Skip to Content
የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን | YEHIWOT MELHEK BETEKIRSTIAN
የ2019 ዓ.ም የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ 📖 ዛሬን አንብብ →

የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን

Yehiwot Melhek Betekirstian

ሳምንት 2 · ቀን 8 (ረቡዕ) 📅 Meskerem 13, 2019

ኦሪት ዘፍጥረት 21, 22, 23 · መዝሙረ ዳዊት 107 · የማርቆስ ወንጌል 8

📖 የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም፦ 1954 መጽሐፍ ቅዱስ አዲሱ መደበኛ ትርጒም

ኦሪት ዘፍጥረት

ምዕራፍ 21

1.እግዚአብሔርም እንደ ተናገረው ሣራን አሰበ፤ እግዚአብሔርም እንደ ተናገረው ለሣራ አደረገላት።2.ሣራም ፀነሰች፥ እግዚአብሔርም በተናገረው ወራት ለአብርሃም በእርጅናው ወንድ ልጅን ወለደችለት።3.አብርሃምም የተወለደለትን ሣራ የወለደችለትን የልጁን ስም ይስሐቅ ብሎ ጠራው።4.አብርሃምም ልጁን ይስሐቅን እግዚአብሔር እንዳዘዘው በስምንተኛ ቀን ገረዘው።5.አብርሃምም ልጁ ይስሐቅ በተወለደለት ጊዜ የመቶ ዓመት ዕድሜ ነበረ።6.ሣራም። እግዚአብሔር ሳቅ አድርጎልኛል፤ ይህንንም የሚሰማ ሁሉ በእኔ ምክንያት ይስቃል አለች።7.ደግሞም። ሣራ ልጆችን እንድታጠባ ለአብርሃም ማን በነገረው? በእርጅናው ልጅን ወልጄለታለሁና አለች።8.ሕፃኑም አደገ፥ ጡትንም ከመጥባት ተቋረጠ፤ አብርሃምም ይስሐቅን ጡት ባስጣለበት ቀን ትልቅ ግብዣን አደረገ።9.ሣራም ግብፃዊቱ አጋር ለአብርሃም የወለደችለትን ልጅ ሲስቅ አየችው።10.አብርሃምንም። ይህችን ባሪያ ከነልጅዋ አሳድድ፤ የዚህች ባሪያ ልጅ ከልጄ ከይስሐቅ ጋር አይወርስምና አለችው።11.ይህም ነገር በአብርሃም ዘንድ ስለ ልጁ እጅግ ችግር ሆነበት።12.እግዚአብሔርም አብርሃምን አለው። ስለ ባሪያህና ስለ ብላቴናው አትዘን፤ ሣራም የምትነግርህን ቃል ሁሉ ስማ፤ በይስሐቅ ዘር ይጠራልሃልና።13.የባሪያይቱን ልጅ ደግሞ ሕዝብ አደርገዋለሁ፥ ዘርህ ነውና።14.አብርሃምም ማልዶ ተነሣ፥ እንጀራንም ወሰደ፥ የውኃ አቁማዳንም ለአጋር በትከሻዋ አሸከማት፥ ብላቴናውንም ሰጥቶ አስወጣት፤ እርስዋም ሄደች በቤርሳቤህም ምድረ በዳ ተቅበዘበዘች።15.ውኃውም ከአቁማዳው አለቀ፤ ብላቴናውንም ከአንድ ቍጥቋጦ በታች ጣለችው፤16.