Skip to Content
የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን | YEHIWOT MELHEK BETEKIRSTIAN
የ2019 ዓ.ም የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ 📖 ዛሬን አንብብ →

የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን

Yehiwot Melhek Betekirstian

ሳምንት 7 · ቀን 31 (ሰኞ) 📅 Tikimt 16, 2019

ኦሪት ዘጸአት 32, 33, 34 · ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 3

📖 የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም፦ 1954 መጽሐፍ ቅዱስ አዲሱ መደበኛ ትርጒም

ኦሪት ዘጸአት

ምዕራፍ 32

1.ሕዝቡም ሙሴ ከተራራው ሳይወርድ እንደ ዘገየ ባዩ ጊዜ፥ ወደ አሮን ተሰብስበው። ይህ ከግብፅ ምድር ያወጣን ሰው ሙሴ ምን እንደ ሆነ አናውቅምና ተነሥተህ በፊታችን የሚሄዱ አማልክት ሥራልን አሉት። 2.አሮንም። በሚስቶቻችሁ በወንዶችና በሴቶች ልጆቻችሁም ጆሮ ያሉትን የወርቅ ቀለበቶች ሰብራችሁ አምጡልኝ አላቸው። 3.ሕዝቡም ሁሉ በጆሮቻቸው ያሉትን የወርቅ ቀለበቶች ሰብረው ወደ አሮን አመጡለት። 4.ከእጃቸውም ተቀብሎ በመቅረጫ ቀረጸው፥ ቀልጦ የተሠራ ጥጃም አደረገው፤ እርሱም። እስራኤል ሆይ፥ እነዚህ ከግብፅ ምድር ያወጡህ አማልክትህ ናቸው አላቸው። 5.አሮንም ባየው ጊዜ መሠዊያን በፊቱ ሠራ፤ አሮንም።ነገ የእግዚአብሔር በዓል ነው ሲል አወጀ። 6.በነጋውም ማልደው ተነሥተው የሚቃጠል መሥዋዕት ሠዉ፥ የደኅነትም መሥዋዕት አቀረቡ፤ ሕዝቡም ሊበሉና ሊጠጡ ተቀመጡ፥ ሊዘፍኑም ተነሡ። 7.እግዚአብሔርም ሙሴን። ከግብፅ ምድር ያወጣኸው ሕዝብህ ኃጢአት ሠርተዋልና ሂድ፥ ውረድ። 8.ካዘዝኋቸው መንገድ ፈጥነው ፈቀቅ አሉ፤ ቀልጦ የተሠራ የጥጃ ምስል ለራሳቸው አደረጉ፥ ሰገዱለትም፥ ሠዉለትም። እስራኤል ሆይ፥ እነዚህ ከግብፅ ምድር ያወጡህ አማልክትህ ናቸው አሉ ሲል ተናገረው። 9.እግዚአብሔርም ሙሴን። እኔ ይህን ሕዝብ አየሁት፥ እነሆም አንገተ ደንዳና ሕዝብ ነው። 10.አሁንም ቍጣዬ እንዲቃጠልባቸው እንዳጠፋቸውም ተወኝ፤ አንተንም ለታላቅ ሕዝብ አደርግሃለሁ አለው። 11.ሙሴም በእግዚአብሔር በአምላኩ ፊት ጸለየ፥ አለም። አቤቱ፥ ቍጣህ በታላቅ ኃይልና በጽኑ እጅ ከግብፅ ምድር ባወጣኸው በሕዝብህ ላይ ስለ ምን ተቃጠለ? 12.ግብፃውያንስ። በተራራ መካከል ሊገድላቸው፥ ከምድርም ፊት ሊያጠፋቸው ለክፋት አወጣቸው ብለው ስለ ምን ይናገራሉ? ከመዓትህ ተመለስ፥ ለሕዝብህም በክፋታቸው ላይ ራራ። 13.ዘራችሁን እንደ ሰማይ ከዋክብት አበዛለሁ፥ ይህችንም የተናገርኋትን ምድር ሁሉ ለዘራችሁ እሰጣታለሁ፥ ለዘላለምም ይወርሱአታል ብለህ በራስህ የማልህላቸውን ባሪያዎችህን አብርሃምንና ይስሐቅን እስራኤልንም አስብ። 14.እግዚአብሔርም በሕዝቡ ላይ ሊያደርግ ስላሰበው ክፋት ራራ። 