Skip to Content
የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን | YEHIWOT MELHEK BETEKIRSTIAN
የ2019 ዓ.ም የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ 📖 ዛሬን አንብብ →

የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን

Yehiwot Melhek Betekirstian

ሳምንት 2 · ቀን 6 (ሰኞ) 📅 Meskerem 11, 2019

ኦሪት ዘፍጥረት 16, 17, 18 · የማርቆስ ወንጌል 6

📖 የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም፦ 1954 መጽሐፍ ቅዱስ አዲሱ መደበኛ ትርጒም

ኦሪት ዘፍጥረት

ምዕራፍ 16

አጋርና እስማኤል

1.የአብራም ሚስት ሦራ፣ ልጆች አልወለደችለትም ነበር፤ እርሷም አጋር የምትባል ግብጻዊት አገልጋይ ነበረቻት። 2.አብራምንም፣ “እግዚአብሔር ልጅ እንዳልወልድ አድርጎኛል። ምናልባት በርሷ በኩል ልጆች አገኝ እንደሆን ሄደህ ከአገልጋዬ ጋራ ተኛ” አለችው።
አብራምም ሦራ ባለችው ተስማማ።
3.አብራም በከነዓን ምድር ዐሥር ዓመት ከኖረ በኋላ ሚስቱ ሦራ ግብጻዊት አገልጋይዋን አጋርን ሚስት እንድትሆነው ለባሏ ሰጠችው። 4.አብራምም ከአጋር ጋራ ተኛ፤ እርሷም ፀነሰች።
አጋርም ነፍሰ ጡር መሆኗን ባወቀች ጊዜ እመቤቷን መናቅ ጀመረች።
5.ሦራም አብራምን፣ “ለደረሰብኝ በደል ተጠያቂው አንተ ነህ፤ አገልጋዬ ዕቅፍህ ውስጥ እንድትገባ እኔው ሰጠሁህ፤ አሁን ግን ይኸው ማርገዟን ስታውቅ ትንቀኝ ጀመር፤ እግዚአብሔር በአንተና በእኔ መካከል ይፍረድ” አለችው። 6.አብራምም፣ “አገልጋይሽ እንደ ሆነች በእጅሽ ውስጥ ናት፤ የፈለግሽውን አድርጊባት” አላት። ከዚያም ሦራ ስላሠቃየቻት አጋር ጥላት ኰበለለች። 7.የእግዚአብሔር መልአክ አጋርን በአንድ የውሃ ምንጭ አጠገብ በምድረ በዳ አገኛት፤ ምንጩም ወደ ሱር በሚወስደው መንገድ ዳር ነበር። 8.መልአኩም፣ “የሦራ አገልጋይ አጋር ሆይ፤ ከየት መጣሽ? ወዴትስ ትሄጃለሽ?” አላት።
እርሷም፣ “ከእመቤቴ ከሦራ ኰብልዬ መምጣቴ ነው” ብላ መለሰች።
9.የእግዚአብሔርም መልአክ፣ “ወደ እመቤትሽ ተመለሽ፤ ለርሷም ተገዥላት” አላት። 10.ደግሞም የእግዚአብሔርም መልአክ፣ “ዘርሽን እጅግ አበዛለሁ፤ ከብዛቱም የተነሣ ሊቈጠር አይችልም” አላት። 11.የእግዚአብሔርም መልአክ በተጨማሪ እንዲህ አላት፤
“እነሆ፤ ፀንሰሻል፤
ወንድ ልጅ ትወልጃለሽ፤
እግዚአብሔር ችግርሽን ተመልክቷል፤
ስሙን እስማኤል ትዪዋለሽ።
12.እርሱም እንደ ዱር አህያ ይሆናል፤
እጁንም ባገኘው ሰው ሁሉ ላይ ያነሣል፤
ያገኘውም ሁሉ እጁን ያነሣበታል፤
ከወንድሞቹ ሁሉ ጋራ እንደ ተጣላ ይኖራል።”
13.እርሷም ያናገራትን እግዚአብሔርን፣ “ኤልሮኢ” ብላ ጠራችው፤ ምክንያቱም “የሚያየኝን አሁን አየሁት” ብላ ነበርና። 14.ከዚህ የተነሣ የዚያ ምንጭ ስም፣ “ብኤርላሃይሮኢ” ተብሎ ተጠራ፤ እስካሁንም በቃዴስና በባሬድ መካከል ይገኛል። 15.አጋር ለአብራም ወንድ ልጅ ወለደችለት፤ አብራምም ስሙን እስማኤል ብሎ ጠራው። 16.አብራም፣ አጋር እስማኤልን በወለደች ጊዜ ዕድሜው
86 ዓመት ነበር።

