ሳምንት 7 · ቀን 32 (ማክሰኞ)
📅 Tikimt 17, 2019
ኦሪት ዘጸአት 35, 36, 37 · መዝሙረ ዳዊት 26 · ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 4
ኦሪት ዘጸአት
ምዕራፍ 35
የሰንበት ሥርዐቶች
1.ሙሴ የእስራኤልን ማኅበረ ሰብ ሁሉ ሰብስቦ እንዲህ አላቸው፤ “እግዚአብሔር እንድትፈጽሟቸው ያዘዛችሁ ነገሮች እነዚህ ናቸው፤ 2.ስድስት ቀን ሥራ ይሠራል፤ ሰባተኛው ቀን ግን ለእግዚአብሔር የሰንበት ዕረፍት፣ የተቀደሰ ቀን ይሆንላችኋል፤ በዕለቱ ማንኛውንም ዐይነት ሥራ የሚሠራ ቢኖር ሞት ይገባዋል። 3.በሰንበት ቀን በማናቸውም መኖሪያዎቻችሁ ውስጥ እሳት አታንድዱ።”ለመገናኛው ድንኳን ዕቃዎች
35፥4-9 ተጓ ምብ – ዘፀ 25፥1-7
35፥10-19 ተጓ ምብ – ዘፀ 39፥32-41
4.ሙሴ ለእስራኤላውያን ማኅበረ ሰብ ሁሉ እንዲህ አላቸው፤ “እግዚአብሔር ያዘዘው ይህ ነው፤
5.ካላችሁ ንብረት ሁሉ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አቅርቡ፤ ፈቃደኛ የሆነ ማንም ለእግዚአብሔር፦“የወርቅ፣ የብር፣ የናስ መባ ያምጣ። 6.ሰማያዊ፣ ሐምራዊና ቀይ ማግ፤ ቀጭን ሐር፣
የፍየል ጠጕር፣ 7.ቀይ የተነከረ የአውራ በግ ቈዳ፣ እንዲሁም የለፋ ቈዳ፣
የግራር ዕንጨት፤ 8.ለመብራት የወይራ ዘይት፣
ለቅብዐ ዘይቱና ለጣፋጭ መዐዛ ላለው ዕጣን የሚሆኑ ቅመሞች፤ 9.በኤፉዱና በደረት ኪስ ላይ የሚሆኑ መረግዶችና ሌሎች ዕንቍዎችን መባ አድርጎ ያምጣ። 10.“በመካከላችሁ ጥበበኞች የሆኑ ሁሉ መጥተው እግዚአብሔር ያዘዘውን ሁሉ ይሥሩ፦ 11.“የመገናኛውን ድንኳን ከነድንኳኑና ከነመደረቢያው፣ ማያያዣዎችን፣ ክፈፎችን፣ አግዳሚዎችን፣ ቋሚዎችንና መሠረቶችን፤ 12.ታቦቱን ከነመሎጊያዎቹ፣ የስርየት መክደኛውንና የሚሸፍነውን መጋረጃ፤ 13.ጠረጴዛውን ከነመሎጊያዎቹ፣ ዕቃዎቹን ሁሉና የገጸ ኅብስቱን፤ 14.ለመብራት የሆነውን መቅረዝ ከነዕቃዎቹ፣ ቀንዲሎችንና ለመብራት የሚሆነውን ዘይት፤ 15.የዕጣን መሠዊያውን ከነመሎጊያዎቹ፣ ቅብዐ ዘይቱንና ጣፋጭ ሽታ ያለውን ዕጣን፤
በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ላይ የሚሆነውን የመግቢያ መጋረጃ፤ 16.የሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያውን ከንሓስ መጫሪያው፣ መሎጊያዎቹንና ዕቃዎቹን ሁሉ፣
