Skip to Content
የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን | YEHIWOT MELHEK BETEKIRSTIAN
የ2019 ዓ.ም የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ 📖 ዛሬን አንብብ →

የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን

Yehiwot Melhek Betekirstian

ሳምንት 2 · ቀን 7 (ማክሰኞ) 📅 Meskerem 12, 2019

ኦሪት ዘፍጥረት 19, 20 · መዝሙረ ዳዊት 1 · የማርቆስ ወንጌል 7

📖 የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም፦ 1954 መጽሐፍ ቅዱስ አዲሱ መደበኛ ትርጒም

ኦሪት ዘፍጥረት

ምዕራፍ 19

ሰዶምና ገሞራ ጠፉ

1.ሁለቱ መላእክት ምሽት ላይ ሰዶም ደረሱ፤ ሎጥም በሰዶም ከተማ መግቢያ በር ተቀምጦ ነበር፤ ሎጥም መላእክቱን ሲያይ ሊቀበላቸው ብድግ አለ፤ በግንባሩም ወደ ምድር ተደፍቶ እጅ ነሣቸው። 2.እርሱም፣ “ጌቶቼ፤ እባካችሁ ወደ እኔ ወደ ባሪያችሁ ቤት ጎራ በሉ፤ ከዚያም እግራችሁን ታጠቡ፤ ዐድራችሁም ጧት በማለዳ ጕዟችሁን ትቀጥላላችሁ” አላቸው።
እነርሱም፣ “አይሆንም፤ እዚሁ አደባባይ ላይ እናድራለን” አሉት።
3.ሎጥ ግን አጥብቆ ስለ ለመናቸው ዐብረውት ወደ ቤቱ ገቡ፤ ከዚያም ቂጣ ጋግሮ አቀረበላቸውና በሉ። 4.ከመተኛታቸውም በፊት፣ የሰዶም ከተማ ነዋሪዎች የሆኑ ወንድ ወጣቶችና ሽማግሌዎች ከየአካባቢው መጥተው ቤቱን ከበቡት። 5.ሎጥንም ጠርተው፣ “በዚህች ምሽት ወደ ቤትህ የገቡት ሰዎች የት አሉ? ሩካቤ ሥጋ እንድንፈጽምባቸው ወደ ውጭ አውጣልን” አሉት። 6.ሎጥም ሊያነጋግራቸው ወደ ውጭ ወጣ፤ መዝጊያውን ከበስተኋላው ዘግቶ፣ 7.እንዲህ አለ፤ “ወዳጆቼ ሆይ፤ እባካችሁ እንዲህ ያለውን ክፉ ነገር አታድርጉ። 8.እነሆ፤ ወንድ የማያውቁ ሁለት ሴቶች ልጆች አሉኝ። እነርሱን ላውጣላችሁና የፈለጋችሁትን አድርጉባቸው። በእነዚህ ሰዎች ላይ ግን አንዳች ነገር አታድርጉባቸው፤ እኔን ብለው ወደ ቤቴ ገብተዋልና።” 9.እነርሱም፣ “ዞር በል! ይህ ሰው ራሱ ትናንት ተሰድዶ የመጣ ነው፤ ዛሬ ደግሞ ዳኛ ልሁን ይላል። ዋ! በእነርሱ ካሰብነው የከፋ እንዳናደርስብህ!” አሉት፤ ከዚያም ሎጥን እየገፈታተሩ የበሩን መዝጊያ ለመስበር ተንደረደሩ። 10.ከቤቱ ውስጥ የነበሩት እንግዶች ግን እጃቸውን በመዘርጋት ሎጥን ስበው ወደ ውስጥ አስገቡት፤ በሩንም ዘጉ። 11.ከዚያም በሩን እንዳያገኙት በቤቱ ደጃፍ ላይ የተሰበሰቡትን ወጣቶችና ሽማግሌዎች ዐይን አሳወሩ። 12.ሁለቱ ሰዎችም ሎጥን እንዲህ አሉት፤ “በከተማዪቱ ውስጥ የሚኖሩ የአንተ የሆኑ ሰዎች አሉህ? ዐማቾች፣ ወንዶችና ሴቶች ወይም ሌሎች ዘመዶች ካሉህ ቶሎ ብለህ ከዚህ እንዲወጡ አድርግ፤ 13.