Skip to Content
የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን | YEHIWOT MELHEK BETEKIRSTIAN
የ2019 ዓ.ም የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ 📖 ዛሬን አንብብ →

የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን

Yehiwot Melhek Betekirstian

ሳምንት 1 · ቀን 5 (አርብ) 📅 Meskerem 8, 2019

ኦሪት ዘፍጥረት 12, 13, 14, 15 · መዝሙረ ዳዊት 148 · የማርቆስ ወንጌል 5

📖 የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም፦ 1954 መጽሐፍ ቅዱስ አዲሱ መደበኛ ትርጒም

ኦሪት ዘፍጥረት

ምዕራፍ 12

የአብራም መጠራት

1.እግዚአብሔር አብራምን እንዲህ አለው፤ “ከአገርህ ከወገንህ ተለይተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ሂድ። 2.“ታላቅ ሕዝብ አደርግሃለሁ፤
ደግሞም እባርክሃለሁ፤
ስምህን ገናና አደርገዋለሁ፤
ለሌሎች በረከት ትሆናለህ።
3.የሚባርኩህን እባርካለሁ፤
የሚረግሙህን ረግማለሁ፤
የምድር ነገዶችም፣
በአንተ ይባረካሉ።”
4.ስለዚህ አብራም እግዚአብሔር እንዳዘዘው ወጣ፤ ሎጥም ዐብሮት ሄደ። አብራም ከካራን ሲወጣ ዕድሜው
75 ዓመት ነበረ።
5.አብራምም ሚስቱን ሦራንና የወንድሙን ልጅ ሎጥን አስከትሎ በካራን ሳሉ ያፈሩትን ሀብትና የነበራቸውን አገልጋዮች ይዘው በመጓዝ ከነዓን ምድር ገቡ። 6.አብራም ትልቁ የሞሬ ዛፍ እስከሚገኝበት እስከ ሴኬም ድረስ በምድሪቱ ዘልቆ ሄደ። በዚያ ጊዜ ከነዓናውያን በዚሁ ምድር ይኖሩ ነበር። 7.እግዚአብሔርም ለአብራም ተገልጦ፣ “ይህችን ምድር ለዘርህ እሰጣለሁ” አለው። እርሱም ለተገለጠለት ለእግዚአብሔር በዚያ ስፍራ መሠዊያ ሠራ። 8.ከዚያም ተነሥቶ ከቤቴል በስተምሥራቅ ወዳሉት ተራሮች ሄደ፤ ቤቴልን በምዕራብ፣ ጋይን በምሥራቅ አድርጎ ድንኳን ተከለ፣ በዚያም ለእግዚአብሔር መሠዊያ ሠራ፤ የእግዚአብሔርን ስም ጠርቶ ጸለየ። 9.አብራምም ከዚያ ተነሥቶ ወደ ኔጌብ ሄደ።

