ሳምንት 4 · ቀን 18 (ረቡዕ)
📅 Meskerem 27, 2019
ኦሪት ዘፍጥረት 45, 46 · መዝሙረ ዳዊት 108 · ወደ ገላትያ ሰዎች 2
ኦሪት ዘፍጥረት
ምዕራፍ 45
ዮሴፍ ለወንድሞቹ ራሱን ገለጠ
1.በዚያ ጊዜ ዮሴፍ አጠገቡ በነበሩ ሰዎች ፊት ስሜቱን ሊገታ ባለመቻሉ፣ “እዚህ ያሉትን ሰዎች በሙሉ አስወጡልኝ” ብሎ ጮኾ ተናገረ፤ ስለዚህም ዮሴፍ ራሱን ለወንድሞቹ በገለጠበት ጊዜ፣ ከርሱ ጋራ ሌላ ማንም ሰው አልነበረም። 2.ዮሴፍም ድምፁን ከፍ አድርጎ በማልቀሱ፣ ግብጻውያን ሰሙት፤ ወሬውም ወደ ፈርዖን ቤተ ሰዎች ደረሰ። 3.ዮሴፍም ወንድሞቹን፣ “እኔ ዮሴፍ ነኝ፤ ለመሆኑ አባቴ እስካሁን በሕይወት አለ?” ሲል ጠየቃቸው። ወንድሞቹ ግን በፊቱ ተደናግጠው ስለ ነበር መልስ ሊሰጡት አልቻሉም። 4.ዮሴፍም ወንድሞቹን፣ “እስኪ ወደ እኔ ቀረብ በሉ” አላቸው፤ ወደ እርሱም በቀረቡ ጊዜ እንዲህ አለ፤ “ወደ ግብጽ የሸጣችሁኝ ወንድማችሁ እኔ ዮሴፍ ነኝ፤ 5.አሁንም በመሸጣችሁ አትቈጩ፤ በራሳችሁም አትዘኑ፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር ሕይወት ለማዳን ሲል ከእናንተ አስቀድሞ እኔን ወደዚህ ልኮኛል። 6.በምድር ላይ ራብ ከገባ ይኸው ሁለት ዓመት ሆነ፤ ከዚህ በኋላም የማይታረስባቸውና ሰብል የማይሰበሰብባቸው ዐምስት ዓመታት ገና አሉ። 7.ነገር ግን እግዚአብሔር ሕይወታችሁን በታላቅ ማዳን ለመታደግና ዘራችሁ ከምድር ላይ እንዳይጠፋ በማሰብ ከእናንተ አስቀድሞ ወደዚህ ላከኝ። 8.“ስለዚህ አሁን ወደዚህ የላከኝ እግዚአብሔር እንጂ እናንተ አይደላችሁም፤ እርሱም ለፈርዖን እንደ አባት፣ በቤት ንብረቱ ላይ ጌታ፣ እንዲሁም በግብጽ ምድር ላይ ገዥ አደረገኝ። 9.አሁንም በፍጥነት ወደ አባቴ ተመልሳችሁ እንዲህ በሉት፤ ልጅህ ዮሴፍ እንዲህ ይላል፤ ‘እግዚአብሔር የመላው ግብጽ ጌታ አድርጎኛል፤ ስለዚህ ሳትዘገይ ወደ እኔ ና። 10.ልጆችህን፣ የልጅ ልጆችህን፣ በጎችህን፣ ፍየሎችህን፣ ከብቶችህንና ያለህን ሁሉ ይዘህ በአቅራቢያዬ በጌሤም ትኖራለህ። 11.ገና ወደ ፊት የሚመጣ የዐምስት ዓመት ራብ ስላለ፣ በዚያ የሚያስፈልጋችሁን እኔ እሰጣችኋለሁ፤ አለዚያ ግን አንተና ቤተ ሰዎችህ ያንተም የሆነው ሁሉ፣ ችግር ላይ ትወድቃላችሁ።’ 12.“ፊታችሁ ሆኜ የማናግራችሁ እኔ ዮሴፍ ራሴ መሆኔን እናንተም ሆናችሁ ወንድሜ ብንያም በዐይናችሁ የምታዩት ነው። 13.በግብጽ ስላለኝ ክብርና ስላያችሁትም ሁሉ ለአባቴ ንገሩት፤ አባቴንም በፍጥነት ይዛችሁት ኑ።” 14.ከዚያም በወንድሙ በብንያም ዐንገት ላይ ተጠምጥሞ አለቀሰ፤ ብንያምም እያለቀሰ ዮሴፍን ዐቀፈው። 15.