ሳምንት 7 · ቀን 33 (ረቡዕ)
📅 Tikimt 18, 2019
ኦሪት ዘጸአት 38, 39, 40 · ወደ ዕብራውያን 1
ኦሪት ዘጸአት
ምዕራፍ 38
1.ርዝመቱ አምስት ክንድ፥ ወርዱም አምስት ክንድ ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆን መሠዊያን ከግራር እንጨት አደረገ፤ አራት ማዕዘንም ነበረ፤ ከፍታው ሦስት ክንድ ነበረ።
2.ቀንዶቹንም በአራቱ ማዕዘን አደረገበት፤ ቀንዶቹም ከእርሱ ጋር በአንድ የተሠሩ ነበሩ፤ በናስም ለበጠው።
3.የመሠዊያውንም ዕቃ ሁሉ፥ ምንቸቶቹንም፥ መጫሪያዎቹንም፥ ድስቶቹንም፥ ሜንጦቹንም፥ ማንደጃዎቹንም አደረገ፤ ዕቃውንም ሁሉ ከናስ አደረገ።
4.እንደ መረብ ሆኖም የተሠራ የናስ መከታ ለመሠዊያ አደረገ፤ መከታውም እስከ መሠዊያው እኩሌታ ይደርስ ዘንድ በመሠዊያው በሚዞረው በደረጃው ታች አደረገው።
5.ለናሱም መከታ ለአራቱ ማዕዘን የመሎጊያዎች ስፍራ ይሆኑ ዘንድ አራት ቀለበቶች አደረገ።
6.መሎጊያዎቹንም ከግራር እንጨት ሠራ፥ በናስም ለበጣቸው።
7.ይሸከሙትም ዘንድ በመሠዊያ ጎን ባሉት ቀለበቶች ውስጥ መሎጊያዎቹን አገባ፤ ከሳንቆቹም ሠርቶ ባዶ አደረገው።
8.የመታጠቢያውን ሰንና መቀመጫውንም በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ከሚያገለግሉ ከሴቶች መስተዋት ከናስ አደረገ።
9.አደባባዩንም አደረገ፤ በደቡብ ወገን ርዝመቱ መቶ ክንድ የሆነ፥ የተፈተለ የጥሩ በፍታ መጋረጆች ነበሩ።
10.ከናስ የተሠሩ ሀያውን ምሰሶችና ሀያውን እግሮች አደረገ፤ የምሰሶቹንም ኩላቦችና ዘንጎች ከብር አደረገ።
11.በሰሜኑም ወገን መቶ ክንድ ርዝመት ያላቸውን መጋረጆች፥ ከናስም የተሠራ ሀያ ምሰሶችንና ሀያ እግሮችን፥ ለምሰሶቹም የብር ኩላቦችንና ዘንጎችን አደረገ።
12.በምዕራብም ወገን አምሳ ክንድ ርዝመት ያላቸውን መጋረጆች፥ አሥሩንም ምሰሶች፥ አሥሩንም የናስ እግሮች፥ ለምሰሶቹም የብር ኩላቦችንና ዘንጎችን አደረገ።
13.በምሥራቅም ወገን አምሳ ክንድ ርዝመት ያላቸውን መጋረጆች አደረገ።
14.በአንድ ወገንም የመጋረጆቹ ርዝመት አሥራ አምስት ክንድ፥ ምሰሶቹም ሦስት፥ እግሮቹም ሦስት ነበሩ።
15.እንዲሁም በሁለተኛው ወገን በአደባባዩ ደጅ በዚህና በዚያ አሥራ አምስት ክንድ ርዝመት ያላቸው መጋረጆች፥ ሦስትም ምሰሶች፥ ሦስትም እግሮች ነበሩ።
16.በአደባባዩ ዙሪያ ያሉ መጋረጆች ሁሉ ከተፈተለ ከጥሩ በፍታ ተሠርተው ነበር።
17.የምሰሶቹም እግሮች የናስ፥ የምሰሶቹም ኩላቦችና ዘንጎች የብር ነበሩ፤ የምሰሶችም ጕልላቶች በብር ተለብጠው ነበር፤ በአደባባዩ ላሉ ምሰሶች ሁሉ የብር ዘንጎች ነበሩአቸው።