ይህን ስፍራ ልናጠፋው ነው። በሕዝቦቿ ላይ ወደ እግዚአብሔር የቀረበው ጩኸት ታላቅ በመሆኑ፣ እንድናጠፋት እግዚአብሔር ልኮናል።” 14.ሎጥ ከቤቱ ወጥቶ የሴት ልጆቹ እጮኞች የሆኑትን ዐማቾቹን፣ “እግዚአብሔር ይህችን ከተማ ሊያጠፋት ነውና በፍጥነት ከዚህ ስፍራ ውጡ” አላቸው፤ ዐማቾቹ ግን የሚቀልድ መሰላቸው። 15.ሲነጋጋም መላእክቱ ሎጥን፣ “ከከተማዪቱ ጋራ ዐብራችሁ እንዳትጠፉ፣ ሚስትህንና ሁለቱን ሴት ልጆችህን ይዘህ ከዚህ ቦታ በፍጥነት ውጣ” ብለው አቻኰሉት። 16.ሎጥ ሲያመነታም፣ እግዚአብሔር ስለ ራራላቸው ሰዎቹ የርሱን፣ የሚስቱንና የሁለት ሴቶች ልጆቹን እጅ ይዘው ከከተማዪቱ በደኅና አወጧቸው። 17.እንዳወጧቸውም፣ መልአኩ፣ “ሕይወታችሁን ለማትረፍ ፈጥናችሁ ሽሹ፤ መለስ ብላችሁ ወደ ኋላችሁ አትመልከቱ፤ ከረባዳው ስፍራ እንኳ ቆም አትበሉ፤ ወደ ተራራው ሽሹ፤ አለዚያ ትጠፋላችሁ” አላቸው። 18.ሎጥም እንዲህ አላቸው፤ “ጌቶቼ ሆይ፤ እባካችሁ እንደዚህስ አይሁን፤ 19.እነሆ፤ እኔ ባሪያህ አንዴ በፊትህ ሞገስ አግኝቻለሁ፤ ሕይወቴን ለማዳን ታላቅ ርኅራኄ አድርገህልኛል፤ እኔ እንደ ሆንሁ ወደ ተራሮቹ ሸሽቼ ማምለጥ ስለማልችል የሚወርደው መዓት ደርሶ ያጠፋኛል። 20.እነሆ፤ ወደዚያ ሸሽቶ ለማምለጥ ቅርብ የሆነች ትንሽ ከተማ አለች፤ ወደ እርሷ ልሽሽ፤ በጣም ትንሽ አይደለችም እንዴ? ወደዚያ ብሸሽ እኮ ሕይወቴ ትተርፋለች።” 21.እርሱም እንዲህ አለው፤ “ይሁን ዕሺ፣ ልመናህን ተቀብያለሁ፤ ያልካትንም ከተማ አላጠፋትም። 22.አንተ እዚያ እስክትደርስ ድረስ አንዳች ማድረግ ስለማልችል ቶሎ ብለህ ወደዚያ ሽሽ።” ስለዚህም የዚያች ከተማ ስም ዞዓር ተባለ። 23.ሎጥ ዞዓር ሲደርስ ፀሓይ በምድሩ ላይ ወጥታ ነበር። 24.ከዚያም እግዚአብሔር በሰዶምና በገሞራ ላይ ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚያቃጥል ዲንና እሳት አዘነበባቸው። 25.እነዚያንም ከተሞችና ረባዳውን ምድር በሙሉ፣ በከተሞቹም የሚኖሩትን ሰዎች ሁሉ፣ የምድሩን ቡቃያ ሳይቀር ገለባበጠው። 26.የሎጥ ሚስት ግን ወደ ኋላዋ ስለ ተመለከተች የጨው ዐምድ ሆና ቀረች። 27.አብርሃም በማግስቱም፣ ማለዳ ተነሥቶ ከዚህ ቀደም በእግዚአብሔር ፊት ቆሞ ወደ ነበረበት ቦታ ሄደ። 28.ሰዶምንና ገሞራን፣ እንዲሁም በረባዳው ስፍራ የሚገኘውን ምድር ሁሉ ቍልቍል ተመለከተ፤ ከእቶን የሚወጣ የመሰለ ጥቅጥቅ ያለ ጢስ ከምድሪቱ ወደ ላይ ሲትጐለጐል አየ። 29.እንደዚህ አድርጎ እግዚአብሔር በረባዳው ስፍራ የነበሩትን ከተሞች ሲያጠፋ አብርሃምን ዐሰበው፤ ስለዚህም የሎጥ መኖሪያ የነበሩትን ከተሞች ካጠፋው መዓት ሎጥን አወጣው።

