Skip to Content
የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን | YEHIWOT MELHEK BETEKIRSTIAN
የ2019 ዓ.ም የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ 📖 ዛሬን አንብብ →

የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን

Yehiwot Melhek Betekirstian

ሳምንት 1 · ቀን 3 (ረቡዕ) 📅 Meskerem 6, 2019

ኦሪት ዘፍጥረት 6, 7, 8 · መዝሙረ ዳዊት 104 · የማርቆስ ወንጌል 3

📖 የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም፦ 1954 መጽሐፍ ቅዱስ አዲሱ መደበኛ ትርጒም

ኦሪት ዘፍጥረት

ምዕራፍ 6

የጥፋት ውሃ

1.ሰዎች በምድር ላይ እየበዙ ሲሄዱ ሴቶች ልጆች ተወለዱላቸው። 2.የእግዚአብሔር ወንዶች ልጆች የሰዎችን ሴቶች ልጆች ውብ ሆነው አዩአቸው፤ ከመካከላቸውም የመረጧቸውን አገቡ። 3.እግዚአብሔርም፣ “ሰው ሟች ስለ ሆነ መንፈሴ እያዘነ ከርሱ ጋራ ለዘላለም አይኖርም፤ ዕድሜው
120 ዓመት ይሆናል” አለ።
4.የእግዚአብሔርም ልጆች የሰዎችን ሴቶች ልጆች ተገናኝተው ልጆች በወለዱ ጊዜም ሆነ ከዚያም በኋላ ኔፊሊም የተባሉ ሰዎች በምድር ላይ ነበሩ። እነርሱም በጥንቱ ዘመን በጀግንነታቸው ከፍ ያለ ዝና ያተረፉ ናቸው። 5.እግዚአብሔር አምላክ የሰው ዐመፅ በምድር ላይ የበዛና የልቡም ሐሳብ ዘወትር ወደ ክፋት ብቻ ያዘነበለ መሆኑን ተመለከተ። 6.እግዚአብሔር ሰውን በምድር ላይ በመፍጠሩ ተጸጸተ፤ ልቡም እጅግ ዐዘነ። 7.ስለዚህም እግዚአብሔር፣ “የፈጠርሁትን የሰው ዘር ከምድረ ገጽ አጠፋለሁ፤ ከሰው እስከ እንስሳ በምድር ላይ ከሚሳቡ ፍጥረታት እስከ ሰማይ ወፎች አጠፋለሁ፤ ስለ ፈጠርኋቸው ተጸጽቻለሁና” አለ። 8.ኖኅ ግን በእግዚአብሔር ዘንድ ሞገስን አገኘ። 9.የኖኅ ታሪክ እንደሚከተለው ነው።
ኖኅ በዘመኑ ከነበሩት ሰዎች ሁሉ ይልቅ ጻድቅና ነቀፋ የሌለበት ሰው ነበር፤ አካሄዱንም ከእግዚአብሔር ጋራ አደረገ።
10.ኖኅም ሴም፣ ካምና ያፌት የሚባሉ ሦስት ወንዶች ልጆች ነበሩት። 11.ምድር በእግዚአብሔር ፊት በክፉ ሥራ ረከሰች፤ በዐመፅም ተሞላች። 12.እግዚአብሔር ምድር ምን ያህል በክፉ ሥራ እንደ ረከሰች አየ። እነሆ፤ ሰው ሁሉ አካሄዱን አበላሽቶ ነበርና 13.ስለዚህ እግዚአብሔር ኖኅን እንዲህ አለው፦ “ሰውን ሁሉ ላጠፋ ነው፤ ምድር በሰው ዐመፅ ስለ ተሞላች በርግጥ ሰውንም ምድርንም አጠፋለሁ። 14.አንተ ግን በጎፈር ዕንጨት መርከብ ሥራ፤ ለመርከቧም ክፍሎች አብጅላት፤ ውስጧንና ውጭዋን በቅጥራን ለብጠው። 15.እንዲህ አድርገህ ሥራት፦ ርዝመቷ መቶ አርባ ሜትር፣ ወርዷ ሃያ ሦስት ሜትር፣ ከፍታዋ ዐሥራ ሦስት ነጥብ ዐምስት ሜትር ይሁን። 16.ለመርከቧ ጣራ አብጅላት፣ ጣራና ግድግዳው በሚጋጠምበት ቦታ ግማሽ ሜትር ክፍተት ተው፤ ከጐኗ በር አውጣላት፤ ባለሦስት ፎቅ አድርገህ ሥራት። 17.እኔም ከሰማይ በታች የሕይወት እስትንፋስ ያለባቸውን ሕያዋን ፍጥረታት ሁሉ ለማጥፋት እነሆ፤ በምድር ላይ የጥፋት ውሃ አወርዳለሁ፤ በምድር ላይ ያለ ሁሉ ይጠፋል። 18.ከአንተ ጋራ ግን ቃል ኪዳን እመሠርታለሁ። አንተና ወንዶች ልጆችህ፣ ሚስትህና የልጆችህ ሚስቶች ከአንተ ጋራ ወደ መርከቧ ትገባላችሁ። 19.ከአንተ ጋራ በሕይወት እንዲቈዩ ከሕያዋን ፍጥረታት ሁሉ ተባዕትና እንስት እያደረግህ ሁለት ሁለቱን ወደ መርከቧ ታስገባለህ። 20.ከእያንዳንዱ የወፍ ወገን፣ ከእያንዳንዱ የእንስሳ ወገን፣ በምድር ላይ ከሚሳቡ ፍጥረታት ሁሉ በየወገናቸው በሕይወት ይቈዩ ዘንድ ሁለት ሁለት እየሆኑ ወደ አንተ ይመጣሉ። 21.ለአንተና ለእነርሱ የሚያስፈልገውን ምግብ ሁሉ አከማች።” 22.ኖኅም ሁሉን እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ።

