ሳምንት 2 · ቀን 10 (አርብ)
📅 Meskerem 15, 2019
ኦሪት ዘፍጥረት 26, 27 · የማርቆስ ወንጌል 10
ኦሪት ዘፍጥረት
ምዕራፍ 26
ይሥሐቅና አቢሜሌክ
26፥1-11 ተጓ ምብ – ዘፍ 12፥10-20፤ 20፥1-18
1.ቀድሞ በአብርሃም ዘመን ከደረሰው ራብ ሌላ፣ በአገሩ ላይ ራብ ሆነ። ይሥሐቅም የፍልስጥኤም ንጉሥ አቢሜሌክ ወደሚኖርበት ወደ ጌራራ ሄደ።
2.በዚያም እግዚአብሔር ለይሥሐቅ ተገልጦ እንዲህ አለው፤ “እኔ በምነግርህ ምድር ተቀመጥ እንጂ፣ ወደ ግብጽ አትውረድ፤
3.ለጥቂት ጊዜ እዚሁ አገር ተቀመጥ፤ እኔም ካንተ ጋራ እሆናለሁ፤ እባርክሃለሁም፤ ይህን ምድር በሙሉ ለአንተና ለዘርህ በመስጠት ለአባትህ ለአብርሃም በመሐላ የገባሁለትን ቃል አጸናለሁ።
4.ዘርህን እንደ ሰማይ ከዋክብት አበዛለሁ፤ ይህን ምድር በሙሉ ለዘርህ እሰጣለሁ፤ የምድር ሕዝቦችም ሁሉ በዘርህ አማካይነት ይባረካሉ።
5.ይኸውም አብርሃም ቃሌን ሰምቶ፣ ድንጋጌዬን፣ ትእዛዜን፣ ሥርዐቴንና ሕጌን በመጠበቁ ነው።”
6.ስለዚህ ይሥሐቅ በጌራራ ተቀመጠ።
7.የዚያም አገር ሰዎች ስለ ሚስቱ በጠየቁት ጊዜ፣ “እኅቴ ናት” አለ፤ ምክንያቱም፣ “ሚስቴ ናት ብል ርብቃ ቈንጆ ስለ ሆነች፣ ያገሬው ሰዎች በርሷ ምክንያት ይገድሉኛል” በማለት ፈርቶ ነበር።
8.ይሥሐቅ ብዙ ጊዜ በዚያ ከኖረ በኋላ፣ የፍልስጥኤም ንጉሥ አቢሜሌክ አንድ ቀን ወደ ውጭ ሲመለከት፣ ይሥሐቅ ሚስቱን ርብቃን ሲዳራት አየ።
9.አቢሜሌክም ይሥሐቅን ጠርቶ፣ “እርሷ ሚስትህ ሆና ሳለች፣ እንዴት ‘እኅቴ ናት’ ትላለህ?” አለው።ይሥሐቅም፣ “በርሷ ሰበብ፣ ሕይወቴን እንዳላጣ ብዬ ነው” አለው። 10.አቢሜሌክም መልሶ፣ “እንዲህ ያለ ነገር ያደረግህብን ለምንድን ነው? ከሰዎቻችን አንዱ ሚስትህን ቢደፍራት ኖሮ በእኛ ላይ በደል አስከትለህብን ነበር እኮ!” አለው። 11.አቢሜሌክም፣ “ይህን ሰው ወይም ሚስቱን የነካ በሞት ይቀጣል” የሚል ትእዛዝ ለሕዝቡ ሁሉ አወጣ። 12.ይሥሐቅም በዚያች ምድር ዘር ዘራ፣ እግዚአብሔርም ባረከለትና በዚያ ዓመት መቶ ዕጥፍ አመረተ። 13.ሰውየውም እጅግ ባለጠጋ እስኪሆን ድረስ ሀብት በሀብት ላይ እየተጨመረለት ሄደ። 14.ብዙ የበግና የፍየል መንጋ፣ ብዙ ከብት፣ ብዙ አገልጋዮችም ስለ ነበሩት፣ ፍልስጥኤማውያን ተመቀኙት። 15.ከዚህ የተነሣ ፍልስጥኤማውያን፣ አባቱ አብርሃም በሕይወት በነበረበት ጊዜ፣ የአብርሃም አገልጋዮች የቈፈሯቸውን የውሃ ጕድጓዶች በሙሉ ዐፈር ሞልተው ደፈኗቸው። 16.አቢሜሌክም ይሥሐቅን፣ “ከእኛ ይልቅ ኀያል ሆነሃልና አገራችንን ልቀቅልን” አለው። 17.