Skip to Content
የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን | YEHIWOT MELHEK BETEKIRSTIAN
የ2019 ዓ.ም የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ 📖 ዛሬን አንብብ →

የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን

Yehiwot Melhek Betekirstian

ሳምንት 7 · ቀን 35 (አርብ) 📅 Tikimt 20, 2019

ኦሪት ዘሌዋውያን 4, 5, 6, 7 · ወደ ዕብራውያን 3

📖 የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም፦ 1954 መጽሐፍ ቅዱስ አዲሱ መደበኛ ትርጒም

ኦሪት ዘሌዋውያን

ምዕራፍ 4

1.እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው። 2.ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው። ማናቸውም ሰው ሳያውቅ ኃጢአት ቢሠራ፥ እግዚአብሔርም። አትሥሩ ካላቸው ትእዛዛት አንዲቱን ቢተላለፍ፥ 3.የተቀባውም ካህን በሕዝቡ ላይ በደል እንዲቈጠርባቸው ኃጢአት ቢሠራ፥ ስለ ሠራው ስለ ኃጢአቱ ነውር የሌለበት ወይፈን ለእግዚአብሔር ለኃጢአት መሥዋዕት ያቀርበዋል። 4.ወይፈኑንም ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ በእግዚአብሔር ፊት ያመጣዋል፤ እጁንም በወይፈኑ ራስ ላይ ይጭነዋል፥ ወይፈኑንም በእግዚአብሔር ፊት ያርደዋል። 5.የተቀባውም ካህን ከወይፈኑ ደም ወስዶ ወደ መገናኛው ድንኳን ያመጣዋል፤ 6.ካህኑም ጣቱን በደሙ ውስጥ ነክሮ በእግዚአብሔር ፊት በመቅደሱ መጋረጃ ፊት ደሙን ሰባት ጊዜ ይረጨዋል። 7.ካህኑም በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በእግዚአብሔር ፊት ያለው ጣፋጭ ዕጣን በሚታጠንበት መሠዊያ ቀንዶች ላይ ከደሙ ያደርጋል፤ የተረፈውንም የወይፈኑን ደም ሁሉ በመገናኛው ድንኳን ደጅ ባለው ለሚቃጠል መሥዋዕት በሚሆነው መሠዊያ በታች ያፈስሰዋል። 8.ለኃጢአትም መሥዋዕት ከሚታረደው ወይፈን ስብን ሁሉ ይወስዳል፤ ሆድ ዕቃውን የሚሸፍነውን ስብ፥ በሆድ ዕቃውም ላይ ያለውን ስብ ሁሉ፥ 9.ሁለቱንም ኵላሊቶች፥ በእነርሱም ላይና በጎድኑ አጠገብ ያለውን ስብ፥ በጕበቱም ላይ ያለውን መረብ ከኵላሊቶች ጋር፥ 10.ለደኅንነት መሥዋዕት ከታረደው ወይፈን እንደ ተወሰደው ይወስዳል። ካህኑም ለሚቃጠል መሥዋዕት በሚሆነው መሠዊያ ላይ ያቃጥለዋል። 11.የወይፈኑን ቁርበት፥ ሥጋውንም ሁሉ፥ ራሱንም፥ እግሮቹንም፥ ሆድ ዕቃውንም፥ 12.ፈርሱንም፥ ወይፈኑን ሁሉ ከሰፈሩ ወደ ውጭ አመድ ወደሚፈስስበት ወደ ንጹሕ ስፍራ ይወስደዋል፥ በእንጨትም ላይ በእሳት ያቃጥለዋል፤ አመድ በሚፈስስበት ስፍራ ይቃጠላል። 13.የእስራኤል ማኅበር ሁሉ ቢስቱ፥ ነገሩም ከጉባኤው ፊት ቢሸሸግ፥ እግዚአብሔርም። አትሥሩ ካላቸው ትእዛዛት አንዲቱን ቢተላለፉ፥ 14.እንዲህም ቢበድሉ፥ የሠሩት ኃጢአት ሲታወቅ ጉባኤው ስለ ኃጢአት መሥዋዕት ወይፈንን ያቀርባሉ፤ ወደ መገናኛውም ድንኳን ፊት ያመጡታል። 15.የጉባኤውም ሽማግሌዎች እጆቻቸውን በወይፈኑ ራስ ላይ በእግዚአብሔር ፊት ይጭናሉ፤ ወይፈኑም በእግዚአብሔር ፊት ይታረዳል። 