ሳምንት 6 · ቀን 27 (ማክሰኞ)
📅 Tikimt 10, 2019
ኦሪት ዘጸአት 19, 20, 21 · መዝሙረ ዳዊት 33 · ወደ ኤፌሶን ሰዎች 5
ኦሪት ዘጸአት
ምዕራፍ 19
1.በሦስተኛውም ወር የእስራኤል ልጆች ከግብፅ ምድር ከወጡ በኋላ በዚያ ቀን ወደ ሲና ምድረ በዳ መጡ።
2.ከራፊድም ተነሥተው ወደ ሲና ምድረ በዳ መጡ፥ በምድረ በዳም ሰፈሩ፤ በዚያም እስራኤል በተራራው ፊት ሰፈረ።
3.ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ወጣ፤ እግዚአብሔርም በተራራው ጠርቶ አለው። ለያዕቆብ ቤት እንዲህ በል፥ ለእስራኤልም ልጆች እንዲህ ንገር።
4.በግብፃውያን ያደረግሁትን፥ በንስርም ክንፍ እንደተሸከምኋችሁ፥ ወደ እኔም እንዳመጣኋችሁ አይታችኋል።
5.አሁንም ቃሌን በእውነት ብትሰሙ ኪዳኔንም ብትጠብቁ፥ ምድር ሁሉ የእኔ ናትና ከአሕዛብ ሁሉ የተመረጠ ርስት ትሆኑልኛላችሁ፤
6.እናንተም የካህናት መንግሥት የተቀደሰም ሕዝብ ትሆኑልኛላችሁ። ለእስራኤል ልጆች የምትነግራቸው ቃል ይህ ነው።
7.ሙሴም መጣ፥ የሕዝቡንም ሽማግሌዎች ጠርቶ እግዚአብሔር ያዘዘውን ይህን ቃል ሁሉ በፊታቸው ተናገረ።
8.ሕዝቡ ሁሉ አንድ አፍ ሆነው። እግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እናደርጋለን ብለው መለሱ፤ ሙሴም የሕዝቡን ቃል ወደ እግዚአብሔር አደረሰ።
9.እግዚአብሔርም ሙሴን። ከአንተ ጋር ስነጋገር ሕዝቡ እንዲሰሙ፥ ደግሞም ለዘላለም እንዲያምኑብህ፥ እነሆ በከባድ ደመና እመጣልሃለሁ አለው። ሙሴም የሕዝቡን ቃል ለእግዚአብሔር ነገረ።
10.እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። ወደ ሕዝቡ ሂድ፥ ዛሬና ነገም ቀድሳቸው፥ ልብሳቸውንም ይጠቡ፤
11.በሦስተኛው ቀን ሕዝቡ ሁሉ ሲያዩ እግዚአብሔር በሲና ተራራ ላይ ይወርዳልና ለሦስተኛው ቀን ይዘጋጁ።
12.ወሰንም ለሕዝቡ በዙሪያው አድርግላቸው። ወደ ተራራው እንዳትወጡ ጫፉንም እንዳትነኩ ተጠንቀቁ፤ ተራራውንም የነካ ፈጽሞ ይሞታል፤
13.የማንም እጅ አይንካ፤ ነገር ግን የሚነካው ሁሉ ይወገራል፥ ወይም በፍላጻ ይወጋል፤ እንስሳ ወይም ሰው ቢሆን አይድንም በላቸው። ሳያቋርጥ የመለከት ድምፅ ሲነፋ በዚያን ጊዜ ወደ ተራራው ይውጡ።
14.ሙሴም ከተራራው ወደ ሕዝቡ ወረደ፥ ሕዝቡንም ቀደሰ፤ ልብሳቸውንም አጠቡ።
15.ሕዝቡንም። ለሦስተኛው ቀን ተዘጋጁ፥ ወደ ሴቶቻችሁ አትቅረቡ አለ።
16.እንዲህም ሆነ፤ በሦስተኛው ቀን በማለዳ ጊዜ ነጐድጓድና መብረቅ ከባድም ደመና እጅግም የበረታ የቀንደ መለከት ድምጽ በተራራው ላይ ሆነ፤ በሰፈሩም የነበሩት ሕዝብ ሁሉ ተንቀጠቀጡ።
