Skip to Content
የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን | YEHIWOT MELHEK BETEKIRSTIAN
የ2019 ዓ.ም የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ 📖 ዛሬን አንብብ →

የሕይወት መልሕቅ ቤተክርስቲያን

Yehiwot Melhek Betekirstian

ሳምንት 5 · ቀን 23 (ረቡዕ) 📅 Tikimt 4, 2019

ኦሪት ዘጸአት 7, 8, 9 · መዝሙረ ዳዊት 105 · ወደ ኤፌሶን ሰዎች 1

📖 የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም፦ 1954 መጽሐፍ ቅዱስ አዲሱ መደበኛ ትርጒም

ኦሪት ዘጸአት

ምዕራፍ 7

1.እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ልብ በል፤ እኔ አንተን ለፈርዖን እንደ አምላክ አድርጌሃለሁ፤ ወንድምህ አሮንም ያንተ ነቢይ ይሆናል። 2.እኔ የማዝህን ሁሉ ትናገራለህ፤ ወንድምህ አሮንም እስራኤላውያንን ከአገሩ እንዲወጡ ይለቅቃቸው ዘንድ ለፈርዖን ይነግረዋል። 3.እኔ ግን የፈርዖንን ልብ አደነድናለሁ፤ ታምራዊ ምልክቶችንና ድንቆችን በግብጽ ላይ በብዛት ባደርግም እንኳ፣ አይሰማችሁም። 4.ከዚያም እጄን በግብጽ ላይ አደርጋለሁ፤ በኀያል ፍርድም ሰራዊቴን፣ ሕዝቤን እስራኤላውያንን አወጣለሁ። 5.እጄን በግብጽ ላይ ስዘረጋና እስራኤላውያንንም ከዚያ ሳወጣ፣ ግብጻውያን እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ያውቃሉ።” 6.ሙሴና አሮን እግዚአብሔር እንደ አዘዛቸው አደረጉ። 7.ፈርዖንን ባነጋገሩበት ጊዜ ሙሴ ዕድሜው ሰማንያ ዓመት፣ አሮን ደግሞ ሰማንያ ሦስት ነበር።

የአሮን በትር እባብ ሆነች

8.እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፣ 9.“ፈርዖን፣ ‘ታምር አሳዩኝ’ ባላችሁ ጊዜ፣ አሮንን እንዲህ በለው፤ ‘በትርህን ውሰድና በፈርዖን ፊት ጣላት፤’ ከዚያም እባብ ትሆናለች።” 10.ስለዚህ ሙሴና አሮን ወደ ፈርዖን ሄደው እግዚአብሔር እንዳዘዛቸው አደረጉ። አሮን በትሩን በፈርዖንና በሹማምቱ ፊት ጣላት፤ እባብም ሆነች። 11.ከዚያም ፈርዖን ጠቢባኑንና መተተኞቹን ጠራ፤ የግብጽ አስማተኞችም በድብቅ ጥበባቸው ያንኑ አደረጉ፤ 12.እያንዳንዱ የያዛትን በትር ጣለ፤ እባብም ሆነች። ነገር ግን የአሮን በትር የእነርሱን በትሮች ዋጠች። 13.ሆኖም የፈርዖን ልብ ደነደነ፤ እግዚአብሔር ተናግሮ እንደ ነበረውም አላደመጣቸውም።