የንሓስ ሰኑን ከነማስቀመጫው፣ 17.የአደባባዩን መጋረጃዎች ከነምሰሶዎቻቸውና ከነመሠረቶቹ፣ የአደባባዩን መግቢያ መጋረጃ፤ 18.ለመገናኛው ድንኳንና ለአደባባዩ የሚሆኑ የድንኳን ካስማዎችና ገመዶቻቸው፤ 19.በመቅደሱ ውስጥ ለማገልገል የሚለበሱ የፈትል ልብሶችን ይኸውም የካህኑ የአሮንን የተቀደሱ ልብሶችንና ካህናት ሆነው ሲያገለግሉ የሚለብሷቸውን የወንዶች ልጆቹን ልብሶች ይሥሩ።” 20.ከዚያም የእስራኤል ማኅበረ ሰብ ሁሉ ከሙሴ ፊት ወጡ፤ 21.ፈቃደኛ የነበረና ልቡን ያነሣሣው ሁሉ በመምጣት ለመገናኛው ድንኳን ሥራ፣ ለአገልግሎቱ ሁሉና ለተቀደሱ ልብሶች የሚሆን ለእግዚአብሔር መባ አመጡ። 22.ፈቃደኛ የነበሩ ሁሉ፣ ወንዶችም ሴቶችም መጥተው ከሁሉም ዐይነት የወርቅ ጌጦች አመጡ፤ የአፍንጫ ጌጦችን፣ ሎቲዎችን፣ ቀለበቶችን፣ ድሪዎችንና ጌጣጌጦችን ሁሉ አመጡ፤ ሁሉም ወርቃቸውን እንደሚወዘወዝ መሥዋዕት ለእግዚአብሔር አቀረቡ። 23.ሰማያዊ፣ ሐምራዊ ወይም ቀይ ማግ ወይም ቀጭን ሐር ወይም የፍየል ጠጕር፣ ቀይ የተነከረ የአውራ በግ ቈዳ ወይም የአቆስጣ ቈዳ አመጡ። 24.የብር ወይም የናስ መባ ማቅረብ የቻሉ ሁሉ ለእግዚአብሔር መባ አድርገው አመጡ፤ የግራር ዕንጨት ያለው ሁሉ አስፈላጊ በሆነው ሥራ እንዲውል አመጣው። 25.ጥበበኞች የሆኑ ሴቶች ሁሉ በእጃቸው ፈተሉ፤ የፈተሉትንም ሰማያዊ ሐምራዊ ወይም ቀይ ማግ ወይም ቀጭን በፍታ አመጡ። 26.ፈቃደኛ የነበሩና ጥበቡ ያላቸው ሴቶች ሁሉ የፍየል ጠጕር ፈተሉ። 27.መሪዎቹም ኤፉድና በደረት ኪሱ ላይ እንዲሆን የከበሩ ድንጋዮችንና ሌሎች ዕንቍዎች አመጡ። 28.እንዲሁም ለመብራቱ፣ ለቅብዐ ዘይቱና ለጣፋጭ ሽታ ዕጣን የሚሆኑ ቅመሞችንና የወይራ ዘይትን አመጡ። 29.ፈቃደኛ የሆኑ እስራኤላውያን ወንዶችና ሴቶች ሁሉ፣ እግዚአብሔር በሙሴ በኩል እንዲያከናውኑት ላዘዛቸው ሥራ ሁሉ የበጎ ፈቃድ ስጦታዎችን ለእግዚአብሔር አመጡ።
ባስልኤልና ኤልያብ
35፥30-35 ተጓ ምብ – ዘፀ 31፥2-6
30.ከዚያም ሙሴ እስራኤላውያንን አላቸው፤ “እነሆ፤ እግዚአብሔር ከይሁዳ ነገድ የሆነውን የሑር ልጅ፣ የኡሪን ልጅ ባስልኤልን መርጧል።
31.በጥበብ፣ በችሎታና በዕውቀት፣ በማንኛውም ዐይነት ሙያ የእግዚአብሔርን መንፈስ ሞልቶበታል፤
32.ይኸውም በወርቅ፣ በብርና በንሓስ የጥበብ ሥራ እንዲሠራ ነው፤
33.ድንጋዮችን እንዲጠርብና እንዲያወጣ፣ የዕንጨት ሥራ እንዲሠራና ማንኛውንም ዐይነት የጥበብ ሙያ እንዲያከናውን ነው።
34.እንዲሁም ለርሱና ከዳን ነገድ ለሆነው ለአሂሳሚክ ልጅ ለኤልያብ፣ ለሁለቱም ሌሎችን የማስተማር ችሎታ ሰጣቸው።
35.የእጅ ጥበብ ባለሙያዎች፣ ዕቅድ አውጭዎች፣ በሰማያዊ በሐምራዊና በቀይ ማግ፣ በቀጭን ሐር ጥልፍ ጠላፊዎችና ፈታዮች፤ ሁሉም ዋና የእጅ ጥበብ ባለሙያዎችና ዕቅድ አውጭዎች በመሆን ማንኛውንም ዐይነት ሥራ ያከናውኑ ዘንድ በጥበብ ሞልቷቸዋል።
ምዕራፍ 36
