Skip to Content
የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን | YEHIWOT MELHEK BETEKIRSTIAN
የ2019 ዓ.ም የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ 📖 ዛሬን አንብብ →

የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን

Yehiwot Melhek Betekirstian

ሳምንት 5 · ቀን 25 (አርብ) 📅 Tikimt 6, 2019

ኦሪት ዘጸአት 13, 14, 15 · መዝሙረ ዳዊት 114 · ወደ ኤፌሶን ሰዎች 3

📖 የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም፦ 1954 መጽሐፍ ቅዱስ አዲሱ መደበኛ ትርጒም

ኦሪት ዘጸአት

ምዕራፍ 13

በኵር ሁሉ ለእግዚአብሔር መቀደሱ

1.እግዚአብሔር ሙሴን አለው፤ 2.“መጀመሪያ የተወለደውን ወንድ ሁሉ ለእኔ ቀድስልኝ፤ ከእስራኤላውያን መካከል የእናቱ የበኵር ልጅ የሆነው ማሕፀን ከፋች ሰውም ሆነ እንስሳ የእኔ ነው።” 3.ከዚያም ሙሴ ሕዝቡን እንዲህ አለ፤ “ከባርነት ምድር ከግብጽ የወጣችሁባትን ይህችን ዕለት አስታውሱ፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር በኀያል ክንዱ አውጥቷችኋል። እርሾ ያለበትን ማንኛውንም ነገር አትብሉ። 4.እነሆ በዚች ዕለት በአቢብ ወር ወጥታችኋል። 5.እግዚአብሔር ለእናንተ ለመስጠት ሲል ቀድሞ ለአባቶቻችሁ ወደ ማለላቸው ማርና ወተት ወደምታፈስሰው ወደ ከነዓናውያን፣ ኬጢያውያን፣ አሞራውያን፣ ኤዊያውያን፣ ኢያቡሳውያን ምድር በምትገቡበት ጊዜ ይህን በዓል በዚህ ወር ታከብራላችሁ። 6.ለሰባት ቀን ያለ እርሾ የተጋገረ ቂጣ ትበላላችሁ፤ በሰባተኛውም ቀን ለእግዚአብሔር በዓል ታደርጋላችሁ። 7.በእነዚህም ሦስት ቀናት ቂጣ ትበላላችሁ፤ በእናንተ ዘንድ እርሾ ያለበት ነገር ፈጽሞ አይገኝ፤ በምድራችሁም አዋሳኝ በየትኛውም ቦታ እርሾ ፈጽሞ አይኑር። 8.በዚያችም ዕለት፣ ‘እኔ ይህን የማደርገው ከግብጽ ምድር በወጣሁበት ጊዜ እግዚአብሔር ስላደረገልኝ ነገር ነው’ ብለህ ለልጅህ ንገረው። 9.የእግዚአብሔር ሕግ በከንፈራችሁ ላይ እንዲሆን ይህ በዓል ለእናንተ በእጃችሁ ላይ እንደ ታሰረ ምልክት፣ በእግራችሁ ላይ እንደሚገኝ መታሰቢያ ይሆንላችኋል። እግዚአብሔር በኀያል ክንዱ ከግብጽ አውጥቷችኋልና። 10.ይህን ሥርዐት በተወሰነው ጊዜ በየዓመቱ ጠብቁት። 11.“እግዚአብሔር ለእናንተና ለቀደሙት አባቶቻችሁ በመሐላ በሰጠው ተስፋ መሠረት ወደ ከነዓናውያን አገር በሚያስገባችሁና ምድሪቱንም ለእናንተ በሚሰጣችሁ ጊዜ፣ 12.የእናቱን ማሕፀን የሚከፍተውን ሁሉ ለእግዚአብሔር ትሰጣላችሁ፤ እንደዚሁም እንስሶቻችሁ በመጀመሪያ የወለዷቸው ወንዶች ሁሉ ለእግዚአብሔር ይሆናሉ። 13.ከአህያ በመጀመሪያ የተወለደውን ውርንጫ ግን በጠቦት ትዋጁታላችሁ፤ አህያውን ካልዋጃችሁት ግን ዐንገቱን ስበሩት። ከወንድ ልጆቻችሁ መካከል በኵር የሆኑትን ሁሉ ዋጁ። 14.“በሚመጡት ዘመናት ልጅህ፣ ‘ይህ ምን ማለት ነው?’ ብሎ ቢጠይቅህ እንዲህ በለው፤ ‘ከባርነት ምድር ከግብጽ እግዚአብሔር በኀያል ክንዱ አወጣን፤ 15.ፈርዖን እኛን አልለቅም ብሎ ልቡን ባደነደነ ጊዜ ከሰው ጀምሮ እስከ እንስሳ ድረስ በኵር ሆኖ በግብጽ የተወለደውን ሁሉ እግዚአብሔር ገደለው። እንግዲህ በመጀመሪያ የእናቱን ማሕፀን የከፈተውን ወንድ ሁሉ ለእግዚአብሔር የምሠዋውና የልጆቼ በኵር ሆኖ የተወለደውን ወንድ ልጅ ሁሉ የምዋጀው በዚህ ምክንያት ነው።’ 16.እግዚአብሔር በኀያል ክንዱ እኛን ከግብጽ ያወጣን ስለ ሆነ ይህ ሥርዐት በእጅህም ሆነ በግንባርህ ላይ እንደ ምልክት ይሆናል።”