የደም መቅሠፍት

14.ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “የፈርዖን ልብ ደነደነ፤ ሕዝቡን ለመልቀቅ አልፈቀደም። 15.ወደ ውሃው በሚሄድበት ጊዜ ማልደህ ወደ ፈርዖን ሂድ፤ እንድታገኘውም በአባይ ዳር ተጠባበቅ፤ ወደ እባብ ተለውጣ የነበረችውንም በትር በእጅህ ያዝ። 16.ከዚያም እንዲህ በለው፤ ‘የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር “ሕዝቤ በምድረ በዳ ያመልኩኝ ዘንድ እንዲሄዱ ልቀቃቸው” ብዬ እንድነግርህ ላከኝ፤ አንተ ግን እስካሁን ድረስ ዕሺ አላልህም። 17.እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፤ “እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ በዚህ ታውቃለህ፤ እይ! በዚህች በእጄ በያዝኋት በትር የአባይን ውሃ እመታለሁ፤ ወደ ደምም ይለወጣል። 18.በአባይ ወንዝ ውስጥ ያለው ዓሣ ይሞታል፤ ወንዙ ይከረፋል፤ ግብጻውያንም ውሃውን መጠጣት አይችሉም።” ’ ” 19.እግዚአብሔር ሙሴን አለው፤ “አሮንን፣ ‘በትርህን ውሰድና በግብጽ ውሆች ላይ፣ ይኸውም በምንጮች፣ በቦዮች፣ በኵሬዎችና በውሃ ማጠራቀሚያዎች ላይ እጅህን ዘርጋ’ ብለህ ንገረው፤ ወደ ደምም ይለወጣሉ። ከዕንጨትና ከድንጋይ በተሠሩ ውሃ መያዣዎች ውስጥም ሳይቀር በግብጽ ምድር ደም በየቦታው ይሆናል።” 20.ሙሴና አሮን እግዚአብሔር እንደ አዘዛቸው አደረጉ። እርሱም በፈርዖንና በሹማምቱ ፊት በትሩን አንሥቶ የአባይን ወንዝ ውሃ መታ፤ ውሃውም በሙሉ ወደ ደም ተለወጠ። 21.በአባይ ያሉት ዓሦች ሞቱ፤ ወንዙም ከመከርፋቱ የተነሣ ግብጻውያኑ ውሃውን ሊጠጡት አልቻሉም። በግብጽ ምድር ሁሉ ደም ነበረ። 22.የግብጽ አስማተኞች በድብቅ ጥበባቸው ተመሳሳይ ነገር አደረጉ፤ የፈርዖንም ልብ ደነደነ፤ ልክ እግዚአብሔር እንደ ተናገረው ሙሴንና አሮንን አልሰማቸውም። 23.ተመልሶ ወደ ቤተ መንግሥቱ ገባ እንጂ ይህን ከቁም ነገር አልቈጠረውም። 24.ግብጻውያን ሁሉ የወንዙን ውሃ መጠጣት ባለመቻላቸው ውሃ ለማግኘት የአባይን ዳር ይዘው ጕድጓድ ቈፈሩ። 25.እግዚአብሔር አባይን ከመታ ሰባት ቀን ሞላ።

ምዕራፍ 8

የጓጕንቸር መቅሠፍት

1.ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን አለው፤ “ወደ ፈርዖን ዘንድ ሄደህ፣ እንዲህ በለው፤ ‘እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፤ “እኔን ያመልኩኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ። 2.እነርሱን ለመልቀቅ እንቢ ብትል አገርህን ሁሉ በጓጕንቸር መቅሠፍት እመታዋለሁ። 3.አባይ በጓጕንቸሮች ይሞላል፤ ወጥተውም ወደ ቤተ መንግሥትህና ወደ መኝታ ክፍልህ፣ ወደ ዐልጋህም ወደ ሹማምቶችህና ወደ ሕዝብህ ቤቶች፣ ወደ ምድጆችህና ወደ ቡሖቃዎችህ ይገባሉ። 4.ጓጕንቸሮቹ ወደ አንተና ወደ ሕዝብህ ወደ ሹማምትህም ሁሉ ይመጡባችኋል።” ’ ” 5.ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን አለው፣ “አሮንን፣ ‘በትርህን ይዘህ በምንጮች፣ በቦዮችና በኵሬዎች ላይ እጅህን ዘርጋ፤ ጓጕንቸሮችም በግብጽ ምድር ላይ እንዲወጡ አድርግ’ ” በለው። 6.አሮንም በግብጽ ውሆች ላይ እጁን ዘረጋ፤ ጓጕንቸሮችም ወጥተው ምድሪቱን ሸፈኑ። 7.ሆኖም ግን አስማተኞቹ በድብቅ ጥበባቸው ተመሳሳይ ነገር ሠሩ፤ እነርሱም በግብጽ ምድር ላይ ጓጕንቸሮች እንዲወጡ አደረጉ። 8.ፈርዖንም ሙሴንና አሮንን አስጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “ጓጕንቸሮቹን ከእኔና ከሕዝቤ ያርቅ ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ጸልዩልኝ፤ ከዚያም ለእግዚአብሔር መሥዋዕትን ትሠዉ ዘንድ ሕዝቡ እንዲሄዱ እፈቅዳለሁ”። 9.ሙሴም ፈርዖንን፣ “በአባይ ወንዝ ካሉት በቀር ከአንተና ከቤቶችህ ጓጕንቸሮቹ እንዲወገዱ ለአንተ፣ ለሹማምትህና ለሕዝብህ የምንጸልይበትን ጊዜ እንድትወስን ለአንተ ትቼዋለሁ” አለው። 10.ፈርዖንም፣ “ነገ ይሁን” አለው።
ሙሴም እንዲህ ብሎ መለሰ፤ “እንደ አምላካችን እንደ እግዚአብሔር ያለ ማንም እንደሌለ ታውቅ ዘንድ አንተ እንዳልኸው ይሆናል።
11.ጓጕንቸሮቹም ከአንተና ከቤቶችህ፣ ከሹማምትህና ከሕዝብህ ተወግደው በአባይ ወንዝ ብቻ ይወሰናሉ።” 12.ሙሴና አሮን ከፈርዖን ዘንድ ከተመለሱ በኋላ፣ በፈርዖን ላይ ስላመጣቸው ጓጕንቸሮች ሙሴ ወደ እግዚአብሔር ጮኸ። 13.እግዚአብሔር ሙሴ እንደ ለመነው አደረገ፤ ጓጕንቸሮቹም በየቤቱ ውስጥ፣ በየዐጥር ግቢውና በየሜዳው ሞቱ። 14.በአንድ ላይ ሰብስበው ከመሯቸው፤ ምድሪቱም ከረፋች። 15.ፈርዖን ችግሩ ጋብ ማለቱን ባየ ጊዜ ግን ልክ እግዚአብሔር እንደ ተናገረው ልቡን በማደንደን ሙሴንና አሮንን አልሰማቸውም።

