕዳት ያደረሰባት ሰው የሴትየዋ ባል የጠየቀውንና ፈራጆቹ የፈቀዱትን ካሣ ሁሉ መክፈል አለበት። 23.ነገር ግን የከፋ ጕዳት ቢደርስ ሕይወት በሕይወት፣ 24.ዐይን በዐይን፣ ጥርስ በጥርስ፣ እጅ በእጅ፣ እግር በእግር፣ 25.ቃጠሎ በቃጠሎ፣ ቍስል በቍስል፣ ግርፋት በግርፋት ታስከፍላለህ። 26.“አንድ ሰው የወንድ ወይም የሴት አገልጋዩን ዐይን መትቶ ቢያጠፋ፣ ስለ ዐይን ካሳ አገልጋዩን ነጻ ይልቀቀው። 27.የወንድ ወይም የሴት አገልጋዩን ጥርስ ቢሰብር፣ ስለ ጥርስ ካሳ አገልጋዩን ነጻ ይልቀቀው። 28.“በሬ አንድን ወንድ ወይም ሴት ወግቶ ቢገድል፣ በሬው በድንጋይ ተወግሮ ይሙት፤ ሥጋውም አይበላ፤ ነገር ግን የበሬው ባለቤት በኀላፊነት አይጠየቅም። 29.ሆኖም በሬው የመውጋት ዐመል ያለበት ሆኖ ለባለቤቱም ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶት ሳለ በበረት ሳያስቀረው ቀርቶ አንድን ወንድ ወይም ሴት ቢገድል፣ በሬው በድንጋይ ይወገር፤ ባለቤቱም እንዲሁ ተወግሮ ይሙት። 30.ሆኖም ካሳ እንዲከፍል ከተጠየቀ፣ የተጠየቀውን ሁሉ በመክፈል ሕይወቱን ይዋጅ። 31.አንድ በሬ አንድን ወንድ ወይም ሴት ልጅ ቢወጋ በዚሁ ሕግ መሠረት ይፈጸም። 32.አንድ በሬ ወንድ ወይም ሴት ባሪያን ቢወጋ ባለቤቱ ሠላሳ የብር ሰቅል ለባሪያው ጌታ መክፈል አለበት፤ በሬውም በድንጋይ ይወገር። 33.“አንድ ሰው ጕድጓድን ከፍቶ ቢተው፣ ወይም ጕድጓድ ቈፍሮ ሳይከድነው ቢቀርና በሬ ወይም አህያ ቢገባበት፣ 34.የጕድጓዱ ባለቤት ኪሳራ ይክፈል፤ ለባለቤቱ መክፈል አለበት፤ የሞተውም እንስሳ ለርሱ ይሆናል። 35.“የአንድ ሰው በሬ የሌላውን ሰው በሬ ወግቶ ቢገድለው፣ በሕይወት ያለውን በሬ ሽጠው ገንዘቡንና የሞተውን እንስሳ እኩል ይካፈሉ። 36.ሆኖም በሬው የመዋጋት ዐመል ያለው መሆኑ ከታወቀ፣ ባለቤቱም በረት ሳይዘጋበት ቢቀር፣ ባለቤቱ በሬውን በበሬው ፈንታ ይክፈል፤ የሞተውም እንስሳ ለርሱ ይሆናል።