ሎጥና ሴት ልጆቹ

30.ሎጥ በዞዓር መኖርን ስለ ፈራ፣ ከዚያ ተነሥቶ ከሁለቱ ሴት ልጆቹ ጋራ በአቅራቢያው ወደሚገኙት ተራሮች ሄደ፤ መኖሪያውንም ከሁለት ሴት ልጆቹ ጋራ በዋሻ ውስጥ አደረገ። 31.አንድ ቀን ታላቂቱ ልጅ፣ ታናሺቱን እንዲህ አለቻት፤ “አባታችን አርጅቷል፤ በምድር ሁሉ እንደሚኖሩ ሰዎች ወግ ዐብሮን የሚተኛ ወንድ በአካባቢያችን የለም። 32.ስለዚህ አባታችንን የወይን ጠጅ እናጠጣውና ከርሱ ጋራ እንተኛ፤ የትውልድ ሐረጋችን እንዳይቋረጥ ዘር ከአባታችን እናትርፍ።” 33.በዚያችም ምሽት አባታቸውን የወይን ጠጅ አጠጡት፤ ከዚያም ትልቋ ልጁ ሄዳ ከአባቷ ጋራ ተኛች፤ እርሱ ግን ስትተኛም ሆነ ስትነሣ አላወቀም ነበር። 34.በማግስቱም ታላቂቱ ልጅ ታናሺቱን፣ “እኔ ትናንትና ማታ ከአባቴ ጋራ ተኝቻለሁ፤ ዛሬም እንደ ገና የወይን ጠጅ እናጠጣው፤ አንቺም ደግሞ ከርሱ ዘንድ ገብተሽ ተኚ፤ በዚህም የትውልድ ሐረጋችን እንዳይቋረጥ ከአባታችን ዘር ማትረፍ እንችላለን” አለቻት። 35.በዚያችም ምሽት ደግሞ አባታቸውን የወይን ጠጅ አጠጡት፤ ትንሿ ልጁም ሄዳ ከአባቷ ጋራ ተኛች፤ እርሱ ግን ስትተኛም ሆነ ስትነሣ አላወቀም ነበር። 36.ስለዚህ ሁለቱም የሎጥ ሴት ልጆች ከአባታቸው አረገዙ። 37.ትልቋ ልጁ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ስሙንም ሞዓብ ብላ ጠራችው፤ እርሱም የዛሬዎቹ ሞዓባውያን አባት ነው። 38.ትንሿ ልጁም እንደዚሁ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ስሙንም ቤንአሚ ብላ ጠራችው፤ እርሱም የዛሬዎቹ አሞናውያን አባት ነው።