17.ሙሴም ሕዝቡን ከእግዚአብሔር ጋር ለማገናኘት ከሰፈር አወጣቸው፤ ከተራራውም እግርጌ ቆሙ።
18.እግዚአብሔርም በእሳት ስለ ወረደበት የሲና ተራራ ሁሉ ይጤስ ነበር፤ ከእርሱም እንደ እቶን ጢስ ያለ ጢስ ይወጣ ነበር፥ ተራራውም ሁሉ እጅግ ይናወጥ ነበር።
19.የቀንደ መለከቱም ድምፅ እጅግ በበረታና በጸና ጊዜ ሙሴ ተናገረ እግዚአብሔርም በድምፅ መለሰለት።
20.እግዚአብሔርም በሲና ተራራ ላይ ወደ ተራራው ራስ ወረደ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን ወደ ተራራው ራስ ጠራው፤ ሙሴም ወጣ።
21.እግዚአብሔርም ሙሴን። ውረድ፥ እግዚአብሔርን ለማየት ዳርቻውን እንዳያልፉ ከእነርሱም ብዙ እንዳይጠፉ ለሕዝቡ አስጠንቅቃቸው፤
22.ወደ እግዚአብሔርም የሚቀርቡት ካህናት ደግሞ እግዚአብሔር እንዳያጠፋቸው ራሳቸውን ይቀድሱ አለው።
23.ሙሴም እግዚአብሔርን። አንተ። በተራራው ዙሪያ ወሰን አድርግ ቀድሰውም ብለህ አስጠንቅቀኸናልና ሕዝቡ ወደ ተራራ ይወጡ ዘንድ አይችሉም አለው።
24.እግዚአብሔርም። ሂድ፥ ውረድ፤ አንተ አሮንም ከአንተ ጋር ትወጣላችሁ፤ ካህናቱና ሕዝቡ ግን እግዚአብሔር እንዳያጠፋቸው ወደ እግዚአብሔር ይወጡ ዘንድ አይተላለፉ አለው።
25.ሙሴም ወደ ሕዝቡ ወረደ፥ ይህንንም ነገራቸው።
ምዕራፍ 20
1.እግዚአብሔርም ይህን ቃል ሁሉ እንዲህ ብሎ ተናገረ።
2.ከግብፅ ምድር ከባርነት ቤት ያወጣሁህ እግዚአብሔር አምላክህ እኔ ነኝ።
3.ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይሁኑልህ። ፕ
4.በላይ በሰማይ ካለው፥ በታችም በምድር ካለው፥ ከምድርም በታች በውኃ ካለው ነገር የማናቸውንም ምሳሌ፥ የተቀረጸውንም ምስል ለአንተ አታድርግ።
5.አትስገድላቸው፥ አታምልካቸውምም፤ በሚጠሉኝ እስከ ሦስተኛና እስከ አራተኛ ትውልድ ድረስ የአባቶችን ኃጢአት በልጆች ላይ የማመጣ፤
6.ለሚወድዱኝ፥ ትእዛዜንም ለሚጠብቁ እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ ምሕረትን የማደርግ እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ቀናተኛ አምላክ ነኝና። ፕ
7.የእግዚአብሔርን የአምላክህን ስም በከንቱ አትጥራ፤ እግዚአብሔር ስሙን በከንቱ የሚጠራውን ከበደል አያነጻውምና።
8.የሰንበትን ቀን ትቀድሰው ዘንድ አስብ።
9.ስድስት ቀን ሥራ ተግባርህንም ሁሉ አድርግ፤
10.ሰባተኛው ቀን ግን ለእግዚአብሔር ለአምላክህ ሰንበት ነው፤ አንተ፥ ወንድ ልጅህም፥ ሴት ልጅህም፥ ሎሌህም፥ ገረድህም፥ ከብትህም፥ በደጆችህም ውስጥ ያለ እንግዳ በእርሱ ምንም ሥራ አትሥሩ፤
