Skip to Content
የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን | YEHIWOT MELHEK BETEKIRSTIAN
የ2019 ዓ.ም የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ 📖 ዛሬን አንብብ →

የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን

Yehiwot Melhek Betekirstian

ሳምንት 7 · ቀን 35 (አርብ) 📅 Tikimt 20, 2019

ኦሪት ዘሌዋውያን 4, 5, 6, 7 · ወደ ዕብራውያን 3

📖 የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም፦ 1954 መጽሐፍ ቅዱስ አዲሱ መደበኛ ትርጒም

ኦሪት ዘሌዋውያን

ምዕራፍ 4

የኀጢአት መሥዋዕት

1.እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው፤ 2.“ለእስራኤል ሕዝብ እንዲህ በላቸው፤ ‘ማንም ሰው ባለማወቅ ኀጢአት ቢሠራ፣ እግዚአብሔር አታድርጉ ብሎ ካዘዛቸውም አንዱን ተላልፎ ቢገኝ፤ 3.“ ‘የተቀባውም ካህን በሕዝቡ ላይ በደል የሚያስከትል ኀጢአት ቢሠራ፣ ስለ ሠራው ኀጢአት እንከን የሌለበት አንድ ወይፈን ለእግዚአብሔር የኀጢአት መሥዋዕት አድርጎ ያቅርብ። 4.ወይፈኑን በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ በእግዚአብሔር ፊት ያቅርብ፤ እጁንም በወይፈኑ ራስ ላይ ይጫን፤ በእግዚአብሔርም ፊት ይረደው። 5.የተቀባው ካህን ከወይፈኑ ደም ጥቂት ወስዶ ወደ መገናኛው ድንኳን ይግባ፤ 6.ካህኑም ጣቱን በደሙ ውስጥ ነክሮ ከመቅደሱ መጋረጃ ትይዩ፣ በእግዚአብሔር ፊት ሰባት ጊዜ ይርጨው። 7.ካህኑ ከደሙ ጥቂት ወስዶ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በእግዚአብሔር ፊት ያለውንና ሽታው ጣፋጭ የሆነ ዕጣን የሚታጠንበትን መሠዊያ ቀንዶች ይቅባ። የተረፈውን የወይፈኑን ደም ሁሉ በመገናኛው ድንኳን መግቢያ ላይ ባለው በሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያ ግርጌ ያፍስሰው። 8.ለኀጢአት መሥዋዕት ከሚቀርበው ወይፈን ሥቡን ሁሉ ያውጣ፤ ይኸውም፦ የሆድ ዕቃውን የሚሸፍነውን ሥብና ከሆድ ዕቃው ጋራ የተያያዘውን ሥብ፣ 9.ሁለቱንም ኵላሊቶች፣ በኵላሊቶቹ ላይና በጐድኑ አጠገብ ያለውን ሥብ እንዲሁም የጕበቱን መሸፈኛ ከኵላሊቶቹ ጋራ ዐብሮ አውጥቶ ያቅርብ፤ 10.ለኅብረት መሥዋዕት ከሚቀርበው ወይፈን እንዳወጣ ሁሉ ሥቡን ያውጣ፤ ካህኑም የሚቃጠል መሥዋዕት በሚቀርብበት መሠዊያ ላይ ያቃጥለው። 11.ነገር ግን የወይፈኑን ቈዳና ሥጋውን ሁሉ፣ ጭንቅላቱንና እግሮቹን፣ ሆድ ዕቃውንና ፈርሱን፣ 12.የወይፈኑን ብልት ሁሉ ከሰፈር ውጭ ዐመድ ወደሚፈስስበት በአምልኮው ሥርዐት መሠረት ንጹሕ ወደ ሆነው ስፍራ ይውሰደው፤ በተቈለለው ዐመድ ላይ ዕንጨት አንድዶ ያቃጥለው። 13.“ ‘መላው የእስራኤል ሕዝብ ባለማወቅ ኀጢአት ቢሠራ፣ አታድርጉ ብሎ እግዚአብሔር ካዘዘውም አንዱን ተላልፎ ቢገኝ፣ ይህ ሕዝብ ጥፋቱ ባይታወቀውም በደለኛ ነው። 14.የሕዝቡ ጉባኤ ኀጢአት መሥራቱን በተረዳ ጊዜ፣ ለኀጢአት መሥዋዕት የሚሆን አንድ ወይፈን በመገናኛው ድንኳን ፊት ያቅርብ። 15.የሕዝቡም ሽማግሌዎች በእግዚአብሔር ፊት እጆቻቸውን በወይፈኑ ራስ ላይ ይጫኑ፤ ወይፈኑም በእግዚአብሔር ፊት ይታረድ። 16.የተቀባውም ካህን ከወይፈኑ ደም ጥቂት ወስዶ ወደ መገናኛው ድንኳን ይግባ። 