ቀይ ባሕርን መሻገር

17.ፈርዖን ሕዝቡን በለቀቀ ጊዜ አቋራጭ ቢሆንም እንኳ እግዚአብሔር በፍልስጥኤም ምድር በሚያልፈው መንገድ አልመራቸውም፤ “ጦርነት ቢያጋጥማቸው ሐሳባቸውን ለውጠው ወደ ግብጽ ይመለሱ ይሆናል” ብሏልና። 18.ስለዚህ እግዚአብሔር ሕዝቡን ዙሪያ በሆነው በምድረ በዳው መንገድ ወደ ቀይ ባሕር መራቸው፤ እስራኤላውያንም ለጦርነት ዝግጁ ሆነው ከግብጽ ወጡ። 19.ዮሴፍ፣ “እግዚአብሔር በርግጥ ይጐበኛችኋል፤ በዚያ ጊዜም ዐፅሜን ይዛችሁ ከዚች ምድር መውጣት አለባችሁ” ብሎ የእስራኤልን ልጆች አስምሏቸው ስለ ነበር ሙሴ የዮሴፍን ዐፅም ይዞ ወጣ። እግዚአብሔር ሕዝቡን ዙሪያ በሆነው በምድረ በዳው መንገድ ወደ ቀይ ባሕር መራቸው፤ እስራኤላውያንም ለጦርነት ዝግጁ ሆነው ከግብጽ ወጡ። 20.እነርሱም ከሱኮት ከተነሡ በኋላ ከምድረ በዳው ጥግ ባለው በኤታም ሰፈሩ። 21.ስለዚህ በቀንም ሆነ በሌሊት መጓዝ ይችሉ ዘንድ፣ እግዚአብሔር በቀን በመንገዳቸው ሊመራቸው በደመና ዓምድ፣ በሌሊት ደግሞ ብርሃን ሊሰጣቸው በእሳት ዐምድ በፊታቸው ይሄድ ነበር። 22.በቀንም ሆነ በሌሊት የደመናውና የእሳቱ ዐምድ ከሕዝቡ ፊት የተለየበት ጊዜ አልነበረም።

