ኦሪት ዘጸአት 10, 11, 12 · ወደ ኤፌሶን ሰዎች 2
ኦሪት ዘጸአት
ምዕራፍ 10
የአንበጣ መንጋ መቅሠፍት
1.ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ተመልሰህ ወደ ፈርዖን ሂድ፤ እነዚህን ታምራዊ ምልክቶች በመካከላቸው ለማድረግ የፈርዖንንና የሹማምቱን ልብ አደንድኛለሁና፤ 2.ይኸውም ግብጻውያንን እንዴት አድርጌ እንደ ቀጣኋቸውና በመካከላቸውም ምልክቶቼን እንዴት እንዳደረግሁ ለልጆቻችሁና ለልጅ ልጆቻችሁ እንድትነግሩና እኔ እግዚአብሔር መሆኔንም እንድታውቁ ነው።” 3.ሙሴና አሮን ወደ ፈርዖን ሄደው እንዲህ አሉት፤ “የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ራስህን በፊቴ ለማዋረድ እስከ መቼ እንቢ ትላለህ? ሕዝቤ ያመልኩኝ ዘንድ ልቀቃቸው። 4.እንዳይሄዱ ብትከለክላቸው ነገ በአገርህ ላይ አንበጣዎችን አመጣለሁ። 5.አንበጣዎቹም ምድሪቱ እስከማትታይ ድረስ ይሸፍኗታል፤ በመስክህ ላይ እያቈጠቈጠ ያለውን ዛፍ ሁሉ ሳይቀር ከበረዶ የተረፈውንም ጥቂቱን ሁሉ ይበሉታል። 6.የአንተን፣ የሹማምትህንና የግብጻውያንን ቤቶች ሁሉ ይሞሏቸዋል፤ ይህም አባቶችህም ሆኑ ቅድመ አያቶችህ በዚህች ምድር ከሰፈሩበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከቶ አይተውት የማያውቁት ነው።’ ” ሙሴም ተመለሰና ከፈርዖን ተለይቶ ሄደ። 7.የፈርዖንም ሹማምት፣ “ይህ ሰው እስከ መቼ ወጥመድ ይሆንብናል? አምላካቸውን እግዚአብሔርን እንዲያመልኩ ሰዎቹን ልቀቃቸውና ይሂዱ። ግብጽ መጥፋቷን እስካሁን አልተገነዘብህምን?” አሉት። 8.ከዚያም ሙሴና አሮን ወደ ፈርዖን እንዲመጡ ተደረገ፤ “ሂዱ አምላካችሁን እግዚአብሔርን አምልኩ፤ ነገር ግን መሄድ የሚገባቸው የትኞቹ ናቸው?” አለ። 9.ሙሴም፣ “ለእግዚአብሔር በዓል ልናከብር ስለ ሆነ ወጣቶቻችንንና ሽማግሌዎቻችንን፣ ወንድና ሴት ልጆቻችንን፣ የበግና የፍየል መንጋዎቻችንን እንዲሁም የቀንድ ከብቶቻችንን ይዘን እንሄዳለን” አለ። 10.ፈርዖንም እንዲህ አለ፤ “ከሴቶቻችሁና ከልጆቻችሁ ጋራ እንድትሄዱ እለቅቃችኋለሁ፤ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋራ ይሁን፤ ነገር ግን ተንኰል ዐስባችኋል። 11.አይሆንም፤ ወንዶቹ ብቻ እንዲሄዱና እግዚአብሔርን እንዲያመልኩ አድርጉ፤ የጠየቃችሁት ይህንኑ ነው።” ከዚያም ሙሴና አሮን ከፈርዖን ፊት እንዲወጡ ተደረገ። 12.እግዚአብሔር ሙሴን፣ “የአንበጣ መንጋ ምድሪቱን እንዲወርር ከበረዶ የተረፈውን ሁሉና በማሳም ላይ የበቀለውን ሁሉ ጠርጎ እንዲበላ እጅህን በግብጽ አገር ላይ ዘርጋ” አለው። 13.ስለዚህ ሙሴ በግብጽ አገር ላይ በትሩን ዘረጋ፤ እግዚአብሔርም በዚያ ቀንና ሌሊት በሙሉ በምድሪቱ ላይ የምሥራቅ ነፋስ እንዲነፍስ አደረገ፤ በማግስቱም ነፋሱ አንበጣዎችን አመጣ። 