Skip to Content
የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን | YEHIWOT MELHEK BETEKIRSTIAN
የ2019 ዓ.ም የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ 📖 ዛሬን አንብብ →

የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን

Yehiwot Melhek Betekirstian

ሳምንት 6 · ቀን 26 (ሰኞ) 📅 Tikimt 9, 2019

ኦሪት ዘጸአት 16, 17, 18 · ወደ ኤፌሶን ሰዎች 4

📖 የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም፦ 1954 መጽሐፍ ቅዱስ አዲሱ መደበኛ ትርጒም

ኦሪት ዘጸአት

ምዕራፍ 16

መናና ድርጭት

1.መላው የእስራኤል ማኅበር ከግብጽ በወጡ በሁለተኛው ወር በዐሥራ ዐምስተኛው ቀን ከኤሊም ተነሥተው በኤሊምና በሲና መካከል ወደምትገኘው ወደ ሲና ምድረ በዳ መጡ። 2.በምድረ በዳውም መላው የእስራኤል ልጆች ማኅበር በሙሴና በአሮን ላይ አጕረመረሙ። 3.እስራኤላውያንም እነርሱን እንዲህ አሏቸው፣ “በሥጋ መቀቀያው ምንቸት ዙሪያ ተቀምጠን የፈለግነውን ያህል ምግብ መመገብ በምንችልበት በግብጽ ሳለን፣ ምነው በእግዚአብሔር እጅ ሞተን ባረፍነው ኖሮ! እናንተ ግን ይህ ሁሉ ጉባኤ በራብ እንዲያልቅ ወደዚህ ምድረ በዳ አመጣችሁን” አሏቸው። 4.ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን አለው፤ “ከሰማይ እንጀራ አዘንብላችኋለሁ። ሕዝቡም በየቀኑ እየወጡ ለዕለት የሚበቃቸውን ይሰብስቡ፤ በዚህም ትእዛዞቼን ይጠብቁ እንደ ሆነ እፈትናቸዋለሁ። 5.በስድስተኛው ቀን በሌሎቹ ዕለታት ከሚሰበስቡት ዕጥፍ ሰብስበው ያዘጋጁ።” 6.ስለዚህ ሙሴና አሮን ለእስራኤላውያን ሁሉ፣ እንዲህ አሉ፤ “ከግብጽ ምድር ያወጣችሁ እግዚአብሔር መሆኑን በዛሬዪቱ ምሽት ታውቃላችሁ። 7.በርሱ ላይ ያሰማችሁትን ማጕረምረም ሰምቷልና በማለዳ የእግዚአብሔርን ክብር ታያላችሁ፤ ለመሆኑ በእኛስ ላይ የምታጕረመርሙት እኛ ምንድን ነንና ነው?” አሏቸው። 8.ሙሴም ንግግሩን በመቀጠል፣ “በርሱ ላይ ማጕረምረማችሁን ሰምቷልና በምሽት የምትበሉትን ሥጋ፣ በማለዳም የምትፈልጉትን ያህል እንጀራ በሚሰጣችሁ ጊዜ እግዚአብሔር መሆኑን ታውቃላችሁ፤ እኛ ማን ነን? በእኛ ላይ አይደለም ያጕረመረማችሁት፤ በእግዚአብሔር ላይ ነው እንጂ” አላቸው። 9.ከዚያም ሙሴ አሮንን፣ “ ‘ማጕረምረማችሁን እርሱ ሰምቷልና ወደ እግዚአብሔር ፊት ቅረቡ’ ብለህ ለመላው የእስራኤል ማኅበር ተናገር” አለው። 10.አሮንም ለመላው የእስራኤል ማኅበር ሲናገር ሳለ ወደ ምድረ በዳው ተመለከቱ፤ በዚያም የእግዚአብሔር ክብር በደመናው ላይ ተገልጦ ይታይ ነበር። 11.እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 12.“የእስራኤላውያንን ማጕረምረም ሰምቻለሁ፤ ይህን ንገራቸው፤ ‘ፀሓይ ከመጥለቋ በፊት ሥጋ ትበላላችሁ፤ ሲነጋም እንጀራ ትበላላችሁ፤ ከዚያም እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ መሆኔን ታውቃላችሁ።’ ” 13.በዚያች ምሽት ድርጭቶች መጥተው ሰፈሩን አለበሱት፤ በነጋውም በሰፈሩ ዙሪያ ጤዛ ተኝቶበት ነበር። 14.ጤዛው ከረገፈ በኋላ በሜዳው ላይ ስስ የሆነ ዐመዳይ የሚመስል የተጋገረ ነገር በምድረ በዳው ላይ ታየ። 15.እስራኤላውያንም ይህን ባዩ ጊዜ ምን እንደ ሆነ ባለማወቃቸው እርስ በርሳቸው፣ “ይህ ነገር ምንድን ነው?” ተባባሉ።
