Skip to Content
የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን | YEHIWOT MELHEK BETEKIRSTIAN
የ2019 ዓ.ም የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ 📖 ዛሬን አንብብ →

የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን

Yehiwot Melhek Betekirstian

ሳምንት 2 · ቀን 8 (ረቡዕ) 📅 Meskerem 13, 2019

ኦሪት ዘፍጥረት 21, 22, 23 · መዝሙረ ዳዊት 107 · የማርቆስ ወንጌል 8

📖 የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም፦ 1954 መጽሐፍ ቅዱስ አዲሱ መደበኛ ትርጒም

ኦሪት ዘፍጥረት

ምዕራፍ 21

የይሥሐቅ መወለድ

1.እግዚአብሔር በተናገረው መሠረት ሣራን ዐሰባት፤ የገባውንም ተስፋ ፈጸመላት። 2.ሣራ ፀነሰች፤ ልክ እግዚአብሔር ባለው ጊዜ ለአብርሃም ወንድ ልጅ ወለደችለት። 3.አብርሃም፣ ሣራ የወለደችለትን ልጅ ስሙን ይሥሐቅ አለው። 4.አብርሃም፣ እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት ልጁን ይሥሐቅን በተወለደ በስምንተኛው ቀን ገረዘው። 5.አብርሃም፣ ልጁ ይሥሐቅ ሲወለድለት፣ ዕድሜው መቶ ዓመት ነበረ። 6.ሣራም፣ “እግዚአብሔር ሣቅ አድሎኛል፤ ስለዚህ፣ ይህን የሚሰማ ሁሉ ከእኔ ጋራ ይሥቃል” አለች። 7.ደግሞም፣ “ለመሆኑ፣ ‘ሣራ ልጆች ታጠባለች’ ብሎ ለአብርሃም ማን ተናግሮት ያውቅ ነበር? ይኸው በስተርጅናው ወንድ ልጅ ወለድሁለት” አለች።

የአጋርና የእስማኤል መባረር

8.ሕፃኑ አደገ፤ ጡት መጥባቱንም ተወ። አብርሃምም ይሥሐቅ ጡት በጣለባት ዕለት ታላቅ ድግስ ደገሰ። 9.በሌላ በኩል ደግሞ፣ ግብጻዊቷ አጋር ለአብርሃም የወለደችለት እስማኤል በይሥሐቅ ላይ ሲያሾፍበት ሣራ አየች፤ 10.አብርሃምንም፣ “ይህችን ባሪያ ከነልጇ አባርራት፤ የዚህች ባሪያ ልጅ፣ ከልጄ ከይሥሐቅ ጋራ አይወርስምና” አለችው። 11.እስማኤል ልጁ ስለ ሆነ ነገሩ አብርሃምን እጅግ አስጨነቀው። 12.እግዚአብሔርም አብርሃምን እንዲህ አለው፤ “ስለ ልጁም ሆነ ስለ አገልጋይህ ሐሳብ አይግባህ፤ ዘር የሚጠራልህ በይሥሐቅ በኩል ስለ ሆነ፣ ሣራ የምትልህን ሁሉ ስማ። 13.የአገልጋይህም ልጅ የራስህ ልጅ ስለ ሆነ፣ እርሱንም ታላቅ ሕዝብ አደርገዋለሁ።” 14.በማግስቱም አብርሃም ማልዶ ተነሣ። ጥቂት ምግብ ወስዶ፣ ውሃ በእርኮት አድርጎ ለአጋር ሰጣት፤ በትከሻዋም አሸክሟት ከነልጇ አሰናበታት። እርሷም ሄደች፤ በቤርሳቤህም ምድረ በዳ ትንከራተት ጀመር። 15.በእርኮት የነበረው ውሃ ባለቀ ጊዜ፣ ልጁን ከአንድ ቍጥቋጦ ሥር አስቀመጠችው። 16.ከዚያም፣ “ልጁ ሲሞት ዐይኔ አያይም” ብላ፣ የቀስት ውርወራ ያህል ርቃ ዐረፍ አለች፤ እርሷም እየተንሰቀሰቀች ታለቅስ ጀመር። 17.እግዚአብሔርም የልጁን ጩኸት ሰማ። የእግዚአብሔር መልአክ ከሰማይ አጋርን እንዲህ አላት፤ “አጋር ሆይ፤ ምን ሆነሻል? ልጅሽ ከተኛበት ሲያለቅስ እግዚአብሔር ሰምቶታል፤ ስለዚህ አትፍሪ። 18.ተነሥተሽ ልጁን አንሺው፤ ያዢውም፤ ታላቅ ሕዝብ አደርገዋለሁና።” 19.እግዚአብሔርም ዐይኖቿን ከፈተላት፤ የውሃ ጕድጓድም አየች፤ ሄዳም በእርኮቱ ውሃ ሞልታ ልጇን አጠጣች። 20.እግዚአብሔር ከልጁ ጋራ ነበር፤ ልጁም እያደገ ሄደ፤ መኖሪያውንም በምድረ በዳ ውስጥ አደረገ፤ ጐበዝ ቀስተኛም ሆነ። 21.በፋራን ምድረ በዳ ሳለም፣ እናቱ ከግብጽ አንዲት ሴት አምጥታ አጋባችው።