17.ካህኑም ጣቱን በደሙ ውስጥ ነክሮ፣ በመጋረጃው ትይዩ በእግዚአብሔር ፊት ሰባት ጊዜ ይርጨው። 18.ከደሙ ጥቂት ወስዶ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በእግዚአብሔር ፊት ያለውን የመሠዊያ ቀንዶች ይቅባ፤ የተረፈውን ደም ሁሉ በመገናኛው ድንኳን መግቢያ ላይ ባለው በሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያ ግርጌ ያፍስሰው። 19.ከወይፈኑም ሥቡን ሁሉ ወስዶ በመሠዊያው ላይ ያቃጥል፤ 20.ለኀጢአት መሥዋዕት ባቀረበው ወይፈን ላይ እንዳደረገው ሁሉ፣ በዚህኛውም ወይፈን ያድርግ፤ በዚህም መሠረት ካህኑ ስለ ሕዝቡ ያስተሰርያል፤ እነርሱም ይቅር ይባላሉ። 21.ወይፈኑንም ከሰፈር ውጭ ያውጣው፤ የመጀመሪያውን ወይፈን እንዳቃጠለው ሁሉ ይህኛውንም ያቃጥል፤ ይህም ስለ ሕዝቡ የሚቀርብ የኀጢአት መሥዋዕት ነው። 22.“ ‘አንድ የሕዝብ መሪ ባለማወቅ ኀጢአት ቢሠራ፣ አምላኩም እግዚአብሔር አታድርጉ ብሎ ከከለከላቸው ትእዛዞች አንዱን ተላልፎ ቢገኝ፣ እርሱ በደለኛ ነው። 23.ኀጢአት መሥራቱን በተረዳ ጊዜ እንከን የሌለበትን ተባዕት ፍየል የግሉ መሥዋዕት አድርጎ ያቅርብ። 24.እጁንም በፍየሉ ራስ ላይ ይጫን፤ የሚቃጠል መሥዋዕት በሚታረድበትም ስፍራ በእግዚአብሔር ፊት ይረደው፤ ይህም የኀጢአት መሥዋዕት ነው። 25.ካህኑም ከመሥዋዕቱ ደም በጣቱ ጥቂት ወስዶ የሚቃጠል መሥዋዕት የሚቀርብበትን መሠዊያ ቀንዶች ይቅባ፤ የተረፈውንም ደም ሁሉ በመሠዊያው ግርጌ ያፍስሰው። 26.የኅብረት መሥዋዕቱን እንዳቃጠለ ሁሉ ሥቡንም በሙሉ በመሠዊያው ላይ ያቃጥል፤ በዚህም መሠረት ካህኑ የሰውየውን ኀጢአት ያስተሰርይለታል፤ ሰውየውም ይቅር ይባላል። 27.“ ‘ከሕዝቡ መካከል አንዱ ሰው ባለማወቅ ኀጢአት ቢሠራ፣ እግዚአብሔር አታድርጉ ብሎ ከከለከላቸው ትእዛዞች አንዱን ተላልፎ ቢገኝ እርሱ በደለኛ ነው። 28.ኀጢአት መሥራቱን በተረዳ ጊዜ፣ እንከን የሌለባትን እንስት ፍየል ስለ ፈጸመው ኀጢአት የግሉ መሥዋዕት አድርጎ ያቅርብ። 29.እጁን ለኀጢአት መሥዋዕት በቀረበችው ፍየል ራስ ላይ ይጫን፤ የሚቃጠል መሥዋዕት በሚታረድበት ስፍራም ይረዳት። 30.ካህኑ በጣቱ ከደሟ ጥቂት ወስዶ የሚቃጠል መሥዋዕት የሚቀርብበትን መሠዊያ ቀንዶች ይቅባ፤ የተረፈውንም ደም ሁሉ በመሠዊያው ግርጌ ያፍስሰው። 31.ሥቡን ከኅብረት መሥዋዕት በወጣበት አኳኋን ሥቡን ሁሉ ያውጣ፤ ካህኑም ሽታው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕት አድርጎ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለው፤ በዚህም መሠረት ካህኑ የሰውየውን ኀጢአት ያስተሰርይለታል፤ ሰውየውም ይቅር ይባላል። 32.“ ‘ስለ ኀጢአት መሥዋዕት የበግ ጠቦት የሚያቀርብ ከሆነ፣ እንከን የሌለባትን እንስት ያቅርብ። 33.እጁን በጠቦቷ ራስ ላይ ይጫን፤ የሚቃጠል መሥዋዕት በሚታረድበት ስፍራም የኀጢአት መሥዋዕት አድርጎ ይረዳት። 34.ካህኑም ከኀጢአት መሥዋዕቱ ደም በጣቱ ጥቂት ወስዶ የሚቃጠል መሥዋዕት የሚቀርብበትን መሠዊያ ቀንዶች ይቅባ፤ የተረፈውንም ደም ሁሉ በመሠዊያ ግርጌ ያፍስሰው። 35.ሥቡ ከኅብረት መሥዋዕት ጠቦት በወጣበት አኳኋን ሥቡን ሁሉ ያውጣ፤ ካህኑም በመሠዊያው ላይ ለእግዚአብሔር በእሳት በሚቀርበው መሥዋዕት ላይ ያቃጥለው። በዚህ መሠረት ሰውየው የሠራውን ኀጢአት ካህኑ ያስተሰርይለታል፤ ሰውየውም ይቅር ይባላል።