1.ስለዚህ የመቅደሱን የግንባታ ሥራ ሁሉ እንዴት ማከናወን እንዳለባቸው እግዚአብሔር ጥበብንና ችሎታን የሰጣቸው፣ ባስልኤል፣ ኤልያብና ጥበበኛ የሆኑ ሰዎች ሁሉ ሥራውን ልክ እግዚአብሔር እንዳዘዘው ይሥሩት።”
2.ከዚያም ሙሴ ባስልኤልንና ኤልያብን እንዲሁም እግዚአብሔር ችሎታ የሰጣቸውን፣ መጥተው ሥራውን ለመሥራት ፈቃደኛ የሆኑትን ጥበብ ያላቸውን ሰዎች ሁሉ አስጠራ።
3.የመቅደሱን የግንባታ ሥራ ለማከናወን እስራኤላውያን ያመጡትን ስጦታ ሁሉ ከሙሴ ተቀበሉ፤ ሕዝቡ የበጎ ፈቃድ ስጦታዎችን በየማለዳው ማምጣታቸውን ቀጠሉ።
4.ስለዚህ የመቅደሱን ሥራ ሁሉ ይሠሩ የነበሩ ጥበበኞች የሆኑ ባለሙያዎች ሁሉ ሥራቸውን ትተው መጡ፤
5.ሙሴንም፣ “ሕዝቡ እግዚአብሔር እንዲሠራ ላዘዘው ሥራ ከበቂ በላይ እያመጡ ነው” አሉት።
6.ከዚያም ሙሴ ትእዛዝ ሰጠ፤ ይህንም ቃል ወደ ሰፈሩ ላኩት፤ “ማንም ወንድ ወይም ሴት ለመቅደሱ ሌላ ምንም ስጦታ ማድረግ የለበትም፤” ስለዚህ ሕዝቡ ትርፍ እንዳያመጡ ተከለከሉ፤
7.ምክንያቱም ሥራውን ሁሉ ለማከናወን በእጃቸው ያለው ከበቂ በላይ ነበረ።
የማደሪያው ድንኳን
36፥8-38 ተጓ ምብ – ዘፀ 26፥1-37
8.የሥራ ችሎታ ካላቸው ሰዎች መካከል ጥበበኛ የሆኑ ሰዎች ሁሉ የማደሪያውን ድንኳን በቀጭኑ ከተፈተለ በፍታና ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊና ከቀይ ማግ፣ በጥልፍ ዐዋቂ፣ ኪሩቤል ከተጠለፉበት ከዐሥር መጋረጃዎች ሠሩት።
9.መጋረጃዎቹም ሁሉ ተመሳሳይ መጠን ያላቸው ሲሆን፣ ቁመታቸው ሃያ ስምንት ክንድ፣ ወርዳቸው አራት ክንድ ነበር።
10.ዐምስቱን መጋረጃዎች በአንድ ላይ በማጋጠም ሰፏቸው፤ የቀሩትን ዐምስቱንም እንዲሁ አደረጉ።
11.ተጋጥሞ ከተሰፋው መጋረጃ ጠርዝ ጫፍ ላይ ከሰማያዊ ግምጃ ቀለበቶችን አበጁ፤ ተጋጥሞ በተሰፋው በሌላው መጋረጃ ጫፍ ላይም ተመሳሳይ ነገር አደረጉ።
12.በአንደኛው መጋረጃ ላይ ዐምሳ ቀለበቶችን በሌላው ተጋጥሞ ከተሰፋው በስተመጨረሻ ካለው መጋረጃ ላይ ዐምሳ ቀለበቶችን እርስ በርሳቸው ትይዩ በማድረግ ሠሩት።
13.ከዚያም ዐምሳ የወርቅ ማያያዣዎችን ሠሩ፤ የማደሪያው ድንኳን አንድ ወጥ ይሆን ዘንድም ተጋጥመው የተሰፉትን ሁለቱን መጋረጃዎች አያያዙባቸው።
14.ከማደሪያው በላይ ለሚሆነው ድንኳን ከፍየል ቈዳ የተሠሩ በጠቅላላ ዐሥራ አንድ መጋረጃዎችን ሠሩ።
15.ዐሥራ አንዱ መጋረጃዎች ተመሳሳይ ልክ ሲኖራቸው፣ ቁመታቸው ሠላሳ ክንድ፣ ወርዳቸውም አራት ክንድ ነበር።
16.ዐምስቱን መጋረጃዎች በአንድ በኩል፣ ሌሎቹን ስድስት መጋረጃዎች ደግሞ በሌላ በኩል አንድ ላይ አያያዟቸው።