16.የተቀባውም ካህን ከወይፈኑ ደም ወደ መገናኛው ድንኳን ያመጣል፤ 17.ካህኑም ጣቱን በደሙ ውስጥ ነክሮ በእግዚአብሔር ፊት በመጋረጃው ፊት ለፊት ሰባት ጊዜ ይረጨዋል። 18.በመገናኛውም ድንኳን ውስጥ በእግዚአብሔር ፊት ባለው በዕጣን መሠዊያው ቀንዶች ላይ ከደሙ ያደርጋል፤ ደሙንም ሁሉ በመገናኛው ድንኳን ደጅ ባለው ለሚቃጠል መሥዋዕት በሚሆነው መሠዊያ በታች ያፈስሰዋል። 19.ስቡንም ሁሉ ከእርሱ ወስዶ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል። 20.እንዲህም በወይፈኑ ያደርጋል፤ ስለ ኃጢአት መሥዋዕት በታረደው ወይፈን እንዳደረገ እንዲሁ በዚህ ያደርጋል፤ ካህኑም ስለ እነርሱ ያስተሰርያል፥ እነርሱም ይቅር ይባላሉ። 21.ወይፈኑንም ከሰፈሩ ወደ ውጭ ይወስደዋል፥ የፊተኛውንም ወይፈን እንዳቃጠለ ያቃጥለዋል፤ ይህ የማኅበሩ የኃጢአት መሥዋዕት ነው። 22.አንድ መኰንንም ኃጢአትን ሲሠሩ፥ ሳያውቅም እግዚአብሔር አምላኩ። አትሥራ ያለውን ትእዛዝ ሲተላለፍ፥ እንዲህም ሲበድል፥ 23.የሠራው ኃጢአት ቢታወቅ፥ ነውር የሌለበትን ተባት ፍየል ለቍርባኑ ያቀርበዋል፤ 24.በፍየሉም ራስ ላይ እጁን ይጭናል፤ የሚቃጠልም መሥዋዕት በሚታረድበት ስፍራ በእግዚአብሔር ፊት ያርደዋል፤ እርሱ የኃጢአት መሥዋዕት ነው። 25.ካህኑም ከኃጢአት መሥዋዕት ደም በጣቱ ወስዶ ለሚቃጠል መሥዋዕት በሚሆነው መሠዊያ ቀንዶች ያደርገዋል፤ የተረፈውንም ደም ለሚቃጠል መሥዋዕት ከሚሆነው መሠዊያ በታች ያፈስሰዋል። 26.ስቡንም ሁሉ እንደ ደኅንነት መሥዋዕት ስብ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል። ካህኑም ኃጢአቱን ያስተሰርይለታል፥ እርሱም ይቅር ይባላል። 27.ከአገሩ ሕዝብም አንድ ሰው ኃጢአትን ሳያውቅ ቢሠራ፥ እግዚአብሔርም። አትሥራ ያለውን ትእዛዝ ቢተላለፍ፥ ቢበድልም፥ 28.ለእርሱም የሠራው ኃጢአት ቢታወቀው፥ ስለ ሠራው ኃጢአት ነውር የሌለባትን እንስት ፍየል ለቍርባኑ ያመጣል። 29.እጁንም በኃጢአት መሥዋዕት ራስ ላይ ይጭናል፤ የሚቃጠልም መሥዋዕት በሚታረድበት ስፍራ የኃጢአትን መስዋዕት ያርዳል። 30.ካህኑም ከደምዋ በጣቱ ወስዶ ለሚቃጠል መሥዋዕት በሚሆነው መሠዊያ ቀንዶች ላይ ያደርገዋል፥ ደሙንም ሁሉ ከመሠዊያው በታች ያፈስሰዋል። 31.ስቡም ሁሉ ከደኅንነት መሥዋዕት ላይ እንደሚወሰድ፥ ስብዋን ሁሉ ይወስዳል፤ ካህኑም ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል፤ ካህኑም ስለ እርሱ ያስተሰርያል፥ እርሱም ይቅር ይባላል። 32.ስለ ኃጢአትም መሥዋዕት የበግ ጠቦት ቢያቀርብ፥ ነውር የሌለባትን እንስት ያመጣል። 33.እጁንም በኃጢአት መሥዋዕት ራስ ላይ ይጭናል፥ የሚቃጠልም መሥዋዕት በሚታረድበት ስፍራ ለኃጢአት መሥዋዕት ያርዳታል። 34.ካህኑም ከኃጢአት መሥዋዕት ደም በጣቱ ወስዶ ለሚቃጠል መሥዋዕት በሚሆነው መሠዊያ ቀንዶች ላይ ያደርገዋል፥ ደሙንም ሁሉ ከመሠዊያው በታች ያፈስሰዋል። 35.ስቡ ሁሉ ለደኅንነት መሥዋዕት ከታረደው ጠቦት ላይ እንደሚወሰድ ስብዋን ይወስዳል፤ ካህኑም ለእግዚአብሔር በእሳት በተቃጠለው ቍርባን ላይ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል። ካህኑም ስለ ሠራው ኃጢአት ያስተሰርይለታል፥ እርሱም ይቅር ይባላል።