ምዕራፍ 5

1.“ ‘አንድ ሰው ስላየውና ስለሚያውቀው ነገር ሕጋዊ ምስክርነቱን እንዲሰጥ ተጠይቆ ቃሉን ለመስጠት ፈቃደኛ ባይሆን፣ ይህ ሰው ኀጢአት ሠርቷልና ይጠየቅበታል። 2.“ ‘ማንኛውም ሰው ሳያውቅ በሥርዐቱ መሠረት የተከለከለውን ርኩስ ነገር ቢነካ፣ ይኸውም፦ የረከሰ የአውሬ በድን ወይም የረከሰ የቤት እንስሳ በድን ወይም በደረቱ እየተሳበ የሚንቀሳቀሰውን የረከሰ ፍጥረት በድን ቢነካ ይህ ሰው ረክሷል፤ በደለኛም ነው። 3.ወይም የሰውን ርኩሰት ይኸውም ርኩስ የሚያደርገውን ማንኛውንም ነገር ሳያውቅ ቢነካ፣ ነገሩን ባወቀ ጊዜ በደለኛ ይሆናል። 4.ሰዎች በሚምሉበት በማናቸውም ነገር፣ በጎ ወይም ክፉ ለማድረግ ሳያስብ በግዴለሽነት ቢምል በኋላ ግን ነገሩን ባወቀ ጊዜ በደለኛ ይሆናል። 5.ማንኛውም ሰው ከእነዚህ በአንዱ በደለኛ ሆኖ ቢገኝ፣ የትኛውን ኀጢአት እንደ ሠራ ገልጾ መናዘዝ አለበት፤ 6.ስለ ኀጢአቱም ቅጣት የኀጢአት መሥዋዕት እንድትሆነው ከመንጋው አንዲት የበግ ወይም የፍየል እንስት ለእግዚአብሔር ያቅርብ፤ ካህኑም ስለ ኀጢአቱ ያስተሰርይለታል። 7.“ ‘ሰውየው ስለ ሠራው ኀጢአት በግ ለማቅረብ ዐቅሙ ካልፈቀደ ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የዋኖስ ጫጩቶች የመጀመሪያውን ለኀጢአት መሥዋዕት፣ ሁለተኛውን ለሚቃጠል መሥዋዕት ለእግዚአብሔር ያቅርብ። 8.ወደ ካህኑም ያምጣቸው፤ እርሱም ለኀጢአት መሥዋዕት የምትሆነውን አስቀድሞ ያቅርብ፤ ራሷን ዐንገቷ ላይ ይቈልምም፤ ነገር ግን ቈርጦ አይጣል፤ 9.ከኀጢአት መሥዋዕቱም ጥቂት ደም ወስዶ በመሠዊያው ዙሪያ ላይ ይርጨው፤ የተረፈውም ደም ሁሉ በመሠዊያው ግርጌ ይፍሰስ፤ ይህም የኀጢአት መሥዋዕት ነው። 10.ካህኑም ቀደም ሲል በታዘዘው መሠረት ሁለተኛዋን የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ ያቅርብ፤ ካህኑም የሰውየውን ኀጢአት ያስተሰርይለታል፤ ሰውየውም ይቅር ይባላል። 11.“ ‘ሰውየው ሁለት ርግቦች ወይም ሁለት የዋኖስ ጫጩቶች ለማቅረብ ዐቅሙ ካልፈቀደ፣ ስለ ሠራው ኀጢአት የኢፍ መስፈሪያ አንድ ዐሥረኛ የላመ ዱቄት ለኀጢአት መሥዋዕት ያቅርብ፤ ነገር ግን የኀጢአት መሥዋዕት ስለ ሆነ ዘይት አያፍስስበት፤ ዕጣንም አይጨምርበት፤ 12.ከዚያም ለካህኑ ያቅርብ፤ ካህኑም ለመታሰቢያ እንዲሆን ዕፍኝ ሙሉ ይዝገንለት፤ በእሳት ከሚቀርበውም ቍርባን በላይ አድርጎ ለእግዚአብሔር በመሠዊያው ላይ በእሳት ያቃጥለው፤ ይህም የኀጢአት መሥዋዕት ነው። 13.ሰውየው ከእነዚህ በአንዱ ኀጢአት ቢሠራ፣ ካህኑ በዚህ ሁኔታ ያስተሰርይለታል፤ ሰውየውም ይቅር ይባላል። ከመሥዋዕቱ የተረፈውም እንደ እህል ቍርባን ሁሉ ለካህኑ ይሆናል።’ ”