11.እግዚአብሔር በስድስት ቀን ሰማይንና ምድርን፥ ባሕርንም፥ ያለባቸውንም ሁሉ ፈጥሮ በሰባተኛው ቀን ዐርፎአልና፤ ስለዚህ እግዚአብሔር የሰንበትን ቀን ባርኮታል ቀድሶታልም።
12.አባትህንና እናትህን አክብር፤ እግዚአብሔር አምላክህ በሚሰጥህ ምድር ዕድሜህ እንዲረዝም።
13.አትግደል።
14.አታመንዝር።
15.አትስረቅ።
16.በባልንጀራህ ላይ በሐሰት አትመስክር።
17.የባልንጀራህን ቤት አትመኝ፤ የባልንጀራህን ሚስት ሎሌውንም ገረዱንም በሬውንም አህያውንም ከባልንጀራህ ገንዘብ ሁሉ ማናቸውንም አትመኝ።
18.ሕዝቡም ሁሉ ነጐድጓዱንና መብረቁን፥ የቀንደ መለከቱን ድምፅ፥ ተራራውንም ሲጤስ አዩ፤ ሕዝቡም ባዩ ጊዜ ተርበደበዱ፥ ርቀውም ቆሙ።
19.ሙሴንም። አንተ ተናገረን እኛም እንሰማለን፤ እንዳንሞት ግን እግዚአብሔር አይናገረን አሉት።
20.ሙሴም ለሕዝቡ። እግዚአብሔር ሊፈትናችሁ፥ ኃጢያትንም እንዳትሠሩ እርሱን መፍራት በልባችሁ ይሆን ዘንድ መጥቶአልና አትፍሩ አለ።
21.ሕዝቡም ርቀው ቆሙ፥ ሙሴም እግዚአብሔር ወዳለበት ወደ ጨለማው ቀረበ።
22.እግዚአብሔር ሙሴን አለው። ለእስራኤል ልጆች እንዲህ በል። እኔ ከሰማይ እንደ ተናገርኋችሁ እናንተ አይታችኋል።
23.በአጠገቤ ምንም አታድርጉ፤ የብር አማልክት የወርቅም አማልክት ለእናንተ አታድርጉ።
24.የጭቃ መሠዊያ ሥራልኝ፥ የሚቃጠለውንና የደኅንነት መሥዋዕትህን በጎችህንም በሬዎችህንም ሠዋበት፤ ስሜን በማሳስብበት ስፍራ ሁሉ ወደ አንተ መጥቼ እባርክሃለሁ።
25.የድንጋይም መሠዊያ ብታደርግልኝ ብረት በነካው ድንጋይ አትሥራው፤ በመሣሪያ ብትነካው ታረክሰዋለህና።
26.ኃፍረተ ሥጋህ በእርሱ እንዳይገለጥ ወደ መሠዊያዬ በደረጃ አትውጣ።
ምዕራፍ 21
1.በፊታቸው የምታደርገው ሥርዓት ይህ ነው።
2.ዕብራዊ ባሪያ የገዛህ እንደሆነ ስድስት ዓመት ያገልግልህ፥ በሰባተኛውም በከንቱ አርነት ይውጣ።
3.ብቻውን መጥቶ እንደሆነ ብቻውን ይውጣ፤ ከሚስቱ ጋር መጥቶ እንደሆነ ሚስቱ ከእርሱ ጋር ትውጣ።
4.ጌታው ሚስት አጋብቶት እንደ ሆነ ወንዶች ወይም ሴቶች ልጆች ብትወልድለት፥ ሚስቱና ልጆችዋ ለጌታው ይሁኑ፥ እርሱም ብቻውን ይውጣ።
5.ባሪያውም። ጌታዬን ሚስቴን ልጅቼንም እወድዳለሁ፥ አርነት አልወጣም ብሎ ቢናገር፥ ጌታው ወደ ፈራጆች ይውሰደው፥
6.ወደ ደጁም ወደ መቃኑ አቅርቦ ጆሮውን በወስፌ ይብሳው፤ ለዘላለምም ባሪያው ይሁን።
7.ሰውም ሴት ልጁን ለባርነት ቢሸጥ ባሪያዎች እንደሚወጡ እርስዋ አትውጣ።