የተባይ መቅሠፍት

16.ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን፣ “አሮንን ‘በትርህን ሰንዝረህ የምድርን ትቢያ ምታ’ በለው፤ ከዚያም በግብጽ ምድር ያለው ትቢያ ሁሉ ተናካሽ ትንኝ ይሆናል” አለው። 17.እነርሱም እንዲሁ አደረጉ፣ አሮን በትሩን እንደ ያዘ እጁን ሲዘረጋና የምድሩን ትቢያ ሲመታ፣ በግብጽ ምድር ያለው ትቢያ ሁሉ ተናካሽ ትንኝ ሆነ። ሰውንም ሆነ እንስሳውን ተናካሽ ትንኝ ወረረው። 18.ነገር ግን አስማተኞቹ በድብቅ ጥበባቸው ተናካሽ ትንኞችን ለመፍጠር ሲሞክሩ አልቻሉም።
ተናካሽ ትንኞቹም ከሰውና ከእንስሳው ላይ አልወረዱም ነበር።
19.አስማተኞቹም ፈርዖንን፣ “ይህ የእግዚአብሔር ጣት ነው” አሉት፤ ነገር ግን የፈርዖን ልብ ደንድኖ ስለ ነበር፣ ልክ እግዚአብሔር እንደ ተናገረው አልሰማቸው አለ።