በቤርሳቤህ የተደረገው ስምምነት

22.በዚያ ጊዜ አቢሜሌክ ከሰራዊቱ አለቃ ከፊኮል ጋራ ሆኖ አብርሃምን እንዲህ አለው፤ “በምታደርገው ነገር ሁሉ እግዚአብሔር ከአንተ ጋራ ነው። 23.እንግዲህ እኔንና ልጆቼን፣ ዘሬንም በመሸንገል አንዳች ክፉ ነገር እንዳታደርስብን በእግዚአብሔር ፊት ማልልኝ። እኔ ለአንተ ቸርነት እንዳደረግሁ፣ አንተም ለእኔና በእንግድነት ለተቀመጥህባት ለዚህች ምድር ቸርነት አድርግ።” 24.አብርሃምም፣ “ዕሺ፤ እምላለሁ” አለ። 25.ከዚያም አብርሃም፣ የአቢሜሌክ አገልጋዮች ነጥቀው ስለያዙበት የውሃ ጕድጓድ መከፋቱን ለአቢሜሌክ ገለጠለት። 26.አቢሜሌክም፣ “መቼም ይህን ድርጊት ማን እንደ ፈጸመ በበኩሌ አላውቅም፤ አንተም አልነገርኸኝም፤ ነገሩንም ገና አሁን መስማቴ ነው” አለው። 27.ስለዚህ አብርሃም፣ በጎችና ከብቶች አምጥቶ ለአቢሜሌክ ሰጠው፤ ሁለቱም በመካከላቸው የስምምነት ውል አደረጉ። 28.አብርሃም ከመንጋው ሰባት እንስት በጎች ለየ፤ 29.አቢሜሌክም፣ “እነዚህን ሰባት እንስት በጎች ለይተህ ለብቻ ያቆምሃቸው ለምንድን ነው?” ሲል አብርሃምን ጠየቀው። 30.አብርሃምም፣ “ይህን የውሃ ጕድጓድ የቈፈርሁ እኔ ለመሆኔ ምስክር እንዲሆን እነዚህን ሰባት እንስት በጎች ዕንካ ተቀበለኝ” አለው። 31.ስለዚህ ቦታው፣ ሁለቱ ተማምለው የተስማሙበት ስፍራ በመሆኑ ቤርሳቤህ ተባለ። 32.በቤርሳቤህ የስምምነት ውል ካደረጉ በኋላ፣ አቢሜሌክና የሰራዊቱ አለቃ ፊኮል ወደ ፍልስጥኤማውያን ምድር ተመለሱ። 33.አብርሃምም በቤርሳቤህ የተምር ዛፍ ተከለ፤ በዚያም እግዚአብሔር የዘላለም አምላክን ስም ጠራ። 34.አብርሃምም በፍልስጥኤማውያን ምድር ለረዥም ጊዜ በእንግድነት ኖረ።