ምዕራፍ 17

የግዝረት ኪዳን

1.አብራም ዕድሜው
99 ዓመት በሆነ ጊዜ፣ እግዚአብሔር ተገልጦለት እንዲህ አለው፤ “እኔ ሁሉን ቻይ አምላክ ነኝ፤ በፊቴ ተመላለስ፤ ነቀፋም አይኑርብህ፤
2.በእኔና በአንተ መካከል የተመሠረተውን ኪዳን አጸናለሁ፤ ዘርህንም እጅግ አበዛለሁ።” 3.አብራም በግንባሩ መሬት ላይ ተደፋ፤ እግዚአብሔርም እንዲህ አለው፤ 4.“እነሆ፤ የምገባልህ ኪዳን ይህ ነው፤ የብዙ ሕዝቦች አባት ትሆናለህ። 5.ከእንግዲህ ወዲያ ስምህ አብራም መባሉ ቀርቶ አብርሃም ይሆናል፤ የብዙ ሕዝቦች አባት አድርጌሃለሁና። 6.ዘርህን እጅግ አበዛለሁ፤ ብዙ ሕዝብም አደርግሃለሁ፤ ነገሥታትም ከአንተ ይወጣሉ። 7.በእኔና በአንተ፣ ከአንተም በኋላ ከዘርህ ጋራ ከትውልድ እስከ ትውልድ የዘላለም ኪዳኔን እመሠርታለሁ፤ በዚህም የአንተና ከአንተም በኋላ የዘርህ አምላክ እሆናለሁ። 8.ይህችን አሁን በእንግድነት የምትኖርባትን የከነዓንን ምድር በሙሉ ለአንተና ከአንተም በኋላ ለዘርህ ለዘላለም ርስት አድርጌ እሰጣቸዋለሁ፤ አምላካቸውም እሆናለሁ።” 9.ከዚያም እግዚአብሔር አብርሃምን እንዲህ አለው፤ “በአንተም በኩል፣ አንተና ከአንተ በኋላ የሚመጣው ዘርህ ከትውልድ እስከ ትውልድ ኪዳኔን ትጠብቃላችሁ። 10.አንተና ከአንተም በኋላ የሚመጣው ዘርህ የምትጠብቁት ኪዳን ይህ ነው፤ በመካከላችሁ ያለ ወንድ ሁሉ ይገረዝ። 11.ስለዚህ ሁላችሁም ሸለፈታችሁን ትገረዛላችሁ፤ ይህም በእኔና በእናንተ መካከል ላለው ኪዳን ምልክት ይሆናል። 12.የሚመጣውም ትውልድ ሁሉ፣ ማንኛውም ወንድ ልጅ፣ ስምንት ቀን ሲሞላው ይገረዝ፤ እንደዚሁም በቤትህ የተወለደውና ከውጭ በገንዘብ የተገዛ ባዕድ ሁሉ ይገረዝ። 13.በቤትህ የተወለደም ሆነ በገንዘብህ የተገዛ ሁሉ መገረዝ አለበት፤ በሥጋችሁ የሚፈጸመው ይህ ኪዳኔ የዘላለም ኪዳን ይሆናል። 14.የሥጋ ሸለፈቱን ያልተገረዘ ማንኛውም ወንድ ኪዳኔን በማፍረሱ ከወገኖቹ ይወገድ።” 15.እግዚአብሔር አብርሃምን እንዲህ አለው፤ “ሦራን ከእንግዲህ ሦራ ብለህ አትጠራትም፤ ስሟ ከዛሬ ጀምሮ ሣራ ይሁን። 16.እኔ እባርካታለሁ ከርሷም ወንድ ልጅ እሰጥሃለሁ፤ የብዙም ሕዝቦች እናት ትሆን ዘንድ እባርካታለሁ፤ የሕዝቦችም ነገሥታት ከርሷ ይወጣሉ።” 17.አብርሃምም በግንባሩ መሬት ላይ ተደፋ፤ ሣቀና በልቡ፣ “እንዲያው ምንስ ቢሆን የመቶ ዓመት ሽማግሌ የልጅ አባት መሆን ይችላልን? ሣራስ በዘጠና ዓመቷ ልጅ መውለድ ትችላለችን?” አለ። 18.አብርሃም እግዚአብሔርን፣ “እስማኤልን ብቻ ባርከህ ባኖርህልኝ” አለው። 19.እግዚአብሔር እንዲህ አለ፤ “ይሁን ዕሺ፤ ነገር ግን ሚስትህ ሣራ ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች፤ ስሙንም ይሥሐቅ ብለህ ትጠራዋለህ፤ እኔም ከርሱ በኋላ ለዘሩ ሁሉ የሚሆን የዘላለም ኪዳን ከርሱ ጋራ እገባለሁ። 20.ስለ እስማኤልም ቢሆን ልመናህን ሰምቼሃለሁ፤ እርሱንም እባርከዋለሁ፤ ፍሬያማም አደርገዋለሁ፤ እጅግም አበዛዋለሁ፤ የዐሥራ ሁለት አለቆች አባት ይሆናል፤ ታላቅም ሕዝብ አደርገዋለሁ። 21.ኪዳኔን ግን የዛሬ ዓመት በዚሁ ጊዜ ሣራ ከምትወልድልህ ልጅ፣ ከይሥሐቅ ጋራ አደርጋለሁ።” 22.እግዚአብሔር ከአብርሃም ጋራ መነጋገሩን ከፈጸመ በኋላ ወደ ላይ ወጣ። 23.በዚያችም ዕለት አብርሃም እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት ልጁን እስማኤልን፣ በቤቱ ውስጥ የተወለዱትንና ከውጭ በገንዘቡ የገዛቸውን ወንዶች በሙሉ ሸለፈታቸውን ገረዛቸው። 24.አብርሃም ሸለፈቱን ሲገረዝ ዕድሜው
99 ዓመት ነበር።
25.ልጁም እስማኤል ሸለፈቱን ሲገረዝ
13 ዓመቱ ነበር።
26.አብርሃምና ልጁ እስማኤል፣ ሁለቱም በዚያ ቀን ተገረዙ። 27.በአብርሃም ቤት ያሉ ወንዶች ሁሉ፣ በቤቱ የተወለዱትም ሆኑ ከውጭ በገንዘብ የተገዙ ከርሱ ጋራ ተገረዙ።