15.ሙሴም ተመለሰ፥ ሁለቱንም የምስክር ጽላቶች በእጁ ይዞ ከተራራው ወረደ፤ ጽላቶቹም በዚህና በዚያ በሁለት ወገን ተጽፎባቸው ነበር። 16.ጽላቶቹም የእግዚአብሔር ሥራ ነበሩ፤ ጽሕፈቱም በጽላቶች ላይ የተቀረጸባቸው የእግዚአብሔር ጽሕፈት ነበረ። 17.ኢያሱም እልል ሲሉ የሕዝቡን ድምፅ ሰምቶ ሙሴን። የሰልፍ ድምፅ በሰፈሩ ውስጥ አለ አለው። 18.እርሱም። ይህ የድል ነሺዎች ወይም የድል ተነሺዎች ድምፅ አይደለም፥ ነገር ግን የዘፈን ድምፅ እሰማለሁ አለው። 19.እንዲህም ሆነ፤ ወደ ሰፈሩ ሲቀርብ ጥጃውንም ዘፈኑንም አየ፤ የሙሴም ቍጣ ተቃጠለ፥ ጽላቶቹንም ከእጁ ጥሎ ከተራራው በታች ሰበራቸው። 20.የሠሩትንም ጥጃ ወስዶ በእሳት አቀለጠው፥ እንደ ትቢያም እስኪሆን ድረስ ፈጨው፥ በውኃውም ላይ በተነው፥ ለእስራኤልም ልጆች አጠጣው። 21.ሙሴም አሮንን። ይህን ታላቅ ኃጢአት ታመጣበት ዘንድ ይህ ሕዝብ ምን አደረገህ? አለው። 22.አሮንም እንዲህ አለ። ጌታዬ ሆይ፥ ቍጣህ አይቃጠል፤ ይህ ሕዝብ ክፋትን እንዲወድድ አንተ ታውቃለህ። 23.እነርሱም። ይህ ከግብፅ ምድር ያወጣን ሰው ሙሴ ምን እንደ ሆነ አናውቅምና በፊታችን የሚሄዱ አማልክት ሥራልን አሉኝ። 24.እኔም። ከእናንተ ወርቅ ያለው ሰው ከእርሱ ሰብሮ ያምጣልኝ አልኋቸው፤ ሰጡኝም፤ በእሳትም ላይ ጣልሁት፥ ይህም ጥጃ ወጣ። 25.ሙሴም በጠላቶቻቸው ፊት እንዲነወሩ አሮን ስድ ለቅቋቸዋልና ሕዝቡ ስድ እንደ ተለቀቁ ባየ ጊዜ፥ 26.በሰፈሩ ደጅ ቆሞ። የእግዚአብሔር ወገን የሆነ ወደ እኔ ይምጣ! አለ፤ የሌዊም ልጆች ሁሉ ወደ እርሱ ተሰበሰቡ። 27.እርሱም። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። የእናንተ ሰው ሁሉ ሰይፉን በወገቡ ላይ ይታጠቅ፥ በሰፈሩም ውስጥ በዚህና በዚያ ከበር እስከ በር ተመላለሱ፥ የእናንተም ሰው ሁሉ ወንድሙን ወዳጁንም ጎረቤቱንም ይግደል አላቸው። 28.የሌዊም ልጆች ሙሴ እንዳለ አደረጉ፤ በዚያም ቀን ከሕዝቡ ሦስት ሺህ ሰዎች ሞቱ። 29.ሙሴም። ዛሬ በረከትን እንዲያወርድላችሁ እያንዳንዳችሁ በልጃችሁና በወንድማችሁ ላይ ዛሬ እጃችሁን ለእግዚአብሔር ቅዱስ አድርጉ አለ። 30.በነጋውም ሙሴ ለሕዝቡ። እናንተ ታላቅ ኃጢአት ሠርታችኋል፤ አሁንም ወደ እግዚአብሔር እወጣለሁ፤ ምናልባት ኃጢአታችሁን አስተሰርይላችኋለሁ አላቸው። 31.ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ተመልሶ። ወዮ! እኒህ ሕዝብ ታላቅ ኃጢአት ሠርተዋል፥ ለራሳቸውም የወርቅ አማልክት አድርገዋል፤ 32.አሁን ይህን ኃጢአታቸውን ይቅር በላቸው፤ ያለዚያ ግን ከጻፍኸው መጽሐፍህ እባክህ ደምስሰኝ አለ። 33.እግዚአብሔርም ሙሴን። የበደለኝን እርሱን ከመጽሐፌ እደመስሰዋለሁ። 34.አሁንም ሂድ፥ ይህንም ሕዝብ ወደ ነገርሁህ ምራ፤ እነሆ መልአኬ በፊትህ ይሄዳል፤ ነገር ግን በምጐበኝበት ቀን ኃጢአታቸውን አመጣባቸዋለሁ አለው። 35.አሮን የሠራውን ጥጃ ስለ ሠሩ እግዚአብሔር ሕዝቡን ቀሠፈ።