ሙሴም፣ “ይህ ትበሉት ዘንድ እግዚአብሔር የሰጣችሁ እንጀራ ነው አላቸው።
16.እግዚአብሔር ያዘዘው ይህ ነው፤ ‘እያንዳንዱ የሚያስፈልገውን ያህል ይሰብስብ፤ በድንኳናችሁ ባለው ሰው ልክ ለእያንዳንዱ አንድ ጎሞር ውሰዱ’ ” ብሎ እግዚአብሔር አዝዟል። 17.እስራኤላውያንም እንደ ተነገራቸው አደረጉ፤ አንዳንዶች አብዝተው፣ አንዳንዶች ደግሞ አሳንሰው ሰበሰቡ። 18.የሰበሰቡትን በጎሞር በሰፈሩ ጊዜ፣ ብዙ የሰበሰበ አላተረፈም፤ ጥቂትም የሰበሰበ አልጐደለበትም፤ እያንዳንዱ የሰበሰበው የሚያስፈልገውን ያህል ሆነ። 19.ሙሴም፣ “ማንም ከዚህ ለነገ ምንም ማስተረፍ የለበትም” አላቸው። 20.ሆኖም ግን አንዳንዶቹ ሙሴ የተናገረውን ቸል በማለት ከሰበሰቡት ውስጥ ከፊሉን አስተርፈው አሳደሩ፤ በማግስቱም ጧት ተልቶ መሽተት ጀመረ፤ ስለዚህ ሙሴ ተቈጣቸው። 21.በየማለዳው እያንዳንዱ የሚያስፈልገውን ያህል ሰበሰበ፤ ፀሓዩ እየበረታ በሄደም ጊዜ ቀለጠ። 22.በስድስተኛው ቀን ለእያንዳንዱ ሰው ሁለት ሁለት ጎሞር አድርገው ዕጥፍ ሰበሰቡ፤ የማኅበሩም አለቆች ወደ ሙሴ መጥተው ይህንኑ ነገሩት። 23.እርሱም አላቸው፤ “እግዚአብሔር ያዘዘው ይህ ነው፤ ‘ነገ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ሰንበት በመሆን፣ የዕረፍት ቀን ይሆናል።’ ስለዚህ መጋገር የምትፈልጉትን ጋግሩ፤ መቀቀል የምትፈልጉትን ቀቅሉ። የተረፈውን አስቀምጡ፤ እስከ ጧትም ድረስ አቈዩት።” 24.ስለዚህ ሙሴ እንዳዘዘው እስከ ጧት ድረስ አቈዩት፤ አልሸተተም፤ ወይም አልተላም። 25.ሙሴም እንዲህ አለ፤ “ዛሬውኑ ብሉት፤ ዛሬ የእግዚአብሔር ሰንበት ነውና። ዛሬ በመሬት ላይ ምንም አታገኙም። 26.ስድስት ቀን ትሰበስቡታላችሁ፤ በሰባተኛው ቀን በሰንበት ዕለት ግን ምንም ነገር አይኖርም።” 27.ሆኖም አንዳንዶቹ በሰባተኛው ቀን ለመሰብሰብ ወጡ፤ ነገር ግን ምንም አላገኙም። 28.ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን አለው፤ “ትእዛዞቼንና መመሪያዎቼን ለመፈጸም እስከ መቼ እንቢ ትላላችሁ? 29.እግዚአብሔር ሰንበትን የሰጣችሁ መሆኑን ልብ በሉ፤ በስድስተኛው ቀን ለሁለት ቀን የሚሆን እንጀራ የሰጣችሁ ለዚህ ነው። በሰባተኛው ቀን እያንዳንዱ ሰው ባለበት ይቈይ፤ ማንም አይወጣም።” 30.ስለዚህ ሕዝቡም በሰባተኛው ቀን ዐረፉ። 31.የእስራኤልም ሕዝብ ምግቡን መና አሉት፤ እርሱም እንደ ድንብላል ዘር ነጭ፣ ጣሙም ከማር እንደ ተጋገረ ቂጣ ነበር። 32.ሙሴም አለ፤ “እግዚአብሔር ያዘዘን ይህ ነው፤ ‘ከግብጽ ባወጣኋችሁ ጊዜ በምድረ በዳ እንድትበሉ የሰጠኋችሁን እንጀራ ያዩ ዘንድ አንድ ጎሞር መና ወስደህ ለሚመጡት ትውልዶች አቈየው።’ ” 33.ስለዚህ ሙሴ አሮንን፣ “አንድ ማሰሮ ወስደህ አንድ ጎሞር መና አስቀምጥበት፤ ለሚመጡት ትውልዶች እንዲቈይም በእግዚአብሔር ፊት አስቀምጠው” አለው። 34.እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው አሮን፣ መናው ይጠበቅ ዘንድ በምስክሩ ፊት አስቀመጠው። 35.እስራኤላውያን ወደ መኖሪያቸው ምድር እስኪመጡ ድረስ ለአርባ ዓመት መና በሉ፤ ወደ ከነዓን ድንበር እስከሚደርሱ ድረስ መና በሉ። 36.አንድ ጎሞር የኢፍ መስፈሪያ አንድ ዐሥረኛ ነው።