የበደል መሥዋዕት

14.እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 15.“ማንኛውም ሰው ለእግዚአብሔር ባይታመን፤ ከተቀደሰ ከማናቸውም ነገር በማጕደል ኀጢአት ቢሠራ፣ ከመንጋው እንከን የሌለበትን አውራ በግ የበደል መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር ያቅርብ። የዋጋውም ግምት በቤተ መቅደሱ ሰቅል መሠረት ተመዝኖ በጥሬ ብር ይሁን፤ ይህም የበደል መሥዋዕት ነው። 16.ከተቀደሱ ነገሮች ያጐደለውንም ይተካ፤ የዚህንም ተመን አንድ ዐምስተኛ በላዩ ጨምሮ ለካህኑ ይስጥ፤ ካህኑም ከበጉ ጋራ የበደል መሥዋዕት አድርጎ በማቅረብ ያስተሰርይለታል፤ ሰውየውም ይቅር ይባላል። 17.“ማንኛውም ሰው ኀጢአት ቢሠራ፣ እግዚአብሔር አታድርጉ ብሎ ከከለከላቸው ትእዛዞች ሳያውቅ አንዱን ተላልፎ ቢገኝ በደለኛ ነው፤ በኀጢአቱም ይጠየቅበታል። 18.እርሱም ከመንጋው ለበደል መሥዋዕት የሚሆን እንከን የሌለበት አውራ በግ ወደ ካህኑ ያምጣ፤ ዋጋውም ተመጣጣኝ ይሁን። ካህኑም በዚህ ሁኔታ ሰውየው ሳያውቅ ስለ ፈጸመው ስሕተት ያስተሰርይለታል፤ ሰውየውም ይቅር ይባላል። 19.ይህ የበደል መሥዋዕት ነው። ሰውየውም በእግዚአብሔር ፊት ጥፋት በመፈጸሙ በደለኛ ነው።”

ምዕራፍ 6

1.እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 2.“ማንኛውም ሰው በዐደራ የተሰጠውን ወይም በመያዣነት የተቀበለውን በማጕደልና ባልንጀራውን በማጭበርበር ባይታመን፣ እግዚአብሔርንም ቢበድል ወይም ባልንጀራውን ቢቀማው ወይም ቢያታልለው፣ 3.ወይም የጠፋ ነገር አግኝቶ አላየሁም ቢል ወይም በሐሰት ቢምል ወይም ሰዎች የሚያደርጉትን እንዲህ ያለውን ማንኛውንም ኀጢአት ቢሠራ፣ 4.በዚህ ሁኔታ ኀጢአት ቢሠራና በደለኛ ቢሆን፣ የሰረቀውን ወይም የቀማውን ወይም በዐደራ የተሰጠውን ወይም ጠፍቶ ያገኘውን ይመልሳል፤ 5.በሐሰት የማለበትንም ሁሉ ይመልስ፤ የበደል መሥዋዕቱን በሚያቀርብበት ጊዜ የወሰደውን በሙሉ የዋናውን አንድ ዐምስተኛ በመጨመር ለባለንብረቱ ንብረቱ ይመልስ። 6.ከመንጋውም እንከን የሌለበትን ዋጋው ተመጣጣኝ የሆነ አውራ በግ ስለ በደሉ መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር ለማቅረብ ወደ ካህኑ ያምጣ፤ 7.በዚህም ሁኔታ ካህኑ በእግዚአብሔር ፊት ያስተሰርይለታል፤ ሰውየውም ስለ ፈጸመው ስለ ማንኛውም በደል ይቅር ይባላል።”

