ሳምንት 7 · ቀን 33 (ረቡዕ)
📅 Tikimt 18, 2019
ኦሪት ዘጸአት 38, 39, 40 · ወደ ዕብራውያን 1
ኦሪት ዘጸአት
ምዕራፍ 38
የሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያ
38፥1-7 ተጓ ምብ – ዘፀ 27፥1-8
1.ከፍታው ሦስት ክንድ የሆነ የሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያ ከግራር ዕንጨት ሠሩ፤ ርዝመቱ ዐምስት ክንድ፣ ወርዱ ዐምስት ክንድ የሆነ ባለአራት ማእዘን ነበረ።
2.ቀንዶቹና መሠዊያው አንድ ወጥ ይሆኑ ዘንድ በአራቱም ማእዘኖች ላይ አራት ቀንድ ሠሩ፤ መሠዊያውንም በንሓስ ለበጡት።
3.ዕቃዎቹንም ሁሉ ይኸውም ምንቸቶቹን፣ መጫሪያዎቹን፣ መርጫ ጐድጓዳ ሳሕኖቹን፣ ሜንጦዎቹንና የእሳት መያዣዎቹን ከንሓስ ሠሯቸው።
4.ለመሠዊያውም ከጠርዝ በታች ሆኖ ከመሠዊያው ግማሽ ቁመት ላይ የሚሆን የንሓስ ፍርግርግ ማንደጃ ሠሩ።
5.ለናሱ ፍርግርግ ማንደጃ አራት ማእዘኖች መሎጊያዎቹን እንዲይዙ የንሓስ ቀለበቶችን ሠሩ።
6.መሎጊያዎቹን ከግራር ዕንጨት ሠርተው በንሓስ ለበጧቸው።
7.መሠዊያውን ለመሸከም በመሠዊያው ጐኖች ይሆኑ ዘንድ መሎጊያዎቹን በቀለበቶቹ ውስጥ አስገቧቸው፤ ውስጡንም ክፍት በማድረግ ከሳንቃዎች ሠሩት።
የመታጠቢያው ሳሕን
8.የናስ መታጠቢያ ሳሕንና የንሓስ መቆሚያውን በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ላይ ከሚያገለግሉት ሴቶች መስተዋት ሠሩት።አደባባዩ
38፥9-20 ተጓ ምብ – ዘፀ 27፥9-19
9.ቀጥሎም አደባባዩን ሠሩ፤ የደቡቡ ክፍል ርዝመት አንድ መቶ ክንድ ሲሆን፣ በቀጭኑ ከተፈተለ በፍታ የተሠሩ መጋረጃዎች ነበሩት፤
10.ሃያ ምሰሶዎችና ሃያ የንሓስ መቆሚያዎች፣ የብር ኵላቦችና በምሰሶዎቹ ላይ ዘንጎች ነበሩት።
11.የሰሜኑም ክፍል ቁመቱ አንድ መቶ ክንድ ነበር፤ ሃያ ምሰሶዎችና ሃያ የንሓስ መቆሚያዎች፣ የብር ኵላቦችና በምሰሶዎቹም ላይ ዘንጎች ነበሩት።
12.የምዕራቡ ጫፍ ወርዱ ዐምሳ ክንድ ነበር፤ ዐሥር ምሰሶዎችና ዐሥር መቆሚያዎች እንዲሁም የብር ኵላቦችና በምሰሶዎቹም ላይ ዘንጎች ያሉት መጋረጃዎች ነበሩት።
13.በፀሓይ መውጫ በኩል ያለው የምሥራቁም ጫፍ ወርዱ ዐምሳ ክንድ ነበር።
14.ከሦስት ምሰሶዎችና ከሦስት መቆሚያዎች ጋራ ርዝመታቸው ዐሥራ ዐምስት ክንድ የሆኑ መጋረጃዎች በአንድ በኩል ባለው መግቢያ ላይ ነበሩ፤
15.ከሦስት ምሰሶዎችና ከሦስት መቆሚያዎች ጋራ ርዝመታቸው ዐሥራ ዐምስት ክንድ የሆኑ መጋረጃዎች በአደባባዩ መግቢያ በሌላው በኩል ነበሩ።
16.በአደባባዩ ዙሪያ ያሉት መጋረጃዎች በሙሉ በቀጭኑ ከተፈተለ በፍታ የተሠሩ ነበሩ።
17.የምሰሶዎቹ መቆሚያዎች ንሓስ ነበሩ፤ ኵላቦቹና በምሰሶዎቹ ላይ ያሉት ዘንጎች ከብር የተሠሩ ነበሩ፤ ጫፎቻቸውም በብር ተለብጠው ነበር፤ ስለዚህ የአደባባዩ ምሰሶዎች ሁሉ የብር ዘንጎች ነበሯቸው።