ምዕራፍ 33

1.እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። ሂድ፥ ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም። ለዘርህ እሰጣታለሁ ብዬ ወደ ማልሁባት ምድር፥ ወተትና ማርም ወደምታፈስሰው ምድር አንተ ከግብፅ ምድር ካወጣኸው ሕዝብ ጋር ከዚህም ውጣ። አንገተ ደንዳና ሕዝብ ስለ ሆንህ በመንገድ ላይ እንዳላጠፋህ እኔ በአንተ መካከል አልወጣምና በፊትህ መልአክ እሰድዳለሁ፤ ከነዓናዊውን አሞራዊውንም ኬጢያዊውንም ፌርዛዊውንም ኤዊያዊውንም ኢያቡሳዊውንም አወጣልሃለሁ። 2. 3. 4.ሕዝቡም ይህን ክፉ ወሬ ሰምተው አዘኑ፤ ከእነርሱም ማንም ጌጡን አልለበሰም። 5.እግዚአብሔርም ሙሴን። ለእስራኤል ልጆች። እናንተ አንገተ ደንዳና ሕዝብ ናችሁ፥ አንድ ጊዜ በእናንተ መካከል ብወጣ አጠፋችኋለሁ፤ አሁንም የማደርግባችሁን አውቅ ዘንድ ጌጣችሁን ከእናንተ አውጡ በላቸው አለው። 6.የእስራኤልም ልጆች ከኮሬብ ተራራ ጀምረው ጌጣቸውን አወጡ። 7.ሙሴም ድንኳኑን እየወሰደ ከሰፈር ውጭ ይተክለው ነበር፤ ከሰፈሩም ራቅ ያደርገው ነበር፤ የመገናኛውም ድንኳን ብሎ ጠራው። እግዚአብሔርንም የፈለገ ሁሉ ከሰፈር ውጭ ወዳለው ወደ መገናኛው ድንኳን ይወጣ ነበር። 8.ሙሴም ወደ ድንኳኑ በሄደ ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ ይነሡ ነበር፥ እያንዳንዱም በድንኳኑ ደጃፍ ይቆም ነበር፥ ሙሴም ወደ ድንኳኑ እስኪገባ ድረስ ይመለከቱት ነበር። 9.ሙሴም ወደ ድንኳኑ በገባ ጊዜ የደመና ዓምድ ይወርድ ነበር፥ በድንኳኑም ደጃፍ ይቆም ነበር፤ እግዚአብሔርም ሙሴን ይናገረው ነበር። 10.ሕዝቡም ሁሉ የደመናው ዓምድ በድንኳኑ ደጃፍ ሲቆም ያየው ነበር፤ ሕዝቡም ሁሉ ተነሥቶ እያንዳንዱ በድንኳኑ ደጃፍ ይሰግድ ነበር። 