ምዕራፍ 20

አብርሃምና አቤሜሌክ

20፥1-18 ተጓ ምብ – ዘፍ 12፥10-20፤ 26፥1-11
1.አብርሃም ከዚያ ተነሥቶ ወደ ኔጌብ አካባቢ ሄዶ በቃዴስና በሱር መካከል ሰፈረ፤ ለጥቂት ጊዜም በጌራራ ተቀመጠ። 2.በዚያም አብርሃም ሚስቱን ሣራን፣ “እኅቴ ናት” ይል ነበር። ስለዚህ የጌራራ ንጉሥ አቢሜሌክ መልእክተኛ ልኮ ሣራን ወሰዳት። 3.እግዚአብሔርም በአንድ ሌሊት በሕልም ወደ አቢሜሌክ መጥቶ፣ “እነሆ፤ በወሰድሃት ሴት ምክንያት ምዉት ነህ፤ እርሷ ባለባል ናት” አለው። 4.አቢሜሌክም ገና አልደረሰባትም ነበርና እንዲህ አለ፤ “ጌታ ሆይ፤ በደል ያልፈጸመውን ሕዝብ ታጠፋለህን? 5.‘እኅቴ ናት’ ያለኝ ራሱ አይደለምን? ደግሞስ ራሷም ብትሆን፣ ‘ወንድሜ ነው’ አላለችምን? እኔ ይህን ያደረግሁት በቅን ልቡናና በንጹሕ እጅ ነው።” 6.እግዚአብሔርም በሕልሙ እንዲህ አለው፤ “አንተ ይህን ያደረግኸው በቅን ልቡና መሆኑን ዐውቄአለሁ፤ በእኔም ላይ ኀጢአት እንዳትሠራ የጠበቅሁህና እንዳትነካትም ያደረግሁት ለዚሁ ነው። 7.አሁንም ሚስቱን ለሰውየው መልስለት፤ ነቢይ ነውና ይጸልይልሃል፤ አንተም ትድናለህ፤ ባትመልስለት ግን አንተም ሆንህ የአንተ የሆነ ሁሉ እንደምትሞቱ ዕወቅ።” 8.በማግስቱም ማለዳ፣ አቢሜሌክ ሹማምቱን ሁሉ ጠርቶ፣ የሆነውን ሁሉ ነገራቸው፤ እነርሱም ታላቅ ፍርሀት ዐደረባቸው። 9.ከዚያም አቢሜሌክ አብርሃምን አስጠርቶ እንዲህ አለው፤ “ይህ ያደረግህብን ነገር ምንድን ነው? ምን በደልሁህና ነው በእኔና በግዛቴ ላይ እንዲህ ያለውን ታላቅ የጥፋት መዘዝ ያመጣህብን? በእውነቱ መደረግ የማይገባውን ነው ያደረግህብን።” 10.ከዚያም አቢሜሌክ፣ “ለመሆኑ ይህን ያደረግህበት ምክንያት ምንድን ነው?” ሲል አብርሃምን ጠየቀው። 11.አብርሃምም አቢሜሌክን እንዲህ አለው፤ “ ‘እዚህ ቦታ ፈሪሀ እግዚአብሔር አለመኖሩን ተገነዘብሁ፤ ሰዎቹም ለሚስቴ ሲሉ ይገድሉኛል’ ብዬ ሠጋሁ፤ 12.ደግሞም እኮ በርግጥ እኅቴ ናት፤ ከአንድ እናት ባንወለድም በአባት አንድ ነን፤ ኋላም አገባኋት። 13.እግዚአብሔር አዝዞኝ ከአባቴ ቤት ወጥቼ በየአገሩ ስዞር፣ ‘ለእኔ ያለሽን ፍቅር በዚህ ግለጭልኝ፤ በየደረስንበት ስፍራ ሁሉ “እርሱ ወንድሜ ነው” በዪ’ ብያት ነበር።” 14.ከዚያም አቢሜሌክ፣ በጎችና የቀንድ ከብቶች፣ ወንድና ሴት አገልጋዮችን ለአብርሃም ሰጠው፤ ሚስቱን ሣራንም መለሰለት። 15.አቢሜሌክም አብርሃምን፣ “እነሆ፤ አገሬ አገርህ ናት፤ በፈቀድህበት ስፍራ መኖር ትችላለህ” አለው። 16.ሣራንም፣ “እነሆ፤ ለወንድምሽ ለአብርሃም አንድ ሺሕ ጥሬ ብር እሰጠዋለሁ፤ ይህም በአንቺ ላይ ለተፈጸመው በደል ካሣ እንዲሆንና ዐብረውሽ ያሉ ሁሉ እንዲያውቁት ነው፤ በዚህም ንጽሕናሽ ይረጋገጣል” አላት። 17.ከዚያም አብርሃም ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤ እግዚአብሔርም አቢሜሌክን፣ ሚስቱንና ሴት አገልጋዮቹን ፈወሳቸው፤ እንደ ገናም ልጅ ለመውለድ በቍ። 18.እግዚአብሔር በአብርሃም ሚስት በሣራ ምክንያት፣ በአቢሜሌክ ቤት የሚገኙትን ሴቶች ማሕፀናቸውን ሁሉ ዘግቶ ነበርና።

መዝሙረ ዳዊት

ምዕራፍ 1

1.አንደኛ መጽሐፍ
ከመዝሙር 1–41
1 ብፁዕ ነው፣
በክፉዎች ምክር የማይሄድ፣
በኀጢአተኞች መንገድ የማይቆም፣
በፌዘኞችም ወንበር የማይቀመጥ፤
2.ነገር ግን ደስ የሚሠኘው በእግዚአብሔር ሕግ ነው፤
ሕጉንም በቀንና በሌሊት ያሰላስለዋል።
3.እርሱም በወራጅ ውሃ ዳር እንደ ተተከለች፣
ፍሬዋን በየወቅቱ እንደምትሰጥ፣
ቅጠሏም እንደማይጠወልግ ዛፍ ነው፤
የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል።
4.ክፉዎች ግን እንዲህ አይደሉም፤
ነገር ግን ነፋስ ጠራርጎ እንደሚወስደው
ገለባ ናቸው።
5.ስለዚህ ክፉዎች በፍርድ ፊት፣
ኀጢአተኞችም በጻድቃን ማኅበር መቆም አይችሉም።
6.እግዚአብሔር የጻድቃንን መንገድ ይጠብቃልና፤
የክፉዎች መንገድ ግን ትጠፋለች።

