Skip to Content
የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን | YEHIWOT MELHEK BETEKIRSTIAN
የ2019 ዓ.ም የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ 📖 ዛሬን አንብብ →

የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን

Yehiwot Melhek Betekirstian

ሳምንት 4 · ቀን 19 (ሐሙስ) 📅 Meskerem 28, 2019

ኦሪት ዘፍጥረት 47, 48 · መዝሙረ ዳዊት 25 · ወደ ገላትያ ሰዎች 3

📖 የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም፦ 1954 መጽሐፍ ቅዱስ አዲሱ መደበኛ ትርጒም

ኦሪት ዘፍጥረት

ምዕራፍ 47

1.ዮሴፍም ወደ ፈርዖን ሄዶ፣ “አባቴና ወንድሞቼ በጎቻቸውን፣ ፍየሎቻቸውን እንዲሁም ያላቸውን ሁሉ ይዘው ከከነዓን አገር መጥተው በጌሤም ሰፍረዋል” አለው። 2.ከወንድሞቹም መካከል ዐምስቱን መርጦ፣ ፈርዖን ፊት አቀረባቸው። 3.ፈርዖን የዮሴፍን ወንድሞች፣ “ሥራችሁ ምንድን ነው?” ሲል ጠየቃቸው።
እነርሱም ፈርዖንን፣ “እኛ አገልጋዮችህ ልክ እንደ አባቶቻችን ከብት አርቢዎች ነን” አሉት፤
4.ደግሞም፣ “በከነዓን ምድር ራቡ እጅግ የጸና በመሆኑ በጎችና ፍየሎች የሚሰማሩበት በማጣታቸው፣ ለጊዜው እዚህ ለመኖር መጥተናል፤ አሁንም ባሮችህ በጌሤም ምድር እንድንኖር እንድትፈቅድልን እንለምንሃለን” አሉት። 5.ፈርዖንም ዮሴፍን እንዲህ አለው፤ “አባትህና ወንድሞችህ ወደ አንተ መጥተዋል፤ 6.የግብጽ ምድር እንደ ሆነ በእጅህ ነው፤ አባትህንና ወንድሞችህን ምርጥ በሆነው ምድር አስፍራቸው፤ በጌሤም ይኑሩ። ከመካከላቸው ልዩ ችሎታ ያላቸው መኖራቸውን የምታውቅ ከሆነ፣ የከብቶቼ ኀላፊዎች አድርጋቸው።” 7.ከዚህ በኋላ ዮሴፍ አባቱን ያዕቆብን ቤተ መንግሥት አስገብቶ በፈርዖን ፊት አቀረበው፤ ያዕቆብም ፈርዖንን ከመረቀው በኋላ 8.ፈርዖን፣ “ለመሆኑ ዕድሜህ ምን ያህል ነው?” ሲል ያዕቆብን ጠየቀው። 9.ያዕቆብም ለፈርዖን፣ “በምድር ላይ በእንግድነት ያሳለፍሁት ዘመን
130 ዓመት ነው፤ ይህም አባቶቼ በእንግድነት ከኖሩበት ዘመን ጋራ ሲነጻጸር ዐጭር ነው፤ ችግር የበዛበትም ነበር” ሲል መለሰለት።
10.ከዚያም ያዕቆብ ፈርዖንን መርቆ፣ ተሰናብቶት ወጣ። 11.ዮሴፍም አባቱንና ወንድሞቹን በግብጽ እንዲኖሩ አደረገ፤ ፈርዖን በሰጠውም ትእዛዝ መሠረት ምርጥ ከሆነው ምድር ራምሴን በርስትነት ሰጣቸው። 12.ዮሴፍም ለአባቱ፣ ለወንድሞቹና ለመላው የአባቱ ቤተ ሰዎች በልጆቻቸው ቍጥር ልክ ቀለብ እንዲሰፈርላቸው አደረገ።