መዝሙረ ዳዊት
መዝሙር 33

1 ጻድቃን ሆይ፤ በእግዚአብሔር ደስ ይበላችሁ፤
ቅኖች ሊወድሱት ይገባቸዋል።
2 እግዚአብሔርን በመሰንቆ አመስግኑት፤
ዐሥር አውታር ባለውም በገና ዘምሩለት።
3 አዲስ መዝሙር ዘምሩለት፤
በገናውን ባማረ ቅኝት ደርድሩ፤ እልልም በሉ።
4 የእግዚአብሔር ቃል እውነት ነውና፤
የሚሠራውም ሁሉ የታመነ ነው።
5 እግዚአብሔር ጽድቅንና ፍትሕን ይወድዳል፤
ምድርም በምሕረቱ የተሞላች ናት።
6 በእግዚአብሔር ቃል ሰማያት ተሠሩ፤
በአፉም እስትንፋስ የከዋክብት ሰራዊት።
7 የባሕርን ውሃ በአንድ ዕቃ ይሰበስባል፤
ቀላዩንም በአንድ ስፍራ ያከማቻል።
8 ምድር ሁሉ እግዚአብሔርን ትፍራው፤
በዓለም የሚኖር ሕዝብ ሁሉ በፊቱ ይንቀጥቀጥ።
9 እርሱ ተናግሯልና ሆኑ፤
አዝዟልና ጸኑም።
10 እግዚአብሔር የሕዝቦችን ምክክር ከንቱ ያደርጋል፤
የሕዝብንም ዕቅድ ያጨናግፋል።
11 የእግዚአብሔር ሐሳብ ግን ለዘላለም ይጸናል፤
የልቡም ሐሳብ ለትውልድ ሁሉ ነው።
12 ብፁዕ ነው፤
እግዚአብሔር አምላኩ የሆነው ሕዝብ፣
ለርስቱ የመረጠውም ወገን፤
13 እግዚአብሔር ከሰማይ ይመለከታል፤
የሰውንም ልጆች ሁሉ ያያል፤
14 ከማደሪያው ቦታ ሆኖ፣
በምድር ወደሚኖሩት ሁሉ ይመለከታል፤
15 እርሱ የሁሉን ልብ የሠራ፣
የሚያደርጉትን ሁሉ የሚያስተውል ነው።
16 ንጉሥ በሰራዊቱ ታላቅነት አይድንም፤
ጀግናም በኀይሉ ብርታት አያመልጥም።
17 በፈረስ ድል አደርጋለሁ ማለት ከንቱ ተስፋ ነው፤
በብርቱ ጕልበቱም ማንንም አያድንም።
18 እነሆ፤ የእግዚአብሔር ዐይኖች በሚፈሩት ላይ ናቸው፤
ምሕረቱንም በሚጠባበቁት ላይ አትኵረዋል።
19 በዚህም ነፍሳቸውን ከሞት ያድናል፤
በራብ ዘመንም በሕይወት ያኖራቸዋል።
20 ነፍሳችን እግዚአብሔርን ተስፋ ታደርጋለች፤
እርሱ ረዳታችንና ጋሻችን ነው።
21 ልባችን በርሱ ደስ ይለዋል፤
በቅዱስ ስሙ ታምነናልና።
22 እግዚአብሔር ሆይ፤ ተስፋ ባደረግንህ፣
በእኛ ላይ ምሕረትህ ትሁን።