የማርቆስ ወንጌል

ምዕራፍ 7

ኢየሱስ የአይሁድን ውጫዊ ሥርዐት ተቃወመ

7፥1-23 ተጓ ምብ – ማቴ 15፥1-20
1.ከዚህ በኋላ ፈሪሳውያንና ከኢየሩሳሌም የመጡ አንዳንድ ጸሐፍት በዙሪያው ተሰበሰቡ፤ 2.ከደቀ መዛሙርቱም አንዳንዶቹ ባልነጻ ማለት ባልታጠበ እጅ እንጀራ ሲበሉ አዩ፤ 3.ፈሪሳውያንና አይሁድ ሁሉ የአባቶችን ወግ ለመጠበቅ ሲሉ፣ በሥርዐቱ መሠረት እጃቸውን በጥንቃቄ ሳይታጠቡ አይበሉም ነበርና። 4.ከገበያ ሲመለሱም ታጥበው ራሳቸውን ካላነጹ በቀር አይበሉም ነበር። እንዲሁም ዋንጫን፣ ማሰሮን፣ ሳሕንና ዐልጋን እንደ ማጠብ ያሉትን ሌሎችን ወጎች ይጠብቁ ነበር። 5.ፈሪሳውያንና ጸሐፍትም፣ “ደቀ መዛሙርትህ እንደ አባቶች ወግ በመኖር ፈንታ ባልታጠበ እጃቸው ለምን እንጀራ ይበላሉ?” ብለው ጠየቁት። 6.እርሱም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ኢሳይያስ ስለ እናንተ፣ ስለ ግብዞች በትክክል ተንብዮአል፤ እንዲህ ተብሎ ተጽፏልና፤
“ ‘ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል፤
ልቡ ግን ከእኔ የራቀ ነው፤
7.በከንቱ ያመልኩኛል፤
ትምህርታቸውም ሰው ሠራሽ ሥርዐት ነው።’
8.የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ትታችሁ የሰዎችን ወግና ሥርዐት ታጠብቃላችሁ።” 9.ደግሞም፣ እንዲህ አላቸው፤ “የራሳችሁን ወግ ለመጠበቅ ስትሉ፣ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ የምትተዉበት ዘዴ አላችሁ። 10.ሙሴ፣ ‘አባትህንና እናትህን አክብር፤ አባቱን ወይም እናቱን የሚሳደብ ይሙት’ ብሎ ነበርና፤ 11.እናንተ ግን አንድ ሰው አባቱን ወይም እናቱን፣ ከእኔ ማግኘት የሚገባችሁን ርዳታ ሁሉ ቍርባን፣ ይኸውም መባ እንዲሆን ሰጥቻለሁ ቢላቸው፣ 12.እናንተም ይህ ሰው ለአባቱም ሆነ ለእናቱ ከዚህ በኋላ ምንም ነገር እንዲያደርግ አትፈቅዱለትም። 13.ስለዚህ ለትውልድ በምታስተላልፉት ወግ የእግዚአብሔርን ቃል ትሽራላችሁ፤ ይህን የመሰለም ብዙ ነገር ታደርጋላችሁ።” 14.ደግሞም ኢየሱስ ሕዝቡን ወደ ራሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “ስሙኝ፤ ሁላችሁም አስተውሉ፤ 15.ከውጭ ወደ ውስጥ ገብቶ ሰውን የሚያረክሰው አንዳች ነገር የለም፤ ይልቁን ሰውን የሚያረክሰው ከራሱ ወደ ውጭ የሚወጣው ነገር ነው፤ [ 16.ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ።”] 17.ሕዝቡን ትቶ ወደ ቤት ከገባ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ስለ ምሳሌው ጠየቁት። 18.እርሱም፣ “እናንተም አይገባችሁምን? ከውጭ ወደ ሰው ገብቶ ሊያረክሰው የሚችል አንዳች ነገር የለም፤ 19.ወደ ልቡ ሳይሆን ወደ ሆዱ ይገባል፤ ከዚያም ከሰውነቱ ይወጣልና።” ኢየሱስ ይህን በማለቱ ምግብ ሁሉ ንጹሕ መሆኑን ገለጠ። 20.ቀጥሎም፣ እንዲህ አለ፤ “ከሰው የሚወጣ ያ ሰውን ያረክሰዋል፤ 21.ከውስጥ፣ ከሰው ልብ የሚወጡት ክፉ ሐሳብ፣ ምንዝር፣ ስርቆት፤ ሰው መግደል፣ ዝሙት፣ 22.መስገብገብ፣ ክፋት፣ ማታለል፣ መዳራት፣ ምቀኛነት፣ ስም ማጥፋት፣ ትዕቢት፣ ስንፍና ናቸው። 23.እነዚህ ክፉ ነገሮች ሁሉ ከውስጥ ይወጣሉ፤ ሰውንም ያረክሱታል።”