ይሥሐቅም ያን ቦታ ትቶ ሄደ፤ በጌራራ ሸለቆም ተቀመጠ። 18.ይሥሐቅም በአባቱ በአብርሃም ጊዜ ተቈፍረው የነበሩትን፣ አባቱ ከሞተ በኋላ ፍልስጥኤማውያን የደፈኗቸውን የውሃ ጕድጓዶች እንደ ገና እንዲከፈቱ አደረገ፤ አባቱ ቀድሞ ባወጣላቸው ስምም መልሶ ጠራቸው። 19.የይሥሐቅ አገልጋዮች በሸለቆው ውስጥ ሲቈፍሩ፣ ከጕድጓዱ የሚፈልቅ ውሃ አገኙ። 20.የጌራራ እረኞች ግን፣ “ውሃው የእኛ ነው” በማለት ከይሥሐቅ እረኞች ጋራ ጠብ አነሡ፤ ከዚህ የተነሣ ይሥሐቅ ያን የውሃ ጕድጓድ ኤሴቅ ብሎ ጠራው፤ በጕድጓዱ ምክንያት ተጣልተውታልና። 21.አሁንም እንደ ገና ሌላ የውሃ ጕድጓድ ቈፈሩ፤ አሁንም ሌላ ግጭት ተፈጠረ፤ ስለዚህ የውሃ ጕድጓዱን ስጥና ብሎ ጠራው። 22.ይሥሐቅም ያን ቦታ ትቶ ሌላ ስፍራ ላይ የውሃ ጕድጓድ አስቈፈረ፤ በዚህ ጊዜ ግን አንድም ሰው ጠብ አላነሣበትም፤ ስለዚህ ያን የውሃ ጕድጓድ፣ “አሁን እግዚአብሔር ሰፊ ቦታ ሰጥቶናል፤ እኛም በምድር ላይ እንበዛለን” ሲል ርኆቦት ብሎ ጠራው። 23.ከዚያም ይሥሐቅ ወደ ቤርሳቤህ ወጣ። 24.በዚያም ሌሊት እግዚአብሔር ተገለጠለትና፣ “እኔ የአባትህ የአብርሃም አምላክ ነኝ፤ ከአንተ ጋራ ነኝና አትፍራ፤ እባርክሃለሁ፤ ስለ አገልጋዬም ስለ አብርሃም ስል ዘርህን አበዛለሁ” አለው። 25.ይሥሐቅም በዚያ ስፍራ መሠዊያ ሠርቶ፣ የእግዚአብሔርን ስም ጠራ፤ ድንኳንም ተከለ፤ አገልጋዮቹም በዚያ የውሃ ጕድጓድ ቈፈሩ። 26.አቢሜሌክም ከአማካሪው ከአዘኮትና ከሰራዊቱ አዛዥ ከፊኮል ጋራ ከጌራራ ተነሥቶ ይሥሐቅ ወዳለበት ስፍራ መጣ። 27.ይሥሐቅም፣ “ጠልታችሁኝ ካባረራችሁኝ በኋላ፣ አሁን ደግሞ ለምን መጣችሁ?” ብሎ ጠየቃቸው። 28.እነርሱም እንዲህ አሉ፤ “እግዚአብሔር ከአንተ ጋራ መሆኑን በግልጽ ተረድተናል፤ ስለዚህም፣ ‘በመሐላ የጸና ውል በመካከላችን መኖር አለበት’ አልን፤ ይህም በእኛና በአንተ መካከል የሚጸና ውል ነው፤ አሁንም ከአንተ ጋራ ስምምነት እናድርግ፤ 29.አንተን እንዳልጐዳንህ፣ ነገር ግን በጎነትን እንዳሳየንህና በሰላም እንደ ሸኘንህ ሁሉ፣ አንተም ክፉ እንዳታደርግብን በመካከላችን ውል ይደረግ፤ አንተን እንደሆን መቼም እግዚአብሔር ባርኮሃል።” 30.ይሥሐቅም ድግስ ደግሶ አበላቸው፤ አጠጣቸው። 31.በማግስቱም በማለዳ ተነሥተው፣ በመካከላቸው መሐላ ፈጸሙ። ይሥሐቅም አሰናበታቸው፤ እነርሱም በሰላም ሄዱ። 32.በዚያ ዕለት፣ የይሥሐቅ አገልጋዮች መጥተው ስለ ቈፈሩት የውሃ ጕድጓድ ነገሩት፤ “ውሃ እኮ አገኘን!” አሉት። 33.እርሱም የውሃውን ጕድጓድ ሳቤህ አለው፤ ከዚያም የተነሣ የከተማዪቱ ስም እስከ ዛሬ ድረስ ቤርሳቤህ ተብሎ ይጠራል። 34.ዔሳው አርባ ዓመት በሆነው ጊዜ፣ የኬጢያዊውን የብኤሪን ልጅ ዮዲትን እንዲሁም የኬጢያዊውን የኤሎንን ልጅ ቤሴሞትን አገባ፤ 35.በእነዚህም ሴቶች ምክንያት የይሥሐቅና የርብቃ ልብ ያዝን ነበር።