17.በስተመጨረሻ በሚገኘው መጋረጃ ጠርዝ ላይ ዐምሳ ቀለበቶችን፣ በሌላ በኩል ባለው በስተመጨረሻ በሚገኘው መጋረጃ ጠርዝ ዐምሳ ቀለበቶችን አበጁ።
18.ድንኳኑን አንድ ወጥ አድርጎ ለማያያዝም ዐምሳ የንሓስ ማያያዣዎችን ሠሩ።
19.ከዚያም ለድንኳኑ መሸፈኛ የሚሆን ቀይ ከተነከረ የአውራ በግ ቈዳ ሠሩ፤ በላዩ ላይ የሚሆንም የአቆስጣ ቈዳ አበጁ።
20.ለማደሪያው ድንኳን ከግራር ዕንጨት ወጋግራዎችን አበጁ።
21.እያንዳንዱም ወጋግራ ቁመቱ ዐሥር ክንድ፣ ስፋቱ አንድ ክንድ ተኩል ነበር፤
22.ትይዩ የሆኑ ሁለት ጕጦች ነበሩት፤ የማደሪያውን ድንኳን ወጋግራዎች በዚህ መልክ ሠሩ።
23.በደቡብ በኩል ላለው የማደሪያው ድንኳን ሃያ ወጋግራዎችን አበጁ፤
24.ለእያንዳንዱ ጕጠት አንድ መቆሚያ፣ ለእያንዳንዱም ወጋግራ ሁለት መቆሚያ ሆኖ አርባ የብር መቆሚያዎችን አበጁ።
25.በስተሰሜን በኩል ላለው የማደሪያው ድንኳን ሃያ ወጋግራዎችን ሠሩ፤
26.ለእያንዳንዱ ወጋግራ ሁለት መቆሚያ የሆኑ አርባ የብር መቆሚያዎችን ሠሩ።
27.በዳር በኩል ይኸውም በስተምዕራብ ጫፍ ባለው ማደሪያው ድንኳን ስድስት ወጋግራዎችን ሠሩ።
28.ዳርና ዳር ላሉት የማደሪያው ድንኳን ማእዘኖችም ሁለት ወጋግራዎችን ሠሩ።
29.በእነዚህ ሁለት ማእዘኖች ላይ ከታች አንሥቶ እስከ ላይ ድረስ ወጋግራዎቹ በአንድ ላይ ተነባብረው በአንድ ቀለበት ውስጥ ተገጥመው ነበር፤ ሁለቱም አንድ አካል ሆነው ተሠርተው ነበር።
30.ስለዚህ ስምንት ወጋግራዎችና ለእያንዳንዱም ወጋግራ ሁለት መቆሚያዎች ሆነው ዐሥራ ስድስት የብር መቆሚያዎች ነበሩ።
31.እንደዚሁም ከግራር ዕንጨት አግዳሚዎችን ሠሩ፤ በማደሪያው ድንኳን በአንድ በኩል ላሉት ወጋግራዎች ዐምስት አግዳሚዎችን ሠሩ፤
32.በሌላ በኩል ላሉት ዐምስት አግዳሚዎች፣ በምዕራብ በኩል በማደሪያው ድንኳን ዳር ላይ ላሉት ወጋግራዎች ዐምስት አግዳሚዎችን ሠሩ።
33.በወጋግራዎቹ መካከል ከዳር እስከ ዳር እንዲዘረጋ ሆኖ መካከለኛውን አግዳሚ ሠሩ።
34.ወጋግራዎቹን በወርቅ ለበጧቸው፤ አግዳሚዎቹን ለመያዝም የወርቅ ቀለበቶችን ሠሩ፤ እንዲሁም አግዳሚዎቹን በወርቅ ለበጧቸው።
35.ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊ፣ ከቀይ ማግና በቀጭኑ ከተፈተለ በፍታ፣ እጀ ጥበብ ባለሙያም ኪሩቤል የተጠለፉበት መጋረጃ ሠራ።
36.ለርሱም አራት ምሰሶዎች ከግራር ዕንጨት ሠርተው በወርቅ ለበጧቸው፤ ለእነርሱም አራት የወርቅ ኵላቦችንና አራት የብር መቆሚያዎችን አበጁላቸው።
37.በድንኳኑ መግቢያ ጥልፍ ጠላፊ እንደሚሠራው ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊ፣ ከቀይ ማግና በቀጭኑ ከተፈተለ በፍታ መጋረጃ አበጁለት፤
