ሳምንት 7 · ቀን 31 (ሰኞ)
📅 Tikimt 16, 2019
ኦሪት ዘጸአት 32, 33, 34 · ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 3
ኦሪት ዘጸአት
ምዕራፍ 32
የወርቅ ጥጃ
1.ሕዝቡ ሙሴ ከተራራው ላይ ሳይወርድ ብዙ እንደ ቈየ ባዩ ጊዜ፣ ወደ አሮን ተሰብስበው፣ “ናና በፊታችን የሚሄዱ አማልክት ሥራልን፤ ያ ከግብጽ ያወጣን ሙሴ ምን እንዳገኘው አናውቅም” አሉት። 2.አሮንም፣ “የሚስቶቻችሁን፣ የወንድና የሴት ልጆቻችሁን የጆሮ ወርቅ አውልቃችሁ ወደ እኔ አምጡ” ብሎ መለሰላቸው። 3.ሕዝቡም ሁሉ የጆሮ ወርቃቸውን አውልቀው ወደ አሮን አመጡ። 4.እርሱም የሰጡትን ወስዶ በመሣሪያ በመቅረጽ በጥጃ ምስል ጣዖት አድርጎ ሠራው፤ ከዚያም እነርሱ፣ “እስራኤል ሆይ፤ ከግብጽ ያወጡህ አማልክት እነዚህ ናቸው” አሉ። 5.አሮን ይህን ባየ ጊዜ በወርቅ ጥጃው ፊት ለፊት መሠዊያ ሠርቶ፣ “ነገ ለእግዚአብሔር በዓል ይሆናል” ብሎ ዐወጀ። 6.በማግስቱም ሕዝቡ በማለዳ ተነሥተው የሚቃጠል መሥዋዕት ሠዉ፤ የኅብረት መሥዋዕት አቀረቡ፤ ከዚህም በኋላ ይበሉና ይጠጡ ዘንድ ተቀመጡ፤ ሊዘፍኑም ተነሡ። 7.ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን፣ “ከግብጽ ያወጣሃቸው ሕዝብህ ስተዋልና ውረድ” አለው። 8.“ካዘዝኋቸው ፈቀቅ ለማለት ፈጣኖች ሆኑ፤ ለራሳቸውም በጥጃ ምስል የተቀረጸ ጣዖትን ሠሩ፤ ለርሱም ሰገዱለት፤ ሠዉለትም፤ እንዲሁም፣ ‘እስራኤል ሆይ፤ ከግብጽ ምድር ያወጡህ አማልክትህ እነዚህ ናቸው’ አሉ።” 9.እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ አለው፤ “እነዚህን ሕዝብ አይቻቸዋለሁ፤ ዐንገተ ደንዳናዎችም ናቸው። 10.አሁንም በእነርሱ ላይ፣ ቍጣዬ እንዲነድድና እንዳጠፋቸው ተወኝ፤ ከዚያም አንተን ለታላቅ ሕዝብ አደርግሃለሁ።” 11.ነገር ግን ሙሴ የአምላኩን የእግዚአብሔርን ቸርነት ፈለገ፤ እንዲህም አለ፤ “እግዚአብሔር ሆይ በታላቅ ሥልጣንህና በኀያል ክንድህ ከግብጽ ባወጣኸው ሕዝብህ ላይ ቍጣህ ለምን ይነድዳል? 12.ግብጻውያን፣ ‘በተራሮቹ ላይ ሊገድላቸው፣ ከገጸ ምድርም ሊያጠፋቸው ስለ ፈለገ ነው ያወጣቸው’ ለምን ይበሉ? ከክፉ ቍጣህ ተመለስ፤ ታገሥ፤ በሕዝብህም ላይ ጥፋት አታምጣ። 13.ለባሪያዎችህ ለአብርሃም፣ ለይሥሐቅና ለእስራኤል፣ ‘ዘርህን እንደ ሰማይ ከዋክብት አበዛዋለሁ፤ ለዘርህም ተስፋ አድርጌ የሰጠኋቸውን ይህችን ምድር ሁሉ እሰጣቸዋለሁ፤ ለዘላለምም ርስታቸው ትሆናለች’ በማለት በራስህ የማልኸውን አስታውስ።” 