ምዕራፍ 27
ይሥሐቅ ያዕቆብን ባረከው
1.ይሥሐቅ አርጅቶ፣ ዐይኖቹ ደክመው ማየት በተሳናቸው ጊዜ፣ ታላቁን ልጁን ዔሳውን ጠርቶ፣ “ልጄ ሆይ” አለው።እርሱም፣ “እነሆ፤ አለሁ” አለ። 2.ይሥሐቅም እንዲህ አለ፤ “ይኸው እኔ አርጅቻለሁ፤ የምሞትበትንም ቀን አላውቅም 3.ስለዚህ የዐደን መሣሪያህን፦ የፍላጻ ኰረጆህንና ቀስትህን ይዘህ ወደ ዱር ሂድ፤ አድነህም አምጣልኝ። 4.ከመሞቴ በፊት እንድመርቅህ የምወድደውን ዐይነት ጣዕም ያለው ምግብ አዘጋጅተህ አብላኝ።” 5.ይሥሐቅ ለልጁ የተናገረውን ርብቃ ትሰማ ስለ ነበር፣ ዔሳው የታዘዘውን ለማምጣት ለዐደን እንደ ወጣ፣ 6.ርብቃ ለልጇ ለያዕቆብ እንዲህ አለችው፤ “አባትህ ዔሳውን፣ 7.‘ከመሞቴ በፊት በእግዚአብሔር ፊት እንድመርቅህ፣ ጥሩ ጣዕም ያለው ምግብ እንድበላ አዘጋጅልኝ።’ ሲለው ሰምቻለሁ፤ 8.ልጄ ሆይ፤ እንግዲህ የምነግርህን በጥሞና ስማኝ፤ የምልህንም አድርግ። 9.ተነሣና ወደ መንጋው ሄደህ ሁለት ፍርጥም ያሉ የፍየል ጠቦቶች አምጣልኝ፤ እኔም አባትህ የሚወድደውን ዐይነት ምግብ አዘጋጅለታለሁ፤ 10.እርሱም ከመሞቱ በፊት እንዲመርቅህ ይዘህለት ግባና ይብላ።” 11.ያዕቆብም እናቱን ርብቃን እንዲህ አላት፤ “ወንድሜ ዔሳው ሰውነቱ ጠጕራም ነው፤ የእኔ ገላ ግን ለስላሳ ነው። 12.ታዲያ፣ አባቴ ቢዳስሰኝ እንዳታለልሁት ያውቃል፤ ይህ ከሆነ ደግሞ፣ በምርቃት ፈንታ ርግማን አተርፋለሁ ማለት ነው።” 13.እናቱም፣ “ልጄ ሆይ፤ የአንተ ርግማን በእኔ ላይ ይድረስ፤ ግድ የለህም፤ እንደ ነገርሁህ ሄደህ ጠቦቶቹን አምጣልኝ” አለችው። 14.እርሱም ሄዶ ጠቦቶቹን ለእናቱ አመጣላት፤ እርሷም ልክ አባቱ እንደሚወድደው ዐይነት አጣፍጣ ጥሩ ምግብ አዘጋጀችለት። 15.ከዚያም ርብቃ በቤት ያስቀመጠችውን የታላቁን ልጇን የዔሳውን ምርጥ ልብስ አንሥታ ለታናሹ ልጇ ለያዕቆብ አለበሰችው። 16.እንዲሁም የዐንገቱን ለስላሳ ክፍል የጠቦቶቹን ቈዳ አለበሰችው። 17.ከዚያም ያሰናዳችውን ጣፋጭ መብልና እንጀራ ለያዕቆብ ሰጠችው። 18.ያዕቆብም ወደ አባቱ ሄዶ፣ “አባቴ ሆይ” አለ፤ ይሥሐቅም፣ “እነሆ፤ አለሁ ልጄ፤ ለመሆኑ አንተ ማን ነህ?” አለው። 19.ያዕቆብም አባቱን፣ “እኔ የበኵር ልጅህ ዔሳው ነኝ፤ ያዘዝኸኝን አድርጌአለሁ፤ እስኪ ቀና በልና እንድትመርቀኝ ዐድኜ ካመጣሁት ብላ” አለ። 20.