አብራም በግብጽ አገር

12፥10-20 ተጓ ምብ – ዘፍ 20፥1-18፤ 26፥1-11
10.በዚያም ምድር ጽኑ ራብ ገብቶ ነበር፤ ከዚህም የተነሣ አብራም ለጥቂት ጊዜ በዚያ ለመኖር ወደ ግብጽ ወረደ። 11.ግብጽ ለመግባት ጥቂት ሲቀረው አብራም ሚስቱን ሦራን እንዲህ አላት፤ “መቼም አንቺ ውብ ሴት መሆንሽን ዐውቃለሁ፤ 12.ግብጻውያን አንቺን በሚያዩበት ጊዜ፣ ‘ይህች ሚስቱ ናት’ ብለው እኔን ይገድላሉ፤ አንቺን ግን ይተዉሻል። 13.ስለዚህ ለአንቺ ሲሉ እንዲንከባከቡኝ፣ ሕይወቴም እንድትተርፍ፣ ‘እኅቱ ነኝ’ በዪ።” 14.አብራም በግብጽ አገር እንደ ደረሰ ግብጻውያን፣ ሦራ እጅግ ውብ ሴት እንደ ሆነች አዩ፤ 15.የፈርዖንም ሹማምት ባዩአት ጊዜ፣ ለፈርዖን አድንቀው ነገሩት፤ ወደ ቤተ መንግሥትም ወሰዷት። 16.በርሷም ምክንያት ፈርዖን አብራምን አክብሮ አስተናገደው፤ በጎችና ከብቶች፣ ተባዕትና እንስት አህዮች፣ ወንድና ሴት አገልጋዮች እንዲሁም ግመሎችን ሰጠው። 17.እግዚአብሔርም በአብራም ሚስት በሦራ ምክንያት ፈርዖንንና ቤተ ሰዎቹን በጽኑ ደዌ መታቸው። 18.ከዚያም ፈርዖን አብራምን አስጠርቶ እንዲህ አለው፤ “ይህ ያደረግህብን ነገር ምንድን ነው? ‘ሚስትህ እንደ ሆነች ለምን አልነገርኸኝም?’ 19.ለምን ‘እኅቴ ናት’ አልኸኝ? ሚስቴ ላደርጋት ነበር። በል አሁንም ሚስትህ ይህችው፤ ይዘሃት ሂድ!” 20.ከዚያም ፈርዖን ስለ አብራም ለባለሟሎቹ ትእዛዝ ሰጠ፤ እነርሱም አብራምን ከሚስቱና ከንብረቱ ሁሉ ጋራ አሰናበቱት።

ምዕራፍ 13

የአብራምና የሎጥ መለያየት

1.አብራም ሚስቱንና ንብረቱን ሁሉ ይዞ ከግብጽ ወደ ኔጌብ ሄደ፤ ሎጥም ዐብሮት ነበረ። 2.አብራም በከብት፣ በብርና በወርቅ እጅግ በልጽጎ ነበር። 3.አብራም ከኔጌብ ተነሥቶ እስከ ቤቴል ተጓዘ፤ ቀድሞ በቤቴልና በጋይ መካከል ድንኳኑን ከተከለበት፣ 4.ለመጀመሪያ ጊዜም መሠዊያ ካቆመበት ስፍራ ደረሰ፤ በዚያም የእግዚአብሔርን ስም ጠራ። 5.