ሳምንት 5 · ቀን 24 (ሐሙስ)
📅 Tikimt 5, 2019
ኦሪት ዘጸአት 10, 11, 12 · ወደ ኤፌሶን ሰዎች 2
ኦሪት ዘጸአት
ምዕራፍ 10
1.1.1-2.እግዚአብሔርም ሙሴን። እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቁ ዘንድ በግብፃውያን ያደረግሁትን ነገር ያደረግሁባቸውንም ተአምራቴን በልጅህ በልጅ ልጅህም ጆሮች ትነግር ዘንድ፥ ይህችንም ተአምራቴን በመካከላቸው አደረግ ዘንድ የእርሱን የባሪያዎቹንም ልብ አደንድኜአለሁና ወደ ፈርዖን ግባ አለው።
3.ሙሴም አሮንም ወደ ፈርዖን ገቡ፥ አሉትም። የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በፊቴ ለመዋረድ እስከ መቼ እንቢ ትላለህ? ያገለግሉኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ።
4.ሕዝቤን ለመልቀቅ እንቢ ብትል ግን፥ እነሆ ነገ በአገርህ አንበጣዎችን አመጣለሁ፤
5.የምድሩንም ፊት ይሸፍኑታልና ምድሩን ለማየት አይቻልም፤ ከበረዶውም አምልጦ የተረፈላችሁን ትርፍ ይበሉታል፥ ያደገላችሁንም የእርሻውን ዛፍ ሁሉ ይበሉታል፤
6.ቤቶችህም የባሪያዎችህም ሁሉ ቤቶች የግብፃውያንም ሁሉ ቤቶች በእነርሱ ይሞላል፤ አባቶችህ የአባቶችህም አባቶች በምድር ላይ ከተቀመጡበት ቀን ጀምሮ እስከዚህ ቀን ድረስ እንደ እርሱ ያለ ያላዩት ነው። ተመልሶም ከፈርዖን ዘንድ ወጣ።
7.የፈርዖንም ባሪያዎች። ይህ ሰው እስከ መቼ ዕንቅፋት ይሆንብናል? አምላካቸውን እግዚአብሔርን ያገለግሉት ዘንድ ሰዎችን ልቀቅ ግብፅስ እንደ ጠፋች ገና አታውቅምን? አሉት።
8.ፈርዖንም ሙሴንና አሮንን መልሶ አስመጣቸው። ሂዱ፥ አምላካችሁን እግዚአብሔርን አገልግሉ፤ ነገር ግን የሚሄዱት እነማን ናቸው? አላቸው።
9.ሙሴም። እኛ እንሄዳለን፥ የእግዚአብሔር በዓል ሆኖልናልና ታናናሾቻችንና ሽማግሌዎቻችን ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችንም በጎቻችንና ከብቶቻችንም ከእኛ ጋር ይሄዳሉ አለ።
10.ፈርዖንም። እናንተን ከልጆቻችሁ ጋር ስለቅቅ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሁን፤ ነገር ግን ክፉ ነገር በፊታችሁ እንደሚሆን ተመልከቱ።
11.እንዲህም አይይደለም፤ እናንተ ወንዶቹ ሂዱ፥ ይህን ፈልጋችኋልና እግዚአብሔርን አገልግሉ አላቸው። ከፈርዖንም ፊት አባረሩአቸው።
12.እግዚአብሔርም ሙሴን። በግብፅ አገር ላይ እንዲወጡ፥ ከበረዶውም የተረፈውን የምድርን ቡቃያ ሁሉ እንዲበሉ፥ ስለ አንበጣዎች በግብፅ አገር ላይ እጅህን ዘርጋ አለው።