ምዕራፍ 14

1.ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን አለው፤ 2.“እስራኤላውያን ተመልሰው በሚግዶልና በባሕሩ መካከል ባለው በፊሀሒሮት አጠገብ እንዲሰፍሩ ንገራቸው፤ በበኣልዛፎንም አንጻር በባሕሩ አጠገብ ይስፈሩ። 3.‘ፈርዖን እስራኤላውያን ግራ ተጋብተው በምድረ በዳ በመቅበዝበዝ ይንከራተታሉ’ ብሎ ያስባል። 4.እኔም የፈርዖንን ልብ ስለማደነድነው ያሳድዳቸዋል፤ ነገር ግን በፈርዖንና በሰራዊቱ ሁሉ ለራሴ ክብርን አገኛለሁ፤ ግብጻውያንም እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ያውቃሉ።” እስራኤላውያንም ይህንኑ አደረጉ። 5.የግብጽ ንጉሥ ሕዝቡ መሄዳቸው በተነገረው ጊዜ፣ ፈርዖንና ሹማምቱ ስለ እነርሱ የነበራቸውን ሐሳብ በመለወጥ፣ “ምን ማድረጋችን ነው? እስራኤላውያን እንዲሄዱ ለቀቅናቸው፤ አገልግሎታቸውንም ዐጣን” አሉ። 6.ስለዚህ ሠረገላው እንዲዘጋጅለት አደረገ፤ ሰራዊቱንም ይዞ ተንቀሳቀሰ። 7.ስድስት መቶ ምርጥ ሠረገላዎችን ከሌሎች የግብጽ ሠረገላዎች ጋራ ከነጦር አዛዦቻቸው አሰልፎ ተነሣ። 8.እግዚአብሔር የንጉሡን የፈርዖንን ልብ ስለ አደነደነው በልበ ሙሉነት ከግብጽ የሚወጡትን እስራኤላውያን አሳደዳቸው። 9.ግብጻውያን፣ ይኸውም የፈርዖን ፈረሶችና ሠረገላዎች፣ ፈረሰኞችና እግረኞች ሁሉ እስራኤላውያንን አሳደዷቸው፤ በበኣልዛፎን አንጻር በባሕሩ አጠገብ በፊሀሒሮት ሰፍረው ሳሉ ደረሱባቸው። 10.ፈርዖን በቀረበ ጊዜ እስራኤላውያን ቀና ብለው ተመለከቱ፤ እነሆ፣ ግብጻውያን ይከታተሏቸው ነበር፤ እነርሱም በታላቅ ፍርሀት ወደ እግዚአብሔር ጮኹ። 11.እነርሱም ሙሴን እንዲህ አሉት፤ “በምድረ በዳ እንድንሞት ያመጣኸን በግብጽ መቃብር ቦታ ጠፍቶ ነውን? ከግብጽ አውጥተህ ምን አደረግህልን? 12.በግብጽ ሳለን፣ ‘ተወን እባክህ፤ ግብጻውያንን እናገልግል’ አላልንህም ነበርን? በምድረ በዳ ከምንሞት ግብጻውያንን ብናገለግል ይሻል ነበር!” 13.ሙሴም ለሕዝቡ መለሰላቸው፤ “አትሸበሩ፣ ጸንታችሁ ቁሙ፤ እግዚአብሔር ዛሬ የሚያደርግላችሁን መታደግ ታያላችሁ፤ ዛሬ የምታዩአቸውን ግብጻውያንን ዳግም አታዩአቸውም። 14.እግዚአብሔር ስለ እናንተ ይዋጋል፤ እናንተ ያለባችሁ መታገሥ ብቻ ነው።” 15.ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ለምን ትጮኹብኛላችሁ? ይልቅስ እስራኤላውያንን ወደ ፊት እንዲጓዙ ንገራቸው፤ 16.ውሃውን ለመክፈል በትርህን አንሣና እጅህን በባሕሩ ላይ ዘርጋ፤ እስራኤላውያን በባሕሩ ውስጥ በየብስ ይሻገራሉ። 