ምዕራፍ 18

ሦስቱ እንግዶች

1.ቀትር ላይ አብርሃም በመምሬ ትልልቅ ዛፎች አቅራቢያ በምትገኘው ድንኳኑ ደጃፍ ተቀምጦ ሳለ እግዚአብሔር ተገለጠለት፤ 2.ቀና ብሎም ሲመለከት፣ ሦስት ሰዎች ቆመው አየ፤ ወዲያውም ከድንኳኑ ደጃፍ ተነሥቶ፣ ፈጥኖ ወደ ሰዎቹ ሄደ፤ ወደ መሬት ዝቅ ብሎም እጅ ነሣ። 3.አብርሃምም እንዲህ አለ፤ “ጌታዬ፤ በፊትህ ሞገስ አግኝቼ እንደ ሆነ፣ ባሪያህን ዐልፈህ አትሂድ፤ 4.ጥቂት ውሃ ይምጣላችሁና እግራችሁን ታጠቡ፤ እዚህም ከዛፉ ሥር ዐረፍ በሉ። 5.ወደ እኔ ወደ አገልጋያችሁ ከመጣችሁ፣ እህል ቀምሳችሁ ትበረቱ ዘንድ ምግብ ላቅርብላችሁና ጕዟችሁን ትቀጥላላችሁ።”
እነርሱም፣ “መልካም፤ እንዳልኸው አድርግ” አሉት።
6.አብርሃም በፍጥነት ሣራ ወዳለችበት ወደ ድንኳኑ ገብቶ፣ “ቶሎ ብለሽ ሦስት መስፈሪያ ስልቅ ዱቄት አቡኪና ቂጣ ጋግሪ” አላት። 7.ከዚያም ወደ መንጋው በጥድፊያ ሄዶ፣ አንድ ፍርጥም ያለ ሥጋው ገር የሆነ ጥጃ መርጦ ለአገልጋዩ ሰጠው፤ አገልጋዩም ጥጃውን ዐርዶ አዘጋጀው። 8.አብርሃምም ርጎ፣ ወተትና የተዘጋጀውን የጥጃ ሥጋ አቀረበላቸው፤ ሲበሉም ዛፉ ሥር አጠገባቸው ቆሞ ነበር። 9.እነርሱም አብርሃምን፣ “ሚስትህ ሣራ የት አለች?” ብለው ጠየቁት።
እርሱም፣ “ድንኳን ውስጥ ናት” አላቸው።
10.እግዚአብሔርም፣ “ጊዜው ሲደርስ በርግጥ በዚህ ጊዜ በሚቀጥለው ዓመት እመለሳለሁ፤ ሚስትህ ሣራ ወንድ ልጅ ትወልዳለች” አለው።
ሣራም በዚህ ጊዜ ከበስተጀርባው ካለው ከድንኳኑ ደጃፍ ሆና ትሰማ ነበር።
11.በዚያ ጊዜ አብርሃምና ሣራ አርጅተው፣ ዕድሜያቸው ገፍቶ ነበር፤ ሣራም ልጅ የመውለጃዋ ዕድሜ ዐልፎ ነበር። 12.ሣራ በልቧ፣ “ካረጀሁና ጌታዬም ከደከመ በኋላ በዚህ ነገር መደሰት ይሆንልኛል?” ብላ ሣቀች። 13.እግዚአብሔርም አብርሃምን እንዲህ አለው፤ “ሣራ፣ ‘ካረጀሁ በኋላ ልጅ እንዴት አድርጌ እወልዳለሁ’ ስትል ለምን ሣቀች? 14.ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር አለን? ጊዜው ሲደርስ እመለሳለሁ፤ ሣራም ልጅ ይኖራታል።” 15.ሣራ ስለ ፈራች፣ “ኧረ አልሣቅሁም” ብላ ዋሸች።
እርሱ ግን፣ “ሣቅሽ እንጂ” አላት።

