Skip to Content
የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን | YEHIWOT MELHEK BETEKIRSTIAN
የ2019 ዓ.ም የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ 📖 ዛሬን አንብብ →

የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን

Yehiwot Melhek Betekirstian

ሳምንት 7 · ቀን 32 (ማክሰኞ) 📅 Tikimt 17, 2019

ኦሪት ዘጸአት 35, 36, 37 · መዝሙረ ዳዊት 26 · ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 4

📖 የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም፦ 1954 መጽሐፍ ቅዱስ አዲሱ መደበኛ ትርጒም

ኦሪት ዘጸአት

ምዕራፍ 35

1.ሙሴም የእስራኤልን ልጆች ማኅበር ሁሉ ሰብስቦ እንዲህ አላቸው። ታደርጉ ዘንድ እግዚአብሔር ያዘዘው ቃል ይህ ነው፤ 2.ስድስት ቀን ሥራ ይደረጋል፥ ሰባተኛው ቀን ግን ለእግዚአብሔር የዕረፍት ሰንበት የተቀደሰ ቀን ይሆንላችኋል፤ የሚሠራበትም ሁሉ ይገደል። 3.በማደሪያዎቻችሁ ውስጥ በሰንበት ቀን እሳትን አታንድዱ። 4.ሙሴም ለእስራኤል ልጆች ማህበር ሁሉ አላቸው። እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ያዘዘው ነገር ይህ ነው፤ 5.ከእናንተ ዘንድ ለእግዚአብሔር ቍርባንን አቅርቡ፤ የልብ ፈቃድ ያለው የእግዚአብሔርን ቍርባን ያምጣ፤ ወርቅና ብርም ናስም፤ 6.ሰማያዊም ሐምራዊም ቀይ ግምጃም፥ ጥሩ በፍታም፥ የፍየል ጠጕርም፤ 7.ቀይም የአውራ በግ ቁርበት፥ የአቆስጣም ቁርበት፥ የግራርም እንጨት፤ 8.ለመብራትም ዘይት፥ ለቅብዓት ዘይትና ለጣፋጭ ዕጣን ቅመም፤ 9.መረግድ ለኤፉዱና ለደረት ኪስ የሚደረግ ፈርጥ ያምጣ። 10.በእናንተም ዘንድ ያሉ በልባቸው ጥበበኞች ሁሉ መጥተው እግዚአብሔር ያዘዘውን ሁሉ ያድርጉ። 11.ማደሪያውን፥ ድንኳኑንም መደረቢያውንም፥ መያዣዎቹንም፥ ሳንቆቹንም፥ መወርወሪያዎቹንም፥ ምሰሶቹንም፥ እግሮቹንም፤ 12.ታቦቱን መሎጊያዎቹንም፥ የስርየት መክደኛውንም በእርሱም ፊት የሚሸፍነውን መጋረጃ፤ 13.ገበታውን መሎጊያዎቹንም ዕቃውንም ሁሉ፥ የገጹንም ኅብስት፤ 14.መብራት የሚያበሩበትን መቅረዙን ዕቃውንም፥ ቀንዲሉንም፥ የመብራቱንም ዘይት፤ 15.የዕጣኑን መሠዊያም መሎጊያዎቹንም፥ የቅብዓቱንም ዘይት፥ ጣፋጩንም ዕጣን፥ ለማደሪያውም ደጃፍ የሚሆን የደጃፉን መጋረጃ፤ 16.ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነውን መሠዊያውን፥ የናሱንም መከታ፥ መሎጊያዎቹንም፥ ዕቃውንም ሁሉ፤ የመታጠቢያውን ሰንም መቀመጫውንም፤ 17.