የራቡ ዘመንና የዮሴፍ አመራር

13.በመላው ምድር እህል ባለመኖሩ ራቡ እየጸና ሄደ፤ ከዚህ የተነሣም ግብጽና ከነዓን በራብ እጅግ ተጐዱ፤ 14.ዮሴፍ የግብጽና የከነዓን ሰዎች እህል በመሸመት የከፈሉትን ገንዘብ ሁሉ ሰብስቦ ወደ ፈርዖን ቤተ መንግሥት አስገባ። 15.የግብጽና የከነዓን ሕዝቦችም ገንዘባቸው ባለቀ ጊዜ፣ ግብጻውያን ሁሉ ወደ ዮሴፍ ቀርበው፣ “የምንበላው እህል ስጠን፤ ገንዘባችን ዐልቆብናል፤ ዐይንህ እያየ እንዴት በራብ እንለቅ?” አሉት። 16.ዮሴፍም፣ “ከብቶቻችሁን አምጡ፤ ገንዘባችሁ ካለቀ በከብቶቻችሁ ለውጥ እህል እሰጣችኋለሁ” አለ። 17.ስለዚህ ከብቶቻቸውን ወደ ዮሴፍ አመጡ፤ እርሱም በፈረሶቻቸው፣ በበጎቻቸው፣ በፍየሎቻቸው፣ በከብቶቻቸውና በአህዮቻቸው ለውጥ እህል ሰጣቸው። በከብቶቻቸው ልዋጭ ባገኙት ምግብ የዚያን ዓመት ራብ እንዲወጡት አደረገ። 18.ያም ዓመት ካለፈ በኋላ ሕዝቡ በሚቀጥለው ዓመት ወደ ዮሴፍ መጥተው እንዲህ አሉት፣ “እንግዲህ ከጌታችን የምንሰውረው ምንም ነገር የለም፤ ገንዘባችን ዐልቋል፤ ከብቶቻችንንም አስረክበንሃል፤ እንግዲህ ለጌታችን የምንሰጠው፣ ከመሬታችንና ከእኛ ከራሳችን በቀር አንዳች ነገር የለም። 19.ታዲያ፣ እያየኸን እንዴት እንለቅ? መሬታችንስ ለምን ጠፍ ሆኖ ይቅር? እኛንና መሬታችንን ውሰድና በለውጡ እህል ስጠን፤ እኛ የፈርዖን ገባሮች እንሁን፤ መሬታችንም የርሱ ርስት ይሁን፤ እኛም እንዳንሞት መሬታችንም ጠፍ ሆኖ እንዳይቀር የምንዘራው ዘር ስጠን።” 20.ስለዚህ ዮሴፍ የግብጽን ምድር ሁሉ ለፈርዖን ገዛለት፤ ራቡም እጅግ ስለ ጸናባቸው ግብጻውያን ሁሉ አንዳቸውም ሳይቀሩ መሬታቸውን ሸጡ፤ ምድሪቱም የፈርዖን ርስት ሆነች። 21.ዮሴፍም የግብጽን ሕዝብ ከዳር እስከ ዳር የፈርዖን ገባር አደረገው። 22.ሆኖም ዮሴፍ የካህናቱን መሬት አልገዛም፤ ምክንያቱም ካህናቱ ከፈርዖን ቋሚ ድርጎ ስለሚያገኙና ፈርዖን ከሚሰጣቸው ድርጎ በቂ ምግብ ስለ ነበራቸው ነው፤ ከዚህም የተነሣ መሬታቸውን አልሸጡም። 23.ዮሴፍ ሕዝቡን እንዲህ አላቸው፤ “እነሆ፣ ዛሬ እናንተንም መሬታችሁንም ለፈርዖን ገዝቻችኋለሁና ይህን ዘር ወስዳችሁ በመሬት ላይ ዝሩ። 24.መከሩ በሚሰበሰብበት ጊዜ ግን ከዐምስት እጅ አንዱን ለፈርዖን ታስገባላችሁ፤ ከዐምስት እጅ አራቱን ደግሞ ለመሬታችሁ ዘር፣ እንዲሁም ለራሳችሁ፣ ለቤተ ሰቦቻችሁና ለልጆቻችሁ ምግብ ታደርጉታላችሁ።” 25.እነርሱም፣ “እንግዲህ ሕይወታችንን አትርፈህልናል፤ በጌታችን ፊት ሞገስ ካገኘን፣ ለፈርዖን ገባሮች እንሆናለን” አሉት። 26.ስለዚህ ዮሴፍ የምርቱ አንድ ዐምስተኛ ለፈርዖን እንዲገባ የሚያዝዝ የመሬት ሕግ በግብጽ አወጣ፤ ይህም ሕግ እስከ ዛሬ ይሠራበታል። በዚያ ጊዜ በፈርዖን እጅ ያልገባው መሬት የካህናቱ ብቻ ነበር። 27.በዚህ ጊዜ እስራኤላውያን በግብጽ አገር በጌሤም ይኖሩ ነበር፤ በዚያም ሀብት ንብረት ዐፈሩ፤ ቍጥራቸውም እጅግ እየበዛ ይሄድ ጀመር። 28.ያዕቆብ በግብጽ ዐሥራ ሰባት ዓመት ኖረ፤ ዕድሜውም አንድ መቶ አርባ ሰባት ዓመት ነበር። 29.እስራኤልም የሚሞትበት ጊዜ መቃረቡን እንደ ተረዳ ልጁን ዮሴፍን አስጠርቶ እንዲህ አለው፤ “በአንተ ዘንድ ሞገስ ካገኘሁ እጅህን በጭኔ ላይ አኑረህ፣ በጎነትንና ታማኝነትን ልታደርግልኝ ቃል ግባልኝ፤ በምሞትበት ጊዜ በግብጽ አትቅበረኝ፤ 30.እኔም ከአባቶቼ ጋራ ሳንቀላፋ፣ ከግብጽ አውጥተህ እነርሱ በተቀበሩበት ቦታ ቅበረኝ።”
ዮሴፍም፣ “ዕሺ፣ እንዳልከኝ አደርጋለሁ” አለ።
31.ያዕቆብም፣ “በል ማልልኝ” አለው። ዮሴፍም ማለለት፤ እስራኤልም በዐልጋው ራስጌ ላይ ሆኖ ጐንበስ አለ።