38.ለእነርሱም ኵላቦች ያሏቸው ዐምስት ምሰሶዎች ሠሩላቸው፤ የምሰሶዎቹን ዐናቶችና ዘንጎች በወርቅ በመለበጥ ዐምስቱን መቆሚያዎች ከንሓስ ሠሩ።
ምዕራፍ 37
የኪዳኑ ታቦት
37፥1-9 ተጓ ምብ – ዘፀ 25፥10-20
1.ባስልኤል ርዝመቱ ሁለት ክንድ ተኩል፣ ወርዱ አንድ ክንድ ተኩል፣ ከፍታው አንድ ክንድ ተኩል የሆነ ታቦት ከግራር ዕንጨት ሠራ።
2.በውስጥና በውጭ በንጹሕ ወርቅ ለበጠው፤ በዙሪያውም የወርቅ ክፈፍ አበጀለት።
3.አራት የወርቅ ቀለበቶችን ሠርቶ ሁለት ቀለበቶችን በአንድ በኩል፣ ሁለት ቀለበቶችንም በሌላ በኩል አድርጎ ከአራቱ እግሮቹ ጋራ አያያዛቸው።
4.ከዚያም መሎጊያዎችን ከግራር ዕንጨት ሠርቶ በወርቅ ለበጣቸው።
5.መሎጊያዎቹንም መሸከሚያ እንዲሆኑ በታቦቱ ጐንና ጐን ባሉት ቀለበቶች ውስጥ አስገባቸው።
6.ርዝመቱ ሁለት ክንድ ተኩል፣ ወርዱም አንድ ክንድ ተኩል የሆነ ከንጹሕ ወርቅ የስርየት መክደኛ ሠራ።
7.ከዚያም ከተቀጠቀጠ ወርቅ ሁለት ኪሩቤልን በስርየት መክደኛው ዳርና ዳር ላይ ሠራ።
8.አንዱን ኪሩብ በአንዱ ጫፍ ላይ፣ ሁለተኛውንም ኪሩብ በሌላው ጫፍ ላይ ሠራ፤ ከሁለቱ ጫፎች ላይ ከክዳኑ ጋራ አንድ ወጥ አድርጎ ሠራቸው፤
9.ኪሩቤልም የስርየት ክዳኑን በመሸፈን ክንፋቸውን ወደ ላይ ዘርግተው ነበር፤ ኪሩቤል ወደ ስርየት መክደኛው እየተመለከቱ እርስ በርሳቸው ገጽ ለገጽ ነበሩ።
የኅብስት ማስቀመጫው ጠረጴዛ
37፥10-16 ተጓ ምብ – ዘፀ 25፥23-29
10.ርዝመቱ ሁለት ክንድ፣ ወርዱ አንድ ክንድ፣ ከፍታውም አንድ ክንድ ተኩል የሆነ ጠረጴዛ ከግራር ዕንጨት ሠሩ።
11.ከዚያም በንጹሕ ወርቅ በመለበጥ በዙሪያው የወርቅ ክፈፍ አበጁለት።
12.በዙሪያውም ስፋቱ አንድ ስንዝር የሆነ ጠርዝ በማበጀት በጠርዙ ላይ የወርቅ ክፈፍ አደረጉበት።
13.ለጠረጴዛው አራት የወርቅ ቀለበቶች አበጅተው አራቱ እግሮች ካሉበት ከአራቱ ማእዘኖች ጋራ አያያዟቸው።
14.ጠረጴዛውን ለመሸከም የሚያገለግሉትን መሎጊያዎች እንዲይዙ ቀለበቶቹ ከጠርዙ አጠገብ ሆኑ።
15.ጠረጴዛውን ለመሸከም የሚያገለግሉት መሎጊያዎች ከግራር ዕንጨት የተሠሩና በወርቅ የተለበጡ ነበሩ።
16.የጠረጴዛውን ዕቃዎች ይኸውም ዝርግ ሳሕኖችን፣ ድስቶችንና ጐድጓዳ ሳሕኖችን እንዲሁም የመጠጥ መሥዋዕቱ ማፍሰሻ የሆኑትን ማንቈርቈሪያዎች ከንጹሕ ወርቅ ሠሯቸው።
መቅረዙ
37፥17-24 ተጓ ምብ – ዘፀ 25፥31-39
17.መቅረዙን ከንጹሕ ወርቅ ሠሩት፤ መቆሚያውንና ዘንጉን ቀጥቅጠው አበጁት፤ የአበባ ቅርጽ ያላቸው ጽዋዎች፣ እንቡጦችና የፈኩ አበቦች ከርሱ ጋራ አንድ ወጥ ሆነው ተሠርተው ነበር።