እርስዋም ሄደች። ብላቴናው ሲሞት አልየው ብላ ቀስት ተወርውሮ የሚደርስበትን ያህል ርቃ በአንጻሩ ተቀመጠች። ፊት ለፊትም ተቀመጠች፥ ቃልዋንም አሰምታ አለቀሰች።17.እግዚአብሔርም የብላቴናውን ድምፅ ሰማ፤ የእግዚአብሔርም መልአክ ከሰማይ አጋርን እንዲህ ሲል ጠራት። አጋር ሆይ፥ ምን ሆንሽ? እግዚአብሔር የብላቴናውን ድምፅ ባለበት ስፍራ ሰምቶአልና አትፍሪ።18.ተነሺ፥ ብላቴናውንም አንሺ፥ እጅሽንም በእርሱ አጽኚው፤ ትልቅ ሕዝብ አደርገዋለሁና።19.እግዚአብሔርም ዓይንዋን ከፈተላት፥ የውኃ ጕድጓድንም አየች፤ ሄዳም አቁማዳውን በውኃ ሞላች፥ ብላቴናውንም አጠጣች።20.እግዚአብሔርም ከብላቴናው ጋር ነበረ፤ አደገም፥ በምድረ በዳም ተቀመጠ፥ ቀስተኛም ሆነ።21.በፋራን ምድረ በዳም ተቀመጠ፤ እናቱም ከምድረ ግብፅ ሚስት ወሰደችለት።22.በዚያም ዘመን አቢሜሌክ ከሙሽራው ወዳጅ ከአኮዘትና ከሠራዊቱ አለቃ ከፊኮል ጋር አብርሃምን አለው። በምታደርገው ሁሉ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነው፤23.አሁንም በእኔም በልጄም በልጅ ልጄም ክፉ እንዳታደርግብኝ በእግዚአብሔር ማልልኝ፤ ነገር ግን ለአንተ ቸርነትን እንዳደረግሁ አንተም ለእኔ ለተቀመጥህባትም ምድር ቸርነትን ታደርጋለህ።24.አብርሃምም። እኔ እምላለሁ አለ።25.አቢሜሌክንም ባሪያዎቹ በነጠቁት በውኃ ጕድጓድ ምክንያት አብርሃም ወቀሰው።26.አቢሜሌክም አለ። ይህን ነገር ያደረገውን አላወቅሁም፤ አንተም ደግሞ ምንም አልነገርኸኝም፥ እኔም ከዛሬ በቀር አልሰማሁም።27.አብርሃምም በጎችንና ላሞችን አምጥቶ ለአቢሜሌክ ሰጠው፤ ሁለቱም ቃል ኪዳን አደረጉ።28.አብርሃምም ሰባት ቄቦች በጎችን ለብቻቸው አቆመ።29.አቢሜሌክም አብርሃምን። ለብቻቸው ያቆምሃቸው እነዚህ ሰባት ቄቦች በጎች ምንድር ናቸው? አለው።30.እርሱም። እኔ ይህችን የውኃ ጕድጓድ እንደቆፈርሁ ምስክር ይሆንልኝ ዘንድ እነዚህን ሰባት ቄቦች በጎች ከእጄ ትወስዳለህ አለው።31.ስለዚህ የዚያን ስፍራ ስም ቤርሳቤህ ብሎ ጠራው፤ ከዚያ ሁለቱ ተማምለዋልና።32.በቤርሳቤህም ቃል ኪዳንን አደረጉ። አቢሜሌክና የሙሽራው ወዳጅ አኮዘት የሠራዊቱ አለቃ ፊኮልም ተነሥተው ወደ ፍልስጥኤም ምድር ተመለሱ።33.አብርሃምም በቤርሳቤህ የተምር ዛፍን ተከለ፤ በዚያም የዘላለሙን አምላክ የእግዚአብሔርን ስም ጠራ።34.አብርሃምም በፍልስጥኤም ምድር ብዙ ቀን እንግዳ ሆኖ ተቀመጠ።