ምዕራፍ 7

1.እግዚአብሔር ኖኅን እንዲህ አለው፤ “በዚህ ትውልድ መካከል አንተን ጻድቅ ሆነህ አግኝቼሃለሁና ቤተ ሰብህን በሙሉ ይዘህ ወደ መርከቧ ግባ። 2.ከንጹሕ እንስሳት ሁሉ ሰባት ሰባት ተባዕትና እንስት፣ ንጹሕ ካልሆኑት እንስሳት ደግሞ ሁለት ሁለት ተባዕትና እንስት ውሰድ፤ 3.እንዲሁም ከወፎች ወገን ሁሉ ሰባት ተባዕትና ሰባት እንስት፣ በምድር ላይ ለዘር እንዲተርፉ ከአንተ ጋራ ታስገባለህ። 4.ከሰባት ቀን በኋላ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በምድር ላይ ዝናብ አዘንባለሁ፤ የፈጠርሁትንም ሕያው ፍጡር ሁሉ ከምድር ገጽ አጠፋለሁ።” 5.ኖኅም እግዚአብሔር ያዘዘውን ሁሉ አደረገ። 6.የጥፋት ውሃ በምድር ላይ በወረደ ጊዜ ኖኅ የስድስት መቶ ዓመት ሰው ነበር። 7.ኖኅና ወንዶች ልጆቹ፣ ሚስቱና የልጆቹ ሚስቶች ከጥፋት ውሃ ለመትረፍ ወደ መርከቧ ገቡ። 8.ንጹሕ ከሆኑትና ንጹሕ ካልሆኑት እንስሳት፣ ከወፎችና በምድር ላይ ከሚሳቡ ፍጥረታት ሁሉ ጥንድ ጥንድ፣ 9.ተባዕትና እንስት ሆነው ወደ ኖኅ መጡ፤ እግዚአብሔር ኖኅን ባዘዘውም መሠረት ወደ መርከቧ ገቡ። 10.ከሰባት ቀንም በኋላ የጥፋት ውሃ በምድር ላይ መጣ። 11.ኖኅ በተወለደ በስድስት መቶኛው ዓመት፣ በሁለተኛው ወር፣ ከወሩም በዐሥራ ሰባተኛው ቀን፣ በዚያ ቀን የታላቁ ጥልቅ ምንጮች በሙሉ ተነደሉ፤ የሰማይ መስኮቶችም ተከፈቱ፤ 12.አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በምድር ላይ ዝናብ ዘነበ። 13.በዚያ ዕለት ኖኅና ልጆቹ ሴም፣ ካምና ያፌት፣ እንዲሁም ሚስቱና ሦስቱ የልጆቹ ሚስቶች ወደ መርከቧ ገቡ። 14.ከዱር እንስሳት ከየወገኑ፣ ከቤት እንስሳት ከየወገኑ፣ በምድር ላይ ከሚሳቡ ፍጥረታት ከየወገናቸው፣ ከወፎችም ከየወገናቸውና ክንፍ ያላቸው ሁሉ ዐብረዋቸው ገቡ። 15.የሕይወት እስትንፋስ ያለባቸው ፍጥረታት በሙሉ ጥንድ ጥንድ እየሆኑ ወደ ኖኅ በመምጣት መርከቧ ውስጥ ገቡ። 16.ከሕያዋንም ፍጥረታት ሁሉ እግዚአብሔር ኖኅን ባዘዘው መሠረት ተባዕትና እንስት እየሆኑ ገቡ፤ ከዚያም እግዚአብሔር ከውጭ ዘጋበት። 17.የጥፋት ውሃም ለአርባ ቀናት ያለ ማቋረጥ በምድር ላይ ዘነበ፤ ውሃው እየጨመረ በሄደ መጠን መርከቧን ከምድር ወደ ላይ አነሣት። 18.ውሃው በምድር ላይ በጣም እየጨመረና ከፍ እያለ ሲሄድ፣ መርከቧ በውሃው ላይ ተንሳፈፈች። 19.ውሃው በጣም ከፍ በማለቱ፣ ከሰማይ በታች ያሉትን ታላላቅ ተራሮች ሁሉ ሸፈናቸው። 20.ውሃው ከተራሮቹ ጫፍ በላይ
7 ሜትር ያህል ከፍ አለ።
21.በምድር ላይ የነበሩ ሕያዋን ፍጥረታት ሁሉ፦ ወፎች፣ የቤት እንሰሳት፣ የዱር እንስሳት በምድር የሚርመሰመሱ ፍጥረታት፣ ሰዎችም በሙሉ ጠፉ። 22.በአፍንጫቸው የሕይወት እስትንፋስ ያላቸው በየብስ የነበሩ ፍጥረታት ሁሉ ሞቱ። 23.ሕይወት ያላቸው ፍጥረታት ሁሉ ከምድር ገጽ ጠፉ፤ ሰዎችና እንስሳት በምድር ላይ የሚሳቡ ፍጥረታትና የሰማይ ወፎች ከምድር ላይ ጠፉ፤ ኖኅና ከርሱ ጋራ በመርከቧ ውስጥ የነበሩት ብቻ ተረፉ። 24.ውሃውም ምድርን ሸፍኖ መቶ ዐምሳ ቀን ቈየ።

