Skip to Content
የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን | YEHIWOT MELHEK BETEKIRSTIAN
የ2019 ዓ.ም የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ 📖 ዛሬን አንብብ →

የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን

Yehiwot Melhek Betekirstian

ሳምንት 1 · ቀን 4 (ሐሙስ) 📅 Meskerem 7, 2019

ኦሪት ዘፍጥረት 9, 10, 11 · የማርቆስ ወንጌል 4

📖 የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም፦ 1954 መጽሐፍ ቅዱስ አዲሱ መደበኛ ትርጒም

ኦሪት ዘፍጥረት

ምዕራፍ 9

እግዚአብሔር ከኖኅ ጋራ የገባው ኪዳን

1.እግዚአብሔር ኖኅንና ልጆቹን እንዲህ ሲል ባረካቸው፤ “ብዙ ተባዙ፤ ምድርንም ሙሏት፤ 2.አስፈሪነታችሁና አስደንጋጭነታችሁ በዱር አራዊት፣ በሰማይ አዕዋፍ፣ በምድር ላይ በሚሳቡ ፍጥረታትና በባሕር ዓሦች ሁሉ ላይ ይሁን፤ በእጃችሁ ተሰጥተዋል። 3.ሕያውና ተንቀሳቃሽ ፍጡር ሁሉ ምግብ ይሁናችሁ፤ ለምለሙን ዕፀዋት እንደ ሰጠኋችሁ፣ አሁን ደግሞ ሁሉን ሰጠኋችሁ። 4.“ነገር ግን ሕይወቱ፣ ማለት ደሙ ገና በውስጡ ያለበትን ሥጋ አትብሉ። 5.ሰውን የገደለ ሁሉ ስለ ሟቹ ደም ተጠያቂ ነው፤ የሟቹን ሰው ደም ከገዳዩ፣ ከእንስሳም ይሁን ከሰው እሻለሁ። 6.“የሰውን ደም የሚያፈስስ ሁሉ፣
ደሙ በሰው እጅ ይፈስሳል፤
በእግዚአብሔር አምሳል፣
እግዚአብሔር ሰውን ሠርቶታልና።
7.እናንተ ግን ብዙ ተባዙ፤ ዘራችሁ በምድር ላይ ይብዛ፤ ይንሰራፋ።” 8.እግዚአብሔር ኖኅንና ዐብረውት ያሉትን ልጆቹን እንዲህ አላቸው፤ 9.“እነሆ፤ ከእናንተና ከእናንተ በኋላ ከሚመጣው ዘራችሁ ጋራ ኪዳኔን እመሠርታለሁ፤ 10.እንዲሁም ከእናንተ ጋራ ከነበሩት ሕያዋን ፍጥረታት ሁሉ፦ ከወፎች፣ ከቤት እንስሳት፣ ከዱር እንስሳት፣ ከእናንተ ጋራ ከመርከቧ ከወጡት በምድር ላይ ካሉት ሕያዋን ፍጥረታት ሁሉ ጋራ ኪዳን እገባለሁ። 11.ከእንግዲህ ሕይወት ያለው ፍጡር ሁሉ በጥፋት ውሃ እንደማይጠፋ፣ ዳግመኛም ምድርን የሚያጠፋ ውሃ ከቶ እንደማይመጣ ከእናንተ ጋራ ኪዳን እገባለሁ።” 12.እግዚአብሔርም እንዲህ አለ፤ “በእኔና በእናንተ መካከል፣ ከእናንተም ጋራ ካሉ ሕያዋን ፍጥረታት ሁሉ ጋራ ከሚመጣውም ትውልድ ሁሉ ጋራ፣ የማደርገው የኪዳኑ ምልክት ይህ ነው፤ 13.ቀስተ ደመናዬን በደመና ላይ አደርጋለሁ፤ ይህም በእኔና በምድር መካከል ለገባሁት ኪዳን ምልክት ይሆናል። 14.ደመናን በምድር ላይ በጋረድሁና ቀስቴም በደመና ላይ በሚታይበት ጊዜ ሁሉ፣ 15.ከእናንተና ከሕያዋን ፍጥረታት ሁሉ ጋራ የገባሁትን ኪዳን ዐስባለሁ፤ ሕይወት ያለውንም ሁሉ ያጠፋ ዘንድ፣ ከእንግዲህ የጥፋት ውሃ ከቶ አይመጣም። 16.ቀስቱ በደመና ላይ ተገልጦ በማይበት ጊዜ ሁሉ፣ በእግዚአብሔርና በምድር ላይ ባሉ ሕያዋን ፍጥረታት መካከል ያለውን ዘላለማዊ ኪዳን ዐስባለሁ።” 17.ስለዚህ እግዚአብሔር ኖኅን፣ “ይህ በእኔና በምድር ላይ በሚኖሩ ሕያዋን ሁሉ መካከል የገባሁት ኪዳን ምልክት ነው” አለው።