የዝንብ መቅሠፍት

20.ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “በጧት ተነሥተህ ፈርዖን ወደ ውሃ በሚወርድበት ጊዜ ከፊቱ ቀርበህ እንዲህ በለው፤ ‘እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፤ ያመልኩኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ። 21.ሕዝቤ እንዲሄዱ ባትለቅቃቸው፣ በአንተና በሹማምትህ ላይ፣ በሕዝብህና በቤቶችህ ላይ የዝንብ መንጋ እሰድዳለሁ። ያረፉበት መሬት እንኳ ሳይቀር፣ የግብጻውያን ቤቶች ሁሉ ዝንብ ብቻ ይሆናሉ። 22.“ ‘በዚያች ዕለት ግን ሕዝቤ የሚኖርባትን የጌሤምን ምድር የተለየች አደርጋታለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር በዚህች ምድር እንዳለሁ ታውቅ ዘንድ የዝንብ መንጋ በዚያ አይኖርም። 23.በሕዝቤና በሕዝብህ መካከል ልዩነት አደርጋለሁ፤ ይህ ታምራዊ ምልክት ነገ ይሆናል።’ ” 24.እግዚአብሔርም እንዲሁ አደረገ፤ አስጨናቂ የዝንብ መንጋ በፈርዖን ቤተ መንግሥትና በሹማምቱ ቤቶች ላይ ወረደ፤ መላው የግብጽ ምድር ከዝንቡ የተነሣ ተበላሽቶ ነበር። 25.ከዚያም ፈርዖን ሙሴንና አሮንን አስጠርቶ፣ “ሂዱና በዚሁ ምድር ለአምላካችሁ ሠዉ” አላቸው። 26.ሙሴ ግን እንዲህ አለ፤ “ይህ ትክክል አይሆንም፤ ለአምላካችን ለእግዚአብሔር የምናቀርበው መሥዋዕት በግብጻውያን ዘንድ አስጸያፊ ነው፤ ታዲያ በእነርሱ ዐይን አስጸያፊ የሆነውን መሥዋዕት ብናቀርብ አይወግሩንምን? 27.ለአምላካችን ለእግዚአብሔር እርሱ እንዳዘዘን መሥዋዕት ለመሠዋት ወደ ምድረ በዳ የሦስት ቀን መንገድ መሄድ አለብን።” 28.ፈርዖንም፣ “ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር በምድረ በዳ መሥዋዕት እንድትሠዉ እፈቅድላችኋለሁ፤ ነገር ግን ርቃችሁ እንዳትሄዱ። ለእኔም ጸልዩልኝ” አላቸው። 29.ሙሴም እንዲህ አለ፤ “ከአንተ እንደ ተለየሁ ወዲያውኑ ወደ እግዚአብሔር እጸልያለሁ፤ ነገም ዝንቡ ሁሉ ከፈርዖን፣ ከሹማምቱና ከሕዝቡ ይወገዳል። ብቻ ሕዝቡ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት እንዲሠዉ ባለመፍቀድ ከዚህ ቀደም ፈርዖን አታልሎ እንዳደረገው አሁንም እንዳያደርግ ርግጠኛ ይሁን።” 30.ከዚያም ሙሴ ከፈርዖን ተለይቶ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ። 31.እግዚአብሔር ሙሴ የለመነውን አደረገ። የዝንቡም መንጋ ከፈርዖን፣ ከሹማምቱና ከሕዝቡ ተወገደ፤ አንድም ዝንብ እንኳ አልቀረም። 32.በዚህም ጊዜ እንኳ ፈርዖን ልቡን አደነደነ እንጂ፣ ሕዝቡን አልለቀቀም።

ምዕራፍ 9

የእንስሳት ዕልቂት

1.ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ወደ ፈርዖን ሂድና እንዲህ በለው፤ ‘የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፤ “ያመልኩኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ።” 2.አሁንም እንዳይሄዱ ብታደርግና ብትከለክላቸው፣ 3.የእግዚአብሔር እጅ በመስክ ላይ ባሉት እንስሳት፣ በፈረሶችህና በአህዮችህ፣ በግመሎችህና በቀንድ ከብቶችህ፣ በበጎችህና በፍየሎችህ ላይ አስከፊ መቅሠፍት ያመጣብሃል። 4.ነገር ግን እግዚአብሔር በእስራኤልና በግብጽ እንስሳት መካከል ልዩነት ያደርጋል፤ ይኸውም የእስራኤል የሆነ ማንኛውም እንስሳ እንዳይሞት ነው።’ ” 5.እግዚአብሔር ጊዜን ወስኖ፣ እንዲህ አለ፤ “በነገው ዕለት እግዚአብሔር በምድሪቱ ላይ ይህን ያደርጋል።” 6.በማግስቱም እግዚአብሔር ነገሩን ፈጸመው፤ የግብጻውያን እንስሳት በሙሉ ዐለቁ፤ ነገር ግን የእስራኤላውያን ከሆኑት እንስሳት አንድም አልሞተም። 7.ፈርዖን ያጣሩ ዘንድ ሰዎች ልኮ ከእስራኤላውያኑ እንስሳት አንድም እንኳ አለመሞቱን ተገነዘበ። ያም ሆኖ ልቡ እንደ ደነደነ ስለ ነበር፣ ሕዝቡን አልለቀቀም።

የዕባጭ መቅሠፍት

8.ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን አላቸው፤ “ከምድጃው ዕፍኝ ዐመድ ወስዳችሁ፣ ሙሴ በፈርዖን ፊት ወደ ሰማይ ይበትነው። 9.በግብጽ ምድር ሁሉ ትቢያ ይሆናል፤ በምድሪቱ ሁሉ በሚገኙት ሰዎችና እንስሳት ላይ መግል የያዘ ዕባጭ ይወጣል።” 10.ስለዚህ ከምድጃው ዐመድ ወስደው በፈርዖን ፊት ቆሙ፤ ሙሴም ወደ ሰማይ በተነው፤ መግል የያዘ ዕባጭም በሰዎችና በእንስሳት ላይ ወጣ። 11.በእነርሱና በግብጻውያን ሁሉ ላይ ዕባጭ ወጥቶ ስለ ነበር፣ አስማተኞቹ በሙሴ ፊት መቆም አልቻሉም። 12.እግዚአብሔር ግን የፈርዖንን ልብ አደነደነ፤ እግዚአብሔር ለሙሴ እንደ ተናገረውም፣ ሙሴንና አሮንን መስማት አልፈለገም።