18.የአደባባዩም ደጅ መጋረጃ ከሰማያዊ ከሐምራዊም ከቀይም ግምጃ፥ ከጥሩም በፍታ በጥልፍ አሠራር የተሠራ ነበረ፤ ርዝመቱ ሀያ ክንድ ነበረ፥ ቁመቱም እንደ አደባባዩ መጋረጆች አምስት ክንድ ነበረ፤
19.ከናስ የተሠሩ ምሰሶቹም አራት፥ እግሮቹም አራት ነበሩ፤ ኩላቦቹ የብር ነበሩ፤ ጕልላቶቹና ዘንጎቹም በብር ተለብጠው ነበር።
20.የማደሪያውም ካስማዎች በዙሪያውም ያለ የአደባባዩ ካስማዎች የናስ ነበሩ።
21.በሙሴ ትእዛዝ ለሌዋውያን ማገልገል ሊሆን በካህኑ በአሮን ልጅ በኢታማር እጅ እንደ ተቈጠረው የማደሪያው፥ የምስክሩ ማደሪያ፥ ዕቃ ድምር ይህ ነው።
22.ከይሁዳ ነገድም የሆነ የሆር የልጅ ልጅ፥ የኡሪ ልጅ ባስልኤል እግዚአብሔር ለሙሴ ያዘዘውን ሁሉ አደረገ።
23.ከእርሱም ጋር ከዳን ነገድ የሆነ የአሂሳሚክ ልጅ ኤልያብ ነበረ፤ እርሱም የቅርጽ ሠራተኛና ብልህ ሠራተኛ፥ በሰማያዊ በሐምራዊም በቀይም ግምጃ፥ በጥሩም በፍታ የሚሠራ ጠላፊ ነበረ።
24.የተሰጠው ወርቅ ሁሉ፥ በመቅደሱ ሥራ ሁሉ የተደረገው ወርቅ፥ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን ሀያ ዘጠኝ መክሊት ሰባት መቶ ሠላሳ ሰቅል ነበረ።
25.በማኅበሩም ከሚቈጠሩት የተገኘ ብር፥ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን፥ መቶ መክሊትና አንድ ሺህ ሰባት መቶ ከሰባ አምስት ሰቅል ነበረ።
26.እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን፥ የሰቅል ግማሽ ከተቈጠረው ከእያንዳንዱ ሰው የተሰጠ ነው፤ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ የተቈጠሩት ሁሉ ስድስት መቶ ሦስት ሺህ አምስት መቶ አምሳ ሰዎች ነበሩ።
27.መቶውም የብር መክሊት የመቅደሱንና የመጋረጃውን እግሮች ለመሥራት ነበረ፤ ከመቶውም መክሊት መቶ እግሮች አደረገ፤ ለአንድ እግርም አንድ መክሊት ነበረ።
28.ከሺህ ሰባት መቶ ሰባ አምስት ሰቅል የምሰሶቹን ኩላቦችና ዘንጎች አደረገ፥ የምሰሶቹንም ጕልላቶች ለበጠ።
29.የተሰጠውም ናስ ሰባ መክሊትና ሁለት ሺህ አራት መቶ ሰቅል ነበረ።
30.ከእርሱም የመገናኛውን ድንኳን ደጃፍ እግሮች፥ የናሱንም መሠዊያ፥ ለእርሱም የሆነውን የናሱን መከታ፥ የመሠዊያውንም ዕቃ ሁሉ፥
31.በአደባባዩ ዙሪያ ያሉትን እግሮች፥ የአደባባዩንም ደጃፍ እግሮች፥ የማደሪያውንም ካስማዎች ሁሉ በአደባባዩ ዙሪያም ያሉትን ካስማዎች ሁሉ አደረገ።
ምዕራፍ 39
1.እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው፥ በመቅደሱ ለማገልገል ከሰማያዊ ከሐምራዊም ከቀይ ግምጃም በብልሃት የተሠራ ልብስ፥ ለአሮንም የተቀደሰውን ልብስ አደረጉ።