ምዕራፍ 48

ምናሴና ኤፍሬም

1.ከጥቂት ጊዜ በኋላም፣ “አባትህ ታሟል” ተብሎ ለዮሴፍ ስለ ተነገረው ሁለቱን ልጆቹን ምናሴንና ኤፍሬምን ይዞ ሄደ። 2.ለያዕቆብ፣ “ልጅህ ዮሴፍ ወደ አንተ መጥቷል” ተብሎ በተነገረው ጊዜ፣ እስራኤል ተበረታትቶ ዐልጋው ላይ ተቀመጠ። 3.ያዕቆብም ዮሴፍን እንዲህ አለው፤ “ሁሉን ቻይ አምላክ በከነዓን ምድር ሎዛ በምትባል ቦታ ተገለጠልኝ፤ ባረከኝም፤ 4.እንዲህም አለኝ፤ ‘ፍሬያማ አደርግሃለሁ፣ አበዛሃለሁ፣ ለብዙ ሕዝብም ጉባኤ አደርግሃለሁ፤ ይህችንም ምድር ከአንተ በኋላ ለሚነሡ ዘሮችህ የዘላለም ርስት አድርጌ እሰጣቸዋለሁ።’ 5.“ወደዚህ ከመምጣቴ በፊት በግብጽ የወለድሃቸው ሁለቱ ልጆችህ ከእንግዲህ የእኔ ልጆች ሆነው ይቈጠራሉ፤ ሮቤልና ስምዖን ልጆቼ እንደ ሆኑ ሁሉ፣ ኤፍሬምና ምናሴም ልጆቼ ይሆናሉ። 6.ከእነርሱ በኋላ የሚወለዱልህ ልጆች ግን፣ የአንተ ይሁኑ፤ በርስት ድልድላቸው ግን በወንድሞቻቸው ስም ይቈጠራሉ። 7.ከሰሜን ምዕራብ መስጴጦምያ መልስ ኤፍራታ ለመድረስ ጥቂት ሲቀረኝ፣ እናትህ ራሔል በከነዓን ምድር ሞታብኝ ዐዘንሁ። እኔም ወደ ኤፍራታ ማለት ወደ ቤተ ልሔም በሚወስደው መንገድ ዳር ቀበርኋት።” 8.እስራኤልም የዮሴፍን ልጆች ባየ ጊዜ፣ “እነዚህ እነማን ናቸው?” ሲል ጠየቀ። 9.ዮሴፍም፣ “እነዚህ እግዚአብሔር የሰጠኝ ልጆች ናቸው” ብሎ ለአባቱ መለሰለት።
እስራኤልም፣ “አቅርባቸውና ልመርቃቸው” አለ።
10.በዚህ ጊዜ እስራኤል ዐይኖቹ በእርጅና ምክንያት በመድከማቸው አጥርቶ ማየት ይሳነው ነበር፤ ስለዚህ ዮሴፍ ልጆቹን አባቱ ዘንድ አቀረባቸው፤ አባቱም ስሞ ዐቀፋቸው። 11.እስራኤልም ዮሴፍን፣ “ዐይንህን እንደ ገና አያለሁ ብዬ አላሰብኩም ነበር፤ እግዚአብሔር ግን ልጆችህን ጭምር ለማየት አበቃኝ” አለው። 12.ዮሴፍም ልጆቹን ከእስራኤል ጕልበት ፈቀቅ በማድረግ አጐንብሶ በግንባሩ መሬት ላይ ተደፋ። 