14.ከዚያም እግዚአብሔር ታገሠ፤ በሕዝቡም ላይ አመጣባቸዋለሁ ያለውን ጥፋት አላመጣባቸውም። 15.ሙሴም ሁለቱን የምስክር ጽላት በእጆቹ ይዞ ከተራራው ወረደ፤ ጽላቱም ከፊትና ከኋላ በሁለቱም ጐኖች ተጽፎባቸው ነበር። 16.ጽላቱ የእግዚአብሔር ሥራ ነበሩ፤ በጽላቱ ላይ የተቀረጸ ጽሕፈትም የእግዚአብሔር ጽሕፈት ነበር። 17.ኢያሱ የሕዝቡን የጩኸት ድምፅ በሰማ ጊዜ ሙሴን፣ “በሰፈሩ ውስጥ የጦርነት ድምፅ አለ አለው።” 18.ሙሴም፣“የድል ድምፅ አይደለም፤
የሽንፈትም ድምፅ አይደለም፤
የምሰማው የዘፈን ድምፅ ነው”
ብሎ መለሰለት። 19.ሙሴ ወደ ሰፈሩ ደርሶ ጥጃውንና ጭፈራውን ባየ ጊዜ ቍጣው ነደደ፤ ጽላቱን ከእጁ በመወርወር ከተራራው ግርጌ ሰባበራቸው። 20.ያበጁትን ጥጃ ወስዶ በእሳት አቃጠለው፤ ከዚያም ዱቄት እስኪሆን ፈጨው፤ በውሃ ላይ በተነው፤ እስራኤላውያንም እንዲጠጡት አደረገ። 21.ሙሴም አሮንን፣ “ወደዚህ አስከፊ ኀጢአት ትመራቸው ዘንድ እነዚህ ሕዝብ ምን አደረጉህ?” አለው። 22.አሮንም መልሶ፣ “ጌታዬ ሆይ፤ አትቈጣ” ብሎ መለሰለት፤ “ይህ ሕዝብ ሁልጊዜ ለክፋት ያዘነበለ መሆኑን አንተ ታውቃለህ። 23.እነርሱም ‘በፊታችን የሚሄዱ አማልክት ሥራልን፤ ያ ከግብጽ ያወጣን ሙሴ ምን እንዳገኘው አናውቅም’ አሉኝ። 24.ስለዚህ፣ ‘ማንኛውም ዐይነት የወርቅ ጌጣጌጥ ያለው ሁሉ ያውልቀው’ አልኋቸው፤ ከዚያም ወርቁን ሰጡኝ፤ ወደ እሳቱ ጣልሁት፤ ይህም ጥጃ ወጣ።” 25.ሕዝቡ ከቍጥጥር ውጭ እንደ ሆኑ፣ አሮንም መረን እንደ ለቀቃቸውና በጠላቶቻቸውም ዘንድ መሣለቂያ እንደ ሆኑ ሙሴ አስተዋለ። 26.ስለዚህ በሰፈሩ መግቢያ ላይ ቆሞ፣ “የእግዚአብሔር የሆነ ሁሉ ወደ እኔ ይምጣ” አለ፤ ሌዋውያኑም ሁሉ ከርሱ ጋራ ሆኑ። 27.ከዚያም፣ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፤ ‘እያንዳንዱ ሰው በወገቡ ላይ ሰይፍ ይታጠቅ፤ በሰፈር ውስጥ ከዳር እዳር እየተመላለሰ እያንዳንዱ ወንድሙን፣ ጓደኛውንና ጎረቤቱን ይግደል’ ” አላቸው። 28.ሌዋውያኑ ሙሴ እንዳዘዛቸው ፈጸሙ፤ በዚያም ዕለት ከሕዝቡ ሦስት ሺሕ ያህል ዐለቁ። 29.ከዚያም ሙሴ፣ “በራሳችሁ ወንዶች ልጆችና ወንድሞች ላይ በመነሣታችሁ፣ በዛሬዋ ቀን ለእግዚአብሔር የተለያችሁ ሆናችኋል፤ በዛሬዋም ዕለት ባርኳችኋል” አለ። 30.በማግስቱም ሙሴ ሕዝቡን፣ “እጅግ የከፋ ኀጢአት ሠርታችኋል፤ አሁን ግን ወደ እግዚአብሔር እወጣለሁ፤ ምናልባት ኀጢአታችሁን ማስተስረይ እችል ይሆናል” አላቸው። 