2.እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው፥ ኤፉዱን ከወርቅ ከሰማያዊም ከሐምራዊም ከቀይ ግምጃም ከተፈተለም ከጥሩ በፍታ አደረገ።
3.ወርቁንም ቀጥቅጠው እንደ ቅጠል ስስ አድርገው እንደ ፈትል ቈረጡ። ብልህ ሠራተኛም እንደሚሠራ ሰማያዊ ሐምራዊም ቀይም ግምጃ የተፈተለም ጥሩ በፍታ ከእርሱ ጠለፉ።
4.ሁለቱ ወገን እንዲጋጠም በሁለቱ ጫንቃዎች ላይ የሚጋጠም ልብስ አደረጉት።
5.በላዩም መታጠቂያ ሆኖ በብልሃት የተጠለፈው የኤፉዱ ቋድ እንደ እርሱ ከእርሱም ጋር አንድ ነበረ፤ ከወርቅና ከሰማያዊ ከሐምራዊ ከቀይ ግምጃም ከተፈተለም ከጥሩ በፍታ የተሠራ ነበረ።
6.እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው፥ በወርቅ ፈርጥ የተያዙ የመረግድ ድንጋዮች ሠርተው እንደ ማኅተም ቅርጽ የእስራኤልን ልጆች ስም ቀረጹባቸው።
7.ለእስራኤል ልጆች የመታሰቢያ ድንጋዮች ይሆኑ ዘንድ በኤፉዱ ጫንቃዎች ላይ አደረጋቸው።
8.እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው፥ የደረቱን ኪስ ብልህ ሠራተኛ እንደሚሠራ እንደ ኤፉዱ አሠራር ከወርቅና ከሰማያዊ ከሐምራዊም ከቀይም ግምጃ ከተፈተለም ከጥሩ በፍታ አደረገው።
9.አራት ማዕዘንም ነበረ፤ የደረቱን ኪስም ድርብ አደረጉ፤ ርዝመቱ ስንዝር፥ ወርዱም ስንዝር፥ ድርብም ነበረ።
10.ዕንቍዎቹንም በአራት ተራ አደረጉበት፤ በፊተኛውም ተራ ሰርድዮን፥ ቶጳዝዮን፥ የሚያብረቀርቅ ዕንቍ፤
11.በሁለተኛውም ተራ በሉር፥ ሰንፔር፥ አልማዝ፤
12.በሦስተኛውም ተራ ያክንት፥ ኬልቄዶን፥ አሜቴስጢኖስ፤
13.በአራተኛውም ተራ ቢረሌ፥ መረግድ፥ ኢያስጲድ በወርቅ ፈርጥ ተደረጉ።
14.የዕንቍዎችም ድንጋዮች እንደ አሥራ ሁለቱ እንደ እስራኤል ልጆች ስሞች ነበሩ፤ በየስማቸውም ማተሚያ እንደሚቀረጽ ተቀረጹ፥ ስለ አሥራ ሁለቱም ነገዶች ነበሩ።
15.ለደረቱ ኪስም የተጐነጐኑትን ድሪዎች እንደ ገመድ አድርገው ከጥሩ ወርቅ ሠሩ።
16.ሁለትም የወርቅ ፈርጦች፥ ሁለትም የወርቅ ቀለበቶች ሠሩ፤ ሁለቱንም ቀለበቶች በደረቱ ኪስ በሁለቱ ወገን አደረጉ።
17.ሁለቱንም የተጐነጐኑትን የወርቅ ድሪዎች በደረቱ ኪስ ወገኖች ወዳሉት ወደ ሁለቱ ቀለበቶች አገቡ።
18.የሁለቱንም ድሪዎች ጫፎች በሁለቱ ፈርጦች ውስጥ አግብተው በኤፉዱ ጫንቃዎች ላይ በፊታቸው አደረጉ።
19.ሁለቱንም የወርቅ ቀለበቶች ሠሩ፥ እነርሱንም በኤፉዱ ፊት ለፊት ባለው በደረቱ ኪስ በሁለት ጫፎቹ ላይ አደረጉአቸው።
20.ደግሞም ሁለት የወርቅ ቀለበቶች ሠሩ፥ በኤፉዱም ፊት፥ ከጫንቃዎች በታች፥ በብልሃት ከተጠለፈ ከኤፉዱ ቋድ በላይ፥ በመያዣው አጠገብ አደረጉአቸው።