ይሥሐቅ ልጁን፣ “ልጄ ሆይ፤ ከመቼው ቀንቶህ መጣህ?” ሲል ጠየቀው። ያዕቆብም፣ “እግዚአብሔር አምላክህ አሳካልኝ” ብሎ መለሰለት። 21.ይሥሐቅም ያዕቆብን፣ “ልጄ ሆይ፤ አንተ በርግጥ ልጄ ዔሳው መሆንህን እንዳውቅ፣ እስኪ ቀረብ በልና ልዳብስህ” አለው። 22.ያዕቆብም ወደ አባቱ ወደ ይሥሐቅ ተጠጋ፤ አባቱም በእጁ እየዳሰሰው፣ “ይህ ድምፅ የያዕቆብ ድምፅ ነው፤ እጆቹ ግን የዔሳው እጆች ናቸው” አለ። 23.እጆቹ እንደ ወንድሙ እንደ ዔሳው እጆች ጠጕራም ስለ ሆኑ፣ ይሥሐቅ ያዕቆብን ለይቶ ማወቅ አልቻለም፤ ስለዚህ ባረከው። 24.ይሥሐቅም፣ “በርግጥ አንተ ልጄ ዔሳው ነህ?” ሲል ጠየቀው።
ያዕቆብም፣ “አዎን፤ ነኝ” ብሎ መለሰ። 25.ከዚያም፣ “በል እንግዲህ ልጄ፤ እንድመርቅህ፣ ዐድነህ ካመጣኸው አቅርብልኝና ልብላ” አለው።
ያዕቆብም ምግቡን ለአባቱ አቀረበለት፤ የወይን ጠጅም አመጣለት፤ እርሱም በላ፤ ጠጣም። 26.ከዚያም አባቱ ይሥሐቅ፣ ያዕቆብን፣ “ልጄ ሆይ፤ እስኪ ቀረብ በልና ሳመኝ” አለው። 27.ያዕቆብም ቀርቦ ሳመው፤ ይሥሐቅ የያዕቆብን ልብስ ካሸተተ በኋላ እንዲህ ብሎ መረቀው፤
“እነሆ፤ የልጄ ጠረን፣
እግዚአብሔር እንደ ባረከው፣
እንደ መስክ መዐዛ ነው። 28.እግዚአብሔር የሰማይን ጠል፣
የምድርንም በረከት፣
የተትረፈረፈ እህልና የወይን ጠጅ ይስጥህ። 29.መንግሥታት ይገዙልህ፤
ሕዝቦችም ተደፍተው እጅ ይንሡህ፤
የወንድሞችህ ጌታ ሁን፤
የእናትህም ልጆች ተደፍተው እጅ ይንሡህ፤
የሚረግሙህ የተረገሙ ይሁኑ፤
የሚባርኩህ የተባረኩ ይሁኑ።” 30.ይሥሐቅ ያዕቆብን መርቆ እንዳበቃ፣ ያዕቆብ ገና ከአባቱ ዘንድ ሳይወጣ ወዲያውኑ፣ ወንድሙ ዔሳው ከዐደን ተመለሰ። 31.እርሱም ደግሞ ጣፋጭ ምግብ በማዘጋጀት ለአባቱ አቅርቦ፣ “አባቴ ሆይ፤ እንድትመርቀኝ፣ እስኪ ቀና በልና ካደንሁት ብላ” አለው። 32.አባቱ ይሥሐቅም፣ “አንተ ደግሞ ማን ነህ?” ሲል ጠየቀው። እርሱም፣ “እኔማ የበኵር ልጅህ ዔሳው ነኝ” አለው። 33.በዚህ ጊዜ ይሥሐቅ ክፉኛ እየተንቀጠቀጠ፣ “ታዲያ ቀደም ሲል ዐድኖ ያመጣልኝ ማን ነበር? አንተ ከመምጣትህ በፊት በልቼ መረቅሁት፤ እርሱም በርግጥ የተባረከ ይሆናል” አለው። 34.ዔሳው የአባቱን ቃል ሲሰማ፣ ድምፁን ከፍ በማድረግ ምርር ብሎ አለቀሰ፤ አባቱንም፣ “አባቴ ሆይ፤ እኔንም ደግሞ እባክህ መርቀኝ” አለው። 35.ይሥሐቅም፣ “ወንድምህ መጥቶ አታልሎኝ ምርቃትህን ወስዶብሃል” አለው። 36.ዔሳውም፣ “ይህ ሰው ያዕቆብ መባሉ ትክክል አይደለምን? እኔን ሲያታልለኝ ይህ ሁለተኛ ጊዜው ነው፤ መጀመሪያ ብኵርናዬን ወሰደብኝ፤ አሁን ደግሞ ምርቃቴን ቀማኝ” አለ። ቀጥሎም፣ “ታዲያ ለእኔ ያስቀረኸው ምንም ምርቃት የለም?” ብሎ ጠየቀ። 