Skip to Content
የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን | YEHIWOT MELHEK BETEKIRSTIAN
የ2019 ዓ.ም የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ 📖 ዛሬን አንብብ →

የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን

Yehiwot Melhek Betekirstian

ሳምንት 7 · ቀን 34 (ሐሙስ) 📅 Tikimt 19, 2019

ኦሪት ዘሌዋውያን 1, 2, 3 · መዝሙረ ዳዊት 27 · ወደ ዕብራውያን 2

📖 የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም፦ 1954 መጽሐፍ ቅዱስ አዲሱ መደበኛ ትርጒም

ኦሪት ዘሌዋውያን

ምዕራፍ 1

የሚቃጠል መሥዋዕት

1.እግዚአብሔር ሙሴን ጠራው፤ ከመገናኛውም ድንኳን እንዲህ ሲል ተናገረው፤ 2.“እስራኤላውያንን ተናገራቸው፤ እንዲህም በላቸው፤ ‘ከእናንተ ማንም ሰው ለእግዚአብሔር ከእንስሳ ወገን መሥዋዕት በሚያቀርብበት ጊዜ ከላሙ፣ ከበጉ ወይም ከፍየሉ መንጋ መካከል ያቅርብ። 3.“ ‘መባው በሚቃጠል መሥዋዕትነት ከላሞች መንጋ መካከል የሚቀርብ ከሆነ፣ ነቀፋ የሌለበትን ተባዕቱን መሥዋዕት በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ላይ ያቅርበው። 4.የሚቃጠል መሥዋዕት ሆኖ በሚቀርበው እንስሳ ራስ ላይም እጁን ይጫን፤ ይህም ያስተሰርይለት ዘንድ በምትኩ ተቀባይነት ያገኛል። 5.ወይፈኑን በእግዚአብሔር ፊት ይረደው፤ ካህናቱ የአሮን ልጆችም ደሙን አምጥተው በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ባለው በመሠዊያው ዙሪያ ሁሉ ይርጩት። 6.እርሱም የሚቃጠለውን መሥዋዕት ቈዳ ይግፈፍ፤ ብልቱንም ያውጣው። 7.የካህኑ የአሮን ልጆች በመሠዊያው ላይ ዕንጨት ረብርበው እሳት ያንድዱበት። 8.ካህናቱ የአሮን ልጆች ጭንቅላቱንና ሥቡን ጨምረው ብልቶቹን በመሠዊያው ላይ በሚነድደው ዕንጨት ላይ ይደርድሩት፤ 9.አቅራቢው የሆድ ዕቃውንና እግሮቹን በውሃ ይጠብ፤ ካህኑም መባውን ሁሉ በመሠዊያው ላይ ያቃጥል፤ ይህም በእሳት የሚቀርብ፣ ሽታውም እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ የሚቃጠል መሥዋዕት ይሆናል። 10.“ ‘መባው በሚቃጠል መሥዋዕትነት ከበግ ወይም ከፍየል መንጋ መካከል የሚቀርብ ከሆነ፣ እንከን የሌለበትን ተባዕቱን ያቅርብ። 11.የሚቀርበውን መሥዋዕት ከመሠዊያው በስተሰሜን በኩል በእግዚአብሔር ፊት ይረደው፤ ካህናቱ የአሮን ልጆችም ደሙን በመሠዊያው ላይ ዙሪያውን ሁሉ ይርጩት። 12.አቅራቢው ብልቶቹን ያውጣ፤ ካህኑም ጭንቅላቱንና ሥቡን ጨምሮ በመሠዊያው ላይ በሚነድደው ዕንጨት ላይ ይደርድረው፤ 13.አቅራቢው የሆድ ዕቃውንና እግሮቹን በውሃ ይጠብ፤ ካህኑ መባውን ሁሉ አምጥቶ በመሠዊያው ያቃጥል፤ ይህም በእሳት የሚቀርብ፣ ሽታውም እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ የሚቃጠል መሥዋዕት ይሆናል። 14.“ ‘ለእግዚአብሔር በሚቃጠል መሥዋዕትነት የሚቀርበው መባ ከወፎች ወገን ከሆነ፣ ዋኖስ ወይም የርግብ ጫጩት ያቅርብ። 15.ካህኑም ወደ መሠዊያው ያምጣው፤ ራሱን ቈልምሞ ይቀንጥሰው፤ የተቈረጠውንም ራስ በመሠዊያው ላይ ያቃጥል፤ ደሙም በመሠዊያው አጠገብ ይንጠፍጠፍ፤ 16.ከሆድ ዕቃውም ጥሬ ቤቱን ለይቶ ከላባዎቹ ጋራ ከመሠዊያው በስተምሥራቅ በኩል፣ ዐመድ በሚፈስስበት ስፍራ ይጣለው። 17.በክንፎቹ በኩል ለሁለት ይሰንጥቀው፤ ነገር ግን ጨርሶ አያለያየው፤ ካህኑም በመሠዊያው ላይ በሚነድደው ዕንጨት ላይ ያቃጥለው፤ ይህም በእሳት የሚቀርብ፣ ሽታውም እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ የሚቃጠል መሥዋዕት ይሆናል።