11.እግዚአብሔርም ሰው ከባልንጀራው ጋር እንደሚነጋገር ፊት ለፊት ከሙሴ ጋር ይነጋገር ነበር። ሙሴም ወደ ሰፈሩ ይመለስ ነበር፤ ነገር ግን ሎሌው ብላቴና የነዌ ልጅ ኢያሱ ከድንኳኑ አይለይም ነበር። 12.ሙሴም እግዚአብሔርን። እነሆ አንተ። ይህን ሕዝብ አውጣ ትለኛለህ፤ ከእኔም ጋር የምትልከውን አላስታወቅኸኝም። አንተም። በስምህ አወቅሁህ፥ ደግሞም በእኔ ፊት ሞገስን አገኘህ አልኸኝ። 13.አሁንም በፊትህ ሞገስን አግኝቼ እንደ ሆነ፥ አውቅህ ዘንድ በፊትህም ሞገስን አገኝ ዘንድ መንገድህን እባክህ አሳየኝ፤ ይህም ሕዝብ ሕዝብህ እንደ ሆነ ተመልከት አለው። 14.እግዚአብሔርም። እኔ ከአንተ ጋር እሄዳለሁ፥ አሳርፍህማለሁ አለው። 15.እርሱም። አንተ ከእኛ ጋር ካልወጣህስ፥ ከዚህ አታውጣን። 16.በምድርም ፊት ካለው ሕዝብ ሁሉ እኔና ሕዝብህ የተለየን እንሆን ዘንድ አንተ ከእኛ ጋር ካልወጣህ፥ እኔና ሕዝብህ በአንተ ዘንድ ሞገስ ማግኘታችን በምን ይታወቃል? አለው። 17.እግዚአብሔርም ሙሴን። በፊቴ ሞገስ ስላገኘህ በስምህም ስላወቅሁህ ይህን ያልኸውን ነገር አደርጋለሁ አለው። 18.እርሱም። እባክህ ክብርህን አሳየኝ አለ። 19.እግዚአብሔርም። እኔ መልካምነቴን ሁሉ በፊትህ አሳልፋለሁ፤ የእግዚአብሔርንም ስም በፊትህ አውጃለሁ፤ ይቅርም የምለውን ይቅር እላለሁ፥ የምምረውንም እምራለሁ አለ። 20.ደግሞም። ሰው አይቶኝ አይድንምና ፊቴን ማየት አይቻልህም አለ። 21.እግዚአብሔርም አለ። እነሆ ስፍራ በእኔ ዘንድ አለ፥ በዓለቱም ላይ ትቆማለህ፤ 22.ክብሬም ባለፈ ጊዜ በሰንጣቃው ዓለት አኖርሃለሁ፥ እስካልፍ ድረስ እጄን በላይህ እጋርዳለሁ፤ 23.እጄንም ፈቀቅ አደርጋለሁ፥ ጀርባዬንም ታያለህ፤ ፊቴ ግን አይታይም።