አብርሃም ስለ ሰዶም ማለደ

16.ሰዎቹም ለመሄድ ሲነሡ፣ ቍልቍል ወደ ሰዶም ተመለከቱ፤ አብርሃምም ሊሸኛቸው ዐብሯቸው ወጣ። 17.እግዚአብሔርም እንዲህ አለ፤ “እኔ የማደርገውን ነገር ከአብርሃም እሰውራለሁን? 18.አብርሃም በእውነት ታላቅና ብርቱ ሕዝብ ይሆናል፤ አሕዛብ ሁሉ በርሱ ይባረካሉ። 19.ትክክለኛና ጽድቅ የሆነውን በማድረግ የእግዚአብሔርን መንገድ ይጠብቁ ዘንድ ልጆቹንና ከርሱ በኋላ ቤተ ሰቦቹን እንዲያዝዝ መርጬዋለሁ፤ ይኸውም እግዚአብሔር ለአብርሃም የሰጠው ተስፋ ሁሉ እንዲፈጸም ነው።” 20.ደግሞም እግዚአብሔር እንዲህ አለ፤ “በሰዶምና በገሞራ ላይ የሚሰማው ጩኸት እጅግ በዝቷል፤ ኀጢአታቸውም እጅግ ከፍቷል፤ 21.አድራጎታቸው እኔ ዘንድ እንደ ደረሰው ጩኸት መሆኑን ለማየት ወደዚያው እወርዳለሁ፤ እንደዚያ ካልሆነም ዐውቃለሁ።” 22.ሰዎቹም ፊታቸውን ወደ ሰዶም አቅንተው ሄዱ፤ አብርሃም ግን በእግዚአብሔር ፊት እንደ ቆመ ነበር። 23.አብርሃምም ወደ እርሱ ቀረብ ብሎ እንዲህ አለ፤ “በርግጥ ጻድቁን ከኀጢአተኛው ጋራ ዐብረህ ታጠፋለህን? 24.ዐምሳ ጻድቃን በከተማዪቱ ቢገኙ፣ በውኑ ነዋሪዎቹን ሁሉ ታጠፋለህን? በውስጧ ለሚገኙ ዐምሳ ጻድቃን ስትል ከተማዪቱን ይቅር አትልምን? 25.እንዲህስ አይሁን፤ ጻድቁን ከኀጢአተኛው ጋራ እንዴት ትገድለዋለህ? ይህን የመሰለው አድራጎት ከአንተ ይራቅ፤ የምድር ሁሉ ዳኛ በቅን አይፈርድምን?” 26.እግዚአብሔርም፣ “በሰዶም ከተማ ዐምሳ ጻድቃን ባገኝ ለእነርሱ ስል አገሪቱን በሞላ እምራለሁ” አለ። 27.ደግሞም አብርሃም እንዲህ አለ፤ “እኔ ከንቱ፣ ትቢያና ዐመድ ሆኜ ሳለሁ ከጌታ ጋራ ለመናገር አንዴ ደፍሬአለሁ፤ 28.ለመሆኑ ከዐምሳው ጻድቃን ዐምስት ቢጐድሉ በዐምስቱ ሰዎች ምክንያት መላ ከተማዋን ታጠፋለህን?”
እርሱም፣ “አርባ ዐምስት ጻድቃን ባገኝ አላጠፋትም” አለ።
29.አብርሃምም እንደ ገና፣ “ምናልባት አርባ ጻድቃን ቢገኙስ?” አለ።
እርሱም፣ “ለአርባው ስል እምራታለሁ” አለ።
30.ደግሞም አብርሃም፣ “ጌታዬ አይቈጣ፤ እባክህ ልናገር፤ ሠላሳ ጻድቃን ብቻ ቢገኙስ?”
እርሱም፣ “ሠላሳ ባገኝ አላጠፋትም” ብሎ መለሰ።
31.አብርሃምም፣ “ከጌታዬ ጋራ እናገር ዘንድ መቼም አንዴ ደፍሬአለሁና ምናልባት ሃያ ብቻ ቢገኙስ?” አለ።
እርሱም፣ “ሃያ ቢገኙ፣ ለእነርሱ ስል እምራታለሁ” አለ።
32.አብርሃምም፣ “ጌታዬ አይቈጣ፤ አንድ ጊዜ ብቻ ልናገር፤ ምናልባት ዐሥር ብቻ ቢገኙስ?” አለ።
እርሱም “ስለ ዐሥሩ ስል አላጠፋትም” ብሎ መለሰ።
33.እግዚአብሔር ከአብርሃም ጋራ ንግግሩን ከጨረሰ በኋላ ሄደ፤ አብርሃምም ወደ ቤቱ ተመለሰ።

የማርቆስ ወንጌል

ምዕራፍ 6

ነቢይ በአገሩ አይከበርም

6፥1-6 ተጓ ምብ – ማቴ 13፥54-58
1.ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ከዚያ ተነሥቶ ወደ ገዛ አገሩ ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱም ተከተሉት። 2.ሰንበትም በደረሰ ጊዜ፣ በምኵራብ ያስተምር ጀመር፤ የሰሙትም ብዙ ሰዎች ተደነቁ።
እነርሱም እንዲህ አሉ፤ “ይህ ሰው እነዚህን ነገሮች ከየት አገኛቸው? ይህ የተሰጠው ጥበብ ምንድን ነው? ደግሞም እነዚህ ታምራት እንዴት በእጁ ይደረጋሉ?
3.ይህ ዐናጺው አይደለምን? የማርያም ልጅ፣ የያዕቆብ፣ የዮሴፍ፣ የይሁዳና የስምዖን ወንድም አይደለምን? እኅቶቹስ እዚሁ እኛው ዘንድ አይደሉምን?” ከዚህም የተነሣ ተሰናከሉበት። 4.ኢየሱስም፣ “ነቢይ የማይከበረው በገዛ አገሩ፣ በዘመዶቹ መካከልና በራሱ ቤት ብቻ ነው” አላቸው። 5.እዚያም በጥቂት ሕመምተኞች ላይ እጁን ጭኖ ከመፈወሱ በቀር ምንም ታምራት ሊሠራ አልቻለም፤ 6.ባለማመናቸውም ተደነቀ።