13.ከዚያም ዮሴፍ ሁለቱን ልጆቹን ይዞ ኤፍሬምን ከራሱ በስተቀኝ፣ ከእስራኤል በስተግራ፣ ምናሴን ደግሞ ከራሱ በስተግራ፣ ከእስራኤል በስተቀኝ በኩል አቀረባቸው። 14.እስራኤል ግን ቀኝ እጁን በታናሹ በኤፍሬም ራስ ላይ አኖረ፤ ግራ እጁንም በቀኝ እጁ ላይ አስተላልፎ በበኵሩ በምናሴ ራስ ላይ አኖረ። 15.ከዚህ በኋላ ዮሴፍን ባረከ፤ እንዲህም አለው፤
“አባቶቼ አብርሃምና ይሥሐቅ በፊቱ
የተመላለሱት እግዚአብሔር፣
ለእኔም እስከ ዛሬ ድረስ
በዘመኔ ሁሉ እረኛ የሆነኝ አምላክ፣
16.ከጕዳትም ሁሉ የታደገኝ መልአክ፣
እርሱ እነዚህን ልጆች ይባርክ፤
እነርሱም በስሜ፣
በአባቶቼ በአብርሃምና
በይሥሐቅ ስም ይጠሩ፤
በምድር ላይ እጅግ ይብዙ።”
17.ዮሴፍ፣ አባቱ ቀኝ እጁን በኤፍሬም ራስ ላይ ማድረጉን ሲያይ ተከፋ፤ ከኤፍሬም ራስ ላይ አንሥቶ በምናሴ ራስ ላይ ለማኖር የአባቱን እጅ ያዘ፤ 18.ዮሴፍም፣ “አባቴ ሆይ፤ እንዲህ አይደለም፤ በኵሩ ይህኛው ስለ ሆነ፣ ቀኝ እጅህን እርሱ ራስ ላይ አድርግ” አለው። 19.አባቱ ግን፣ “ዐውቃለሁ፤ ልጄ ዐውቃለሁ፤ እርሱም እኮ ሕዝብ ይሆናል፤ ታላቅም ይሆናል፤ ይሁን እንጂ ታናሽ ወንድሙ ከርሱ ይበልጣል፤ ዘሮቹም ታላቅ ሕዝቦች ይሆናሉ” ብሎ እንቢ አለው። 20.በዚያ ዕለት ባረካቸው፤ እንዲህም አላቸው፤
“በአንተ ስም እስራኤል እንዲህ ብሎ ይመርቃል፤
‘እግዚአብሔር እንደ ኤፍሬምና እንደ ምናሴ ያድርጋችሁ።’ ”
በዚህ ሁኔታም ኤፍሬምን ከምናሴ አስቀደመው።
21.ከዚህ በኋላ እስራኤል ዮሴፍን እንዲህ አለው፤ “እኔ የምሞትበት ጊዜ ተቃርቧል፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ከእናንተ ጋራ ይሆናል፤ ወደ አባቶቻችሁም ምድር መልሶ ያገባችኋል። 22.እነሆ በሰይፌና በቀስቴ ከአሞራውያን እጅ የወሰድኋትን ዐምባ ከወንድሞችህ ድርሻ አብልጬ ለአንተ ሰጥቼሃለሁ።”