37.ይሥሐቅም ለዔሳው፣ “በአንተ ላይ የበላይነት እንዲኖረው፣ ወንድሞቹ ሁሉ አገልጋዮቹ እንዲሆኑ፣ እህሉ፣ የወይን ጠጁም የተትረፈረፈ እንዲሆንለት መርቄዋለሁ። ታዲያ ልጄ፣ ለአንተ ምን ላደርግልህ እችላለሁ?” ሲል መለሰለት። 38.ዔሳውም አባቱን፣ “አባቴ ሆይ፤ ምርቃትህ ይህችው ብቻ ናትን? እባክህ አባቴ፣ እኔንም መርቀኝ” አለው፤ ድምፁንም ከፍ አድርጎ አለቀሰ። 39.አባቱ ይሥሐቅም እንዲህ ሲል መለሰለት፤
“መኖሪያህ
ከምድር በረከት፣
ከላይም ከሰማይ ጠል የራቀ ይሆናል፤ 40.በሰይፍ ትኖራለህ፤
የወንድምህም አገልጋይ ትሆናለህ።
አምርረህ በተነሣህ ጊዜ ግን፣
ቀንበሩን ከጫንቃህ ላይ፣
ወዲያ ትጥላለህ።”
ያዕቆብ ወደ ላባ ሸሸ
41.አባቱ ያዕቆብን ስለ መረቀው፣ ዔሳው በያዕቆብ ላይ ቂም ያዘ፤ በልቡም፣ “ግድ የለም፤ የአባቴ መሞቻው ተቃርቧል፤ ከልቅሶው በኋላ ወንድሜን ያዕቆብን እገድላለሁ” ብሎ ዐሰበ። 42.ርብቃ፣ ታላቁ ልጇ ዔሳው ያሰበው በተነገራት ጊዜ ታናሹን ልጇን ያዕቆብን አስጠርታ እንዲህ አለችው፤ “ወንድምህ ዔሳው ሊገድልህ ጊዜ እየጠበቀ ነው፤ 43.አሁንም ልጄ ሆይ፤ እኔ የምልህን አድርግ፤ በካራን ምድር ወደሚኖረው ወደ ላባ ቶሎ ሽሽ። 44.የወንድምህ ቍጣ እስከሚበርድ እዚያው ቈይ፤ 45.ነገር ግን ቍጣው በርዶለት ያደረግህበትን ከረሳ በኋላ፣ እንድትመለስ እልክብህና ትመጣለህ። ሁለታችሁንም በአንድ ቀን ለምን ልጣ?” 46.ከዚያም ርብቃ ይሥሐቅን፣ “ዔሳው ባገባቸው በኬጢያውያን ሴቶች ምክንያት መኖር አስጠልቶኛል፤ ያዕቆብም ከዚሁ አገር ከኬጢያውያን ሴቶች ሚስት የሚያገባ ከሆነ፣ ሞቴን እመርጣለሁ” አለችው።የማርቆስ ወንጌል
ምዕራፍ 10
የባልና የሚስት ፍች
10፥1-12 ተጓ ምብ – ማቴ 19፥1-9
1.ኢየሱስ ከዚያ ተነሥቶ ከዮርዳኖስ ማዶ ወዳለው ወደ ይሁዳ አውራጃ ሄደ፤ ሕዝቡም እንደ ገና በዙሪያው ተሰበሰበ፤ ከዚህ ቀደም ያደርገው እንደ ነበረውም አስተማራቸው።
2.አንዳንድ ፈሪሳውያንም መጥተው፣ “አንድ ባል ሚስቱን እንዲፈታ ተፈቅዷልን?” ብለው ሊፈትኑት ጠየቁት።
3.እርሱም መልሶ፣ “ሙሴ ምን ብሎ አዘዛችሁ?” አላቸው።
4.እነርሱም፣ “ሙሴማ የፍችውን ጽሕፈት ጽፎ እንዲፈታት ፈቅዷል” አሉ።
5.ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “ሙሴ ይህን ሕግ የጻፈላችሁ ልባችሁ ደንዳና በመሆኑ ነው።
6.ነገር ግን በፍጥረት መጀመሪያ እግዚአብሔር ‘ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው።’