14.እነርሱም ግብጽን በሙሉ ወረሩ፤ ስፍር ቍጥር የሌላቸው ሆነው የሀገሪቱን ዳር ድንበር ሁሉ አለበሱ። እንዲህ ያለ የአንበጣ መዓት ከዚህ ቀደም አልነበረም፤ ወደ ፊትም ደግሞ አይኖርም። 15.ምድሩ ሁሉ ጠቍሮ እስኪጨልም ድረስ አለበሱት። ከበረዶ የተረፈውን፣ በመስክ ላይ የበቀለውንና በዛፍ ላይ ያለውን ፍሬ ሁሉ ጠርገው በሉ። በግብጽ ምድር ሁሉ በዛፍ ላይ ወይም በተክል ላይ አንዳች ቅጠል አልተረፈም ነበር። 16.ከዚያም ፈርዖን ሙሴንና አሮንን በፍጥነት አስጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “በአምላካችሁ በእግዚአብሔር በእናንተም ላይ ኀጢአት ሠርቻለሁ፤ 17.እንግዲህ አሁን አንድ ጊዜ ደግሞ ኀጢአቴን ይቅር በሉኝና ይህን ቀሣፊ መዓት እንዲያስወግድልኝ አምላካችሁን እግዚአብሔርን ለምኑልኝ።” 18.ሙሴም ከፈርዖን ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ። 19.ከዚያም እግዚአብሔር ነፋሱን ወደ ብርቱ የምዕራብ ነፋስ ለወጠው፤ ያም ነፋስ አንበጣዎቹን እየነዳ ወደ ቀይ ባሕር ከተታቸው፤ በግብጽ ምድር በየትኛውም ቦታ አንድም አንበጣ አልቀረም። 20.እግዚአብሔር ግን የፈርዖንን ልብ አደነደነ፤ ፈርዖንም እስራኤላውያን እንዲሄዱ አልፈቀደም።የጨለማ መቅሠፍት
21.ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን፣ “በግብጽ ላይ ድቅድቅ ጨለማ እንዲወርድ እጅህን ወደ ሰማይ ዘርጋ” አለው። 22.ሙሴም እጁን ወደ ሰማይ ዘረጋ፤ በመላው ግብጽ ላይ ለሦስት ቀናት ድቅድቅ ያለ ጨለማ ሆነ። 23.በእነዚያ ሦስት ቀናት ውስጥ አንዱ ሌላውን ማየት ወይም ከነበረበት ቦታ መንቀሳቀስ አይችልም ነበር። ይሁን እንጂ እስራኤላውያን በሚኖሩበት ስፍራ ሁሉ ብርሃን ነበር። 24.ከዚያም ፈርዖን ሙሴን አስጠርቶ፣ “ሄዳችሁ እግዚአብሔርን አምልኩ፤ ሴቶቻችሁና ልጆቻችሁ ሳይቀሩ ዐብረዋችሁ ይሂዱ፤ በጎቻችሁ፣ ፍየሎቻችሁና የጋማ ከብቶቻችሁ ብቻ እዚሁ ይቅሩ” አለው። 25.ሙሴም እንዲህ አለው፤ “ለአምላካችን ለእግዚአብሔር መሥዋዕትና የሚቃጠል መሥዋዕት እንድንሠዋ ፍቀድልን፤ 26.እንስሶቻችን ሁሉ ዐብረው መሄድ አለባቸው። አንድ ሰኰና እንኳ አይቀርም። ከእንስሶቻችን መካከል ለአምላካችን ለእግዚአብሔር አምልኮ የምናቀርባቸው ይኖራሉ፤ ሆኖም እዚያ ከመድረሳችን በፊት እግዚአብሔርን ለማምለክ የምናቀርባቸው እንስሳት የትኞቹ እንደ ሆኑ አስቀድመን ለይተን ማወቅ አንችልም።” 27.ነገር ግን እግዚአብሔር የፈርዖንን ልብ አደነደነ፤ ፈርዖንም ሕዝቡን መልቀቅ አልፈቀደም። 28.ፈርዖን ሙሴን፣ “ከፊቴ ጥፋ! ሁለተኛ እኔ ዘንድ እንዳትደርስ! ፊቴን ባየህበት በዚያ ቀን ፈጽመህ እንደምትሞት ዕወቅ” አለው። 29.ሙሴም፣ “እንዳልከው ይሁን፤ እኔም ዳግመኛ ከፊትህ አልደርስም” አለው።ምዕራፍ 11