ምዕራፍ 17

ከዐለት የፈለቀ ውሃ

1.መላው የእስራኤል ማኅበር ከሲና ምድረ በዳ ተነሥቶ እግዚአብሔር እንዳዘዘው ከስፍራ ወደ ስፍራ ተጕዞ በራፊዲም ሰፈረ፤ ነገር ግን ሕዝቡ የሚጠጡት ውሃ አልነበረም። 2.ስለዚህ፣ “የምንጠጣውን ውሃ ስጠን” በማለት ሙሴን ተጣሉት።
ሙሴም፣ “እኔን ለምን ትጣሉኛላችሁ? እግዚአብሔርንስ ለምን ትፈታተኑታላችሁ?” አለ።
3.ነገር ግን ሕዝቡ በዚያ ተጠምተው ስለ ነበር፣ በሙሴ ላይ አጕረመረሙ። እነርሱም፣ “እኛና ልጆቻችን እንዲሁም ከብቶቻችን በውሃ ጥም እንድናልቅ፣ ከግብጽ ለምን አወጣኸን?” አሉት። 4.ከዚያም ሙሴ፤ “በዚህ ሕዝብ ምን ላድርግ? በድንጋይ ሊወግሩኝ ተዘጋጅተዋል” ብሎ ወደ እግዚአብሔር ጮኸ። 5.እግዚአብሔር ለሙሴ እንዲህ መለሰለት፤ “ከሕዝቡ ፊት ሂድ፤ ከእስራኤል አለቆች አንዳንዶቹን እንዲሁም አባይን የመታህባትን በትር ያዝና ሂድ። 6.ኮሬብ አጠገብ ባለው ዐለት በዚያ እኔ በአንተ ፊት እቆማለሁ። ዐለቱን ምታው፤ ከርሱም ሕዝቡ የሚጠጡት ውሃ ይወጣል።” ስለዚህ ሙሴ በእስራኤል አለቆች ፊት ይህንኑ አደረገ። 7.ስፍራውንም ማሳህና መሪባ ብሎ ጠራው፤ እስራኤላውያን ጠብ ፈጥረው፣ “እግዚአብሔር ከእኛ ጋራ ነው ወይስ አይደለም” በማለት እግዚአብሔርን ተፈታትነዋልና።