7.‘ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፤ ከሚስቱም ጋራ ይጣመራል፤
8.ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ።’ ከእንግዲህ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ሁለት አይደሉም።
9.ስለዚህ እግዚአብሔር ያጣመረውን ሰው አይለየው።”
10.እንደ ገና ወደ ቤት በገቡ ጊዜ፣ ደቀ መዛሙርቱ ይህንኑ አንሥተው ጠየቁት።
11.እርሱም፣ “ማንም ሚስቱን ፈትቶ ሌላዪቱን የሚያገባ በርሷ ላይ ያመነዝራል።
12.እርሷም ባሏን ፈትታ ሌላ ብታገባ ታመነዝራለች” አላቸው።
ኢየሱስ ሕፃናትን ባረከ
10፥13-16 ተጓ ምብ – ማቴ 19፥13-15፤ ሉቃ 18፥15-17
13.ኢየሱስ እንዲዳስሳቸው፣ ሰዎች ሕፃናትን ወደ እርሱ አመጡ፤ ደቀ መዛሙርቱ ግን ገሠጿቸው።
14.ኢየሱስም ይህን ሲያይ ተቈጥቶ እንዲህ አላቸው፤ “ሕፃናት ወደ እኔ እንዲመጡ ፍቀዱላቸው፤ አትከልክሏቸውም፤ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደ እነዚህ ላሉት ናትና።
15.እውነት እላችኋለሁ፤ የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደ ሕፃን የማይቀበል ሁሉ ከቶ አይገባባትም።”
16.ሕፃናቱንም ዐቀፋቸው፤ እጁንም ጭኖ ባረካቸው።
ሀብታሙ ወጣት
10፥17-31 ተጓ ምብ – ማቴ 19፥16-30፤ ሉቃ 18፥18-30
17.ከዚያ ተነሥቶ መንገዱን ሲጀመር፣ አንድ ሰው ወደ እርሱ እየሮጠ መጣ፤ በፊቱም በጕልበቱ ተንበርክኮ፣ “መልካም መምህር ሆይ፤ የዘላለምን ሕይወት ለመውረስ ምን ማድረግ ይገባኛል” አለው።
18.ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ስለ ምን ቸር ትለኛለህ? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር መልካም ማንም የለም፤
19.‘አታመንዝር፣ አትግደል፣ አትስረቅ፣ በሐሰት አትመስክር፣ አታታልል፣ አባትህንና እናትህን አክብር’ የሚለውን ትእዛዝ ታውቃለህ።”
20.ሰውየውም፣ “መምህር ሆይ፤ እነዚህን ሁሉ ከልጅነቴ ጀምሮ ጠብቄአለሁ” አለው።
21.ኢየሱስም ተመለከተውና ወደደው፤ “እንግዲያው አንድ ነገር ይጐድልሃል፤ ሂድና ያለህን ሁሉ ሸጠህ ለድኾች ስጥ፤ በሰማይ ሀብት ይኖርሃል፤ ከዚያም መጥተህ ተከተለኝ” አለው።
22.ሰውየው ይህን ሲሰማ ክፉኛ አዘነ፤ ብዙ ሀብት ስለ ነበረው እየተከዘ ሄደ።
23.ኢየሱስ ዙሪያውን በመመልከት ደቀ መዛሙርቱን፣ “ለሀብታሞች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት ምንኛ ከባድ ነገር ነው!” አላቸው።