መዝሙረ ዳዊት

ምዕራፍ 25

1.የዳዊት መዝሙር።
1 እግዚአብሔር አምላክ ሆይ፤
ነፍሴን ወደ አንተ አነሣለሁ።
2.አምላኬ ሆይ፣ በአንተ እታመናለሁ፤
እባክህ አታሳፍረኝ፤
ጠላቶቼም አይዘባነኑብኝ።
3.አንተን ተስፋ የሚያደርጉ፣
ከቶ አያፍሩም፤
ነገር ግን እንዲያው ያለ ምክንያት፣
ተንኰለኞች የሆኑ ያፍራሉ።
4.እግዚአብሔር ሆይ፤ አካሄድህን እንዳውቅ አድርገኝ፤
መንገድህንም አስተምረኝ።
5.አንተ አዳኜ፣ አምላኬም ነህና፣
በእውነትህ ምራኝ፤ አስተምረኝም፤
ቀኑን ሙሉ አንተን ተስፋ አድርጌአለሁ።
6.እግዚአብሔር ሆይ፤ ምሕረትህንና ፍቅርህን ዐስብ፤
እነዚህ ከጥንት የነበሩ ናቸውና።
7.የልጅነቴን ኀጢአት፣
መተላለፌንም አታስብብኝ፤
እግዚአብሔር ሆይ፤ እንደ ቸርነትህ ብዛት፣
እንደ ምሕረትህም መጠን አስበኝ።
8.እግዚአብሔር መልካምና ቅን ነው፤
ስለዚህ ኀጢአተኞችን በመንገድ ይመራቸዋል።
9.ዝቅ ያሉትን በፍትሕ ይመራቸዋል፤
ለትሑታንም መንገዱን ያስተምራቸዋል።
10.ኪዳኑንና ምስክርነቱን ለሚጠብቁ፣
የእግዚአብሔር መንገድ ሁሉ ቸርነትና እውነት ናቸው።
11.እግዚአብሔር ሆይ፤ ኀጢአቴ ታላቅ ነውና፣
ስለ ስምህ ይቅር በልልኝ።
12.እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው ማን ነው?
በተመረጠለት መንገድ ያስተምረዋል።
13.ዘመኑን በተድላ ደስታ ያሳልፋል፤
ዘሩም ምድርን ይወርሳል።
14.እግዚአብሔር ምስጢሩን ከሚፈሩት ወዳጆቹ አይሰውርም፤
ኪዳኑንም ይገልጥላቸዋል።
15.ዐይኖቼ ሁልጊዜ ወደ እግዚአብሔር ናቸው፤
እግሮቼን ከወጥመድ የሚያላቅቃቸው እርሱ ነውና።
16.እኔ ብቸኛና የተጨነቅሁ እንደ መሆኔ፣
ወደ እኔ ተመለስ፤ ምሕረትም አድርግልኝ።
17.የልቤ መከራ በዝቷል፤
ከጭንቀቴ ገላግለኝ።
18.ጭንቀቴንና መከራዬን ተመልከት፤
ኀጢአቴንም ሁሉ ይቅር በለኝ።
19.ጠላቶቼ እንዴት እንደ በዙ ተመልከት፤
እንዴት አምርረው እንደሚጠሉኝ እይ።
20.ነፍሴን ጠብቃት፤ ታደገኝም፤
መጠጊያዬ ነህና አታሳፍረኝ።
21.አንተን ተስፋ አድርጌአለሁና፣
ታማኝነትና ቅንነት ይጠብቁኝ።
22.አምላክ ሆይ፤ እስራኤልን
ከመከራው ሁሉ አድነው።