18.ሦስቱ በአንድ በኩል ሦስቱ በሌላ በኩል በመሆን ስድስት ቅርንጫፎች ከመቅረዙ ጐኖች ተሠርተው ነበር።
19.ከእንቡጦችና ከፈኩ አበቦች ጋራ የለውዝ አበባ የሚመስሉ ሦስት ጽዋዎች በአንዱ ቅርንጫፍ ላይ፣ ሦስቱ ደግሞ በሚቀጥለው ቅርንጫፍ ላይ ነበሩ፤ ከመቅረዙ ለወጡት ለስድስቱም ቅርንጫፎች ሁሉ እንዲሁ ነበር።
20.እንቡጦችና የፈኩ አበቦች ያሉባቸው የለውዝ አበባ የሚመስሉ አራት ጽዋዎች በመቅረዙ ላይ ነበሩ።
21.አንደኛው እንቡጥ ከመቅረዙ ወጣ ብለው በሚገኙት በመጀመሪያው ጥንድ ቅርንጫፎች ሥር፣ ሁለተኛውም እምቡጥ በሁለተኛው ጥንድ ሥር እንዲሁም ሦስተኛው እንቡጥ በሦስተኛው ጥንድ ሥር ነበር፤ በስድስቱም ቅርንጫፎች እንዲሁ ነበር።
22.እንቡጦቹና ቅርንጫፎቹ ሁሉ ከንጹሕ ወርቅ ተሠርተው ከመቅረዙ ጋራ አንድ ወጥ ነበሩ።
23.የመቅረዙን ሰባት መብራቶች፣ እንዲሁም መኰስተሪያዎችንና የኵስታሪ ማስቀመጫዎችን ከንጹሕ ወርቅ ሠሩ።
24.መቅረዙንና ዕቃዎቹን ሁሉ ከአንድ መክሊት ንጹሕ ወርቅ ሠሩ።
የዕጣን መሠዊያው
37፥25-28 ተጓ ምብ – ዘፀ 30፥1-5
25.የዕጣን መሠዊያውን ከግራር ዕንጨት ሠሩ፤ ርዝመቱ አንድ ክንድ፣ ወርዱ አንድ ክንድ፣ ከፍታው ሁለት ክንድ ነበር፤ ቀንዶቹም ከርሱ ጋራ አንድ ወጥ ሆነው ተሠርተው ነበር።
26.ላዩን፣ ጐኖቹን ሁሉና ቀንዶቹን በንጹሕ ወርቅ ለበጧቸው፤ በዙሪያው የወርቅ ክፈፍ አበጁ።
27.ለሸክም የሚሆኑትን መሎጊያዎች ለመያዝ ትይዩ የሆኑ ከክፈፉ ሥር ሁለት የወርቅ ቀለበቶችን ሠሩ።
28.መሎጊያዎቹን ከግራር ዕንጨት ሠሩ፤ በወርቅም ለበጧቸው።
29.እንዲሁም የተቀደሰውን ቅብዐ ዘይትና የሽቱ ቀማሚ ሥራ የሆነውን፣ ንጹሕና መልካም መዐዛ ያለውን ዕጣን ሠሩ።
መዝሙረ ዳዊት
ምዕራፍ 26
1.የዳዊት መዝሙር።
1 እግዚአብሔር ሆይ፤ ያለ ነቀፋ እንደ መሆኔ፣
አንተው ፍረድልኝ።
ወዲያ ወዲህ ሳልልም፣
በእግዚአብሔር ታምኛለሁ። 2.እግዚአብሔር ሆይ፤ ፈትነኝ፤ መርምረኝም፤
ልቤንና ውስጤን መርምር፤ 3.ምሕረትህ ከፊቴ አልተለየምና፣
በእውነትህም ተመላለስሁ። 4.ከማይረቡ ጋራ አልተቀመጥሁም፤
ከግብዞችም ጋራ አልተባበርሁም። 5.የክፉዎችን ማኅበር ተጸየፍሁ፤
ከዐመፀኞችም ጋራ አልቀመጥም። 6.እጆቼን በየዋህነት እታጠባለሁ፤
እግዚአብሔር ሆይ፤ መሠዊያህንም እዞራለሁ፤ 7.የምስጋናን ድምፅ አሰማ ዘንድ፣
ታምራትህንም አወራ ዘንድ ነው። 8.እግዚአብሔር ሆይ፤ የምትኖርበትን ቤት፣
የክብርህን ማደሪያ ቦታ ወደድሁ። 9.ነፍሴን ከኀጢአተኞች ጋራ፣
ሕይወቴንም ከደም አፍሳሾች ጋራ አታስወግዳት። 10.በእነርሱ እጅ የተንኰል ዕቅድ አለ፤
ቀኝ እጃቸውም ጕቦን ያጋብሳል። 11.እኔ ግን በተአማኒ ሕይወት እጓዛለሁ፤