31.ስለዚህ ሙሴ ወደ እግዚአብሔር ተመልሶ እንዲህ አለው፤ “ወዮ እነዚህ ሕዝብ የሠሩት ምን ዐይነት የከፋ ኀጢአት ነው! ለራሳቸውም የወርቅ አማልክት ሠሩ። 32.አሁን ግን አቤቱ ኀጢአታቸውን ይቅር በል፤ አለዚያ ግን ከጻፍኸው መጽሐፍ እኔን ደምስሰኝ።” 33.እግዚአብሔር ለሙሴ እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “የበደለኝን ሁሉ ከመጽሐፌ እደመስሰዋለሁ። 34.አሁን ሂድ፤ ሕዝቡን ወደ ተናገርሁት ስፍራ ምራው፤ መልአኬም በፊትህ ይሄዳል፤ ሆኖም የምቀጣበት ጊዜ ሲደርስ፣ ስለ ኀጢአታቸው እቀጣቸዋለሁ።” 35.አሮን በሠራው ጥጃ ባደረጉት ነገር እግዚአብሔር ሕዝቡን በመቅሠፍት መታ።
ምዕራፍ 33
1.ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን አለው፤ “አንተና ከግብጽ ያወጣኸው ሕዝብህ ይህን ስፍራ ለቅቃችሁ ‘ለዘርህ እሰጣለሁ’ በማለት ለአብርሃም፣ ለይሥሐቅና ለያዕቆብ በመሐላ ተስፋ ወደ ገባሁላችሁ ምድር ሂዱ።
2.መልአክን በፊትህ በመላክ፣ ከነዓናውያንን፣ አሞራውያንን፣ ኬጢያውያንን፣ ፌርዛውያንን፣ ኤዊያዊያንንና ኢያቡሳውያንን አስወጣለሁ።
3.ማርና ወተት ወደምታፈስሰው ምድር ውጡ፤ ነገር ግን ዐንገተ ደንዳና ሕዝብ ስለ ሆናችሁ፣ በመንገድ ላይ እንዳላጠፋችሁ እኔ ከእናንተ ጋራ አልሄድም።”
4.ሕዝቡም እነዚህን አሳዛኝ ቃላት በሰሙ ጊዜ ይተክዙ ጀመር፤ ማንም ሰው አንዳች ጌጥ አላደረገም።
5.እግዚአብሔርም ሙሴን፣ “እስራኤላውያንን፣ ‘እናንተ ዐንገተ ደንዳና ሕዝብ ናችሁ፤ ለአንዳፍታ እንኳ ከእናንተ ጋራ ዐብሬአችሁ ብሄድ አጠፋችሁ ነበር፤ አሁንም ጌጣጌጦቻችሁን አውልቁ፤ እናንተን ምን ማድረግ እንዳለብኝ እወስናለሁ’ ብለህ ንገራቸው” አለው።
6.ስለዚህ እስራኤላውያን በኮሬብ ተራራ ላይ ጌጣጌጦቻቸውን አወለቁ።
የመገናኛው ድንኳን
7.ሙሴ “የመገናኛው ድንኳን” ብሎ የጠራውን በመውሰድ፣ ከሰፈሩ ውጭ ራቅ ባለ ቦታ ላይ ይተክለው ነበር። እግዚአብሔርን መጠየቅ የሚፈልግ ሁሉ ከሰፈሩ ውጭ ወዳለው ወደ መገናኛው ድንኳን ይሄድ ነበር። 8.ሙሴ ወደ ድንኳኑ በወጣ ጊዜ ሕዝቡ በመነሣት ወደ ድንኳኑ እስኪገባ ድረስ በየድንኳኖቻቸው ደጃፍ ላይ ቆመው ይጠባበቁ ነበር። 9.ሙሴ ወደ ድንኳኑ ገብቶ እግዚአብሔር ከሙሴ ጋራ እየተነጋገረ ሳለ የደመናው ዐምድ ወርዶ በመግቢያው ላይ ይቆም ነበር። 10.ሕዝቡ የደመናውን ዐምድ በድንኳኑ ደጃፍ ላይ ቆሞ ሲያዩት ሁሉም በየድንኳኖቻቸው ደጃፍ ላይ ቆመው ይሰግዱ ነበር። 11.ሰው ከባልንጀራው ጋራ እንደሚነጋገር እግዚአብሔር ከሙሴ ጋራ ፊት ለፊት ይነጋገር ነበር፤ ከዚያም ሙሴ ወደ ሰፈሩ ይመለሳል፤ ረዳቱ የነበረው ብላቴናው የነዌ ልጅ ኢያሱ ግን ከድንኳኑ አይለይም ነበር።ሙሴና የእግዚአብሔር ክብር