ምዕራፍ 5

1.ማንም ሰው የሚያምለውን ቃል ቢሰማ፥ ምስክር ሆኖም አንድ ነገር አይቶ እንደ ሆነ ወይም አውቆ እንደ ሆነ ባይናገር፥ ኃጢአት መሥራቱ ነውና በደሉን ይሸከማል። 2.ማናቸውም ሰው ሳይታወቀው ርኩስ ነገር ቢነካ፥ የረከሰም አውሬ በድን፥ ወይም የረከሰ ከብት በድን፥ ወይም የረከሰ የተንቀሳቀሰ እንስሳ በድን ቢሆን፥ እርሱም ርኩስ ቢሆን ነገሩ በታወቀው ጊዜ በደል ይሆንበታል፤ 3.ወይም ርኩስነቱን ሳይውቅ ርኩስን ሰው ቢነካ፥ በማናቸውም ርኵሰት ቢረክስ፥ ነገሩ በታወቀው ጊዜ በደል ይሆንበታል። 4.ማናቸውም ሰው ሳያውቅ ክፉን ወይም መልካምን ያደርግ ዘንድ ሳያስብ በከንፈሩ ተናግሮ ቢምል፤ ሳያስብ የማለው ስለ ማናቸውም ነገር ቢሆን፤ በታወቀው ጊዜ ከዚህ ነገር በአንዱ በደለኛ ይሆናል። 5.ከእነዚህ ነገሮች በአንዲቱ በደለኛ ሲሆን፥ የሠራውን ኃጢአት ይናዘዛል። 6.ስለ ሠራው ኃጢአት ለእግዚአብሔር የበደል መሥዋዕት ያመጣል፤ እርሱም ከመንጋው የበግ ወይም የፍየል እንስት ለኃጢአት መሥዋዕት ይሆናል፤ ካህኑም ስለ ኃጢአቱ ያስተሰርይለታል። 7.ስለ ሠራው ኃጢአት ለበደል መሥዋዕት ጠቦትን ለማምጣት ገንዘቡ ያልበቃ እንደ ሆነ፥ ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የርግብ ግልገሎች፥ አንዱን ለኃጢአት መሥዋዕት ሁለተኛውንም ለሚቃጠል መሥዋዕት፥ ለእግዚአብሔር ያቀርባል። 8.ወደ ካህኑም ያመጣቸዋል፤ እርሱም አስቀድሞ ለኃጢአት መሥዋዕት የሆነውን ያቀርባል፥ ራሱንም ከአንገቱ ይቈለምመዋል፥ ነገር ግን አይቈርጠውም። 9.ከኃጢአቱም መሥዋዕት ደም በመሠዊያው ግድግዳ ላይ ይረጨዋል፤ የተረፈውም ደም ከመሠዊያው በታች ይንጠፈጠፋል፤ እርሱ የኃጢአት መሥዋዕት ነው። 10.እንደ ሥርዓቱም ሁለተኛውን ለሚቃጠል መሥዋዕት ያዘጋጀዋል። ካህኑም ስለ ሠራው ኃጢአት ያስተሰርይለታል፥ እርሱም ይቅር ይባላል። 11.ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የርግብ ግልገሎች ለማምጣት ገንዘቡ ያልበቃ እንደ ሆነ፥ ስለ ሠራው ኃጢአት የኢፍ መስፈሪያ አሥረኛ ክፍል መልካም ዱቄት ለኃጢአት መሥዋዕት ያቀርበዋል፤ የኃጢአት መሥዋዕት ነውና ዘይት አያፈስስበትም፥ ዕጣንም አይጨምርበትም። 12.ወደ ካህኑም ያመጣዋል፥ ካህኑም መታሰቢያው ይሆን ዘንድ ከእርሱ እፍኝ ሙሉ ይውሰድ፥ ለእግዚአብሔርም በእሳት በተቃጠለው ቍርባን ላይ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል፤ እርሱም የኃጢአት መሥዋዕት ነው። 13.ካህኑም ከእነዚያ በአንዳቸው ስለ ሠራው ኃጢአት ያስተሰርይለታል፥ እርሱም ይቅር ይባላል። የተረፈውም እንደ እህል ቍርባን ለካህኑ ይሆናል። 14.እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው። 15.ማናቸውም ሰው ቢበድል፥ ሳያውቅም ለእግዚአብሔር በተቀደሰው በማናቸውም ነገር ኃጢአትን ቢሠራ፥ ለበደል መሥዋዕት ለእግዚአብሔር ከመንጋ ነውር የሌለበትን አውራ በግ ያቀርባል፤ እንደ ግምጋሜህ መጠን በብር ሰቅል እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን ለበደል መሥዋዕት ያቀርበዋል። 16.በተቀደሰ ነገር ላይ ስለ ሠራው ኃጢአት ዕዳ ይከፍላል፥ አምስተኛውንም እጅ ይጨምርበታል፥ ለካህኑም ይሰጠዋል። ካህኑም በበደል መሥዋዕት አውራ በግ ያስተሰርይለታል፥ እርሱም ይቅር ይባላል። 17.ማናቸውም ሰው ኃጢአት ቢሠራ፥ እግዚአብሔርም። አትሥሩ ካላቸው ትእዛዛት አንዲቱን ቢተላለፍ፥ ባያውቅም፥ ያ ሰው በደለኛ ነው፥ ኃጢአቱንም ይሸከማል። 18.ነውር የሌለበትን አውራ በግ ከመንጋው ለበደል መሥዋዕት እንደ ግምጋሜህ መጠን ወደ ካህኑ ያመጣዋል፤ ካህኑም ሳያውቅ ስለ ሳተው ስሕተት ያስተሰርይለታል፥ እርሱም ይቅር ይባላል። 19.እርሱም የበደል መሥዋዕት ነው፤ በእውነት በእግዚአብሔር ፊት በደለኛ ነው።