ምዕራፍ 34

1.እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። ሁለት የድንጋይ ጽላቶች እንደ ፊተኞች አድርገህ ጥረብ፤ በሰበርኻቸው በፊተኞቹ ጽላቶች የነበሩትን ቃሎች እጽፍባቸዋለሁ። 2.ነገም የተዘጋጀህ ሁን፥ በማለዳም ወደ ሲና ተራራ ወጥተህ በዚያ በተራራው ራስ ላይ በፊቴ ቁም። 3.ከአንተም ጋር ማንም ሰው አይውጣ፥ በተራራውም ሁሉ ማንም አይታይ፤ መንጎችና ከብቶችም በዚያ ተራራ ፊት አይሰማሩ። 4.ሙሴም እንደ ፊተኞቹ አድርጎ ሁለት የድንጋይ ጽላቶች ጠረበ፤ በነጋውም ማልዶ እግዚአብሔር እንዳዘዘው ወደ ሲና ተራራ ወጣ፥ ሁለቱንም የድንጋይ ጽላቶች በእጁ ወሰደ፥ 5.እግዚአብሔርም በደመናው ውስጥ ወረደ፥ በዚያም ከእርሱ ጋር ቆመ፥ የእግዚአብሔርንም ስም አወጀ። 6.እግዚአብሔርም በፊቱ አልፎ። እግዚአብሔር፥ እግዚአብሔር መሐሪ፥ ሞገስ ያለው፥ ታጋሽም፥ ባለ ብዙ ቸርነትና እውነት፥ 7.እስከ ሺህ ትውልድም ቸርነትን የሚጠብቅ፥ አበሳንና መተላለፍን ኃጢአትንም ይቅር የሚል፥ በደለኛውንም ከቶ የማያነጻ፥ የአባቶችንም ኃጢአት በልጆች እስከ ሦስትና እስከ አራት ትውልድም በልጅ ልጆች የሚያመጣ አምላክ ነው ሲል አወጀ። 8.ሙሴም ፈጥኖ ወደ መሬት ተጐነበሰና ሰገደ። 9.አቤቱ በፊትህስ ሞገስን አግኝቼ እንደ ሆነ፥ ይህ አንገተ ደንዳና ሕዝብ ነውና ጌታዬ በመካከላችን ይሂድ፤ ጠማማነታችንንና ኃጢአታችንንም ይቅር በለን፥ ለርስትህም ተቀበለን አለ። 10.እርሱም አለው። እነሆ እኔ ቃል ኪዳን አደርጋለሁ፤ በምድር ሁሉ፥ በአሕዛብም ሁሉ ዘንድ እንደ እርሱ ያለ ከቶ ያልተደረገውን ተአምራት በሕዝብህ ሁሉ ፊት አደርጋለሁ፤ እኔም በአንተ ዘንድ የምሠራው ነገር የሚያስፈራ ነውና አንተ ያለህበት ይህ ሕዝብ ሁሉ የእግዚአብሔርን ሥራ ያያል። 11.በዚህ ቀን የማዝዝህን ነገር ጠብቅ፤ እነሆ እኔ አሞራዊውን ከነዓናዊውንም ኬጢያዊውንም ፌርዛዊውንም ኤዊያዊውንም ኢያቡሳዊውንም በፊትህ አወጣለሁ። 12.በመካከልህ ወጥመድ እንዳይሆኑብህ አንተ በምትሄድባት ምድር ከሚኖሩ ሰዎች ጋር ቃል ኪዳን እንዳታደርግ ተጠንቀቅ፤ 13.ነገር ግን መሠዊያዎቻቸውን ታፈርሳላችሁ፥ ሐውልቶቻቸውንም ትሰብራላችሁ፥ የማምለኪያ ዓፀዶቻቸውንም ትቈርጣላችሁ፤ 14.ስሙ ቀናተኛ የሆነ እግዚአብሔር ቅንዓት ያለው አምላክ ነውና ለሌላ አምላክ አትስገድ። 15.በዚያች ምድር ከሚኖሩ ሰዎች ጋር ቃል ኪዳን እንዳታደርግ፥ እነርሱ አምላኮቻቸውን ተከትለው ባመነዘሩና በሠዉላቸው ጊዜ እንዳይጠሩህ፥ ከመሥዋዕታቸውም እንዳትበላ፥ 16.ሴት ልጆቻቸውንም ከወንድ ልጆችህ ጋር እንዳታጋባ፥ ልጆቻቸውም አምላኮቻቸውን ተከትለው ሲያመነዝሩ ከአምላኮቻቸው በኋላ ሄደው አመንዝረውም ልጆችህን እንዳያስቱ ተጠንቀቅ። 17.ቀልጠው የተሠሩትን የአማልክት ምስሎች ለአንተ አታድርግ። 18.