ምዕራፍ 8

1.እግዚአብሔር ኖኅንና በመርከቧ ውስጥ ከርሱ ጋራ የነበሩትን የዱርና የቤት እንስሳት ሁሉ ዐሰበ፤ በምድር ላይ ነፋስ እንዲነፍስ አደረገ፤ ውሃውም ጐደለ። 2.የጥልቁ ምንጮችና የሰማይ ውሃ መስኮቶች ተዘጉ፤ ዝናቡም መዝነቡን አቆመ። 3.ውሃው ከምድር ላይ ቀስ በቀስ እየቀነሰ መጣ፤ ከመቶ ዐምሳ ቀን በኋላም ጐደለ። 4.በሰባተኛው ወር፣ በዐሥራ ሰባተኛው ቀን መርከቧ በአራራት ተራሮች ላይ ዐረፈች። 5.ውሃው እስከ ዐሥረኛው ወር ድረስ እየቀነሰ መጣ፤ በዐሥረኛው ወር፣ በመጀመሪያው ቀን የተራሮቹ ጫፎች ታዩ። 6.ከአርባ ቀን በኋላ ኖኅ የሠራውን የመርከቧን መስኮት ከፍቶ፣ 7.ቍራን ወደ ውጭ ላከ፤ ቍራውም ውሃው ከምድር ላይ እስኪደርቅ ድረስ ወዲያና ወዲህ ይበር ነበር። 8.ከዚያም በኋላ፣ ኖኅ ውሃው ከምድር ገጽ ጐድሎ እንደ ሆነ ለማወቅ ርግብን ላከ፤ 9.ነገር ግን ውሃው የምድርን ገጽ ገና እንደ ሸፈነ ስለ ነበር፣ ተመልሳ ኖኅ ወዳለበት መርከብ መጣች፤ እርሱም እጁን ዘርግቶ ተቀበላት፤ ወደ መርከቢቱም አስገባት። 10.ሰባት ቀን ከቈየ በኋላ ኖኅ ርግቧን እንደ ገና ላካት። 11.እርሷም ወደ ማታ ተመለሰች፤ እነሆም የለመለመ የወይራ ቅጠል በአፏ ይዛ ነበር፤ ያን ጊዜ ኖኅ ውሃው ከምድር ላይ መጕደሉን ዐወቀ። 12.ሰባት ቀንም ቈይቶ ርግቧን እንደ ገና ላካት፤ በዚህ ጊዜ ግን ርግቧ ወደ እርሱ አልተመለሰችም። 13.ኖኅ በተወለደ በስድስት መቶ አንደኛው ዓመት፣ በመጀመሪያው ወር፣ ከወሩም በመጀመሪያው ቀን ውሃው ከምድር ላይ ደረቀ። 14.ኖኅ በመርከቡ ላይ ያለውን ክዳን አንሥቶ ተመለከተ፤ የመሬቱም ገጽ እንደ ደረቀ አየ። በሁለተኛው ወር፣ በሃያ ሰባተኛው ቀን ምድሪቱ ሙሉ በሙሉ ደረቀች። 15.ከዚያም እግዚአብሔር ኖኅን እንዲህ አለው፤ 16.“አንተና ሚስትህ፣ ልጆችህና የልጆችህ ሚስቶች ከመርከቧ ውጡ። 17.እንዲዋለዱ፣ እንዲራቡና በምድር ላይ እንዲበዙ፣ ከአንተ ጋራ ያሉትን ወፎች፣ እንስሳትና በምድር ላይ የሚሳቡ ፍጥረታትን ሁሉ ይዘሃቸው ውጣ።” 18.ኖኅም ከልጆቹ፣ ከሚስቱና ከልጆቹ ሚስቶች ጋራ ወጣ። 19.እንስሳቱ ሁሉ፣ ወፎችም፣ በምድር ላይ የሚሳቡ ፍጥረታት ሁሉ በየወገናቸው ከመርከቧ ወጡ። 20.ከዚያም ኖኅ ለእግዚአብሔር መሠዊያ ሠራ፤ መሠዊያው ላይ ንጹሕ ከሆኑት እንስሳት ሁሉ፣ እንዲሁም ንጹሕ ከሆኑት ወፎች የሚቃጠል መሥዋዕት አቀረበ፤ 21.እግዚአብሔርም ደስ የሚያሠኘውን መዐዛ አሸተተ፤ በልቡም እንዲህ አለ፤ “ምንም እንኳ ሰው ገና ከልጅነቱ ጀምሮ ሐሳቡ ወደ ክፋት ያዘነበለ ቢሆንም በርሱ ምክንያት ሁለተኛ ምድርን አልረግማትም፤ አሁን እንዳደረግሁት ሕያዋን ፍጥረታትን ዳግመኛ አላጠፋም። 22.“ምድር እስካለች ድረስ፣
የዘር ወቅትና መከር፣
ሙቀትና ቅዝቃዜ
በጋና ክረምት፣
ቀንና ሌሊት፣
አይቋረጡም።”