ምዕራፍ 22

አብርሃም ተፈተነ

1.ከዚህ ሁሉ በኋላ እግዚአብሔር አብርሃምን ፈተነው፤ “አብርሃም!” አለው።
እርሱም “አቤቱ አለሁ” አለ።
2.እግዚአብሔርም፣ “የምትወድደውን አንዱን ልጅህን፣ ይሥሐቅን ይዘህ ወደ ሞሪያ ምድር ሂድ፤ እኔ በማመለክትህ በአንዱ ተራራ ላይ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገህ ሠዋው” አለው። 3.በማግስቱም ጧት አብርሃም ማልዶ ተነሣ፤ አህያውን ጭኖ፣ ሁለት አገልጋዮቹንና ልጁን ይሥሐቅን ይዞ፣ ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚበቃውን ዕንጨት ከቈረጠ በኋላ እግዚአብሔር ወዳመለከተው ቦታ ለመሄድ ጕዞውን ጀመረ፤ 4.በሦስተኛው ቀን አብርሃም ቀና ብሎ ቦታውን ከሩቅ ተመለከተ፤ 5.አገልጋዮቹንም “እናንተ አህያውን ይዛችሁ እዚህ ቈዩን፤ እኔና ልጄ ግን ወደዚያ ሄደን ለእግዚአብሔር ሰግደን እንመለሳለን” አላቸው። 6.አብርሃም ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነውን ዕንጨት ወስዶ፣ ልጁን ይሥሐቅን አሸከመው፤ እሳቱንና ቢላዋውንም ራሱ ያዘ። ሁለቱም ዐብረው ሄዱ። 7.ይሥሐቅም አባቱን አብርሃምን፣ “አባቴ ሆይ” አለው።
አብርሃምም፣ “እነሆኝ፤ አለሁ ልጄ” አለው።
ይሥሐቅም፣ “እሳቱና ዕንጨቱ ይኸው፤ ነገር ግን የሚቃጠለው መሥዋዕት በግ የት አለ?” ብሎ ጠየቀ።
8.አብርሃምም፣ “ልጄ ሆይ፤ ለሚቃጠለው መሥዋዕት የሚሆነውን በግ እግዚአብሔር ያዘጋጃል” አለው። ሁለቱም ዐብረው ጕዟቸውን ቀጠሉ። 9.እግዚአብሔር ወደ አመለከተው ቦታ እንደ ደረሱ፣ አብርሃም መሠዊያ ሠራ፤ በላዩም ላይ ዕንጨት ረበረበ፤ ልጁን ይሥሐቅንም አስሮ በመሠዊያው ዕንጨት ላይ አጋደመው። 10.ከዚያም ልጁን ለማረድ እጁን ዘርግቶ ቢላዋውን አነሣ። 11.የእግዚአብሔር መልአክ ግን ከሰማይ፣ “አብርሃም! አብርሃም!” ብሎ ጠራው።
አብርሃምም፣ “እነሆ፤ አለሁ” አለ።
12.እርሱም፣ “እጅህን በብላቴናው ላይ አታሳርፍ፤ ምንም ጕዳት አታድርስበት፤ እነሆ፤ እግዚአብሔርን እንደምትፈራ ተረድቻለሁ፤ ልጅህን፣ ያውም አንዱን ልጅህን ለእኔ ለመስጠት አልሣሣህምና” አለው። 13.አብርሃም ቀና ብሎ ተመለከተ፤ በቍጥቋጦ መካከልም ቀንዶቹ የተጠላለፉ አንድ አውራ በግ ከበስተኋላው አየ፤ ወደዚያው ሄዶ በጉን አመጣና የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ ሠዋው። 14.ከዚህም የተነሣ አብርሃም የዚያን ስፍራ ስም፣ “እግዚአብሔር ያዘጋጃል” ብሎ ጠራው፤ እስከ ዛሬም ድረስ፣ “በእግዚአብሔር ተራራ ላይ ይዘጋጃል” ይባላል። 15.የእግዚአብሔርም መልአክ አብርሃምን ከሰማይ ዳግመኛ ጠራው፤ 16.እንዲህም አለው፤ “እግዚአብሔርም በራሴ ማልሁ አለ፤ አንዱን ልጅህን ለእኔ ለመስጠት አልሣሣህምና፣ 17.በርግጥ እባርክሃለሁ፤ ዘርህን እንደ ሰማይ ከዋክብት፣ እንደ ባሕር ዳር አሸዋም አበዛዋለሁ። ዘሮችህም የጠላቶቻቸውን ደጆች ይወርሳሉ፤ 18.አሕዛብ ሁሉ በዘርህ ይባረካሉ፤ ቃሌን ሰምተሃልና።” 19.ከዚያም አብርሃም ወደ አገልጋዮቹ ተመለሰ፤ ተያይዘውም ወደ ቤርሳቤህ ሄዱ፤ አብርሃምም በቤርሳቤህ ኖረ።