ወደ ገላትያ ሰዎች

ምዕራፍ 3

እምነት ወይስ የኦሪትን ሕግ መጠበቅ

1.እናንተ የማታስተውሉ የገላትያ ሰዎች ሆይ! ለመሆኑ ማን መተት አደረገባችሁ? ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ተሰቀለ ሆኖ በፊት ለፊታችሁ በግልጽ ተሥሎ ነበር። 2.ከእናንተ ዘንድ አንድ ነገር ብቻ ማወቅ እፈልጋለሁ፤ መንፈስን የተቀበላችሁት ሕግን በመጠበቅ ነው ወይስ የተሰበከላችሁን በማመን? 3.ይህን ያህል የማታስተውሉ ናችሁን? በመንፈስ ጀምራችሁ በሥጋ ፍጹም ለመሆን ትጥራላችሁን? 4.በርግጥ ለከንቱ ከሆነ፣ ይህን ያህል መከራ የተቀበላችሁት እንዲያው ነውን? 5.እግዚአብሔር መንፈሱን የሚሰጣችሁ፣ በእናንተም ዘንድ ታምራትን የሚሠራው ሕግን ስለ ጠበቃችሁ ነው ወይስ የሰማችሁትን ስላመናችሁ? 6.ልክ እንደዚሁ፣ አብርሃም “እግዚአብሔርን አመነ፤ ጽድቅም ሆኖ ተቈጠረለት።” 7.እንግዲህ እነዚያ የሚያምኑት የአብርሃም ልጆች እንደ ሆኑ አስተውሉ። 8.መጽሐፍ፣ እግዚአብሔር አሕዛብን በእምነት እንደሚያጸድቅ አስቀድሞ በማየት፣ “አሕዛብ ሁሉ በአንተ ይባረካሉ” በማለት ወንጌልን ለአብርሃም አስቀድሞ አስታወቀው። 9.ስለዚህ በእምነት የሆኑት፣ የእምነት ሰው ከሆነው ከአብርሃም ጋራ ቡሩካን ናቸው። 10.ሕግን በመጠበቅ የሚተማመኑ ሁሉ ከርግማን በታች ናቸው፤ “በሕግ መጽሐፍ የተጻፈውን ሁሉ የማያደርግ የተረገመ ነው” ተብሎ ተጽፏልና። 11.“ጻድቅ በእምነት ይኖራል” ስለ ተባለ፣ ማንም በእግዚአብሔር ፊት በሕግ እንደማይጸድቅ ግልጽ ነው። 12.ሕግ በእምነት ላይ የተመሠረተ አይደለም፤ ነገር ግን “እነዚህን የሚፈጽም ሰው በእነርሱ ሕያው ይሆናል” ተብሏል። 13.“በዕንጨት ላይ የሚሰቀል ሁሉ የተረገመ ነው” ተብሎ ስለ ተጻፈ፣ ክርስቶስ ስለ እኛ ርግማን ሆኖ ከሕግ ርግማን ዋጅቶናል። 14.ለአብርሃም የተሰጠው በረከት፣ በክርስቶስ ኢየሱስ ለአሕዛብ እንዲደርስ ዋጅቶናል፤ ይኸውም በእምነት የመንፈስን ተስፋ እንድንቀበል ነው።