በበኵሮች ላይ የወረደ መቅሠፍት
1.እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “በፈርዖንና በግብጽ ላይ አንድ ሌላ መቅሠፍት አወርድባቸዋለሁ፤ ከዚያም በኋላ ፈርዖን ይለቅቃችኋል፤ ሲለቅቃችሁም አንዳችሁን ሳያስቀር ያስወጣችኋል። 2.ለእስራኤል ሕዝብ፣ ለወንዶቹም ሆነ ለሴቶቹ የብርና የወርቅ ዕቃዎች ከየጎረቤቶቻቸው ስጡን ብለው እንዲወስዱ ንገራቸው።” 3.እግዚአብሔርም እስራኤላውያን በግብጻውያን ዘንድ ሞገስ እንዲያገኙ አደረጋቸው። ሙሴም በግብጽ ምድር በፈርዖን ሹማምትና በመላው ሕዝብ ዘንድ እጅግ የተከበረ ሰው ሆነ። 4.ከዚህ በኋላ ሙሴ እንዲህ አለ፤ “እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፤ ‘እኩለ ሌሊት ሲሆን በመላው የግብጽ ምድር ላይ ዐልፋለሁ። 5.በዙፋኑ ላይ ከተቀመጠው ከፈርዖን ልጅ አንሥቶ የወፍጮ መጅ ገፊ እስከ ሆነችው እስከ ባሪያዪቱ ልጅ ድረስ በግብጽ ምድር በኵር ሆኖ የተወለደ ወንድ ልጅ ሁሉ ይሞታል፤ እንዲሁም የቀንድ ከብቱ በኵር በሙሉ ያልቃል። 6.በግብጽ ምድር ሁሉ ከዚህ በፊት ያልተሰማ ወደ ፊትም የማይሰማ ታላቅ ዋይታ ይሆናል። 7.በእስራኤላውያን ዘንድ ግን በሰውም ሆነ በእንስሳት ላይ ውሻ እንኳ አይጮኽባቸውም።’ በዚህም እግዚአብሔር በግብጻውያንና በእስራኤላውያን መካከል ልዩነት የሚያደርግ መሆኑን ታውቃላችሁ። 8.ሹማምትህ በሙሉ ወደ እኔ ይመጣሉ፤ እጅ እየነሡም ‘አንተም ሆንህ የምትመራቸው ሰዎች በሙሉ ውጡልን’ ብለው ይለምኑኛል፤ እኔም ከዚያ በኋላ እሄዳለሁ።” ከዚያም ሙሴ በታላቅ ቍጣ ከፈርዖን ዘንድ ወጣ። 9.እግዚአብሔር ሙሴን “ድንቅ ሥራዎቼ በግብጽ ምድር በብዛት ይታዩ ዘንድ ፈርዖን እናንተን አይሰማችሁም” አለው። 10.ሙሴና አሮንም እነዚህን ድንቅ ታምራት በፈርዖን ፊት አደረጉ። ነገር ግን እግዚአብሔር የፈርዖንን ልብ አደነደነ፤ ፈርዖንም እስራኤላውያን ከአገሩ ለቅቀው እንዲሄዱ አልፈቀደም።ምዕራፍ 12
የፋሲካ በዓል
ከግብጽ መውጣት
31.ፈርዖን ሙሴንና አሮንን ሌሊቱን አስጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “ተነሡ፤ እናንተና እስራኤላውያን ከሕዝቤ መካከል ውጡ፤ ሂዱ፤ በጠየቃችሁት መሠረት እግዚአብሔርን አምልኩ፤ 32.እንዳላችሁት የበግና የፍየል መንጋችሁን፣ የቀንድና የጋማ ከብቶቻችሁን ይዛችሁ ሂዱ፤ እኔንም ባርኩኝ።” 33.ግብጻውያን አገራቸውን በአስቸኳይ ለቅቀው እንዲወጡላቸው እስራኤላውያንን አጣደፏቸው። “አለዚያማ ሁላችንም ማለቃችን ነው” አሉ። 34.ስለዚህ ሕዝቡ ያልቦካውን ሊጥ በየቡሖ ዕቃው አድርገው በጨርቅ ጠቅልለው በትከሻቸው ተሸከሙ። 35.እስራኤላውያን ሙሴ እንዳዘዛቸው የብርና የወርቅ ዕቃዎች፣ እንደዚሁም ልብስ እንዲሰጧቸው ግብጻውያኑን ጠየቋቸው። 