ምዕራፍ 6

1.እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው። 2.ማናቸውም ሰው ኃጢአትን ቢሠራ፥ እግዚአብሔርንም ቢበድል፥ ያኖረበትን አደራ ወይም ብድር ወስዶ ባልንጀራውን ቢክድ፥ ወይም ቢቀማ፥ ወይም በባልንጀራው ላይ ግፍ ቢያደርግ፥ 3.ወይም የጠፋውን ነገር ቢያገኝ፥ ያንንም ሸሽጎ በሐሰት ቢምል፥ ሰው ከሚያደርጋቸው ከእነዚህ ነገሮች ሁሉ በአንዲቱ ቢበድል፥ 4.እርሱ ኃጢአትን ሠርቶ በደለኛ ቢሆን፥ በቅሚያ የወሰደውን ወይም በግፍ የተቀበለውን ወይም የተሰጠውን አደራ ወይም ጠፍቶ ያገኘውን፥ 5.ወይም በሐሰት የማለበትን ነገር ይመልስ፤ በሙሉ ይመልስ፥ ከዚያም በላይ አምስተኛውን ክፍል ጨምሮ የበደሉን መሥዋዕት በሚያቀርብበት ቀን ለባለ ገንዘቡ ይስጠው። 6.ስለ በደል መሥዋዕትም ለእግዚአብሔር ከመንጋው ነውር የሌለበትን አውራ በግ እንደ ግምጋሜህ መጠን ስለ በደል መሥዋዕት ወደ ካህኑ ያምጣ። 7.ካህኑም በእግዚአብሔር ፊት ያስተሰርይለታል፥ ስለዚያም ስላደረገው በደል ሁሉ ይቅር ይባላል። 8.እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው። 9.አሮንንና ልጆቹን እንዲህ ብለህ እዘዛቸው። የሚቃጠለው የመሥዋዕቱ ሕግ ይህ ነው፤ የሚቃጠለው መሥዋዕት በመሠዊያው ላይ ባለው እንጨት ላይ ሌሊቱን ሁሉ እስኪጸባ ድረስ ይሆናል፤ እሳቱም በመሠዊያው ላይ ዘወትር ይነድዳል። 10.ካህኑም የበፍታ ቀሚስና የበፍታ ሱሪ በሥጋው ላይ ይለብሳል፤ በመሠዊያውም ላይ የሚቃጠለውን መሥዋዕት እሳቱ ከበላው በኋላ አመዱን አንሥቶ በመሠዊያው አጠገብ ያፈስሰዋል። 11.ልብሱንም ያወልቃል፥ ሌላም ልብስ ይለብሳል፤ አመዱንም ተሸክሞ ከሰፈሩ ንጹሕ ስፍራ ወደ ሆነ ወደ ውጭ ያወጣዋል። 12.እሳቱም በመሠዊያው ላይ ዘወትር ይነድዳል፥ አይጠፋም፤ ካህኑም ማለዳ ማለዳ እንጨት ያቃጥልበታል፤ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት በዚያ ላይ ይረበርባል፤ በዚያም የደኅንነትን መሥዋዕት ስብ ያቃጥላል። 13.ዘወትር በመሠዊያው ላይ እሳት ይነድዳል፤ አይጠፋም። 14.የእህሉም ቍርባን ሕግ ይህ ነው፤ የአሮን ልጆች በእግዚአብሔር ፊት በመሠዊያው ፊት ያቀርቡታል። 15.ካህኑም ከእህሉ ቍርባን መልካሙን ዱቄት ከዘይት ጋር እፍኝ ሙሉ፥ ደግሞም በእህሉ ቍርባን ላይ ያለውን ዕጣን ሁሉ ያነሣል፥ ለእግዚአብሔርም ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን ለመታሰቢያ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል። 