ከአብራም ጋራ ዐብሮት ይጓዝ የነበረው ሎጥ በጎች፣ ከብቶችና ድንኳኖች ነበሩት። 6.ሆኖም ሁለቱ አንድ ላይ ሲኖሩ ስፍራው አልበቃቸውም፤ ንብረታቸው እጅግ ብዙ ስለ ነበር፣ ዐብረው መኖር አልቻሉም። 7.ይህም በመሆኑ በአብራምና በሎጥ መንጎች እረኞች መካከል ጠብ ተፈጠረ። በዚያ ዘመን ከነዓናውያንና ፌርዛውያን በዚያው አገር ይኖሩ ነበር። 8.አብራምም ሎጥን እንዲህ አለው፤ “እኛ ወንድማማቾች ነንና፣ በአንተና በእኔ ወይም በእረኞቻችን መካከል ጠብ ሊኖር አይገባም። 9.ይኸው እንደምታየው አገሩ ሰፊ ነው፤ ብንለያይ ይሻላል። አንተ ግራውን ብትመርጥ፣ እኔ ወደ ቀኝ እሄዳለሁ፤ አንተ ቀኙን ብትመርጥ፣ እኔ ወደ ግራ አመራለሁ።” 10.ሎጥ ዐይኑን አቅንቶ ሲመለከት፣ የዮርዳኖስ ረባዳ ሜዳ እንደ እግዚአብሔር ገነት፣ በዞዓር አቅጣጫ እንዳለው እንደ ግብጽ ምድር ውሃማ ቦታ ሆኖ አገኘው። እንዲህም የነበረው እግዚአብሔር የሰዶምንና የገሞራን ከተሞች ከማጥፋቱ በፊት ነው። 11.ሎጥ የዮርዳኖስን ረባዳ ሜዳ በሙሉ መርጦ ወደ ምሥራቅ አመራ፤ ሁለቱ ሰዎች በዚሁ ተለያዩ። 12.አብራም መኖሪያውን በከነዓን ምድር አደረገ፤ ሎጥ ግን በረባዳው ሜዳ ውስጥ ባሉት ከተሞች መካከል በሰዶም አቅራቢያ ድንኳኑን ተከለ። 13.የሰዶም ሰዎች ግን ክፉዎችና በእግዚአብሔር ፊት እጅግ ኃጥኣን ነበሩ። 14.ሎጥ ከተለየው በኋላ እግዚአብሔር አብራምን እንዲህ አለው፤ “ካለህበት ስፍራ ቀና ብለህ ወደ ሰሜንና ወደ ደቡብ፣ ወደ ምሥራቅና ወደ ምዕራብ ተመልከት፤ 15.ዐይንህ የሚያየውን ምድር ሁሉ ለአንተና ለዘርህ ለዘላለም እሰጣለሁ። 16.ዘርህን እንደ ምድር ትቢያ አበዛዋለሁ፤ ማንም የምድርን ትቢያ ሊቈጥር እንደማይችል ሁሉ የአንተም ዘር የማይቈጠር ይሆናል። 17.እንግዲህ ምድሪቱን ስለምሰጥህ ተነሣ፤ በርዝመቷም፣ በስፋቷም ተመላለስባት።” 18.አብራምም ድንኳኑን ነቀለ፤ ሄዶም ኬብሮን በሚገኙት ትልልቅ የመምሬ ዛፎች አጠገብ ተቀመጠ፤ በዚያም ለእግዚአብሔር መሠዊያ ሠራ።