የአደባባዩን መጋረጆች ምሰሶቹንም እግሮቻቸውንም፥ የአደባባዩንም ደጃፍ መጋረጃ፤ 18.የማደሪያውን ካስማዎች፥ የአደባባዩንም ካስማዎች አውታሮቻቸውንም፤ 19.በመቅደስ ውስጥ ለማገልገል በብልሃት የተሠሩትን ልብሶች፥ በክህነት ያገለግሉበት ዘንድ የተቀደሱትን የካህኑን የአሮን ልብሶች፥ የልጆቹንም ልብሶች። 20.የእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ ከሙሴ ፊት ወጡ። 21.ከእነርሱም ሰው ሁሉ ልቡ እንዳነሣሣው መንፈሱም እሺ እንዳሰኘው ለመገናኛው ድንኳን ሥራ ለማገልገያውም ሁሉ ለተቀደሰውም ልብስ ለእግዚአብሔር ስጦታ አመጡ። 22.ወንዶችና ሴቶችም ልባቸው እንደ ፈቀደ ማርዳዎችን፥ ሎቲዎችንም፥ ቀለበቶችንም፥ ድሪዎችንም፥ የወርቅ ጌጦችንም ሁሉ አመጡ፤ ሰዎችም ሁሉ የወርቅ ስጦታ ወደ እግዚአብሔር አቀረቡ። 23.ሰማያዊም ሐምራዊም ቀይ ግምጃም፥ ጥሩ በፍታም፥ የፍየል ጠጕርም፥ ቀይ የአውራ በግ ቁርበትም፥ የአቆስጣ ቁርበትም ያላቸው ሰዎች ሁሉ አመጡ። 24.ስእለት የተሳለ ሁሉ የብርንም የናስንም ስጦታ ለእግዚአብሔር ቍርባን አቀረበ፤ የግራርም እንጨት ያለው ሁሉ ለማገልገያ ሥራ አመጣ። 25.በልባቸው ጥበበኞች የሆኑ ሴቶችም በእጃቸው ፈተሉ፥ የፈተሉትንም ሰማያዊውን ሐምራዊውንም ቀዩንም ግምጃ፥ ጥሩውንም በፍታ አመጡ። 26.ልባቸውም በጥበብ ያስነሣቸው ሴቶች ሁሉ የፍየልን ጠጕር ፈተሉ። 27.አለቆችም መረግድን፥ ለኤፉድና ለደረት ኪስ የሚገቡትንም ፈርጦችን፥ 28.ለመብራትም ለቅብዓት ዘይትም ለጣፋጭ ዕጣንም ሽቱንና ዘይትን አመጡ። 29.ከእስራኤል ልጆችም ያመጡ ዘንድ ልባቸው ያስነሣቸው ወንዶችና ሴቶች ሁሉ ሙሴ ይሠራ ዘንድ እግዚአብሔር ላዘዘው ሥራ ሁሉ ለእግዚአብሔር ስጦታ በፈቃዳቸው አመጡ። 30.ሙሴም የእስራኤልን ልጆች አላቸው። እዩ፥ እግዚአብሔር ከይሁዳ ነገድ የሆነውን የሆር የልጅ ልጅ፥ የኡሪ ልጅ ባስልኤልን በስሙ ጠራው። 31.በሥራ ሁሉ ብልሃት በጥበብም በማስተዋልም በእውቀትም የእግዚአብሔርን መንፈስ ሞላበት፤ 32.የጥበብን ሥራ ያስተውል ዘንድ፥ በወርቅና በብር በናስም ይሠራ ዘንድ፥ 33.በፈርጥ የሚሆነውን የዕንቍ ድንጋይ ይቀርጽ ዘንድ፥ እንጨቱንም ይጠርብ ዘንድ፥ የብልሃት ሥራውንም ሁሉ ይሠራ ዘንድ። 34.እርሱና የዳን ነገድ የሆነው የአሂሳሚክ ልጅ ኤልያብ ያስተምሩ ዘንድ በልባቸው አሳደረባቸው። 35.በአንጥረኛ፥ በብልህ ሠራተኛም፥ በሰማያዊና በሐምራዊ በቀይም ግምጃ በጥሩ በፍታም በሚሠራ ጠላፊ፥ በሸማኔም ሥራ የሚሠራውን፥ ማናቸውንም ሥራና በብልሃት የሚሠራውን ሁሉ ያደርጉ ዘንድ በእነርሱ ልብ ጥበብን ሞላ።