የኖኅ ልጆች

18.ከመርከቧ የወጡትም የኖኅ ልጆች ሴም፣ ካምና ያፌት ነበሩ፤ ካም የከነዓን አባት ነው። 19.ሦስቱ የኖኅ ልጆች እነዚህ ሲሆኑ፣ በምድር ላይ የሚኖሩ ሕዝቦች ሁሉ የተገኙት ከእነዚሁ ነው። 20.ኖኅ ገበሬ ነበረና ወይን ተከለ፤ 21.ከወይኑም ጠጅ ጠጥቶ ሰከረና በድንኳኑ ውስጥ ዕርቃኑን ተኛ። 22.የከነዓን አባት ካም የአባቱን ዕርቃነ ሥጋ አየ፤ ወደ ውጭም ወጥቶ ለሁለቱ ወንድሞቹ ነገራቸው። 23.ሴምና ያፌት ግን ልብስ ወስደው በጫንቃቸው ላይ አደረጉና የአባታቸውን ዕርቃነ ሥጋ እንዳያዩ ፊታቸውን አዙረው የኋሊት በመሄድ የአባታቸውን ዕርቃነ ሥጋ ሸፈኑ። 24.ኖኅ ከወይን ጠጁ ስካር ሲነቃ፣ ታናሽ ልጁ ያደረገበትን ዐወቀ፤ 25.እንዲህም አለ፤
“ከነዓን የተረገመ ይሁን፤
ለወንድሞቹም፣ የባሪያ ባሪያ ይሁን።”
26.ደግሞም፤
“የሴም አምላክ እግዚአብሔር ይባረክ፤
ከነዓንም የሴም ባሪያ ይሁን።
27.እግዚአብሔር የያፌትን ግዛት ያስፋ፤
ያፌት በሴም ድንኳኖች ይኑር፤
ከነዓንም የርሱ ባሪያ ይሁን” አለ።
28.ኖኅ ከጥፋት ውሃ በኋላ
350 ዓመት ኖረ፤
29.ኖኅ በአጠቃላይ
950 ዓመት ኖሮ ሞተ።

ምዕራፍ 10

የኖኅ ልጆች ትውልድ

1.የኖኅ ልጆች የሴም፣ የካምና የያፌት ትውልድ ይህ ነው፤ እነርሱም ራሳቸው ከጥፋት ውሃ በኋላ ወንዶች ልጆችን ወለዱ።

የያፌት ዝርያዎች

10፥2-5 ተጓ ምብ – 1ዜና 1፥5-7
2.የያፌት ልጆች፣
ጎሜር፣ ማጎግ፣ ማዴ፣ ያዋን፣ ቶቤል፣ ሜሼኽ፣ ቴራስ።
3.የጎሜር ልጆች፦
አስከናዝ፣ ሪፋት፣ ቶጋርማ።
4.የያዋን ልጆች፦
ኤሊሳ፣ ተርሴስ፣ ኪቲም፣ ሮድኢ።
5.ከእነዚህም በየነገዳቸው፣ በየጐሣቸውና በየቋንቋቸው ተከፋፍለው በባሕር ዳርና በደሴቶች፣ በየምድራቸው የሚኖሩ ሕዝቦች ወጡ።

