Skip to Content
የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን | YEHIWOT MELHEK BETEKIRSTIAN
የ2019 ዓ.ም የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ 📖 ዛሬን አንብብ →

የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን

Yehiwot Melhek Betekirstian

ሳምንት 4 · ቀን 17 (ማክሰኞ) 📅 Meskerem 26, 2019

ኦሪት ዘፍጥረት 43, 44 · መዝሙረ ዳዊት 24 · ወደ ገላትያ ሰዎች 1

📖 የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም፦ 1954 መጽሐፍ ቅዱስ አዲሱ መደበኛ ትርጒም

ኦሪት ዘፍጥረት

ምዕራፍ 43

የዮሴፍ ወንድሞች ዳግመኛ ወደ ግብጽ መሄዳቸው

1.ራቡ አሁንም በምድሪቱ ላይ እንደ ጸና ነበር፤ 2.ከግብጽ ያመጡትንም እህል በልተው ከጨረሱ በኋላ፣ አባታቸው “እስኪ እንደ ገና ወርዳችሁ፣ ጥቂት እህል ሸምቱልን” አላቸው። 3.ይሁዳ ግን እንዲህ አለው፤ “ያ ሰውየው ‘ወንድማችሁን ይዛችሁ ካልመጣችሁ ዳግመኛ ፊቴን አታዩም’ ብሎ በጥብቅ አስጠንቅቆናል፤ 4.ወንድማችን ከእኛ ጋራ እንዲወርድ ከፈቀድህ ወደዚያ ሄደን እህል እንሸምትልሃለን፤ 5.እርሱን የማትልከው ከሆነ ግን እኛም ወደዚያ አንወርድም፤ ያም ሰው፣ ‘ወንድማችሁን ይዛችሁ ካልመጣችሁ ዳግመኛ ፊቴን አታዩም’ ብሎናል።” 6.እስራኤልም፣ “ሌላ ወንድም አለን ብላችሁ ለዚያ ሰው በመንገር ለምን ይህን ችግር እንዲደርስብኝ አደረጋችሁ?” ሲል ጠየቃቸው። 7.እነርሱም፣ “ሰውየው ስለ ራሳችንና ስለ ቤተ ሰባችን አጥብቆ ጠየቀን፤ እንደ ገናም ‘አባታችሁ አሁንም በሕይወት አለ? ሌላስ ወንድም አላችሁ?’ ሲል ጠየቀን። እኛም ለጥያቄው መልስ ሰጠነው። ታዲያ፣ ‘ወንድማችሁን ይዛችሁ ወደዚህ እንድትመጡ’ እንደሚል እንዴት ማወቅ እንችል ነበር?” ብለው መለሱለት። 8.ይሁዳም አባቱን እስራኤልን እንዲህ አለው “ልጁን ከእኔ ጋራ ስደደው፤ እኛም በቶሎ እንሂድ፤ ይህ ከሆነ፣ አንተም፣ እኛም፣ ልጆቻችንም አንሞትም፤ እንተርፋለን። 9.ስለ ልጁ ደኅንነት እኔ ራሴ ኀላፊ ነኝ፤ ስለ እርሱም በግል ተጠያቂ እሆናለሁ፤ እርሱንም በደኅና መልሼ ባላመጣውና እዚህ በፊትህ ባላቆመው ለዘላለም በደለኛው እኔ ልሁን። 10.ይህን ያህል ባንዘገይ ኖሮ፣ እስካሁን ሁለት ጊዜ ደርሰን መመለስ በቻልን ነበር።” 11.ከዚህ በኋላ አባታቸው እስራኤል እንዲህ አላቸው፤ “ነገሩ እንዲህ ከሆነስ ይህን አድርጉ፤ ምድሪቱ ከምታፈራው ምርጥ ነገሮች ጥቂት በለሳን፣ ጥቂት ማር፣ ሽቱ፣ ከርቤ፣ ተምርና አልሙን በየስልቻችሁ ይዛችሁ ለዚያ ሰው እጅ መንሻ ውሰዱለት። 12.በየስልቾቻችሁ አፍ ላይ የተገኘውን ብር መመለስ ስላለባችሁ፣ ዕጥፍ ገንዘብ ያዙ፤ ያ በየስልቾቻችሁ ውስጥ የተገኘው ብር ምናልባት በስሕተት የመጣ ሊሆን ይችላል። 13.ወንድማችሁንም ይዛችሁ ወደ ሰውየው በቶሎ ሂዱ። 14.ሌላውን ወንድማችሁንና ብንያምን ይዛችሁ ለመመለስ እንድትችሉ ሁሉን ቻይ አምላክ በምሕረቱ የዚያን ሰው ልብ ያራራላችሁ። እንግዲህ ልጆቼንም ባጣ ምን አደርጋለሁ፤ ያመጣውን እቀበላለሁ።” 15.ሰዎቹም እጅ መንሻውን፣ የብሩን ዕጥፍ እንዲሁም ብንያምን ይዘው ተነሡ፤ ወደ ግብጽም በፍጥነት ወረዱ፤ ዮሴፍም ፊት ቀረቡ። 