ምዕራፍ 22

1.ከእነዚህም ነገሮች በኋላ እግዚአብሔር አብርሃምን ፈተነው፥ እንዲህም አለው። አብርሃም ሆይ። አብርሃምም። እነሆ፥ አለሁ አለ።2.የምትወደውን አንድ ልጅህን ይስሐቅን ይዘህ ወደ ሞሪያም ምድር ሂድ፤ እኔም በምነግርህ በአንድ ተራራ ላይ በዚያ መሥዋዕት አድርገህ ሠዋው አለ።3.አብርሃምም በማለዳ ተነሥቶ አህያውን ጫነ፥ ሁለቱንም ሎሌዎቹንና ልጁን ይስሕቅን ከእርሱ ጋር ወሰደ፥ እንጨትንም ለመሥዋዕት ሰነጠቀ፤ ተነሥቶም እግዚአብሔር ወዳለው ቦታ ሄደ።4.በሦስተኛውም ቀን አብርሃም ዓይኑን አነሣና ቦታውን ከሩቅ አየ።5.አብርሃምም ሎሌዎቹን አላቸው። አህያውን ይዛችሁ ከዚህ ቆዩ፤ እኔና ልጄ ወደዚያ ሄደን እንሰግዳለን፥ ወደ እናንተም እንመለሳለን።6.አብርሃምም የመሥዋዕቱን እንጨት አንሥቶ ለልጁ ለይስሐቅ አሸከመው፤ እርሱም እሳቱንና ቢላዋውን በእጁ ያዘ፥ ሁለቱም አብረው ሄዱ።7.ይስሐቅም አባቱን አብርሃምን ተናገረው። አባቴ ሆይ አለ። እርሱም። እነሆኝ፥ ልጄ አለው። እሳቱና እንጨቱ ይኸው አለ፤ የመሥዋዕቱ በግ ግን ወዴት ነው? አለ።8.አብርሃምም። ልጄ ሆይ፥ የመሥዋዕቱን በግ እግዚአብሔር ያዘጋጃል አለው፤ ሁለቱም አብረው ሄዱ።9.እግዚአብሔር ወዳለውም ቦታ ደረሱ፤ አብርሃምም በዚያ መሠዊያውን ሠራ፥ እንጨትንም ረበረበ፤ ልጁን ይስሐቅንም አስሮ በመሠዊያው በእንጨቱ ላይ አጋደመው።10.አብርሃምም እጁን ዘረጋ፥ ልጁንም ያርድ ዘንድ ቢላዋ አነሣ።11.የእግዚአብሔር መልአክም ከሰማይ ጠራና። አብርሃም አብርሃም አለው፤12.እርሱም። እነሆኝ አለ። እርሱም። በብላቴናው ላይ እጅህን አትዘርጋ፥ አንዳችም አታድርግበት፤ አንድ ልጅህን ለእኔ አልከለከልህምና እግዚአብሔርን የምትፈራ እንደ ሆንህ አሁን አውቄአለሁ አለ።13.አብርሃምም ዓይኑን አነሣ፥ በኋላውም እነሆ አንድ በግ በዱር ውስጥ ቀንዶቹ በዕፀ ሳቤቅ ተይዞ አየ፤ አብርሃምም ሄደ በጉንም ወሰደው፥ በልጁም ፋንታ መሥዋዕት አድርጎ ሠዋው።14.አብርሃምም ያንን ቦታ ያህዌ ይርኤ ብሎ ጠራው፤ እስከ ዛሬም ድረስ በእግዚአብሔር ተራራ ይታያል ይባላል።15.የእግዚአብሔር መልአክም አብርሃምን ከሰማይ ሁለተኛ ጊዜ ጠራው፥16.እንዲህም አለው። እግዚአብሔር። በራሴ ማልሁ ይላል፤ ይህን ነገር አድርገሃልና፥ አንድ ልጅህንም አልከለከልህምና17.በእውነት በረከትን እባርክሃለሁ፥ ዘርህንም እንደ ሰማይ ከዋክብትና በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ አበዛዋለሁ፤ ዘርህም የጠላቶችን ደጅ ይወርሳል፤18.የምድር አሕዛብ ሁሉም በዘርህ ይባረካሉ፥ ቃሌን ሰምተሃልና።19.አብርሃምም ወደ ብላቴኖቹ ተመለሰ፥ ተነሥተውም ወደ ቤርሳቤህ አብረው ሄዱ፤ አብርሃምም በቤርሳቤህ ተቀመጠ።20.ይህም ከሆነ በኋልላ ለአብርሃም እንዲህ ተብሎ ተነገረ። እነሆ፥ ሚልካ ደግሞ ለወንድምህ ለናኮር ልጆችን ወለደች፤21.እነርሱም በኵሩ ዑፅ፥ ወንድሙ ቡዝ፥ የአራም አባት ቀሙኤል፥22.ኮዛት፥ ሐዞ፥ ፊልዳሥ፥ የድላፍ፥ ባቱኤል ናቸው።23.ባቱኤልም ርብቃን ወለደ፤ እነዚህን ስምንቱን ሚልካ ለአብርሃም ወንድም ለናኮር ወለደች።24.ሬሕማ የሚሉአት ቁባቱ ደግሞ ጥባህን፥ ገአምን፥ ተሐሸን፥ ሞክሳን ወለደች። a