ኢየሱስ ዐሥራ ሁለቱን ላከ

6፥7-11 ተጓ ምብ – ማቴ 10፥1፤ 10፥9-14፤ ሉቃ 9፥1፤ 9፥3-5

ከዚያም ኢየሱስ በየመንደሩ እየተዘዋወረ ያስተምር ነበር።

7.ዐሥራ ሁለቱን ወደ ራሱ ጠርቶ፣ ሁለት ሁለቱን ላካቸው፤ በርኩሳን መናፍስትም ላይ ሥልጣን ሰጣቸው። 8.ይህንም ትእዛዝ ሰጣቸው፤ “ለመንገዳችሁ ከበትር በቀር፣ እንጀራ ወይም ከረጢት ወይም ደግሞ ገንዘብ በመቀነታችሁ አትያዙ፤ 9.ጫማ አድርጉ፤ ነገር ግን ትርፍ እጀ ጠባብ አትልበሱ፤ 10.ወደ አንድ ቤት በምትገቡበት ጊዜ ከዚያች ከተማ እስክትወጡ ድረስ እዚያው ቈዩ፤ 11.የትኛውም ቦታ የማይቀበላችሁ ወይም የማይሰማችሁ ከሆነ፣ ከዚያ ስፍራ ስትወጡ ምስክር እንዲሆንባቸው የእግራችሁን ትቢያ በዚያ አራግፋችሁ ውጡ።” 12.እነርሱም ከዚያ ወጥተው፤ ሰዎች ንስሓ እንዲገቡ ሰበኩ፤ 13.ብዙ አጋንንት አስወጡ፤ ብዙ ሕመምተኞችንም ዘይት እየቀቡ ፈወሱ።