21.የደረቱ ኪስ በብልሃት ከተጠለፈው ከኤፉዱ ቋድ በላይ እንዲሆን፥ ከኤፉዱም እንዳይለይ የደረቱን ኪስ ከቀለበቶቹ ጋር ወደ ኤፉዱ ቀለበቶች በሰማያዊ ፈትል አሰሩት።
22.እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው፥ የኤፉዱን ቀሚስ ሞላውን በሸማኔ ሥራ ሰማያዊ አደረገው።
23.በቀሚሱም መካከል አንገትጌ ነበረ፤ እንዳይቀደድም እንደ ጥሩር የተሠራ ጥልፍ በአንገትጌው ዙሪያ ነበረ።
24.በቀሚሱም ታችኛ ዘርፍ ከሰማያዊ ከሐምራዊም ከቀይም ግምጃ፥ ከተፈተለ በፍታም ሮማኖች አደረጉ።
25.ከጥሩ ወርቅም ሻኵራዎችን ሠሩ፥ ሻኵራዎቹንም ከሮማኖች መካከል በቀሚሱ ዘርፍ ዙሪያ አደረጉ።
26.በቀሚሱ ዘርፍ ዙሪያ ሻኵራንና ሮማንን፥ ሻኵራንና ሮማንን ለማገልገል አደረጉ።
27.እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው፥ እንደ ሸማኔ ሥራ ከጥሩ በፍታ ለአሮንና ለልጆቹ ሸሚዞችን፥
28.ከጥሩ በፍታም መጠምጠሚያውን፥ ከጥሩ በፍታም መልካሞቹን ቆቦች፥ ከተፈተለም ከጥሩ በፍታ የእግር ሱሪዎችን፥
29.ከተፈተለም ከጥሩ በፍታ፥ ከሰማያዊም ከሐምራዊም ከቀይም ግምጃ በጥልፍ አሠራር የተሠራ መታጠቂያውን አደረጉ።
30.እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው፥ ከጥሩ ወርቅ የተቀደሰውን የአክሊል ምልክት ሠሩ፤ በእርሱም እንደ ማኅተም ቅርጽ አድርገው። ቅድስና ለእግዚአብሔር የሚል ጻፉበት።
31.በመጠምጠሚያውም ላይ ያንጠለጥሉት ዘንድ ሰማያዊውን ፈትል አሰሩበት።
32.እንዲሁም የመገናኛው ድንኳን የማደሪያው ሥራ ሁሉ ተጨረሰ። እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው ሁሉ የእስራኤል ልጆች አደረጉ፤ እንዲሁ አደረጉ።
33.ማደሪያውንም፥ ድንኳኑንም፥ ዕቃውንም ሁሉ ወደ ሙሴ አመጡ፤ መያዣዎቹን፥ ሳንቆቹን፥ መወርወሪያዎቹን፥ ምሰሶቹንም፥ እግሮቹንም፤
34.ከቀይ ከአውራ በግ ቁርበትም የተሠራ መደረቢያ፥ ከአቆስጣ ቁርበትም የተሠራ መደረቢያ፥ የሚሸፍነውንም መጋረጃ፤
35.የምስክሩንም ታቦት፥ መሎጊያዎቹንም፥ የስርየት መክደኛውንም፤
36.ገበታውንም፥ ዕቃውንም ሁሉ፥ የገጹንም ኅብስት፤
37.ጥሩውንም መቅረዝ፥ መብራቶቹንም፥ በተራ የሚሆኑትንም ቀንዲሎች፥ ዕቃውንም ሁሉ፥ የመብራቱንም ዘይት፤
38.የወርቁንም መሠዊያ፥ የቅብዓቱንም ዘይት፥ ጣፋጩንም ዕጣን፥ የድንኳኑንም ደጃፍ መጋረጃ፤
39.የናሱንም መሠዊያ፥ የናሱንም መከታ፥ መሎጊያዎቹንም፥ ዕቃውንም ሁሉ፥ የመታጠቢያውን ሰንም መቀመጫውንም፤
40.የአደባባዩንም መጋረጆች፥ ምሰሶቹንም፥ እግሮቹንም፥ የአደባባዩንም ደጃፍ መጋረጃ፥ አውታሮቹንም፥ ካስማዎቹንም፥ ለመገናኛው ድንኳን ለማደሪያው ማገልገያ የሚሆኑን ዕቃዎች ሁሉ፤