የበረዶ መቅሠፍት

13.ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ማልደህ በጧት ተነሣ፤ ከፈርዖን ፊት ቀርበህ እንዲህ በለው፤ የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፤ ‘ያመልኩኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ፤ 14.አለዚያ በአንተ በሹማምትህና በሕዝብህ ላይ የመቅሠፍቴን መዓት ሁሉ አሁን አወርድብሃለሁ፤ ይኸውም በምድር ሁሉ እንደ እኔ ያለ ማንም እንደሌለ ታውቅ ዘንድ ነው። 15.አሁን እጄን ዘርግቼ አንተንና ሕዝብህን ከገጸ ምድር ሊያጠፋችሁ በሚችል መቅሠፍት በመታኋችሁ ነበር። 16.ነገር ግን ኀይሌን እንዳሳይህና ስሜም በምድር ሁሉ እንዲታወቅ ለዚህ አስነሣሁህ። 17.እስካሁንም በሕዝቤ ላይ እንደ ተነሣህ ነው፤ ይሄዱም ዘንድ አትለቅቃቸውም። 18.ስለዚህ ነገ በዚህ ጊዜ ከተመሠረተችበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ በግብጽ ላይ ወርዶ የማያውቅ አስከፊ የበረዶ ማዕበል እልካለሁ። 19.ከብቶችህና በመስክ ላይ ያለህ ማንኛውም ነገር ወደ መጠለያ ይገቡ ዘንድ አሁን ትእዛዝ ስጥ፤ ምክንያቱም በረዶው ወደ መጠለያ ባልገቡትና በመስክ ላይ በቀሩት በማንኛውም ሰውና እንስሳት ላይ ወርዶባቸው ስለሚሞቱ ነው።’ ” 20.የእግዚአብሔርን ቃል የፈሩት የፈርዖን ሹማምት፣ ባሮቻቸውንና ከብቶቻቸውን ለማስገባት ተጣደፉ። 21.የእግዚአብሔርን ቃል ችላ ያሉት ግን ባሮቻቸውንና ከብቶቻቸውን በመስክ ላይ እንደ ነበሩ ተዉአቸው። 22.ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን፣ “በመላዪቱ የግብጽ ምድር ባሉት ሰዎች፣ በእንስሳት እንዲሁም በምድሪቱ ላይ በሚበቅሉት ነገሮች ሁሉ ላይ በረዶ እንዲወርድ እጅህን ወደ ሰማይ አንሣ” አለው። 23.ሙሴ በትሩን ወደ ሰማይ ባነሣ ጊዜ እግዚአብሔር ነጐድጓድና በረዶ አወረደ፤ መብረቅም በምድሪቱ ላይ ሆነ። እግዚአብሔር በግብጽ ምድር በረዶ አዘነበ፤ 24.በረዶ ወረደ፤ መብረቅም አብረቀረቀ፤ ግብጽ አገር ከሆነችበት ዘመን አንሥቶ በምድሪቱ ሁሉ እንደዚህ ያለ አስከፊ ማዕበል ሆኖ አያውቅም። 25.በመላው ግብጽ በረዶ በመስክ ላይ ያለውን ሁሉ፣ ሰዎችንና እንስሳትንም መታ፤ በመስክ ላይ የበቀለውን ሁሉ አጠፋ፤ ዛፉን ሁሉ ባዶ አስቀረ። 26.በረዶ ያልወረደበት ቢኖር እስራኤላውያን የሚኖሩበት የጌሤም ምድር ብቻ ነበር። 27.ከዚያም ፈርዖን ሙሴንና አሮንን አስጠራ፤ እንዲህም አላቸው፤ “አሁንስ በድያለሁ፤ እግዚአብሔር ትክክል ነው፤ እኔና ሕዝቤ ግን ስተናል። 28.መብረቅና በረዶ በዝቶብናልና ወደ እግዚአብሔር ጸልዩልን፤ እንድትሄዱ እለቃችኋለሁ፤ ከዚህ በኋላ በዚህ የመኖር ግዴታ የለባችሁም።” 29.ሙሴም መልሶ፣ “ከከተማዋ በወጣሁ ጊዜ፣ እጆቼን ለጸሎት ወደ እግዚአብሔር እዘረጋለሁ፤ አንተም ምድር የእግዚአብሔር እንደ ሆነች ታውቅ ዘንድ መብረቁ ያቆማል፤ ከእንግዲህ በኋላ በረዶ አይኖርም። 30.ሆኖም አንተና ሹማምትህ አሁንም ቢሆን እግዚአብሔር አምላክን እንደማትፈሩ ዐውቃለሁ።” 31.ተልባው አብቦ፣ ገብሱም ፍሬ ይዞ ስለ ነበር፣ ተልባውና ገብሱ ከጥቅም ውጭ ሆኑ። 32.ስንዴውና አጃው ግን በዚያ ወቅት ባለማፍራቱ አልጠፋም ነበር። 33.ከዚያም ሙሴ ከፈርዖን ተለይቶ ከከተማው ወጣ። እጁን ወደ እግዚአብሔር ዘረጋ፤ ነጐድጓዱና በረዶው ቆመ፤ ዝናቡም በምድሪቱ ላይ መዝነቡን አቆመ። 34.ፈርዖንም ዝናቡ፣ በረዶውና ነጐድጓዱ መቆሙን ባየ ጊዜ እንደ ገና በደለ፤ እርሱና ሹማምቱ ልባቸውን አደነደኑ። 35.ስለዚህ የፈርዖን ልብ ደነደነ፤ እግዚአብሔር ለሙሴ እንደ ተናገረውም እስራኤላውያን ይሄዱ ዘንድ አልለቀቃቸውም።