16.ከእርሱም የተረፈውን አሮንና ልጆቹ ይበሉታል፤ ቂጣ ሆኖ በተቀደሰ ስፍራ ይበላል፤ በመገናኛው ድንኳን ዙሪያ ባለው አደባባይ ይበሉታል። 17.በእርሾ ቦክቶ አይጋገርም። እርሱን ከእሳቱ ቍርባኔ ለእነርሱ እድል ፈንታ እንዲሆን ሰጠሁ፤ እርሱም እንደ ኃጢአትና እንደ በደል መሥዋዕት ቅዱስ ቅዱሳን ነው። 18.ለእግዚአብሔር ከቀረበ ከእሳት ቍርባን ለዘላለም ለልጅ ልጃችሁ እድል ፈንታቸው እንዲሆን ከአሮን ልጆች ወንዶቹ ሁሉ ይበሉታል። የሚነካቸው ሁሉ ቅዱስ ይሆናል። 19.እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው። 20.በተቀቡበት ቀን የኢፍ መስፈሪያ አሥረኛ ክፍል መልካሙን ዱቄት እኵሌታውን በጥዋት፥ እኵሌታውንም በማታ ለዘወትር የእህል ቍርባን አድርገው ለእግዚአብሔር የሚያቀርቡት የአሮንና የልጆቹ ቍርባን ይህ ነው። 21.ከዘይት ጋር በምጣድ ላይ ይደረጋል፤ ሲለወስ ታገባዋለህ፤ ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን የእህሉን ቍርባን ቈራርሰህ ታቀርበዋለህ። 22.ከልጆቹም በአባቱ ፋንታ የተቀባው ካህን ያቀርበዋል። ለዘላለም ሥርዓት እንዲሆን ፈጽሞ ለእግዚአብሔር ይቃጠላል። 23.ካህኑም የሚያቀርበው የእህል ቍርባን ሁሉ ፈጽሞ ይቃጠላል፤ ከእርሱም አንዳች አይበላም። 24.እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው። 25.አሮንንና ልጆቹን እንዲህ ብለህ ተናገራቸው። የኃጢአት መሥዋዕት ሕግ ይህ ነው፤ የሚቃጠል መሥዋዕት በሚታረድበት ስፍራ የኃጢአቱ መሥዋዕት በእግዚአብሔር ፊት ይታረዳል፤ እርሱ ቅዱስ ቅዱሳን ነው። 26.ለኃጢአት የሚሠዋው ካህን ይበላዋል፤ በመገናኛው ድንኳን ዙሪያ ባለው አደባባይ በተቀደሰ ስፍራ ይበላል። 27.ሥጋውን የሚነካ ሁሉ ቅዱስ ይሆናል፤ ማናቸው ልብስ ደም ቢረጭበት የተረጨበትን በተቀደሰ ስፍራ ታጥበዋለህ። 28.የሚቀቀልበትም ሸክላ ይሰበራል፤ በናስም ዕቃ ቢቀቀል ይፈገፈጋል፥ በውኃም ይለቀለቃል። 29.ከካህናት ወገን የሆነ ወንድ ሁሉ ከእርሱ ይበላል፤ እርሱ ቅዱስ ቅዱሳን ነው። 30.ነገር ግን በመቅደሱ ውስጥ ለማስተስረያ ይሆን ዘንድ ከደሙ ወደ መገናኛው ድንኳን የሚገባው የኃጢአት መሥዋዕት ሁሉ አይበላም፤ በእሳት ይቃጠላል።