አማሌቃውያን ተሸነፉ

8.አማሌቃውያን መጥተው እስራኤላውያንን ራፊዲም ላይ ወጉ፤ 9.ሙሴም ኢያሱን፣ “ከሰዎቻችን አንዳንዶቹን ምረጥና አማሌቃውያንን ለመውጋት ውጣ፤ በነገው ዕለት የእግዚአብሔርን በትር በእጆቼ ይዤ በኰረብታው ጫፍ ላይ እቆማለሁ።” 10.ስለዚህ ኢያሱ ሙሴ ባዘዘው መሠረት ከአማሌቃውያን ጋራ ተዋጋ፤ ሙሴ፣ አሮንና ሖርም ወደ ኰረብታው ጫፍ ወጡ። 11.ሙሴ እጆቹን ወደ ላይ በሚያነሣበት ጊዜ ሁሉ እስራኤላውያን ድል ያደርጉ ነበር። እጆቹን ባወረደ ጊዜ ግን አማሌቃውያን ያሸንፉ ነበር። 12.የሙሴ እጆች እየዛሉ በሄዱ ጊዜ ድንጋይ ወስደው ከበታቹ አደረጉ፤ እርሱም ተቀመጠበት፤ አሮንና ሖርም አንዱ በአንዱ በኩል ሌላውም በሌላ በኩል ሆነው እጆቹን ወደ ላይ ያዙ። ይኸውም እጆቹ ፀሓይ እስክትጠልቅ ድረስ ጸንተው እንዲቈዩ ነው። 13.ስለዚህ ኢያሱ የአማሌቃውያንን ሰራዊት በሰይፍ ድል አደረገ። 14.ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን፣ “ሲታወስ እንዲኖር ይህን በጥቅልል መጽሐፍ ላይ ጻፈው፤ ኢያሱም መስማቱን አረጋግጥ፤ ምክንያቱም የአማሌቃውያንን ዝክር ከሰማይ በታች ፈጽሜ እደመስሳለሁ” አለው። 15.ሙሴም መሠዊያውን ሠርቶ፣ “እግዚአብሔር ዐርማዬ ነው” ብሎ ሰየመው። 16.“እጆች ወደ እግዚአብሔር ዙፋን ተዘርግተዋልና፤ እግዚአብሔር አማሌቃውያንን ከትውልድ እስከ ትውልድ ይዋጋቸዋል” አለ።