18.በአደባባዩ መግቢያ ላይ ያለው መጋረጃ ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊ፣ ከቀይ ማግና የጥልፍ ባለሙያ ከጠለፈው፣ በቀጭኑ ከተፈተለ በፍታ የተሠራ ነበር፤ ቁመቱ ሃያ ክንድ፣ እንደ አደባባዩ መጋረጃዎች ከፍታው ዐምስት ክንድ ነበረ፤
19.አራት ምሰሶዎችና አራት መቆሚያዎች ነበሩት፤ ኵላቦቻቸውና ዘንጎቻቸው የብር ሲሆኑ፣ ጫፎቻቸው በብር ተለብጠው ነበር።
20.የማደሪያው ድንኳንና የአደባባዩ ዙሪያ ካስማዎች ሁሉ ከንሓስ የተሠሩ ነበሩ።
ለአገልግሎት የዋሉ ዕቃዎች
21.ለማደሪያው ድንኳን፣ ይኸውም ለምስክሩ ድንኳን ሙሴ ባዘዘው፣ በካህኑ በአሮን ልጅ በኢታምር መሪነት ሌዋውያኑ በጻፉት መሠረት የዕቃዎቹ ቍጥር ይህ ነው። 22.ከይሁዳ ነገድ የሆር የልጅ ልጅ፣ የኡሪ ልጅ የሆነው ባስልኤል፣ እግዚአብሔር ሙሴን ያዘዘውን ሁሉ አደረገ። 23.ከርሱም ጋራ ከዳን ነገድ የሆነው የአሂሳሚክ ልጅ ኤልያብ፣ ዕቅድ አውጭና የእጅ ጥበብ ባለሙያ፣ በሰማያዊ፣ በሐምራዊ፣ በቀይ ማግና በቀጭን በፍታ ጥልፍ ጠላፊ ነበር። 24.ለመቅደሱ ሥራ ሁሉ ከመወዝወዙ ስጦታ በመቅደሱ ሰቅል መሠረት የዋለው ጠቅላላ ወርቅ ሃያ ዘጠኝ መክሊትና ሰባት መቶ ሠላሳ ሰቅል ነበረ። 25.በቈጠራው ወቅት ተቈጥረው ከነበሩት ማኅበረ ሰብ የተገኘው ብር ለመቅደሱ ሰቅል አንድ መቶ መክሊትና አንድ ሺሕ ሰባት መቶ ሰባ ዐምስት ሰቅሎች ነበሩ። 26.ከተቈጠሩት ጋራ ዐብረው ከሆኑት ሃያና ከሃያ ዓመት በላይ የሆናቸው ስድስት መቶ ሦስት ሺሕ ዐምስት መቶ ዐምሳ ሰዎች የሰጡት እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን በአንድ ሰው አንድ ቤካ ይኸውም ግማሽ ሰቅል ነበረ። 27.አንድ መቶ የብር መክሊቶች የመቅደሱንና የመጋረጃዎቹን መቆሚያዎች ለመሥራት አገልግሎት ላይ ውለው ነበር፤ ይኸውም ከአንድ መቶ መክሊቶች አንድ መቶ መቆሚያዎች ሲሆን፣ ለእያንዳንዱ መቆሚያ አንድ መክሊት ማለት ነው። 28.አንድ ሺሕ ሰባት መቶ ሰባ ዐምስት ሰቅሎችን ለምሰሶዎቹ ኵላቦች፣ የምሰሶዎቹን ዐናት ለመለበጥና ዘንጎቻቸውንም ለመሥራት አገልግሎት ላይ ውለው ነበር። 29.ከመወዝወዙ ስጦታ የሆነው ናስ ሰባ መክሊትና ሁለት ሺሕ አራት መቶ ሰቅል ነበረ። 30.ለመገናኛው ድንኳን መግቢያ ለናስ መሠዊያው ከናስ መጫሪያው፣ ለዕቃዎቹም ሁሉ መቆሚያዎቹን ለመሥራት አገልግሎት ላይ አውለውት ነበር፤ 31.ለአደባባዩ ዙሪያ፣ ለመግቢያው እንዲሁም ለማደሪያው ድንኳን ካስማዎች ሁሉና ለአደባባዩ ዙሪያ ሁሉ እንዲሁ አገልግሎት ላይ አውለውት ነበር።ምዕራፍ 39
የካህናት አልባሳት