17.ተከትለዋቸው እንዲገቡም የግብጻውያንን ልብ አጸናለሁ፤ በፈርዖንና በሰራዊቱ ሁሉ፣ በሠረገሎቹና በፈረሰኞቹ ለራሴ ክብርን አገኛለሁ። 18.በፈርዖንና በሰራዊቱ ሁሉ በከበርሁ ጊዜ፣ ግብጻውያን እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።” 19.ከዚያም ከእስራኤል ሰራዊት ፊት ፊት ሆኖ ሲሄድ የነበረው የእግዚአብሔር መልአክ ተመለሰና ወደ ኋላቸው መጣ፤ የደመናውም ዐምድ እንዲሁ ከፊት ተነሥቶ ከኋላቸው ቆመ፤ 20.በግብጽና በእስራኤል ሰራዊት መካከል በመሆን፣ ሌሊቱን ሙሉ ደመናው በአንድ በኩል ጨለማን ሲያመጣ፣ በሌላው በኩል ብርሃን አመጣ፤ ስለዚህ ሌሊቱን በሙሉ አንዱ ወደ ሌላው ሊጠጋ አልቻለም። 21.ሙሴ እጁን በባሕሩ ላይ ዘረጋ፤ እግዚአብሔር ሌሊቱን በሙሉ ብርቱ የምሥራቅ ነፋስ አስነሥቶ ባሕሩን ወደ ኋላ በማሸሽ ደረቅ ምድር አደረገው፤ ውሃውም ተከፈለ። 22.እስራኤላውያን ውሃው በግራና በቀኝ እንደ ግድግዳ ሆኖ በየብስ በባሕሩ ውስጥ ዐለፉ። 23.ግብጻውያንም አሳደዷቸው፤ የፈርዖን ፈረሶች፣ ሠረገሎችና ፈረሰኞች በሙሉ ተከትለዋቸው ወደ ባሕሩ ገቡ። 24.ሲነጋጋም እግዚአብሔር በእሳትና በደመና ዐምድ ሆኖ የግብጻውያንን ሰራዊት ቍልቍል ተመለከተ፤ በግብጻውያን ሰራዊት ላይም ሽብር ላከባቸው። 25.መንዳት እንዳይችሉም የሠረገላዎቹን መሽከርከሪያዎች አቈላለፈባቸው፤ ግብጻውያኑም፣ “ከእስራኤላውያን እንሽሽ! እግዚአብሔር ግብጽን እየተዋጋላቸው ነው” አሉ። 26.ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን፣ “ውሃው ግብጻውያንን ሠረገሎቻቸውንና ፈረሰኞቻቸውን ተመልሶ እንዲሸፍናቸው እጅህን በባሕሩ ላይ ዘርጋ” አለው። 27.ሙሴም እጁን በባሕሩ ላይ ዘረጋ፤ ንጋት ላይም ባሕሩ ወደ ቀድሞ ቦታው ተመለሰ። ግብጻውያን ከውሃው ሸሹ፤ እግዚአብሔርም ግብጻውያንን በባሕሩ ውስጥ ጣላቸው። 28.ውሃውም ተመልሶ እስራኤላውያንን ተከትለው ወደ ባሕሩ የገቡትን ሠረገሎች፣ ፈረሰኞች፣ መላውን የፈርዖን ሰራዊት ሁሉ ሸፈነ። አንድም እንኳ አልተረፈም። 29.እስራኤላውያን ግን ውሃው ግራና ቀኝ እንደ ግድግዳ ሆኖ፣ በደረቅ ምድር ባሕሩን ተሻገሩ። 30.በዚያች ዕለት እግዚአብሔር እስራኤልን ከግብጻውያን እጅ አዳናቸው፤ እስራኤልም የግብጻውያን ሬሳ በባሕሩ ዳርቻ ወድቆ ተመለከቱ። 31.እስራኤላውያን እግዚአብሔር በግብጻውያን ላይ ያደረገውን ታላቅ ኀይል ባዩ ጊዜ፣ እግዚአብሔርን ፈሩ፤ በእግዚአብሔርና በባሪያው በሙሴም አመኑ።