የካም ዝርያዎች

10፥6-20 ተጓ ምብ – 1ዜና 1፥8-16
6.የካም ልጆች፦
ኵሽ፣ ምጽራይም፣ ፉጥ፣ ከነዓን ናቸው።
7.የኵሽ ልጆች፦
ሳባ፣ ኤውላጥ፣ ሰብታ፣ ራዕማ፣ ሰብቃታ ናቸው።
የራዕማ ልጆች፦
ሳባ፣ ድዳን ናቸው።
8.ኵሽ የናምሩድን አባት ነበረ፤
እርሱም በምድር ላይ የመጀመሪያው ኀያል ጦረኛ ሆነ።
9.በእግዚአብሔር ፊት ብርቱ ዐዳኝ ነበረ፤ ስለዚህም፣ “በእግዚአብሔር ፊት እንደ ናምሩድ ብርቱ ዐዳኝ” ይባል ነበር። 10.የግዛቱም የመጀመሪያ ከተሞች፦ ባቢሎን፣ ኦሬክ፣ አርካድና ካልኔ ናቸው፤ እነዚህ በሰናዖር ምድር ነበሩ። 11.ከዚያም ምድር ወደ አሦር ወጥቶ ነነዌን፣ ርኆቦትን፣ ካለህን 12.እንዲሁም በነነዌና በካለህ መካከል ሬስን ቈረቈረ፤ ታላቁንም ከተማ መሠረተ። 13.ምጽራይም፦
የሉዳማውያን፣ የዐናሚማውያን፣ የላህቢያውያን፣ የነፍተሂማውያን፣
14.የፈትሩሲማውያን፣ ፍልስጥኤማውያን የተገኙባቸው፣ የከስሉሂማውያንና የቀፍቶሪማውያን አባት ነበረ። 15.ከነዓንም፦
የበኵር ልጁ የሲዶን፣ የኬጢያውያን፣
16.የኢያቡሳውያን፣ የአሞራውያን፣ የጌርጌሳውያን፣ 17.የኤዊያውያን፣ የዐርካውያን፣ የሲኒውያን፣ 18.የአራዴዎያውያን፣ የሰማሪናውያንና የአማቲያውያን አባት ነበረ።
ከጊዜ በኋላ የከነዓን ጐሣዎች በየስፍራው ተሠራጩ፤
19.የከነዓን ወሰን ከሲዶና አንሥቶ በጌራራ በኩል እስከ ጋዛ ይደርሳል፤ ከዚያም በሰዶም በኩል ገሞራን፣ አዳማንና ስቦይን ይዞ እስከ ላሣ ይዘልቃል። 20.እነዚህም በየጐሣቸውና በየቋንቋቸው፣ በየምድራቸውና በየነገዳቸው ይኖሩ የነበሩ የካም ዝርያዎች ናቸው።

የሴም ዝርያዎች

10፥21-31 ተጓ ምብ – ዘፍ 11፥10-27፤ 1ዜና 1፥17-27
21.ለያፌት ታላቅ ወንድም ለሴም ደግሞ ወንዶች ልጆች ተወለዱለት፤ እርሱም የዔቦር ልጆች ሁሉ ቅደመ አያት ነው። 22.የሴም ልጆች፦
ኤላም፣ አሦር፣ አርፋክስድ፣ ሉድ፣ አራም ናቸው።
23.የአራም ልጆች፤
ዑፅ፣ ሁል፣ ጌቴር፣ ሜሼኽ።
24.አርፋክስድ ሳላን ወለደ፤
ሳላም ዔቦርን ወለደ።
25.ለዔቦርም ሁለት ወንዶች ልጆች ተወለዱለት፤
አንደኛው ልጅ በዘመኑ ምድር ተከፍላ ስለ ነበር ፋሌቅ ተባለ፤ ወንድሙም ዮቅጣን ተባለ።
26.ዮቅጣንም፦
አልሞዳድን፣ ሣሌፍን፣ ሐስረሞትን፣ ያራሕን፣
27.ሀዶራምን፣ አውዛልን፣ ደቅላን፣ 28.ዖባልን፣ አቢማኤልን፣ ሳባን፣ 29.የኦፊር፣ የኤውላጥ፣ የዮባብ አባት ነበረ፤ እነዚህ ሁሉ የዮቅጣን ልጆች ናቸው። 30.መኖሪያ ስፍራቸውም እስከ ሶፋር ድረስ ይዘልቃል። 31.እነዚህም በየጐሣቸውና በየቋንቋቸው፣ በየምድራቸውና በየነገዳቸው ይኖሩ የነበሩ የሴም ዝርያዎች ናቸው። 32.የኖኅ ወንዶች ልጆች ጐሣዎች እንደ ትውልዳቸው በየነገዳቸው እነዚህ ነበሩ። ከጥፋት ውሃ በኋላ ሕዝቦች በምድር ላይ የተሠራጩት ከእነዚሁ ነው።