16.ዮሴፍ ብንያምን ከወንድሞቹ ጋራ ባየው ጊዜ የቤቱን አዛዥ፣ “እነዚህን ሰዎች ወደ ቤት ይዘሃቸው ሂድ፤ ዛሬ ቀትር ላይ ዐብረውኝ ስለሚበሉ ፍሪዳ ተጥሎ ምሳ ይዘጋጅ” አለው። 17.አዛዡም ዮሴፍ የነገረውን አደረገ፤ ሰዎቹንም ወደ ዮሴፍ ቤት ወሰዳቸው። 18.ሰዎቹም ወደ ዮሴፍ ቤት በመወሰዳቸው ፈሩ፤ እነርሱም፣ “ወደዚህ የመጣነው፣ ቀደም ሲል እዚህ መጥተን ስንመለስ በየስልቾቻችን ውስጥ ተመልሶ በተጨመረው ብር ሰበብ ነው። ሰውየው ጥቃት ሊፈጽምብን፣ አስገድዶ ባሮቹ ሊያደርገንና አህዮቻችንን ሊቀማን ይፈልጋል” ብለው ሠጉ። 19.ወደ ዮሴፍ ቤት አዛዥ ቀርበው፣ በቤቱ መግቢያ ላይ አነጋገሩት፤ 20.“እንዲህም አሉት፤ ጌታችን ሆይ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ እህል ለመሸመት ወደዚህ መጥተን ነበር፤ 21.ነገር ግን ለዐዳር በሰፈርንበት ቦታ የየስልቾቻችንን አፍ ስንከፍት፣ እያንዳንዳችን በስልቾቻችን አፍ ላይ፣ ብራችንን ሙሉውን አገኘነው። ገንዘቡንም ይኸው መልሰን ይዘን መጥተናል። 22.አሁንም እህል መሸመቻ የሚሆነን ተጨማሪ ብር ይዘን መጥተናል፤ ያኔ ገንዘቡን በየስልቾቻችን ውስጥ ማን መልሶ እንዳስቀመጠው ግን አናውቅም” አሉት። 23.የቤቱ አዛዥም፣ “አይዟችሁ አትፍሩ፤ በየስልቾቻችሁ ውስጥ ያገኛችሁትን ገንዘብ የሰጣችሁ የእናንተም የአባቶቻችሁም አምላክ ነው፤ እኔ እንደ ሆንሁ ብሩን ተቀብያለሁ” አላቸው። ከዚያም ስምዖንን አውጥቶ አገናኛቸው። 24.የቤቱ አዛዥ ሰዎቹን ወደ ዮሴፍ ቤት አስገብቶ እግራቸውን የሚታጠቡበት ውሃ አቀረበላቸው፤ ለአህዮቻቸውም የሚበሉት ገፈራ ሰጣቸው። 25.ምሳ በዚያ እንደሚበሉ ተነግሯቸው ስለ ነበር፣ ዮሴፍ በቀትር ከመግባቱ በፊት እጅ መንሻዎቻቸውን ለማበርከት ተዘጋጁ። 26.ዮሴፍም ወደ ቤቱ ሲገባ ያመጧቸውን እጅ መንሻዎች አበረከቱለት፤ ወደ መሬት ዝቅ ብለውም እጅ ነሡት። 27.ዮሴፍም ስለ ደኅንነታቸው ጠየቃቸው፤ ከዚያም “ሽማግሌ አባት እንዳላችሁ ነግራችሁኝ ነበር፤ ደኅና ነው? አሁንም በሕይወት አለ?” አላቸው። 28.እነርሱም መልሰው፣ “አገልጋይህ አባታችን አሁንም በሕይወት አለ፤ ደኅና ነው” በማለት ወደ መሬት ዝቅ ብለው በአክብሮት እጅ ነሡት። 29.ዮሴፍ በዐይኑ ሲቃኝ የእናቱን ልጅ ብንያምን አየና፣ “ያ የነገራችሁኝ ታናሽ ወንድማችሁ ይህ ነው?” ብሎ ጠየቃቸው። ብንያምንም፣ “ልጄ፤ እግዚአብሔር ይባርክህ” አለው። 30.ዮሴፍ ወንድሙን በማየቱ ስሜቱ በጥልቅ ስለ ተነካ፣ ፈጥኖ ከፊታቸው ገለል አለ፤ ሰወር ያለ ቦታም ፈልጎ፣ ዕልፍኙ ውስጥ አለቀሰ። 31.ፊቱን ከታጠበ በኋላ ተመልሶ፣ ስሜቱን በመቈጣጠር፣ “ማእድ ይቅረብ” አለ። 32.ለዮሴፍ ለብቻው ቀረበለት፤ ለወንድሞቹም ለብቻቸው ቀረበላቸው፤ እንዲሁም ከርሱ ጋራ ለሚበሉት ግብጻውያን ደግሞ ሌላ ገበታ ቀረበላቸው፤ ምክንያቱም ግብጻውያን ከዕብራውያን ጋራ ዐብሮ መመገብን እንደ ጸያፍ ይቈጥሩት ነበር። 33.ወንድማማቾቹ ከበኵሩ እስከ ታናሹ እንደየዕድሜያቸው በዮሴፍ ፊት በተርታ ተቀምጠው ነበር፤ በመገረምም እርስ በርሳቸው ተያዩ። 34.ከዮሴፍ ገበታ ላይ እየተነሣ ለእያንዳንዳቸው ምግብ ሲቀርብ፣ የብንያም ድርሻ ከሌሎቹ ዐምስት ዕጥፍ ነበር። እነርሱም እንዲህ ባለ ሁኔታ ዐብረውት ተደሰቱ፤ እስኪረኩም ጠጡ።