36.እግዚአብሔር በግብጻውያን ፊት ለእስራኤላውያን ሞገስ ስለ ሰጣቸው፣ የጠየቋቸውን ሁሉ ሰጧቸው፤ ስለዚህ የግብጻውያንን ንብረት በዝብዘው ወሰዱ። 37.እስራኤላውያን ከራምሴ ተነሥተው ወደ ሱኮት ሄዱ። ከሴቶቹና ከልጆቹ ሌላ፣ ስድስት መቶ ሺሕ እግረኛ ወንዶች ነበሩ። 38.ከእነርሱም ጋራ ቍጥሩ የበዛ ሌላ ድብልቅ ሕዝብ ዐብሯቸው ወጣ፤ እንዲሁም አያሌ የበግ፣ የፍየል፣ የጋማና የቀንድ ከብት መንጋ ይዘው ወጡ። 39.ከግብጽ ይዘው ከወጡት ሊጥ ያልቦካ ቂጣ ጋገሩ፤ ሊጡ አልቦካም ነበር፤ ምክንያቱም ከግብጽ በጥድፊያ እንዲወጡ ስለተደረጉ፣ ለራሳቸው ምግብ ለማዘጋጀት ጊዜ አልነበራቸውም። 40.እንግዲህ እስራኤላውያን በግብጽ የኖሩበት ዘመን አራት መቶ ሠላሳ ዓመት ነበር። 41.ልክ አራት መቶ ሠላሳው ዓመት በተፈጸመ ዕለት የእግዚአብሔር ሰራዊት ሁሉ ግብጽን ለቅቆ ወጣ። 42.እግዚአብሔር በዚያች ሌሊት እነርሱን ከግብጽ ለማውጣት ዘብ የቆመበት በመሆኑ፣ ለሚቀጥሉት ትውልዶች ሁሉ እግዚአብሔርን ያከብሩ ዘንድ፣ በዚያች ሌሊት እስራኤላውያን ሁሉ ዘብ መቆም ይኖርባቸዋል።የፋሲካ በዓል እንዴት መከበር እንዳለበት
43.እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤ “የፋሲካ በዓል አከባበር ሥርዐት እንዲህ ነው፤ ባዕድ የሆነ ሰው ከፋሲካው ምግብ አይብላ፤ 44.በገንዘብ የገዛኸው ማንኛውም ባሪያ ከገረዝኸው በኋላ መብላት ይችላል፣ 45.ነገር ግን ለጊዜው የተቀመጠ እንግዳና ቅጥር ሠራተኛ መብላት የለበትም። 46.“ምግቡ በአንድ ቤት ውስጥ መበላት አለበት፤ ምንም ሥጋ ከቤት እንዳይወጣ፤ ምንም ዐጥንት እንዳትሰብሩ። 47.የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ በዓሉን ማክበር ይኖርበታል። 48.“በመካከላችሁ የሚኖር መጻተኛ የእግዚአብሔርን የፋሲካ በዓል ማክበር ቢፈልግ፣ በቤተ ሰቡ ያሉት ወንዶች ሁሉ መገረዝ አለባቸው፤ ከዚያም እንደ ተወላጅ ተቈጥሮ የሥርዐቱ ተካፋይ ይሁን። ያልተገረዘ ወንድ ግን የፋሲካን ምግብ አይብላ። 49.ይህም ሕግ በዜጋውም ሆነ በመካከላችሁ በሚኖሩት መጻተኞች ላይ እኩል ተፈጻሚነት ይኖረዋል።” 50.እስራኤላውያን በሙሉ እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን ያዘዘውን ሁሉ ፈጸሙ። 51.በዚያችው ዕለት እግዚአብሔር እስራኤላውያንን በየሰራዊታቸው አድርጎ ከግብጽ ምድር አወጣቸው።2 በክርስቶስ ሕያው መሆን
እናንተም በበደላችሁና በኀጢአታችሁ ምክንያት ሙታን ነበራችሁ፤
2 በዚህም፣ የዓለምን ክፉ መንገድ ተከትላችሁ፣ በአየር ላይ ላሉት መንፈሳውያን ኀይላት ገዥ ለሆነውና አሁንም ለእግዚአብሔር በማይታዘዙት ሰዎች ላይ ለሚሠራው መንፈስ እየታዘዛችሁ ትኖሩ ነበር።