ምዕራፍ 36

1.ለመቅደስም ማገልገያ ሥራ ሁሉ ያደርጉ ዘንድ እንዲያውቁ እግዚአብሔር ጥበብንና ማስተዋልን የሰጣቸው ባስልኤልና ኤልያብ በልባቸው ጥበበኞችም ሁሉ እግዚአብሔር እንዳዘዘው ነገር ሁሉ አደረጉ። 2.ሙሴም ባስልኤልንና ኤልያብን፥ እግዚአብሔርም በልቡ ጥበብን ያደረገለትን በልብ ጥበበኛ ሰው ሁሉ፥ ሥራውንም ለመሥራት ይቀርብ ዘንድ ልቡ ያስነሣውን ሁሉ ጠራቸው። 3.እነርሱም የእስራኤል ልጆች ለመቅደስ ማገልገያ ሥራ ያመጡትን ስጦታ ሁሉ ይሠሩ ዘንድ ከሙሴ ተቀበሉ። እነዚያም እንደ ፈቃዳቸው ማለዳ ማለዳ ስጦታውን ገና ወደ እርሱ ያመጡ ነበር። 4.የመቅደሱንም ሥራ የሚሠሩ ጠቢባን ሁሉ የሚያደርጉትን ሥራ ትተው መጡ፥ 5.እነርሱም ሙሴን። እግዚአብሔር ለማገልገያ ሥራ ይደረግ ዘንድ ላዘዘው ከሚበቃ ይልቅ እጅግ የሚበልጥ ሕዝቡ አመጡ ብለው ተናገሩት። 6. 7.ያመጡትም ነገር ሥራን ሁሉ ለመፈጸም በቅቶ ገና ይተርፍ ስለ ነበረ ሙሴ አዘዘና። ወንድ ወይም ሴት ለመቅደስ ስጦታ ከዚህ የበለጠ የሚያመጣ አይኑር ብሎ በሰፈሩ ውስጥ አሳወጀ። ሕዝቡም እንዳያመጡ ተከለከሉ። ፕ 8.በእነርሱም ዘንድ ያሉት ሥራ ሲሠሩ የነበሩት በልባቸው ጥበበኞች ሁሉ ማደሪያውን ከአሥር መጋረጆች ሠሩ፤ እነርሱንም ከተፈተለ ከጥሩ በፍታ፥ ከሰማያዊም ከሐምራዊም ከቀይም ግምጃ ሠሩ፤ በእነርሱም ላይ ብልህ ሠራተኛ እንደሚሠራ ኪሩቤልን አደረጉባቸው። 9.የእያንዳንዱ መጋረጃ ርዝመት ሀያ ስምንት ክንድ፥ ወርዱም አራት ክንድ ነበረ፤ የመጋረጆቹ ሁሉ ልክ ትክክል ነበረ። 10.አምስቱንም መጋረጆች እርስ በርሳቸው አጋጠሙ፤ አምስቱንም መጋረጆች እንዲሁ እርስ በርሳቸው አጋጠሙ። 11.ከሚጋጠሙትም መጋረጆች በአንደኛው መጋረጃ ዘርፍ ላይ የሰማያዊውን ግምጃ ቀለበቶች አደረጉ፤ ደግሞ ከተጋጠሙት ከሌሎቹ በአንደኛው መጋረጃ ዘርፍ ላይ እንዲሁ አደረጉ። 12.አምሳ ቀለበቶችንችን በአንድ መጋረጃ አደረጉ፤ አምሳውንም ቀለበቶች በሁለተኛው መጋረጃ ዘርፍ አደረጉ፤ ቀለበቶቹ እርስ በርሳቸው ፊት ለፊት የሚተያዩ ነበሩ። 13.አምሳም የወርቅ መያዣዎች ሠሩ፤ መጋረጆችንም እርስ በርሳቸው በመያዣዎች አጋጠሙአቸው፤ አንድ ማደሪያም ሆነ። 14.ከማደሪያውም በላይ ለድንኳን የሚሆኑ መጋረጆችን ከፍየል ጠጕር አደረጉ፤ አሥራ አንድ መጋረጆች አደረጉ። 15.እያንዳንዱም መጋረጃ ርዝመቱ ሠላሳ ክንድ፥ እያንዳንዱም መጋረጃ ወርዱ አራት ክንድ ነበረ፤ የአሥራ አንዱም መጋረጆች መጠናቸው ትክክል ነበረ። 16.አምስቱንም መጋረጆች እርስ በርሳቸው አንድ አድርገው፥ ስድስቱንም መጋረጆች አንድ አድርገው አጋጠሙአቸው። 17.