የመጥምቁ ዮሐንስ መሰየፍ

6፥14-29 ተጓ ምብ – ማቴ 14፥1-12
6፥14-16 ተጓ ምብ – ሉቃ 9፥7-9
14.የኢየሱስ ስም እየታወቀ በመምጣቱ፣ ንጉሥ ሄሮድስ ይህንኑ ሰማ። አንዳንዶችም፣ “የዚህ ዐይነት ታምር በርሱ የሚሠራው መጥምቁ ዮሐንስ ከሙታን ቢነሣ ነው” ይሉ ነበር። 15.ሌሎቹም፣ “ኤልያስ ነው” አሉ።
አንዳንዶች ደግሞ፣ “ከቀደምት ነቢያት እንደ አንዱ ነቢይ ነው” ይሉ ነበር።
16.ሄሮድስ ነገሩን ሲሰማ ግን፣ “እኔ ራሱን ያስቈረጥሁት ዮሐንስ ከሙታን ተነሥቷል!” አለ። 17.ሄሮድስ ራሱ የወንድሙን የፊልጶስን ሚስት ሄሮድያዳን በማግባቱ ምክንያት፣ ተይዞ እንዲታሰር ትእዛዝ በመስጠት ዮሐንስን ወህኒ ቤት አስገብቶት ነበር። 18.ዮሐንስ ሄሮድስን፣ “የወንድምህን ሚስት ታገባት ዘንድ ሕግ ይከለክልሃል” ይለው ነበርና። 19.ሄሮድያዳም በዚህ ቂም ይዛበት ልታስገድለው ፈለገች፤ ነገር ግን አልሆነላትም። 20.ምክንያቱም ዮሐንስ ጻድቅና ቅዱስ ሰው መሆኑን ሄሮድስ በማወቁ ይፈራውና ይጠብቀው ነበር። ዮሐንስ የሚናገረውን ሲሰማ ሄሮድስ ቢታወክም በደስታ ያደምጠው ነበር። 21.በመጨረሻም አመቺ ቀን መጣ። ሄሮድስ በተወለደበት ዕለት ለከፍተኛ ሹማምቱ፣ ለጦር አዛዦቹና በገሊላ ለታወቁ ታላላቅ ሰዎች ግብዣ አደረገ። 22.የሄሮድያዳም ልጅ ገብታ በዘፈነች ጊዜ ሄሮድስንና ተጋባዦቹን ደስ አሠኘቻቸው።
ንጉሡም ብላቴናዪቱን፣ “የምትፈልጊውን ሁሉ ጠይቂኝ እሰጥሻለሁ” አላት።
23.ደግሞም “እስከ መንግሥቴ እኩሌታ ድረስ እንኳ ቢሆን፣ የምትጠይቂኝን ሁሉ እሰጥሻለሁ” ሲል በመሐላ ቃል ገባላት። 24.እርሷም ወጥታ እናቷን፣ “ምን ልለምነው?” አለቻት።
እናቷም፣ “የመጥምቁ ዮሐንስን ራስ” አለቻት።
25.ብላቴናዪቱም ወዲያው ፈጥና ወደ ንጉሡ በመመለስ፣ “የመጥምቁ ዮሐንስን ራስ አሁን በሳሕን እንድትሰጠኝ እፈልጋለሁ” አለችው። 26.ንጉሡ በነገሩ እጅግ ዐዘነ፤ ይሁን እንጂ ስለ መሐላውና ከርሱ ጋራ ስለ ነበሩ እንግዶች ሲል ቃሉን ለማጠፍ አልፈለገም። 27.ወዲያውኑም ንጉሡ አንዱን ወታደር በፍጥነት ልኮ፣ የዮሐንስን ራስ ቈርጦ እንዲያመጣ አዘዘው፤ እርሱም ሄዶ በወህኒ ቤቱ ውስጥ ራሱን ቈረጠ፤ 28.በሳሕን አምጥቶ ለብላቴናዪቱ ሰጣት፤ ብላቴናዪቱም ለእናቷ ሰጠች። 29.የዮሐንስ ደቀ መዛሙርትም ይህን እንደ ሰሙ መጡ፤ ሬሳውንም ወስደው ቀበሩት።