ምዕራፍ 23

1.የሣራም ዕድሜ መቶ ሀያ ሰባት ዓመት ሆነ።2.በቂርያትአርባቅም ሞተች፤ እርስዋም በከነዓን ምድር ያለች ኬብሮን ናት፤ አብርሃምም ለሣራ ሊያዝንላትና ሊያለቅስላት ተነሣ።3.አብርሃምም ከሬሳው አጠገብ ተነሣ፥4.ለኬጢ ልጆችም እንዲህ ሲል ተናገረ። እኔ በእናንተ ዘንድ ስደተኛና መጻተኛ ነኝ፤ በእናንተ ዘንድ የመቃብር ርስት ስጡኝ፥ ሬሳዬንም ከፊቴ ልቅበር።5.የኬጢ ልጆችም ለአብርሃም መለሱ፥ አሉትም።6.ጌታ ሆይ፥ ስማን፤ አንተ በእኛ መካከል ከእግዚአብሔር አለቃ ነህ፤ ከመቃብር ስፍራችን በመልካሙ ቦታ ሬሳህን ቅበር፤ ሬሳህን ትቀብር ዘንድ ከእኛ መቃብሩን የሚከለክልህ የለም።7.አብርሃምም ተነሣ፥ ለምድሩ ሕዝብም፥ ለኬጢ ልጆች፥ ሰገደ።8.እንዲህም አላቸው። ሬሳዬን ከፊቴ እንድቀብር ከወደዳችሁስ ስሙኝ፥ ከሰዓር ልጅ ከኤፍሮንም ለምኑልኝ፤9.በእርሻው ዳር ያለችውን ድርብ ክፍል ያላትን ዋሻውን በሙሉ ዋጋ በመካከላችሁ ይስጠኝ፥ መቃብሩ የእኔ ርስት እንዲሆን።10.ኤፍሮንም በኬጢ ልጆች መካከል ተቀምጦ ነበር፤ የኬጢ ሰው ኤፍሮንም የኬጢ ልጆችና ወደ ከተማ የሚገቡ ሁሉ ሲሰሙ ለአብርሃም እንዲህ ሲል መለሰለት።11.አይደለም፥ ጌታዬ፥ ስማኝ፤ እርሻውን ሰጥቼሃለሁ በእርሱም ዳር ያለውን ዋሻ ሰጥቼሃለሁ፤ በወገኔ ልጆች ፊት ሰጥቼሃለሁ፤ ሬሳህን ቅበር።12.አብርሃምም በአገሩ ሰዎች ፊት ሰገደ፤13.የአገሩ ሰዎችም ሲሰሙ ለኤፍሮን እንዲህ ሲል ተናገረ። ነገሬን ትሰማ ዘንድ እለምንሃለሁ፤ የእርሻውን ዋጋ እሰጥሃለሁ፤ አንተም ከእኔ ዘንድ ውሰድ፥ ሬሳዬንም በዚያ እቀብራለሁ።14.ኤፍሮንም ለአብርሃም እንዲህ ሲል መለሰለት።15.ጌታዬ ሆይ፥ እኔን ስማኝ፤ የአራት መቶ ሰቅል ዋጋ ምድር በእኔና በአንተ መካክለ ምንድር ነው? ሬሳህንም ቅበር።16.አብርሃምም የኤፍሮንን ነገር ሰማ፤ አብርሃምም በኬጢ ልጆች ፊት የነገረውን አራት መቶ ሰቅል መዝኖ ለኤፍሮን ሰጠው፤ ብሩም ለመሸጫ ለመለወጫ የሚተላለፍ ነበረ።17.በመምሬ ፊት ያለው ባለድርብ ክፍል የሆነው የኤፍሮን እርሻ ለአብርሃም ጸና፤18.እርሻው በእርሱም ያለው ዋሻው፥ በእርሻውም ውስጥ በዙሪያውም ያለው እንጨት ሁሉ በኬጢ ልጆችና በከተማይቱ በር በሚገቡ ሁሉ ፊት ለአብርሃም ርስቱ ሆነ።19.ከዚህም በኋላ ኬብሮን በምትባል በመምሬ ፊት በከነዓን ምድር ባለው እርሻ ባለ ድርብ ክፍል በሆነው ዋሻ ውስጥ አብርሃም ሚስቱን ሣራን ቀበረ።20.እርሻውና በእርሱ ያለው ዋሻው በኬጢ ልጆች ዘንድ ለአብርሃም የመቃብር ርስት ሆኖ ጸና።