መዝሙረ ዳዊት

ምዕራፍ 104

1.ነፍሴ ሆይ፤ እግዚአብሔርን ባርኪ፤
እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ፤ አንተ እጅግ ታላቅ ነህ፤
ክብርንና ግርማን ለብሰሃል።
2.ብርሃንን እንደ ሸማ ተጐናጽፈሃል፤
ሰማያትንም እንደ ድንኳን መጋረጃ ዘረጋህ፤
3.የእልፍኝህን አግዳሚ በውሆች ላይ አኖርህ፤
ደመናትን ሠረገላህ አደረግህ፤
በነፋስ ክንፍ ትሄዳለህ።
4.መላእክትህን መንፈስ፣
አገልጋዮችህንም የእሳት ነበልባል ታደርጋለህ።
5.ለዘላለም እንዳትናወጥ፣
ምድርን በመሠረቷ ላይ አጸናት።
6.በጥልቁ እንደ ልብስ ሸፈንሃት፤
ውሆችም ከተራሮች በላይ ቆሙ።
7.በገሠጽሃቸው ጊዜ ግን ፈጥነው ሄዱ፤
የነጐድጓድህንም ድምፅ በሰሙ ጊዜ ሸሹ።
8.በተራሮች ላይ ፈሰሱ፤
ወዳዘጋጀህላቸው ስፍራ፣
ወደ ሸለቆዎች ወረዱ።
9.ተመልሰው ምድርን እንዳይሸፍኑ፣
ዐልፈውም እንዳይመጡ ድንበር አበጀህላቸው።
10.ምንጮችን በሸለቆ ውስጥ እንዲሄዱ አደረግህ፤
በተራሮችም መካከል ይፈስሳሉ፤
11.የዱር እንስሳትም ከዚያ ይጠጣሉ፤
የሜዳ አህዮችም ጥማቸውን ይቈርጣሉ።
12.የሰማይ ወፎች ጐጇቸውን በወንዞቹ ዳር ይሠራሉ፤
በቅርንጫፎችም መካከል ይዘምራሉ።
13.ከላይ ከእልፍኝህ ተራሮችህን ታጠጣለህ፤
ምድርም በሥራህ ፍሬ ትረካለች።
14.ከምድር ምግብን ታወጣ ዘንድ፣
ለእንስሳት ሣርን፣
ለሰው ልጆች ሥራ ዕፀዋትን ታበቅላለህ፤
15.የሰውን ልብ ደስ የሚያሰኝ ወይን፣
ፊቱን የሚያወዛ ዘይት፣
ልቡን የሚያበረታ እህል በዚህ ይገኛል።
16.ደግሞም የእግዚአብሔር ዛፎች፣
እርሱ የተከላቸውም የሊባኖስ ዝግባዎች ጠጥተው ይረካሉ፤
17.ወፎች ጐጇቸውን በዚያ ይሠራሉ፤
ሽመላ በጥዶቹ ውስጥ ማደሪያ ታገኛለች።
18.ረዣዥሙ ተራራ የዋሊያ መኖሪያ፣