ምዕራፍ 2

የእህል ቍርባን

1.“ ‘ማንኛውም ሰው የእህል ቍርባን ለእግዚአብሔር በሚያቀርብበት ጊዜ፣ ዱቄቱ የላመ ይሁን፤ ዘይት ያፍስስበት፤ ዕጣንም ይጨምርበት፤ 2.ወደ ካህናቱም ወደ አሮን ልጆች ያምጣው። ካህኑ ከላመው ዱቄትና ከዘይቱ አንድ ዕፍኝ ሙሉ ያንሣለት፤ ዕጣኑንም ሁሉ ይውሰደው፤ ይህንም በእሳት የሚቀርብ፣ ሽታውም እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕት አድርጎ ለመታሰቢያ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለው። 3.የተረፈውም የእህሉ ቍርባን ለአሮንና ለልጆቹ ይሰጥ፤ ይህም ለእግዚአብሔር በእሳት ከሚቀርበው ቍርባን እጅግ የተቀደሰ ክፍል ነው። 4.“ ‘በማብሰያ ምድጃ የተጋገረ የእህል ቍርባን በምታቀርብበት ጊዜ፣ ከላመ ዱቄት ተዘጋጅቶ እርሾ ሳይገባበት በዘይት ተለውሶ የተጋገረ ኅብስት ይሁን፤ አለዚያም ያለ እርሾ በሥሡ ተጋግሮ ዘይት የተቀባ ቂጣ ይሁን። 5.የእህል ቍርባንህ በምጣድ የሚጋገር ከሆነ፣ እርሾ ሳይገባበት በዘይት የተለወሰ የላመ ዱቄት ቂጣ ይሁን። 6.ቈራርሰህ ዘይት አፍስስበት፤ ይህ የእህል ቍርባን ነው። 7.የእህል ቍርባንህ በመጥበሻ የሚበስል ከሆነ፣ ከላመ ዱቄትና ከዘይት ይዘጋጅ። 8.በዚህ ሁኔታ የተዘጋጀውን የእህል ቍርባን ወደ እግዚአብሔር አምጥተህ ለካህኑ አስረክብ፤ ካህኑም ወደ መሠዊያው ይወስደዋል፤ 9.ካህኑም ከእህሉ ቍርባን ላይ ለመታሰቢያ የሚሆነውን ክፍል ያነሣና በእሳት የሚቃጠል፣ ሽታውም እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕት አድርጎ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለዋል። 10.የተረፈውም የእህሉ ቍርባን ለአሮንና ለልጆቹ ይሰጥ፤ ይህም ለእግዚአብሔር በእሳት ከሚቀርበው ቍርባን እጅግ የተቀደሰ ክፍል ነው። 11.“ ‘ለእግዚአብሔር በእሳት በምታቀርቡት ቍርባን ውስጥ እርሾ ወይም ማር ጨምራችሁ ማቃጠል ስለማይገባችሁ፣ በምታቀርቡት በማንኛውም የእህል ቍርባን እርሾ አይኑርበት። 12.እነዚህን የበኵራት ቍርባን አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር ማቅረብ ትችላላችሁ፤ ነገር ግን ሽታው ደስ የሚያሰኝ ቍርባን ሆነው በመሠዊያ ላይ ለመቃጠል አይቀርቡም። 13.የምታቀርበውን የእህል ቍርባን ሁሉ በጨው ቀምመው፤ የአምላክህ የቃል ኪዳን ጨው ከእህል ቍርባንህ አይታጣ፤ በቍርባንህም ላይ ጨው ጨምርበት። 14.“ ‘የእህል በኵራት ቍርባን ለእግዚአብሔር በምታመጣበት ጊዜ፣ የተፈተገና በእሳት የተጠበሰ እሸት አቅርብ። 15.ዘይት ጨምርበት፤ ዕጣንም በላዩ አስቀምጥ፤ ይህ የእህል ቍርባን ነው። 16.ካህኑም ከተፈተገው እህልና ከዘይቱ ወስዶ፣ ከዕጣኑ ሁሉ ጋራ ለእግዚአብሔር በእሳት የሚቀርብ መታሰቢያ አድርጎ ያቃጥል።