41.በመቅደስ ውስጥ ለማገልገል በብልሃት የተሠሩትን ልብሶች፥ በክህነትም ያገለግሉበት ዘንድ የተቀደሱትን የካህኑን የአሮንን ልብሶች፥ የልጆቹንም ልብሶች አመጡ።
42.እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘ ሁሉ እንዲሁ የእስራኤል ልጆች ሥራውን ሁሉ ሠሩ።
43.ሙሴም ሥራውን ሁሉ አየ፥ እነሆም አድርገውት ነበር፤ እግዚአብሔር እንዳዘዘው እንዲሁ አድርገውት ነበር፤ ሙሴም ባረካቸው።
ምዕራፍ 40
1.እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው።
2.ከመጀመሪያው ወር በፊተኛው ቀን የመገናኛውን ድንኳን ማደሪያ ትተክላለህ።
3.በእርሱም ውስጥ የምስክሩን ታቦት ታኖራለህ፥ ታቦቱንም በመጋረጃ ትጋርዳለህ።
4.ገበታውንም አግብተህ በእርሱ ላይ የሚኖረውን ዕቃ ታሰናዳለህ፤ መቅረዙንም አግብተህ ቀንዲሎቹን ትለኵሳለህ።
5.ለዕጣንም የሚሆነውን የወርቅ መሠዊያ በምስክሩ ታቦት ፊት ታኖራለህ፥ በማደሪያውም ደጃፍ ፊት መጋረጃውን ትጋርዳለህ።
6.ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነውንም መሠዊያ በመገናኛው ድንኳን በማደሪያው ደጅ ፊት ታኖረዋለህ።
7.የመታጠቢያውን ሰንም በመገናኛው ድንኳንና በመሠዊያው መካከል አኑረህ ውኃ ትጨምርበታለህ።
8.በዙሪያውም አደባባዩን ትተክላለህ፥ የአደባባዩንም ደጃፍ መጋረጃ ትዘረጋለህ።
9.የቅብዓቱንም ዘይት ወስደህ ማደሪያውን በእርሱም ያለውን ሁሉ ትቀባለህ፥ እርሱንም ዕቃውንም ሁሉ ትቀድሳለህ፤ ቅዱስም ይሆናል።
10.ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነውንም መሠዊያ ዕቃውንም ሁሉ ትቀባዋለህ፥ መሠዊያውንም ትቀድሳለህ፤ መሠዊያውም ቅድስተ ቅዱሳን ይሆናል።
11.የመታጠቢያውን ሰንና መቀመጫውን ቀብተህ ትቀድሳለህ።
12.አሮንንና ልጆቹንም ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ አቅርበህ በውኃ ታጥባቸዋለህ።
13.የተቀደሰውንም ልብስ አሮንን ታለብሰዋለህ፤ በክህነትም ያገለግለኝ ዘንድ ቀብተህ ትቀድሰዋለህ።
14.ልጆቹንም አቅርበህ ሸሚዞችን ታለብሳቸዋለህ፤
15.በክህነትም ያገለግሉኝ ዘንድ አባታቸውን እንደ ቀባህ ትቀባቸዋለህ፤ መቀባታቸውም ለልጅ ልጃቸው ለዘላለም ክህነት ይሆንላቸዋል።
16.ሙሴም እንዲሁ አደረገ፤ እግዚአብሔር እንዳዘዘው ሁሉ እንዲሁ አደረገ።
17.እንዲህም ሆነ፤ በሁለተኛው ዓመት በፊተኛው ወር በመጀመሪያው ቀን ማደሪያው ተተከለ።
18.እግዚአብሔርም እንዳዘዘው ሙሴ ማደሪያውን ተከለ፥ እግሮቹንም አኖረ፥ ሳንቆቹንም አቆመ፥ መወርወሪያዎቹንም አደረገባቸው፥ ምሰሶቹንም አቆመ።