የዐለቱም ዋሻዎች የሽኮኮ መሸሸጊያ ናቸው።
19.ጨረቃን የወቅቶች መለያ አደረግሃት፤
ፀሓይም የምትጠልቅበትን ጊዜ ታውቃለች።
20.ጨለማን ታመጣለህ፤ ሌሊትም ይሆናል፤
የዱር አራዊትም ሁሉ በዚህ ጊዜ ወጥተው ይራወጣሉ።
21.የአንበሳ ግልገሎች ምግብ ፍለጋ ይጮኻሉ፤
የሚበሉትንም ከእግዚአብሔር ይሻሉ።
22.ፀሓይ በወጣች ጊዜም ይመለሳሉ፤
በየጐሬያቸውም ገብተው ይተኛሉ።
23.ሰውም ወደ ሥራው ይሄዳል፤
እስኪመሽም በተግባሩ ላይ ይሰማራል።
24.እግዚአብሔር ሆይ፤ ሥራህ እንዴት ብዙ ነው!
ሁሉን በጥበብ ሠራህ፤
ምድርም በፍጥረትህ ተሞላች።
25.ይህች ባሕር ሰፊና የተንጣለለች ናት፤
ታላላቅና ታናናሽ እንስሳት፣
ስፍር ቍጥር የሌላቸውም የሚርመሰመሱ ፍጥረታት በውስጧ አሉ።
26.መርከቦች በላይዋ ይመላለሳሉ፤
አንተ የፈጠርኸውም ሌዋታን በውስጧ ይፈነጫል።
27.ምግባቸውን በወቅቱ ትሰጣቸው ዘንድ፣
እነዚህ ሁሉ አንተን ተስፋ ያደርጋሉ።
28.በሰጠሃቸውም ጊዜ፣
አንድ ላይ ያከማቻሉ፤
እጅህንም ስትዘረጋ፣
በመልካም ነገር ይጠግባሉ።
29.ፊትህን ስትሰውር፣
በድንጋጤ ይሞላሉ፤
እስትንፋሳቸውንም ስትወስድባቸው ይሞታሉ፤
ወደ ዐፈራቸውም ይመለሳሉ።
30.መንፈስህን ስትልክ፣
እነርሱ ይፈጠራሉ፤
የምድርንም ገጽ ታድሳለህ።
31.የእግዚአብሔር ክብር ለዘላለም ጸንቶ ይኑር፤
እግዚአብሔር በሥራው ደስ ይበለው፤
32.እርሱ ምድርን ሲመለከት፣ ትንቀጠቀጣለች፤
ተራሮችም እርሱ ሲዳስሳቸው ይጤሳሉ።
33.በሕይወት ሳለሁ ለእግዚአብሔር እዘምራለሁ፤
ቆሜ እስከ ሄድሁ ድረስም አምላኬን እወድሳለሁ።
34.እኔ በእግዚአብሔር ደስ እንደሚለኝ፣
የልቤ ሐሳብ እርሱን ደስ ያሠኘው።
35.ኃጥኣን ከምድር ገጽ ይጥፉ፤
ዐመፀኞች ከእንግዲህ አይገኙ።
ነፍሴ ሆይ፤ እግዚአብሔርን ባርኪ።
ሃሌ ሉያ።