1.ለመቅደሱ አገልግሎት ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊና ከቀይ ማግ የተፈተሉ ልብሶችን ሠሩ፤ እንዲሁም እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው ለአሮን የተቀደሱ ልብሶችን ሠሩ።ኤፉድ
39፥2-7 ተጓ ምብ – ዘፀ 28፥6-14
2.ኤፉዱን ከወርቅ፣ ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊና ከቀይ ማግ፣ በቀጭኑ ከተፈተለ ሐር ሠሩት።
3.ጥበበኛ ባለሙያ እንደሚሠራው በሰማያዊ፣ በሐምራዊ፣ በቀይ ማግና በቀጭን በፍታ ይሠራ ዘንድ ወርቁን በሥሡ ቀጥቅጠው እንደ ክር ቈራረጡት።
4.ለኤፉዱ ከሁለቱ ጐኖቹ ጋራ ተያይዘው ያሉትን የትከሻ ንጣዮችን ሠሩ፤ ይኸውም ማያያዝ እንዲቻል ነው።
5.በጥበብ የተፈተለው መታጠቂያ በተመሳሳይ መልክ ሆኖ እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው፣ ከኤፉዱ ጋራ አንድ ወጥ የሆነና ከወርቅ፣ ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊና ከቀይ ማግ፣ በቀጭኑ ከተፈተለ ሐር የተሠራ ነበረ።
6.የከበሩ መረግዶችን በወርቅ ፈርጦች በመክፈፍ፣ እንደ ማኅተም የእስራኤልን ልጆች ስሞች ቀረጹባቸው።
7.ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው በኤፉዱ የትከሻ ንጣዮች ላይ ለእስራኤል ልጆች እንደ መታሰቢያ ድንጋዮች አያያዟቸው።
የደረት ኪስ
39፥8-21 ተጓ ምብ – ዘፀ 28፥15-28
8.የደረት ኪሱንም ጥበበኛ ባለሙያ እንደሚሠራው ሥራ በተመሳሳይ መንገድ ሠሩት፤ እንደ ኤፉዱም ከወርቅ፣ ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊና ከቀይ ማግ በቀጭኑም ከተፈተለ በፍታ ሠሩት።
9.ርዝመቱ አንድ ስንዝር ወርዱም አንድ ስንዝር ሲሆን፣ ጥንድ ድርብ ሆኖ ባለአራት ማእዘን ነበረ።
10.ከዚያም የከበሩ ድንጋዮችን በአራት ረድፍ በላዩ ላይ አደረጉበት፤ በመጀመሪያው ረድፍ ሰርድዮን፣ ቶጳዝዮንና የሚያብረቀርቅ ዕንቍ ነበር፤
11.በሁለተኛውም ረድፍ በሉር፣ ሰንፔርና አልማዝ፣
12.በሦስተኛውም ረድፍ ያክንት፣ ኬልቄዶንና አሜቴስጢኖስ፣
13.በአራተኛውም ረድፍ ቢረሌ፣ መረግድና ኢያሰጲድ ነበረ፤ በወርቅ ፈርጥ ላይ ተደርገው ነበር።
14.ለእያንዳንዱ የእስራኤል ልጆች ስም አንዳንድ ሆኖ፣ በእያንዳንዱ ላይ እንደ ማኅተም ከዐሥራ ሁለቱ ነገዶች የአንዱ ስም የተቀረጸበት ዐሥራ ሁለት ድንጋዮች ነበሩ።
15.ለደረት ኪሱም ልክ እንደ ገመድ ከንጹሕ ወርቅ የተጐነጐኑ ድሪዎችን አበጁለት።
16.ሁለት የወርቅ ፈርጦችንና ሁለት የወርቅ ቀለበቶችን ሠርተው ቀለበቶቹን ከደረት ኪሱ ሁለት ጐኖች ጋራ አያያዟቸው።
17.ሁለቱን የወርቅ ድሪዎች በደረት ኪሱ ጐንና ጐን ካሉት ቀለበቶች ጋራ አያያዟቸው፤