ምዕራፍ 7

1.የበደል መሥዋዕት ሕግ ይህ ነው፤ ቅዱስ ቅዱሳን ነው። 2.የሚቃጠለውን መሥዋዕት በሚያርዱበት ስፍራ የበደሉን መሥዋዕት ያርዱታል፤ ደሙንም በመሠዊያው ላይ በዙሪያው ይረጨዋል። 3.ስቡንም ሁሉ፥ ላቱንም፥ የሆድ ዕቃውንም የሚሸፍነውን ስብ ያቀርበዋል። 4.ሁለቱንም ኵላሊቶች፥ በእነርሱም ላይና በጎድኑ አጠገብ ያለውን ስብ፥ በጕበቱም ላይ ያለውን መረብ ከኵላሊቶቹ ጋር ይወስዳል። 5.ካህኑም ለእግዚአብሔር የእሳት ቍርባን እንዲሆን በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል፤ እርሱ የበደል መሥዋዕት ነው። 6.ከካህናት ወገን የሆነ ወንድ ሁሉ ይበላዋል፤ በተቀደሰ ስፍራ ይበሉታል፤ ቅዱስ ቅዱሳን ነው። 7.የኃጢአት መሥዋዕት እንደ ሆነ እንዲሁ የበደል መሥዋዕት ነው፤ ለሁለቱ አንድ ሕግ ነው፤ በእርሱ የሚያስተሰርይ ካህን ይወስደዋል። 8.የማናቸውንም ሰው የሚቃጠል መሥዋዕት የሚያቀርብ ካህን ያቀረበው የሚቃጠለው መሥዋዕት ቁርበት ለዚያው ካህን ይሆናል። 9.በእቶን የተጋገረው የእህል ቍርባን ሁሉ፥ በመቀቀያም ወይም በምጣድ የበሰለው ሁሉ ለሚያቀርበው ካህን ይሆናል። 10.በዘይትም የተለወሰው ወይም የደረቀው የእህል ቍርባን ሁሉ ለአሮን ልጆች ሁሉ ይሆናል፤ ለሁሉም ይሆናል። 11.ሰው ለእግዚአብሔር የሚያቀርበው የደኅንነት መሥዋዕት ሕግ ይህ ነው። 12.ለምስጋና ቢያቀርበው፥ ከምስጋናው መሥዋዕት ጋር በዘይት የተለወሰ የቂጣ እንጎቻ፥ በዘይትም የተቀባ ስስ ቂጣ፥ በዘይትም የተለወሰ መልካም ዱቄት ያቀርባል። 13.ለምስጋና የሚሆነውን የደኅንነት መሥዋዕት ባቀረበ ጊዜ እርሾ ያለበትን ኅብስት ያቀርባል። 14.ከቍርባኑም ሁሉ ለእግዚአብሔር የማንሣት ቍርባን እንዲሆን ከእነርሱ አንዱን ያነሣል። እርሱም የደኅንነትን መሥዋዕት ደም ለሚረጨው ካህን ይሆናል። 15.ለምስጋና የሚሆነው የደኅንነት መሥዋዕት ሥጋ በሚቀርብበት ቀን ይበሉታል፤ ከእርሱ እስከ ነገ ምንም አያድርም። 16.የቍርባኑም መሥዋዕት የስእለት ወይም የፈቃድ ቢሆን፥ መሥዋዕቱ በሚቀርብበት ቀን ይብሉት፤ ከእርሱም የቀረውን በነጋው ይብሉት፤ 17.ከመሥዋዕቱም ሥጋ እስከ ሦስተኛው ቀን የሚቆየው በእሳት ይቃጠላል። 18.በሦስተኛው ቀን ከደኅንነት መሥዋዕት ሥጋ ቢበላ፥ አይሠምርም፤ ላቀረበው ሰው የተጠላ ይሆንበታል እንጂ ቍርባን ሆኖ አይቈጠርለትም፤ ከእርሱም ቢበላ ኃጢአቱን ይሸከማል። 19.ርኩስ ነገር የሚነካውን ሥጋ አይብሉት፤ በእሳት ይቃጠል። ንጹሕ የሆነ ሰው ሁሉ ግን ከሥጋው ይብላ። 20.ሰውም የረከሰ ቢሆን፥ ለእግዚአብሔርም ከሆነው ከደኅንነት መሥዋዕት ሥጋ ቢበላ፥ ያ ሰው ከሕዝቡ ተለይቶ ይጥፋ። 