ምዕራፍ 18

ዮቶር ወደ ሙሴ መጣ

1.የምድያም ካህን የሙሴ ዐማት ዮቶር፣ እግዚአብሔር ለሙሴና ለሕዝቡ ለእስራኤል ያደረገላቸውን ሁሉ እንዲሁም እግዚአብሔር እስራኤልን ከግብጽ እንዴት እንዳወጣቸው ሰማ። 2.ሙሴ ሚስቱን ሲፓራን ከመለሳት በኋላ ዐማቱ ዮቶር እርሷንና ሁለት ወንድ ልጆቿን ተቀብሏቸው ነበር። 3.ሙሴ፣ “በባዕድ አገር መጻተኛ ነኝ” ለማለት የመጀመሪያ ልጁን ስም ጌርሳም አለው። 4.“የአባቴ አምላክ ረዳቴ ነው፤ ከፈርዖን ሰይፍ አድኖኛልና” ለማለት ደግሞ ሁለተኛውን ልጁን አልዓዛር አለው። 5.የሙሴ ዐማት ዮቶር ከሙሴ ወንድ ልጆችና ሚስት ጋራ ሆኖ በምድረ በዳ ከእግዚአብሔር ተራራ አጠገብ ወደ ሰፈረበት ወደ ሙሴ መጣ። 6.ዮቶር ወደ ሙሴ፣ “እኔ ዐማትህ ዮቶር፣ ከሚስትህና ከሁለት ወንዶች ልጆቿ ጋራ እየመጣን ነው” ሲል መልእክት ላከበት። 7.ስለዚህ ሙሴ ዐማቱን ሊቀበለው ወጣ፤ ዝቅ ብሎ እጅ በመንሣትም ሳመው፤ ከዚያም ሰላምታ ተለዋውጠው ወደ ድንኳኑ ገቡ። 8.ሙሴም እግዚአብሔር ለእስራኤል ሲል በፈርዖንና በግብጻውያን ላይ ያደረገውን ሁሉ፣ በመንገድም ላይ ስላጋጠማቸው መከራ ሁሉና እግዚአብሔርም እንዴት እንዳዳናቸው ለዐማቱ ነገረው። 9.ዮቶርም እግዚአብሔር እነርሱን ከግብጻውያን እጅ በመታደግ ለእስራኤል ያደረገውን በጎ ነገር ሁሉ በመስማቱ ተደሰተ። 10.እንዲህም አለ፤ “ከግብጻውያን እጅና ከፈርዖን ለታደጋችሁ፣ ከግብጻውያን እጅ ሕዝቡን ለታደገ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን። 11.እግዚአብሔር ከአማልክት ሁሉ በላይ ኀያል እንደ ሆነ አሁን ዐወቅሁ፤ እስራኤልን በትዕቢት ይዘው በነበሩት ሁሉ ላይ ይህን አድርጓልና።” 12.ከዚያም የሙሴ ዐማት ዮቶር የሚቃጠል መሥዋዕትና ሌሎች መሥዋዕቶች ለእግዚአብሔር አቀረበ፤ አሮንም ከሙሴ ዐማት ጋራ በእግዚአብሔር ፊት እንጀራ ለመብላት ከእስራኤል አለቆች ሁሉ ጋራ መጣ። 13.በማግስቱም ሙሴ ሕዝቡን ለመዳኘት ተቀመጠ፤ እነርሱም በዙሪያው ከጧት እስከ ማታ ድረስ ቆሙ። 14.ዐማቱም ሙሴ ለሕዝቡ የሚያደርገውን ሁሉ ባየ ጊዜ፣ “ምን ማድረግህ ነው? እነዚህ ሁሉ ሰዎች ከጧት እስከ ማታ በዙሪያህ ቆመው ሳለ፣ ብቻህን በፍርድ ወንበር ላይ ለምን ትቀመጣለህ?” አለው። 15.ሙሴም እንዲህ ብሎ መለሰለት፤ “ምክንያቱም ሰዎቹ የእግዚአብሔር ፈቃድ በመፈለግ ወደ እኔ ይመጣሉ። 16.ክርክር በኖራቸው ቍጥር ጕዳያቸው ወደ እኔ ይመጣል፤ ለግራና ለቀኙ የሚሆነውን እኔ ወስኜ የእግዚአብሔርን ሥርዐትና ሕጎች እነግራቸዋለሁ።” 17.የሙሴ ዐማት መልሶ እንዲህ አለው። “የምትሠራው መልካም አይደለም። 18.አንተና ወደ አንተ የሚመጡት እነዚህ ሰዎች የምታደርጉት ነገር ቢኖር ራሳችሁን ማድከም ነው፤ ሥራው ለአንተ ከባድ ሸክም ነው፤ ብቻህን ልትወጣው አትችልም። 19.ምክር እሰጥሃለሁና አሁን እኔን ስሙኝ፤ እግዚአብሔር ከአንተ ጋራ ይሁን። አንተ በእግዚአብሔር ፊት ሕዝብን የምትወክል መሆን አለብህ፤ ክርክራቸውን ወደ እርሱ ታቀርባለህ። 20.ሥርዐቶቹንና ሕጎቹን አስተምራቸው፤ እንዴት መኖር እንዳለባቸውና ምን መሥራት እንደሚገባቸው አሳያቸው። 21.ነገር ግን ችሎታ ያላቸውን ሰዎች ከሕዝቡ ሁሉ ምረጥ፤ እነዚህም ሰዎች እግዚአብሔርን የሚፈሩ፣ ታማኞችና በማታለል የሚገኘውን ጥቅም የሚጸየፉ ይሁኑ። የሺሕ፣ የመቶ፣ የዐምሳ፣ የዐሥር፣ አለቃ አድርገህ ሹማቸው። 22.በማንኛውም ጊዜ ሕዝቡን ይዳኙ፤ ቀላሉን ነገር እነርሱ ይወስኑ፤ አስቸጋሪ የሆነውን ጕዳይ ሁሉ ግን ለአንተ እንዲያቀርቡ አድርግ፤ ሥራውን ስለሚያግዙህ ሸክምህ ይቃለላል። 23.አንተ ይህን ብታደርግና እግዚአብሔርም ይህንኑ ቢያዝዝህ፣ ድካምህን መቋቋም ትችላለህ፤ እነዚህም ሰዎች ሁሉ ረክተው ወደ ቤታቸው ይሄዳሉ።” 24.ሙሴ ዐማቱን ሰማ፤ ያለውንም ሁሉ ፈጸመ። 25.ሙሴም ከእስራኤል መካከል ችሎታ ያላቸውን ሰዎች መረጠና፤ የሕዝብ መሪዎች፣ በሺሕዎች፣ በመቶዎች፣ በዐምሳዎች በዐሥሮች ላይም አለቆች አደረጋቸው። 26.ሁልጊዜም የሕዝብ ዳኞች ሆነው አገለገሉ፤ አስቸጋሪ ጕዳዮችን ወደ ሙሴ አመጡ፤ ቀላል የሆነውን ራሳቸው ወሰኑ። 27.ከዚያም ሙሴ ዐማቱን በጕዞው ሸኘው፤ ዮቶርም ወደ አገሩ ተመለሰ።