ምዕራፍ 14

አብራም ሎጥን መታደጉ

1.አምራፌል የሰናዖር ንጉሥ፣ አርዮክ የእላሳር ንጉሥ፣ ኮሎዶጎምር የኤላም ንጉሥ፣ ቲድዓል የጎይም ንጉሥ በነበሩበት ዘመን፣ 2.ከሰዶም ንጉሥ ከበላ፣ ከገሞራ ንጉሥ ከብርሳ፣ ከአዳማ ንጉሥ ከሰነአብ፣ ከስቦይ ንጉሥ ከሰሜበር፣ እንዲሁም ዞዓር ከተባለች ከቤላ ንጉሥ ጋራ ለመዋጋት ወጡ። 3.እነዚህ የኋለኞቹ ዐምስቱ ነገሥታት በሲዲም ሸለቆ፣ በጨው ባሕር ተሰበሰቡ። 4.እነርሱም ዐሥራ ሁለት ዓመት ለኮሎዶጎምር ከተገዙ በኋላ በዐሥራ ሦስተኛው ዓመት ዐመፁ። 5.በዐሥራ አራተኛው ዓመት ኮሎዶጎምርና ከርሱ ጋራ የተባበሩት ነገሥታት ወጡ፤ ራፋይምን በአስጣሮት ቃርናይም፣ ዙዚምን በሃም፣ ኤሚማውያን በሴዊ ቂርያታይም፣ 6.የሖሪ ሰዎችንም በተራራማው አገር በሴይር በረሓማ አጠገብ እስካለው እስከ ኤልፋራን ድረስ ድል አደረጓቸው። 7.ከዚያም ተመልሰው ዓይንሚስፖጥ ወደተባለው ወደ ቃዴስ መጡ፤ የአማሌቃውያንና በሐሴሶን ታማር ይኖሩ የነበሩትን የአሞራውያንን ግዛት በሙሉ ድል አድርገው ያዙ። 8.ከዚያም የሰዶም፣ የገሞራ፣ የአዳማ፣ የስቦይ እንዲሁም ዞዓር የተባለችው የቤላ ነገሥታት በሲዲም ሸለቆ ሰራዊታቸውን አስተባበሩ። 9.እነዚህ ዐምስቱ፣ በኤላም ንጉሥ በኮሎዶጎምር፣ በጎይም ንጉሥ በቲድዓል፣ በሰናዖር ንጉሥ በአምራፌል፣ በእላሳር ንጉሥ በአርዮክ፣ በእነዚህ በአራቱ ላይ ዘመቱባቸው። 10.በሲዲም ሸለቆ ብዙ የቅጥራን ጕድጓዶች ስለ ነበሩ የሰዶምና የገሞራ ነገሥታት ሲሸሹ ከሰዎቻቸው አንዳንዶቹ በእነዚህ ጕድጓዶች ውስጥ ወደቁ፤ የቀሩትም ወደ ተራሮች ሸሹ። 11.አራቱ ነገሥታትም በሰዶምና በገሞራ ያገኙትን ሀብትና ምግብ ሁሉ ዘርፈው ሄዱ። 12.የአብራም ወንድም ልጅ ሎጥ፣ ሰዶም ይኖር ስለ ነበር እርሱንም ማርከው ንብረቱንም ዘርፈው ሄዱ። 13.ከዚህም ያመለጠ አንድ ሰው መጥቶ ለዕብራዊው ለአብራም ይህን ነገረ፤ አብራም በዚያ ጊዜ ይኖር የነበረው በአሞራዊው መምሬ ታላላቅ ዛፎች አጠገብ ነበር። መምሬ፣ ወንድሞቹ ኤስኮልና አውናን የአብራም የኪዳን አጋሮቹ ነበሩ። 14.አብራም የወንድሙን ልጅ መማረክ እንደ ሰማ በቤቱ ተወልደው አድገው የሠለጠኑ
318 ጦረኞች አሰልፎ እስከ ዳን ድረስ ገሠገሠ።
15.አብራም ጠላቶቹን ለማጥቃት ሰራዊቱን ሌሊቱን በቡድን በቡድን ከፋፍሎ ከደማስቆ በስተሰሜን እስከሚገኘው እስከ ሖባ ድረስ አሳደዳቸው። 16.አብራም ጠላት የማረከውን በሙሉ አስጣለ፤ የወንድሙን ልጅ ሎጥን፣ ንብረቱን እንዲሁም ሴቶቹንና ሌሎቹን ምርኮኞች አስመለሰ። 17.አብራም ኮሎዶጎምርንና ዐብረውት የተሰለፉትን ነገሥታት ድል አድርጎ ሲመለስ፣ የሰዶም ንጉሥ፣ “የንጉሥ ሸለቆ” ተብሎ በሚጠራው በሴዊ ሸለቆ ሊቀበለው ወጣ። 18.የልዑል አምላክ ካህን የነበረው የሳሌም ንጉሥ መልከ ጼዴቅም እንጀራና የወይን ጠጅ ይዞ ወጣ፤ 19.አብራምንም እንዲህ ሲል ባረከው፤
“ሰማይንና ምድርን የፈጠረ
ልዑል አምላክ አብራምን ይባርክ፤
20.ጠላቶችህን አሳልፎ በእጅህ የሰጠህ፣
ልዑል አምላክ ይባረክ።”
አብራምም ከሁሉ ነገር ዐሥራትን አውጥቶ ሰጠው።
21.የሰዶም ንጉሥም አብራምን፣ “ሰዎቹን ለእኔ ስጠኝ፤ ንብረቱን ግን ለራስህ አስቀር” አለው። 22.አብራም ግን ለሰዶም ንጉሥ እንዲህ አለው፤ “ሰማይንና ምድርን ወደ ፈጠረ ወደ እግዚአብሔር፣ ወደ ልዑል አምላክ እጆቼን አንሥቻለሁ፤ 23.‘አብራምን አበለጸግሁት’ እንዳትል፣ ብጣሽ ክርም ሆነ የጫማ ማሰሪያ እንኳ ከአንተ አንዳች አልፈልግም። 24.ሰዎቼ ከበሉትና ከእኔ ጋራ ከሄዱት ሰዎች ድርሻ በቀር ለራሴ አንዳች ነገር አልቀበልም፤ አውናን፣ ኤስኮልና መምሬ ድርሻቸውን ይውሰዱ።”