የቀሩትንም ወንድሞቹን አንድ በአንድ እየሳመ አለቀሰ። ከዚያም ወንድሞቹ ከርሱ ጋራ መጨዋወት ጀመሩ። 16.የዮሴፍ ወንድሞች መምጣት በፈርዖን ቤተ መንግሥት በተሰማ ጊዜ፣ ፈርዖንና ሹማምቱ ሁሉ ደስ አላቸው። 17.ፈርዖንም ዮሴፍን እንዲህ አለው፤ “ለወንድሞችህ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤ ‘እንዲህ አድርጉ፤ አህዮቻችሁን ጭናችሁ ወደ ከነዓን ምድር ተመለሱ። 18.ከዚያም አባታችሁንና ቤተ ሰባችሁን ይዛችሁ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም እጅግ ለም ከሆነው የግብጽ ምድር እሰጣችኋለሁ፤ በምድሪቱ በረከት ደስ ብሏችሁ ትኖራላችሁ።’ 19.“ደግሞም እንዲህ ብለህ እዘዛቸው፤ ‘ይህን አድርጉ፤ ከግብጽ ምድር ልጆቻችሁንና ሚስቶቻችሁን የምታጓጕዙበት ሠረገላዎች ወስዳችሁ፣ አባታችሁን ይዛችሁት ኑ። 20.ስለ ንብረታችሁ ምንም አታስቡ፤ ከግብጽ ምድር እጅግ ለም የሆነው የእናንተ ይሆናልና።’ ” 21.የእስራኤልም ልጆች ይህንኑ አደረጉ። ዮሴፍም ፈርዖን ባዘዘው መሠረት ሠረገላዎች አቀረበላቸው፤ የመንገድም ስንቅ አስያዛቸው። 22.ለእያንዳንዳቸው ሁለት ሁለት የክት ልብስ ሰጣቸው፤ ለብንያም ግን ሦስት መቶ ጥሬ ብርና ዐምስት የክት ልብስ ሰጠው። 23.ለአባቱም በግብጽ ምድር ከሚገኘው የተመረጠ ነገር በዐሥር አህዮች፣ እንደዚሁም ለመንገዱ ስንቅ የሚሆነው እህል፣ ዳቦና ሌላ ምግብ በዐሥር እንስት አህዮች አስጭኖ ሰደደለት። 24.ከዚህ በኋላ ወንድሞቹን አሰናበታቸው፤ ከርሱም ሲሰናበቱ፣ “መንገድ ላይ እንዳትጣሉ!” አላቸው። 25.እነርሱም ከግብጽ ወጥተው በከነዓን ምድር ወደሚኖረው ወደ አባታቸው ወደ ያዕቆብ መጡ። 26.አባታቸውንም፣ “እነሆ ዮሴፍ በሕይወት አለ፤ እንዲያውም በግብጽ ምድር ሁሉ ገዥ ሆኗል” ብለው ነገሩት። ያዕቆብም በድንጋጤ ክው አለ፤ ሊያምናቸውም አልቻለም። 27.ነገር ግን ዮሴፍ የነገራቸውን ሁሉ ሲያጫውቱትና እርሱንም ወደ ግብጽ ለማጓጓዝ ዮሴፍ የላከለትን ሠረገላዎች ሲያይ የአባታቸው የያዕቆብ መንፈስ ታደሰ። 28.ከዚያም እስራኤል፤ “ልጄ ዮሴፍ በሕይወት አለ፤ ከመሞቴ በፊት ሄጄ ልየው” አለ።ምዕራፍ 46
ያዕቆብ ወደ ግብጽ ሄደ
1.እስራኤልም ጓዙን ሁሉ ጠቅልሎ ተነሣ፤ ቤርሳቤህም ሲደርስ፣ ለአባቱ ለይሥሐቅ አምላክ መሥዋዕት ሠዋ። 2.እግዚአብሔርም ሌሊት በራእይ ለእስራኤል ተገልጦ “ያዕቆብ ያዕቆብ” ብሎ ጠራው።እርሱም፣ “እነሆ፤ አለሁ” አለ። 3.እግዚአብሔርም እንዲህ አለው፤ “እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ የአባትህ አምላክ ነኝ፤ ወደ ግብጽ ለመውረድ አትፍራ፤ በዚያ ታላቅ ሕዝብ አደርግሃለሁና፤ 4.