ምዕራፍ 3

የኅብረት መሥዋዕት

1.“ ‘ማንኛውም ሰው የሚያቀርበው ቍርባን ከላሞች መንጋ የሚቀርብ የኅብረት መሥዋዕት ከሆነ፣ እንከን የሌለበትን ተባዕት ወይም እንስት በእግዚአብሔር ፊት ያቅርብ። 2.በመሥዋዕቱ ራስ ላይ እጁን ይጫን፤ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ላይ ይረደው፤ ካህናቱም የአሮን ልጆች ደሙን በመሠዊያው ላይ ዙሪያውን ይርጩት። 3.ከኅብረት መሥዋዕቱ ለእግዚአብሔር በእሳት የሚቀርብ ቍርባን አድርጎ ያምጣ፤ የሆድ ዕቃውን የሚሸፍነውን ሥብ፣ በሆድ ዕቃው ላይ ያለውን ሥብ ሁሉ፣ 4.ሁለቱን ኵላሊቶች፣ በኵላሊቶቹ ላይና በጐድኑ አጠገብ ያለውን ሥብ እንዲሁም የጕበቱን መሸፈኛ፣ ከኵላሊቶቹ ጋራ አንድ ላይ አውጥቶ ያቅርብ። 5.የአሮንም ልጆች በመሠዊያው በሚነድደው ዕንጨት ላይ ባለው በሚቃጠለው መሥዋዕት ላይ አድርገው ያቃጥሉት፤ ይህም በእሳት የሚቀርብ፣ ሽታውም እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕት ይሆናል። 6.“ ‘ከበግ ወይም ከፍየሉ መንጋ ለእግዚአብሔር የኅብረት መሥዋዕት የሚያቀርብ ከሆነ፣ እንከን የሌለበትን ተባዕት ወይም እንስት ያቅርብ። 7.መሥዋዕቱ የበግ ጠቦት ከሆነም፣ በእግዚአብሔር ፊት ያምጣው፤ 8.በመሥዋዕቱ ራስ ላይ እጁን ይጫን፤ በመገናኛው ድንኳን ፊት ለፊት ይረደው፤ የአሮንም ልጆች ደሙን በመሠዊያው ላይ ዙሪያውን ይርጩት። 9.ከኅብረት መሥዋዕቱ ለእግዚአብሔር በእሳት የሚቀርብ እንከን የሌለው መሥዋዕት ያምጣ፤ ሥቡን፣ እስከ ጀርባ ዐጥንቱ ድረስ የተቈረጠ ላቱን በሙሉ፣ የሆድ ዕቃውን የሸፈነውን ሥብ፣ ከሆድ ዕቃው ጋራ የተያያዘውን ሥብ ሁሉ፣ 10.ሁለቱን ኵላሊቶች፣ ኵላሊቶቹ ላይና በጐድኑ አጠገብ ያለውን ሥብ እንዲሁም የጕበቱን መሸፈኛ ከኵላሊቶቹ ጋራ ዐብሮ አውጥቶ ያቅርብ። 11.ካህኑም ይህን ሁሉ ለእግዚአብሔር በእሳት የሚቀርብ የመብል ቍርባን አድርጎ በመሠዊያው ላይ ያቃጥል። 12.“ ‘መሥዋዕቱ ፍየል ከሆነ፣ በእግዚአብሔር ፊት ያቅርብ፤ 13.በራሱም ላይ እጁን ይጫንበት፤ በመገናኛው ድንኳን ፊት ለፊት ይረደው፤ የአሮንም ልጆች ደሙን በመሠዊያው ላይ ዙሪያውን ይርጩት። 14.ከሚያቀርበውም መሥዋዕት ላይ ለእግዚአብሔር በእሳት የሚቀርብ ቍርባን አድርጎ ያቅርብ፤ የሆድ ዕቃውን የሚሸፍነውን ሥብ፣ ከሆድ ዕቃው ጋራ የተያያዘውን ሥብ ሁሉ፣ 15.ሁለቱን ኵላሊቶች፣ በኵላሊቶቹ ላይና በጐድኑ አጠገብ ያለውን ሥብ፣ እንዲሁም የጕበቱን መሸፈኛ ከኵላሊቶቹ ጋራ ዐብሮ አውጥቶ ያቅርብ። 16.ካህኑም ይህን ሁሉ በእሳት የሚቀርብና ሽታውም ደስ የሚያሰኝ የመብል ቍርባን አድርጎ በመሠዊያው ላይ ያቃጥል፤ ሥብ ሁሉ የእግዚአብሔር ነው። 17.“ ‘በምትኖሩበት ስፍራ ሁሉ፣ ሥብ ወይም ደም ከቶ አትብሉ፤ ይህ ለመጪው ትውልድ ሁሉ የተሰጠ የዘላለም ሥርዐት ነው።’ ”