የናኮር ልጆች

20.ከዚህ በኋላ እንዲህ ተብሎ ለአብርሃም ተነገረው፤ “ሚልካም ደግሞ የልጆች እናት ሆናለች፤ ለወንድምህም ለናኮር ወንዶች ልጆችን ወልዳለች። 21.እነርሱም የበኵር ልጁ ዑፅና ወንድሙ ቡዝ፣
የአራም አባት ቀሙኤል፣
22.ኮዛት፣ ሐዞ፣ ፊልዳሥ፣ የድላፍና ባቱኤል ናቸው።” 23.ባቱኤልም ርብቃን ወለደ።
ሚልካ ለአብርሃም ወንድም ለናኮር የወለደችለት እነዚህ ስምንት ወንዶች ልጆች ናቸው።
24.ከእነዚህም ሌላ የናኮር ቁባት ሬናሕ ደግሞ ጥባሕ፣ ገአም፣ ተሐሽና ሞክሳ የተባሉ ወንዶች ልጆች ወለደችለት።

ምዕራፍ 23

የሣራ ሞት

1.ሣራ አንድ መቶ ሃያ ሰባት ዓመት ኖረች፤ 2.በከነዓን ምድር፣ በቂርያት አርባቅ ማለትም በኬብሮን ከተማ ሞተች፤ አብርሃምም ለሣራ ሊያለቅስና ሊያዝን መጣ። 3.ከዚያም አብርሃም ከተቀመጠበት ከሚስቱ ሬሳ አጠገብ ተነሣ፤ ኬጢያውያንንም እንዲህ አላቸው፤ 4.“እኔ ለአገሩ እንግዳ፣ ለሰዉ ባዳ ሆኜ በመካከላችሁ የምኖር ነኝና ለመቃብር የምትሆን ቦታ ሽጡልኝ፤ የሚስቴንም ሬሳ ልቅበርበት።” 5.ኬጢያውያንም ለአብርሃም እንዲህ ሲሉ መለሱለት፤ 6.“ስማን ጌታዬ፤ አንተ እኮ በእኛ ዘንድ እንደ ኀያል መስፍን ነህ፤ ከመቃብር ቦታችን በመረጥኸው ስፍራ ሬሳህን መቅበር ትችላለህ፤ ማንኛችንም ብንሆን የሞተብህን ሰው እንዳትቀብርበት የመቃብር ቦታችንን አንከለክልህም።” 7.ከዚያም አብርሃም ተነሥቶ የአገሬውን ሕዝብ፣ ኬጢያውያንን እጅ ነሣ፤ 8.እንዲህም አላቸው፤ “እንድቀብር ከፈቀዳችሁልኝ፣ አንዴ ስሙኝና የሰዓርን ልጅ ኤፍሮንን ስለ እኔ ሆናችሁ ለምኑልኝ። 9.ይኸውም በዕርሻው ድንበር ላይ ያለችውን መክፈላ የተባለችውን ዋሻውን እንዲሸጥልኝ ነው፤ በመካከላችሁም የመቃብር ቦታ እንድትሆነኝ በሙሉ ዋጋ እንዲሸጥልኝ ለምኑልኝ።” 10.ኬጢያዊው ኤፍሮንም እዚያው መካከላቸው ተቀምጦ ስለ ነበር፣ ወደ ከተማው በር መግቢያ መጥተው የተሰበሰቡት ኬጢያውያን በሙሉ እየሰሙ ለአብርሃም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ 11.“እንዲህ አይደለም ጌታዬ፤ ስማኝ፤ ዕርሻውን በውስጡ ካለው ዋሻ ጋራ ውሰደው። እነሆ፤ በወገኖቼ ኬጢያውያን ፊት ሰጥቼሃለሁ፤ ሬሳህን ቅበርበት።” 12.አብርሃም እንደ ገና የአገሬውን ሕዝብ እጅ ነሣና 13.ሁሉም እየሰሙት ኤፍሮንን፣ “የዕርሻውን ቦታ ዋጋ ልክፈል፤ እባክህን ተቀበለኝና ሬሳዬን ልቅበርበት” አለው። 14.ኤፍሮንም ለአብርሃም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ 15.“ጌታዬ ስማኝ፤ የመሬቱ ዋጋማ አራት መቶ ጥሬ ብር ነው፤ ታዲያ ይህ በእኔና በአንተ መካከል ምን ቁም ነገር አለው? ይልቅስ ሬሳህን ቅበርበት” አለው። 16.አብርሃምም፣ ኤፍሮን በኬጢያውያን ፊት በተናገረው ዋጋ ተስማማ፤ በወቅቱም የንግድ መለኪያ መሠረት አራት መቶ ጥሬ ብር መዘነለት። 17.በዚህ ሁኔታ፣ በመምሬ አጠገብ በመክፈላ ያለው የኤፍሮን ዕርሻ ቦታ ከነዋሻው በክልሉ ካሉት ዛፎች ሁሉ ጭምር ለአብርሃም በርስትነት ተላለፈ፤ 18.ወደ ከተማው በር በመጡት ኬጢያውያንም ሁሉ ፊት የአብርሃም ንብረት መሆኑም ተረጋገጠለት። 19.ከዚህም በኋላ አብርሃም በከነዓን ምድር፣ በመምሬ አጠገብ፣ መክፈላ በተባለች ዕርሻ ውስጥ ባለችው ዋሻ የሚስቱን የሣራን ሬሳ ቀበረ፤ ይህችም ኬብሮን ናት። 20.ስለዚህ ዕርሻውና ውስጡ የሚገኘው ዋሻ የመቃብር ቦታ እንዲሆን ከኬጢያውያን ለአብርሃም በርስትነት ተላለፈለት።