12.ሙሴ እግዚአብሔርን አለው፤ “ ‘እነዚህን ሕዝብ ምራ’ ብለህ ነግረኸኝ ነበር፤ ከእኔ ጋራ የምትልከው ማን እንደ ሆነ ግን አላሳወቅኸኝም፤ ‘አንተን በስም ዐውቅሃለሁ፤ በፊቴም ሞገስ አግኝተሃል’ ብለህ ነበር። 13.በእኔ ደስ ተሠኝተህ ከሆነ፣ አንተን ዐውቅህና ያለ ማቋረጥ በፊትህ ሞገስ አገኝ ዘንድ መንገድህን አስተምረኝ፤ ይህ ሕዝብ የአንተ ሕዝብ መሆኑን አስታውስ።” 14.እግዚአብሔር “ሀልዎቴ ከአንተ ጋራ ይሄዳል፤ ዕረፍትም እሰጥሃለሁ” ብሎ መለሰ። 15.ከዚያም ሙሴ እንዲህ አለው፤ “ሀልዎትህ ከእኛ ጋራ ካልሄደ ከዚህ አትስደደን። 16.አንተ ከእኛ ጋራ ካልሄድህ፣ አንተ በእኔና በሕዝብህ መደሰትህን ሌላው እንዴት ያውቃል? እኔንና ሕዝብህንስ በገጸ ምድር ከሚገኙት ከሌሎቹ ሕዝቦች ሁሉ ልዩ የሚያደርገን ሌላ ምን አለ?” 17.እግዚአብሔርም ሙሴን፣ “በአንተ ደስ ስላለኝና በስም ስለማውቅህ፣ የጠየቅኸውን ያንኑ አደርጋለሁ” አለው። 18.ከዚያም ሙሴ “እባክህ፤ ክብርህን አሳየኝ” አለው። 19.እግዚአብሔር እንዲህ አለ፤ “መልካምነቴ ሁሉ በፊትህ እንዲያልፍ አደርጋለሁ፤ በፊትህም ስሜን እግዚአብሔርን ዐውጃለሁ፤ የምምረውን እምረዋለሁ፤ የምራራለትንም ራራለታለሁ፤ 20.ነገር ግን፣ ማንም እኔን አይቶ መኖር ስለማይችል፣ ፊቴን ማየት አትችልም።” 21.ከዚያም እግዚአብሔር እንዲህ አለ፤ “በአጠገቤ ስፍራ አለ፤ አንተም በዐለት ላይ ትቆማለህ፤ 22.ክብሬ በዚያ ሲያልፍ በዐለቱ ስንጥቅ ውስጥ አደርግሃለሁ፤ በዚያም እስከማልፍ ድረስ በእጄ እጋርድሃለሁ፤ 23.ከዚያም እጄን አነሣለሁ፤ ጀርባዬንም ታያለህ፤ ፊቴ ግን መታየት የለበትም።”ምዕራፍ 34
አዲሶቹ የድንጋይ ጽላት
1.እግዚአብሔር ሙሴን አለው፤ “እንደ መጀመሪያዎቹ ያሉ ሁለት የድንጋይ ጽላት ጥረብ፤ እኔም አንተ በሰበርሃቸው በመጀመሪያዎቹ ጽላት ላይ የነበሩትን ቃሎች እጽፍባቸዋለሁ። 2.በማለዳ ተዘጋጅተህ ወደ ሲና ተራራ ውጣ፤ በዚያ በተራራው ጫፍ ላይ በፊቴ ቁም፤ 3.ከአንተ ጋራ ማንም እንዳይመጣ ወይም በተራራው ላይ በየትኛውም ቦታ እንዳይታይ፤ የበግና የፍየል መንጋዎች የቀንድ ከብቶችም እንኳ፣ በተራራው ፊት ለፊት መጋጥ የለባቸውም።” 