8.ጌታዋን ደስ ባታሰኘው በዎጆ ይስደዳት፤ ስለ ናቃት ለሌላ ወገን ሰዎች ይሸጣት ዘንድ አይገባውም።
9.ለልጁም ብድራት፥ ለሴት ልጆች የሚገባውን ያድርግላት።
10.ከእርስዋ ሌላም ቢያጋባው፥ መኖዋን ልብስዋንም ለምንጣፍዋም ተገቢውን አያጕድልባት።
11.ይህንም ሦስት ነገር ባያደርግላት ያለ ገንዘብ በከንቱ ትውጣ።
12.ሰው ሰውን ቢመታ ቢሞትም፥ እርሱ ፈጽሞ ይገደል።
13.ባይሸምቅበትም፥ ነገር ግን እግዚአብሔር ድንገት በእጁ ቢጥለው፥ የሚሸሽበት ስፍራ እኔ አደርግልሃለሁ።
14.ሰው ግን ቢደፍር፥ ባልጀራውን በተንኰል ቢገድለው፥ እንዲሞት ከመሠዊያዬ አውጥተህ ውሰደው።
15.አባቱን ወይም እናቱን የሚመታ ፈጽሞ ይገደል።
16.ሰውን ሰርቆ ቢሸጥ፥ ወይም በእጁ ቢገኝ፥ እርሱ ፈጽሞ ይገደል።
17.አባቱን ወይም እናቱን የሚሰድብ ፈጽሞ ይገደል።
18.ሁለት ሰዎችም ቢጣሉ፥ አንዱም ሌላውን በድንጋይ ወይም በጡጫ ቢመታ፥ ያም ባይሞት ነገር ግን ታምሞ በአልጋው ላይ ቢተኛ፥
19.ተነሥቶም በምርኩዝ ወደ ሜዳ ቢወጣ፥ የመታው ንጹሕ ነው፤ ነገር ግን ተግባሩን ስላስፈታው ገንዘብ ይከፍለው ዘንድ፥ ያስፈውሰውም ዘንድ ግዴታ አለበት።
20.ሰውም ወንድ ባሪያውን ወይም ሴት ባሪያውን በበትር ቢመታ፥ ቢሞትበትም፥ ፈጽሞ ይቀጣ።
21.የተመታው ግን አንድ ወይም ሁለት ቀን ቢቈይ ገንዘቡ ነውና አይቀጣ።
22.ሁለት ሰዎች ቢጣሉ፥ ያረገዘችንም ሴት ልጁን እስክትጨነግፍ ቢገፉአት ባትጐዳ ግን፥ የሴቲቱ ባል የጫነበትን ያህል ካሳ ይስጥ፤ ፈራጆቹም እንደ ፈረዱበት ይክፈል።
23.ጕዳት ግን ቢያገኛት ሕይወት በሕይወት፥
24.ዓይን በዓይን፥ ጥርስ በጥርስ፥ እጅ በእጅ፥
25.እግር በእግር፥ መቃጠል በመቃጠል፥ ቍስል በቍስል፥ ግርፋት በግርፋት ይከፈል።
26.ሰውም የባሪያውን ወይም የባሪይይቱን ዓይን ቢመታ ቢያጠፋውም፥ ስለ ዓይኑ አርነት ያውጣው።
27.የባሪያውን ወይም የባሪያይቱን ጥርስ ቢሰብር፥ ስለ ጥርሱ አርነት ያውጣው።
28.በሬም ወንድን ወይም ሴትን እስኪሞቱ ድረስ ቢወጋ፥ በሬው ይወገር፥ ሥጋውም አይበላ፤ የበሬው ባለቤት ግን ንጹሕ ነው።
29.በሬው ግን አስቀድሞ ተዋጊ ቢሆን፥ ሰዎችም ለባለቤቱ ቢመሰክሩለት ባይጠብቀውም፥ ወንድንም ወይም ሴትን ቢገድል፥ በሬው ይወገር፥ ባለቤቱ ደግሞ ይገደል።
30.ከእርሱ ግን ካሳ ቢፈልጉ፥ የሕይወቱን ዎጆ የጫኑበትን ያህል ይስጥ።
31.ደግሞ ወንድን ልጅ ቢወጋ ሴትንም ልጅ ቢወጋ፥ ይህንኑ ፍርድ ያድርጉበት።
32.በሬው ወንድ ባሪያ ወይም ሴት ባሪያ ቢወጋ፥ የበሬው ባለቤት ሠላሳ የብር ሰቅል ለጌታቸው ይስጥ፥ በሬውም ይወገር።
33.ሰውም ጕድጓድ ቢከፍት፥ ወይም ጕድጓድ ቢቈፍር ባይከድነውም፥ በሬም ወይም አህያ ቢወድቅበት፥