18.የድሪዎቹን ሌሎች ጫፎች ከፊት ካለው ከኤፉዱ የትከሻ ንጣዮች ጋራ በማገናኘት ከሁለቱ የወርቅ ፈርጦች ጋራ አያያዟቸው።
19.ሁለት የወርቅ ቀለበቶችን ሠርተው ከኤፉዱ ቀጥሎ ካሉት ከሌሎቹ ሁለት የደረት ኪስ ጐኖች ጋራ ከውስጠኛው ጠርዝ ላይ አያያዟቸው።
20.ከዚያም ሁለት ተጨማሪ የወርቅ ቀለበቶችን ሠርተው ልክ ከኤፉዱ መታጠቂያ በላይ፣ ከመጋጠሚያው አጠገብ፣ ከኤፉዱ ፊት ለፊት ካሉት ከትከሻ ንጣዮች ጋራ አያያዟቸው።
21.እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው የደረት ኪሱ ከኤፉዱ ተነጥሎ ለብቻው እንዳይንጠለጠል የደረት ኪሱን ቀለበቶች ከመታጠቂያው ጋራ በማገናኘት፣ ከኤፉዱ ቀለበቶች ጋራ በሰማያዊ ፈትል አሰሯቸው።
ሌሎች የካህናት አልባሳት
39፥22-31 ተጓ ምብ – ዘፀ 28፥31-43
22.የኤፉዱን ቀሚስ በሸማኔ ሥራ ሙሉ በሙሉ ከሰማያዊ ጨርቅ ሠሩት፤
23.ይህም እንደ ክሳዱ ቅድ ከቀሚሱ መካከል ላይ ዐንገትጌ ነበረው፤ እንዳይተረተርም በዐንገትጌው ዙሪያ ላይ ቅምቅማት ነበረው።
24.በቀሚሱ ጠርዝ ዙሪያ ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊና ከቀይ ማግ እንዲሁም በቀጭኑ ከተፈተለ በፍታ ላይ ሮማኖቹን አደረጉ።
25.ከንጹሕ ወርቅም ሻኵራዎችን ሠሩ፤ እነዚህንም በሮማኖቹ መካከል በጠርዙ ዙሪያ አደረጉ።
26.እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው ለአገልግሎት ይለበሱ ዘንድ ሻኵራዎቹና ሮማኖቹ በቀሚሱ ጠርዝ ዙሪያ ላይ ተሰባጥረው ይገኙ ነበር።
27.ለአሮንና ለወንዶች ልጆቹ የሸማኔ ሥራ የሆነውን ከቀጭን በፍታ ሸሚዞችን ሠሩ፤
28.እንዲሁም ከቀጭን በፍታ ጥምጥምን፣ የሐር ቆቦቹንና በቀጭኑ ከተፈተለም በፍታ ሱሪዎችን ሠሩ።
29.መታጠቂያው እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው በቀጭኑ ከተፈተለ በፍታና ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊና ከቀይ ማግ፣ የጥልፍ ጠላፊ ሥራ ሆኖ የተሠራ ነበረ።
30.ከንጹሕ ወርቅ የተቀደሰውን አክሊል ሰሌዳ ሠርተው፣ በማኅተም ላይ እንደ ተቀረጸ ጽሑፍ፤ቅዱስ ለእግዚአብሔር
የሚል ቀረጹበት። 31.ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው ከመጠምጠሚያው ጋራ ለማያያዝ ሰማያዊ ፈትል አሰሩበት።
ሙሴ የማደሪያውን ድንኳን መቈጣጠሩ
39፥32-41 ተጓ ምብ – ዘፀ 35፥10-19
32.በዚህ መሠረት የማደሪያው ድንኳን፣ የመገናኛው ድንኳን ሥራ በሙሉ ተጠናቀቀ። እስራኤላውያን ልክ እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው ሁሉን ነገር ሠሩ።