መዝሙረ ዳዊት

ምዕራፍ 105

105፥1-15 ተጓ ምብ – 1ዜና 16፥8-22
1.እግዚአብሔርን አመስግኑ፤ ስሙንም ጥሩ፤
ሥራውንም በሕዝቦች መካከል አሳውቁ።
2.ተቀኙለት፤ ዘምሩለት፤
ድንቅ ሥራዎቹንም ሁሉ ተናገሩ።
3.በቅዱስ ስሙ ተጓደዱ፤
እግዚአብሔርን የሚፈልጉ ሁሉ፣ ልባቸው ሐሤት ያድርግ።
4.እግዚአብሔርንና ብርታቱን ፈልጉ፤
ፊቱንም ዘወትር ፈልጉ።
5.ያደረጋቸውን ድንቅ ሥራዎች፣
ታምራቱንና የሰጠውንም ፍርድ አስታውሱ፤
6.እናንተ የአገልጋዩ የአብርሃም ዘሮች፣
ለራሱም የመረጣችሁ የያዕቆብ ልጆች ሆይ፤ አስታውሱ።
7.እርሱ እግዚአብሔር አምላካችን ነው፤
ፍርዱም በምድር ሁሉ ላይ ነው።
8.ኪዳኑን ለዘላለም፣
ያዘዘውንም ቃል እስከ ሺሕ ትውልድ ያስባል።
9.ከአብርሃም ጋራ የገባውን ቃል ኪዳን፣
ለይሥሐቅም የማለውን መሐላ አይረሳም።
10.ይህንም ለያዕቆብ ሥርዐት አድርጎ፣
ለእስራኤልም የዘላለም ኪዳን አድርጎ አጸናለት፤
11.እንዲህም አለ፤ “የርስትህ ድርሻ አድርጌ፣
የከነዓንን ምድር እሰጥሃለሁ።”
12.ቍጥራቸው ገና ጥቂት ሳለ፣
በርግጥ ጥቂትና መጻተኞች ሳሉ፣
13.ከአንዱ ሕዝብ ወደ ሌላው ሕዝብ፣
ከአንዱም መንግሥት ወደ ሌላው ተንከራተቱ፣
14.ማንም እንዲጨቍናቸው አልፈቀደም፤
ስለ እነርሱም ነገሥታትን ገሠጸ፤
15.“የቀባኋቸውን አትንኩ፤
በነቢያቴም ላይ ክፉ አታድርጉ።”
16.በምድሪቱ ላይ ራብን ጠራ፤
የምግብንም አቅርቦት ሁሉ አቋረጠ፤
17.በባርነት የተሸጠውን ሰው፣
ዮሴፍን ከእነርሱ አስቀድሞ ላከ።
18.እግሮቹ በእግር ብረት ተላላጡ፤
በዐንገቱም የብረት ማነቆ ገባ።
19.የተናገረው ቃል እስኪፈጸምለት፣
የእግዚአብሔር ቃል ፈተነው።
20.ንጉሥ ልኮ አስፈታው፤
የሕዝቦችም ገዥ ነጻ አወጣው።
21.የቤቱ ጌታ፣
የንብረቱም ሁሉ አስተዳዳሪ አደረገው፤
22.ይኸውም ሹማምቱን በራሱ መንገድ ይመራ ዘንድ፣
ሽማግሌዎቹንም ጥበብ ያስተምር ዘንድ ነበር።
23.እስራኤል ወደ ግብጽ ገባ፤
ያዕቆብ በካም ምድር መጻተኛ ሆነ።
24.እግዚአብሔር ሕዝቡን እጅግ አበዛ፤
ከጠላቶቻቸውም ይልቅ አበረታቸው፤
25.ሕዝቡን እንዲጠሉ፣