ምዕራፍ 11

የባቤል ግንብ

1.በዚያ ጊዜ ሰዎች ሁሉ የሚናገሩትና የሚግባቡበት ቋንቋ አንድ ብቻ ነበር። 2.ሰዎቹም ምሥራቁን ይዘው ሲጓዙ፣ በሰናዖር አንድ ሜዳ አግኝተው በዚያ ሰፈሩ። 3.እነርሱም እርስ በርሳቸው፣ “ኑ፤ ጡብ እንሥራ፤ እስኪበቃውም በእሳት እንተኵሰው” ተባባሉ። በድንጋይ ፈንታ ጡብ፣ ለማያያዣም ቅጥራን ተጠቀሙ። 4.ከዚያም “ለስማችን መጠሪያ እንዲሆንና በምድር ላይ እንዳንበተን፣ ኑ፤ ከተማ፣ ሰማይ የሚደርስ ግንብም ለራሳችን እንሥራ” አሉ። 5.እግዚአብሔር ግን ሰዎቹ ይሠሩ የነበሩትን ከተማና ግንብ ለማየት ወረደ። 6.እግዚአብሔርም እንዲህ አለ፤ “እንዲህ እንደ አንድ ሕዝብ አንድ ቋንቋ በመናገር ይህን ማድረግ ከጀመሩ፣ ከእንግዲህ ያቀዱትን ሁሉ ማከናወን አያዳግታቸውም። 7.ኑ እንውረድ፤ እርስ በርሳቸውም እንዳይግባቡ ቋንቋቸውን እንደበላልቀው።” 8.ስለዚህ እግዚአብሔር በምድር ሁሉ ላይ በታተናቸው፤ ከተማዋንም መሥራት አቆሙ። 9.እግዚአብሔር በዚያ የመላውን ዓለም ቋንቋ ስለ ደበላለቀ የከተማዪቱ ስም ባቤል ተባለ። ከዚያም እግዚአብሔር ሰዎቹን በምድር ሁሉ በተናቸው።