24.ደቀ መዛሙርቱም በንግግሩ ተገረሙ፤ ኢየሱስ ግን እንደ ገና መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “ልጆች ሆይ፤ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት ምንኛ ከባድ ነገር ነው!
25.ሀብታም ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ይልቅ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀልለዋል።”
26.ደቀ መዛሙርቱም ይበልጥ በመገረም፣ “ታዲያ ማን ሊድን ይችላል?” ተባባሉ።
27.ኢየሱስም አያቸውና፣ “ይህ በሰው ዘንድ አይቻልም፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን እንዲህ አይደለም፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ሁሉም ነገር ይቻላል” አላቸው።
28.ጴጥሮስም፣ “እነሆ፤ እኛ ሁሉን ትተን ተከትለንሃል!” አለው።
29.ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለ፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ ስለ እኔና ስለ ወንጌል ሲል ቤትን ወይም ወንድሞችን ወይም እኅቶችን ወይም እናትን ወይም አባትን ወይም ልጆችን ወይም ዕርሻን የተወ ሁሉ፣
30.አሁን በዚህ ዘመን ከስደት ጋራ ቤቶችን፣ ወንድሞችን፣ እኅቶችን፣ እናቶችን፣ ልጆችንና ዕርሻን መቶ ዕጥፍ የማይቀበል፣ በሚመጣውም ዓለም የዘላለም ሕይወት የማይወርስ የለም።
31.ነገር ግን ብዙ ፊተኞች ኋለኞች፣ ኋለኞችም ፊተኞች ይሆናሉ።”ኢየሱስ ዳግም ስለ ሞቱ አስቀድሞ ተናገረ
10፥32-34 ተጓ ምብ – ማቴ 20፥17-19፤ ሉቃ 18፥31-33
32.ወደ ኢየሩሳሌም ለመውጣት በመንገድ ላይ ሳሉ፣ ኢየሱስ ፊት ፊታቸው ይሄድ ነበር፤ ደቀ መዛሙርቱ ተገረሙ፣ ሌሎች የተከተሉት ደግሞ ፈርተው ነበር። ደግሞም ዐሥራ ሁለቱን ከሕዝቡ ለይቶ ምን እንደሚደርስበት ነገራቸው፤
33.እንዲህም አላቸው፤ “እንግዲህ ወደ ኢየሩሳሌም እንወጣለን፤ የሰው ልጅ ለካህናት አለቆችና ለጸሐፍት ዐልፎ ይሰጣል፤ እነርሱም የሞት ፍርድ ይፈርዱበታል፤ አሳልፈው ለአሕዛብ ይሰጡታል፤
34.ያፌዙበታል፤ ይተፉበታል፤ ይገርፉታል፤ ከዚያም ይገድሉታል፤ እርሱ ግን ከሦስት ቀን በኋላ ይነሣል።”
የያዕቆብና የዮሐንስ ጥያቄ
10፥35-45 ተጓ ምብ – ማቴ 20፥20-28