ምዕራፍ 15

እግዚአብሔር ለአብራም የገባው ኪዳን

1.ከዚህም በኋላ፣ የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል በራእይ ወደ አብራም መጣ፤
“አብራም ሆይ፤ አትፍራ፤
እኔ ለአንተ ጋሻህ ነኝ፤
ታላቅ ዋጋህም እኔው ነኝ።”
2.አብራምም፣ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ ያለ ልጅ የቀረሁ ስለ ሆንሁ፣ የቤቴ ወራሽ የደማስቆ ሰው ኤሊዔዘር ነው፤ ታዲያ ምን ትሰጠኛለህ?” አለው። 3.“አንተ ልጆች ስላልሰጠኸኝ፣ ከቤቴ አገልጋይ አንዱ ወራሼ መሆኑ አይቀርም።” 4.በዚህ ጊዜ የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል መጣለት፤ “ይህ ሰው ወራሽህ አይሆንም፤ ነገር ግን ከአብራክህ የሚከፈል ልጅ ወራሽህ ይሆናል።” 5.ወደ ውጭም አውጥቶ፣ “ቀና ብለህ ወደ ሰማይ ተመልከት፤ እስኪ መቍጠር ከቻልህ፣ ከዋክብቱን ቍጠራቸው፤ ዘርህም እንዲሁ ይበዛል” አለው። 6.አብራም እግዚአብሔርን አመነ፤ እርሱም ጽድቅ አድርጎ ቈጠረለት። 7.ደግሞም እግዚአብሔር፣ “ይህችን ምድር ላወርስህ፣ ከከለዳውያን ምድር፣ ከዑር ያወጣሁህ እግዚአብሔር እኔ ነኝ” አለው። 8.አብራምም፣ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ ይህችን ምድር እንደምወርሳት በምን ዐውቃለሁ?” አለ። 9.እግዚአብሔርም “እያንዳንዳቸው ሦስት ዓመት የሆናቸው አንዲት ጊደር፣ አንድ ፍየልና አንድ በግ፣ በተጨማሪም አንድ ዋኖስና አንድ ርግብ ዐብረህ አቅርብልኝ” አለው። 10.አብራምም እነዚህን ሁሉ አቀረበለት፤ ቈርጦም ሁለት ቦታ ከከፈላቸው በኋላ፣ እያንዳንዱን ክፍል በሌላው ወገን ትይዩ አስቀመጠ፤ ወፎችን ግን ለሁለት አልከፈላቸውም። 11.አሞሮችም ሥጋውን ለመብላት ወረዱ፤ አብራም ግን አባረራቸው። 12.ፀሓይ ልትገባ ስትል አብራም እንቅልፍ ወሰደው፤ የሚያስፈራም ድቅድቅ ጨለማ መጣበት። 13.እግዚአብሔርም እንዲህ አለው፤ “ዘርህ በባዕድ አገር መጻተኛ እንደሚሆን በርግጥ ዕወቅ፤ አራት መቶ ዓመትም በባርነት ተረግጦ ይገዛል። 14.ነገር ግን በባርነት የሚገዛቸውን ሕዝብ እቀጣዋለሁ፤ ከዚያም ብዙ ሀብት ይዘው ይወጣሉ። 15.አንተ ግን ወደ አባቶችህ በሰላም ትሄዳለህ፤ ዕድሜም ጠግበህ ወደ መቃብር ትወርዳለህ፤ 16.በአራተኛውም ትውልድ ዘርህ ወደዚህ ምድር ይመለሳል፤ የአሞራውያን ኀጢአት ገና ጽዋው አልሞላምና።” 17.ፀሓይ ገብታ ከጨለመ በኋላ የምድጃ ጢስና የሚንበለበል ፋና ታየ፤ በተከፈለውም ሥጋ መካከል ዐለፈ። 18.በዚያ ዕለት እግዚአብሔር ለአብራም እንዲህ ሲል ኪዳን ገባለት፤ “ከግብጽ ወንዝ ጀምሮ እስከ ታላቁ የኤፍራጥስ ወንዝ ድረስ ያለውን ምድር ለዘርህ እሰጣለሁ፤ 19.የምሰጣቸውም የቄናውያንን፣ የቄኔዛውያንን፣ የቃድሞናውያንን፣ 20.የኬጢያውያንን፣ የፌርዛውያንን፣ የራፋይምን፣ 21.የአሞራውያንን፣ የከነዓናውያንን፣ የጌርጌሳውያንንና የኢያቡሳውያንን ምድር ነው።”