ሲሮፊኒቃዊቷ ሴት

7፥24-30 ተጓ ምብ – ማቴ 15፥21-28
24.ከዚያ ተነሥቶ ወደ ጢሮስ አገር ሄደ፤ ወደ አንድ ቤት ገብቶ እዚያ መኖሩን ማንም እንዳያውቅበት ፈለገ፤ ሆኖም እዚያ መኖሩ ሊሸሸግ አልቻለም። 25.ወዲያው ግን ትንሺቱ ልጇ በርኩስ መንፈስ የተያዘችባት አንዲት ሴት ስለ እርሱ ሰምታ መጣችና በእግሩ ላይ ወደቀች። 26.ሴትዮዋም ግሪካዊት፣ በትውልዷም ሲሮፊኒቃዊት ነበረች። እርሷም ኢየሱስ ጋኔኑን ከልጇ እንዲያስወጣላት ለመነችው። 27.እርሱ ግን፣ “የልጆችን እንጀራ ወስዶ ለውሾች መጣል ተገቢ ስላልሆነ፣ መጀመሪያ ልጆቹ ጠግበው ይብሉ” አላት። 28.እርሷም መልሳ፣ “አዎን፣ ጌታ ሆይ፤ ውሾችም እኮ ከገበታ በታች ሆነው የልጆችን ፍርፋሪ ይበላሉ” አለችው። 29.እርሱም፣ “ስለዚህ ይህን ስላልሽ ሂጂ፤ ጋኔኑ ከልጅሽ ወጥቷል” አላት። 30.እርሷም ወደ ቤቷ ስትመለስ ልጇ ዐልጋ ላይ ተኝታ፣ ጋኔኑም ለቅቋት አገኘቻት።

የደንቈሮውና የድዳው መፈወስ

7፥31-37 ተጓ ምብ – ማቴ 15፥29-31
31.ከዚያም ኢየሱስ ከጢሮስ አገር ተነሥቶ፣ በሲዶና በኩል አድርጎ ዐሥር ከተማ በተባለው አገር በማለፍ ወደ ገሊላ ባሕር መጣ። 32.በዚያም ሰዎች ደንቈሮና ዲዳ የሆነ አንድ ሰው ወደ እርሱ አመጡ፤ እጁንም እንዲጭንበት ለመኑት። 33.ኢየሱስም ሰውየውን ከሕዝቡ ለይቶ ከወሰደው በኋላ፣ ጣቶቹን በጆሮው አስገባ፤ ከዚያም እንትፍ ብሎ የሰውየውን ምላስ ዳሰሰ። 34.ወደ ሰማይም ተመልክቶ ቃተተና፣ “ኤፍታህ!” አለው፤ ይኸውም፣ “ተከፈት” ማለት ነው። 35.ወዲያውም ጆሮዎቹ ተከፈቱ፤ ምላሱም ተፈትቶ አጥርቶ መናገር ጀመረ። 36.ኢየሱስ ይህን ለማንም እንዳይናገሩ አዘዛቸው፤ ሆኖም እርሱ እንዳይናገሩ ባዘዛቸው መጠን፣ ነገሩን አስፍተው አወሩት። 37.ሕዝቡም ከመጠን በላይ በመደነቅ፣ “ያደረገው ሁሉ ጥሩ ነው፤ ደንቈሮዎች እንዲሰሙ፣ ድዳዎች እንዲናገሩ እንኳ አድርጓል” አሉ።