ኢየሱስ ዐምስት ሺሕ ሰዎች መገበ

6፥32-44 ተጓ ምብ – ማቴ 14፥13-21፤ ሉቃ 9፥10-17፤ ዮሐ 6፥5-13
6፥32-44 ተጓ ምብ – ማር 8፥2-9
30.ሐዋርያትም በኢየሱስ ዙሪያ ተሰብስበው የሠሩትንና ያስተማሩትን ሁሉ ነገሩት። 31.ብዙ ሰዎች ይመጡና ይሄዱ ስለ ነበር ምግብ እንኳ ለመብላት ጊዜ ስላልነበራቸው፣ “እስኪ ብቻችሁን ከእኔ ጋራ ወደ አንድ ገለልተኛ ስፍራ እንሂድና ጥቂት ዕረፉ” አላቸው። 32.ስለዚህ ብቻቸውን ወደ አንድ ገለልተኛ ስፍራ በጀልባ ሄዱ። 33.እነርሱም ሲሄዱ ብዙ ሰዎች አይተው ዐወቋቸው፤ ከከተሞችም ሁሉ በእግር እየሮጡ ቀድመዋቸው ደረሱ። 34.ኢየሱስ ከጀልባዋ በሚወርድበት ጊዜ ብዙ ሕዝብ ተሰብስቦ አየ፤ እረኛ እንደሌላቸው በጎች ስለ ነበሩም ዐዘነላቸው፤ ብዙ ነገርም ያስተምራቸው ጀመር። 35.በዚህ ጊዜ ቀኑ እየመሸ በመሄዱ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው እንዲህ አሉት፤ “ይህ ቦታ ምድረ በዳ ነው፤ ቀኑም መሽቷል፤ 36.በአካባቢው ሰው ወዳለበት መንደር ሄደው የሚበላ ነገር ገዝተው እንዲመገቡ ሕዝቡን አሰናብታቸው።” 37.እርሱ ግን መልሶ፣ “የሚበሉትን እናንተው ስጧቸው” አላቸው።
እነርሱም፣ “ሄደን በሁለት መቶ ዲናር እንጀራ ገዝተን የሚበሉትን እንስጣቸውን?” አሉት።
38.እርሱም፣ “ስንት እንጀራ አላችሁ? እስኪ ሄዳችሁ እዩ” አላቸው።
አይተውም፣ “ዐምስት እንጀራና ሁለት ዓሣ” አሉት።
39.ከዚያም፣ ሕዝቡን በለመለመ ሣር ላይ በቡድን በቡድን እንዲያስቀምጡ አዘዛቸው። 40.ሕዝቡም መቶ መቶና ዐምሳ፣ ዐምሳ ሆነው በቡድን በቡድን ተቀመጡ። 41.እርሱም ዐምስቱን እንጀራና ሁለቱን ዓሣ ይዞ ወደ ሰማይ በማየት ባረከ፤ እንጀራውንም ቈርሶ እንዲያቀርቡላቸው ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፤ ሁለቱንም ዓሣ ለሁሉም አካፈለ። 42.ሁሉም በልተው ጠገቡ፤ 43.ከተበላው እንጀራና ዓሣ፣ ዐሥራ ሁለት መሶብ ሙሉ ፍርፋሪ አነሡ። 44.እንጀራውንም የበሉት ዐምስት ሺሕ ወንዶች ነበሩ።