መዝሙረ ዳዊት

ምዕራፍ 107

1.ዐምስተኛ መጽሐፍ
ከመዝሙር 107–150
1 ቸር ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ፤
ምሕረቱም ለዘላለም ነውና።
2.እግዚአብሔር የተቤዣቸው፣
ከጠላት እጅ የታደጋቸው ይህን ይበሉ፤
3.ከምሥራቅና ከምዕራብ፣ ከሰሜንና ከደቡብ፣
ከየአገሩ የሰበሰባቸው እንዲህ ይናገሩ።
4.አንዳንዶቹ ጭው ባለ በረሓ ተቅበዘበዙ፤
ወደሚኖሩባት ከተማ የሚያደርስ መንገድ ዐጡ።
5.ተራቡ፤ ተጠሙ፤
ነፍሳቸውም በውስጣቸው ዛለች።
6.በተጨነቁ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤
እርሱም ከመከራቸው አዳናቸው።
7.ወደሚኖሩባትም ከተማ፣
በቀና መንገድ መራቸው።
8.እግዚአብሔርን ልክ ስለሌለው ፍቅሩ፣
ለሰው ልጆችም ስላደረገው ድንቅ ሥራ ያመስግኑት፤
9.እርሱ የተጠማችውን ነፍስ አርክቷልና፤
የተራበችውንም ነፍስ በበጎ ነገር አጥግቧል።
10.አንዳንዶቹ በብረት ሰንሰለት ታስረው የተጨነቁ፣
በጨለማ፣ በጥልማሞት ውስጥ የተቀመጡ ነበሩ፤
11.በእግዚአብሔር ቃል ላይ በማመፅ፣
የልዑልን ምክር አቃልለዋልና።
12.ስለዚህ በጕልበት ሥራ ልባቸውን አዛለ፤
ተዝለፈለፉ፤ የሚደግፋቸውም አልነበረም።
13.በተጨነቁ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤
እርሱም ከመከራቸው አዳናቸው።
14.ከጨለማና ከጥልማሞት አወጣቸው፤
እስራታቸውንም በጠሰላቸው።
15.እግዚአብሔርን ልክ ስለሌለው ፍቅሩ፣
ለሰው ልጆችም ስላደረገው ድንቅ ሥራ ያመስግኑት፤
16.እርሱ የናሱን በሮች ሰብሯልና፤
የብረቱንም መወርወሪያ ቈርጧል።
17.አንዳንዶቹ ከዐመፃቸው የተነሣ ቂሎች ሆኑ፤
ከበደላቸው የተነሣ ችግር ውስጥ ገቡ።
18.ሰውነታቸው የምግብ ዐይነት ሁሉ ተጸየፈች፤
ወደ ሞትም ደጆች ቀረቡ።
19.በተጨነቁ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤
እርሱም ከመከራቸው አዳናቸው።
20.ቃሉን ልኮ ፈወሳቸው፤
ከመቃብርም አፋፍ መለሳቸው።
21.እግዚአብሔርን ልክ ስለሌለው ፍቅሩ፣