34.የጕድጓዱ ባለቤት ዋጋቸውን ለባለቤታቸው ይክፈል፤ የሞተውም ለእርሱ ይሁን።
35.የሰው በሬ የሌላውን በሬ እስኪሞት ድረስ ቢወጋ፥ ደኅናውን በሬ ይሽጡ፥ ዋጋውንም በትክክል ይካፈሉ፤ የሞተውንም ደግሞ በትክክል ይካፈሉ።
36.በሬውም አስቀድሞ ተዋጊ መሆኑ ቢታወቅ፥ ባለቤቱም ባይጠብቀው፥ በሬውን በበሬው ፈንታ ይስጥ፥ የሞተውም ለእርሱ ይሁነው።
መዝሙረ ዳዊት
ምዕራፍ 33
1.የዳዊት መዝሙር።
ጻድቃን ሆይ፥ በእግዚአብሔር ደስ ይበላችሁ፤ ለቅኖች ምስጋና ይገባል። 2.እግዚአብሔርን በመሰንቆ አመስግኑት፥ አሥር አውታርም ባለው በበገና ዘምሩለት። 3.አዲስ ቅኔም ተቀኙለት፥ በእልልታም መልካም ዝማሬ ዘምሩ፤ 4.የእግዚአብሔር ቃል ቅን ነውና ሥራውም ሁሉ በእምነት ነውና። 5.ጽድቅንና ፍርድን ይወድዳል፤ የእግዚአብሔር ቸርነት ምድርን ሞላች። 6.በእግዚአብሔር ቃል ሰማዮች ጸኑ፥ ሠራዊታቸውም ሁሉ በአፉ እስትንፋስ፤ 7.የባሕርን ውኃ እንደ ረዋት የሚሰበስበው፥ ቀላዮችንም በመዝገቦች የሚያኖራቸው። 8.ምድር ሁሉ እግዚአብሔርን ትፍራው፥ በዓለም የሚኖሩ ሁሉም ከእርሱ የተነሣ ይደንግጡ። 9.እርሱ ተናግሮአልና፥ ሆኑም፤ እርሱ አዘዘ፥ ጸኑም። 10.እግዚአብሔር የአሕዛብን ምክር ያጠፋል፥ የአሕዛብንም አሳብ ይመልሳል። 11.የእግዚአብሔር ምክር ግን ለዘላለም ይኖራል። የልቡም አሳብ ለልጅ ልጅ ነው። 12.እግዚአብሔር አምላኩ የሚሆንለት ሕዝብ ምስጉን ነው፥ እርሱ ለርስቱ የመረጠው ሕዝብ። 13.እግዚአብሔር ከሰማይ ተመለከተ፥ የሰውንም ልጆች ሁሉ አየ። 14.ከማደሪያው ቦታ ሆኖ በምድር ወደሚኖሩ ሁሉ ተመለከተ፥ 15.እርሱ ብቻውን ልባቸውን የሠራ ሥራቸውንም ሁሉ የሚያስተውል። 16.ንጉሥ በሠራዊቱ ብዛት አይድንም ኃያልም በኃይሉ ብዛት አያመልጥም። 17.ፈረስም ከንቱ ነው፥ አያድንም፤ በኃይሉም ብዛት አያመልጥም። 18.እነሆ፥ የእግዚአብሔር ዓይኖች ወደሚፈሩት ናቸው፥ በምሕረቱም ወደሚታመኑ፥ 19.ነፍሳቸውን ከሞት ያድን ዘንድ፥ በራብም ጊዜ ይመግባቸው ዘንድ። 20.ነፍሳችን እግዚአብሔርን ተስፋ ታደርገዋለች፥ ረዳታችንና መጠጊያችን እርሱ ነውና። 21.ልባችን በእርሱ ደስ ይለዋልና፥ በቅዱስ ስሙም ታምነናልና። 22.አቤቱ፥ ምሕረትህ በላያችን ትሁን፥ በአንተ እንደ ታመንን።