3 እኛ ሁላችን በአንድ ወቅት የሥጋችንን ምኞት እያረካን፣ መንገዱንም እየተከተልን በመካከላቸው እንኖር ነበር፤ እንደ ሌሎቹም የቍጣ ልጆች ነበርን።
4 ነገር ግን በምሕረቱ ባለጠጋ የሆነ እግዚአብሔር ለእኛ ካለው ከታላቅ ፍቅሩ የተነሣ፣
5 በበደላችን ሙታን ሆነን ሳለ፣ በክርስቶስ ሕያዋን አደረገን፤ የዳናችሁት በጸጋ ነው።
6 እግዚአብሔርም ከክርስቶስ ጋራ አስነሣን፤ በክርስቶስ ኢየሱስ በሰማያዊ ስፍራ ከርሱ ጋራ አስቀመጠን፤
7 ይኸውም በሚመጣው ዘመን በክርስቶስ ኢየሱስ በቸርነቱ የገለጠልንን ወደር የሌለውን የጸጋውን ባለጠግነት ያሳይ ዘንድ ነው።
8 በእምነት፣ በጸጋ ድናችኋልና፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም፤
9 ማንም እንዳይመካ በሥራ አይደለም፤
10 ምክንያቱም፣ እግዚአብሔር አስቀድሞ እንድንመላለስባቸው ያዘጋጀልንን መልካም የሆኑትን ሥራዎች እንድንሠራ በክርስቶስ ኢየሱስ የተፈጠርን የእግዚአብሔር እጅ ሥራዎች ነን።
አይሁድና አሕዛብ በክርስቶስ አንድ መሆን
11 ስለዚህ እናንተ ቀድሞ በትውልድ አሕዛብ የሆናችሁ፣ በአካል ላይ በሰው እጅ ከተደረገው የተነሣ፣ ራሳቸውን “ተገርዘናል” በሚሉት፣ “ያልተገረዙ” የተባላችሁ ያን አስታውሱ፤
12 በዚያ ዘመን ከክርስቶስ ተለይታችሁ፣ ከእስራኤል ወገንነት ርቃችሁ፣ ለኪዳኑም ተስፋ ባዕዳን ሆናችሁ፣ በዓለም ላይ ያለ ተስፋና ያለ እግዚአብሔር እንደ ነበራችሁ አስታውሱ።
13 አሁን ግን እናንተ ቀድሞ ርቃችሁ የነበራችሁ፣ በክርስቶስ ኢየሱስ ሆናችሁ በክርስቶስ ደም አማካይነት ቀርባችኋል።
14 ሁለቱን አንድ ያደረገ፣ የሚለያየውንም የጥል ግድግዳ ያፈረሰ ሰላማችን እርሱ ራሱ ነውና፤
15 ሕግንም፣ ከትእዛዞቹና ከሥርዐቱ ጋራ በሥጋው ሻረ። ዐላማውም ከሁለቱ አንድን አዲስ ሰው በራሱ ፈጥሮ ሰላምን ለማድረግ ነው።
16 ጥልን በገደለበት በመስቀሉም ሁለቱን በዚህ በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋራ አስታረቀ።
17 መጥቶም ርቃችሁ ለነበራችሁት ለእናንተ፣ ቀርበው ለነበሩትም ለእነርሱ ሰላምን ሰበከ፤
18 ሁላችንም በርሱ አማካይነት በአንዱ መንፈስ ወደ አብ መቅረብ እንችላለንና።
19 ከዚህ የተነሣ እናንተ ከቅዱሳን ጋራ የአንድ አገር ዜጋ፣ የእግዚአብሔርም ቤተ ሰብ አባል ናችሁ እንጂ፣ ከእንግዲህ ወዲህ መጻተኞችና እንግዶች አይደላችሁም።
20 በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል፤ የማእዘኑ ራስ ድንጋይም ክርስቶስ ኢየሱስ ራሱ ነው፤
21 በርሱ ሕንጻ ሁሉ አንድ ላይ ተገጣጥሞ በጌታ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንዲሆን ያድጋል።
22 እናንተም ደግሞ እግዚአብሔር በመንፈሱ የሚኖርበት ማደሪያ ትሆኑ ዘንድ ዐብራችሁ እየተገነባችሁ ነው።