ከተጋጠሙትም መጋረጆች በአንደኛው መጋረጃ ዘርፍ ላይ አምሳ ቀለበቶች አደረጉ፤ ደግሞ ከተጋጠሙት ከሌሎቹ በአንደኛው መጋረጃ ዘርፍ ላይ አምሳ ቀለበቶች አደረጉ። 18.ድንኳኑም አንድ እንዲሆን ያጋጥሙት ዘንድ አምሳ የናስ መያዣዎችን ሠሩ። 19.ለድንኳኑም መደረቢያ ከቀይ ከአውራ በግ ቁርበት፥ ከዚያም በላይ ሌላ መደረቢያ ከአቆስጣ ቁርበት አደረጉ። 20.ለማደሪያውም ከግራር እንጨት የሚቆሙትን ሳንቆች አደረጉ። 21.የሳንቃው ሁሉ ርዝመቱ አሥር ክንድ፥ ወርዱም አንድ ክንድ ተኩል ነበረ። 22.ለእያንዳንዱም ሳንቃ አንዱን በአንዱ ላይ የሚያያይዙ ሁለት ማጋጠሚያዎች ነበሩ፤ ለማደሪያው ሳንቆች ሁሉ እንዲሁ አደረጉ። 23.ለማደሪያውም በደቡብ ወገን ሀያ ሳንቆችን አደረጉ፤ 24.ከሀያውም ሳንቆች በታች አርባ የብር እግሮች አደረጉ፤ ከእያንዳንዱም ሳንቃ በታች ለሁለቱ ማጋጠሚያዎች ሁለት እግሮች ነበሩ። 25.ለማደሪያው ለሁለተኛው ወገን በሰሜን በኩል ሀያ ሳንቆች አደረጉ፤ 26.ለእነርሱም አርባ የብር እግሮች፥ ከእያንዳንዱም ሳንቃ በታች ሁለት እግሮች አደረጉ። 27.ለማደሪያውም በምዕራቡ ወገበስተ ኋላ ስድስት ሳንቆች አደረጉ። 28.ለማደሪያውም ለሁለቱ ማዕዘን በስተ ኋላ ሁለት ሳንቆች አደረጉ። 29.ከታችም እስከ ላይ እስከ አንደኛው ቀለበት ድረስ አንድ ሳንቃ ድርብ ነበረ፤ ለሁለቱም ማዕዘን እንዲሁ ሁለት ነበሩ። 30.ስምንት ሳንቆችና አሥራ ስድስቱ የብር እግሮቻቸው፥ ከእያንዳንዱም ሳንቃ በታች ሁለት ሁለት እግሮች ነበሩ። 31.ከግራርም እንጨት በማደሪያው በአንደኛው ወገን ላሉት ሳንቆች አምስት መወርወሪያዎች፥ 32.በማደሪያውም በሁለተኛው ወገን ላሉት ሳንቆች አምስት መወርወሪያዎች፥ ከማደሪያውም በስተ ኋላ በምዕራቡ ወገን ላሉት ሳንቆች አምስት መወርወሪያዎች አደረጉ። 33.መካከለኛውንም መወርወሪያ በሳንቆቹ መካከል ከዳር እስከ ዳር አሳለፉ። 34.ሳንቆቹንም በወርቅ ለበጡአቸው፤ ቀለበቶቻቸውንም የመወርወሪያ ቤት እንዲሆኑላቸው ከወርቅ አደረጉ፤ መወርወሪያዎቹንም በወርቅ ለበጡአቸው። 35.መጋረጃውንም ከሰማያዊና ከሐምራዊ ከቀይም ግምጃ፥ ከተፈተለም ከጥሩ በፍታ አደረጉ፤ ብልህ ሠራተኛ እንደሚሠራ ኪሩቤልን በእርሱ ላይ አደረጉ። 36.ከግራርም እንጨት አራት ምሰሶች አደረጉለት፥ በወርቅም ለበጡአቸው፤ ኩላቦቻቸው የወርቅ ነበሩ፤ ለእነርሱም አራት የብር እግሮች አደረጉ። 37.ለድንኳኑም ደጃፍ ከሰማያዊና ከሐምራዊ ከቀይም ግምጃ፥ ከተፈተለም ከጥሩ በፍታ በጥልፍ አሠራር የተሠራ መጋረጃ አደረጉ፤ 38.አምስቱንም ምሰሶች፥ ኩላቦቻቸውንም አደረጉ፤ ጕልላቶቻቸውንና ዘንጎቻቸውንም በወርቅ ለበጡአቸው፤ አምስቱም እግሮቻቸው የናስ ነበሩ።