መዝሙረ ዳዊት

ምዕራፍ 27

1.የዳዊት መዝሙር።
1 እግዚአብሔር ብርሃኔና መድኅኔ ነው፤
የሚያስፈራኝ ማን ነው?
እግዚአብሔር ለሕይወቴ ዐምባዋ ነው፤
ማንን እፈራለሁ?
2.ሥጋዬን ይበሉ ዘንድ፣
ክፉዎች ገፍተው በመጡ ጊዜ፣
ጠላቶቼና ባላጋራዎቼ በተነሡብኝ ጊዜ፣
እነርሱ ተሰነካክለው ወደቁ።
3.ሰራዊት ቢከብበኝ እንኳ፣
ልቤ አይፈራም፤
ጦርነት ቢነሣብኝ እንኳ፣
ልበ ሙሉ ነኝ።
4.እግዚአብሔርን አንዲት ነገር እለምነዋለሁ፤
እርሷንም እሻለሁ፤
ይኸውም በሕይወቴ ዘመን ሁሉ፣
በእግዚአብሔር ቤት እኖር ዘንድ፣
የእግዚአብሔርን ክብር ውበት አይ ዘንድ፣
በመቅደሱም ሆኜ አሰላስል ዘንድ ነው።
5.በመከራ ቀን፣
በድንኳኑ ውስጥ ይሰውረኛልና፤
በተቀደሰ ድንኳኑም ውስጥ ይሸሽገኛል፤
በዐለቱ ላይ ከፍ ያደርገኛል።
6.በዚህ ጊዜ በዙሪያዬ ባሉ ጠላቶቼ ላይ፣
ራሴ ከፍ ከፍ ይላል፤
በድንኳኑም ውስጥ የእልልታ መሥዋዕት እሠዋለሁ፤
ለእግዚአብሔር እቀኛለሁ፤ እዘምርለታለሁም።
7.እግዚአብሔር ሆይ፤ ድምፄን ከፍ አድርጌ ስጮኽ ስማኝ፤
ራራልኝ፤ ስማኝም።
8.“ፊቴን ፈልጉ” ባልህ ጊዜ፤
ልቤ፣ እግዚአብሔር ሆይ፤ ፊትህን እሻለሁ አለች።
9.ፊትህን ከእኔ አትሰውር፤
ተቈጥተህ አገልጋይህን አታርቀው፤
መቼም ረዳቴ ነህና።
አዳኝ አምላኬ ሆይ፤
አትጣለኝ፤ አትተወኝም።
10.አባቴና እናቴ ቢተዉኝ እንኳ፣
እግዚአብሔር ይቀበለኛል።
11.እግዚአብሔር ሆይ፤ መንገድህን አስተምረኝ፤
ስለ ጠላቶቼም፣
በቀና መንገድ ምራኝ።
12.ለጠላቶቼ ፍላጎት አሳልፈህ አትስጠኝ፤
የሐሰት ምስክሮች ተነሥተውብኛልና፣
ዐመፃ የሚረጩ ናቸው።
13.የእግዚአብሔርን ቸርነት
በሕያዋን ምድር እንደማይ
ሙሉ እምነቴ ነው።
14.እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ፤
አይዞህ፣ በርታ፤
እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ።
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