ወደ ኤፌሶን ሰዎች

ምዕራፍ 4

በክርስቶስ አካል ያለ አንድነት

1.እንግዲህ በጌታ እስረኛ የሆንሁ እኔ፣ ለተቀበላችሁት ጥሪ የሚገባ ኑሮ ትኖሩ ዘንድ እለምናችኋለሁ። 2.ፍጹም ትሑታንና ገሮች ሁኑ፤ እርስ በርሳችሁም በፍቅር እየተቻቻላችሁ ትዕግሥተኞች ሁኑ። 3.በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ። 4.በተጠራችሁ ጊዜ ወደ አንድ ተስፋ እንደ ተጠራችሁ ሁሉ አንድ አካልና አንድ መንፈስ አለ፤ 5.አንድ ጌታ፣ አንድ እምነትና አንድ ጥምቀት አለ፤ 6.ከሁሉም በላይ የሆነ፣ በሁሉም የሚሠራ፣ በሁሉ የሚኖር የሁሉም አባት የሆነ አንድ አምላክ አለ። 7.ነገር ግን ክርስቶስ በወሰነው መጠን ለእያንዳንዳችን ጸጋ ተሰጥቶናል። 8.ስለዚህም እንዲህ ይላል፤
“ወደ ላይ በወጣ ጊዜ፣
ምርኮን ማረከ፤
ለሰዎችም ስጦታን ሰጠ።”
9.ታዲያ፣ “ወደ ላይ ወጣ” ማለት ደግሞ ወደ ምድር ታችኛው ክፍል ወረደ ማለት ካልሆነ በቀር ምን ማለት ነው? 10.ወደ ታች የወረደውም፣ መላውን ፍጥረተ ዓለም ይሞላ ዘንድ ከሰማያት ሁሉ በላይ የወጣው እርሱ ራሱ ነው። 11.አንዳንዶቹ ሐዋርያት፣ አንዳንዶቹ ነቢያት፣ አንዳንዶቹም ወንጌል ሰባኪዎች፣ ሌሎቹ ደግሞ እረኞችና አስተማሪዎች ይሆኑ ዘንድ የሰጠ እርሱ ነው፤ 12.ይኸውም የክርስቶስ አካል ይገነባ ዘንድ፣ ቅዱሳንን ለአገልግሎት ሥራ ለማዘጋጀት ሲሆን፣ 13.ይህም የሚሆነው፣ ሁላችንም የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኘው አንድነት በመምጣትና ሙሉ ሰው በመሆን፣ በክርስቶስ ወዳለው ፍጹምነት ደረጃ እስከምንደርስ ነው። 14.ከእንግዲህ በማዕበል ወደ ፊትና ወደ ኋላ እየተነዳን፣ በልዩ ልዩ ዐይነት የትምህርት ነፋስ፣ በሰዎችም ረቂቅ ተንኰልና ማታለል ወዲያና ወዲህ እየተንገዋለልን ሕፃናት አንሆንም። 15.ይልቁንም እውነትን በፍቅር እየተናገርን፣ ራስ ወደ ሆነው ወደ እርሱ በነገር ሁሉ እናድጋለን፤ እርሱም ክርስቶስ ነው። 16.ከርሱም የተነሣ፣ አካል ሁሉ በሚያገናኘው ጅማት እየተያያዘና እየተጋጠመ፣ እያንዳንዱ ክፍል የራሱን ሥራ እያከናወነ በፍቅር ያድጋል፤ ራሱንም ያንጻል።