የማርቆስ ወንጌል

ምዕራፍ 3

1.በሌላ ጊዜ ወደ ምኵራብ ገባ፤ በዚያም እጁ የሰለለች ሰው ነበር። 2.በምክንያት ሊከስሱት የሚፈልጉ ሰዎችም በሰንበት ቀን ይፈውሰው እንደ ሆነ ለማየት ይጠባበቁ ነበር። 3.እርሱም እጁ የሰለለችበትን ሰው፣ “ተነሥተህ መካከል ላይ ቁም” አለው። 4.ኢየሱስም፣ “በሰንበት ቀን የተፈቀደው መልካም ማድረግ ነው ወይስ ክፉ? ሕይወት ማዳን ነው ወይስ ማጥፋት?” አላቸው። እነርሱ ግን ዝም አሉ። 5.በልባቸው ደንዳናነት ዐዝኖ በዙሪያው የቆሙትን በቍጣ ተመለከታቸውና ሰውየውን፣ “እጅህን ዘርጋ!” አለው፤ ሰውየውም እጁን ዘረጋ፤ እጁም ፍጹም ደኅና ሆነችለት። 6.ፈሪሳውያንም እንዴት እንደሚገድሉት ከሄሮድስ ወገን ከሆኑት ጋራ መመካከር ጀመሩ።

ብዙ ሰዎች ኢየሱስን ተከተሉ

3፥7-12 ተጓ ምብ – ማቴ 12፥15-16፤ ሉቃ 6፥17-19
7.ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋራ ወደ ባሕሩ ሄደ፤ ከገሊላ የመጣ እጅግ ብዙ ሕዝብም ተከተለው፤ 8.የሚሠራውን ነገር የሰሙ ሰዎችም ከይሁዳ፣ ከኢየሩሳሌም፣ ከኤዶምያስ፣ በዮርዳኖስ ማዶ ካለው አገር እንዲሁም ከጢሮስና ከሲዶና አካባቢ ወደ እርሱ መጡ። 9.የተሰበሰበውም ሕዝብ እንዳያጨናንቀው አነስተኛ የሆነ ጀልባ እንዲያዘጋጁለት ደቀ መዛሙርቱን አዘዛቸው። 10.ብዙዎችን ፈውሶ ስለ ነበር፣ በሕመም የሚሠቃዩ ሁሉ ሊዳስሱት ይሽቀዳደሙ ነበር። 11.ርኩሳን መናፍስትም ባዩት ቍጥር ከፊቱ እየወደቁ፣ “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ” በማለት ይጮኹ ነበር። 12.እርሱ ግን ማንነቱን እንዳይገልጹ አጥብቆ ይገሥጻቸው ነበር።

የዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት መሾም

3፥16-19 ተጓ ምብ – ማቴ 10፥2-4፤ ሉቃ 6፥14-16፤ ሐሥ 1፥13
13.ኢየሱስም ወደ ተራራ ወጥቶ የሚፈልጋቸውን ወደ እርሱ እንዲመጡ ጠራቸው፤ እነርሱም ወደ እርሱ መጡ። 14.ከርሱ ጋራ እንዲሆኑ፣ ለስብከትም እንዲልካቸው ዐሥራ ሁለቱን ሾማቸው፤ ሐዋርያትም ብሎ ጠራቸው፤ 15.አጋንንትን እንዲያስወጡም ሥልጣን ሰጣቸው። 16.የሾማቸውም ዐሥራ ሁለቱ እነዚህ ናቸው፤
ጴጥሮስ ብሎ የጠራው ስምዖን፣
17.ቦአኔርጌስ ይኸውም፣ “የነጐድጓድ ልጆች” ብሎ የጠራው የዘብዴዎስ ልጅ ያዕቆብና ወንድሙ ዮሐንስ፤ 18.እንድርያስ፣
ፊልጶስ፣
በርተሎሜዎስ፣
ማቴዎስ፣
ቶማስ፣
የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብ፣
ታዴዎስ፣
ቀነናዊው ስምዖን፣
19.እንዲሁም አሳልፎ የሰጠው የአስቆሮቱ ይሁዳ።

ኢየሱስና ብዔልዜቡል

3፥23-27 ተጓ ምብ – ማቴ 12፥25-29፤ ሉቃ 11፥17-22
20.ከዚያም ኢየሱስ ወደ አንድ ቤት ገባ፤ እርሱና ደቀ መዛሙርቱ ምግብ መብላት እንኳ እስኪሳናቸው ድረስ ሕዝቡ እንደ ገና በብዛት ተሰበሰበ። 21.ሁኔታውን የሰሙ ዘመዶቹም፣ “አእምሮውን ስቷል” በማለት ይዘውት ለመሄድ ወዳለበት መጡ። 22.ከኢየሩሳሌም የመጡ ጸሐፍትም፣ “ብዔልዜቡል ዐድሮበታል! አጋንንትን የሚያወጣው በአጋንንት አለቃ ነው” አሉ። 23.እርሱም ጠራቸውና በምሳሌ እንዲህ አላቸው፤ “ሰይጣን ሰይጣንን እንዴት ሊያስወጣ ይችላል? 24.እርስ በርሱ የሚከፋፈል መንግሥት ሊጸና አይችልም፤ 25.ቤትም እርስ በርሱ ከተከፋፈለ ሊቆም አይችልም። 26.እንደዚሁም ሰይጣን እርስ በርሱ የሚፃረርና የሚከፋፈል ከሆነ ሊቆም አይችልም፤ ያበቃለታል። 27.ከዚህም የተነሣ አንድ ሰው አስቀድሞ ኀይለኛውን ሰው ሳያስር ወደ ኀይለኛው ሰው ቤት ሊገባና ንብረቱን ሊዘርፍ አይችልም፤ ቤቱን መዝረፍ የሚቻለው ኀይለኛውን ሰው ሲያስር ብቻ ነው። 28.እውነት እላችኋለሁ፤ የሰው ልጆች ኀጢአትና የሚሳደቡት ስድብ ሁሉ ይሰረይላቸዋል፤ 29.ነገር ግን በመንፈስ ቅዱስ ላይ የስድብ ቃል የሚናገር ሁሉ የዘላለም ኀጢአት ዕዳ ይሆንበታል እንጂ ለዘላለም አይሰረይለትም።” 30.ይህንም ያለው፣ “ርኩስ መንፈስ አለበት” ስላሉት ነበር።

የኢየሱስ እናትና ወንድሞቹ

3፥31-35 ተጓ ምብ – ማቴ 12፥46-50፤ ሉቃ 8፥19-21
31.ከዚህ በኋላ እናቱና ወንድሞቹ መጡ፤ በውጭ ቆመውም ሰው ልከውበት አስጠሩት። 32.በዙሪያው የተቀመጡ ብዙ ሰዎችም፣ “እነሆ፤ እናትህና ወንድሞችህ ውጭ ይፈልጉሃል” አሉት። 33.እርሱም መልሶ፣ “እናቴ ማን ናት፣ ወንድሞቼስ እነማን ናቸው?” አላቸው። 34.በዙሪያው ወደ ተቀመጡትም በመመልከት፣ እንዲህ አለ፤ “እናቴና ወንድሞቼ እነዚህ ናቸው! 35.የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ እርሱ ወንድሜ፣ እኅቴ፣ እናቴም ነውና።”