የቂጣውን በዓል ትጠብቀዋለህ። በአቢብ ወር ከግብፅ ወጥተሃልና በታዘዘው ዘመን በአቢብ ወር እንዳዘዝሁህ ሰባት ቀን ቂጣ እንጀራ ብላ። 19.ማኅፀንንም የሚከፍት ሁሉ የእኔ ነው፤ የከብትህም ተባት በኵር ሁሉ፥ በሬም ቢሆን በግም ቢሆን፥ የእኔ ነው። 20.የአህያውንም በኵር በጠቦት ትዋጀዋለህ፤ ባትዋጀውም አንገቱን ትሰብረዋለህ። የልጆችህንም በኵር ሁሉ ትዋጃለህ። በፊቴም አንድ ሰው ባዶ እጁን አይታይ። 21.ስድስት ቀን ትሠራለህ፥ በሰባተኛውም ቀን ታርፋለህ፤ በምታርስበትና በምታጭድበት ዘመን ታርፋለህ። 22.የሰባቱንም ሱባዔ በዓል ታደርጋለህ፥ እርሱም የስንዴ መከር በኵራት ነው፤ በዓመቱም ፍጻሜ የመክተቻ በዓል ታደርጋለህ። 23.በአንተ ዘንድ ያለው ወንድ ሁሉ በእስራኤል አምላክ በጌታ በእግዚአብሔር ፊት በዓመት ሦስት ጊዜ ይታይ። 24.አሕዛብን ከፊትህ አወጣለሁ፥ አገርህንም አሰፋለሁ፤ በአምላክህም በእግዚአብሔር ፊት ለመታየት በዓመት ሦስት ጊዜ ስትወጣ ማንም ምድርህን አይመኝም። 25.የመሥዋዕቴን ደም ከቦካ እንጀራ ጋር አትሠዋ፤ የፋሲካውም በዓል መሥዋዕት እስከ ነገ አይደር። 26.የተመረጠውን የምድርህን ፍሬ በኵራት ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ቤት ታገባለህ። ጠቦቱን በእናቱ ወተት አትቀቅልም። 27.እግዚአብሔርም ሙሴን። በእነዚህ ቃሎች መጠን ከአንተና ከእስራኤል ጋር ቃል ኪዳን አድርጌአለሁና እነዚህን ቃሎች ጻፍ አለው። 28.በዚያም አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ከእግዚአብሔር ጋር ነበረ፤ እንጀራም አልበላም፥ ውኃም አልጠጣም። በጽላቶቹም አሥሩን የቃል ኪዳን ቃሎች ጻፈ። 29.እንዲህም ሆነ፤ ሙሴ ከሲና ተራራ በወረደ ጊዜ ሁለቱ የምስክር ጽላቶች በሙሴ እጅ ነበሩ፤ ሙሴም ከተራራው በወረደ ጊዜ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ስለ ተነጋገረ የፊቱ ቁርበት እንዳንጸባረቀ አላወቀም ነበር። 30.አሮንና የእስራኤልም ልጆች ሁሉ ሙሴን ባዩ ጊዜ፥ እነሆ የፊቱ ቁርበት አንጸባረቀ፤ ወደ እርሱም ይቀርቡ ዘንድ ፈሩ። 31.ሙሴም ጠራቸው፤ አሮንም የማኅበሩን አለቆች ሁሉ ወደ እርሱ ተመለሱ፤ ሙሴም ተናገራቸው። 32.ከዚያም በኋላ የእስራኤል ልጆች ሁሉ ቀረቡ፤ እግዚአብሔርም በሲና ተራራ የተናገረውን ነገር ሁሉ አዘዛቸው። 33.ሙሴም ለእነርሱ ተናግሮ ከጨረሰ በኋላ በፊቱ መሸፈኛ አደረገ። 34.ሙሴም ከእርሱ ጋር ሲነጋገር ወደ እግዚአብሔር በገባ ጊዜ እስኪ ወጣ ድረስ መሸፈኛውን ከፊቱ አነሣ፤ በወጣም ጊዜ ለእስራኤል ልጆች የታዘዘውን ነገር ነገረ። 35.የእስራኤልም ልጆች የሙሴን ፊት ቁርበት እንዳንጸባረቀ ያዩ ነበር፤ እርሱም ከእርሱ ጋር ሊነጋገር እስኪገባ ድረስ እንደ ገና በፊቱ መሸፈኛ ያደርግ ነበር።

ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች

ምዕራፍ 3

1.በቀረውስ፥ ወንድሞቼ ሆይ፥ በጌታ ደስ ይበላችሁ። ስለ አንድ ነገር መልሼ ልጽፍላችሁ እኔን አይታክተኝም ለእናንተ ግን ደኅና ነው። 2.ከውሾች ተጠበቁ፥ ከክፉዎችም ሠራተኞች ተጠበቁ፥ ከሐሰተኛም መገረዝ ተጠበቁ። 3.እኛ በመንፈስ እግዚአብሔርን የምናመልክ በክርስቶስ ኢየሱስም የምንመካ በሥጋም የማንታመን እኛ የተገረዝን ነንና። 4.እኔ ግን በሥጋ ደግሞ የምታመንበት አለኝ። ሌላ ሰው ማንም ቢሆን በሥጋ የሚታመንበት እንዳለው ቢመስለው፥ እኔ እበልጠዋለሁ። 5.በስምንተኛው ቀን የተገረዝሁ፥ ከእስራኤል ትውልድ፥ ከብንያም ወገን፥ ከዕብራውያን ዕብራዊ ነኝ፤ ስለ ሕግ ብትጠይቁ፥ ፈሪሳዊ ነበርሁ፤ 6.ስለ ቅንዓት ብትጠይቁ፥ ቤተ ክርስቲያንን አሳዳጅ ነበርሁ፤ በሕግ ስለሚገኝ ጽድቅ ብትጠይቁ፥ ያለ ነቀፋ ነበርሁ። 7.ነገር ግን ለእኔ ረብ የነበረውን ሁሉ ስለ ክርስቶስ እንደ ጉዳት ቈጥሬዋለሁ።
8 -
9.አዎን፥ በእውነት ከሁሉ ይልቅ ስለሚበልጥ ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ ስለ ጌታዬ እውቀት ነገር ሁሉ ጉዳት እንዲሆን እቈጥራለሁ፤ ስለ እርሱ ሁሉን ተጐዳሁ፥ ክርስቶስንም አገኝ ዘንድ፥ በክርስቶስም በማመን ያለው ጽድቅ ማለት በእምነት ከእግዚአብሔር ዘንድ ያለው ጽድቅ እንጂ ከሕግ ለእኔ ያለው ጽድቅ ሳይሆንልኝ፥ በእርሱ እገኝ ዘንድ ሁሉን እንደ ጕድፍ እቈጥራለሁ፤
10 -
11.እርሱንና የትንሣኤውን ኃይል እንዳውቅ፥ በመከራውም እንድካፈል፥ ወደ ሙታንም ትንሣኤ ልደርስ ቢሆንልኝ፥ በሞቱ እንድመስለው እመኛለሁ። 12.አሁን እንዳገኘሁ ወይም አሁን ፍጹም እንደ ሆንሁ አይደለም፥ ነገር ግን ስለ እርሱ በክርስቶስ ኢየሱስ የተያዝሁበትን ያን ደግሞ እይዛለሁ ብዬ እፈጥናለሁ። 13.ወንድሞች ሆይ፥ እኔ ገና እንዳልያዝሁት እቈጥራለሁ፤ ነገር ግን አንድ ነገር አደርጋለሁ፤ በኋላዬ ያለውን እየረሳሁ በፊቴ ያለውን ለመያዝ እዘረጋለሁ፥ 14.በክርስቶስ ኢየሱስ ከፍ ከፍ ያለውን የእግዚአብሔርን መጥራት ዋጋ እንዳገኝ ምልክትን እፈጥናለሁ። 15.እንግዲህ ፍጹማን የሆንን ሁላችን ይህን እናስብ፤ በአንዳች ነገርም ልዩ አሳብ ቢኖራችሁ፥ እግዚአብሔር ይህን ደግሞ ይገልጥላችኋል፤ 16.ሆኖም በደረስንበት በዚያ እንመላለስ። 17.ወንድሞች ሆይ፥ እኔን የምትመስሉ ሁኑ፥ እኛም እንደ ምሳሌ እንደምንሆንላችሁ፥ እንዲሁ የሚመላለሱትን ተመልከቱ። 18.ብዙዎች ለክርስቶስ መስቀል ጠላቶቹ ሆነው ይመላለሳሉና፤ ብዙ ጊዜ ስለ እነርሱ አልኋችሁ፥ አሁንም እንኳ እያለቀስሁ እላለሁ። 19.መጨረሻቸው ጥፋት ነው፥ ሆዳቸው አምላካቸው ነው፥ ክብራቸው በነውራቸው ነው፥ አሳባቸው ምድራዊ ነው። 20.እኛ አገራችን በሰማይ ነውና፥ ከዚያም ደግሞ የሚመጣ መድኃኒትን እርሱንም ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን እንጠባበቃለን፤ 21.እርሱም ሁሉን እንኳ ለራሱ ሊያስገዛ እንደሚችልበት አሠራር፥ ክቡር ሥጋውን እንዲመስል የተዋረደውን ሥጋችንን ይለውጣል።
♫
Listen to the reading 4 chapter tracks
ኦሪት ዘጸአት Chapter 32
ኦሪት ዘጸአት Chapter 33
ኦሪት ዘጸአት Chapter 34
ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች Chapter 3
Swipe to browse chapters
Listen 4