ከሴም እስከ አብራም

11፥10-27 ተጓ ምብ – ዘፍ 10፥21-32፤ 1ዜና 1፥17-27
10.የሴም ትውልድ ይህ ነው፦

ሁለት ዓመት ከጥፋት ውሃ በኋላ ሴም በ

100 ዓመቱ አርፋክስድን ወለደ።

11.ሴም፣ አርፋክስድን ከወለደ በኋላ
500 ዓመት ኖረ፤ ሌሎች ወንዶችና ሴቶች ልጆችን ወለደ።
12.አርፋክስድ በ
35 ዓመቱ ሳላን ወለደ፤
13.ሳላን ከወለደ በኋላ አርፋክስድ
403 ዓመት ኖረ፤ ሌሎች ወንዶችና ሴቶችን ወለደ።
14.ሳላ በ
30 ዓመቱ ዔቦርን ወለደ፤
15.ዔቦርን ከወለደ በኋላ ሳላ
403 ዓመት ኖረ፤ ሌሎች ወንዶችና ሴቶች ልጆችን ወለደ።
16.ዔቦር በ
34 ዓመቱ ፋሌቅን ወለደ፤
17.ፋሌቅን ከወለደ በኋላ ዔቦር
430 ዓመት ኖረ፤ ሌሎች ወንዶችና ሴቶች ልጆችን ወለደ።
18.ፋሌቅ በ
30 ዓመቱ ራግውን ወለደ፤
19.ራግውን ከወለደ በኋላ ፋሌቅ
209 ዓመት ኖረ፤ ሌሎች ወንዶችና ሴቶች ልጆችን ወለደ።
20.ራግው በ
32 ዓመቱ ሴሮሕን ወለደ፤
21.ሴሮሕን ከወለደ በኋላ ራግው
207 ዓመት ኖረ፤ ሌሎች ወንዶችና ሴቶች ልጆችን ወለደ።
22.ሴሮሕ በ
30 ዓመቱ ናኮርን ወለደ፤
23.ናኮርን ከወለደ በኋላ ሴሮሕ
200 ዓመት ኖረ፤ ሌሎች ወንዶችና ሴቶች ልጆችን ወለደ።
24.ናኮር በ 29.ዓመቱ ታራን ወለደ፤
25 ታራን ከወለደ በኋላ ናኮር
119 ዓመት ኖረ፤ ሌሎች ወንዶችና ሴቶች ልጆችን ወለደ።
26 ታራ
70 ዓመት ከሆነው በኋላ አብራምን፣ ናኮርንና ሐራንን ወለደ።
27 የታራ ትውልድ ይህ ነው።
ታራ፣ አብራምን ናኮርንና ሐራንን ወለደ፤ ሐራንም ሎጥን ወለደ።
28 ሐራን፣ አባቱ ታራ ገና በሕይወት እንዳለ በከለዳውያን ምድር በምትገኘው በተወለደባት ከተማ በዑር ሞተ።
29 አብራምና ናኮር ሁለቱም ሚስት አገቡ፤ የአብራም ሚስት ሦራ ስትባል፣ የናኮር ሚስት ደግሞ ሚልካ ትባል ነበር፤ ሚልካም የሐራን ልጅ ናት፤ ሐራንም የሚልካና የዮስካ አባት ነበረ።
30.ሦራ መካን ነበረች፤ ልጅ አልነበራትም። 31.ታራ ልጁን አብራምን፣ ሐራን የወለደውን የልጅ ልጁን ሎጥን እንዲሁም የአብራምን ሚስት ምራቱን ሦራን ይዞ ወደ ከነዓን ለመሄድ በከለዳውያን ምድር ከምትገኘው ከዑር ዐብረው ወጡ፤ ነገር ግን ካራን በደረሱ ጊዜ በዚያ ተቀመጡ። 32.ታራ205 ዓመት ኖሮ በካራን ሞተ።