የሚቃጠል መሥዋዕት

8.እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 9.“አሮንና ልጆቹን እንዲህ ብለህ እዘዛቸው፤ ‘ስለሚቃጠለው መሥዋዕት አቀራረብ የምትከተለው ሥርዐት ይህ ነው፤ የሚቃጠለው መሥዋዕት ሌሊቱን ሁሉ እስኪነጋ ድረስ በመሠዊያው ላይ ባለው ማንደጃ ላይ ይቀመጥ፤ እሳቱም በመሠዊያው ላይ ዘወትር ሲነድድ ይደር። 10.ካህኑም ከበፍታ የተሠራ የውስጥ ሱሪውን ካጠለቀ በኋላ፣ የበፍታ ቀሚሱን ይልበስ፤ እሳቱ በመሠዊያው ላይ መሥዋዕቱን ከበላው በኋላ የሚቀረውን ዐመድ አንሥቶ፣ በመሠዊያው አጠገብ ያፍስስ። 11.ከዚያም ልብሱን አውልቆ ሌላ ልብስ ይቀይር፤ ዐመዱንም ተሸክሞ ከሰፈር ውጭ በአምልኮው ሥርዐት መሠረት ንጹሕ ወደ ሆነ ስፍራ ይውሰድ። 12.በመሠዊያው ላይ ያለው እሳት ዘወትር ይንደድ፤ ምን ጊዜም አይጥፋ። ካህኑ ጧት ጧት እሳቱ ላይ ማገዶ ይጨምር፤ በእሳቱ ላይ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ያዘጋጅ፤ በዚህም ላይ የኅብረት መሥዋዕቱን ሥብ ያቃጥል። 13.በመሠዊያው ላይ ያለው እሳት ዘወትር ይንደድ፤ ምን ጊዜም አይጥፋ።

ምዕራፍ 7

የበደል መሥዋዕት

1.“ ‘እጅግ ቅዱስ የሆነው የበደል መሥዋዕት የአቀራረብ ሥርዐት ይህ ነው፦ 2.የሚቃጠል መሥዋዕት በሚታረድበት ስፍራ የበደሉም መሥዋዕት እዚያው ይታረድ፤ ደሙም በመሠዊያው ላይ ዙሪያውን ይረጭ። 3.ሥቡን በሙሉ ያቅርብ፤ ይኸውም፦ ላቱን፣ የሆድ ዕቃውን የሚሸፍነውን ሥብ፣ 4.ሁለቱን ኵላሊቶች፣ በኵላሊቶቹ ላይና በጐድኑ አጠገብ ያለውን ሥብ እንዲሁም የጉበቱን መሸፈኛ ከኵላሊቶቹ ጋራ አንድ ላይ አውጥቶ ያቅርብ። 5.ካህኑም ለእግዚአብሔር በእሳት የሚቀርብ አድርጎ በመሠዊያው ላይ ያቃጥል፤ ይህም የበደል መሥዋዕት ነው። 6.ከካህን ወገን የሆነ ወንድ ሁሉ ከዚህ መብላት ይችላል፤ ነገር ግን በተቀደሰ ስፍራ ይበላ፤ ይህም እጅግ ቅዱስ ነው። 7.“ ‘የኀጢአት መሥዋዕትና የበደል መሥዋዕት አቀራረብ ሥርዐት አንድ ነው፤ መሥዋዕቶቹ የስርየቱን ሥርዐት ለሚያስፈጽመው ካህን ይሰጣሉ። 8.ስለ ማንኛውም ሰው የሚቃጠል መሥዋዕት የሚያቀርበው ካህን ቈዳውን ለራሱ ይውሰድ። 9.በማብሰያ ምድጃ የተጋገረ፣ በመቀቀያ ወይም በምጣድ የበሰለ ማንኛውም የእህል ቍርባን ለሚያቀርበው ካህን ይሰጥ። 10.ማንኛውም በዘይት የተለወሰ ወይም ደረቅ የእህል ቍርባን ለአሮን ልጆች ሁሉ እኩል ይሰጥ።