35.ከዚያም የዘብዴዎስ ልጆች ያዕቆብና ዮሐንስ ወደ እርሱ ቀርበው፣ “መምህር ሆይ፤ የምንለምንህን ሁሉ እንድታደርግልን እንፈልጋለን” አሉት።
36.እርሱም፣ “ምን እንዳደርግላችሁ ትፈልጋላችሁ?” አላቸው።
37.እነርሱም፣ “በክብርህ ጊዜ አንዳችን በቀኝህ፣ አንዳችን በግራህ እንድንቀመጥ ፍቀድልን” አሉት።
38.ኢየሱስም፣ “የምትለምኑትን አታውቁም፤ እኔ የምጠጣውን ጽዋ ልትጠጡ፣ የምጠመቀውንስ ጥምቀት ልትጠመቁ ትችላላችሁን?” አላቸው።
39.እነርሱም፣ “አዎን እንችላለን” አሉት።ኢየሱስም፣ “እኔ የምጠጣውን ጽዋ ትጠጣላችሁ፤ እኔ የምጠመቀውንም ጥምቀት ትጠመቃላችሁ፤ 40.ነገር ግን በቀኜ ወይም በግራዬ መቀመጥ ለተዘጋጀላቸው የሚሆን እንጂ እኔ የምሰጠው ነገር አይደለም” አላቸው። 41.ዐሥሩ ይህን ሲሰሙ፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን መቈጣት ጀመሩ። 42.ኢየሱስም ወደ ራሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “የአሕዛብ ገዦች ተብለው የሚታሰቡት እንደሚገዟቸው፣ ባለሥልጣኖቻቸውም በእነርሱ ላይ እንደሚሠለጥኑባቸው ታውቃላችሁ፤ 43.በእናንተ ዘንድ ግን እንዲህ አይደለም፤ ከመካከላችሁ ታላቅ መሆን የሚፈልግ ሁሉ አገልጋይ ይሁን፤ 44.ፊተኛ ለመሆን የሚፈልግ ሁሉ፣ የሁሉ ባሪያ ይሁን፤ 45.የሰው ልጅ እንዲያገለግሉት ሳይሆን፣ ለማገልገልና ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ አድርጎ ለመስጠት መጥቷልና።”
ኢየሱስ ዐይነ ስውሩን በርጤሜዎስን ፈወሰ
10፥46-52 ተጓ ምብ – ማቴ 20፥29-34፤ ሉቃ 18፥35-43
46.ከዚህ በኋላ ወደ ኢያሪኮ መጡ። ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ከብዙ ሕዝብ ጋራ ከኢያሪኮ ሲወጡ ዐይነ ስውሩ የጤሜዎስ ልጅ በርጤሜዎስ በመንገድ ዳር ተቀምጦ ይለምን ነበር።
47.እርሱም የናዝሬቱ ኢየሱስ መሆኑን በሰማ ጊዜ፣ “የዳዊት ልጅ፣ ኢየሱስ ሆይ፤ ማረኝ!” እያለ ይጮኽ ጀመር።
48.ብዙዎችም ዝም እንዲል ገሠጹት፤ እርሱ ግን፣ “የዳዊት ልጅ ሆይ፤ ማረኝ!” እያለ የባሰ ጮኸ።
49.ኢየሱስም ቆም ብሎ፣ “ጥሩት” አላቸው።እነርሱም ዐይነ ስውሩን፣ “አይዞህ፤ ተነሥ፤ ይጠራሃል!” አሉት። 50.እርሱም ልብሱን ጥሎ፣ ዘልሎ ተነሥቶ ወደ ኢየሱስ መጣ። 51.ኢየሱስም፣ “ምን እንዳደርግልህ ትፈልጋለህ?” አለው።
ዐይነ ስውሩም፣ “መምህር ሆይ፤ ዳግም እንዳይ እፈልጋለሁ” አለው። 52.ኢየሱስም፣ “ሂድ፣ እምነትህ አድኖሃል” አለው፤ ወዲያውም ዐይኑ በራለት፤ በመንገድም ኢየሱስን ተከትሎት ሄደ።