የማርቆስ ወንጌል

ምዕራፍ 4

የዘሪው ምሳሌ

4፥1-12 ተጓ ምብ – ማቴ 13፥1-15፤ ሉቃ 8፥4-10
4፥13-20 ተጓ ምብ – ማቴ 13፥18-23፤ ሉቃ 8፥1-15
1.በሌላ ጊዜ ደግሞ በባሕሩ አጠገብ ያስተምር ጀመር። እርሱ ባለበት አካባቢ እጅግ ብዙ ሕዝብ ስለ ተሰበሰበ፣ በባሕሩ ላይ ወዳለች ጀልባ ላይ ወጥቶ ተቀመጠ፤ ሕዝቡም ሁሉ በባሕሩ ዳርቻ ባለው ስፍራ ላይ ተሰብስቦ ነበር። 2.እርሱም ብዙ ነገሮችን በምሳሌ አስተማራቸው፤ እንዲህም አላቸው፤ 3.“ስሙ፤ አንድ ዘሪ ዘር ሊዘራ ወጣ። 4.ሲዘራም ሳለ አንዳንዱ ዘር መንገድ ላይ ወደቀ፤ ወፎችም መጥተው ለቅመው በሉት። 5.አንዳንዱም ዘር በቂ ዐፈር በሌለበት በድንጋያማ መሬት ላይ ወደቀ፤ ዐፈሩ ጥልቀት ስላልነበረው ፈጥኖ በቀለ፤ 6.ፀሓይ በወጣ ጊዜ ግን ጠወለገ፤ ሥር ባለመስደዱም ደረቀ። 7.ሌላው ዘር ደግሞ በእሾኽ መካከል ወደቀ፤ እሾኹም አድጎ የዘሩን ተክል ስላነቀው ፍሬ አላፈራም። 8.ሌላውም ዘር ደግሞ በመልካም መሬት ላይ ስለ ወደቀ በቅሎ አደገ፤ ፍሬም ሰጠ፤ አንዱ ሠላሳ፣ አንዱ ስድሳ፣ ሌላውም መቶ ፍሬ አፈራ።” 9.ቀጥሎም ኢየሱስ፣ “ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ” አለ። 10.ብቻውን በሆነ ጊዜ፣ ዐሥራ ሁለቱና ዐብረውት የነበሩት ሌሎች ስለ ምሳሌዎቹ ጠየቁት። 11.እርሱም፣ “ለእናንተ የእግዚአብሔር መንግሥት ምስጢር ተሰጥቷችኋል፤ በውጭ ላሉት ግን ነገር ሁሉ በምሳሌ ይነገራቸዋል፤ 12.ይኸውም፣
“ ‘ማየቱን እንዲያዩ እንዳያስተውሉትም፣
መስማቱን እንዲሰሙ
ልብ እንዳይሉትም፣ እንዳይመለሱና ኀጢአታቸው
እንዳይሰረይላቸው ነው’ አላቸው።”
13.ከዚያም ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፤ “ይህን ምሳሌ አልተረዳችሁትምን? ታዲያ ሌሎቹን ምሳሌዎች ሁሉ እንዴት ልትረዱ ትችላላችሁ? 14.ዘሪው ቃሉን ይዘራል። 15.አንዳንድ ሰዎች በመንገድ ላይ የወደቀውን ዘር ይመስላሉ፤ ቃሉን በሚሰሙበት ጊዜ ሰይጣን ወዲያውኑ መጥቶ በውስጣቸው የተዘራውን ቃል ይወስደዋል። 16.እንዲሁም ሌሎች በጭንጫ መሬት ላይ የተዘራውን ዘር ይመስላሉ፤ ቃሉን በሚሰሙበት ጊዜ ወዲያው በደስታ ይቀበሉታል፤ 17.ነገር ግን ሥር ስላልሰደዱ፣ የሚቈዩት ለጥቂት ጊዜ ብቻ ነው፤ በቃሉ ምክንያት መከራ ወይም ስደት በመጣ ጊዜ ወዲያውኑ ይሰናከላሉ። 18.ሌሎቹ ደግሞ በእሾኽ መካከል የተዘራውን ዘር ይመስላሉ፤ ቃሉን መስማት ይሰማሉ፤ 19.ነገር ግን የዚህ ዓለም ውጣ ውረድ፣ የሀብት አጓጊነት እንዲሁም የሌሎች ነገሮች ምኞት ቃሉን ዐንቀው በመያዝ ፍሬ እንዳያፈራ ያደርጉታል። 20.ሌሎቹ በመልካም መሬት ላይ የተዘራውን ዘር ይመስላሉ፤ እነዚህም ቃሉን ሰምተው የሚቀበሉና ሠላሳ፣ ስድሳ፣ መቶም ፍሬ የሚያፈሩ ናቸው።”

የመቅረዙ መብራት ምሳሌ

21.እንዲህም አላቸው፤ “መብራት ተወስዶ ከእንቅብ በታች ወይም ከዐልጋ ሥር ይቀመጣልን? የሚቀመጠው በመቅረዝ ላይ አይደለምን? 22.ስለዚህ ተደብቆ የማይገለጥ፣ ተሸሽጎ ወደ ብርሃን የማይወጣ የለም፤ 23.ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ።” 24.በመቀጠልም፣ “ስለምትሰሙት ነገር ጥንቃቄ አድርጉ፤ በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ይሰፈርላችኋል፤ እንዲያውም ከዚያ የበለጠ ይጨመርላችኋል። 25.ላለው ይጨመርለታል፤ ከሌለው ላይ ግን፣ ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል” አላቸው።