የኅብረት መሥዋዕት

11.“ ‘አንድ ሰው ለእግዚአብሔር የኅብረት መሥዋዕት በሚያቀርብበት ጊዜ፣ ሊከተለው የሚገባው ሥርዐት ይህ ነው፤ 12.“ ‘መሥዋዕቱን የሚያቀርበው ለምስጋና መግለጫ ከሆነ፣ ከምስጋና መሥዋዕቱ ጋራ ያለ እርሾ የተጋገረና በዘይት የተለወሰ ኅብስት እርሾ ሳይገባበት፣ በሥሡ ተጋግሮ፣ ዘይት የተቀባ ቂጣ በሚገባ ታሽቶ፣ በዘይት የተለወሰም የላመ ዱቄት ኅብስት ዐብሮ ያቅርብ። 13.ለምስጋና ከሚሆነው የኅብረት መሥዋዕት ጋራ፣ በእርሾ የተጋገረ ኅብስት ያቅርብ። 14.ከእያንዳንዱም ዐይነት አንዳንድ አንሥቶ ለእግዚአብሔር የተለየ ቍርባን በማድረግ ያቅርብ፤ ይህም የኅብረት መሥዋዕቱን ደም ለሚረጨው ካህን ይሰጥ። 15.ለምስጋና የሚሆነው የኅብረት መሥዋዕት ሥጋ፣ በቀረበበት ዕለት ይበላ እንጂ አንዳች አይደር። 16.“ ‘መሥዋዕቱ ስእለት በመፈጸሙ ወይም የበጎ ፈቃድ ስጦታ ከሆነ፣ በቀረበበት ዕለት ይበላ፤ የተረፈውም ሁሉ በማግስቱም ይበላ። 17.እስከ ሦስት ቀን የቈየ ማንኛውም የመሥዋዕቱ ሥጋ ይቃጠል። 18.ማንኛውም የኅብረት መሥዋዕት ሥጋ በሦስተኛው ቀን ከተበላ ተቀባይነት የለውም፤ ርኩስ በመሆኑ ላቀረበው ሰው ዋጋ አይኖረውም፤ ከዚያም የበላ ሰው የበደል ዕዳ ይሆንበታል። 19.“ ‘ርኩስ ከሆነ ነገር ጋራ የተነካካ ሥጋ ይቃጠል እንጂ አይበላ። ሌላውን ሥጋ ግን በሥርዐቱ መሠረት ንጹሕ የሆነ ማንኛውም ሰው ይብላ፤ 20.ነገር ግን ንጹሕ ያልሆነ ማንኛውም ሰው ለእግዚአብሔር የቀረበውን የትኛውንም የኅብረት መሥዋዕት ሥጋ ቢበላ፣ ከሕዝቡ ፈጽሞ ይወገድ። 21.ማንኛውም ሰው የሰውን ርኩሰት ወይም ርኩስ እንስሳን ወይም ማንኛውንም ርኩስ ነገር ቢነካና ለእግዚአብሔር ከቀረበው የኅብረት መሥዋዕት ሥጋ ቢበላ፣ ያ ሰው ፈጽሞ ከሕዝቡ ይወገድ።’ ”

ሥብና ደም መብላት መከልከሉ

22.እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 23.“ለእስራኤላውያን እንዲህ በላቸው፤ ‘የበሬ ወይም የላም፣ የበግ ወይም የፍየል ሥብ አትብሉ። 24.ሞቶ የተገኘ ወይም አውሬ የገደለው ከብት ሥብ ለሌላ ተግባር ይዋል እንጂ አይበላ። 25.ለእግዚአብሔር በእሳት ከሚቀርብ እንስሳ ሥብ የሚበላ ማንኛውም ሰው ከሕዝቡ ይወገድ። 26.በየትኛውም ቦታ ብትኖሩ የማንኛውንም የወፍ ዘር ወይም የእንስሳ ደም አትብሉ። 27.ማንኛውም ሰው ደም ቢበላ፣ ያ ሰው ከሕዝቡ ይወገድ።’ ”

የካህኑ ድርሻ

28.እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 29.“ለእስራኤላውያን እንዲህ በላቸው፤ ‘የኅብረት መሥዋዕት ለእግዚአብሔር የሚያቀርብ ማንኛውም ሰው ስለ ራሱ መሥዋዕት አድርጎ ከዚሁ ላይ ለእግዚአብሔር ያቅርብ። 30.በእሳት ለእግዚአብሔር የሚቀርበውን መሥዋዕት በራሱ እጅ ያቅርበው፤ ሥቡን ከፍርምባው ጋራ ያቅርብ፤ ፍርምባውን መሥዋዕት አድርጎ በእግዚአብሔር ፊት ይወዝውዘው። 31.ካህኑ ሥቡን በመሠዊያው ላይ ያቃጥል፤ ፍርምባው ግን ለአሮንና ለልጆቹ ይሰጥ። 32.የኅብረት መሥዋዕታችሁን የቀኝ ወርች ለካህኑ የተለየ አድርጋችሁ ስጡት። 33.የኅብረት መሥዋዕቱን ደምና ሥብ የሚያቀርበው የአሮን ልጅ ቀኝ ወርቹን የራሱ ድርሻ አድርጎ ይውሰድ። 34.ከእስራኤላውያን የኅብረት መሥዋዕት ላይ የተወዘወዘውን ፍርምባና የቀረበውን ወርች ወስጃለሁ፤ ለካህኑ ለአሮንና ለልጆቹም ከእስራኤላውያን የሚያገኙት መደበኛ ድርሻቸው እንዲሆን ሰጥቻቸዋለሁ።’ ” 35.ካህናት ሆነው እግዚአብሔርን እንዲያገለግሉ በቀረቡ ቀን፣ በእሳት ለእግዚአብሔር ከቀረበው መሥዋዕት ላይ ለአሮንና ለልጆቹ የተመደበላቸው ድርሻ ይህ ነው። 36.ካህናቱ በተቀቡበት ቀን፣ እስራኤላውያን መደበኛ ድርሻ አድርገው ከትውልድ እስከ ትውልድ ይህን እንዲሰጧቸው እግዚአብሔር አዘዘ። 37.እንግዲህ የሚቃጠል መሥዋዕት፣ የእህል ቍርባን፣ የኀጢአት መሥዋዕት፣ የበደል መሥዋዕት፣ የክህነት ሹመት መሥዋዕትና የኅብረት መሥዋዕት ሥርዐት ይህ ነው፤ 38.ይህም፣ በሲና ምድረ በዳ እስራኤላውያን መሥዋዕታቸውን ለእግዚአብሔር እንዲያቀርቡ ባዘዛቸው ቀን በሲና ተራራ ላይ ለሙሴ የሰጠው ሥርዐት ነው።