13.ሙሴም በግብፅ አገር ላይ በትሩን ዘረጋ፥ እግዚአብሔርም የምሥራቅን ነፋስ ያን ቀን ሁሉ ሌሊቱን ሁሉ አመጣ፤ ማለዳም በሆነ ጊዜ የምሥራቁ ነፋስ አንበጣዎቹን አመጣ።
14.አንበጣዎችም በግብፅ አገር ሁሉ ላይ ወጡ፥ በግብፅም ዳርቻ ሁሉ ላይ ተቀመጡ፤ እጅግም ብዙ ነበሩ፤ ይህንም የሚያህል አንበጣ በፊት አልነበረም፥ ወደ ፊትም ደግሞ እንደ እርሱ አይሆንም።
15.የምድሩንም ፊት ፈጽመው ሸፈኑት አገሪቱም ጨለመች፤ የአገሪቱን ቡቃያ ሁሉ በረዶውም የተወውን በዛፉ የነበረውን ፍሬ ሁሉ በሉ፤ ለምለም ነገር ዛፍም የምድር ሣርም በግብፅ አገር ሁሉ አልቀረም።
16.ፈርዖንም ሙሴንና አሮንን በፍጥነት ጠራ። አምላካችሁን እግዚአብሔርን እናንተንም በደልሁ፤
17.አሁን እንግዲህ በዚህ ጊዜ ብቻ ኃጢአቴን ይቅር በሉኝ፥ ይህንም ሞት ብቻ ከእኔ ያነሣልኝ ዘንድ አምላካችሁን እግዚአብሔርን ለምኑ አላቸው።
18.ሙሴም ከፈርዖን ፊት ወጣ፥ ወደ እግዚአብሔርም ለመነ።
19.እግዚአብሔርም ከምዕራብ ዐውሎ ነፋሱን አስወገደ፥ አንበጣዎችንም ወስዶ በኤርትራ ባሕር ውስጥ ጣላቸው፤ አንድ አንበጣም በግብፅ ዳርቻ ሁሉ አልቀረም።
20.እግዚአብሔር የፈርዖንን ልብ አጸና የእስራኤልንም ልጆች አልለቀቀም።
21.እግዚአብሔርም ሙሴን። እጅህን ወደ ሰማይ ዘርጋ፥ በግብፅም አገር ላይ ሰው የሚዳስሰው ፅኑ ጨለማ ይሁን አለው።
22.ሙሴም እጁን ወደ ሰማይ ዘረጋ፥ በግብፅም አገር ሁሉ ላይ ፅኑ ጨለማ ሦስት ቀን ሆነ፤
23.ማንም ወንድሙን አላየም፥ ሦስት ቀንም ሙሉ ከስፍራው ማንም አልተነሣም፤ ለእስራኤል ልጆች ሁሉ ግን በተቀመጡበት ስፍራ ብርሃን ነበራቸው።
24.ፈርዖንም ሙሴን ጠርቶ። ሂዱ፥ እግዚአብሔርን አገልግሉ፤ ነገር ግን በጎቻችሁንና ከብቶቻችሁን ተዉ፤ ልጆቻችሁ ደግሞ ከእናንተ ጋር ይሂዱ አለው።
25.ሙሴም። አንተ ደግሞ ለአምላካችን ለእግዚአብሔር የምንሠዋው መሥዋዕትንና የሚቃጠል መሥዋዕትን ትሰጠናለህ።
26.አምላካችንን እግዚአብሔርን ለማገልገል ከእነርሱ እንወስዳለንና ከብቶቻችን ከእኛ ጋር ይሄዳሉ፥ አንድ ሰኮናም አይቀርም፤ አምላካችን የምናገለግለው ምን እንደሆነ ከዚያ እስክንደርስ አናውቅም አለ።
27.እግዚአብሔር የፈርዖንን ልብ አጸና፥ ሊለቅቃቸውም አልወደደም።
28.ፈርዖንም። ከእኔ ዘንድ ሂድ፤ ፊቴን ባየህበት ቀን ትሞታለህና ፊቴን እንዳታይ ተጠንቀቅ አለው።
29.ሙሴም። እንደ ተናገርህ ይሁን፤ ፊትህን እንደ ገና አላይም አለ።
ምዕራፍ 11
1.እግዚአብሔርም ሙሴን። በፈርዖንና በግብፅ ላይ ገና አንዲት መቅሰፍት አመጣለሁ፥ ከዚያ ወዲያም ይለቅቃችኋል፤ ሲለቅቃችሁም አባርሮ ይሰድዳችኋል።
2.ወንዱ ከወዳጁ ሴቲቱም ከወዳጅዋ የብርና የወርቅ ዕቃ ይሹ ዘንድ በሕዝቡ ጆሮ ተናገር አለው።