የኦሪት ሕግና የተስፋ ቃል

15.ወንድሞች ሆይ፤ ከሰው ዕለታዊ ሕይወት የተለመደውን ምሳሌ አድርጌ ላቅርብ፤ የሰው ኪዳን እንኳ አንድ ጊዜ ከጸደቀ በኋላ ማንም ሊሽረው ወይም በርሱ ላይ ሊጨምርበት እንደማይችል ሁሉ፣ በዚህም ጕዳይ ቢሆን እንደዚሁ ነው። 16.የተስፋውም ቃል የተነገረው ለአብርሃምና ለዘሩ ነበር፤ መጽሐፍ፣ ለብዙ ሰዎች እንደሚነገር፣ “ለዘሮቹ” አይልም፤ ነገር ግን ለአንድ ሰው እንደሚነገር፣ “ለዘርህ” ይላል፤ እርሱም ክርስቶስ ነው። 17.የምለው እንዲህ ነው፦ ከአራት መቶ ሠላሳ ዓመት በኋላ የተሰጠው ሕግ፣ አስቀድሞ በእግዚአብሔር የጸናውን ኪዳን አፍርሶ የተስፋውን ቃል አይሽርም። 18.ርስትን መውረስ በሕግ ቢሆን ኖሮ፣ በተስፋ ቃል ባልተገኘ ነበርና፤ እግዚአብሔር ግን በጸጋው በተስፋ ቃል አማካይነት ለአብርሃም ሰጥቶታል። 19.ታዲያ ሕግ የተሰጠበት ምክንያት ምንድን ነው? ሕግ የተጨመረው ከመተላለፍ የተነሣ ተስፋው ያመለከተው ዘር እስኪመጣ ድረስ ነበር፤ ሕጉም የመጣው በመላእክት በኩል፣ በአንድ መካከለኛ እጅ ነበር። 20.ሆኖም መካከለኛው አንድን ወገን ብቻ የሚወክል አይደለም፤ እግዚአብሔር ግን አንድ ነው። 21.ታዲያ ሕግ የእግዚአብሔርን የተስፋ ቃል የሚቃወም ነውን? ከቶ አይሆንም! ሕግ የተሰጠው ሕይወትን ለማስገኘት ቢሆን ኖሮ፣ በርግጥም ጽድቅ በሕግ በኩል በተገኘ ነበር። 22.መጽሐፍ ግን ዓለም ሁሉ የኀጢአት እስረኛ መሆኑን ያውጃል፤ ይኸውም በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የሚገኘው ተስፋ ለሚያምኑት ሁሉ ይሰጥ ዘንድ ነው።

የእግዚአብሔር ልጆች

23.ይህ እምነት ከመምጣቱ በፊት በሕግ አማካይነት እስረኞች ሆነን፣ እምነት እስከሚገለጥ ድረስ ተዘግቶብን ነበር። 24.ስለዚህ በእምነት እንጸድቅ ዘንድ ሕግ ወደ ክርስቶስ የሚያደርሰን ሞግዚታችን ሆነ። 25.አሁን ግን ያ እምነት ስለ መጣ፣ ከእንግዲህ በሕግ ሞግዚትነት ሥር አይደለንም። 26.ሁላችሁም በክርስቶስ ኢየሱስ በማመን የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁ፤ 27.ከክርስቶስ ጋራ አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁላችሁ ክርስቶስን ለብሳችሁታልና። 28.በአይሁድና በግሪክ፣ በባሪያና በነጻ ሰው፣ በወንድና በሴት መካከል ልዩነት የለም፤ ሁላችሁም በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ናችሁ። 29.የክርስቶስ ከሆናችሁ፣ እናንተ የአብርሃም ዘር ናችሁ፤ እንደ ተስፋውም ቃል ወራሾች ናችሁ።