ምዕራፍ 37

1.ባስልኤልም ከግራር እንጨት ታቦቱን ሠራ፤ ርዝመቱም ሁለት ክንድ ተኩል፥ ወርዱም አንድ ክንድ ተኩል፥ ቁመቱም አንድ ክንድ ተኩል ነበረ። 2.በውስጥም በውጭም በጥሩ ወርቅ ለበጠው፤ በዙሪያውም የወርቅ አክሊል አደረገለት። 3.አራት የወርቅ ቀለበቶችም አደረገለት፤ እነርሱንም በአራቱ እግሮቹ ላይ አኖረ። በአንድ ወገን ሁለት ቀለበቶች፥ በሌላውም ወገን ሁለት ቀለበቶች ሆኑ። 4.መሎጊያዎቹንም ከግራር እንጨት ሠራ፥ በወርቅም ለበጣቸው። 5.ታቦቱንም ለመሸከም በታቦቱ አጠገብ ባሉት ቀለበቶች መሎጊያዎቹን አገባ። 6.ከጥሩ ወርቅም ርዝመቱ ሁለት ክንድ ተኩል፥ ወርዱም አንድ ክንድ ተኩል የሆነ የስርየት መክደኛ ሠራ። 7.ሁለት ኪሩቤልንም ከተቀጠቀጠ ወርቅ ሠራ፤ በስርየት መክደኛውም ላይ በሁለት ወገን አደረጋቸው። 8.ከስርየት መክደኛውም ጋር አንዱን ኪሩብ በአንድ ወገን፥ ሁለተኛውንም ኪሩብ በሌላው ወገን አድርጎ በአንድ ላይ ሠራቸው። 9.ኪሩቤልም ክንፎቻቸውን ወደ ላይ የዘረጉ ሆኑ፥ የስርየት መክደኛውንም በክንፎቻቸው ሸፈኑ፥ እርስ በርሳቸውም ተያዩ፤ የኪሩቤልም ፊቶቻቸው ወደ መክደኛው ተመለከቱ። 10.ርዝመቱ ሁለት ክንድ፥ ወርዱም አንድ ክንድ፥ ቁመቱም አንድ ክንድ ተኩል የሆነውን ገበታ ከግራር እንጨት ሠራ። 11.በጥሩም ወርቅ ለበጠው፥ በዙሪያውም የወርቅ አክሊል አደረገለት። 12.በዙሪያውም አንድ ጋት የሚያህል ክፈፍ አደረገለት፤ የወርቅም አክሊል በክፈፉ ዙሪያ አደረገለት። 13.አራትም የወርቅ ቀለበቶች አደረገለት፤ ቀለበቶቹንም አራቱ እግሮቹ ባሉበት በአራቱ ማዕዘኖች አደረገ። 14.ገበታውንም ለመሸከም መሎጊያዎቹ እንዲሰኩባቸው ቀለበቶች በክፈፉ አቅራቢያ ነበሩ። 15.ገበታውንም ይሸከሙባቸው ዘንድ መሎጊያዎቹን ከግራር እንጨት ሠርቶ በወርቅ ለበጣቸው። 16.ለማፍሰሻም ይሆኑ ዘንድ በገበታው ላይ የሚኖሩትን ዕቃዎች፥ ወጭቶቹንና ጭልፋዎቹን ጽዋዎቹንም መቅጃዎቹንም፥ ከጥሩ ወርቅ አደረጋቸው። 17.መቅረዙንም ከጥሩ ወርቅ አደረገ፤ መቅረዙንም ከእግሩና ከአገዳው ጋር በተቀረጸ ሥራ አደረገ፤ ጽዋዎቹን፥ ጕብጕቦቹን፥ አበቦቹን ከዚያው በአንድነት አደረገ። 18.በስተ ጎኑም ስድስት ቅርንጫፎች ወጡለት፤ ሦስቱ የመቅረዙ ቅርንጫፎች በአንድ ወገን፥ ሦስቱም የመቅረዙ ቅርንጫፎች በሌላ ወገን ወጡ። 19.በአንደኛው ቅርንጫፍ ጕብጕቡንና አበባውን ሦስትም የለውዝ አበባ የሚመስሉትን ጽዋዎች፥ በሁለተኛውም ቅርንጫፍ ጕብጕቡንና አበባውን ሦስትም የለውዝ አበባ የሚመስሉትን ጽዋዎች፥ እንዲሁም ከመቅረዙ ለወጡ ለስድስቱ ቅርንጫፎች አደረገ። 20.በመቅረዙም ጕብጕቦቹንና አበቦቹን አራትም የለውዝ አበባ የሚመስሉትን ጽዋዎች አደረገ። 21.ከመቅረዙ ለወጡ ለስድስት ቅርንጫፎች ከሁለት ቅርንጫፎች በታች አንድ ሆኖ የተሠራ አንድ ጕብጕብ፥ ከሁለትም ቅርንጫፎች በታች አንድ ሆኖ የተሠራ አንድ ጕብጕብ፥ ደግሞ ከሁለት ቅርንጫፎች በታች አንድ ሆኖ የተሠራ አንድ ጕብጕብ ነበረ። 22.ጕብጕቦቹና ቅርንጫፎቹ ከእርሱ ጋር አንድ ነበሩ፤ ሁሉም አንድ ሆኖ ከተቀረጸ ከጥሩ ወርቅ ተሠርቶ ነበር። 23.ሰባቱንም መብራቶች መኰስተሪያዎቹንም፥ የኩስታሪ ማድረጊያዎቹንም ከጥሩ ወርቅ ሠራ። 24.መቅረዙንም ዕቃውንም ሁሉ ከአንድ መክሊት ጥሩ ወርቅ አደረገ። 25.የዕጣን መሠዊያ ከግራር እንጨት ሠራ፤ ርዝመቱ አንድ ክንድ፥ ስፋቱ አንድ ክንድ፥ አራት ማዕዘን ነበረ፤ ከፍታውም ሁለት ክንድ ነበረ፤ ቀንዶቹም ከእርሱ ጋር በአንድነት የተሠሩ ነበሩ። 26.ላይኛውንና የግድግዳውንም ዙሪያ ቀንዶቹንም በጥሩ ወርቅ ለበጠው፤ በዙሪያውም የወርቅ ክፈፍ አደረገበት። 27.ከክፈፉም በታች ሁለት የወርቅ ቀለበቶች አደረገበት፥ በዚህና በዚያ በሁለቱም ጎን አደረጋቸው፤ ለመሸከምም የመሎጊያዎች ስፍራ ነበሩ። 28.መሎጊያዎቹንም ከግራር እንጨት አደረገ፥ በወርቅም ለበጣቸው። 29.የተቀደሰውንም የቅብዓቱን ዘይት፥ ጥሩውንም የጣፋጭ ሽቱ ዕጣን በቀማሚ ብልሃት እንደ ተሠራ አደረገ።