ምዕራፍ 15

የሙሴና የማርያም መዝሙር

1.ከዚያም ሙሴና እስራኤላውያን ይህን መዝሙር ለእግዚአብሔር ዘመሩ፤
“ከፍ ከፍ ብሎ ከብሯልና፣
ለእግዚአብሔር እዘምራለሁ፤
ፈረሱንና ፈረሰኛውን፣
በባሕር ውስጥ ጥሏልና።
2.“እግዚአብሔር ብርታቴና ዝማሬዬ ነው፤
ድነቴም ሆነልኝ፤
እርሱ አምላኬ ነው፤ አመሰግነዋለሁ፤
የአባቴ አምላክ ነው፤ እኔም ከፍ ከፍ አደርገዋለሁ።
3.እግዚአብሔር ተዋጊ ነው፤
ስሙም እግዚአብሔር ነው።
4.የፈርዖንን ሠረገሎችና ሰራዊት፣
ባሕር ውስጥ ጣላቸው፤
ምርጥ የሆኑት የፈርዖን ሹማምት፣
ቀይ ባሕር ውስጥ ሰጠሙ።
5.ቀላያትንም ለበሱ፤
እንደ ድንጋይ ወደ ጥልቁ ወረዱ።
6.አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ፤
ቀኝ እጅህ በግርማ ከበረ፤
አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ፤
ቀኝ እጅህ ጠላትን አደቀቀ።
7.“በግርማህ ታላቅነት፣
የተቃወሙህን ጣልሃቸው፤
ቍጣህን ሰደድህ፤
እንደ ገለባም በላቸው።
8.በአፍንጫህ እስትንፋስ፣
ውሆች ተቈለሉ፤
ፈሳሾችም እንደ ግድግዳ ቆሙ፤
የጥልቁ ውሃ ባሕሩ ውስጥ ረጋ።
9.ጠላት፣ ‘አሳድዳቸዋለሁ፤
እማርካቸዋለሁ፤
ምርኮን እካፈላለሁ፤
ነፍሴ በእነርሱ ትጠግባለች፤
ሰይፌን እመዝዛለሁ፤
እጄም ትደመስሳቸዋለች አለ።’
10.አንተ ግን እስትንፋስህን አነፈስህ፤
ባሕርም ከደናቸው፤
በኀያላን ውሆች፣
እንደ ብረት ሰጠሙ።
11.አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ፤
ከአማልክት መካከል፣ እንደ አንተ ማን አለ?
በቅድስናው የከበረ፣
በክብሩ የሚያስፈራ፣
ድንቆችን የሚያደርግ፣
እንደ አንተ ማን አለ?
12.“ቀኝ እጅህን ዘረጋህ፤
ምድርም ዋጠቻቸው።
13.በማይለወጠው ፍቅርህ፣
የተቤዠሃቸው ሕዝብህን ትመራለህ፤
እነርሱን በብርታትህ፣
ወደ ቅዱስ ማደሪያህ ትመራቸዋለህ።
14.አሕዛብ ይሰማሉ፤ ይንቀጠቀጡማል፤
የፍልስጥኤምን ሕዝብ ሥቃይ ይይዛቸዋል።
15.የኤዶምም አለቆች ይርዳሉ፤
የሞዓብ አለቆች በእንቅጥቃጤ ይያዛሉ፤
የከነዓን ሕዝብ ይቀልጣሉ።
16.አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ፤ ሕዝብህ
እስከሚያልፉ ድረስ፣
የተቤዠሃቸው ሕዝብህ እስኪያልፉ ድረስ፣
ድንጋጤና ሽብር በእነርሱ ላይ ይመጣል፤
በክንድህ ብርታት፣
እንደ ድንጋይ የማይንቀሳቀሱ ይሆናሉ።
17.እግዚአብሔር ሆይ፤ ማደሪያህ
እንዲሆን በሠራኸው ስፍራ፣
ጌታ ሆይ፤ እጆችህ በሠሩት መቅደስ፣
በርስትህ ተራራ ላይ፣ ታመጣቸዋለህ፤ ትተክላቸዋለህም።
18.“እግዚአብሔር፣
ከዘላለም እስከ ዘላለም ይነግሣል።”
19.የፈርዖን ፈረሶች፣ ሠረገሎቹና ፈረሰኞቹ ወደ ባሕሩ በገቡ ጊዜ እግዚአብሔር የባሕሩን ውሃ በላያቸው ላይ መለሰባቸው፤ እስራኤላውያን ግን በባሕሩ ውስጥ በደረቅ ምድር ተሻገሩ። 20.ከዚያም የአሮን እኅት ነቢዪቱ ማርያም ከበሮዋን አንሥታ ያዘች፤ የቀሩትም ሴቶች ሁሉ ከበሮ ይዘው እያሸበሸቡ ተከተሏት። 21.ማርያምም፣
“ፈረሱንና ፈረሰኛውን፣
በባሕር ውስጥ ጥሏል፤ ለእግዚአብሔር ዘምሩ፤
እጅግ ከፍ ከፍ ብሏልና”
እያለች ዘመረችላቸው።