እንደ ብርሃን ልጆች መኖር

17.ስለዚህ ይህን እነግራችኋለሁ፤ በጌታም ዐደራ እላለሁ፤ በአስተሳሰባቸው ከንቱነት እንደሚኖሩት እንደ አሕዛብ ልትመላለሱ አይገባም። 18.እነርሱ ከልባቸው መደንደን የተነሣ ስለማያስተውሉ ልቡናቸው ጨልሟል፤ ከእግዚአብሔርም ሕይወት ተለይተዋል። 19.ኅሊናቸው ስለ ደነዘዘ በማይረካ ምኞት፣ በርኩሰት ሁሉ እንዳሻቸው ለመኖር ቅጥ ለሌለው ብልግና ራሳቸውን አሳልፈው ሰጥተዋል። 20.እናንተ ግን ክርስቶስን ያወቃችሁት እንደዚህ ባለ መንገድ አይደለም፤ 21.በርግጥ ስለ እርሱ ሰምታችኋል፤ በኢየሱስም እንዳለው እውነት በርሱ ተምራችኋል። 22.ቀድሞ ስለ ነበራችሁበት ሕይወትም፣ በሚያታልል ምኞቱ የጐደፈውን አሮጌ ሰውነታችሁን አውልቃችሁ እንድትጥሉ ተምራችኋል፤ 23.ደግሞም በአእምሯችሁ መንፈስ እንድትታደሱ፣ 24.እውነተኛ በሆነው ጽድቅ እንዲሁም ቅድስና እግዚአብሔርን እንዲመስል የተፈጠረውን አዲሱን ሰው እንድትለብሱ ነው። 25.ስለዚህ ውሸትን አስወግዳችሁ፣ እያንዳንዳችሁ ከባልንጀራችሁ ጋራ እውነትን ተነጋገሩ፤ ሁላችንም የአንድ አካል ብልቶች ነንና። 26.“ተቈጡ፤ ነገር ግን ኀጢአት አትሥሩ፤” በቍጣችሁ ላይ ፀሓይ አይግባ፤ 27.ለዲያብሎስም ስፍራ አትስጡት። 28.ይሰርቅ የነበረ ከእንግዲህ አይስረቅ፤ ነገር ግን ለተቸገሩት የሚያካፍለው ነገር እንዲኖረው በገዛ እጆቹ በጎ የሆነውን እየሠራ ለማግኘት ይድከም። 29.እንደ አስፈላጊነቱ ሌሎችን የሚያንጽና ሰሚዎችን የሚጠቅም ቃል እንጂ የማይረባ ቃል ከአፋችሁ አይውጣ። 30.ለቤዛ ቀን የታተማችሁበትን ቅዱሱን የእግዚአብሔር መንፈስ አታሳዝኑ። 31.መራርነትን ሁሉ፣ ቍጣና ንዴትን፣ ጭቅጭቅና ስድብን ከማንኛውም ክፋት ጋራ ከእናንተ ዘንድ አስወግዱ። 32.እግዚአብሔር በክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ፣ እናንተም ይቅር ተባባሉ፤ እርስ በርሳችሁ ቸሮችና ርኅሩኆች ሁኑ።