መዝሙረ ዳዊት

ምዕራፍ 148

1.ሃሌ ሉያ።
እግዚአብሔርን ከሰማያት አመስግኑት፤
በላይ በአርያም አመስግኑት።
2.መላእክቱ ሁሉ አመስግኑት፤
ሰራዊቱ ሁሉ አመስግኑት፤
3.ፀሓይና ጨረቃ አመስግኑት፤
የምታበሩ ከዋክብት ሁሉ አመስግኑት።
4.ሰማየ ሰማያት አመስግኑት፤
ከሰማያትም በላይ ያላችሁ ውሆች አወድሱት።
5.እርሱ ስላዘዘ ተፈጥረዋልና፣
የእግዚአብሔርን ስም ያመስግኑት።
6.ከዘላለም እስከ ዘላለም አጸናቸው፤
የማይሻርም ሕግ ደነገገላቸው።
7.የባሕር ውስጥ ግዙፍ ፍጥረትና ጥልቅ ውሆች ሁሉ፣
እግዚአብሔርን ከምድር አመስግኑት።
8.እሳትና በረዶ፣ ዐመዳይና ጭጋግ፣
ትእዛዙንም የሚፈጽም ዐውሎ ነፋስ፣
9.ተራሮችና ኰረብቶች ሁሉ፣
የፍሬ ዛፎችና ዝግቦች ሁሉ፣
10.የዱር አራዊትና የቤት እንስሳት ሁሉ፣
በምድር የሚሳቡ ፍጥረታትና የሚበርሩ ወፎችም፣
11.የምድር ነገሥታትና ሕዝቦች ሁሉ፣
መሳፍንትና የምድር ገዦች ሁሉ፣
12.ወጣት ወንዶችና ደናግል፣
አረጋውያንና ልጆች ያመስግኑት።
13.ስሙ ብቻውን ከፍ ያለ ነውና፣
ክብሩም ከምድርና ከሰማይ በላይ ነውና፣
እነዚህ ሁሉ የእግዚአብሔርን ስም ያመስግኑ።
14.እርሱ ለሕዝቡ ቀንድን አስነሥቷል፤
ለቅዱሳኑ ሁሉ ምስጋና፣
እጅግ ቅርቡ ለሆነው ሕዝቡ፣ ለእስራኤል ልጆች።
ሃሌ ሉያ።