ምዕራፍ 44

የብር ዋንጫ በየስልቻቸው መገኘቱ

1.ከዚህ በኋላ ዮሴፍ ለቤቱ አዛዥ እንዲህ ሲል መመሪያ ሰጠው፤ “የሰዎቹ ስልቻ የሚይዘውን ያህል እህል፣ እንዲሁም ብር በየስልቻቸው አፍ ክተተው። 2.ከዚያም የብር ዋንጫዬን በታናሹ ወንድማቸው ስልቻ አፍ ከእህሉ ዋጋ ጋራ ጨምረው።” አዛዡም ዮሴፍ እንዳለው አደረገ። 3.ጎሕ ሲቀድ ሰዎቹ ከነአህዮቻቸው ተሸኙ። 4.ከከተማው ምንም ያህል ርቀው ሳይሄዱ፣ ዮሴፍ የቤቱን አዛዥ እንዲህ አለው፤ “እነዚያን ሰዎች ቶሎ ድረስባቸውና፣ ‘ለበጎ ነገር ስለ ምን ክፉ መለሳችሁ? 5.ይህ ጌታዬ የሚጠጣበት፣ የተሰወረ ነገርም የሚያውቅበት ጽዋ አይደለምን? የፈጸማችሁት ድርጊት ክፉ ነው’ ” በላቸው። 6.የቤቱ አዛዥም እንደ ደረሰባቸው፣ ልክ እንደ ተባለው ተናገራቸው። 7.እነርሱ ግን እንዲህ አሉት፤ “ጌታችን እንዲህ ያለ ነገር ለምን ይናገራል? እኛ አገልጋዮችህ እንዲህ ያለውን ነገር አናደርገውም። 8.ከዚህ ቀደምም በየስልቾቻችን አፍ የተገኘውን ብር ከከነዓን እንኳ መልሰን አምጥተናል፤ ታዲያ አሁን ብር ወይም ወርቅ ከጌታህ ቤት እንዴት እንሰርቃለን? 9.የጠፋው ዕቃ ከአገልጋዮችህ የተገኘበት ይሙት፤ የቀረነው የጌታችን ባሮች እንሁን።” 10.እርሱም “መልካም ነው፤ እንዳላችሁት ይሁን፤ ጽዋው የተገኘበት ሰው ባሪያዬ ይሆናል፤ የቀራችሁት ግን ከበደሉ ነጻ ትሆናላችሁ” አላቸው። 11.እያንዳንዱ ሰው ጭነቱን ወዲያውኑ አራግፎ ስልቻውን ፈታ። 12.ከዚያም አዛዡ ፍተሻውን ከታላቁ ጀምሮ እስከ ታናሹ ድረስ ቀጠለ። በመጨረሻም፣ ጽዋው በብንያም ስልቻ ውስጥ ተገኘ። 13.በዚህ ጊዜ ልብሳቸውን በሐዘን ቀደዱ፤ ሁሉም ስልቾቻቸውን በየአህዮቻቸው ጭነው ወደ ከተማዪቱ ተመለሱ። 14.ይሁዳና ወንድሞቹ ወደ ዮሴፍ ቤት ሲገቡ፣ እርሱ ገና ከቤቱ አልወጣም ነበር። እነርሱም ከፊቱ መሬት ላይ ተደፉ። 15.ዮሴፍም፣ “ለምን እንዲህ ያለ ነገር አደረጋችሁ? እንደ እኔ ያለ ሰው ስውር ነገርን የሚያውቅበት ልዩ ጥበብ እንዳለው አታውቁምን?” ሲል ጠየቃቸው። 16.ይሁዳም፣ “ከእንግዲህ ለጌታችን ምን ማለት እንችላለን? ምንስ እንመልሳለን? እንዲህ ካለው በደል ንጹሕ መሆናችንን ማስረዳትስ እንዴት ይቻለናል? እግዚአብሔር የእኛን የአገልጋዮችህን በደል ገልጧል፤ ከእንግዲህ ጽዋው የተገኘበት ብቻ ሳይሆን ሁላችንም ባሮችህ ነን” አለ። 17.ዮሴፍም፣ “ይህንስ ፈጽሞ አላደርገውም፤ ባሪያዬ የሚሆነው ጽዋው የተገኘበት ሰው ብቻ ነው፤ የቀራችሁት በሰላም ወደ አባታችሁ ተመለሱ” አላቸው። 18.