3.እግዚአብሔርም በግብፃውያን ፊት ለሕዝቡ ሞገስን ሰጠው። ሙሴም በፈርዖን ባሪያዎችና በሕዝቡ ፊት በግብፅ አገር እጅግ የከበረ ሰው ነበረ።
4.ሙሴም አለ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በእኩል ሌሊት እኔ በግብፅ መካከል እወጣለሁ፤
5.በግብፅም አገር ያለ በኵር ሁሉ፥ በዙፋኑ ከሚቀመጠው ከፈርዖን በኵር ጀምሮ በወፍጮ እግር እስካለችው እስከ ባሪያይቱ በኵር ድረስ፥ የከብቱም በኵር ሁሉ ይሞታል።
6.በግብፅም አገር ሁሉ አስቀድሞ እንደ እርሱ ያልሆነ ኋላም ደግሞ የማይሆን ታላቅ ጩኸት ይሆናል።
7.እግዚአብሔር ግን በግብፃውያንና በእስራኤል መካከል እንዲለይ እንድታውቁ በእስራኤል ልጆች መካከል ከሰው ጀምሮ እስከ እንስሳ ድረስ ውሻ ምላሱን አያንቀሳቅስባቸውም።
8.እነዚህም ባሪያዎችህ ሁሉ። አንተ ውጣ የሚከተሉህም ሕዝብ ሁሉ ይውጡ እያሉ ወደ እኔ ይወርዳሉ፥ ለእኔም ይሰግዳሉ፤ ከዚያም በኋላ እወጣለሁ። ሙሴም በጽኑ ቁጣ ከፈርዖን ዘንድ ወጣ።
9.እግዚአብሔርም ሙሴን። ተአምራቴ በግብፅ አገር ብዙ እንዲሆን ፈርዖን አይሰማችሁም አለው።
10.ሙሴና አሮንም እነዚህን ተአምራቶች ሁሉ በፈርዖን ፊት አደረጉ፤ እግዚአብሔር የፈርዖንን ልብ አጸና፥ የእስራኤልንም ልጆች ከአገሩ አልለቀቀም።
ምዕራፍ 12
1.እግዚአብሔርም በግብፅ አገር ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው።
2.ይህ ወር የወሮች መጀመሪያ ይሁናችሁ፤ የዓመቱም መጀመሪያ ወር ይሁናችሁ።
3.ለእስራኤል ልጆች ሁሉ ተናገሩ፥ በሉአቸውም። በዚህ ወር በአሥረኛው ቀን ሰው ሁሉ ለአባቱ ቤት አንድ ጠቦት፥ ለአንድ ቤትም አንድ ጠቦት ይውሰድ።
4.የቤቱ ሰዎች ቍጥርም ለጠቦቱ የማይበቃ ቢሆን እርሱና ለቤቱ የቀረበው ጎረቤቱ እንደ ነፍሶቻቸው ቍጥር አንድ ጠቦት ይውሰድ፤ እያንዳንዱም እንደሚበላው መጠን ከጠቦቱ ይካፈሉ።
5.የእናንተ ጠቦት ነውር የሌለበት የአንድ ዓመት ተባት ይሁን፤ ከበጎች ወይም ከፍየሎች ውሰድ።
6.በዚህም ወር እስከ አሥራ አራተኛው ቀን ድረስ ጠብቁት፤ የእስራኤልም ማኅበር ጉባኤ ሁሉ ሲመሽ ይረዱት።
7.ከደሙም ወስደው በሚበሉበት ቤት ሁለቱን መቃንና ጉበኑን ይቅቡት።
8.በእሳት የተጠበሰውን ሥጋውንና ቂጣውን እንጀራ በዚያች ሌሊት ይብሉ፤ ከመራራ ቅጠል ጋር ይበሉታል።
9.ጥሬውን በውኃም የበሰለውን አትብሉ፥ ነገር ግን ከራሱ ከጭኑ ከሆድ ዕቃው ጋር በእሳት የተጠበሰውን ብሉት።
10.ከእርሱም እስከ ጥዋት አንዳች አታስቀሩ፤ እስከ ጥዋትም የቀረውን በእሳት አቃጥሉት።