ለሰው ልጆችም ስላደረገው ድንቅ ሥራ ያመስግኑት፤
22.የምስጋናም መሥዋዕት ያቅርቡለት፤
ሥራውንም ደስ በሚል ዝማሬ ይግለጹ።
23.አንዳንዶቹ በመርከብ ወደ ባሕር ወረዱ፤
በታላቅም ውሃ ላይ ሥራቸውን አከናወኑ፤
24.የእግዚአብሔርን ሥራ በዚያ አዩ፤
ድንቅ አድራጎቱንም በጥልቁ ውስጥ ተመለከቱ።
25.እርሱ ተናግሮ ዐውሎ ነፋስን አስነሣ፤
ነፋሱም ማዕበሉን ከፍ ከፍ አደረገ።
26.ወደ ሰማይ ወጡ፤ ወደ ጥልቅም ወረዱ፤
ከመከራቸውም የተነሣ ሐሞታቸው ፈሰሰ።
27.እንደ ሰከረ ሰው ዞሮባቸው ወዲያ ወዲህ ተንገዳገዱ፤
መላው ጠፍቶባቸው የሚያደርጉትን ዐጡ።
28.በተጨነቁ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤
እርሱም ከመከራቸው አዳናቸው።
29.ዐውሎ ነፋሱን ጸጥ አደረገ፤
የባሕሩም ሞገድ ረጭ አለ።
30.ጸጥ በማለቱም ደስ አላቸው፤
ወዳሰቡትም ወደብ አደረሳቸው።
31.እግዚአብሔርን ልክ ስለሌለው ፍቅሩ፣
ለሰው ልጆችም ስላደረገው ድንቅ ሥራ ያመስግኑት፤
32.በሕዝብ ጉባኤ መካከል ከፍ ከፍ ያድርጉት፤
በሽማግሌዎችም ሸንጎ ይወድሱት።
33.ወንዞችን ወደ ምድረ በዳ፣
የውሃ ምንጮችንም ወደ ደረቅ ምድር ለወጠ።
34.ከነዋሪዎቿ ክፋት የተነሣ፣
ፍሬያማዋን ምድር በጨው የተበከለች አደረጋት።
35.ምድረ በዳውን ወደ ውሃ መከማቻ፣
ደረቁንም ምድር ወደ ውሃ ምንጭ ቀየረ።
36.የተራቡትን በዚያ አስቀመጠ፤
የሚኖሩባትንም ከተማ ሠሩ።
37.በዕርሻውም ዘሩበት፤ ወይንም ተከሉ፤
ብዙ ፍሬም አመረቱ።
38.ይባርካቸዋል፤ እነርሱም እጅግ ይበዛሉ፤
የከብቶቻቸውም ብዛት እንዲያንስ አያደርግም።
39.በጭንቅ፣ በመከራና በሐዘን፣
ቍጥራቸው አንሶ፣ ተዋርደው ነበር፤
40.በመኳንንቱም ላይ መናቅን አዘነበባቸው፤
መውጫ መግቢያው በማይታወቅ በረሓ ውስጥም አንከራተታቸው።
41.ድኾችን ግን ከጭንቀታቸው መዝዞ አወጣቸው፤
ቤተ ሰባቸውንም እንደ በግ መንጋ አበዛ።
42.ልበ ቅኖች ይህን አይተው ሐሤት ያደርጋሉ፤
ጥመትም ሁሉ አፏን ትዘጋለች።
43.እንግዲህ ማንም ብልኅ ቢሆን፣ ይህን ነገር ልብ ይበል፤
እርሱም የእግዚአብሔርን ምሕረት ያስተውላል።