የማርቆስ ወንጌል

ምዕራፍ 5

አጋንንት ያደሩበት ሰው መፈወሱ

5፥1-17 ተጓ ምብ – ማቴ 8፥28-34፤ ሉቃ 8፥26-37
5፥18-20 ተጓ ምብ – ሉቃ 8፥38-39
1.ባሕሩን ተሻግረው ጌርጌሴኖን ወደሚባል አገር መጡ። 2.ኢየሱስ ከጀልባ እንደ ወረደ፣ ርኩስ መንፈስ ያደረበት ሰው ከመቃብር ቦታ ወጥቶ ሊገናኘው ወደ እርሱ መጣ። 3.ይህ ሰው በመቃብር ቦታ ውስጥ የሚኖርና ማንም በሰንሰለት እንኳ ሊያስረው የማይችል ነበር። 4.ብዙ ጊዜ በእግር ብረትና በሰንሰለት ይታሰር ነበር፤ ነገር ግን የእጅ ሰንሰለቱን ይበጥስ፣ የእግር ብረቱንም ይሰብር ነበር። ማንም ይዞ ሊያቈየው የሚችል አልነበረም። 5.በመቃብሮቹና በተራሮቹ መካከል ቀንና ሌሊት እየተዘዋወረ በመጮኽ ሰውነቱን በድንጋይ ይቈራርጥ ነበር። 6.ይህም ሰው ኢየሱስን ከሩቅ ባየው ጊዜ ወደ እርሱ ሮጦ ከፊቱ ተንበርክኮ ሰገደለት፤ 7.በታላቅ ድምፅ ጮኾም፣ “አንተ የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ሆይ፤ ከእኔ ምን አለህ? እንዳታሠቃየኝ በእግዚአብሔር ይዤሃለሁ!” አለው። 8.ይህንም ያለው ኢየሱስ፣ “አንተ ርኩስ መንፈስ ከዚህ ሰው ውጣ!” ብሎት ስለ ነበር ነው። 9.ከዚያም ኢየሱስ፣ “ስምህ ማን ነው?” ብሎ ጠየቀው።
“ብዙ ነንና ስሜ ሌጌዎን ነው” አለው።
10.እርሱም ከአገር እንዳያስወጣቸውም አጥብቆ ለመነው። 11.በአቅራቢያውም በሚገኝ ኰረብታ ላይ ትልቅ የዐሣማ መንጋ ተሰማርቶ ነበር። 12.ርኩሳን መናፍስቱም ኢየሱስን፣ “ወደ ዐሣማዎቹ ስደደን፤ እንድንገባባቸውም ፍቀድልን” ብለው ለመኑት። 13.እርሱም ፈቀደላቸው። ርኩሳን መናፍስቱም ወጥተው በዐሣማዎቹ ገቡባቸው፤ ሁለት ሺሕ ያህል ዐሣማዎችም በገደሉ አፋፍ በመንደርደር ቍልቍል ወርደው በባሕር ውስጥ ሰጠሙ። 14.እረኞቹ ሸሽተው ሄዱ፤ ወሬውን በከተማና በገጠር አዳረሱት፤ ሕዝቡም የሆነውን ለማየት ካለበት ወጣ። 15.ወደ ኢየሱስም በመጡ ጊዜ፣ የአጋንንት ሰራዊት ሌጌዎን ዐድረውበት የነበረው ሰው፣ ልብስ ለብሶና አእምሮው ተመልሶለት በዚያ ተቀምጦ አዩት፤ ፈሩም። 16.ይህን ያዩ ሰዎችም አጋንንት ላደሩበት ሰው የሆነውንና ስለ ዐሣማዎቹም ለሕዝቡ አወሩ። 17.ከዚያም አገራቸውን ለቅቆ እንዲሄድላቸው ኢየሱስን ይለምኑት ጀመር። 18.ኢየሱስ ወደ ጀልባዪቱ በሚገባበት ጊዜ፣ አጋንንት ዐድረውበት የነበረው ሰው ዐብሮት ለመሆን ለመነው። 19.ኢየሱስ አልፈቀደለትም፤ ነገር ግን፣ “ወደ ቤትህ ሂድ፣ ለዘመዶችህም ጌታ ምን ያህል ታላቅ ነገር እንዳደረገልህና ያሳየህን ምሕረት ንገራቸው” አለው። 20.ሰውየውም ሄደ፤ ኢየሱስ ያደረገለትን ነገር ሁሉ ዐሥር ከተማ በተባለው አገር ያወራ ጀመር፤ የሰሙትም ሁሉ ተደነቁ።