የአዳጊው ዘር ምሳሌ

26.ከዚያም፣ እንዲህ አለ፤ “የእግዚአብሔር መንግሥት ይህን ትመስላለች፤ አንድ ሰው መሬት ላይ ዘር ይዘራል። 27.ሰውየው ሌሊት ይተኛል፤ ቀን ይነሣል፤ ነገር ግን እርሱ ሳያውቅ ያ ዘር በቅሎ ያድጋል፤ 28.ምድርም ራሷ በመጀመሪያ ቡቃያውን፣ ቀጥሎ ዛላውን፣ ከዚያም በዛላው ላይ የጐመራ ፍሬ ታስገኛለች፤ 29.ፍሬው እንደ በሰለም መከር በመድረሱ፣ ሰውየው ወዲያው ማጭዱን አንሥቶ ዐጨዳ ይጀምራል።”

የሰናፍጭ ቅንጣት ምሳሌ

4፥30-32 ተጓ ምብ – ማቴ 13፥31-32፤ ሉቃ 13፥18-19
30.ደግሞም እንዲህ አለ፤ “የእግዚአብሔርን መንግሥት ከምን ጋራ እናነጻጽራታለን? በምንስ ምሳሌ እንገልጻታለን? 31.በምድር ላይ ከሚዘራው ዘር ሁሉ እጅግ ያነሰችውን የሰናፍጭ ቅንጣት ትመስላለች፤ 32.ተዘርታ ካደገች በኋላ ግን፣ በአትክልቱ ቦታ ከሚገኙት ዕፀዋት ሁሉ ትበልጣለች፤ የሰማይ ወፎችም በትልልቅ ቅርንጫፎቿ ጥላ ሥር ያርፋሉ።” 33.ኢየሱስም ሰዎች መረዳት በሚችሉበት መጠን፣ እነዚህን በመሳሰሉ ብዙ ምሳሌዎች ነገራቸው። 34.ምንም ነገር ያለ ምሳሌ አይነግራቸውም ነበር። እርሱና ደቀ መዛሙርቱ ብቻ በሚሆኑበት ጊዜ ግን ሁሉንም ነገር በዝርዝር ያስረዳቸው ነበር።
ኢየሱስ ማዕበሉን ጸጥ አደረገ
4፥35-41 ተጓ ምብ – ማቴ 8፥18፤ 8፥23-27፤ ሉቃ 8፥22-25
35.ያ ቀን በመሸ ጊዜ፣ “ወደ ማዶ እንሻገር” አላቸው። 36.እነርሱ ሕዝቡን ትተው በጀልባዋ ውስጥ እንዳለ በዚያው ይዘውት ሄዱ፤ ሌሎች ጀልባዎችም ዐብረውት ነበሩ። 37.በዚህ ጊዜ ኀይለኛ ዐውሎ ነፋስ ተነሣ፤ ማዕበሉም ውሃ እስኪሞላት ድረስ ጀልባዋን ያናውጣት ነበር። 38.ኢየሱስ ግን ትራስ ተንተርሶ ከጀልባዋ በስተኋላ በኩል ተኝቶ ነበር። እነርሱም ቀስቅሰውት፣ “መምህር ሆይ፤ ስንጠፋ አይገድድህምን?” አሉት። 39.እርሱም ተነሥቶ ነፋሱን ገሠጸው፤ ባሕሩንም፣ “ጸጥ፣ ረጭ በል!” አለው። ነፋሱም ጸጥ፣ ረጭ አለ፤ ፍጹምም ጸጥታ ሆነ። 40.ደቀ መዛሙርቱንም፣ “ስለ ምን እንዲህ ፈራችሁ? እስከዚህ እምነት የላችሁምን?” አላቸው። 41.እነርሱም በፍርሀት ተውጠው እርስ በርሳቸው፣ “ነፋሱም ሞገዱም የሚታዘዙለት ይህ ማን ነው?” ተባባሉ።