11.ወገቦቻችሁን ታጥቃችሁ፥ ጫማችሁን በእግራችሁ፥ በትራችሁንም በእጃችሁ አድርጋችሁ እንዲህ ብሉት፥ ፈጥናችሁም ትበሉታላችህ፤ እርሱ የእግዚአብሔር ፋሲካ ነው።
12.እኔም በዚያች ሌሊት በግብፅ አገር አልፋለሁ፥ በግብፅም አገር ከሰው እስከ እንስሳ ድረስ በኵርን ሁሉ እገድላለሁ፤ በግብፅም አማልክት ሁሉ ላይ እፈርድባቸዋለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
13.ደሙም ባላችሁበት ቤቶች ምልክት ይሆንላችኋል፤ ደሙንም ባየሁ ጊዜ ከእናንተ አልፋለሁ፤ እኔም የግብፅን አገር በመታሁ ጊዜ መቅሰፍቱ ለጥፋት አይመጣባችሁም።
14.ይህም ቀን መታሰቢያ ይሁናችሁ፥ ለእግዚአብሔርም በዓል ታደርጉታላችሁ፤ ለልጅ ልጃችሁ ሥርዓት ሆኖ ለዘላለም ታደርጉታላችሁ።
15.ሰባት ቀን ቂጣ እንጀራ ትበላላችሁ፤ በመጀመሪያም ቀን እርሾውን ከቤታችሁ ታወጣላችሁ፤ ከመጀመሪያውም ቀን አንሥቶ እስከ ሰባተኛው ቀን እርሾ ያለበትን እንጀራ የሚበላ ነፍስ ከእስራኤል ተለይቶ ይጥፋ።
16.በመጀመሪያውም ቀን የተቀደሰ ጉባኤ እንዲሁም በሰባተኛውም ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይሆንላችኋል። ከሚበላው በቀር በእነርሱም ምንም አትሠሩም፥ ይህንም ብቻ ታደርጉታላችሁ።
17.በዚህም ቀን ሠራዊታችሁን ከግብፅ አገር አውጥቼአለሁና የቂጣውንም በዓል ጠብቁት፤ እንግዲህ ይህን ቀን ለልጅ ልጃችሁ ለዘላለም ሥርዓት ትጠብቃላችሁ።
18.በመጀመሪያውም ወር በአሥራ አራተኛው ቀን በመሸ ጊዜ ከወሩም እስከ ሀያ አንድ ቀን በመሸ ጊዜ የቂጣ እንጀራ ትበላላችሁ።
19.ሰባት ቀን በቤታችሁ እርሾ አይገኝ፤ እርሾ ያለበትንም እንጀራ የሚበላ ነፍስ፥ ከመጻተኛው ጀምሮ እስከ አገር ልጁ ድረስ፥ ከእስራኤል ማኅበር ተለይቶ ይጥፋ።
20.እርሾ ያለበትን ምንም አትብሉ፥ በቤቶቻችሁም ሁሉ ውስጥ ቂጣ እንጀራ ብሉ።
21.ሙሴም የእስራኤልን ሽማግሌዎች ጠርቶ አላቸው። በየቤታችሁ ጠቦት ምረጡ፥ ወስዳችሁም ለፋሲካ እረዱት።
22.ከሂሶጵ ቅጠልም ጭብጥ ውሰዱ፥ በዕቃ ውስጥ ባለውም ደም ንከሩት፥ በዕቃውም ውስጥ ካለው ደም ሁለቱን መቃኖችና ጉበኑን እርጩ፤ ከእናንተም አንድ ሰው ከቤቱ ደጅ እስኪነጋ ድረስ አይውጣ።
23.እግዚአብሔር ግብፃውያንን ይመታ ዘንድ ያልፋልና፤ ደሙንም በጉበኑና በሁለቱ መቃኖች ላይ ባየ ጊዜ እግዚአብሔር በደጁ ላይ ያልፋል፥ አጥፊውም ይመታችሁ ዘንድ ወደ ቤታችሁ እንዲገባ አይተውም።
24.ለእናንተ ለልጆቻችሁም ለዘላለም ሥርዓት አድርጋችሁ ይህችን ነገር ጠብቁ።
25.እንዲህም ይሆናል፤ እግዚአብሔር እንደ ተናገረ ወደ ሚሰጣችሁ አገር በገባችሁ ጊዜ ይህን አምልኮ ጠብቁት።
26.እንዲህም ይሆናል፤ ልጆቻችሁ። ይህ አምልኮ ለእናንተ ምንድር ነው?