ዐብሬህ ወደ ግብጽ እወርዳለሁ፤ ከዚያም መልሼ አወጣሃለሁ፤ የዮሴፍ የራሱ እጆችም ዐይኖችህን ይገጥሟቸዋል።” 5.ከዚህ በኋላ ያዕቆብ ከቤርሳቤህ ተነሣ፤ የእስራኤል ወንዶች ልጆችም አባታቸውን ያዕቆብን፣ ልጆቻቸውንና ሚስቶቻቸውን ፈርዖን ለያዕቆብ በላካቸው ሠረገላዎች ላይ አወጧቸው። 6.ከብቶቻቸውንና በከነዓን ምድር ያፈሩትን ሀብት ንብረታቸውን ይዘው፣ ያዕቆብና ዘሮቹ በሙሉ ወደ ግብጽ ወረዱ። 7.ወደ ግብጽም የወረደው፣ ወንዶች ልጆቹንና ወንዶች የልጅ ልጆቹን፣ ሴቶች ልጆቹንና ሴቶች የልጅ ልጆቹን፣ ማለትም ዘሮቹን ሁሉ ይዞ ነው። 8.ወደ ግብጽ የወረዱት የእስራኤል ልጆች፣ ያዕቆብና ዘሮቹ እነዚህ ናቸው፦
የያዕቆብ የበኵር ልጅ ሮቤል። 9.የሮቤል ልጆች፦
ሄኖኅ፣ ፈሉስ፣ አስሮን እና ከርሚ ናቸው። 10.የስምዖን ልጆች፦
ይሙኤል፣ ያሚን፣ ኦሃድ፣ ያኪን፣ ጾሐርና ከከነዓናዊቷ ሴት የተወለደው ሳኡል ናቸው። 11.የሌዊ ልጆች፦
ጌርሶን፣ ቀዓት እና ሜራሪ ናቸው። 12.የይሁዳ ልጆች፦
ዔር፣ አውናን፣ ሴሎም፣ ፋሬስ እና ዛራ ናቸው። ነገር ግን ዔርና አውናን በከነዓን ምድር ሞቱ።
የፋሬስ ልጆች፦
ኤስሮምና ሐሙል ናቸው። 13.የይሳኮር ልጆች፦
ቶላ፣ ፉዋ፣ ዮብና ሺምሮን ናቸው፤ 14.የዛብሎን ልጆች፦
ሴሬድ፣ ኤሎንና ያሕልኤል ናቸው፤ 15.እነዚህ ወንዶች ልጆች ያዕቆብ በሰሜን ምዕራብ መስጴጦምያ ሳለ፣ ልያ የወለደችለት ናቸው። ሴቷን ዲናን ጨምሮ፣ የወንዶችና የሴቶች ልጆቹ ቍጥር ሠላሳ ሦስት ነው። 16.የጋድ ልጆች፦
ጽፎን፣ ሐጊ፣ ሹኒ፣ ኤስቦን፣ ዔሪ፣ አሮዲና አርኤሊ ናቸው፤ 17.የአሴር ልጆች፦
ዪምና፣ የሱዋ፣ የሱዊና በሪዓ ናቸው፤ እኅታቸውም ሤራሕ ናት፤
የበሪዓ ልጆች፦
ሔቤርና መልኪኤል ናቸው፤ 18.እነዚህ ዐሥራ ስድስት ልጆች ሁሉ፣ ላባ ለልጁ ለልያ ከሰጣት ከዘለፋ ላይ ያዕቆብ የወለዳቸው ናቸው። 19.የያዕቆብ ሚስት የራሔል ልጆች፦
ዮሴፍና ብንያም ናቸው፤ 20.በግብጽም የሄልዮቱ ከተማ ካህን የጶጥፌራ ልጅ አስናት፣ ምናሴንና ኤፍሬምን ለዮሴፍ ወለደችለት። 21.የብንያም ልጆች፦
ቤላ፣ ቤኬር፣ አስቤል፣ ጌራ፣ ናዕማን፣ አኪ፣ ሮስ፣ ማንፌን ሑፊምና አርድ ናቸው። 22.እነዚህ ዐሥራ አራቱ፣ ራሔል ለያዕቆብ የወለደችለት ልጆችና የልጅ ልጆች ናቸው። 23.የዳን ልጅ፦
ሑሺም ነው፤ 24.የንፍታሌም ልጆች፦