የእህል ቍርባን

14 “ ‘የእህል ቍርባን ሥርዐት ይህ ነው፦ የአሮን ልጆች ቍርባኑን በመሠዊያው ትይዩ በእግዚአብሔር ፊት ያቅርቡት።

15 ካህኑ ከላመው ዱቄትና ከዘይቱ አንድ ዕፍኝ ያንሣለት፤ በእህሉ ቍርባን ላይ ያለውንም ዕጣን በሙሉ ይውሰድ፤ ይህንም፣ ሽታው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕት አድርጎ፣ ለመታሰቢያ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለው።

16 የተረፈውንም አሮንና ልጆቹ ይብሉት፤ ቂጣውን በተቀደሰው ስፍራ፣ በመገናኛው ድንኳን ቅጥር ግቢ ውስጥ አደባባዩ ላይ ይብሉት።

17 ያለ እርሾ መጋገር አለበት፤ በእሳት ከሚቀርብልኝ ቍርባን ይህን የእነርሱ ድርሻ አድርጌ ሰጥቻቸዋለሁ። ይህም፣ እንደ ኀጢአት መሥዋዕትና እንደ በደል መሥዋዕት ሁሉ እጅግ የተቀደሰ ነው።

18 ማንኛውም ከአሮን ዘር የተወለደ ወንድ ሊበላው ይችላል፤ ለእግዚአብሔር ከሚቀርበው የእሳት ቍርባን ለርሱ የተመደበ የዘላለም ድርሻው ነው፤ የሚነካውም ሁሉ ቅዱስ ይሆናል።’ ”

19 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ አለው፤

20 “አሮን ወይም ልጆቹ በተቀቡበት ዕለት ለእግዚአብሔር የሚያቀርቡት ቍርባን ይህ ነው፦ የኢፍ አንድ ዐሥረኛው የላመ ዱቄት ግማሹን ለጧት፣ ግማሹን ለማታ የዘወትር የእህል ቍርባን አድርገው ያቅርቡት።

21 በሚገባ በዘይት ተለውሶ በምጣድ ላይ ይጋገር፤ ከዚያም የእህሉን ቍርባን ቈራርሰህ ሽታው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ይሆን ዘንድ አቅርብ።

22 በርሱ ቦታ ተቀብቶ ካህን የሚሆነው ልጁ ይህን ያዘጋጅ፤ ለእግዚአብሔር የተመደበ ድርሻ ነውና ፈጽሞ ይቃጠል።

23 ካህኑ የሚያቀርበው የእህል ቍርባን ሁሉ ፈጽሞ ይቃጠል እንጂ አይበላ።”

የኀጢአት መሥዋዕት

24 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤

25 “አሮንንና ልጆቹን እንዲህ በላቸው፤ ‘ስለ ኀጢአት መሥዋዕት አቀራረብ የምትከተለው ሥርዐት ይህ ነው፤ የሚቃጠል መሥዋዕት በሚታረድበት ስፍራ የኀጢአቱም መሥዋዕት እዚያው በእግዚአብሔር ፊት ይታረድ፤ ይህም እጅግ ቅዱስ ነው።

26 መሥዋዕቱንም የሚያቀርበው ካህን ይብላው፤ ይህም በተቀደሰው ስፍራ በመገናኛው ድንኳን ቅጥር ግቢ ውስጥ፣ በአደባባዩ ላይ ይበላ።