27.ባሉአችሁ ጊዜ፥ እናንተ። በግብፅ አገር በእስራኤል ልጆች ቤቶች ላይ አልፎ ግብፃዊያንን በመታ ጊዜ፥ ቤቶቻችንን ያዳነ የእግዚአብሔር የማለፉ መሥዋዕት ይህች ናት ትሉአቸዋላችሁ።
28.ሕዝቡም ተጎነበሰ ሰገደም። የእስራኤልም ልጆች ሄዱ፥ እንዲሁም አደረጉ፤ እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንዳዘዘ እንዲሁ አደረጉ።
29.እንዲህም ሆነ፤ እኩል ሌሊት በሆነ ጊዜ እግዚአብሔር፥ በዙፋን ከተቀመጠው ከፈርዖን በኵር ጀምሮ በግዞት እስካሉት እስከ ምርኮኞቹ በኵር ድረስ፥ የግብፃውያንን በግብፅ ምድር የተገኘውን በኵር ሁሉ፥ የእንስሳውንም በኵሮች ሁሉ መታ።
30.ፈርዖንም ባሪያዎቹም ሁሉ ግብፃውያንም ሁሉ በሌሊት ተነሡ፤ የሞተ የሌለበት ቤት አልነበረምና በግብፅ ምድር ታላቅ ልቅሶ ሆነ።
31.ፈርዖንም ሙሴንና አሮንን በሌሊት ጠርቶ። እናንተ የእስራኤልም ልጆች ተነሡ፥ ከሕዝቤ መካከል ውጡ፤ ሂዱም፥ እንዳላችሁም እግዚአብሔርን አገልግሉ፤
32.እንዳላችሁም መንጎቻችሁንና ከብቶቻችሁን ውሰዱ፥ ሂዱም፥ እኔንም ደግሞ ባርኩኝ አለ።
33.ግብፃውያንም ፈጥነው ከምድሩ ይወጡ ዘንድ ሕዝቡን ያስቸኵሉአቸው ነበር። ሁላችን እንሞታለን ብለዋልና።
34.ሕዝቡም ሊጡን ሳይቦካ ተሸከሙ፥ ቡሃቃውንም በልብሳቸው ጠቅልለው በትከሻቸው ተሸከሙት።
35.የእስራኤልም ልጆች ሙሴ እንዳዘዘ አደረጉ፥ ከግብፃውያንም የብርንና የወርቅን ዕቃ ልብስንም ለመኑ።
36.እግዚአብሔርም ለሕዝቡ በግብፃውያን ፊት የፈለጉትን እንዲሰጡአቸው ሞገስን ሰጠ። እነርሱም ግብፃውያንን በዘበዙ።
37.የእስራኤልም ልጆች ከራምሴ ተነሥተው ወደ ሱኮት ሄዱ፤ ከሕፃናቱም ሌላ ስድስት መቶ ሺህ ሰው የሚያህል እግረኛ ነበረ።
38.ደግሞም ሌላ ብዙ ድብልቅ ሕዝብ መንጎችና ላሞችም እጅግ ብዙም ከብቶች ከእነርሱ ጋር ወጡ።
40.እንዲህም ሆነ፤ አራት መቶ ሠላሳ ዓመት ከተፈጸመ በኋላ በዚያ ቀን የእግዚአብሔር ሠራዊት ሁሉ ከግብፅ ምድር ወጣ።
41.ይህች ሌሊት ከግብፅ ምድር ስላወጣቸው ለእግዚአብሔር የተጠበቀች ናት፤ ይህች ሌሊት በእስራኤል ልጆች ሁሉ ዘንድ እስከ ልጅ ልጃቸው ድረስ ለእግዚአብሔር የተጠበቀች ናት።
42.እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን አለ። ይህ የፋሲካ ሕግ ነው፤ ከእርሱ እንግዳ ሰው አይብላ።
43.በብር የተገዛ ባሪያ ቢኖር ከተገረዘ በኋላ ከእርሱ ይብላ።
44.መጻተኛና ሞያተኛ ግን ከእርሱ አይብሉ።
45.በአንድ ቤትም ይበላ፤ ከሥጋውም አንዳች ከቤት ወደ ሜዳ አታውጡ፤ አጥንትም አትስበሩበት።
46.የእስራኤልም ጉባኤ ሁሉ ያድርጉት።
47.እንግዳ ሰውም በመካከላችሁ ቢቀመጥ ለእግዚአብሔርም ፋሲካን ሊያደርግ ቢወድድ፥ አስቀድሞ ወንድ ሁሉ ይገረዝ፥ ከዚያም ወዲያ ይቅረብ ያድርግም፤ እንደ አገር ልጅም ይሆናል፤ ያልተገረዘ ሁሉ ግን ከእርሱ አይብላ።
48.ለአገር ልጅ በእናንተ መካከልም ለሚቀመጡ እንግዶች አንድ ሥርዓት ይሆናል።