የማራና የኤሊም ውሃ

22.ከዚያም ሙሴ እስራኤልን ከቀይ ባሕር እየመራቸው ወደ ሱር ምድረ በዳ ሄዱ፤ ለሦስት ቀናት ውሃ ሳያገኙም በምድረ በዳ ተጓዙ። 23.ማራ በደረሱ ጊዜ ውሃው መራራ ስለ ነበር ሊጠጡት አልቻሉም፤ ቦታው ማራ ተብሎ የተጠራውም ከዚህ የተነሣ ነው። 24.ሕዝቡም በሙሴ ላይ በማጕረምረም፣ “ምን እንጠጣ?” አሉ። 25.ከዚያም ሙሴ ወደ እግዚአብሔር ጮኸ፤ እግዚአብሔር አንዲት ዛፍ አሳየው፤ ዕንጨቷንም ወደ ውሃው ጣላት፤ ውሃውም ጣፋጭ ሆነ።
በዚያም እግዚአብሔር ሕግና ሥርዐት አበጀላቸው፤ በዚያም ስፍራ ፈተናቸው።
26.እርሱም አለ፤ “የአምላካችሁን እግዚአብሔር ድምፅ በጥንቃቄ ብትሰሙ፣ በፊቱም ትክክል የሆነውን ብትፈጽሙ፣ ትእዛዞቹን ልብ ብትሉና ሥርዐቱንም ሁሉ ብትጠብቁ፣ በግብጻውያን ላይ ያመጣሁባቸውን ማንኛውንም ዐይነት በሽታ በእናንተ ላይ አላመጣም፤ ፈዋሻችሁ እኔ እግዚአብሔር ነኝና።” 27.ከዚያም ዐሥራ ሁለት ምንጮችና ሰባ የዘንባባ ዛፎች ወዳሉበት ወደ ኤሊም መጡ፤ እነርሱም በውሃው አጠገብ በዚያ ሰፈሩ።

መዝሙረ ዳዊት

ምዕራፍ 114

1.እስራኤል ከግብጽ ወጥቶ ሲሄድ፣
የያዕቆብም ቤት ቋንቋው ልዩ ከሆነ ሕዝብ ተለይቶ ሲወጣ፣
2.ይሁዳ የእግዚአብሔር መቅደስ፣
እስራኤልም ግዛቱ ሆነ።
3.ባሕር አየች፤ ሸሸችም፤
ዮርዳኖስም ወደ ኋላው ተመለሰ።
4.ተራሮች እንደ አውራ በግ፣
ኰረብቶችም እንደ ጠቦት ዘለሉ።
5.አንቺ ባሕር፤ የሸሸሽው አንቺም ዮርዳኖስ ያፈገፈግሽው ለምንድን ነው? 6.እናንተ ተራሮች እንደ አውራ በግ፣
ኰረብቶችም እንደ ጠቦት ለምን ዘለላችሁ?
7.ምድር ሆይ፤ በጌታ ፊት፣
በያዕቆብ አምላክ ፊት ተንቀጥቀጪ፤
8.እርሱ ዐለቱን ወደ ኵሬ፣
ቋጥኙንም ወደ ውሃ ምንጭ ለወጠ።