ጻድቃን ሆይ፥ በእግዚአብሔር ደስ ይበላችሁ፤ ለቅኖች ምስጋና ይገባል። 2.እግዚአብሔርን በመሰንቆ አመስግኑት፥ አሥር አውታርም ባለው በበገና ዘምሩለት። 3.አዲስ ቅኔም ተቀኙለት፥ በእልልታም መልካም ዝማሬ ዘምሩ፤ 4.የእግዚአብሔር ቃል ቅን ነውና ሥራውም ሁሉ በእምነት ነውና። 5.ጽድቅንና ፍርድን ይወድዳል፤ የእግዚአብሔር ቸርነት ምድርን ሞላች። 6.በእግዚአብሔር ቃል ሰማዮች ጸኑ፥ ሠራዊታቸውም ሁሉ በአፉ እስትንፋስ፤ 7.የባሕርን ውኃ እንደ ረዋት የሚሰበስበው፥ ቀላዮችንም በመዝገቦች የሚያኖራቸው። 8.ምድር ሁሉ እግዚአብሔርን ትፍራው፥ በዓለም የሚኖሩ ሁሉም ከእርሱ የተነሣ ይደንግጡ። 9.እርሱ ተናግሮአልና፥ ሆኑም፤ እርሱ አዘዘ፥ ጸኑም። 10.እግዚአብሔር የአሕዛብን ምክር ያጠፋል፥ የአሕዛብንም አሳብ ይመልሳል። 11.የእግዚአብሔር ምክር ግን ለዘላለም ይኖራል። የልቡም አሳብ ለልጅ ልጅ ነው። 12.እግዚአብሔር አምላኩ የሚሆንለት ሕዝብ ምስጉን ነው፥ እርሱ ለርስቱ የመረጠው ሕዝብ። 13.እግዚአብሔር ከሰማይ ተመለከተ፥ የሰውንም ልጆች ሁሉ አየ። 14.ከማደሪያው ቦታ ሆኖ በምድር ወደሚኖሩ ሁሉ ተመለከተ፥ 15.እርሱ ብቻውን ልባቸውን የሠራ ሥራቸውንም ሁሉ የሚያስተውል። 16.ንጉሥ በሠራዊቱ ብዛት አይድንም ኃያልም በኃይሉ ብዛት አያመልጥም። 17.ፈረስም ከንቱ ነው፥ አያድንም፤ በኃይሉም ብዛት አያመልጥም። 18.እነሆ፥ የእግዚአብሔር ዓይኖች ወደሚፈሩት ናቸው፥ በምሕረቱም ወደሚታመኑ፥ 19.ነፍሳቸውን ከሞት ያድን ዘንድ፥ በራብም ጊዜ ይመግባቸው ዘንድ። 20.ነፍሳችን እግዚአብሔርን ተስፋ ታደርገዋለች፥ ረዳታችንና መጠጊያችን እርሱ ነውና። 21.ልባችን በእርሱ ደስ ይለዋልና፥ በቅዱስ ስሙም ታምነናልና። 22.አቤቱ፥ ምሕረትህ በላያችን ትሁን፥ በአንተ እንደ ታመንን።
ወደ ኤፌሶን ሰዎች
ምዕራፍ 5
እንግዲህ እንደ ተወደዱ ልጆች እግዚአብሔርን የምትከተሉ ሁኑ፥
2.ክርስቶስም ደግሞ እንደ ወደዳችሁ ለእግዚአብሔርም የመዓዛ ሽታ የሚሆንን መባንና መሥዋዕትን አድርጎ ስለ እናንተ ራሱን አሳልፎ እንደ ሰጠ በፍቅር ተመላለሱ። 3.ለቅዱሳን እንደሚገባ ግን ዝሙትና ርኵሰት ሁሉ ወይም መመኘት በእናንተ ዘንድ ከቶ አይሰማ፤ 4.የሚያሳፍር ነገርም የስንፍና ንግግርም ወይም ዋዛ የማይገቡ ናቸውና አይሁኑ፥ ይልቁን ምስጋና እንጂ። 5.ይህን እወቁ፤ አመንዝራም ቢሆን ወይም ርኵስ ወይም የሚመኝ እርሱም ጣዖትን የሚያመልክ በክርስቶስና በእግዚአብሔር መንግሥት ርስት የለውም። 6.ከዚህ የተነሣ በማይታዘዙት ልጆች ላይ የእግዚአብሔር ቁጣ ይመጣልና ማንም በከንቱ ንግግር አያታልላችሁ። 7.እንግዲህ ከእነርሱ ጋር ተካፋዮች አትሁኑ፤ 8.ቀድሞ ጨለማ ነበራችሁና፥ አሁን ግን በጌታ ብርሃን ናችሁ፤9 - 10.የብርሃኑ ፍሬ በበጎነትና በጽድቅ በእውነትም ሁሉ ነውና ለጌታ ደስ የሚያሰኘውን እየመረመራችሁ፥ እንደ ብርሃን ልጆች ተመላለሱ፤ 11.