33.ከዚያም የማደሪያውን ድንኳን ወደ ሙሴ አመጡት፦እነዚህም ድንኳንና ዕቃዎቹ ሁሉ፣ ማያያዣዎችን፣ ክፈፎችን፣ አግዳሚዎችን፣ ቋሚዎችንና መሠረቶችን፤ 34.ቀይ ከተነከረ የአውራ በግ ቈዳ የተሠራ መደረቢያ፣ የለፋ የአቆስጣ ቈዳ መደረቢያና መከለያ መጋረጃ፤ 35.የምስክሩ ታቦት፣ ከመሎጊያዎቹና ከስርየት መክደኛው ጋራ፤ 36.ጠረጴዛውን ከነመሎጊያዎቹ ዕቃዎቹን ሁሉና ከገጸ ኅብስቱ ጋራ፤ 37.ከንጹሕ ወርቅ የሆነው መቅረዝ ከተደረደሩት መብራቶችና ከዕቃዎቹ ሁሉ ጋራ፣ የመብራቱም ዘይት፤ 38.የወርቅ መሠዊያው፣ ቅብዐ ዘይቱ፣ መልካም መዐዛ ያለው ዕጣን እንዲሁም የድንኳኑ መግቢያ መጋረጃ፤ 39.የንሓስ መሠዊያው ከንሓስ መጫሪያው፣ መሎጊያዎቹና ዕቃዎቹ ሁሉ ጋራ፤
የመታጠቢያው ሳሕን ከነማስቀመጫው፤ 40.የአደባባዩ መጋረጃዎች ከምሰሶዎቹና ከመቆሚያዎቹ ጋራ፣ የአደባባዩ መግቢያ መጋረጃ፤
ገመዶቹና የአደባባዩ ድንኳን ካስማዎች፤
የማደሪያው የመገናኛው ድንኳን ዕቃዎች ሁሉ፤ 41.በመቅደሱ ሲያገለግሉ የሚለበሱት የተፈተሉት ቀሚሶች፣ ለካህኑ ለአሮን የተቀደሱት ቀሚሶችና ወንዶች ልጆቹ ካህናት ሆነው ሲያገለግሉ የሚያደርጓቸው ቀሚሶች ናቸው። 42.እስራኤላውያን ልክ እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው ሥራውን ሁሉ አከናወኑ። 43.ሙሴ ሥራውን አየ፤ ልክ እግዚአብሔር እንዳዘዘው መሥራታቸውንም ተመለከተ፤ ስለዚህ ባረካቸው።
ምዕራፍ 40
የማደሪያውን ድንኳን መትከል
1.ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን አለው፤ 2.“ማደሪያውን ይኸውም የመገናኛውን ድንኳን በወሩ የመጀመሪያ ቀን ትከለው፤ 3.የምስክሩን ታቦት በውስጡ አኑር፤ ታቦቱንም በመጋረጃው ጋርደው። 4.ጠረጴዛውንም ወደ ውስጥ አምጥተህ ዕቃዎቹን በላዩ ላይ አሰናዳ፤ ከዚያም መቅረዙን አስገብተህ መብራቶቹን በቦታቸው አስቀምጥ። 5.የዕጣኑን የወርቅ መሠዊያ በምስክሩ ታቦት ፊት ለፊት አስቀምጠው፤ ከማደሪያውም መግቢያ ላይ መጋረጃውን አድርግ። 6.“የሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያውን በማደሪያው መግቢያ ፊት ለፊት፣ በመገናኛው ድንኳን አስቀምጠው። 7.የመታጠቢያውን ሰን በመገናኛው ድንኳንና በመሠዊያው መካከል አኑርበት፤ ውሃም አኑርበት። 8.በዙሪያውም የአደባባዩን ቅጥር ትከል፤ መጋረጃውንም በአደባባዩ መግቢያ ላይ አድርገው። 9.“ቅብዐ ዘይቱን ወስደህ ማደሪያውንና በውስጡ ያለውን ሁሉ ቅባ፤ እርሱንና ዕቃውን ሁሉ ቀድስ፤ የተቀደሰም ይሆናል። 10.ከዚያም የሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያውንና ዕቃዎቹን ሁሉ ቅባ፤ መሠዊያውን ቀድስ፣ እጅግም የተቀደሰ ይሆናል። 11.የመታጠቢያው ሰንና ማስቀመጫውን ቅባ፤ ቀድሳቸውም። 12.