ኢየሱስ በባሕር ላይ እየተራመደ ሄደ

6፥45-51 ተጓ ምብ – ማቴ 14፥22-32፤ ዮሐ 6፥15-21
6፥53-56 ተጓ ምብ – ማቴ 14፥34-36
45.ወዲያውም እርሱ ሕዝቡን እያሰናበተ ሳለ፣ ደቀ መዛሙርቱ በጀልባ ወደ ቤተ ሳይዳ ቀድመውት እንዲሻገሩ አዘዛቸው፤ 46.ከዚያም ትቷቸው ሊጸልይ ወደ ተራራ ወጣ። 47.በመሸም ጊዜ ጀልባዋ ባሕሩ መካከል ነበረች፤ እርሱም ብቻውን በምድር ላይ ነበር። 48.ነፋስ በርትቶባቸው ስለ ነበር፣ እነርሱ ከመቅዘፊያው ጋራ ሲታገሉ አያቸው፤ በአራተኛውም ክፍለ ሌሊት ገደማ፣ በባሕር ላይ እየሄደ ወደ እነርሱ መጣ፤ በአጠገባቸውም ዐልፎ ሊሄድ ነበር። 49.ነገር ግን በባሕሩ ላይ ሲራመድ ባዩት ጊዜ ምትሀት መስሏቸው ጮኹ፤ 50.ሁሉም እርሱን ባዩት ጊዜ ደንግጠው ነበርና።
እርሱም ወዲያውኑ አነጋገራቸውና፣ “አይዟችሁ እኔ ነኝ፤ አትፍሩ!” አላቸው።
51.እርሱም በጀልባዋ ላይ ወጥቶ ዐብሯቸው ሆነ፤ ነፋሱም ጸጥ አለ፤ እነርሱም እጅግ ተደነቁ። 52.የእንጀራውን ታምር አላስተዋሉም ነበርና፤ ልባቸውም ደንድኖ ነበር። 53.በተሻገሩም ጊዜ፣ ወደ ጌንሴሬጥ ምድር ደረሱ፤ ጀልባዋንም እዚያው አስጠጉ። 54.ወዲያው ከጀልባዋ እንደ ወረዱም፣ ሕዝቡ ኢየሱስን ዐወቁት፤ 55.ወደ አካባቢውም ሁሉ በመሮጥ ሕመምተኞችን በዐልጋ ላይ እየተሸከሙ እርሱ ወደሚገኝበት ስፍራ ሁሉ ያመጡ ነበር። 56.በየደረሰበት መንደር ወይም ከተማ ወይም ገጠር ሁሉ ሕመምተኞችን በየአደባባዩ እያስቀመጡ የልብሱን ጫፍ እንኳ ለመንካት ይለምኑት ነበር፤ የነኩትም ሁሉ ይፈወሱ ነበር።