የማርቆስ ወንጌል

ምዕራፍ 8

ኢየሱስ አራት ሺሕ ሰዎች መገበ

8፥1-9 ተጓ ምብ – ማቴ 15፥32-39
8፥1-9 ተጓ ምብ – ማር 6፥32-44
8፥11-21 ተጓ ምብ – ማቴ 16፥1-12
1.በዚያ ጊዜ፣ እንደ ገና ብዙ ሕዝብ ተሰበሰበ። የሚበሉት ምንም ምግብ ስላልነበራቸው ደቀ መዛሙርቱን ወደ ራሱ ጠርቶ፣ እንዲህ አላቸው፤ 2.“ከእኔ ጋራ ሦስት ቀን ስለ ቈዩና የሚበሉትም ስለሌላቸው ለእነዚህ ሰዎች ዐዝንላቸዋለሁ፤ 3.እንዲህ እንደ ተራቡ ወደ ቤታቸው ብሰድዳቸው አንዳንዶቹ ከሩቅ የመጡ ስለ ሆኑ በመንገድ ላይ ዝለው ይወድቃሉ።” 4.ደቀ መዛሙርቱም መልሰው፣ “በዚህ ምድረ በዳ እነዚህን ለመመገብ የሚያስችል እንጀራ ከወዴት ይገኛል?” አሉት። 5.እርሱም፣ “ስንት እንጀራ አላችሁ?” ብሎ ጠየቃቸው።
እነርሱም፣ “ሰባት” አሉት።
6.እርሱም፣ መሬት ላይ እንዲቀመጡ ሕዝቡን አዘዘ፤ ሰባቱን እንጀራ ይዞ ካመሰገነ በኋላ ቈርሶ ለሰዎቹ እንዲያድሉ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጣቸው፤ እነርሱም ለሕዝቡ ዐደሉት። 7.እንዲሁም ትንንሽ ዓሣዎች ነበሯቸው፤ እርሱም ዓሣዎቹን ባርኮ እንዲያድሏቸው አዘዘ። 8.ሕዝቡም በልተው ጠገቡ፤ ከዚያም ደቀ መዛሙርቱ የተረፈውን ቍርስራሽ ሰባት መሶብ ሙሉ አነሡ። 9.በዚያም አራት ሺሕ ያህል ሰዎች ነበሩ፤ ካሰናበታቸውም በኋላ፣ 10.ከደቀ መዛሙርቱ ጋራ ወደ ጀልባ ገብቶ ዳልማኑታ ወደ ተባለ ስፍራ ሄደ። 11.ፈሪሳውያንም ወጥተው ከኢየሱስ ጋራ ይከራከሩ ጀመር። ሊፈትኑትም ፈልገው ከሰማይ ምልክት እንዲያሳይ ጠየቁት። 12.እርሱም በመንፈሱ እጅግ በመቃተት፣ “ይህ ትውልድ ምልክት የሚፈልገው ለምንድን ነው? እውነት እላችኋለሁ፤ ለዚህ ትውልድ ምንም ምልክት አይሰጠውም!” አለ። 13.ከዚያም ትቷቸው በጀልባ ወደ ማዶ ተሻገረ።

የፈሪሳውያንና የሄሮድስ እርሾ

14.ደቀ መዛሙርቱ እንጀራ መያዝ ስለ ረሱ፣ ከአንድ እንጀራ በቀር በጀልባ ውስጥ ምንም አልነበራቸውም። 15.ኢየሱስም፣ “ተጠንቀቁ፤ ከፈሪሳውያንና ከሄሮድስ እርሾ ተጠበቁ” ብሎ አዘዛቸው። 16.እነርሱም እርስ በርሳቸው፣ “እንዲህ የሚለን እኮ እንጀራ ስለሌለን ነው” ተባባሉ። 17.ኢየሱስም ሐሳባቸውን ዐውቆ እንዲህ አላቸው፤ “እንጀራ ስለሌለን ነው በማለት የምትነጋገሩት ስለ ምንድን ነው? አሁንም አታስተውሉምን? ልብ አትሉምን? ወይስ ልባችሁ ደንድኗል? 18.ዐይን እያላችሁ አታዩምን? ጆሮ እያላችሁ አትሰሙምን? አታስታውሱምን? 19.ዐምስቱን እንጀራ ለዐምስት ሺሕ ሰው በቈረስሁ ጊዜ ስንት መሶብ ሙሉ ትርፍራፊ አነሣችሁ?”
እነርሱም፣ “ዐሥራ ሁለት” አሉት።
20.“ሰባቱንስ እንጀራ ለአራት ሺሕ በቈረስሁ ጊዜ ስንት መሶብ ሙሉ ትርፍራፊ አነሣችሁ?” አላቸው።
እነርሱም፣ “ሰባት” አሉት።
21.እርሱም፣ “እስከ አሁን አላስተዋላችሁም ማለት ነውን?” አላቸው።