የሞተችው ልጅና የታመመችው ሴት

5፥22-43 ተጓ ምብ – ማቴ 9፥18-26፤ ሉቃ 8፥41-56
21.ኢየሱስ እንደ ገና በጀልባ ወደ ማዶ በተሻገረ ጊዜ፣ ብዙ ሕዝብ በዙሪያው ተሰባሰበ፤ በባሕሩ ዳርቻም እንዳለ፣ 22.ከምኵራብ አለቆች አንዱ ኢያኢሮስ የተባለው ወደዚያ መጥቶ ስለ ነበር፣ ኢየሱስን ባየው ጊዜ በእግሮቹ ላይ ወድቆ፣ 23.“ትንሿ ልጄ በሞት አፋፍ ላይ ናትና ድና በሕይወት እንድትኖር መጥተህ እጅህን ጫንባት” በማለት አጥብቆ ለመነው። 24.ኢየሱስም ዐብሮት ሄደ።
ብዙ ሕዝብም ዙሪያውን እያጨናነቀው ተከተለው።
25.ዐሥራ ሁለት ዓመት ደም ሲፈስሳት የኖረች አንዲት ሴት በዚያ ነበረች፤ 26.በብዙ ባለመድኀኒቶች ዘንድ በመንከራተት ያላትን ሁሉ ብትጨርስም፣ ሕመሙ ባሰባት እንጂ አልተሻላትም ነበር። 27.ስለ ኢየሱስም በሰማች ጊዜ፣ ከበስተኋላው በሰዎች መካከል መጥታ ልብሱን ነካች፤ 28.ምክንያቱም፣ “እንደ ምንም ብዬ ልብሱን ብቻ እንኳ ብነካ እፈወሳለሁ” የሚል እምነት ነበራት። 29.የሚፈስሰው ደሟም ወዲያውኑ ቆመ፤ ከሥቃይዋ መገላገሏም በሰውነቷ ታወቃት። 30.ወዲያውኑ ኢየሱስ፣ ኀይል ከርሱ እንደ ወጣ ዐውቆ፤ ወደ ሕዝቡ ዘወር በማለት፣ “ልብሴን የነካው ማን ነው?” አለ። 31.ደቀ መዛሙርቱም፣ “ሕዝቡ ተጨናንቆ ሲጋፋህ እያየህ፣ ‘ማን ነው የነካኝ?’ እንዴት ትላለህ?” አሉት። 32.ኢየሱስ ግን ይህን ያደረገው ማን እንደ ሆነ ለማየት ዙሪያውን ተመለከተ። 33.ሴትዮዋም ምን እንደ ተደረገላት ባወቀች ጊዜ እየፈራችና እየተንቀጠቀጠች መጥታ በፊቱ ተደፋች፤ እውነቱንም ሁሉ ነገረችው። 34.እርሱም፣ “ልጄ ሆይ፤ እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ፤ ከሥቃይሽም ዕረፊ” አላት። 35.ኢየሱስም በመነጋገር ላይ እያለ፣ ሰዎች ከምኵራቡ አለቃ ከኢያኢሮስ ቤት መጥተው፣ “ልጅህ ሞታለች፤ ከእንግዲህ መምህሩን ለምን ታደክመዋለህ?” አሉት። 36.ኢየሱስ ግን ሰዎቹ የተናገሩትን ችላ በማለት የምኵራቡን አለቃ፣ “እመን ብቻ እንጂ አትፍራ፤” አለው። 37.ከጴጥሮስና ከያዕቆብ እንዲሁም ከያዕቆብ ወንድም ከዮሐንስ በቀር ማንም እንዲከተለው አልፈቀደም። 38.ወደ ምኵራቡ አለቃ ቤት እንደ ደረሱ፣ ኢየሱስ ግርግሩንና ሰዎቹም ዋይ ዋይ እያሉ አምርረው ሲያለቅሱ ተመለከተ። 39.ወደ ቤትም ገብቶ፣ “ይህ ሁሉ ግርግርና ልቅሶ ምንድን ነው? ብላቴናዪቱ ተኝታለች እንጂ አልሞተችም” አላቸው። 40.ሰዎቹ ግን ሣቁበት።
ሰዎቹን ሁሉ ከቤት ካስወጣ በኋላ፣ የብላቴናዪቱን አባትና እናት እንዲሁም ዐብረውት የመጡትን ደቀ መዛሙርት አስከትሎ ብላቴናዪቱ ወዳለችበት ገባ።
41.ከዚያም የብላቴናዪቱን እጅ ይዞ፣ “ጣሊታ ቁሚ!” አላት፤ ትርጕሙም፣ “አንቺ ልጅ ተነሺ” ማለት ነው። 42.ብላቴናዪቱም ወዲያውኑ ተነሥታ ቆመች፤ ወዲያ ወዲህም ሄደች። ዕድሜዋም ዐሥራ ሁለት ዓመት ነበር። ሰዎቹም በሁኔታው እጅግ ተደነቁ። 43.እርሱም ይህን ነገር ማንም እንዳያውቅ አጥብቆ አስጠነቀቃቸው፤ የሚበላ ነገር እንዲሰጧትም ነገራቸው።