ይሁዳም ወደ ዮሴፍ ቀረብ ብሎ፣ “ጌታዬ ሆይ፤ እኔ አገልጋይህ አንዲት ቃል ብቻ ልናገር፤ አንተም የፈርዖንን ያህል የተከበርህ ስለ ሆንህ፣ እባክህን እኔን አገልጋይህን አትቈጣኝ። 19.ጌታዬ፣ ‘አባት ወይም ወንድም አላችሁ?’ ብሎ አገልጋዮቹን ጠይቆ ነበር። 20.እኛም፣ ‘አዎን፣ ሽማግሌ አባት አለን፤ አባታችንም በስተርጅና የወለደው ትንሽ ልጅ አለው፤ ወንድምየው ሞቷል፤ ከአንድ እናት ከተወለዱት ልጆች መካከል የተረፈው እርሱ ብቻ ነው፤ አባቱም በጣም ይወድደዋል’ ብለንህ ነበር። 21.“ከዚያም አንተ አገልጋዮችህን፣ ‘እንዳየው ወደ እኔ አምጡት’ አልኸን። 22.እኛም ለጌታዬ ‘ልጁ ከአባቱ ሊለይ አይችልም፤ ከተለየው ደግሞ አባትየው ይሞታል’ አልንህ። 23.አንተ ግን እኛን አገልጋዮችህን፣ ‘ታናሽ ወንድማችሁ ዐብሯችሁ ወደዚህ ካልመጣ ዳግመኛ ፊቴን አታዩም’ አልኸን። 24.እኛም ወደ አገልጋይህ ወደ አባቴ በተመለስን ጊዜ፣ አንተ ጌታዬ ያልኸንን ነገር ነው። 25.“ከዚያም አባታችን ‘እስኪ ተመልሳችሁ ጥቂት እህል ሸምቱልን’ ሲለን፤ 26.‘መሄድ አንችልም፤ መሄድ የምንችለው ታናሽ ወንድማችን ዐብሮን ሲሄድ ብቻ ነው። ታናሽ ወንድማችንን ይዘን ካልሄድን በቀር፣ የሰውየውን ፊት ማየት አንችልም’ አልነው። 27.“አገልጋይህ አባቴም እንዲህ አለን፤ ‘ሚስቴ ሁለት ወንዶች ልጆች እንደ ወለደችልኝ ታውቃላችሁ፤ 28.አንዱ በወጣበት በመቅረቱ፣ “በርግጥ የአውሬ እራት ሆኗል” አልሁ፤ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ይኸው የውሃ ሽታ ሆኖ ቀርቷል። 29.አሁን ደግሞ ይህን ልጅ ወስዳችሁ አንዳች ጕዳት ቢደርስበት ሽበቴን በመሪር ሐዘን ወደ መቃብር ታወርዱታላችሁ።’ 30.“እንግዲህ አሁን ልጁን ሳንይዝ ወደ አገልጋይህ ወደ አባቴ ብመለስ፣ ሕይወቱ ከልጁ ሕይወት ጋራ በጥብቅ የተሳሰረ ስለ ሆነ፣ 31.የልጁን ከእኛ ጋራ አለመኖር ሲያይ አባቴ ይሞታል። ከዚህም የተነሣ እኛ አገልጋዮችህ የአባታችንን ሽበት በመሪር ሐዘን ወደ መቃብር እናወርደዋለን። 32.እኔ አገልጋይህ፣ ‘ልጅህን መልሼ ሳላመጣ ብቀር፣ ለዘላለም በደለኛ አድርገህ ቍጠረኝ’ በማለት፣ ስለ ልጁ ደኅንነት በአባቴ ፊት ራሴን ዋስ አድርጌአለሁ። 33.“ስለዚህ አሁን፣ አገልጋይህ በልጁ ፈንታ የአንተ የጌታዬ ባሪያ ሆኜ እዚሁ ልቅር፤ ልጁ ግን ከወንድሞቹ ጋራ ይመለስ። 34.ልጁን ሳልይዝ እንዴት ተመልሼ ወደ አባቴ እሄዳለሁ? ፈጽሞ አላደርገውም፤ እባክህ በአባቴ ላይ የሚደርሰውን መከራ እንዳይ አታድርገኝ።”