21.ማናቸውንም ርኵስ ነገር ቢነካ፥ የሰውን ወይም የረከሰን እንስሳ ወይም ሌላውን የተጠላ ርኩስን ቢነካ፥ ለእግዚአብሔርም ከሆነው ከደኅንነት መሥዋዕት ሥጋ ቢበላ፥ ያ ሰው ከሕዝቡ ተለይቶ ይጥፋ። 22.እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 23.የእስራኤልን ልጆች እንዲህ ብለህ ተናገራቸው። የበሬ ወይም የበግ ወይም የፍየል ስብ ከቶ አትብሉ። 24.የሞተውን ስብ፥ አውሬ የሰበረውንም ስብ ለሌላ ተግባር አድርጉት፤ ነገር ግን ከእርሱ ምንም አትብሉ፤ 25.ለእግዚአብሔር በእሳት ከሚቀርበው ከእንስሳ ስብ የሚበላ ሁሉ፥ ያ የበላ ሰው ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ ይጠፋልና። 26.በማደሪያዎቻችሁም ሁሉ የወፍ ወይም የእንስሳ ደም ቢሆን አትብሉ። 27.ደም የሚበላ ሰው ሁሉ ያ ሰው ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ ይጥፋ። 28.እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። 29.የእስራኤልን ልጆች እንዲህ ብለህ ተናገራቸው። ለእግዚአብሔር የደኅንነት መሥዋዕት የሚያቀርብ ሰው ቍርባኑን ለእግዚአብሔር ከደኅንነቱ መሥዋዕት ያመጣል። 30.የእርሱ እጆች ለእግዚአብሔር የእሳቱን ቍርባን ያመጣሉ፤ ፍርምባው በእግዚአብሔር ፊት ለመወዝወዝ ቍርባን ይወዘውዝ ዘንድ ስቡንና ፍርምባውን ያመጣል። 31.ካህኑም ስቡን በመሠዊያው ላይ ያቃጥላል፤ ፍርምባውም ለአሮንና ለልጆቹ ይሁን። 32.ከደኅንነት መሥዋዕታችሁ ቀኝ ወርቹን ለማንሣት ቍርባን እንዲሆን ለካህኑ ትሰጡታላችሁ። 33.ከአሮንም ልጆች የደኅንነትን መሥዋዕት ደሙንና ስቡን ለሚያቀርብ ለእርሱ ቀኝ ወርቹ እድል ፈንታው ይሆናል። 34.የሚወዘወዘውን ፍርምባና የሚነሣውን ወርች ከእስራኤል ልጆች ከደኅንነት መሥዋዕታቸው ወስጄአለሁ፥ ለካህኑ ለአሮንና ለልጆቹም ለዘላለም እድል ፈንታ እንዲሆን ከእስራኤል ልጆች ዘንድ ሰጥቼአቸዋለሁ። 35.እግዚአብሔርን በክህነት ያገለግሉት ዘንድ ባቀረባቸው ቀን ለእግዚአብሔር ከሆነ ከእሳት ቍርባን የአሮንና የልጆቹ እድል ፈንታ ይህ ነው። 36.ለልጅ ልጃቸው ለዘላለም እድል ፈንታቸው እንዲሆን በቀባቸው ቀን የእስራኤል ልጆች ይሰጡአቸው ዘንድ እግዚአብሔር ያዘዘው ይህ ነው። 37.የሚቃጠል መሥዋዕትና የእህል ቍርባን፥ የኃጢአትና የበደል መሥዋዕት፥ የቅድስናና የደኅንነት መሥዋዕት ሕግ ይህ ነው። 38.እግዚአብሔር በሲና ምድረ በዳ ቍርባናቸውን ለእግዚአብሔር ያቀርቡ ዘንድ ለእስራኤል ልጆች ባዘዘ ጊዜ በሲና ተራራ ለሙሴ ያዘዘው ይህ ነው።