መዝሙረ ዳዊት

ምዕራፍ 107

1.ቸር ነውና፥ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ፤2.እግዚአብሔር ያዳናቸው፥ ከጠላቶች እጅ ያዳናቸው ይናገሩ።3.ከምሥራቅና ከምዕራብ፥ ከሰሜንና ከባሕር፥ ከየአገሩ ሰበሰባቸው።4.ውኃ በሌለበት ምድረ በዳ ተቅበዘበዙ፤ የሚኖሩበትንም ከተማ መንገድ አላገኙም።5.ተራቡ ተጠሙም፥ ነፍሳቸውም በውስጣቸው አለቀች።6.በተጨነቁ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፥ ከመከራቸውም አዳናቸው፤7.ወደሚኖሩበት ከተማ ይሄዱ ዘንድ የቀና መንገድን መራቸው።8.ለሰው ልጆች ስላደረገው ተኣምራት ስለ ምሕረቱም እግዚአብሔርን ያመስግኑ፤9.የተራበችን ነፍስ አጥግቦአልና፥ የተራቈተችንም ነፍስ በበረከት ሞልቶአልና።10.በጨለማ በሞትም ጥላ የተቀመጡ፥ በችግር በብረትም የታሰሩ፤11.የእግዚአብሔርን ቃል ስለ ዐመፁ፥ የልዑልንም ምክር ስለ ናቁ፥12.ልባቸው በድካም ተዋረደ፤ ታመሙ የሚረዳቸውም አጡ።13.በተጨነቁ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፥ በመከራቸውም አዳናቸው።14.ከጨለማና ከሞት ጥላ አወጣቸው፥ እስራታቸውንም ሰበረ።15.ለሰው ልጆች ስላደረገው ተኣምራት ስለ ምሕረቱም እግዚአብሔርን ያመስግኑ፤16.የናሱን ደዶች ሰብሮአልና፥ የብረቱንም መወርወሪያ ቈርጦአልና።17.ስለ ዓመፃቸው ሰነፉ፥ ስለ ኃጢአታቸውም ተቸገሩ።18.ሰውነታቸው መብልን ሁሉ ተጸየፈች፥ ወደ ሞትም ደጆች ቀረቡ።19.በተጨነቁ ጊዜም ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፥ ከመከራቸውም አዳናቸው።20.ቃሉን ላከ ፈወሳቸውም፥ ከጥፋታቸውም አዳናቸው።21.ለሰው ልጆች ስላደረገው ተኣምራት ስለ ምሕረቱም እግዚአብሔርን ያመሰግኑ፤22.የምስጋና መሥዋዕትንም ይሠውለት፥ በእልልታም ሥራውን ይንገሩ።23.በመርከቦች ወደ ባሕር የሚወርዱ፥ በታላቅ ውኃ ሥራቸውን የሚሠሩ፥24.እነርሱ የእግዚአብሔርን ሥራ፥ በጥልቅም ያለችውን ድንቁን አዩ።25.ተናገረ፥ ዐውሎ ነፋስም ተነሣ፥ ሞገድም ከፍ ከፍ አለ።26.ወደ ሰማይ ይወጣሉ ወደ ጥልቅም ይወርዳሉ፤ ነፍሳቸውም በመከራ ቀለጠች።27.ደነገጡ እንደ ስካርም ተንገደገዱ፥ ጥበባቸውም ሁሉ ተዋጠች።28.በተጨነቁ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፥ ከመከራቸውም አዳናቸው።29.ዐውሎንም ጸጥ አደረገ፥ ሞገዱም ዝም አለ።30.ዝም ብሎአልና ደስ አላቸው፤ ወደ ፈለጉትም ወደብ መራቸው።31.ለሰው ልጆች ስላደረገው ተአምራት ስለ ምሕረቱም እግዚአብሔርን ያመስግኑ።32.በአሕዛብ ጉባኤ ከፍ ከፍ ያድርጉት፥ በሽማግሌዎችም ሸንጎ ያመስግኑት።33.ወንዞችን ምድረ በዳ፥ የውኃውንም ምንጮች ደረቅ አደረጋቸው፤34.ከተቀመጡባት ክፋት የተነሣ ፍሬያማዋን ምድር ጨው አደረጋት።35.ምድረ በዳን ለውኃ መቆሚያ፥ ደረቁንም ምድር የውኃ ምንጮች አደረገ።36.በዚያም ራብተኞችን አስቀመጠ፥ የሚኖርባትንም ከተማ ሠሩ።37.እርሻዎችንም ዘሩ ወይኖችንም ተከሉ፥ የእህልንም ሰብል አደረጉ።38.ባረካቸውም እጅግም በዙ፤ እንስሶቻቸውንም አላሳነሰባቸውም።39.እነርሱ በችግር በክፋት በጭንቀት ተዋረዱ እያነሱም ሄዱ፤40.በአለቶችም ላይ ኅሣርን፥ አፈሰሰ፥ መንገድም በሌለበት በምድረ በዳ አሳታቸው።41.ችግረኛንም ከችግሩ ረዳው፤ እንደ በጎች መንጋ ወገን አደረገው።42.ቅኖች ያያሉ፥ ደስም ይላቸዋል፤ ኃጢአትም ሁሉ አፍዋን ትዘጋለች።43.ጥበበኛ የሆነና ይህን የሚጠብቅ ማን ነው? እርሱ የእግዚአብሔርን ምሕረት ያስተውላል።