መዝሙረ ዳዊት

ምዕራፍ 24

1.የዳዊት መዝሙር።
1 ምድርና በርሷ ያለው ሁሉ፣
ዓለምና በውስጧ የሚኖር ሁሉ የእግዚአብሔር ነው፤
2.እርሱ በባሕሮች ላይ መሥርቷታልና፤
በውሆችም ላይ አጽንቷታል።
3.ወደ እግዚአብሔር ተራራ ማን ሊወጣ ይችላል?
በተቀደሰ ስፍራውስ ማን ይቆማል?
4.ንጹሕ እጅና ቅን ልብ ያለው፤
ነፍሱን ለሐሰት ነገር የማያስገዛ፤
በውሸት የማይምል።
5.እርሱ በረከትን ከእግዚአብሔር ዘንድ፣
ጽድቅንም ከአዳኝ አምላኩ ይቀበላል።
6.እርሱን የሚፈልግ ትውልድ እንዲህ ነው፤
የያዕቆብ አምላክ ሆይ፤ ፊትህን የሚፈልግ እንዲህ ያለ ነው።ሴላ
7.እናንተ ደጆች፤ ቀና በሉ፤
እናንተ የዘላለም በሮች፤
የክብር ንጉሥ እንዲገባ ብድግ በሉ!
8.ይህ የክብር ንጉሥ ማን ነው?
እግዚአብሔር ነው ብርቱና ኀያል፤
እግዚአብሔር ነው በውጊያ ኀያል።
9.እናንተ ደጆች፤ ቀና በሉ፤
እናንተ የዘላለም በሮች፤
የክብር ንጉሥ እንዲገባ ብድግ በሉ!
10.ይህ የክብር ንጉሥ ማን ነው?
የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፣
እርሱ የክብር ንጉሥ ነው።

ወደ ገላትያ ሰዎች

ምዕራፍ 1

1.ከሰዎች ወይም በሰው ከተላከው ሳይሆን፣ በኢየሱስ ክርስቶስና ከሙታን ባስነሣው በእግዚአብሔር አብ ሐዋርያ ከሆነው ከጳውሎስ፤ 2.ዐብረውኝም ካሉት ወንድሞች ሁሉ፤
በገላትያ ላሉት አብያተ ክርስቲያናት፦
3.ከአባታችን ከእግዚአብሔር፣ ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን። 4.እንደ አምላካችንና እንደ አባታችን ፈቃድ፣ ከዚህ ክፉ ዓለም ያድነን ዘንድ ስለ ኀጢአታችን ራሱን ሰጠ፤ 5.ከዘላለም እስከ ዘላለም ለርሱ ክብር ይሁን። አሜን።