19.ድንኳኑንም በማደሪያው ላይ ዘረጋ፥ የድንኳኑን መደረቢያ በላዩ አደረገበት።
20.እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው ጽላቱን ወስዶ በታቦቱ ውስጥ አኖረው፥ መሎጊያዎቹን በታቦቱ ዘንድ አደረገ፥ የስርየት መክደኛውንም በታቦቱ ላይ አኖረው፤
21.ታቦቱን ወደ ማደሪያው አገባ፥ የሚሸፍነውንም መጋረጃ አድርጎ የምስክሩን ታቦት ሸፈነ።
22.እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው ገበታውን በመገናኛው ድንኳን ውስጥ፥ ከመጋረጃው ውጭ፥ በማደሪያው በሰሜን በኩል አኖረው፤
23.እንጀራውን በላዩ በእግዚአብሔር ፊት አሰናዳ።
24.እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው መቅረዙን በመገናኛው ድንኳን ውስጥ፥ በገበታው ፊት ለፊት፥ በማደሪያው በደቡብ በኩል አኖረ፤
25.ቀንዲሎቹን በእግዚአብሔር ፊት ለኰሰ።
26.እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው የወርቁን መሠዊያ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በመጋረጃው ፊት አኖረ፤
27.የጣፋጩን ሽቱ ዕጣን ዐጠነበት።
28.እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው በማደሪያው ደጃፍ ፊት መጋረጃውን ዘረጋ።
29.ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነውን መሠዊያ በመገናኛው ድንኳን በማደሪያው ደጅ ፊት አኖረ፥ የሚቃጠለውንና የእህልን መሥዋዕት ሠዋበት።
30.እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው የመታጠቢያውን ሰን በመገናኛው ድንኳንና በመሠዊያው መካከል አኖረ፥ ለመታጠቢያም ውኃን ጨመረበት።
31.በእርሱም ሙሴና አሮን ልጆቹም እጆቻቸውንና እግሮቻቸውን ታጠቡ፤
32.ወደ መገናኛው ድንኳን በገቡ ጊዜ፥ ወደ መሠዊያውም በቀረቡ ጊዜ ይታጠቡ ነበር።
33.በማደሪያውና በመሠዊያውም ዙሪያ አደባባዩን ተከለ፤ የአደባባዩንም ደጃፍ መጋረጃ ዘረጋ። እንዲሁም ሙሴ ሥራውን ፈጸመ።
34.ደመናውም የመገናኛውን ድንኳን ከደነ፥ የእግዚአብሔርም ክብር ማደሪያውን ሞላ።
35.ደመናውም በላዩ ስለ ነበረ የእግዚአብሔርም ክብር ማደሪያውን ስለ ሞላ ሙሴ ወደ መገናኛው ድንኳን ይገባ ዘንድ አልቻለም።
36.ደመናውም ከማደሪያው በተነሣ ጊዜ የእስራኤል ልጆች በመንገዳቸው ሁሉ ይጓዙ ነበር።
37.ደመናው ባይነሣ እስከሚነሣበት ቀን ድረስ አይጓዙም ነበር።
38.በመንገዳቸውም ሁሉ በእስራኤል ቤት ሁሉ ፊት የእግዚአብሔር ደመና በማደሪያው ላይ በቀን ነበረና፥ እሳትም በሌሊት በዚያ ላይ ነበረና።