የማርቆስ ወንጌል

ምዕራፍ 8

1.በዚያ ወራት ደግሞ ብዙ ሕዝብ ነበረ የሚበሉትም ስለሌላቸው ደቀ መዛሙርቱን ጠርቶ።2.ሕዝቡ ከእኔ ጋር እስካሁን ሦስት ቀን ውለዋልና የሚበሉት ስለሌላቸው አዝንላቸዋለሁ፤3.ከእነርሱም አንዳንዶቹ ከሩቅ መጥተዋልና ጦማቸውን ወደ ቤታቸው ባሰናብታቸው በመንገድ ይዝላሉ አላቸው።4.ደቀ መዛሙርቱም። በዚህ በምድረ በዳ እንጀራ ከየት አግኝቶ ሰው እነዚህን ማጥገብ ይችላል? ብለው መለሱለት።5.እርሱም። ስንት እንጀራ አላችሁ? ብሎ ጠየቃቸው፥ እነርሱም። ሰባት አሉት።6.ሕዝቡም በምድር እንዲቀመጡ አዘዘ። ሰባቱንም እንጀራ ይዞ አመሰገነ፥ ቈርሶም እንዲያቀርቡላቸው ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፥ ለሕዝቡም አቀረቡ።7.ጥቂትም ትንሽ ዓሣ ነበራቸው፤ ባረከውም ይህንም ደግሞ እንዲያቀርቡላቸው አዘዘ።8.በሉም ጠገቡም፥ የተረፈውንም ቍርስራሽ ሰባት ቅርጫት አነሡ።9.የበሉትም አራት ሺህ ያህል ነበሩ።10.አሰናበታቸውም። ወዲያውም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ታንኳይቱ ገብቶ ወደ ዳልማኑታ አገር መጣ።11.ፈሪሳውያንም ወጡና ሊፈትኑት ከሰማይ ምልክት ከእርሱ ፈልገው ከእርሱ ጋር ይከራከሩ ጀመር።12.በመንፈሱም እጅግ ቃተተና። ይህ ትውልድ ስለ ምን ምልክት ይፈልጋል? እውነት እላችኋለሁ፥ ለዚህ ትውልድ ምልክት አይሰጠውም አለ።13.ትቶአቸውም እንደ ገና ወደ ታንኳይቱ ገብቶ ወደ ማዶ ሄደ።14.እንጀራ መያዝም ረሱ፥ ለእነርሱም ከአንድ እንጀራ በቀር በታንኳይቱ አልነበራቸውም።15.እርሱም። ተጠንቀቁ፤ ከፈሪሳውያንና ከሄሮድስ እርሾ ተጠበቁ ብሎ አዘዛቸው።16.እርስ በርሳቸውም። እንጀራ ስለሌለን ይሆናል ብለው ተነጋገሩ።17.ኢየሱስም አውቆ እንዲህ አላቸው። እንጀራ ስለሌላችሁ ስለ ምን ትነጋገራላችሁ? ገና አልተመለከታችሁምን? አላስተዋላችሁምን?18.ልባችሁስ ደንዝዞአልን? ዓይን ሳላችሁ አታዩምን? ጆሮስ ሳላችሁ አትሰሙምን? ትዝስ አይላችሁምን?19.አምስቱን እንጀራ ለአምስት ሺህ በቈረስሁ ጊዜ፥ ቍርስራሹ የሞላ ስንት መሶብ አነሣችሁ? እነርሱም። አሥራ ሁለት አሉት።20.ሰባቱን እንጀራስ ለአራት ሺህ በቈረስሁ ጊዜ፥ ቍርስራሹ የሞላ ስንት ቅርጫት አነሣችሁ? እነርሱም። ሰባት አሉት።21.ገና አላስተዋላችሁምን? አላቸው።22.ወደ ቤተ ሳይዳም መጡ። ዕውርም አመጡለት፥ እንዲዳስሰውም ለመኑት።