ምዕራፍ 26

1.የዳዊት መዝሙር።
አቤቱ፥ እኔ በየውሃቴ ሄጃለሁና ፍረድልኝ፤ በእግዚአብሔርም አምኛለሁና አልናወጥም።
2.አቤቱ፥ ፍተነኝ መርምረኝም፤ ኵላሊቴንና ልቤን ፍተን። 3.ምሕረትህ በዓይኔ ፊት ነውና፥ በእውነትህም ተመላለስሁ። 4.በከንቱ ሸንጎ አልተቀመጥሁም፥ ከዓመፀኞችም ጋር አልገባሁም። 5.የክፉዎችን ማኅበር ጠላሁ፥ ከዝንጉዎችም ጋር አልቀመጥም። 6.እጆቼን በንጽሕና አጥባለሁ፤ አቤቱ፥ መሠዊያህን እዞራለሁ፥ 7.የምስጋናን ድምፅ እሰማ ዘንድ፥ ተአምራትህንም ሁሉ እነግር ዘንድ። 8.አቤቱ፥ የቤትህን ስፍራ የክብርህንም ማደሪያ ቦታ ወደድሁ። 9.ከኃጢአተኞች ጋር ነፍሴን፥ ከደም ሰዎችም ጋር ሕይወቴን አታጥፋ። 10.በእጃቸው ተንኰል አለባቸው፥ ቀኛቸውም መማለጃ ተሞልታለች። 11.እኔ ግን በየውሃቴ ሄጃለሁ፤ አድነኝ ማረኝም። 12.እግሮቼ በቅንነት ቆመዋልና፤ አቤቱ፥ በማኅበር አመሰግንሃለሁ።

ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች

ምዕራፍ 4

1.ስለዚህ፥ የምወዳችሁና የምናፍቃችሁ፥ ደስታዬና አክሊሌ የምትሆኑ ወንድሞቼ ሆይ፥ እንዲሁ በጌታ ቁሙ፥ ወዳጆች ሆይ። 2.በአንድ አሳብ በጌታ እንዲስማሙ ኤዎድያንን እመክራለሁ ሲንጤኪንንም እመክራለሁ። 3.አንተም ደግሞ በሥራዬ አብረህ የተጠመድህ እውነተኛ ሆይ፥ እንድታግዛቸው እለምንሃለሁ፤ ስሞቻቸው በሕይወት መጽሐፍ ከተጻፉት ከቀሌምንጦስና ደግሞ ከእኔ ጋር አብረው ከሠሩት ከሌሎቹ ጋር በወንጌል ከእኔ ጋር አብረው ተጋድለዋልና። 4.ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ፤ ደግሜ እላለሁ፥ ደስ ይበላችሁ። 5.ገርነታችሁ ለሰው ሁሉ ይታወቅ። 6.ጌታ ቅርብ ነው። በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ። 7.አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል። 8.በቀረውስ፥ ወንድሞች ሆይ፥ እውነተኛ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ጭምትነት ያለበትን ነገር ሁሉ፥ ጽድቅ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ንጹሕ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ ፍቅር ያለበትን ነገር ሁሉ፥ መልካም ወሬ ያለበትን ነገር ሁሉ፥ በጎነት ቢሆን ምስጋናም ቢሆን፥ እነዚህን አስቡ፤ 9.ከእኔ የተማራችሁትንና የተቀበላችሁትን የሰማችሁትንም ያያችሁትንም እነዚህን አድርጉ፤ የሰላምም አምላክ ከእናንተ ጋር ይሆናል። 10.ነገር ግን አሁን ከጊዜ በኋላ ስለ እኔ እንደ ገና ልታስቡ ስለ ጀመራችሁ፥ በጌታ እጅግ ደስ ይለኛል፤ ጊዜ አጣችሁ እንጂ፥ ማሰብስ ታስቡ ነበር። 11.ይህን ስል ስለ ጉድለት አልልም፤ የምኖርበት ኑሮ ይበቃኛል ማለትን ተምሬአለሁና። 12.መዋረድንም አውቃለሁ መብዛትንም አውቃለሁ፤ በእያንዳንዱ ነገር በነገርም ሁሉ መጥገብንና መራብንም መብዛትንና መጉደልን ተምሬአለሁ። 13.ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ። 14.ሆኖም በመከራዬ ከእኔ ጋር ስለ ተካፈላችሁ መልካም አደረጋችሁ። 15.የፊልጵስዩስ ሰዎች ሆይ፥ ወንጌል በመጀመሪያ ሲሰበክ፥ ከመቄዶንያ በወጣሁ ጊዜ፥ ከእናንተ ብቻ በቀር ሌላ ቤተ ክርስቲያን በመስጠትና በመቀበል ስሌት ከእኔ ጋር እንዳልተካፈለች እናንተ ደግሞ ታውቃላችሁ፤ 16.በተሰሎንቄ እንኳ ሳለሁ፥ አንድ ጊዜና ሁለት ጊዜ ያስፈለገኝን ሰዳችሁልኝ ነበርና። 17.በስሌታችሁ የሚበዛውን ፍሬ እንጂ ስጦታውን ፈላጊ አይደለሁም። 18.ነገር ግን ሁሉ አለኝ ይበዛልኝማል፤ የመዓዛ ሽታና የተወደደ መሥዋዕት የሚሆነውን ለእግዚአብሔርም ደስ የሚያሰኘውን ስጦታችሁን ከአፍሮዲጡ ተቀብዬ ተሞልቼአለሁ። 19.አምላኬም እንደ ባለ ጠግነቱ መጠን በክብር በክርስቶስ ኢየሱስ የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ ይሞላባችኋል። 20.ለአምላካችንና ለአባታችንም እስከ ዘላለም ድረስ ክብር ይሁን፤ አሜን። 21.ለቅዱሳን ሁሉ በክርስቶስ ኢየሱስ ሰላምታ አቅርቡ። ከእኔ ጋር ያሉቱ ወንድሞች ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። 22.ቅዱሳን ሁሉ ይልቁንም ከቄሣር ቤት የሆኑቱ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። 23.የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከመንፈሳችሁ ጋር ይሁን፤ አሜን።
♫
Listen to the reading 5 chapter tracks
ኦሪት ዘጸአት Chapter 35
ኦሪት ዘጸአት Chapter 36
ኦሪት ዘጸአት Chapter 37
መዝሙረ ዳዊት Chapter 26
ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች Chapter 4
Swipe to browse chapters
Listen 5