በባሪያዎቹም ላይ እንዲያሤሩ ልባቸውን ለወጠ።
26.ባሪያውን ሙሴን፣
የመረጠውንም አሮንን ላከ።
27.እነርሱም ታምራታዊ ምልክቶችን በመካከላቸው፣
ድንቅ ነገሮቹንም በካም ምድር አደረጉ።
28.ጨለማን ልኮ ምድሪቱን ጽልመት አለበሰ፤
እነርሱም በቃሉ ላይ ማመፅን ተዉ።
29.ውሃቸውን ወደ ደም ለወጠ፤
ዓሦቻቸውንም ፈጀ።
30.ምድራቸውም፣ የነገሥታታቸው እልፍኝ ሳይቀር፣
ጓጕንቸር ተርመሰመሰባቸው።
31.እርሱ በተናገረ ጊዜ የዝንብ መንጋ መጣ፤
ትንኞችም ምድራቸውን ወረሩ።
32.ዝናባቸውን በረዶ አደረገው፤
ምድራቸውም ሁሉ መብረቅ አወረደ።
33.ወይናቸውንና በለሳቸውን መታ፤
የአገራቸውንም ዛፍ ከተከተ።
34.እርሱ በተናገረ ጊዜ አንበጣ መጣ፤
ስፍር ቍጥር የሌለውም ኵብኵባ ከተፍ አለ፤
35.የምድሪቱንም ዕፀዋት ሁሉ በላ፤
የመሬታቸውንም ፍሬ ሙጥጥ አደረገ፤
36.ደግሞም በአገራቸው ያለውን በኵር ሁሉ፣
የኀይላቸውንም ሁሉ በኵራት መታ።
37.የእስራኤልንም ሕዝብ ብርና ወርቅ ጭኖ እንዲወጣ አደረገ፤
ከነገዶቻቸውም አንድም አልተደናቀፈም።
38.እጅግ ፈርተዋቸው ነበርና፣
ወጥተው ሲሄዱ ግብጽ ደስ አላት።
39.ደመናን እንደ መጋረጃ ዘረጋላቸው፤
እሳትም በሌሊት አበራላቸው።
40.በለመኑትም ጊዜ፣ ድርጭት አመጣላቸው፤
የሰማይንም እንጀራ አጠገባቸው።
41.ዐለቱን ሰነጠቀ፤ ውሃም ተንዶለደለ፤
እንደ ወንዝም በበረሓ ፈሰሰ።
42.ለባሪያው ለአብርሃም የሰጠውን፣
ቅዱስ የተስፋ ቃሉን አስቧልና።
43.ሕዝቡን በደስታ፣
ምርጦቹንም በእልልታ አወጣቸው።
44.የሌሎችን ሕዝቦች ምድር ሰጣቸው፤
የእነዚህንም የድካም ፍሬ ወረሱ፤
45.ይህም ሥርዐቱን ይጠብቁ ዘንድ፣
ሕጉንም ይፈጽሙ ዘንድ ነው።
ሃሌ ሉያ።

ወደ ኤፌሶን ሰዎች

ምዕራፍ 1

1.በእግዚአብሔር ፈቃድ የክርስቶስ ኢየሱስ ሐዋርያ ከሆነው ከጳውሎስ፤
በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉ፣ ለታመኑ፣ በኤፌሶን ለሚገኙ ቅዱሳን፤
2.ከአባታችን ከእግዚአብሔር፣ ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።