ወደ ዕብራውያን

ምዕራፍ 2

ትኵረት የሚያሻው ጕዳይ

1.ስለዚህ ከሰማነው ነገር ስተን እንዳንወድቅ፣ ለሰማነው ነገር አብልጠን ልንጠነቀቅ ይገባናል። 2.ምክንያቱም በመላእክት በኩል የተነገረው ቃል ጽኑ ከሆነና ማንኛውም መተላለፍና አለመታዘዝ ተገቢውን ቅጣት ከተቀበለ፣ 3.እኛስ እንዲህ ያለውን ታላቅ ድነት ቸል ብንል እንዴት ልናመልጥ እንችላለን? ይህ ድነት በመጀመሪያ በጌታ ተነገረ፤ ከርሱ የሰሙትም ለእኛ አረጋገጡልን። 4.እግዚአብሔርም በምልክት፣ በድንቅና በልዩ ልዩ ታምራት እንዲሁም እንደ ፈቃዱ በታደሉት የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች ስለዚሁ ነገር መስክሯል።

ኢየሱስ ወንድሞቹን መሰለ

5.ይህን የምንናገርለትን መጪውን ዓለም ለመላእክት አላስገዛም። 6.ነገር ግን አንዱ በሌላ ስፍራ እንዲህ ብሎ መስክሯል፤
“በሐሳብህ ስፍራ ትሰጠው ዘንድ ሰው ምንድን ነው?
ትጠነቀቅለትም ዘንድ የሰው ልጅ ምንድን ነው?
7.ከመላእክት በጥቂት አሳነስኸው፤
ክብርንና ግርማን አጐናጸፍኸው፤
8.ሁሉን ከእግሮቹ በታች አስገዛህለት።”
እግዚአብሔር ሁሉን ከበታቹ ሲያስገዛለት፣ ያላስገዛለት ምንም ነገር የለም፤ ይሁን እንጂ በአሁኑ ጊዜ ሁሉም ተገዝቶለት አናይም።
9.ነገር ግን በእግዚአብሔር ጸጋ ስለ ሰው ሁሉ ሞትን ይቀምስ ዘንድ ከመላእክት ጥቂት እንዲያንስ ተደርጎ የነበረው ኢየሱስ፣ የሞትን መከራ በመቀበሉ አሁን የክብርና የምስጋና ዘውድ ተጭኖለት እናየዋለን። 10.ሁሉ ነገር ለርሱና በርሱ የሚኖር እግዚአብሔር፣ ብዙ ልጆችን ወደ ክብር ለማምጣት፣ የድነታቸውን መሥራች በመከራ ፍጹም ሊያደርገው የተገባ ነበር። 11.ሰዎችን የሚቀድሰውና የሚቀደሱት ሰዎች ከአንድ ቤተ ሰብ ናቸው፤ ስለዚህ ኢየሱስ ወንድሞች ብሎ ሊጠራቸው አያፍርም። 12.እንዲህም ይላል፤
“ስምህን ለወንድሞቼ ዐውጃለሁ፤
በጉባኤም መካከል አወድስሃለሁ።”
13.እንዲሁም፣
“እኔ በርሱ እታመናለሁ።”
ደግሞም እንዲህ ይላል፤
“እነሆ፤ እኔና እግዚአብሔር የሰጠኝ ልጆች።”
14.ልጆቹ በሥጋና በደም እንደሚካፈሉ፣ እርሱ ራሱ ደግሞ ያንኑ ተካፈለ፤ ይኸውም በሞት ላይ ኀይል ያለውን ዲያብሎስን በሞቱ ኀይል እንዲደመስስ ነው፤ 15.እንዲሁም በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ በሞት ፍርሀት ባርነት የታሰሩትን ነጻ እንዲያወጣ ነው። 16.እርሱ የመጣው መላእክትን ለመርዳት ሳይሆን፣ የአብርሃምን ዘር ለመርዳት እንደ ሆነ ግልጽ ነው። 17.ስለዚህ በሁሉም ነገር ወንድሞቹን መምሰል ተገባው፤ ይህንም ያደረገው መሓሪና ታማኝ ሊቀ ካህናት ሆኖ፣ እግዚአብሔርን ለማገልገልና ለሕዝቡ የኀጢአትን ስርየት ለማስገኘት ነው። 18.እርሱ ራሱ በተፈተነ ጊዜ መከራን ስለ ተቀበለ፣ የሚፈተኑትን ሊረዳቸው ይችላልና።