23.ዕውሩንም እጁን ይዞ ከመንደር ውጭ አወጣው፥ በዓይኑም ተፍቶበት እጁንም ጭኖበት። አንዳች ታያለህን ብሎ ጠየቀው።24.አሻቅቦም። ሰዎች እንደ ዛፍ ሲመላለሱ አያለሁ አለ።25.ከዚህም በኋላ ደግሞ እጁን በዓይኑ ላይ ጫነበት አጥርቶም አየና ዳነም ከሩቅም ሳይቀር ሁሉን ተመለከተ።26.ወደ ቤቱም ሰደደውና። ወደ መንደሩ አትግባ በመንደሩም ለማንም አንዳች አትናገር አለው።27.ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱም በፊልጶስ ቂሣርያ ወዳሉ መንደሮች ወጡ በመንገድም። ሰዎች እኔ ማን እንደ ሆንሁ ይላሉ? ብሎ ደቀ መዛሙርቱን ጠየቃቸው።28.እነርሱም። መጥምቁ ዮሐንስ፥ ሌሎችም ኤልያስ፥ ሌሎችም ከነቢያት አንዱ ብለው ነገሩት።29.እናንተስ እኔ ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ? ብሎ ጠየቃቸው። ጴጥሮስም። አንተ ክርስቶስ ነህ ብሎ መለሰለት።30.ስለ እርሱም ለማንም እንዳይናገሩ አዘዛቸው።31.የሰው ልጅ ብዙ መከራ ሊቀበል፥ ከሽማግሌዎችም ከካህናት አለቆችም ከጻፎችም ሊጣል፥ ሊገደልም ከሦስት ቀንም በኋላ ሊነሣ እንዲገባው ያስተምራቸው ጀመር፤ ቃሉንም ገልጦ ይናገር ነበር።32.ጴጥሮስም ወደ እርሱ ወስዶ ይገሥጸው ጀመር።33.እርሱ ግን ዘወር አለ ደቀ መዛሙርቱንም አይቶ ጴጥሮስን ገሠጸውና። ወደ ኋላዬ ሂድ፥ አንተ ሰይጣን፤ የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን ነገር አታስብምና አለው።34.ሕዝቡንም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ጠርቶ እንዲህ አላቸው። በኋላዬ ሊመጣ የሚወድ ቢኖር፥ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ።35.ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታልና፥ ስለ እኔና ስለ ወንጌል ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ግን ያድናታል።36.ሰው ዓለምን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጐድል ምን ይጠቅመዋል?37.ሰውስ ስለ ነፍሱ ቤዛ ምን ይሰጣል?38.በዚህም በዘማዊና በኃጢአተኛ ትውልድ መካከል በእኔና በቃሌ የሚያፍር ሁሉ፥ የሰው ልጅ ደግሞ በአባቱ ክብር ከቅዱሳን መላእክት ጋር በመጣ ጊዜ በእርሱ ያፍርበታል።