ወደ ኤፌሶን ሰዎች

ምዕራፍ 5

1.እንግዲህ እንደ ተወደዱ ልጆች እግዚአብሔርን ምሰሉ፤ 2.ክርስቶስ እንደ ወደደን ራሱንም ስለ እኛ መልካም መዐዛ ያለው መባና መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር እንደ ሰጠ እናንተም በፍቅር ተመላለሱ። 3.ማንኛውም የዝሙት ወይም የርኩሰት ወይም የሥሥት ነገር ከቶ በመካከላችሁ አይነሣ፤ ይህ ቅዱስ ለሆነው ለእግዚአብሔር ሕዝብ አይገባምና። 4.የሚያሳፍርና ተራ የሆነ ንግግር፣ ዋዛ ፈዛዛም ለእናንተ ስለማይገባ በመካከላችሁ አይኑር፤ ይልቁንስ የምታመሰግኑ ሁኑ። 5.ደግሞም ይህን ዕወቁ፤ ማንም አመንዝራ ወይም ርኩስ ወይም ስግብግብ፣ ይኸውም ጣዖት አምላኪ በክርስቶስና በእግዚአብሔር መንግሥት ርስት የለውም። 6.ማንም በከንቱ ንግግር አያታልላችሁ፤ ምክንያቱም የእግዚአብሔር ቍጣ በማይታዘዙ ልጆች ላይ የሚመጣው በእንደዚህ ዐይነት ነገር ነው። 7.ስለዚህ እንዲህ ካሉ ጋራ አትተባበሩ። 8.ቀድሞ ጨለማ ነበራችሁ፤ አሁን ግን በጌታ ብርሃን ናችሁ። እንደ ብርሃን ልጆች ኑሩ፤ 9.የብርሃኑ ፍሬ በበጎነት፣ በጽድቅና በእውነት ሁሉ ዘንድ ነውና። 10.እንዲሁም ጌታን ደስ የሚያሠኘውን ፈልጉ። 11.ፍሬ ከሌለው ከጨለማ ሥራ ጋራ ምንም ዐይነት ግንኙነት አይኑራችሁ፤ ይልቁን ግለጡት፤ 12.በድብቅ የሚሠሩትን ነገር መናገር ራሱ አሳፋሪ ነውና። 13.ብርሃን የበራበት ነገር ሁሉ ግልጽ ሆኖ ይታያል፤ 14.ምክንያቱም ሁሉን ነገር እንዲታይ የሚያደርገው ብርሃን ነውና፤ ስለዚህም፣
“አንተ የተኛህ ንቃ፤
ከሙታን ተነሣ፤
ክርስቶስም ያበራልሃል” ተብሏል።
15.እንግዲህ ጥበብ እንደሌላቸው ሳይሆን እንደ ጥበበኞች እንዴት እንደምትኖሩ ተጠንቀቁ። 16.ቀኖቹ ክፉ ናቸውና ዘመኑን በሚገባ ዋጁ። 17.ስለዚህ ሞኞች አትሁኑ፤ የጌታ ፈቃድ ምን እንደ ሆነ አስተውሉ እንጂ። 18.በመንፈስ ተሞሉ እንጂ በወይን ጠጅ አትስከሩ፤ ይህ ብክነት ነውና። 19.በመዝሙርና በውዳሴ፣ በመንፈሳዊም ዝማሬ እርስ በርሳችሁ ተነጋገሩ፤ በልባችሁ ለጌታ ተቀኙ፤ አዚሙም። 20.በዚህም እግዚአብሔር አብን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ስለ ሁሉ ነገር ሁልጊዜ አመስግኑ። 21.ለክርስቶስ ካላችሁ አክብሮታዊ ፍርሀት የተነሣ አንዳችሁ ለአንዳችሁ ተገዙ።

ለክርስቲያን ቤተ ሰብ የተሰጠ መመሪያ

5፥22–6፥9 ተጓ ምብ – ቈላ 3፥18–4፥1
22.ሚስቶች ሆይ፤ ለጌታ እንደምትገዙ ለባሎቻችሁ ተገዙ፤ 23.ክርስቶስ፣ አካሉ ለሆነችውና አዳኟ ለሆናት ቤተ ክርስቲያን ራስ እንደ ሆነ ሁሉ፣ ባልም የሚስቱ ራስ ነውና። 24.እንግዲህ ቤተ ክርስቲያን ለክርስቶስ እንደምትገዛ፣ ሚስቶችም ለባሎቻቸው በማንኛውም ነገር እንደዚሁ መገዛት ይገባቸዋል። 25.ባሎች ሆይ፤ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳትና ራሱንም ስለ እርሷ አሳልፎ እንደ ሰጠ፣ እናንተም ሚስቶቻችሁን ውደዱ፤ 26.በቃሉ አማካይነት በውሃ ዐጥቦ በማንጻት እንድትቀደስ፣ 27.እንዲሁም ጕድፍ ወይም የፊት መጨማደድ ወይም አንዳች እንከን ሳይገኝባት ቅድስትና እንከን አልባ የሆነች ክብርት ቤተ ክርስቲያን አድርጎ ለራሱ ሊያቀርባት ነው። 28.ባሎችም እንደዚሁ ሚስቶቻቸውን እንደ ገዛ ሥጋቸው መውደድ ይገባቸዋል። ሚስቱን የሚወድድ ራሱን ይወድዳል። 29.የገዛ ሥጋውን የሚጠላ ማንም የለም፤ ይመግበዋል፤ ይንከባከበዋል፤ ክርስቶስም ለቤተ ክርስቲያን ያደረገው ልክ እንደዚሁ ነው፤ 30.እኛ የክርስቶስ አካል ብልቶች ነንና። 31.“ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፤ ከሚስቱም ጋራ ይጣመራል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ።” 32.ይህ ጥልቅ ምስጢር ነው፤ እኔም ይህን ስለ ክርስቶስና ስለ ቤተ ክርስቲያን እናገራለሁ። 33.ሆኖም ከእናንተ እያንዳንዱ ሚስቱን እንደ ራሱ አድርጎ ይውደድ፤ ሚስትም ባሏን ታክብር