አድነኝ፤ ምሕረትንም አድርግልኝ። 12.እግሮቼ በደልዳላ ስፍራ ቆመዋል፤
በታላቅ ጉባኤ መካከልም እግዚአብሔርን እባርከዋለሁ።
1 እግዚአብሔር ሆይ፤ ያለ ነቀፋ እንደ መሆኔ፣
አንተው ፍረድልኝ።
ወዲያ ወዲህ ሳልልም፣
በእግዚአብሔር ታምኛለሁ። 2.እግዚአብሔር ሆይ፤ ፈትነኝ፤ መርምረኝም፤
ልቤንና ውስጤን መርምር፤ 3.ምሕረትህ ከፊቴ አልተለየምና፣
በእውነትህም ተመላለስሁ። 4.ከማይረቡ ጋራ አልተቀመጥሁም፤
ከግብዞችም ጋራ አልተባበርሁም። 5.የክፉዎችን ማኅበር ተጸየፍሁ፤
ከዐመፀኞችም ጋራ አልቀመጥም። 6.እጆቼን በየዋህነት እታጠባለሁ፤
እግዚአብሔር ሆይ፤ መሠዊያህንም እዞራለሁ፤ 7.የምስጋናን ድምፅ አሰማ ዘንድ፣
ታምራትህንም አወራ ዘንድ ነው። 8.እግዚአብሔር ሆይ፤ የምትኖርበትን ቤት፣
የክብርህን ማደሪያ ቦታ ወደድሁ። 9.ነፍሴን ከኀጢአተኞች ጋራ፣
ሕይወቴንም ከደም አፍሳሾች ጋራ አታስወግዳት። 10.በእነርሱ እጅ የተንኰል ዕቅድ አለ፤
ቀኝ እጃቸውም ጕቦን ያጋብሳል። 11.እኔ ግን በተአማኒ ሕይወት እጓዛለሁ፤
አድነኝ፤ ምሕረትንም አድርግልኝ። 12.እግሮቼ በደልዳላ ስፍራ ቆመዋል፤
በታላቅ ጉባኤ መካከልም እግዚአብሔርን እባርከዋለሁ።
ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች
ምዕራፍ 4
ጳውሎስ በጽናትና በአንድነት እንዲቆሙ የሰጠው ምክር
1.ስለዚህ የምወድዳችሁና የምናፍቃችሁ፣ ወንድሞቼ ደስታዬና አክሊሌ የሆናችሁ፣ እንዲሁም ወዳጆች ሆይ፤ በዚህ ሁኔታ በጌታ ጸንታችሁ ቁሙ! 2.በጌታ አንድ ሐሳብ እንዲኖራቸው ኤዎድያንን እለምናለሁ፤ ሲንጤኪንንም እለምናለሁ። 3.አዎን፤ አንተ ታማኝ ባልደረባዬ ሆይ፤ ወንጌልን በማሠራጨት ረገድ ከእኔና ከቀሌምንጦስ ጋራ እንዲሁም ስማቸው በሕይወት መጽሐፍ ከተጻፉት ከሌሎች የሥራ ጓደኞቼ ጋራ የተጋደሉትን እነዚህን ሴቶች እንድትረዳቸው እለምንሃለሁ።የመዝጊያ ምስጋና
4.ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ፤ ደግሜ እላለሁ ደስ ይበላችሁ! 5.ገርነታችሁ በሁሉ ዘንድ የታወቀ ይሁን፤ ጌታ ቅርብ ነው። 6.በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ፣ ከምስጋናም ጋራ ልመናችሁን በእግዚአብሔር ፊት አቅርቡ እንጂ ስለ ማንኛውም ነገር አትጨነቁ። 7.ከማስተዋል በላይ የሆነው የእግዚአብሔር ሰላም፣ ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል። 8.በመጨረሻም ወንድሞች ሆይ፤ እውነት የሆነውን ሁሉ፣ ክቡር የሆነውን ሁሉ፣ ትክክል የሆነውን ሁሉ፣ ንጹሕ የሆነውን ሁሉ፣ ተወዳጅ የሆነውን ሁሉ፣ መልካም የሆነውን ሁሉ፣ በጎነት ቢሆን ወይም ምስጋና እንደ እነዚህ ስላሉት ነገሮች አስቡ። 9.ከእኔ የተማራችሁትን ወይም የተቀበላችሁትን፣ የሰማችሁትን ወይም ያያችሁትን ማንኛውንም ነገር አድርጉ፤ የሰላም አምላክም ከእናንተ ጋራ ይሆናል።ላደረጉት ችሮታ የቀረበ ምስጋና