“አሮንና ወንዶች ልጆቹን ወደ መገናኛው ድንኳን መግቢያ አምጥተህ በውሃ ዕጠባቸው። 13.ከዚያም አሮንን የተቀደሰውን ልብስ አልብሰው፤ ካህን ሆኖ ያገለግለኝ ዘንድ ቅባው፤ ቀድሰውም። 14.ወንዶች ልጆቹን አምጥተህ ሸሚዝ አልብሳቸው። 15.ካህናት ሆነው ያገለግሉኝ ዘንድ ልክ አባታቸውን እንደ ቀባህ ቅባቸው፤ መቀባታቸውም በሚመጡት ትውልዶች ሁሉ ለሚቀጥል ክህነት ነው።” 16.ሙሴ ሁሉንም ነገር ልክ እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ። 17.እንዲሁም በሁለተኛው ዓመት፣ የመጀመሪያው ወር በገባ በመጀመሪያው ቀን የማደሪያው ድንኳን ተተከለ። 18.ሙሴ የማደሪያውን ድንኳን በተከለ ጊዜ፣ መቆሚያዎቹን በቦታቸው አኖረ፤ ወጋግራዎቹን አቆመ፤ አግዳሚዎቹን አስገባ፤ ምሰሶዎቹንም ተከለ። 19.ከዚያም እግዚአብሔር እንዳዘዘው ድንኳኑን በማደሪያው ላይ፣ መደረቢያውንም በድንኳኑ ላይ ዘረጋው። 20.ምስክሩን ወስዶ በታቦቱ ውስጥ አስቀመጠው፤ መሎጊያዎቹንም ከታቦቱ ጋራ አያያዛቸው፤ የስርየት መክደኛውንም በላዩ ላይ አደረገው። 21.ከዚያም እግዚአብሔር እንዳዘዘው ታቦቱን ወደ ማደሪያው ድንኳን አስገብቶ መከለያ መጋረጃውን ሰቀለ፤ የምስክሩንም ታቦት ጋረደው። 22.ሙሴ ጠረጴዛውን በመገናኛው ድንኳን ውስጥ፣ ከማደሪያው በስተሰሜን ከመጋረጃው ውጭ አኖረው፤ 23.እግዚአብሔር እንዳዘዘውም ኅብስቱን በላዩ ላይ በእግዚአብሔር ፊት አኖረ። 24.መቅረዙን በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ከጠረጴዛው ትይዩ ከማደሪያው ድንኳን በስተ ደቡብ በኩል አኖረው፤ 25.እግዚአብሔር እንዳዘዘውም መብራቶቹን በእግዚአብሔር ፊት አበራ። 26.ሙሴ የወርቅ መሠዊያውን በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ከመጋረጃው ፊት ለፊት አኖረው፤ 27.እግዚአብሔር እንዳዘዘውም መልካም መዐዛ ያለውን ዕጣን አጠነበት። 28.ከዚያም መጋረጃውን በማደሪያው ድንኳን መግቢያ ላይ ሰቀለው። 29.የሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያውንም በማደሪያው፣ በመገናኛው ድንኳን መግቢያ ላይ አኖረው፤ እግዚአብሔር እንዳዘዘውም የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የእህሉን መሥዋዕት በላዩ ላይ አቀረበ። 30.የመታጠቢያውን ሰን በመገናኛው ድንኳንና በመሠዊያው መካከል አስቀመጠ፤ ለመታጠቢያም ውሃ አደረገበት፤ 31.ሙሴና አሮን፣ ወንዶች ልጆቹም እጆቻቸውንና እግሮቻቸውን ይታጠቡበት ነበር። 32.እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው ወደ መገናኛው ድንኳን በገቡና ወደ መሠዊያው በቀረቡ ቍጥር ይታጠቡ ነበር። 33.ከዚያም ሙሴ በማደሪያውና በመሠዊያው ዙሪያ አደባባዩን ተከለ፤ በአደባባዩም መግቢያ ላይ መጋረጃውን ሰቀለ፤ እንደዚህ አድርጎ ሙሴ ሥራውን ፈጸመ።የእግዚአብሔር ክብር