በቤተ ሳይዳ የተፈወሰው ዐይነ ስውር

22.ከዚያም ወደ ቤተ ሳይዳ መጡ፤ ጥቂት ሰዎችም አንድ ዐይነ ስውር ወደ ኢየሱስ አምጥተው እንዲዳስሰው ለመኑት። 23.እርሱም የዐይነ ስውሩን እጅ ይዞ ከሰፈር ውጭ አወጣው፤ በዐይኖቹም ላይ እንትፍ ብሎበት፣ እጁንም በላዩ ጭኖ፣ “ምን የሚታይህ ነገር አለ?” ሲል ጠየቀው። 24.እርሱም ቀና ብሎ አይቶ፣ “ሰዎች እንደ ዛፍ ሲንቀሳቀሱ አያለሁ” አለ። 25.ኢየሱስም እንደ ገና እጆቹን በሰውየው ዐይኖች ላይ ጫነ፤ በዚህ ጊዜ ዐይኖቹ በሩ፤ ብርሃኑም ተመለሰለት፤ ሁሉንም ነገር አጥርቶ ማየት ቻለ። 26.ከዚያም፣ “ወደ መንደሩ አትግባ! በመንደሩም ለማንም አትናገር” ብሎ ወደ ቤቱ ሰደደው።

ጴጥሮስ ስለ ኢየሱስ የነበረው ግንዛቤ

8፥27-29 ተጓ ምብ – ማቴ 16፥13-16፤ ሉቃ 9፥18-20
27.ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋራ ወደ ፊልጶስ ቂሳርያ መንደሮች ሄደ፤ በመንገድ ላይ ሳሉም ደቀ መዛሙርቱን፣ “ሰዎች እኔን ማን ነው ይሉኛል?” ብሎ ጠየቃቸው። 28.እነርሱም፣ “መጥምቁ ዮሐንስ የሚሉህ አሉ፤ ሌሎች ኤልያስ ነው ይሉሃል፤ ሌሎች ደግሞ ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ” ብለው ነገሩት። 29.ቀጥሎም፣ “እናንተስ ማን ትሉኛላችሁ?” ሲል ጠየቃቸው።
ጴጥሮስም፣ “አንተ ክርስቶስ ነህ” አለው።
30.ኢየሱስም ስለ እርሱ ለማንም እንዳይናገሩ አስጠነቀቃቸው።
ኢየሱስ ስለ ሞቱ አስቀድሞ ተናገረ
8፥31–9፥1 ተጓ ምብ – ማቴ 16፥21-28፤ ሉቃ 9፥22-27
31.ከዚያም የሰው ልጅ ብዙ መከራ እንደሚቀበል፣ በሽማግሌዎች፣ በካህናት አለቆችና በጸሐፍት እንደሚናቅ፣ እንደሚገደል፣ ከሦስት ቀንም በኋላ እንደሚነሣ ያስተምራቸው ጀመር። 32.እርሱም ይህን በግልጽ ነገራቸው። በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ኢየሱስን ለብቻው ወስዶ ይገሥጸው ጀመር። 33.ኢየሱስ ግን ዘወር ብሎ ደቀ መዛሙርቱን እያየ ጴጥሮስን፣ “አንተ ሰይጣን፤ ወደ ኋላዬ ሂድ! የሰው እንጂ የእግዚአብሔር ነገር በሐሳብህ የለምና” በማለት ገሠጸው። 34.ከዚህ በኋላ፣ ሕዝቡን ከደቀ መዛሙርቱ ጋራ ወደ እርሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “ሊከተለኝ የሚወድድ ቢኖር ራሱን ይካድ፤ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ። 35.ነፍሱን ለማዳን የሚወድድ ሁሉ ያጠፋታል፤ ስለ እኔና ስለ ወንጌል ነፍሱን የሚያጠፋት ሁሉ ግን ያድናታል። 36.ሰው ዓለሙ ሁሉ የርሱ ቢሆንና ነፍሱን ቢያጠፋ ምን ይጠቅመዋል? 37.ለመሆኑ፣ ሰው ለነፍሱ ምን መተኪያ አለው? 38.በዚህ ዘማዊና ኀጢአተኛ ትውልድ መካከል በእኔና በቃሌ የሚያፍር ሁሉ፣ የሰው ልጅም በአባቱ ግርማ፣ ከቅዱሳን መላእክት ጋራ ሲመጣ ያፍርበታል።”