4.ስለዚህ ሙሴ እንደ መጀመሪያዎቹ ያሉ ሁለት የድንጋይ ጽላት ጠርቦ፣ እግዚአብሔር እንዳዘዘው በማለዳ ወደ ሲና ተራራ ወጣ፤ ሁለቱን የድንጋይ ጽላትም በእጆቹ ያዘ። 5.ከዚያም እግዚአብሔር በደመና ወረደ፤ በዚያም ከርሱ ጋራ ቆሞ ስሙን እግዚአብሔርን ዐወጀ። 6.እርሱም በሙሴ ፊት እንዲህ እያለ እያወጀ ዐለፈ፤ “እግዚአብሔር ርኅሩኅና ቸር አምላክ፣ እግዚአብሔር ለቍጣ የዘገየ፣ ፍቅሩና ታማኝነቱ የበዛ፣ 7.ፍቅርን ለሺሕዎች የሚጠብቅ፣ ክፋትን፣ ዐመፅንና ኀጢአትን ይቅር የሚል፣ በደለኛውን ግን ሳይቀጣ ዝም ብሎ አይተውም፤ በአባቶች ኀጢአት ልጆችን የልጅ ልጆቻቸውን እስከ ሦስትና አራት ትውልድ ይቀጣል።” 8.ሙሴም ወዲያውኑ ወደ መሬት ዝቅ ብሎ ሰገደ፤ 9.“አቤቱ ጌታ ሆይ፤ በፊትህ ሞገስ አግኝቼ ከሆነ፣ ጌታ ከእኛ ጋራ ይሂድ፤ ይህ ዐንገተ ደንዳና ሕዝብ ቢሆንም እንኳ፣ ክፋታችንንና ኀጢአታችንን ይቅር በል፤ እንደ ርስትህም አድርገህ ውሰደን።” 10.ከዚያም እግዚአብሔር እንዲህ አለ፤ “ከአንተ ጋራ ኪዳን እገባለሁ፤ ከዚህ ቀደም በዓለም ሁሉ ለየትኛውም ሕዝብ ከቶ ያልተደረገ፣ በሕዝብህ ሁሉ ፊት ድንቅ አደርጋለሁ፤ በመካከላቸው ዐብረሃቸው የምትኖር ሕዝብ እኔ እግዚአብሔር ለአንተ የማደርግልህ ሥራ የቱን ያህል አስፈሪ እንደ ሆነ ያያሉ። 11.ዛሬ የማዝዝህን ፈጽም፤ አሞራውያንን፣ ከነዓናውያንን፣ ኬጢያውያንን፣ ፌርዛውያንን፣ ኤዊያውያንንና ኢያቡሳውያንን በፊትህ አስወጣቸዋለሁ። 12.ከምትሄድበት አገር ነዋሪዎች ጋራ ቃል ኪዳን እንዳታደርግ ተጠንቀቅ፤ አለዚያ በመካከልህ ወጥመድ ይሆኑብሃል። 13.መሠዊያዎቻቸውን ሰባብሩ፤ የማምለኪያ ዐምዶቻቸውን አድቅቁ፤ የአሼራ ዐጸዶቻቸውንም ቍረጡ። 14.ስሙ ቀናተኛ የሆነው እግዚአብሔር ቀናተኛ አምላክ ነውና ሌላ አምላክ አታምልክ። 15.“በምድሪቱ ከሚኖሩት ጋራ ቃል ኪዳን እንዳታደርግ ተጠንቀቅ፤ ምክንያቱም አምላኮቻቸውን ተከትለው ባመነዘሩና መሥዋዕትም ባቀረቡላቸው ጊዜ ይጋብዙሃል፤ አንተም መሥዋዕታቸውን ትበላለህ። 16.ለወንዶች ልጆችህም ሴቶች ልጆቻቸውን ስታጭላቸውና እነዚህም ሴቶች ልጆች አምላኮቻቸውን በመከተል ሲያመነዝሩ፣ ወንዶች ልጆችህን ተመሳሳይ ድርጊት እንዲፈጽሙ ያነሣሧቸዋል። 17.“ቀልጠው የሚሠሩ አማልክትን አታብጅ። 18.“የቂጣን በዓል አክብር። እንዳዘዝሁህም ለሰባት ቀን ቂጣ ብላ፤ ይህንም በተወሰነው ጊዜ በአቢብ ወር አድርግ፤ በዚያ ወር ከግብጽ ወጥተሃልና። 19.