49.የእስራኤልም ልጆች ሁሉ እንዲህ አደረጉ፤ እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንዳዘዘ እንዲሁ አደረጉ።
50.በዚያም ቀን እግዚአብሔር የእስራኤልን ልጆች ከሠራዊታቸው ጋር ከግብፅ ምድር አወጣ።
ወደ ኤፌሶን ሰዎች
ምዕራፍ 2
1.በበደላችሁና በኃጢአታችሁ ሙታን ነበራችሁ፤ በእነርሱም፥2.በዚህ ዓለም እንዳለው ኑሮ፥ በማይታዘዙትም ልጆች ላይ አሁን ለሚሠራው መንፈስ አለቃ እንደ ሆነው በአየር ላይ ሥልጣን እንዳለው አለቃ ፈቃድ፥ በፊት ተመላለሳችሁባቸው።
3.በእነዚህም ልጆች መካከል እኛ ሁላችን ደግሞ፥ የሥጋችንንና የልቡናችንን ፈቃድ እያደረግን፥ በሥጋችን ምኞት በፊት እንኖር ነበርን እንደ ሌሎቹም ደግሞ ከፍጥረታችን የቁጣ ልጆች ነበርን።
4.ነገር ግን እግዚአብሔር በምሕረቱ ባለ ጠጋ ስለ ሆነ፥5.ከወደደን ከትልቅ ፍቅሩ የተነሣ በበደላችን ሙታን እንኳ በሆንን ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ሕይወት ሰጠን፥ በጸጋ ድናችኋልና፥6.-7.በሚመጡ ዘመናትም በክርስቶስ ኢየሱስ ለእኛ ባለው ቸርነት ከሁሉ የሚበልጠውን የጸጋውን ባለ ጠግነት ያሳይ ዘንድ፥ ከእርሱ ጋር አስነሣን በክርስቶስ ኢየሱስም በሰማያዊ ስፍራ ከእርሱ ጋር አስቀመጠን።
8.ጸጋው በእምነት አድኖአችኋልና፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም፤
9.ማንም እንዳይመካ ከሥራ አይደለም።
10.እኛ ፍጥረቱ ነንና፤ እንመላለስበት ዘንድ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን።
11.ስለዚህ እናንተ አስቀድሞ በሥጋ አሕዛብ የነበራችሁ፥ በሥጋ በእጅ የተገረዙ በተባሉት ያልተገረዙ የተባላችሁ፥ ይህን አስቡ፤
12.በዚያ ዘመን ከእስራኤል መንግሥት ርቃችሁ ለተስፋውም ቃል ኪዳን እንግዶች ሆናችሁ በዚህም ዓለም ተስፋን አጥታችሁ ከእግዚአብሔርም ተለይታችሁ ያለ ክርስቶስ ነበራችሁ።
13.አሁን ግን እናንተ በፊት ርቃችሁ የነበራችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ ሆናችሁ በክርስቶስ ደም ቀርባችኋል።
15.ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው።
16.መጥቶም ርቃችሁ ለነበራችሁ ለእናንተ ሰላምን፥ ቀርበው ለነበሩትም ሰላምን የምስራች ብሎ ሰበከ፤
17.በእርሱ ሥራ ሁላችን በአንድ መንፈስ ወደ አብ መግባት አለንና።
18.እንግዲያስ ከእንግዲህ ወዲህ ከቅዱሳን ጋር ባላገሮችና የእግዚአብሔር ቤተ ሰዎች ናችሁ እንጂ እንግዶችና መጻተኞች አይደላችሁም።
19.በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል፥ የማዕዘኑም ራስ ድንጋይ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፤
20.በእርሱም ሕንጻ ሁሉ እየተጋጠመ በጌታ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንዲሆን ያድጋል፤
21.በእርሱም እናንተ ደግሞ ለእግዚአብሔር መኖሪያ ለመሆን በመንፈስ አብራችሁ ትሠራላችሁ።