10.ከብዙ ጊዜ በኋላ እንደ አዲስ ስለ እኔ ማሰብ በመጀመራችሁ፣ በጌታ እጅግ ደስ ይለኛል፤ በርግጥ በተግባር ለመግለጽ ዕድሉ አልነበራችሁም እንጂ ማሰቡንስ ታስቡልኝ ነበር። 11.ይህን የምለው ስለ ቸገረኝ አይደለም፤ ምክንያቱም በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ያለኝ ይበቃኛል ማለትን፣ 12.ማጣትን ዐውቀዋለሁ፤ ማግኘትንም ዐውቀዋለሁ። ብጠግብም ሆነ ብራብ፣ ባገኝም ሆነ ባጣ፣ በማንኛውም ሆነ በየትኛውም ሁኔታ ያለኝ ይበቃኛል የማለትን ምስጢር ተምሬአለሁ። 13.ኀይልን በሚሰጠኝ በርሱ ሁሉን ማድረግ እችላለሁ። 14.ሆኖም የመከራዬ ተካፋይ ስለ ሆናችሁ መልካም አድርጋችኋል። 15.ከዚህም በላይ፣ እናንተ የፊልጵስዩስ ሰዎች ራሳችሁ እንደምታውቁት፣ በመጀመሪያ ወንጌልን በተቀበላችሁ ጊዜ ከመቄዶንያ ስነሣ፣ ከእናንተ በቀር በመስጠትና በመቀበል የትኛውም ቤተ ክርስቲያን አልተባበረኝም። 16.በተሰሎንቄ በነበርሁበት ጊዜ እንኳ፣ በችግሬ ወቅት ደጋግማችሁ ርዳታ ልካችሁልኛልና። 17.ይኸውም፣ ትርፉ ለእናንተ እየበዛ እንዲሄድ እንጂ ስጦታውን ጓጕቼ አይደለም። 18.የሚያስፈልገኝን ሁሉ፣ ከሚያስፈልገኝም በላይ ተቀብያለሁ፤ የላካችሁትንም ስጦታ ከአፍሮዲጡ እጅ ተቀብዬ ተሞልቻለሁ፤ ይህም መዐዛው የጣፈጠ፣ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ያለውና ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕት ነው። 19.አምላኬም እንደ ታላቅ ባለጠግነቱ መጠን የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ በክርስቶስ ኢየሱስ ይሞላባችኋል። 20.ለአምላካችንና ለአባታችን ከዘላለም እስከ ዘላለም ክብር ይሁን። አሜን።የስንብት ሰላምታ
21.ለቅዱሳን ሁሉ በክርስቶስ ኢየሱስ ሰላምታ አቅርቡልኝ።ከእኔ ጋራ ያሉት ወንድሞችም ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። 22.ቅዱሳን ሁሉ፣ በተለይም ከቄሳር ቤተ ሰው የሆኑት ወገኖች ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። 23.የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከመንፈሳችሁ ጋራ ይሁን። አሜን።