27 ሥጋውን የሚነካ ሁሉ የተቀደሰ ይሆናል፤ ደሙ በልብስ ላይ ቢረጭ፣ ያን ልብስ በተቀደሰ ስፍራ ዕጠብ።

28 ሥጋው የተቀቀለበት የሸክላ ዕቃ ይሰበር፤ የናስ ዕቃ ከሆነ ግን ተፈግፍጎ በውሃ ይታጠብ።

29 ከካህናት ወገን የሆነ ወንድ ሁሉ ከዚህ መብላት ይችላል፤ ይህም እጅግ ቅዱስ ነው።

30 ነገር ግን ደሙ ማስተስረያ እንዲሆን ወደ መገናኛው ድንኳን ወደ ቅድስት የቀረበው የኀጢአት መሥዋዕት ሁሉ በእሳት ይቃጠል እንጂ አይበላ።

ወደ ዕብራውያን

ምዕራፍ 3

ኢየሱስ ከሙሴ በላይ ነው

1.እንግዲህ የሰማያዊው ጥሪ ተካፋዮች የሆናችሁ ቅዱሳን ወንድሞች ሆይ፤ የእምነታችን ሐዋርያና ሊቀ ካህናት የሆነውን ኢየሱስን አስቡ። 2.ሙሴ በእግዚአብሔር ቤት ሁሉ ላይ ታማኝ እንደ ነበር፣ እርሱም ለሾመው ታማኝ ነበር። 3.ቤትን የሚሠራ ከቤቱ ይልቅ የሚበልጥ ክብር እንዳለው፣ ኢየሱስም ከሙሴ የሚበልጥ ክብር የተገባው ሆኖ ተገኝቷል። 4.እያንዳንዱ ቤት የራሱ ሠሪ አለው፤ ነገር ግን ሁሉን የሠራ እግዚአብሔር ነው። 5.“ሙሴ ወደ ፊት ስለሚነገረው ነገር እየመሰከረ፣ በእግዚአብሔር ቤት ሁሉ ላይ እንደ አንድ ታማኝ አገልጋይ ነበር።” 6.ክርስቶስ ግን በእግዚአብሔር ቤት ላይ እንደ ታማኝ ልጅ ነው። እኛም የምንተማመንበትንና የምንመካበትን ተስፋ አጥብቀን ብንይዝ ቤቱ ነን።

ስለ አለማመን የተሰጠ ማስጠንቀቂያ

7.ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ እንደሚል፣
“ዛሬ ድምፁን ብትሰሙ፣
8.በምድረ በዳ በፈተና ቀን፣
በዐመፅ እንዳደረጋችሁት፣
ልባችሁን አታደንድኑ።
9.አባቶቻችሁ በዚያ ተፈታተኑኝ፤
መረመሩኝ፤ ያደረግሁትንም ሁሉ ለአርባ ዓመት አዩ።
10.በዚያም ትውልድ ላይ የተቈጣሁት ለዚህ ነበር፤
እንዲህም አልሁ፤ ‘በልባቸው ዘወትር ይስታሉ፤
መንገዴንም አላወቁም።’
11.ስለዚህ በቍጣዬ እንዲህ ብዬ ማልሁ፤
‘ወደ ዕረፍቴ ከቶ አይገቡም።’ ”
12.ወንድሞች ሆይ፤ ከእናንተ ማንም ከሕያው እግዚአብሔር የሚያስኰበልል፣ ኀጢአተኛና የማያምን ልብ እንዳይኖረው ተጠንቀቁ። 13.ነገር ግን ከመካከላችሁ ማንም በኀጢአት ተታልሎ ልቡ እንዳይደነድን፣ “ዛሬ” እየተባለ ሳለ በየቀኑ እርስ በርሳችሁ ተጽናኑ። 14.በመጀመሪያ የነበረንን እምነት እስከ መጨረሻው አጽንተን ብንይዝ ከክርስቶስ ጋራ ተካፋዮች እንሆናለን። 15.ይኸውም፣
“ዛሬ ድምፁን ብትሰሙ፣
በዐመፅ እንዳደረጋችሁት፣
አሁንም ልባችሁን አታደንድኑ”
እንደ ተባለው ነው።
16.ሰምተው ያመፁት እነማን ነበሩ? ሙሴ ከግብጽ መርቶ ያወጣቸው ሁሉ አይደሉምን? 17.አርባ ዓመት የተቈጣውስ እነማንን ነበር? ኀጢአት ሠርተው ሬሳቸው በምድረ በዳ ወድቆ የቀረውን አይደለምን? 18.ያልታዘዙትን ካልሆነ በቀር ወደ ዕረፍቱ እንዳይገቡ የማለባቸው እነማን ነበሩ? 19.እንግዲህ ሊገቡ ያልቻሉት ካለማመናቸው የተነሣ እንደ ሆነ እንረዳለን።