ሌላ ወንጌል የለም

6.በክርስቶስ ጸጋ የጠራችሁን እርሱን ትታችሁ፣ ወደ ተለየ ወንጌል እንዲህ ፈጥናችሁ መዞራችሁ ደንቆኛል፤ 7.እንደ እውነቱ ከሆነ ሌላ ወንጌል የለም። የሚያደነጋግሯችሁና የክርስቶስን ወንጌል ለማጣመም ጥረት የሚያደርጉ አንዳንድ ሰዎች አሉ። 8.ነገር ግን እኛም ብንሆን ወይም የሰማይ መልአክ፣ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የተለየ ወንጌል ቢሰብክላችሁ እርሱ ለዘላለም የተረገመ ይሁን! 9.ቀደም ብለን እንዳልነው፣ አሁንም ደግሜ እላለሁ፤ ማንም ከተቀበላችሁት ሌላ የተለየ ወንጌል ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን! 10.አሁን እኔ ተቀባይነት ለማግኘት የምሻው በሰዎች ዘንድ ነው ወይስ በእግዚአብሔር ዘንድ? ወይስ ሰዎችን ደስ ለማሠኘት እየተጣጣርሁ ነው? ሰዎችን ደስ ለማሠኘት የምጥር ብሆን ኖሮ፣ የክርስቶስ ባሪያ ባልሆንሁ ነበር።

ጳውሎስ በእግዚአብሔር ስለ መጠራቱ

11.ወንድሞች ሆይ፤ የሰበክሁላችሁ ወንጌል ሰው ሠራሽ አለመሆኑን እንድታውቁ እፈልጋለሁ፤ 12.ከማንም ሰው አልተቀበልሁትም፤ ከማንም አልተማርሁትም፤ ይልቁንስ በመገለጥ ከኢየሱስ ክርስቶስ ተቀበልሁት። 13.ቀድሞ በአይሁድ ሃይማኖት እንዴት እንደ ኖርሁ፣ የእግዚአብሔርንም ቤተ ክርስቲያን እንዴት በእጅጉ እንዳሳደድሁ፣ ለማጥፋትም እንዴት እንደ ጣርሁ ሰምታችኋል። 14.በእኔ ዕድሜ ዘመን ከነበሩት ከብዙዎቹ አይሁድ ይበልጥ በአይሁድ ሃይማኖት እልቅ ነበር፤ ስለ አባቶቼም ወግ እጅግ ቀናተኛ ነበርሁ። 15.ነገር ግን፣ ከእናቴ ማሕፀን ጀምሮ የለየኝና በጸጋው የጠራኝ እግዚአብሔር፣ 16.በአሕዛብ መካከል ስለ እርሱ እንድሰብክ ልጁን በእኔ ሊገልጥ በወደደ ጊዜ፣ ከማንም ሥጋ ለባሽ ጋራ አልተማከርሁም፤ 17.ከእኔ በፊት ሐዋርያት ወደሆኑትም ወደ ኢየሩሳሌም አልወጣሁም፤ ነገር ግን ወዲያው ወደ ዐረብ አገር ሄድሁ፤ በኋላም ወደ ደማስቆ ተመለስሁ። 18.ከዚያም ከሦስት ዓመት በኋላ፣ ኬፋን አገኘው ዘንድ ወደ ኢየሩሳሌም ወጣሁ፤ ከርሱም ጋራ ዐሥራ ዐምስት ቀን ተቀመጥሁ። 19.ነገር ግን ከጌታ ወንድም ከያዕቆብ በቀር፣ ከሐዋርያት ማንንም አላየሁም። 20.በምጽፍላችሁ ነገር በእግዚአብሔር ፊት ሐሰት እንደማልናገር አስረግጬ እነግራችኋለሁ። 21.ከዚያም በኋላ፣ ወደ ሶርያና ወደ ኪልቅያ አገር ሄድሁ። 22.በክርስቶስ ያሉት የይሁዳ አብያተ ክርስቲያናትም ፊቴን አይተው አያውቁም ነበር፤ 23.እነርሱ ግን፣ “ቀድሞ እኛን ሲያሳድድ የነበረ ሰው፣ ከዚህ በፊት ሊያጠፋው ይፈልግ የነበረውን እምነት አሁን እየሰበከ ነው” የሚለውን ወሬ ብቻ ሰምተው ነበር፤ 24.በእኔም ምክንያት እግዚአብሔርን አመሰገኑ።