ወደ ዕብራውያን

ምዕራፍ 3

1.ስለዚህ፥ ከሰማያዊው ጥሪ ተካፋዮች የሆናችሁ ቅዱሳን ወንድሞች ሆይ፥ የሃይማኖታችንን ሐዋርያና ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስን ተመልከቱ፤ 2.ሙሴ ደግሞ በቤቱ ሁሉ የታመነ እንደሆነ፥ እርሱ ለሾመው የታመነ ነበረ። 3.ቤትን የሚያዘጋጀው ከቤቱ ይልቅ የሚበልጥ ክብር እንዳለው መጠን፥ እንዲሁ እርሱ ከሙሴ ይልቅ የሚበልጥ ክብር የተገባው ሆኖ ተቆጥሮአልና። 4.እያንዳንዱ ቤት በአንድ ሰው ተዘጋጅቶአልና፥ ሁሉን ያዘጋጀ ግን እግዚአብሔር ነው። 5.ሙሴስ በኋላ ስለሚነገረው ነገር ምስክር ሊሆን በቤቱ ሁሉ እንደ ሎሌ የታመነ ነበረ፥ ክርስቶስ ግን እንደ ልጅ በቤቱ ላይ የታመነ ነው፤ 6.እኛም የምንደፍርበትን የምንመካበትንም ተስፋ እስከ መጨረሻው አጽንተን ብንጠብቅ ቤቱ ነን። 7.ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ እንደሚል።
8 -
9.ዛሬ ድምፁን ብትሰሙት፥ አባቶቻችሁ እኔን የፈተኑበት የመረመሩበትም አርባ ዓመትም ሥራዬን ያዩበት በምድረ በዳ በፈተና ቀን በማስመረር እንደ ሆነ፥ ልባችሁን እልከኛ አታድርጉ። 10.ስለዚህ ያን ትውልድ ተቆጥቼ። ዘወትር በልባቸው ይስታሉ መንገዴን ግን አላወቁም አልሁ፤ 11.እንዲሁ። ወደ ዕረፍቴ አይገቡም ብዬ በቍጣዬ ማልሁ። 12.ወንድሞች ሆይ፥ ምናልባት ሕያው እግዚአብሔርን የሚያስክዳችሁ ክፉና የማያምን ልብ ከእናንተ በአንዳችሁ እንዳይኖር ተጠንቀቁ፤ 13.ነገር ግን ከእናንተ ማንም በኃጢአት መታለል እልከኛ እንዳይሆን፥ ዛሬ ተብሎ ሲጠራ ሳለ፥ በእያንዳንዱ ቀን እርስ በርሳችሁ ተመካከሩ፤ 14.የመጀመሪያ እምነታችንን እስከ መጨረሻው አጽንተን ብንጠብቅ፥ የክርስቶስ ተካፋዮች ሆነናልና፤ 15.እየተባለ። ዛሬ ድምጹን ብትሰሙት፥ በማስመረር እንደሆነ ልባችሁን እልከኛ አታድርጉ። 16.ሰምተው ያስመረሩት እነማን ነበሩ? በሙሴ ተመርተው ከግብጽ የወጡ ሁሉ አይደሉምን? 17.አርባ አመትም የተቆጣባቸው እነማን ነበሩ? ሬሳቸው በምድረ በዳ የወደቀ፥ ኃጢአትን ያደረጉት እነርሱ አይደሉምን? 18.ካልታዘዙትም በቀር ወደ እረፍቱ እንዳይገቡ የማለባቸው እነማን ነበሩ? 19.ባለማመናቸውም ጠንቅ ሊገቡ እንዳልተቻላቸው እናያለን።
♫
Listen to the reading 5 chapter tracks
ኦሪት ዘሌዋውያን Chapter 4
ኦሪት ዘሌዋውያን Chapter 5
ኦሪት ዘሌዋውያን Chapter 6
ኦሪት ዘሌዋውያን Chapter 7
ወደ ዕብራውያን Chapter 3
Swipe to browse chapters
Listen 5