ፍሬም ከሌለው ከጨለማ ሥራ ጋር አትተባበሩ፥ ይልቁን ግለጡት እንጂ፥ 12.እነርሱ በስውር ስለሚያደርጉት መናገር እንኳ ነውር ነውና፤ 13.ሁሉ ግን በብርሃን ሲገለጥ ይታያል፤ የሚታየው ሁሉ ብርሃን ነውና። 14.ስለዚህ። አንተ የምትተኛ ንቃ ከሙታንም ተነሣ ክርስቶስም ያበራልሃል ይላል። 15.እንግዲህ እንደ ጥበበኞች እንጂ ጥበብ እንደሌላቸው ሳይሆን እንዴት እንድትመላለሱ በጥንቃቄ ተጠበቁ፤ 16.ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁ። 17.ስለዚህ የጌታ ፈቃድ ምን እንደ ሆነ አስተውሉ እንጂ ሞኞች አትሁኑ። 18.መንፈስ ይሙላባችሁ እንጂ በወይን ጠጅ አትስከሩ ይህ ማባከን ነውና፤ 19.በመዝሙርና በዝማሬ በመንፈሳዊም ቅኔ እርስ በርሳችሁ ተነጋገሩ፤ ለጌታ በልባችሁ ተቀኙና ዘምሩ፤ 20.ሁልጊዜ ስለ ሁሉ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አምላካችንንና አባታችንን ስለ ሁሉ አመስግኑ። 21.ለእያንዳንዳችሁ በክርስቶስ ፍርሃት የተገዛችሁ ሁኑ። 22.ሚስቶች ሆይ፥ ለጌታ እንደምትገዙ ለባሎቻችሁ ተገዙ፤ 23.ክርስቶስ ደግሞ የቤተ ክርስቲያን ራስ እንደ ሆነ እርሱም አካሉን የሚያድን እንደ ሆነ ባል የሚስት ራስ ነውና። 24.ዳሩ ግን ቤተ ክርስቲያን ለክርስቶስ እንደምትገዛ እንዲሁ ሚስቶች ደግሞ በሁሉ ለባሎቻቸው ይገዙ።
25 - 26.ባሎች ሆይ፥ ክርስቶስ ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳት ሚስቶቻችሁን ውደዱ፤ በውኃ መታጠብና ከቃሉ ጋር አንጽቶ እንዲቀድሳት ስለ እርስዋ ራሱን አሳልፎ ሰጠ፤ 27.እድፈት ወይም የፊት መጨማደድ ወይም እንዲህ ያለ ነገር ሳይሆንባት ቅድስትና ያለ ነውር ትሆን ዘንድ ክብርት የሆነችን ቤተ ክርስቲያን ለራሱ እንዲያቀርብ ፈለገ። 28.እንዲሁም ባሎች ደግሞ እንደ ገዛ ሥጋቸው አድርገው የገዛ ሚስቶቻቸውን ሊወዱአቸው ይገባቸዋል። የገዛ ሚስቱን የሚወድ ራሱን ይወዳል፤
29 - 30.ማንም የገዛ ሥጋውን የሚጠላ ከቶ የለምና፥ ነገር ግን የአካሉ ብልቶች ስለሆንን፥ ክርስቶስ ደግሞ ለቤተ ክርስቲያን እንዳደረገላት፥ ይመግበዋል ይከባከበውማል። 31.ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር ይተባበራል ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ። 32.ይህ ምሥጢር ታላቅ ነው፥ እኔ ግን ይህን ስለ ክርስቶስና ስለ ቤተ ክርስቲያን እላለሁ። 33.ሆኖም ከእናንተ ደግሞ እያንዳንዱ የገዛ ሚስቱን እንዲህ እንደ ራሱ አድርጎ ይውደዳት፥ ሚስቱም ባልዋን ትፍራ።