“የመንጋህ ወይም የበግና የፍየልህ፣ የቀንድ ከብትህ ተባዕት በኵር ሁሉ ሳይቀር፣ ከማሕፀን በኵር ሆኖ የሚወጣ ሁሉ የእኔ ነው። 20.የአህያን በኵር በበግ ጠቦት ዋጀው፤ ካልዋጀኸው ግን ዐንገቱን ስበረው። በኵር ወንድ ልጆችህን ሁሉ ዋጅ።“ማንም በፊቴ ባዶ እጁን አይቅረብ። 21.“ስድስት ቀን ሥራ፤ በሰባተኛው ቀን ግን ዕረፍ፤ በዕርሻና በመከር ወቅት እንኳ ቢሆን ማረፍ አለብህ። 22.“የሰባቱን ሱባዔ የመከር በዓል ከስንዴው መከር በኵራት ጋራ፣ እንዲሁም የመክተቻ በዓልን በዓመቱ መጨረሻ ላይ አክብር። 23.በዓመት ሦስት ጊዜ ወንድ ሁሉ በእስራኤል አምላክ በጌታ እግዚአብሔር ፊት ይቅረብ። 24.አሕዛብን ከፊትህ አስወጣለሁ፤ ድንበርህን አሰፋለሁ፤ በዓመት ሦስት ጊዜ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ለመቅረብ ስትወጣ፣ ምድርህን ማንም አይመኝም። 25.“እርሾ ካለው ከማንኛውም ነገር ጋራ የደም መሥዋዕት ለእኔ አታቅርብ፤ ከፋሲካ በዓል የተረፈው መሥዋዕት እስከ ማለዳ አይቈይ። 26.“የምድርህን ምርጥ ፍሬ በኵራት ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ቤት አምጣ።
“ጠቦት ፍየልን በእናቱ ወተት አትቀቅል።” 27.ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን፣ “እነዚህን ቃሎች ጻፋቸው፤ በእነዚህ ቃሎች መሠረት ከአንተና ከእስራኤል ጋራ ቃል ኪዳን አድርጌአለሁና” አለው። 28.ሙሴ እህል ሳይበላ፣ ውሃም ሳይጠጣ ከእግዚአብሔር ጋራ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በዚያ ነበር፤ በጽላቱ ላይ የቃል ኪዳኑን ቃሎች፣ ዐሥርቱ ትእዛዛትን ጻፈ።
የሚያበራው የሙሴ ፊት
29.ሙሴ ሁለቱን የምስክር ጽላት በእጆቹ ይዞ ከሲና ተራራ በወረደ ጊዜ ከእግዚአብሔር ጋራ ከመነጋገሩ የተነሣ ፊቱ እንደሚያበራ አላወቀም ነበር። 30.አሮንና እስራኤላውያን ሁሉ ሙሴን ባዩት ጊዜ ፊቱ ያበራ ነበር፤ ወደ እርሱ ለመቅረብም ፈርተው ነበር። 31.ሙሴ ግን ጠራቸው፤ ስለዚህ አሮንና የማኅበሩ መሪዎች ወደ እርሱ ተመለሱ፤ እርሱም አናገራቸው። 32.ከዚያም በኋላ እስራኤላውያን ሁሉ ወደ እርሱ ቀረቡ፤ እግዚአብሔር በሲና ተራራ የሰጠውን ትእዛዞች ሁሉ ሰጣቸው። 33.ሙሴ ለእነርሱ ተናግሮ ከጨረሰ በኋላ በፊቱ ላይ መሸፈኛ አደረገ። 34.ሙሴም ከርሱ ጋራ ለመነጋገር ወደ እግዚአብሔር ሀልዎት በሚገባበት ጊዜ ሁሉ ግን፣ እስከሚወጣ ድረስ መሸፈኛውን ያነሣ ነበር፤ በወጣም ጊዜ የታዘዘውን ለእስራኤላውያን ነገራቸው። 35.የእስራኤልም ልጆች ፊቱ የሚያበራ መሆኑን አዩ፤ ከዚያም ሙሴ ከእግዚአብሔር ጋራ ለመነጋገር ተመልሶ እስኪሄድ ድረስ መሸፈኛውን መልሶ በፊቱ ላይ ያደርግ ነበር።ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች
ምዕራፍ 3
በሥጋ አለመመካት
1.ከዚህ በተረፈ ወንድሞቼ ሆይ፤ በጌታ ደስ ይበላችሁ! ያንኑ ደግሜ ብጽፍላችሁ፣ እኔ አይሰለቸኝም፤ ለእናንተም ይጠቅማችኋል። 2.ከእነዚያ ውሾች ተጠንቀቁ፤ ክፋትን ከሚያደርጉና ሥጋን ከሚቈራርጡ ሰዎች ተጠበቁ። 3.እኛ በእውነት የተገረዝን በእግዚአብሔር መንፈስ የምናመልክ፣ በክርስቶስ ኢየሱስ የምንመካ፣ በሥጋም የማንታመን ነንና። 4.ካስፈለገ እኔም በሥጋ የምመካበት አለኝ።ማንም በሥጋ የሚመካበት ነገር ያለው ቢመስለው፣ እኔ እበልጠዋለሁ፤ 5.በስምንተኛው ቀን የተገረዝሁ፣ ከእስራኤል ዘር፣ ከብንያም ወገን የተወለድሁ ስሆን፣ ከዕብራውያንም ዕብራዊ ነኝ፤ ስለ ሕግ ከተነሣ፣ ፈሪሳዊ ነበርሁ፤ 6.ስለ ቅናት ከሆነ፣ የቤተ ክርስቲያን አሳዳጅ ነበርሁ፤ ሕግን በመፈጸም ስለሚገኝ ጽድቅ ከሆነም፣ ያለ ነቀፋ ነበርሁ። 7.ነገር ግን ይጠቅመኝ የነበረውን ሁሉ አሁን ለክርስቶስ ስል እንደ ጕድለት ቈጥሬዋለሁ። 8.ከዚህም በላይ ለርሱ ብዬ ሁሉን ነገር የተውሁለትን፣ ወደር የሌለውን ጌታዬን ክርስቶስ ኢየሱስን ከማወቅ ታላቅነት ጋራ ሳነጻጽር፣ ሁሉንም ነገር እንደ ጕድለት እቈጥረዋለሁ፤ ለርሱ ስል ሁሉን ዐጥቻለሁ፤ ክርስቶስን አገኝ ዘንድ ሁሉን እንደ ጕድፍ እቈጥራለሁ፤ 9.ሕግ በመጠበቅ የሚገኝ የራሴ ጽድቅ ኖሮኝ ሳይሆን፣ በክርስቶስ በማመን ይኸውም ከእግዚአብሔር የሚመጣ፣ ከእምነትም በሆነ ጽድቅ በርሱ ዘንድ እንድገኝ ነው። 10.ክርስቶስንና የትንሣኤውን ኀይል እንዳውቅ፣ በሥቃዩ ተካፋይ እንድሆንና በሞቱም እርሱን እንድመስል እመኛለሁ፤ 11.ለሙታን ትንሣኤም እንድደርስ እናፍቃለሁ። 12.ይህን ሁሉ አግኝቻለሁ ወይም ፍጹም ሆኛለሁ ማለት አይደለም፤ ነገር ግን ክርስቶስ ኢየሱስ እኔን የራሱ ያደረገበትን ያን፣ እኔም የራሴ ለማድረግ እጣጣራለሁ። 13.ወንድሞች ሆይ፤ እኔ ገና እንደ ያዝሁት አድርጌ ራሴን አልቈጥርም፤ ነገር ግን አንድ ነገር አደርጋለሁ፤ ከኋላዬ ያለውን እየረሳሁ ከፊቴ ወዳለው እዘረጋለሁ። 14.እግዚአብሔር በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ላይ ስለ ጠራኝ፣ ሽልማት ለመቀዳጀት ወደ ግቡ እፈጥናለሁ።