ያሕጽኤል፣ ጉኒ፣ ዬጽርና ሺሌም ናቸው። 25.እነዚህ ሰባቱ ልጆች ሁሉ ላባ ለልጁ ለራሔል ከሰጣት ከባላ ላይ ያዕቆብ የወለዳቸው ናቸው። 26.ከያዕቆብ ጋራ ወደ ግብጽ የሄዱት የገዛ ዘሮቹ ብዛት ስድሳ ስድስት ሲሆን ይህ ቍጥር ግን የልጆቹን ሚስቶች አይጨምርም። 27.ዮሴፍ በግብጽ የወለዳቸውን ሁለት ልጆች ጨምሮ፣ ወደ ግብጽ የወረደው የያዕቆብ ቤተ ሰብ ቍጥር ሰባ ነበር። 28.ያዕቆብም ወደ ጌሤም ለመሄድ መመሪያን ይቀበል ዘንድ ይሁዳን አስቀድሞ ወደ ዮሴፍ ላከው። እነርሱም ጌሤም ሲደርሱ፣ 29.ዮሴፍ ሠረገላውን አዘጋጅቶ፤ አባቱን እስራኤልን ለመቀበል ወደ ጌሤም አመራ። ዮሴፍ አባቱ ዘንድ እንደ ደረሰ፣ ዐንገቱ ላይ ተጠምጥሞ ለረዥም ጊዜ አለቀሰ። 30.እስራኤልም ዮሴፍን፣ “በሕይወት መኖርህን ስላየሁ፣ ከእንግዲህ ብሞትም አይቈጨኝ” አለው። 31.ከዚህ በኋላ ዮሴፍ ወንድሞቹንና የአባቱን ቤተ ሰዎች እንዲህ አላቸው፤ “ወደ ፈርዖን ወጥቼ አናግረዋለሁ፤ እንዲህም እለዋለሁ፣ ‘በከነዓን ምድር የሚኖሩት ወንድሞቼና የአባቴ ቤተ ሰዎች ወደ እኔ መጥተዋል። 32.ሰዎቹ ከብት የሚጠብቁ ስለ ሆኑ እረኞች ናቸው፤ ሲመጡም በጎቻቸውን፣ ፍየሎቻቸውንና ከብቶቻቸውን እንዲሁም ያላቸውን ሁሉ ይዘው መጥተዋል።’ 33.ፈርዖን አስጠርቷችሁ፣ ‘ሥራችሁ ምንድን ነው?’ ብሎ ቢጠይቃችሁ፣ 34.እናንተ፣ ‘እኛ ባሮችህ ሥራችን ከልጅነታችን ጀምሮ ልክ እንደ አባቶቻችን ከብት ማርባት ነው’ ብላችሁ መልሱለት። ከዚያም ግብጻውያን ከብት አርቢዎችን እንደ ጸያፍ ስለሚቈጥሩ፣ በጌሤም ምድር እንድትኖሩ ይፈቅድላችኋል።”
መዝሙረ ዳዊት
ምዕራፍ 108
108፥1-5 ተጓ ምብ – መዝ 57፥7-11
108፥6-13 ተጓ ምብ – መዝ 60፥5-12
1.የዳዊት መዝሙር፤ ማሕሌት።1 አምላክ ሆይ፤ ልቤ ጽኑ ነው፤
እቀኛለሁ፤ በፍጹም ነፍሴም እዘምራለሁ። 2.በገናና መሰንቆም ተነሡ፤
እኔም ማልጄ እነሣለሁ። 3.ጌታ ሆይ፤ በሕዝቦች መካከል አመሰግንሃለሁ፤
በሰዎችም መካከል እዘምርልሃለሁ። 4.ምሕረትህ ከሰማያት በላይ ታላቅ ናትና፤
ታማኝነትህም እስከ ሰማያት ትደርሳለች። 5.አምላክ ሆይ፤ ከሰማያት በላይ ከፍ ከፍ በል፤
ክብርህም በምድር ሁሉ ላይ ትንሰራፋ። 6.ወዳጆችህ ይድኑ ዘንድ፣
በቀኝ እጅህ ርዳን፤ መልስልንም። 7.እግዚአብሔር ከመቅደሱ ተናገረ፤
“ደስ እያለኝ ሴኬምን እከፋፍላለሁ፤
የሱኮትንም ሸለቆ እለካለሁ። 8.ገለዓድ የእኔ ነው፤ ምናሴም የእኔ ነው፤
ኤፍሬም የራስ ቍሬ ነው፤
ይሁዳም በትረ መንግሥቴ ነው። 9.ሞዓብ የመታጠቢያ ገንዳዬ ነው፤
በኤዶምያስ ላይ ጫማዬን እወረውራለሁ፤
በፍልስጥኤም ላይ በድል አድራጊነት እጮኻለሁ።” 10.ወደ ተመሸገችው ከተማ ማን ይወስደኛል?
ወደ ኤዶምያስ ማን ይመራኛል? 11.እግዚአብሔር ሆይ፤ የጣልኸን አንተ አይደለህምን?
አምላክ ሆይ፤ ከሰራዊታችንም ጋራ አትወጣም። 12.በጠላት ላይ ድልን አቀዳጀን፤
የሰው ርዳታ ከንቱ ነውና። 13.በእግዚአብሔር ክንደ ብርቱ እንሆናለን፤
ጠላቶቻችንን የሚረጋግጥልን እርሱ ነውና።