በክርስቶስ የሚገኝ መንፈሳዊ በረከት

3.በሰማያዊ ስፍራ በመንፈሳዊ በረከት ሁሉ በክርስቶስ የባረከን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ፤ 4.በፊቱ ቅዱስና እንከን አልባ እንድንሆን ዓለም ከመፈጠሩ አስቀድሞ በርሱ መርጦናልና። በፍቅር፣ 5.በኢየሱስ ክርስቶስ ልጆቹ እንሆን ዘንድ፣ እንደ በጎ ፈቃዱ አስቀድሞ ወሰነን፤ 6.ይኸውም፣ በሚወድደው በርሱ በኩል በነጻ የተሰጠን ክቡር የሆነው ጸጋው እንዲመሰገን ነው። 7.በርሱም እንደ እግዚአብሔር ጸጋ ባለጠግነት መጠን፣ በደሙ በተደረገ ቤዛነት፣ የኀጢአት ይቅርታ አገኘን፤ 8.ጸጋውንም በጥበብና በማስተዋል ሁሉ አበዛልን። 9.በክርስቶስ ያቀደውንም የፈቃዱን ምስጢር እንደ በጎ ሐሳቡ እንድናውቅ አደረገ። 10.በዘመን ፍጻሜ ይሆን ዘንድ ያለው ሐሳቡ፣ በሰማይም ሆነ በምድር ያሉትን ነገሮች ሁሉ ራስ በሆነው በክርስቶስ ሥር ለመጠቅለል ነው። 11.ሁሉን በፈቃዱ ምክር መሠረት እንደሚሠራው እንደ እርሱ ዕቅድ፣ አስቀድሞ የተወሰንን እኛ ደግሞ በርሱ ተመርጠናል፤ 12.ይኸውም በክርስቶስ ተስፋ በማድረግ የመጀመሪያ የሆንነው እኛ ለክብሩ ምስጋና እንሆን ዘንድ ነው። 13.እናንተም ደግሞ የእውነትን ቃል፣ ይህም የድነታችሁን ወንጌል በሰማችሁ ጊዜ ወደ ክርስቶስ ተጨምራችኋል። አምናችሁም በርሱ በመሆን፣ ተስፋ ሆኖ በተሰጠው በመንፈስ ቅዱስ ማኅተም ታትማችኋል። 14.ለክብሩ ምስጋና ለመሆን የእግዚአብሔር የሆኑት እስኪዋጁ ድረስ፣ እርሱ ለርስታችን ዋስትና የሚሆን መያዣ ነው።

የምስጋናና ጸሎት

15.ስለዚህ በጌታ ኢየሱስ ስላላችሁ እምነት፣ ለቅዱሳንም ሁሉ ስላላችሁ ፍቅር ከሰማሁበት ጊዜ አንሥቶ፣ 16.በጸሎቴ እያስታወስኋችሁ ስለ እናንተ ምስጋና ማቅረብን አላቋረጥሁም። 17.የክብር አባት የሆነውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክ ይበልጥ እንድታውቁት፣ የጥበብና የመገለጥን መንፈስ እንዲሰጣችሁ ያለ ማቋረጥ እለምናለሁ። 18.እንዲሁም በርሱ የተጠራችሁለት ተስፋ፣ ይህም በቅዱሳኑ ዘንድ ያለውን ክቡር የሆነውን የርስቱን ባለጠግነት ምን እንደ ሆነ ታውቁ ዘንድ የልባችሁ ዐይኖች እንዲበሩ 19.ለእኛ ለምናምነውም ከሁሉ በላይ ታላቅ የሆነውን ኀይሉን እንድታውቁ እጸልያለሁ። ይህም ኀይል እንደ እርሱ ታላቅ ብርታት አሠራር፣ 20.ክርስቶስን ከሙታን ሲያስነሣውና በሰማያዊ ስፍራ በቀኙ ሲያስቀምጠው የታየው ነው። 21.የተቀመጠውም ከግዛትና ከሥልጣን፣ ከኀይልና ከጌትነት እንዲሁም በአሁኑ ዘመን ብቻ ሳይሆን በሚመጣውም ዘመን ቢሆን ሊሰየም ከሚቻለው ስም ሁሉ በላይ ነው። 22.እግዚአብሔርም ሁሉን ከእግሩ በታች አስገዛለት፤ በቤተ ክርስቲያንም በማንኛውም ነገር ላይ ራስ አድርጎ ሾመው። 23.እርሷም ሁሉን ነገር በሁሉም ረገድ የሚሞላው፣ የርሱ ሙላት የሆነች አካሉ ናት።