34.ከዚያም ደመናው የመገናኛውን ድንኳን ሸፈነ፤ የእግዚአብሔርም ክብር ማደሪያውን ሞላ። 35.ደመናው በላዩ ላይ ስለ ነበረና የእግዚአብሔርም ክብር ማደሪያውን ስለ ሞላው፣ ሙሴ ወደ መገናኛው ድንኳን መግባት አልቻለም። 36.በእስራኤላውያን ጕዞ ሁሉ ደመናው ከማደሪያው ላይ በተነሣ ጊዜ፣ ይጓዙ ነበር፤ 37.ደመናው ካልተነሣ ግን፣ እስከሚነሣበት ቀን ድረስ አይጓዙም ነበር። 38.ስለዚህ በጕዟቸው ሁሉ ወቅት፣ በእስራኤል ቤት ፊት ሁሉ የእግዚአብሔር ደመና በቀን ከማደሪያው በላይ፣ በሌሊትም እሳቱ በደመናው ውስጥ ነበር።ወደ ዕብራውያን
ምዕራፍ 1
የእግዚአብሔር የመጨረሻ ቃል–ልጁ
1.እግዚአብሔር ከጥንት ጀምሮ በተለያየ ጊዜና በልዩ ልዩ መንገድ በነቢያት በኩል ለአባቶቻችን ተናግሮ፣ 2.በዚህ መጨረሻ ዘመን ግን ሁሉን ወራሽ ባደረገውና ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ ለእኛ ተናገረን። 3.እርሱ የእግዚአብሔር ክብር ነጸብራቅና የባሕርዩ ትክክለኛ ምሳሌ ሆኖ፣ በኀያል ቃሉ ሁሉን ደግፎ ይዟል። የኀጢአት መንጻት ካስገኘ በኋላ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ። 4.ስለዚህ የወረሰው ስም ከመላእክት ስም እንደሚበልጥ ሁሉ፣ እርሱም ከመላእክት እጅግ የላቀ ሆኗል። 5.እግዚአብሔር፣“አንተ ልጄ ነህ፤
እኔ ዛሬ ወለድሁህ፤”
ወይስ ደግሞ፣
“እኔ አባት እሆነዋለሁ፤
እርሱም ልጄ ይሆናል”
ያለው ከመላእክት ከቶ ለማን ነው? 6.ደግሞም እግዚአብሔር በኵሩን ወደ ዓለም ሲያስገባ፣
“የእግዚአብሔር መላእክት ሁሉ ይስገዱለት”
ይላል። 7.ስለ መላእክትም ሲናገር፣
“መላእክቱን ነፋሳት፣
አገልጋዮቹንም የእሳት ነበልባል ያደርጋል”
ይላል። 8.ስለ ልጁ ግን እንዲህ ይላል፤
“አምላክ ሆይ፤ ዙፋንህ ከዘላለም እስከ ዘላለም ጸንቶ ይኖራል፤
የመንግሥትህ በትር የቅንነት በትር ይሆናል። 9.ጽድቅን ወደድህ፤ ዐመፃን ጠላህ፤
ስለዚህ እግዚአብሔር አምላክህ ከባልንጀሮችህ በላይ አስቀመጠህ፣
የደስታንም ዘይት ቀባህ።” 10.ደግሞም እንዲህ ይላል፤
“ጌታ ሆይ፤ አንተ
በመጀመሪያ የምድርን መሠረት አኖርህ፤
ሰማያትም የእጆችህ ሥራ ናቸው። 11.እነርሱ ይጠፋሉ፤ አንተ ግን ጸንተህ ትኖራለህ፤
ሁሉም እንደ ልብስ ያረጃሉ፤ 12.እንደ መጐናጸፊያ ትጠቀልላቸዋለህ፤
እንደ ልብስም ይለወጣሉ።
አንተ ግን ያው አንተ ነህ፤
ዘመንህም ፍጻሜ የለውም።” 13.እግዚአብሔር፣
“ጠላቶችህን ለእግርህ መረገጫ እስከማደርግልህ ድረስ፣
በቀኜ ተቀመጥ”
ያለው ከመላእክት ከቶ ለማን ነው? 14.መላእክት ሁሉ መዳንን የሚወርሱትን ለማገልገል የሚላኩ አገልጋይ መናፍስት አይደሉምን?