ወደ ኤፌሶን ሰዎች

ምዕራፍ 3

ለአሕዛብ ሐዋርያ የሆነው ጳውሎስ

1.በዚህም ምክንያት እኔ ጳውሎስ ለእናንተ ለአሕዛብ የክርስቶስ ኢየሱስ እስረኛ ሆኛለሁ። 2.ስለ እናንተ ስለ ተሰጠኝ የእግዚአብሔር ጸጋ መጋቢነት በርግጥ ሰምታችኋል፤ 3.ቀደም ሲል በዐጭሩ እንደ ጻፍሁት፣ በመገለጥ እንዳውቀው የተደረገው ምስጢር ይህ ነው። 4.እንግዲህ ይህን ስታነብቡ፣ የክርስቶስን ምስጢር እንዴት እንደማስተውል ለመረዳት ትችላላችሁ። 5.ይህም ምስጢር በመንፈስ አሁን ለቅዱሳኑ ሐዋርያትና ነቢያት የተገለጠውን ያህል ባለፉት ዘመናት ለነበሩ ሰዎች አልተገለጠም ነበር። 6.ይህም ምስጢር አሕዛብ በወንጌል አማካይነት ከእስራኤል ጋራ ዐብረው ወራሾች፣ ዐብረው የአንዱ አካል ብልቶች እንዲሁም በክርስቶስ ኢየሱስ በሆነው ተስፋ ዐብረው ተካፋይ መሆናቸው ነው። 7.እኔም በኀይሉ አሠራር በተሰጠኝ በእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ የዚህ ወንጌል አገልጋይ ሆኛለሁ። 8.ምንም እንኳ ከቅዱሳን ሁሉ ያነስሁ ብሆንም፣ የማይመረመረውን የክርስቶስን ባለጠግነት ለአሕዛብ እሰብክ ዘንድ ይህ ጸጋ ለእኔ ተሰጠኝ። 9.እንዲሁም ሁሉን በፈጠረ በእግዚአብሔር ላለፉት ዘመናት የተሰወረውን የዚህን ምስጢር አሠራር ለሁሉም እገልጥ ዘንድ ተሰጠኝ። 10.ሐሳቡም በአሁኑ ዘመን በቤተ ክርስቲያን አማካይነት ብዙ ገጽታ ያለው የእግዚአብሔር ጥበብ በሰማያዊ ስፍራ ላሉት ገዦችና ባለሥልጣናት ይታወቅ ዘንድ ነው፤ 11.ይህም በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን በፈጸመው ዘላለማዊ ዕቅዱ መሠረት ነው። 12.በርሱና በርሱ ላይ ባለን እምነት አማካይነት፣ በነጻነትና በልበ ሙሉነት ወደ እግዚአብሔር መቅረብ እንችላለን። 13.ስለዚህ ክብራችሁ በሆነው ስለ እናንተ በደረሰብኝ መከራ ተስፋ እንዳትቈርጡ ዐደራ እላችኋለሁ።

ለኤፌሶን ሰዎች የተደረገ ጸሎት

14.በዚህም ምክንያት በአብ ፊት እንበረከካለሁ፤ 15.ከርሱም በሰማይና በምድር ያለ ቤተ ሰብ ሁሉ ስያሜ ያገኛል። 16.በውስጥ ሰውነታችሁ እንድትጠነክሩ፣ ከክብሩ ባለጠግነት በመንፈሱ በኩል ኀይል እንዲሰጣችሁ እጸልያለሁ፤ 17.ይኸውም በእምነት ክርስቶስ በልባችሁ እንዲያድር ነው። ደግሞም ሥር ሰድዳችሁ፣ በፍቅር ታንጻችሁ፣ 18.የክርስቶስ ፍቅር ስፋቱ፣ ርዝመቱ፣ ከፍታውና ጥልቀቱ ምን ያህል እንደ ሆነ፣ ከቅዱሳን ሁሉ ጋራ የመገንዘብ ኀይልን እንድታገኙ ነው። 19.እስከ እግዚአብሔር ሙላት ሁሉ ልክ ደርሳችሁ እንድትሞሉ፣ ከመታወቅ በላይ የሆነውን የክርስቶስን ፍቅር ታውቁም ዘንድ ነው። 20.እንግዲህ በእኛ ውስጥ እንደሚሠራው እንደ ኀይሉ መጠን፣ ከምንለምነው ወይም ከምናስበው ሁሉ በላይ እጅግ አብልጦ ማድረግ ለሚቻለው፣ 21.በቤተ ክርስቲያን እንዲሁም በክርስቶስ ኢየሱስ፣ በዘመናት ሁሉ ከዘላለም እስከ ዘላለም ለርሱ ክብር ይሁን! አሜን።